ru
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

Открыть в Telegram

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

Больше
611
Подписчики
Нет данных24 часа
-17 дней
-930 дней
Архив постов
                                                       ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦"ወትቀውም ንግሥት በየማንከ።  በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት። ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ"። መዝ44፥9-10። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥39-57።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል። እግዚአብሔር ውስተ ማእከላ ኢትትሀወክ። ወይረድኣ እግዚአብሔር ፍጽመ"። መዝ4፥4-5 ወይም መዝ 121፥6-7። የሚነበቡት መልዕክታት የሚነበበው ሮሜ 8፥31-ፍ.ም 2ኛ ዮሐ 1፥1-7 እና የሐዋ ሥራ 1፥12-15። ወንጌል ማቴ 26፥26-31። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእነ። መልካም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የትንሣኤዋና የዕረገቷ በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።                

ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta) Saints Of The Orthodox Tewahedo Church.: ❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #ነሐሴ ፲፮ (16) ቀን። ❤ እንኳን #ለእናታችን_ለእመቤታችን_ለቅድስት_ድንግል_ማርያም_ለትንሣኤዋና_ለዕርገቷ በዓል፣ ለሰማዕታት አለቃ #ለቅዱስ_ጊዮርጊስ_ሥጋው_ከፋርስ አገር ወደ #አገሩ_ልዳ_በክብር_ለፈለሰበት በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ ከሶርያ መስፍን ከታላቁ ሰማዕት ከቅዱስ ጊጋር (በስደቷ ጊዜ እመቤታችንና ልጇን መድኀኔዓለምን ዮሴፍን ሰሎሜን አብሮ ወደቤቱ አስገብቶ በመደበቅ ከሄሮድስ ጭፍሮች ያዳናቸው ነው) ከዕረፍት እግዚአብሔር አምላክ ረድኤት በረከትን ያሳትፈን።                                                    ✝️ ✝️ ✝️ ❤ በዚህች ቀን #አምላክን የወለደች #የእመቤታችን_ድንግል_ማርያም ሥጋዋ ወደ ሰማይ ያረገበት መታሰቢያዋ ሆነ ። ከዕረፍቷም በኋላ ከእርሳቸው ስለመለየቷ ሐዋርያት ፈጽሞ እያዘኑ ነበር ። ❤ ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ተገለጠላቸው እርሷን በሥጋ ያዩ ዘንድ እንዳላቸውም ተስፋ ሰጣቸው ። ወንጌላዊ ዮሐንስም እስያ በሚባል አገር እያስተማረ ሳለ በነሐሴ ወር ዐሥራ ስድስተኛ ቀን ተድላ ደስታ ወደአለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቀ። የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ሥር ተቀምጦ አየው። የንጽሕት እናቱንም ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው ። እነርሱም "የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል" አሏት ። ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ወጣ ። ❤ የክብር ባለቤት ጌታችንም እንዲህ እያለ አረጋጋት "የተወደድሽ የወለድሽኝ እናቴ ሆይ ዘላለማዊ ወደ ሆነ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ ነዪ"። ያን ጊዜም በገነት ያሉ ዕፀዋት ሁሉም አዘነበሉ መላእክት የመላእክት አለቆች ጻድቃን ሰማዕታትም እየሰገዱላትና ፈጽሞ እያመሰገኗት አሳረጓት ። አባቷ ዳዊትም "ንግሥት እመቤታችን ወርቀ ዘቦ ለብሳ ደርባ ደራርባ በቀኝህ ትቀመጣለች" እያለ በበገና አመሰገናት ። በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጣ ከዐረገች በኋላ በልጁዋና በፈጣሪዋ ቀኝ በታላቅ ክብር ተቀመጠች ። ❤ ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ሰግዶላት ተመልሶ ከሰማይ ወረደ ሐዋርያትን ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው ። እርሱም እንደ አየ እንደ ሰማ ሥጋዋንም በታላቅ ክብር በምስጋና እንደ አሳረጓት ነገራቸው ። ❤ ሐዋርያትም በሰሙ ጊዜ ዮሐንስ እንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ ። ከዚህም በኋላ እያዘኑ ሳሉ እነሆ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸውና "የፍቅር አንድነት ልጆች ሰላም ይሁንላችሁ ስለ እናቴ ማርያም ሥጋ ለምን ታዝናላችሁ። እነሆ እኔ እርሷን በሥጋ ላሳያችሁ ልባችሁም ደስ ሊለው ይገባዋል" አላቸው ይህንንም ብሎ ከእርሳትው ዘንድ ወደ ሰማያት ዐረገ ። ❤ ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ የነሐሴም ወር በባተ ቀን ሐዋርያት ዮሐንስ እንዲህ አላቸው "አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት የተዘጋጀን አድርጎ ያሰየን ዘንድ ኑ ይህን ሁለት ሱባዔ በመጾም የክብር ባለቤት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው በልጅዋ በወዳጅዋ ቀኝ ተቀምጣ አይተን በእርሷ ደስ እንዲለን"። ❤ በዚያን ጊዜም ዮሐንስ እንዳላቸው በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ የነሐሴ ወር እንደ ዛሬ ዐሥራ ስድስተኛ ቀን በሆነ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው። በታላቅ ክብር በተወደደ ልጅዋ ቀኝ ተቀምጣ ከሥጋዋ ተዋሕዳ ተነሥታ እመቤታችን ማርያምን አዩዋት። እጆቿንም ዘርግታ የከበሩ ሐዋርያትን እያንዳንዳቸውን ባረከቻቸው በልባቸውም እጅግ ደስ አላቸው። ❤ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በከበረ ሥጋውና ደሙ ላይ ሠራዒ ካህን ሆነ ። እስጢፋኖስም አዘጋጀ ዮሐንስም "በመፍራት ቁሙ" አለ። ሁሉም ሐዋርያት በመሠዊያው ዙሪያ ቆሙ በዚያን ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ። ❤ ጌታችንም የቅዳሴውን ሥርዓት በፈጸመ ጊዜ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው። ከዚያም በኪሩቤልና በሱራፌል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ እመቤታችን ማርያምን እንዲህ ብሎ ተናገራት "በዚች ቀን የሆነ የዕርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰብኩ ልጆችሽ ሐዋርያትን እዘዣቸው። መታሰቢያሽን የሚያደርገውን ሁሉ ተጠብቆም በዚች ቀን ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበለውን ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ። የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም መታሰቢያሽን ለሚያደርግ ሁሉ በዚች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውት ቸርነቴ ትገናኘዋለች ይህም ሥጋሽ ወደ ሰማይ ያረገበት ነው"። ❤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ክብር ይግባውና ጌታችንን እንዲህ አለችው "ልጄ ሆይ እነሆ በዐይኖቻቸው አዩ በጆሮቻቸውም ሰሙ በእጆቻቸውም ያዙ ሌሎችም ታላላቅ ደንቆች ሥራዎችን አዩ"። እመቤታችንም ይህን ስትናገር ጌታችን ሰላምታ ሰጥቷቸው በታላቅ ደስታ ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ። ❤ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ በፍጹም ደስታ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ ይገባናል እርሷ ስለእኛ ወደ ተወደደ ልጅዋ ሁልጊዜ ትማልዳለችና። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይማረን ። በረከቷም ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከአባ መርቆሬዎስና ከአባ ማትያስ ከሁሉም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት ጋራ ሐዋርያት ከሰበሰቧት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ከሁላችን ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።                                                       ✝️ ✝️ ✝️ ❤ በዚህችም ዕለት የሰማዕታት አለቃ #የቅዱስ_ጊዮርጊስ_ሥጋው_ከፋርስ አገር ወደ አገሩ ልዳ በክብር የፈለሰበት ነው። የሥጋውም ፍልሰት ከእመቤታችን ድንግል ማርያም የሥጋ ፍልሰት ጋር አንድ ሆኗልና ስለዚህም እርሷን መውደዱን የሚያወቁ ሥዕሉን ከሥዕሏ አጠገብ ይሥላሉ በስሙ ለሚማፀኑ የድኅነት ወደብ ይሆን ዘንድ። ❤ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በኃያሉ ተጋዳይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎት በእኛ ላይ ምሕረት ይቅርታ ቸርነት ይሁን ለዘላለሙ አሜን።                                                    ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የሶሪያ_መስፍን_ሰማዕቱ_ቅዱስ_ጊጋር፦ ሰማዕት የሆነበትም ምክንያት ጌታችን ከእመቤታችን ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋራ በተሰደደ ጊዜ በሊባኖስ ተራራ ሳለ ኄሮድስ ሰምቶ ከበው ይዘው ይገድሏቸው ዘንድ ጭፍሮቹን ላከ ጊጋርም ጭፍሮች እንዳገኟቸው አሸሻቸው። ❤ ስለዚህም ኄሮድስ ተቆጣ ጊጋርንም ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው ሕዋሳቱንም ሁሉ ቆራረጠ። ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦለት ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ገድሉንም ለሚጽፍ ቃል ኪዳን ሰጠው ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡት በሦስት አክሊሎችም ተጋረደ ሦስት አክሊላትን ተቀዳጀ። ❤ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ጊጋር በአማላጅነቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

❤ ያን ጊዜም ተነሥቶ ወደዚያ ገዳም ሒዶ መነኰሳቱን ይረግማቸው ጀመረ። አበምኔቱም ሰምቶ ወጣና "መነኰሳቱን ለምን ትረግማቸዋለህ እግዚአብሔርን አትፈራውምን" አለው እርሱም በልጁ ላይ የሆነውን ነገረው አንዲህም አለው "አባ እንባመሪና የሚሉት ወጣት መነኰሴ የልጄን ድንግልና ስለደፈረ ነው" አለው። አበ ምኔቱም በሰማ ጊዜ እውነት መሰለውና እጅግ አዘነ ሰውየውንም እንዲህ ብሎ ለመነው "በአንድ ሰው በደል ንጹሐን የሆኑ መነኰሳትን በሕዝባውያን ፊት አታዋርዳቸው ይህንንም ነገር ሠውር"። ❤ ከዚህም በኋላ ቅድስት እንባመሪናን ጠርቶ ይገሥጻትና ይረግማት ጀመረ እርሷም ስለምን እንደሚረግማት አላወቀችም ነበር በአወቀችም ጊዜ ከእግሩ በታች ወደቃ "እኔ ወጣት ነኝና በደሌን ይቅር በለኝ" ብላ ለመነችው እርሱም አጅግ ተቆጥቶ ከገዳሙ አባረራት እርሷም ከገዳም ውጭ ሁና እየተጋደለች ኖረች። ❤ ያቺም ልጅ በወለደች ጊዜ የልጅቷ አባት ሕፃኑን አምጥቶ ለቅድስት እንባመሪና ሰጣት እርሷም እግዚአብሔርን እያመሰገነች ተቀበለችው በላሞችና በበጎች ጠባቂዎች ዘንድ ለሕፃኑ ወተትን እየለመነች መዞርን ጀመረች እንደዚህም አድርጋ ሕፃኑን አሳደገችው። ከሦስት ዓመትም በኋላ መነኰሳቱ ተሰብስበው አባ ምኔቱን ለመኑት አባ እንባመሪናን ይቅርታ አድርጎለት ወደ ገዳሙ ይመልሰው ዘንድ እርሱም ልመናቸውን ተቀብሎ ከመነኰሳቱ ጋራ ቀላቀላት ይኸውም ከባድ ቀኖና ከሰጣት በኋላ ነው። ❤ ከዚህም በኋላ ጭንቅ የሆኑ ሥራዎችን ትሠራ ጀመረች የመነኰሳቱንም ቤቶች ጠርጋ ተሸክማ ወስዳ ከገዳሙ ውጭ ትጥለዋለች ውኃንም ቀድታ ታጠጣቸዋለች ምግባቸውንም ታዘጋጃለች። ያም ሕፃን አደገ የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት ተምሮ መነኰሰ። ❤ አርባ ዓመትም ሲፈጸም ሦስት ቀኖች ያህል ታማ በሰላም አረፈች ደወልንም ደውለው መነኰሳቱ ሁሉ ተሰበሰቡ ሊገንዙም ገብተው ልብሶቿን በገለጡ ጊዜ እርሷ ሴት እንደ ሆነች አግኝተዋት ደነገጡ መሪር እንባንም አለቀሱ አበ ምኔቱም በመጣም ጊዜ ያለ በደሏ ከባድ ንስሐ ቀኖና ስለ ሰጣትና በእርሷ ላይ ስለ አደረገው ተግሣጽ መሪር ዕንባን አለቀሰ። ❤ ከዚህም በኋላ መልእክተኞችን ልኮ የዚያችን የሐሰተኛ ልጅ አባቷን አስመጥቶ እንባመሪና ሴት እንደሆነች ነገረው ። ከዚህም በኋላ በድኗን ተሸክመው ይቅር ይበለን የሚል ቃል ከበድኗ እስከ ሰሙ ድረስ "አቤቱ ክርስቶስ ማረን" እያሉ ጸለዩ ከዚያም በኋላ በዝማሬና በማኅሌት ከብዙ ልቅሶ ጋር ገነዟት ከሥጋዋም ተባርከው ቀበሩዋት። ❤ እነሆ እግዚአብሔር ክፉ ሰይጣንን አዝዞት ያቺን ሐሰተኛ ሴት ልጅና ድንግልናዋን የደፈረውን ጉልማሳ ያዘው እያጓተተም አሠቃይቶ ይቀጣቸው ጀመረ ወደ ቅድስት እንባመሪና መቃብር ሔደው ኃጢአታቸውን በሕዝቡ ሁሉ ፊት እስከሚአምኑ እጅግ አሠቃያቸው። ከመቃብርዋም ቁጥር የሌላቸው ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት እንባ መሪና በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #ሰማዕቱ_ቅዱስ_ለውረንዮስ፦ በንጉሥ ዳስዮስ ቄሣር ዘመን ሰማዕትነት የተቀበለ ነው። ይህም ቅዱስ በሃይማኖት የጸና ነው የክብር ባለቤት ስለ ሆነ ስለ ክርስቶስ ሃይማኖት ሊቀ ዲቁና ተሹሞ የሊቀ ጵጵስናውን ገንዘብ ይጠብቅ ነበር። ❤ ንጉሥ ስለርሱ ሰምቶ አምጥተው ከወህኒ ቤት እንዲአስገቡት አዘዘ በአስገቡትም ጊዜ በዚያ ዕውር ሰውን አገኘና "አይኖችህ ይገለጡ ዘንድ በሕያው እግዚአብሔር ልጅ አምነህ በስሙ ትጠመቃለህን?" አለው ዕውሩም "አዎን ጌታዬ" አለ። ያን ጊዜም በውኃው ላይ ጸልዮ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቀው ያን ጊዜም አይኖቹ ተገለጠ። እንዲህም ብሎ ጮኸ "በአገልጋዩ ለውረንዮስ ጸሎት ዐይኖቼን የገለጠ የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይክበር ይመስገን" ብሎ ጮኸ። ይህንንም ድንቅ አይተው ብዙዎች አመኑ። ❤ ንጉሡም በሰማ ጊዜ የከበረ ለውረንዮስን ወደርሱ ያቀርቡት ዘንድ አዘዘ በአቀረቡትም ጊዜ ለአማልክት እንዲሰዋ አግባባው እምቢ ባለውም ጊዜ ጥርሶቹን በደንጊያ ሰበሩ ልብሶቹንም ገፈው በብረት ዐልጋ ላይ አስተኝተው ሥጋው እስከሚቀልጥ ከበታቹ እሳትን አነደዱ። ❤ እርሱም ነፍሱን እስከአሳለፈ ድረስ ወደ ፈጣሪው ይጸልይ ነበር። መላእክትም ሃሌ ሉያ እያሉ ተቀብለው ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት አስገቡት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ ቅዱስ ለውረንዮስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘለላለሙ አሜን፡፡ ምንጭ፦ የነሐሴ 15 ስንክሳር።                             ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ውስተ ኵሉ ምድር ወፅአ ነገሮሙ። ወእስከ አፅናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ። ወውስተ ፀሓይ ሤመ ጽላሎቶ"። መዝ 18፥4-5። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 12፥18-ፍ.ም፣ ይሁ 1፥17-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 1፥12-15። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 10፥1-15። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱሳን የሐዋርያት ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።

ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta) Saints Of The Orthodox Tewahedo Church.: ❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #ነሐሴ ፲፭ (15) ቀን። ❤ እንኳን አምላክን ስለወለደችን #እመቤታችን_ድንግል_ማርያም ሥጋዋን ለመግነዝ  #ሐዋርያት_ለተሰበሰቡበት ቀን፣ #ጌታችን ከከበሩ #ቅዱሳን_መላእክቶቹ ጋር መጥቶ ላጠመቃት፣ #ቅዱስ_ሚካኤል በእሳጉጠት ቅዱስ ሥጋውን ክብር ደሙን ላቀበላትና ዋስ ለሆናት በተአምራቷም ሠላሳ ሺህ ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ላሳመነችው ለመኰንን ርባኖስ ልጅ ለታላቋ ሰማዕት #ለቅድስት_ክርስጢ ለዕረፍት በዓል፣ ሴት ሆና እንደ ወንድ መስላ ከወንዶች ገዳም ገብታ ገድሏን ለፈጸመች ታላቅ እናት #ለቅድስት_ከአባ_እንባመሪና ለዕረፍት በዓልና በንጉሥ ዳንዮስ ቄሣር ዘመን በሰማዕትነት ለተቀበለ #ለቅዱስ_ለውረንዮስ ለዕረፍቱ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪም በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከሠላሳ ሺህ ዐሥራ ሁለት #ከቅድስት_ክርስጢና_ማኅበረ ሰማዕታት እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ በዚህች ቀን አምላክን ስለወለደች #እመቤታችን_ድንግል_ማርያም ሥጋዋን ስለመገነዝ የሐዋርያት ስብሰባ ሆነ። ጸሎቷና በረከቷ የሐዋርያትም በረከታቸው ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።                                                        ✝ ✝ ✝ ❤ #የመኰንን_ርባኖስ_ልጅ_ታላቋ_ሰማዕት #ቅድስት_ክርስጢና፦አባቷ ጣዖታትን የሚያመልክ ነው። እርሷም አባቷ እንደ አስተማራት ታጥናቸው ነበር። በአንዲት ዕለትም አስባ ተመራመረች በልቧም እግዚአብሔርን መፍራት አደረ ተነሥታም ፊቷን ወደ ምሥራቅ መልሳ ቆመች የምትጓዝበትንም የሕይወት መንገድ ይመራት ዘንድ ጸለየች መንፈስ ቅዱስም አንድነቱንና ሦስትነቱን ገለጠላት። ❤ አባቷም በመጣ ጊዜ "ልጄ እንዴት አለሽ" አላት "በክብር ባለቤት በክርስቶስ ሕይወት አለሁ" አለችው። አባቷም ሰምቶ ደነገጠ "ልብሽን ምን ለወጠው" አላት እርሷም "ከሰማይ አምላክ ተማረኩ" አለችው። ከዚህም በኋላ አባቷ እያዘነ ሔደ። እርሷም ተነሥታ ወደ እግዚአብሔር ጸለየች ያን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ እንዲህ አላት "በርቺ ከሦስት መኳንንት ትሠቃዪ ዘንድ አለሽ" አዳኝ በሆነ በጌታችን ክርስቶስ መስቀልም አማተመች ሰማያዊ ኅብስትንም ሰጣት። ❤ ከዚህም በኋላ ተነሥታ ጣዖታቱ ወደ አሉበት ቤት ገብታ ቀጠቀጠቻቸው። አባቷም አይቶ እጅግ ተቆጣ ልጁንም ይገርፏት ዘንድ አዘዘ ከሥጋዋም ስለ ደም ፈንታ ማር ወጣ። ሁለተኛም በብረት ዐልጋ ላይ አስተኝተው ከበታችዋ እሳትን እንዲያነዱ አዘዘ እርሷን የነካት የለም ግን ከአረማውያን ብዙዎችን አቃጠለ። ❤ ዳግመኛም በታንኳ አድርገው ወደ ባሕር ይጥሏት ዘንድ አዘዘ በጸለየችንም ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክት ጋራ መጥቶ ራሱ አጠመቃት ቅዱስ ሚካኤልም በእሳት ጉጠት የክብር ባለቤት የሆነ የክርስቶስን ሥጋና ደም አቀበላት ከጣዖታት እድፍም አነጻት በዚያችም ሌሊት አባቷ ርባኖስ ሞተ ። ስሙ ድዮስ የሚባል ሌላ መኰንን መጣ ቅድስት ክርስጢናን አምጥተው ራቁቷን ሰቅለው ከበታችዋ እሳትን እንዲያነዱ አዘዘ። ሴቶችም ራቁትነቷን አይተው መኰንኑን ረገሙት እነርሱም በሰይፍ አስቆረጣቸው እርሷን ግን ምንም ምን አልነካትም ሕዝቡም ይህን ተአምር አይተው የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሠላሳ ሺህ ዐሥራ ሁለት ሰዎች አምነው በሰማዐትነት ሞቱ ከሀዲው መኰንን ድዮስም በድንገት ሞተ። ❤ ሦስተኛም መኰንን መጣ የከበረች ክርስጢናንም ይዞ ለአማልክት ትሠዋ ዘንድ አባበለት እርሷም እንዲህ አለችው። "አንተና አማልክቶችህ ለዘላለም ወደማ ይጠፋ የገሀነም እሳት ትወርዳላችሁ"። እጅግም ተቆጥቶ ወደ እሳት ማንደጃ ውስጥ እንዲጨምርዋት አዘዘ ምንም የነካት የለም። ዳግመኛም ለአራዊት ይጥሏት ዘንድ አዘዘ እነርሱም የእግርዋን ትቢያ ላሱ እባቦችንም የሚያጠምደውን ነከሱትና ወዲያውኑ ሞተ። ❤ ሁለተኛም ምላሷንና ጡቶቿን ቆረጡ የምላሷንም ቁራጭ አንሥታ ከመኰንኑ ዐይኖች ላይ ጣለችውና ዐይኖቹን አሳወረችው። ቁጣውንም ተመልቶ ለእባቦች እንዲጥሏት አዘዘ አንዲቷም እባብ ልቧን ነደፈቻት አንዲቱ ደግሞ ጐኗን እንዲህም የምስክርነቷን ተጋድሎ ፈጸመች ነፍሷንም አሳልፋ የድል አክሊልን ተቀዳጀች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በታላቋ ሰማዕት በቅድስት ክርስጢና በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                                                                              ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅድስት_አባ_እንባ_መሪና፦ የዚችም ቅድስት የእናቷ ስም ማርያም ይባላል ሕፃንም ሁና ሳለች እናቷ ሞተች አባቷም አድጋ አካለ መጠን እስከምታደርስ መልካም ትምህርትን እያስተማረ አሳደጋት። አባቷም እሷን አጋብቶ እርሱ ወደ አንድ ገዳም ሒዶ ይመነኲስ ዘንድ ወደደ ። እርሷም አባቷን "ያንተን ነፍስ አድነህ የኔን ነፍስ ታጠፋለህን" አለችው። እርሱም "ስለ አንቺ እንዴት አደርጋለሁ ከገዳም ውስጥ ሴትን አይቀበሉምና" አላት እርሷም እንዲህ አለችው "አባቴ ሆይ የሴቶችን ልብስ ከላዬ አስወግደህ የወንዶችን ልብስ አልብሰኝና ከአንተ ጋራ ውሰደኝ"። ❤ የልቧንም ጽናት አይቶ የወንድ ልብስ አልብሶ ከእርሱ ጋር ወሰዳት የቀድሞ ስሟ መሪና ነበር እርሱ ግን ስሟን ለውጦ እንባመሪና ብሎ ጠራት ገንዘቡንም ሁሉ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች በተነ ልጁንም በወንድ ስም እየጠራ ከእርሱ ጋራ ወስዳት ወደ አንድ የመነኰሳት ገዳምም ደርሰው በዚያ እየተጋደሉ ኖሩ። ❤ ከዚህም በኋላ አባቷ ታመመ ለሞትም በቀረበ ጊዜ አበ ምኔቱን ጠርቶ እርሷን ልጁን አደራ ሰጠው ስለ ገዳም አገልግሎት ከገዳም እንዳትወጣ ከዚያም በኋላ አረፈና ቀበሩት። የከበረች እንባመሪናም ከአባቷ ተለይታ ብቻዋን ቀረች በጾም በጸሎት በስግደት ከቀድሞዋ ዕጥፍ አድርጋ ተጋድሎ ጀመረች። ❤ ከዚህም በኋላ የገዳሙ መነኰሳት "ይህ ወጣት መነኰስ ከእኛ ጋራ ለገዳሙ አገልግሎት ለምን አይወጣም" ብለው ተቃወሟት እንዲህም አበምኔቱን በአሰጨነቁት ጊዜ ከእርሳቸው ጋራ ሰደዳት። ለመነኰሳቱ ቀልብ የሚሆነውን የገዳሙን እህል የሚሰበስብ አንድ ሰው አለ መነኰሳቱም በሚወጡ ጊዜ ከእርሱ ዘንድ አድረው እህላቸውን ይጭናሉ የእንግዳ መቀበያ ቤትም አለው በዚያ ያድራሉ። ❤ በዚያችም ዕለት ከጐረቤቱ አንድ ጐልማሳ ሰው መጥቶ በዚህ ሰው ቤት አድሮ የልጅን ድንግልና አጠፋ። እንድህም አላት "አባትሽ ማን ደፈረሽ ብሎ የጠየቀሽ እንደሆነ አባ እንባመሪና የሚሉት ወጣት መነኰሴ ደፈረኝ በይው"። በፀነሰችም ጊዜ አባቷ አወቀ "ማነው የደፈረሽ" ብሎ ጠየቃት እርሷም እንዲህ ብላ መለሰችለት "አባ እንባመሪና የሚሉት ወጣት መነኵሴ ደፈረኝ"።

ነሐሴ ፲፬ /14/ በዚችም ቀን ቅዱስ ባስሊቆስ በሰማዕትነት ሞተ። በእሥር ቤትም ሳለ ጌታችን ተገልጦለት የምስክርነትህ ጊዜ ስለደረሰ  ዘመዶችህን ተሰናበታቸው አለውና ተሰናበታቸው። ከዚህም በኋላ በብዙ አሰቃዪት። ሰዎችም የልብሱን ጫፍ ለመንካት የሚጋፉ ሆኑ። ከዚህም በኋላ ዋርሲኖስ ወደሚባል አገር በመርከብ ወሰዱት ወታደሮችም እንዳትሞት እህልን ብላ አሉት እርሱም እኔ ከሰማያዊ መብል የጠገብኩ ነኝ ምድራዊ መብልን አልመርጥም አላቸው። ወደ መኰንኑም በአቀረቡት ጊዜ ለአማልክት መሥዋዕትን አቅርብ አለው የከበረ በስሊቆስም እኔ አንድ ለሆነ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የምስጋና መሥዋዕትን አቀርባለሁ አለው። ሁለተኛም ወደ ጣዖታቱ ቤት እንዲአስገቡት አዘዘ እርሱም ቁሞ ወደ እግዚአብሔርጸለየ ያን ጊዜ እሳት ወርዶ ጣዖታቱን አቃጠላቸው መኰንኑም ፈርቶ ሸሽቶ ወደውጭወጣ። ቁጣንም ተመልቶ ይገድሉት ዘንድ ያ መኰንን አዘዘ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ባስሊቆስ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ መከራውን ይሳተፍ ዘንድ ስለ አደለውም አመሰገነው። ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡት ብዙዎችም መላእክት ነፍሱን ሲያሳርጓት አዩዋት ጌታችን ኢየሱስም ወዳጄ ባስሊቆስ ወደ እኔ ና እኔ የምዋሽ አይደለሁም ተስፋ ያስደረግሁህን እፈጽምልሃለሁ ብሎ ጠራው። እንዲህም ተጋድሎውን ፈጸመ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ምንጭ:- መጽሐፈ ስንክሳር

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #ነሐሴ ፲፫ (13) ቀን። ❤ እንኳን #ጌታችን_ልክ_በደብረ_ታቦር ለእነ #ቅዱስ_ጴጥሮስ ብርሃነ መለኮቱን እንደገለጠላቸው ሁሉ ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ ለሆኑት ለአባታችን #ለአቡነ_ሊቃኖስም እንዲሁ በበዓታቸው #በደብረ_ቆናጽል_ገዳም ሳሉ ብርሃነ መለኮቱን ገልጦ ለአሳያቸው ዓመታዊ መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ በዚች ቀን ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዓይነት መንገድ በሀገራችን በሚገኘው በደብረ ቆናጽል ገዳም ላይም ብርሃነ መለኮቱን ገልጦበታል። የተገለጠውም እንደነ ሄኖክና ኤልያስ በሞት ፋንታ የለተሰወሩት ለአቡነ ሊቃኖስ ነው። ❤ አቡነ ሊቃኖስ ከዘጠኙ ቅዱሳን ውስጥ አቡነ ሊቃኖስ ለየት የሚሉበት ነገር ቢኖር ዓሥሩም የእጆቻቸውና የእግሮቻቸው ጣቶች እንደፋና ያበሩ ነበር፡፡ ይህንንም ገድለ አቡነ አረጋዊ "ቆመው ጸሎት በሚጸልዩበት ጊዜ ዓሥሩ የእጆቻቸው ጣቶችና ዓሥሩ የእግሮቻቸው ጣቶች እንደፋና የሚያበሩበትና እንደመብረቅ የሚብለጨልጩበት ጊዜ አለ" በማለት ይገልጸዋል፡፡ በሥዕላቸውም ላይ ይህንኑ ለማሳየት አባቶቻችን የራሳቸውን ጥበብ ተጠቅመዋል፡፡ ❤ የአቡነ ሊቃኖስ ገዳማቸው በደብረ ቁናጽል አክሱም ከአባ ጰንጠሌዎን ገዳም አቅራቢያ ይገኛል፡፡ ጻድቁ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ያደረጉ ነበር፡፡ መላእክትም ዘወትር ባለመለየት ይጎበኙዋቸው ነበር፡፡ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዘወትር እየተገለጠላቸው ይባርካቸውና ቃልኪዳን ይሰጣቸው ነበር፡፡ ❤ ጌታችን ነሐሴ 13 ቀን ልክ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዓይነት መንገድ በዚህ በፎቶው ላይ በሚታየው በአቡነ ሊቃኖስ ገዳም ላይም ብርሃነ መለኮቱን ገልጦበታል። ❤ አቡነ ሊቃኖስ በደረቅ ጭንጫ ላይ ውሃ በተአምራት አፍልቀው ለቅዳሴ ማይ ጸሎት ይጠቀሙበት ነበር፡፡ አቡነ ሊቃኖስም እንደ መሴ ከጭንጫ ላይ ያፈለቁትን ውሃ በወንፊት አድርገው ለአቡነ ገሪማና ለአቡነ ጰንጠሌዎን ይልኩላቸዋል፡፡ ከዳግማዊው ሙሴ ከአቡነ ሊቃኖስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ ከገድላት አንደበት።

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያክ ፲፫ኛ ዓመት የዕረፍተ ሥጋ የመታሰቢያ ጸሎተ ፍትሐት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የሸገር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ብፁዕ አ
+6
የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያክ ፲፫ኛ ዓመት የዕረፍተ ሥጋ  የመታሰቢያ ጸሎተ ፍትሐት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የሸገር  ሀገረ  ስብከት ሊቀ ጳጳስና የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ፣የራያ አህጉረ  ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፣ የጠቅላይ ቤተክህነት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት  በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዛሬ ነሐሴ 10/2017 ዓ.ም ተከናወነ ።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #ነሐሴ ፱ (9) ቀን። ❤ እንኳን #ለአባታች_ለአቡነ_እስትንፋሰ_ክርስቶስ ለወራዊ መታሰቢያ በዓል (በዚች ቀን አባታችን እስትፋሰ ክርስቶስ ከሰማይ የወረደውን የቊርባን ኅብስት ተቀብለው ያቀበሉበት ነው ብሎ ገድላቸው ይናገራል)ና ስጥኑፍ ከሚባል አገር ለሆኑ ለሰማዕቱ ለካህኑ #አባ_ኦር ለዕረፍት በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በፍቅር አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ሚታሰቡ፦ #ከሊቀ_ጳጳስ_አባ_ጲላጦስ ከመታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                            ✝ ✝ ✝ ❤ ስጥኑፍ ከሚባል አገር የሆነ የከበረ #ቄስ_አባ_ኦሪ፦ ይህ ቅዱስ ብዙ ርኅራኄ ያለው በሥጋው በነፍሱም ንጹሕ የሆነ ነው ብዙ ጊዜም አምላካዊ ራእይን ያያል። ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመሠዊያው ላይ ታይቶ ብዙ ምሥጢራትን ገለጠለት። ❤ ከዚህም በኋላ የአባ ኦሪ ዜናው በኒቅዮስ አገር መኰንን ዘንድ ተሰማ ወደርሱም አስቀርቦ "ለአማልክት ዕጣን አቅርብ" አለው እርሱም "ለረከሱና ለተሠሩ አማልክት አልሠዋም" ብሎ እምቢ አለው። መኰንኑም ተቆጥቶ በብዙ ሥራ አስፈራራው ቅዱስ ኦሪም ሥቃዩን ምንም ምን አልፈራውም ጹኑ ሥቃይንም አሠቃየው። ❤ ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ አገር ላከው በዚያም ጽኑዕ የሆነ ሥቃይን አሠቃይተው በወህኒ ቤት ጣሉት። በዚያም ድንቆች ተአምራቶችን በማድረግ በሽተኞችን ፈወሳቸው ። ዜናውም በተሰማ ጊዜ ደዌ ያለባቸው ሁሉ ከየአገሩ ብዙዎች ሰዎች ወደርሱ መጥተው አዳናቸው። ይህንንም መኰንኑ ሰምቶ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ በመንግስተ ሰማያትም የሰማዕትነትን አክሊል ተቀበለ። ❤ ከዚህም በኋላ የከበረ ዮልዮስ ሥጋውን አንሥቶ ገንዘው ወደ ሀገሩ ስጥኑፍም ላከው። የመከራውም ወራት ካለፈ በኋላ ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ሠርተውለት ሥጋውን በውስጧ አኖሩ ከሥጋውም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ። በማመንም ለሚመጡ በሽተኞች ሁሉ ታላቅ ፈውስ ሆነ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አባ ኦሪ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 9 ስንክሳር።                           ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት። ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ"። መዝ 44፥9-10። የሚነበቡት መልዕክታት ፊሊ 1፥12-24፣ 2ኛ ዮሐ 1፥6-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 15፥19-25። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 10፥1-22። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።

ነሐሴ ፰ /8/
በዚች ቀን አልዓዛርና ሚስቱ ሰሎሜ አንኤም አንጦኒኃስ ዖዝያ አልዓዛር አስዮና ስሙና መርካሎስ የሚባሉ ልጆቻቸውም ሰባቱ በሰማዕትነት አረፉ። ይህም አረጋዊ አልዓዛር ከመምህራነ ኦሪት አንዱ ነው እርሱም ለሕዝቡ አለቃና ሊቀ ካህናትም ነው በፈሪሀ እግዚአብሔርም ሁኖ ያስተዳድራቸው ነበር። ከዚህም በኋላ ዳታንና አቤሮን በሙሴና አሮን ላይ እንደተነሡባቸው ከዘመዶቹ ወገን ሦስት ካህናት በእርሱ ላይ ቀንተው ተነሡበት። የእሊህም ስማቸው ስምዖን አልፍሞስ መባልስ ይባላል ሹመቱንም እንዲለቅላቸው ፈለጉ ሕዝቡ ግን የአልዓዛር ሹመቱ ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰው አይደለም ብለው ከለከሉአቸው። ስለዚህም ነገር ወደ ግሪክ አገር ወርደው ንጉሥ አንጥያኮስን አነሳሡት መጥቶም የእስራኤልን መንግሥት እንዲወስድ ቀሰቀሱት ። በመጣ ጊዜም ወደ ከተማቸው በተንኮል እንዲገባ አደረጉት። በገባ ጊዜም ሊቀ ካህናቱ አልዓዛርን ይዞ የእሪያ መሥዋዕትን ለሕዝቡ እንዲሠዋ አዘዘው እምቢ ባለውም ጊዜ ሰባቱን ልጆቹን ገደላቸው ። እርሱንና ሚስቱን በእሳት በአጋሉት ብረት ምጣድ ላይ አስተኙአቸው እንዲህም ምስክርነታቸውን ፈጸሙ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የእሊህ ቅዱሳንም በረከታቸው ከእኛ ጋራ ትኑርለዘላለሙ አሜን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ምንጭ:- መጽሐፈ ስንክሳር

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #ነሐሴ ፯ (7) ቀን። ❤ እንኳን #ለእናታችን_ለእመቤታች_ለቅድስት #ድንግል_ማርያም_ለፅንሰቷ_በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላም አደረሰን።                                                     ✝ ✝ ✝ ❤ በዚች ቀን እግዚአብሔር የመላእት አለቃ #ቅዱስ_ገብርኤልን ወደ ከበረና ከፍ ከፍ ወዳለ #ጻድቅ_ኢያቄም ላከው አምላክን የወለደች #የእመቤታችን_የድንግል_ማርያምን_ፅንሰቷን ልደቷን በእርሷም ለዓለሙ ሁሉ ድኅነትና ተድላ ደስታ እንደሚሆን ነገረው። ❤ ይህም ጻድቅ ሰው ኢያቄምና የከበረች ሚስቱ ሐና ልጅ ሳይወልዱ ሸመገሉ የከበረች ሐና መካን ሁናለችና ስለዚህም እጅግ ያዝኑ ነበር የእስራኤልም ልጆች ልጅ ያልወለደውን ከእግዚአብሔር በረከትን ያጣ ነው እያሉ ያቃልሉት ነበርና። እነርሱም ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ዘወትር ፈጽሞ ይለምኑ ነበር። ❤ ከዚህም በኋላ ወንድ ልጅን ወይም ሴት ልጅን ቢወልዱ ለእግዚአብሔር ቤት አገልጋይ ሊያደረጉ ስለትን ተሳሉ። የከበረ ኢያቄምም በተራራ ላይ ሳለ ሲጸልይና ሲማልድ እነሆ በላዩ እንቅልፍ እንቅልፍ ብሎት አሸለበ ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የተላከ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ተገለጸለት እንዲህም አለው "ሚስትህ ሐና ትፀንሳለች ዓለሙ ሁሉ ደስ የሚሰኝባትን የብዙዎች ዐይነ ልቡ ናቸው በእርሷ የሚበራላቸውን በእርሷም ድኅነት የሚሆንባትን ሴት ልጅን ትወልድልሃለች። ❤ በነቃ ጊዜም ወደ ቤቱ ሒዶ ለሚስቱ ለቅድስት ሐና ነገራት ራእይዋን እውነት እንደሆነች አመኑዋት ከዚህም በኋላ ነሐሴ ሰባት በዚች ቀን የከበረች ሐና ፀነሰች ለዓለም ሁሉ መመኪያ የሆች በሁለት ወገን ድንግል የሆነች የአምላክ እናት አመቤታችንን ማርያምን ወለደቻት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ በቅዱስ ኢያቄምና በቅድስት ሐና ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን። ለምንጭ፦ የነሐሴ 7 ስንክሳር።                             ✝ ✝ ✝ ✝ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን። ያበድሮን እግዚአብሔር ለአናቅጸ ጽዮን። እምኵሉ ተዐይኒሁ ለያዕቆብ"። መዝ 86፥1-2። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 1፥1-17።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ብፁዕ ብእሲ ዘአንተ ገሠፅኮ እግዚኦ። ወዘመሀርኮ ሕገከ። ከመ ይትገኃሥ እመዋዕለ እኩያት።" መዝ 93፥12-13 ወይም መዝ 84፥11-12። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 9፥1-11፣ 1ኛ ጴጥ 2፥6-18 እና የሐዋ ሥራ 16፥13-19። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 16፥13-24። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ቅዳሴ ነው፡፡ መልካም የእመቤታችን የፅንሰት በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤                ❤ #ነሐሴ ፬ (4) ቀን። ❤ እንኳን #ከዳዊት_ዘር_ለሆነ ለአካዝ ልጅ ንስሃ በመግባቱ በእድሜ ላይ 15 ዓመት ለተጨመረለት #ለንጉሥ_ቅዱስ_ሕዝቅያስና እንደ በግ የጸጉር ልብስ ለብሶ በበረሃ ለሚኖር ሰማዕቱ #ቅዱስ_መርምኅናምን ላሳመነና እህቱን ሣራንም ከለምፅዋ ላነፃት ለአባታችን #አባ_ማቴዎስ_ለዕረፍታቸው_በዐል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከከበሩ #ዳዊትና_ወንድሞቹና ከግብጽ ደቡብ ስንካር ከሚባል አገር በሰማዕትነት ከዐረፈ #ከቅዱስ_ፊልጶስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                         ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_ንጉሥ_ሕዝቅያስ፦ ይህ ንጉሥ ከዳዊት ዘር የአካዝ ልጅ ነው። ከጻድቁ ንጉሥ ከዳዊት በኋላ እንደ ሕዝቅያስ ያለ በእስራኤል ውስጥ አልተሾመም ከዚህ ጻድቅ ንጉሥ በቀር ሁሉም ጣዖትን አምልከዋልና መሠዊያም ሠርተዋልና። ❤ እርሱም በነገሠ ጊዜ ጣዖታትን ሰበረ መሠዊያቸውንም አፈረሰ ከነሐስ የተሠራውንም እባብ ቆራረጠ የእስራኤል ልጆች አምልከውት ነበርና እግዚአብሔርም ዘመነ መንግሥቱን እጅግ አሳመለት በጎ ነገርንም ሁሉ ሰጠው። ❤ ሕዝቅያስም በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዘመን የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ኢየሩሳሌምን ከበባት ይህም ሰናክሬም በዘመኑ እንደርሱ ያለ የሌለ ኃይለኛ ብርቱ የምድር ነገሥታት ሁሉ የፈሩትና የታዘዙለት ነው። ሕዝቅያስም ከእርሱ ግርማ የተነሣ ፈርቶ አገሩን እንዳያጠፋ ብዙ ወርቅና ብር እጅ መንሻ ላከለት ሰናክሬምም ደስ ብሎት ምንም ምን አልተቀበለም በእርሱ ላይና በልዑል እግዚአብሔር ላይ ተቆጥቶ "እግዚአብሔር ከእኔ እጅ ሊያድናችሁ አይችልም " በማለት የስድብ ቃል ላከ እንጂ። ❤ ሁለተኛም በልዑል ስም ላይ ስድብና ቊጣ የተጻፈበትን ደብዳቤ ላከ ሕዝቅያስም በሰማ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ አለቀሰ ልብሱንም ቀዶ ማቅ ለበሰ እንዲህም ብሎ ጸለየ "አቤቱ የእስራኤል አምላክ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ አንተም ብቻህን ዓለም መንግሥታት ላይ ንጉሥ የሆንክ አንተም ሰማይና ምድርን የፈጠርህ ልመናዬን አድምጥ። ዐይኖችህን ገልጠህ ተመልከት ሕያው እግዚአብሔር አንተን እያቃለለ ሰናክሬም የላከውን ቃሉን ስማ"። ❤ ከዚህም በኋላ ንጉሥ ሕዝቅያስ የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬም የተናገረውን እንዲነግሩትና ስለርሱና ስለ ሕዝቡ ይጸልይ ዘንድ ወደ ኢሳይያስ መልእክተኞችን ላከ። ኢሳይያስም ከእግዚአብሔር ቃልን ተቀብሎ እንዲህ ብሎ መለሰለት "ልብህን አጽና አትፍራ በዓለሙ ሁሉ እንደርሱ ያለ ያልተማ ዕፁብ ድንቅ የሆነ ሥራ በሰናክሬም ላይ ሊሠራ እግዚአብሔር አለውና"። ❤ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር የላከው መልአክ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ ከፋርስ ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሰዎችን ገደለ የለኪሶም ሰዎች ሲነጋ በተነሡ ጊዜ የሞቱትን ሰዎች ሬሳ ሁሉ አገኙ የተረፉትም ከንጉሣቸው ጋራ ሸሽተው ነነዌ አገር ገቡ። ሰናክሬምም ሊጸልይ ወደ ጣዖቱ ቤት በገባ ጊዜ ልጆቹ አድራማሌክና ሶርሶር በሰይፍ መትተው ገደሉት። ሕዝቅያስም ከሰናክሬም እጅ ድኖ የተመሰገነ እግዚአብሔርን አመሰገነው። ❤ በዚያም ወራት ሕዝቅያስ ታመመ ለሞትም ደረሰ የአሞፅ ልጅ ኢሳይያስም ወደርሱ መጥቶ "እግዚአብሔር እንዲህ አለ ትሞታለህ እንጂ አትድንም ቤትህን ሥራ" አለው። ሕዝቅያስም ፊቱን ወደግድግዳው መልሶ ወደ እግዚአብሔር ለመነ እያመሰገነውም እንዲህ አለ "አቤቱ በቀና ልቡና በዕውነት ሥራ በፊትህ ጸንቼ እንደኖርኩ ፈቃድህንም እንደፈጸምሁ አስብ" ብሎ ሕዝቅያስ ፈጽሞ ጽኑዕ ልቅሶን አለቀሰ። ❤ ኢሳይያስም ወደ መካከለኛው ዐፀድ ደረሰ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው "ሒደህ ለወገኖቼ ንጉሥ ለሕዝቅያስ ያባትህ የዳዊት ፈጣሪ እግዚአብሔር እንዲህ አለ በለው። ጸሎትህን ሰማሁ ዕንባህንም አየሁ እነሆ እኔ አድንሃለሁ እስከ ሦስት ቀንም ወደ እግዚአብሔር ቤት ትመጣለህ። በዘመኖችህም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት ጨምሬልሃለሁ ከፋርስ ንጉሥ እጅም አድንሃለሁ ይቺንም አገር ስለ እኔና ስለ ባላሟሌ ዳዊት አጽንቼ እጠብቃታለሁ"። ❤ ሕዝቅያስም ኢሳይያስን እንዲህ አለው "እግዚአብሔር እንደሚያድነኝ እስከ ሦስት ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት ለመውጣቴ ምልክት ምንድ ነው"። ኢሳይያስም እንዲህ አለው "የተናገረውን ቃል ያደርግ ዘንድ ከእግዚአብሔር የተገኘ ምልክቱ ይህ ነው አነሆ ጥላው ወደ ዐሥረኛው እርከን ይወርዳል። ወደ ዐሥረኛው እርከን ቢመለስ ምልክቱ ይህ ነው"። ሕዝያስም "እንዲህ አይደለም የጥላው ወደ ዐሥረኛ እርከ መመለስ ቀላል ነው። መመለስስ ከሆነ ፀሐይ ወደ ዐሥረኛው እርከን ይመለስ" አለ። ኢሳያስም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ ፀሐይም ዐሥሩን እርከን ተመለሰ። ❤ ሕዝቅያስንም የምድር ነገሥታት ሁሉ ፈሩት እጅ መንሻም አገቡለት የእግዚአብሔር ኃይል ከእርሱ ጋራ እንዳለ አውቀዋልና። በመንበረ መንግሥቱም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነግሦ ኖረ። እግዚአብሔርን አገልግሎ ነሐሴ 4 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በንጉሥ ቅዱስ ሕዝቅያስ በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።                               ✝ ✝ ✝ ❤ በዚችም ቀን እንደ በግ የደጒር ልብስ ለብሶ በበረሃ የሚኖር #አባ_ማቴዎስ ዐረፈ። እርሱም መርኅናምን ያሳመነው ሣራንም ከለምፅዋ ያነፃት ነው። የአባ ማቴዎስ በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 4 ስንክሳር።                              ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለሕዝቅያስ_ዘጸለየ_በሕቁ። ዘተወሰከ ዘመኑ ወፈድፈደ እምኊልቁ። እመኒ ሶቤሃ ተዐየርዋ ለድድቁ። በእደ መልአክ ሠራዊት ፋርስ ኀልቁ። ወለመልኮሙ ቀተልዎ ደቁ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የነሐሴ_4።                ❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤ ❤ እንኳን #ለጾመ_ፍልሰት_የመጀመሪያ_ሳምንት ለዕለት እሑድ እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዚህ_ሳምንት_መዝሙር፦  ሃሌ ሉያ በ፪ "ዮም ንወድሳ ለማርያም በእንተ ዘተወልደ እምኔሃ መንክር ግርማ ኀይለ ልዑል ጸለላ ፆረቶ በከርሣ ውእቱኒ ቀደሳ አዝ (መ) እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት መንክር ግርማ ኀይለ ልዑል ጸለላ አማን መላእክት ይኬልልዋ"። ትርጉም፦ አምላክ ከርሷ ስለተወለደ ማርያምን ኑ ዛሬ እናወድሳት፤ በድንቅ ግርማ የልዑል ኀይል ጋረዳት፤ የምሕረት አባት በድንቅ ግርማ በታላቅ ኀይል ጋረዳት፤ የምሕረትን አባት በማኅፀኗ ወሰነችው፤ እርሱም ቀደሳት፣ ለያት፣ ከፍ ከፍ አደረጋት፣ አጸናት ልዩ አደረጋት፤ የሰንበት ጌታ የምሕረት አባት በድንቅ ግርማ በታላቅ ኀይል ጋረዳት፤ በእውነት መላእክት አመሰገኗት። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በድጓው_ላይ።                          ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዚህ_ሳምንት_የዕለቱ_ምስባክ፦ "እመነ ጽዮን ይብል ሰብእ። ወብእሲ ተወልደ በውስቴታ። ወውእቱ ልዑል ሣረራ"። መዝ 86፥5። የሚነበቡ መልክታት 1ኛ ቆሮ 8፥1-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 4፥1-6 እና የሐዋ ሥራ 26፥1-24። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥39-46። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም ዕለተ ሰንበትና የሱባዔ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #ነሐሴ ፫ (3) ቀን። ❤ እንኳን #በገድል_ለተጠመዱ ስልሳ ክንድ የድንጋይ ምሰሶ ላይ ወጥተው በዚያም ሳይቀመጡ ቆመው እያስተማሩና እየጸለዩ #ለ42_ዓመታት ለተጋደሉ ለታላቁ አባት #ለአባ_ስምዖን_ዘዓምድ_ሶርያዊ ለዕረፍት በዐልና ከመንግሥት ወገን ለሆነች #ለቅድስት_ሶፍያ_ዘሮምና_ለሦስት_ሴት_ደናግል ልጆቿ ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዐል በሰላም አደረሰን።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ስምዖን_ዘዓምድ_ሶርያዊ፦ ለዚህም ቅዱስ ስድስት ዓመት በሆነው ጊዜ አባቱ የበጎቹ ጠባቂ አደረገው። ወደ ቤተ ክርስቲያንም በመሔድ ሁል ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን ይሰማ ነበር የእግዚአብሔርም ቸርነት አነሳሥቶት ወደ አንድ ገዳም ሒዶ መነኰሰ ብዙ ዘመናትም በገድል ተጠምዶ ሲጋደልና ሰውነቱን ሲያስጨንቅ ኖረ። ❤ ከዚህም በኋላ ገመዱ ሥጋውን ቆርጦ እስቲገባ ድረስ በወገቡ ላይ ገመድን አሠረ። ሥጋውም ተልቶ ከእርሱ ክፉ ሽታ ይወጣ ነበር ስለ ክፉ ሽታውም መነኰሳቱ አዘኑ ተጸየፉትም ወደ አበ ምኔቱም ተሰብስበው "ይህን መነኰስ ስምዖንን ከእኛ ዘንድ ካላወጣኸው አለዚያ አንተን ትተን ወደሌላ እንሔዳለን" አሉት እርሱም "ምን አደረገ" አላቸው እነርሱም "ጥራውና አንተ ራስህ እይ" አሉት። ጠርቶትም መጥቶ በፊቱ በቆመ ጊዜ ደም ከመግል ጋራ በእግሮቹ ላይ ሲፈስ አየ አበ ምኔቱንም እጅግ አስጨነቀው። ልብሶቹንም ገልጦ በሥጋው ውስጥ የገባውን ያንን ገመድ አየው አበ ምኔቱም በእርሱ ላይ ተቆጥቶ "ይህን ታደርግ ዘንድ እንዴት ደፈርክ" አለው በታላቅ ድካምም ያንን ገመድ ከሥጋው ውስጥ አወጡት ቍስሉም እስከሚድን መድኃኒት እያደረጉለት ኃምሳ ቀኖች ያህል ኖረ። ❤ ከዚህም በኋላ አበ ምኔቱ እንዲህ አለው "ልጄ ስምዖን ሆይ እንግዲህስ ወደ ፈለግኸው ቦታ ሒድ" ከዚያም ወጥቶ ሔደ በደረቅ ጕድጓድ ውስጥም ገብቶ ከእባቦችና ከጊንጦች ጋራ ኖረ። ❤ ከዚህም በኋላ "አገልጋዩ ስምዖንን ለምን ሰደድከው አሁንም ፈልገህ መልሰው በፍርድ ቀን እርሱ ከአንተ ይሻላልና" ብሎ ሲገሥጸው አበ ምኔቱ ራእይን አየ። አባ ስምዖንንም ከገዳሙ ስለመውጣቱ ገሠጸው። በነጋም ጊዜ አበ ምኔቱ ራእይን እንዳየ ስለ አባ ስምዖንም እንደገሠጸው ለመነኰሳቱ ነገራቸው ወንድሞችም ደንግጠው እጅግ አዘኑ "እስከምታገኙትም ሔዳችሁ በቦታው ሁሉ ፈልጉት" አላቸው ሔደውም ፈለጉት ግን አላገኙትም። ከዚህም በኋላ መብራትን አብርተው ወደ ጕድጓድ ውስጥ ገቡ ያለ መብልና መጠጥም ከእባቦችና ከጊንጦች ጋራ ተቀምጦ አዩት። ❤ ገመድም አውረዱለትና ከዚያ አወጡት በፊቱም ሰግደው "በአንተ ላይ ያደረግነውን በደላችንን ይቅር በለን" አሉት "እኔንም ስለ አሳዘንኳችሁ ይቅር በሉኝ" አላቸው። ከዚህም በኋላ ወደ ገዳማቸው ወሰዱት በብዙ ገድልም ተጠምዶ ሲያገለግል ኖረ። ❤ ከዚህም በኋላ ከዚያ ገዳም በሥውር ወጥቶ ወደ አንዲት ዐለት ቋጥኝ ደረሰ። በእርስዋም ላይ ሳያረፍና ሳይተኛ ስልሳ ቀን ቆመ። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ስለ ብዙ ሰዎች ድኅነት እግዚአብሔር እንደ ጠራው ነገረው። ከዚያም ሔዶ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ የሚሆን የድንጋይ ምሰሶ አገኘ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ በሽተኞችንም እየፈወሰ ወደርሱ የሚመጡትንም እያስተማረ ዐሥራ ሁለት ዓመት በድንጋይ ምሰሶው ላይ ቆመ። ❤ አባቱም ፍልጎት ነበር ግን ሳያየው ሞተ እናቱ ግን ወሬውን ሰምታ ከብዙ ዘመናት በኋላ ወደርሱ መጣች በድንጋይ ምሰሶውም ላይ ቁሞ አገኘችው አይታውም አለቀሰች ከድንጋይ ምሰሶውም በታች ተኛች። ቅዱስ ስምዖንም ጌታችን በጎ ነገርን ያደርግላት ዘንድ ስለርሷ ለመነ ያን ጊዜም እንደተኛች ዐረፈችና ከደንጊያው ምሰሶ በታች ቀበሩዋት። ❤ ሰይጣንም በእርሱ ላይ ቀንቶ እግሩን መታው ከእግሩ ትል እየወደቀ በአንዲት እግሩ ብዙ ዓመታት ኖረ። ከዚህም በኋላ የሽፍቶች አለቃ ወደርሱ መጥቶ ንስሐ ገባ ጥቂት ቀኖችም ኑሮ ዐረፈ በጸሎቱም ሕይወትን ወረሰ። ወደርሱ ስለሚመጡ ብዙ ሕዝቦችም የውኃ ጥማት እንዳያስጨንቃቸው ወደ እግዚአብሔር ለምኖ ከድንጋይ ምሰሶው በታች ውኃን አፈለቀላቸው። ❤ ዳግመኛም ወደ ሌላ ምሰሶ ተዛወረ በእርሱም ላይ እየተጋደለ ሠላሳ ዓመት ኖረ። ብዙዎች አረማውያንንና ከሀድያንን ካስተማራቸውና ወደ ፈጠራቸው እግዚአብሔር ከመለሳቸው በኋላ ክብር ይግባውና ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔደ በሰላምም ዐርፎ የዘላለም ሕይወትን ወረሰ። ❤ ከዚህም በኋላ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባ ስምዖን እንዳረፈ በሰማ ጊዜ ካህናትን ዲያቆናትንና የአገሩን መኳንንቶች ከእርሱ ጋራ ይዞ የቅዱስ አባ ስምዖን ሥጋው ወዳለበት ደረሰ በታላቅ ክብርም ተሸክመው እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ እስክንድርያ አድርሰው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት ከሥጋውም ድንቆችና ተአምራቶች ታላቅ ፈውስም ተገለጡ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛን በመስተጋድል በአባ ስምዖን ዘአምድ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅድስት_ሶፍያ_ሦስቱ_ደናግል_ልጆቿ፦ ለዚችም ቅድስት ብዙ ሀብትና ብዙ ጥሪት ነበራት ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ ፍቅር የክርስቶስን መከራ መስቀል አንሥታ ትሸከም ዘንድ ከሦስት ሴቶች ልጆቿ ጋራ ወደ ሮም ከተማ ሔደች። ❤ ንጉሥ እንድርያሰኖስም ክርስቲያን እንደ ሆነች አውቆ ከልጆቹ ጋራ ወደ አደባባይ አስቀረባትና ስለ ሀገርዋና ስለ ስሟ ጠየቃት እርሷም "የሚቀደመው ስሜ ክርስቲያን ነኝ ወላጆቼ ያውጡልኝ ስም ሶፊያ ነው እኔም በኢጣልያ ባለ ብዙ ወገን ነኝ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ፈቃድም ልጆቼን መሥዋዕት አድርጌ ላቀርብ ወደ አገርህ መጣሁ" አለችው። ከዚህም በኋላ የከዳተኛው ንጉሥ ሥቃዩ እንዳያስፈራቸው ልጆቿን አበረታቻቸው። ❤ ምስክርነታቸውንም ፈጽመው ከሞቱ በኋላ ገንዛ ከሮሜ ከተማ ውጭ ቀበረቻቸው። በሦስተኛውም ቀን መታሰቢያቸውን ታደርግ ዘንድ ልጆቿ ወደ ተቀበሩበት ከብዙዎች ከከተማው ሴቶች ጋራ ሔደች እንዲህ ብላም ጸለየች "አክሊላትን የተቀዳጃችሁ የምታምሩ ፍጹማት የሆናችሁ ልጆቼ ሆይ እኔንም ከእናንተ ጋራ ውሰዱኝ" ይህንንም እንዳለች ወዲያውኑ ዐረፈች ከልጆቿም ጋር ተቀበረች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ሶፍያና በሦስቱ ደናግል ልጆቿ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ "#ሰላም_ለስምዖን_እንተ_ለሐቌሁ_አድንዖ። በኀብለ በቀልት ይቡስ ዘይገምዶ ወይበልዖ። በእንተ ዝንቱ እምደብር ሶበ አበምኔት አውጽኦ። በቃለ ተግሣጽ እግዚአብሔር አውሥኦ። ለገብርየ ስምዖን እንዘ ይብል አግብኦ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የነሐሴ_3።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወይሰግዳ ሎቱ አዋልደ ጢሮስ በአምኃ። ወለገጽኪ ይትመሀለሉ ኵሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር። ኵሉ ክብራ ለወለተ ንጉሥ፡ሐሴቦን"። መዝ 44፥12-13። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ተሰ 3፥1-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 3፥10-15 እና የሐዋ ሥራ 14፥20-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 18፥9-18። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ቅዳሴ ነው፡፡ መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።

በአዲስ አበባ ሃ/ስብከት ስብከተ ወንጌል መምሪያ መልካም ፈቃድ በደብራችን የተዘጋጀ መንፈሳዊ ጉባኤ ነሐሴ 11 እና 12 ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሁላችሁም ታስተዋውቁት ዘንድ በአክብሮት እጠይቃለሁ ።
በአዲስ አበባ ሃ/ስብከት ስብከተ ወንጌል መምሪያ መልካም ፈቃድ በደብራችን የተዘጋጀ መንፈሳዊ ጉባኤ ነሐሴ 11 እና 12 ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሁላችሁም ታስተዋውቁት ዘንድ በአክብሮት እጠይቃለሁ ።