ru
Feedback
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን🙏

የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን🙏

Открыть в Telegram

የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና የጠበቁ የነፍስ ስንቅ የምናገኝበት፦ ✍️"ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም" ፩ኛ ቆሮ. ፰፥፪ #ለተጨማሪ፦👇✞👇 https://www.youtube.com/EOTC2921 https://www.facebook.com/eotc2921 https://www.tiktok.com/@eotc2921 https://www.instagram.com/eotc2921

Больше
4 374
Подписчики
Нет данных24 часа
Нет данных7 дней
Нет данных30 дней
Архив постов
✞በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን✞ •••✞✞✞•••✞✞✞•••✞✞✞••• 🌿🌿✞ #ምስጢረ_ስላሴን ✞🌿🌿 ✞ #ለህፃናት_እንዲህ_እናስተምር ✞ #ማን_ፈጠረን? ☞✞ ስላሴ #ስላሴ_ስንት_ናቸው? ☞✞ አንድም ሶስትም #ሶስትነታቸው_በምን_በምን_ነው? ☞✞ በስም፣ በአካል፣ በግብር #አንድነታቸውስ_በምን_ነው? ☞✞ በባህሪ፣በህልውና፣ በመለኮት፣ በፍቃድ፣ በስም፣ በአካል፣ በግብር ይህችን፣ አለም በመፍጠርና በማሳለፍ #የስም_ሦስትነታቸው_እንዴት_ነው? ☞✞ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ #የአካል_ሶስትነታቸው_እንዴት_ነው? ☞✞ #አብ ፍፁም አካል ፍፁም መልክ ፍፁም ገፅ አለው። ☞✞ #ወልድ ፍፁም አካል ፍፁም መልክ ፍፁም ገፅ አለው። ☞✞ #መንፈስቅዱስ ፍፁም አካል ፍፁም መልክ ፍፁም ገፅ አለው። #የግብር_ሶስትነታቸው_እንዴት_ነው? ☞✞ አብ=ወላዲ፤ ወልድ=ተወላዲ፤ መንፈስ ቅዱስ=ሰራፂ #አብ_ምን_ማለት_ነው? ☞✞ አባት፦ መንፈስ ቅዱስን ያሰረጸ፤ ያለእናት ወልድን የወለደ #ወልድ_ምን_ማለት_ነው? ☞✞ ልጅ፦ የሚወለድ፤ ያለእናት ቅድመ ዓለም፤ ያለ አባት ድህረ ዓለም የተወለደ #መንፈስ_ቅዱስ_ምን_ማለት_ነው? ☞✞ ሰራፂ፦ ረቂቅ፣ ልዩ፣ ንፁህ ሁኖ ከአብ የሰረፀ ✞✞✞•••✞✞✞•••✞✞✞ የእግዚአብሔር አብ በረከት፣ የእግዚአብሔር ወልድ ፍቅር፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን፡፡ ✞✞✞•••✞✞✞•••✞✞✞

✞በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን✞ •••✞✞✞•••✞✞✞•••✞✞✞••• #ምስጢረ_ስላሴ_በጥቂቱ •••✞✞✞•••✞✞✞•••✞✞✞••• እኛ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች የእግዚአብሔር አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው፤ ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፋፍለው በአንድነትና በሦስትነት የሚመሰገን አንድ ሕያው አምላክ በሆነው በእግዚአብሔር እናምናለን፡፡ #አንድ_ሲሆን_ሦስት_ሦስት_ሲሆን_አንድ_በአካል_ሦስት_ሲሆን_በመለኮት_በአንድ_አምላክ_በሆነው_በልዑል_እግዚአብሔር ብቻ ነው የምናምን፡፡ ይህ ምስጢር ስጋን በለበሰ ህሊናችን ተመራምሮ ማወቅ አይቻልም በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ካልሆነ በስተቀር፡፡ ለዛም ነው ቤተ ክርስቲያናችን አምስቱ አዕማደ ምስጢራትን ስታስተምር በመጀመሪያ ምስጢረ ስላሴን መማር እንዳለብን ያስቀመጠችልን፡፡ ምስጢር ማለት፦ እጅግ ጥልቅ፣ የተሰወረ፣ የረቀቀ፤ ከመሆኑ የተነሳ #ምስጢር ይባላል፡፡ #ስላሴ ማለት ደግሞ "ሰለሠ" ወይም ሦስት አደረገ ማለት ሲሆን ትርጉሙም፦ ሦስትነት ማለት ነው፡፡ ✞✞✞ #የስላሴ_አንድነትና_ሦስትነት፦ ✞✞✞ ☞✞ #የስላሴ_አንድነት ፦ በአገዛዝ፣ በስልጣን፣ ይህን አለም በመፍጠርና በማሳለፍ፣ በህልውና፣ በመለኮት፣ በልብ፣ በቃል፣ በእስትንፋስ፤ በእነዚህ ሁሉ የመለኮት ባህርይ #አንድ ነው፡፡ #የእግዚአብሔር_ሦስትነት_ስንል፦እግዚአብሔር የማይለያይና የማይቀላቀል ፍጹም የሆነ ሦስትነት አለው ማለታችን ነው። የእግዚአብሔር ሦስትነትም፦ በስም፣ በግብር፣ በአካል ነው። ☞✞ እግዚአብሔር #በስም ሦስት ነው ስንል ሦስት የተለያዩ ስሞች አሉት ማለታችን ነው። እነዚህም፦ #አብ #ወልድ #መንፈስ_ቅዱስ የሚባሉት ሲሆኑ እርስ በርሳቸው አይወራረሱም፤ አንዱ በሌላው ስም አይጠራም። "ዘፍ፡1፥2 ፣ ምሳ፡30፥4" ። ☞✞ እግዚአብሔር #በግብር ሦስት ነው ስንል፤ ሦስት የተለያዩ የአካል ሥራዎች አሉት ማለት ነው። እነሱም፦ መውለድና ማስረጽ =የአብ፤ መወለድ=የወልድ፤ መስረጽ =የመንፈስ ቅዱስ፤ የሚሉት ሲሆኑ የአካል ግብር ይባላሉ። "መዝ፡2፥7" ☞✞ እግዚአብሔር በአካል ሦስት ነው ማለት ደግሞ #ለአብ፦ ፍፁም መልክ፤ ፍፁም ገጽ፤ ፍፁም አካል አለው። #ለወልድ ፤ ፍፁም መልክ፤ ፍፁም ገጽ፤ ፍፁም አካል አለው ። #ለመንፈስ_ቅዱስ ፤ፍፁም መልክ፤ ፍፁም ገጽ፤ ፍፁም አካል አለው ማለታችን ነው። ☞✞ የሦስቱ የእግዚአብሔር ስሞች ትርጉም፦ #አብ፦ ማለት አባት ማለት ሲሆን የሚወልድ፤የሚያሰርጽ ወይም የሚያስገኝ ያለ እናት ወልድን የወለደ፤ መንፈስ ቅዱስን ያሰረጸ ነው። #ወልድ፦ ልጅ ማለት ሲሆን የሚወለድ ወይም ያለ እናት ቅድመ ዓለም፤ ያለ አባት ድህረ ዓለም የተወለደ ነው። "መዝ፡2፥7" #መንፈስ_ቅዱስ፦ ረቂቅ፣ ልዩ፣ ንፁህ ከፍጡራን መናፍስት ሁሉ የተለየ ማለት ነው። "እዮ፡26፥13" ✞በመጽሐፍ_ቅዱስም ከበቂ በላይ ሁኖ ተገልፆልናል፡፡ ዘፍ፡1፥26 ፣ ዘፍ፡11፥7 ፣ ኢሳ፡6፥1-3 ፣ ኢሳ፡48፥16 ፣ ማቴ፡3፥16 ፣ ማቴ፡28፥19 ሉቃ፡1፥35 ፣ ዮሐ፡14፥25 ፣ ማቴ፡21፥18 ፣ 1ኛ ቆሮ፡12፥3 ፣ 2ኛ ቆሮ፡13፥14 ፣ ዘፍ፡3፥22 ፣ ማር፡10፥6 ፣ ማር፡10፥18 ፣ ዘፍ፡1፥3 ፣ ዘፅ፡5፥1 ፣ ዘፅ፡7፥17 ፣ ኢያ፡3፥17 ፣ ሐዋ፡1፥23 ወዘተ.... ከዚህም በላይ ስለአንድነትና ሦስትነታቸው እናገኛለን፡፡ የእግዚአብሔር አብ በረከት፣ የእግዚአብሔር ወልድ ፍቅር፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት፣ የእመቤታችን የድንግል ማርያም አማላጅነት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ ✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ✞

🌿🌾✞ #ድንግል_ማርያም_በሉ ✞🌾🌿 ድንግል ማርያም በሉ ምዕመናን ሁላችሁ በአማላጅነቷ ጥላ ስር ያላችሁ እንደኔ ከፍቅሯ ፍቅርን ያገኛችሁ/፪/ //፪// #አዝ የሐና የኢያቄም የበረከት ፍሬ ድንግል ስጦታዬ ክብሬ ከለላዬ ጥላሽን ጣይብኝ ያኔ እጽናናለሁ አረጋጊኝ ድንግል ባንቺ ታምኛለሁ #አዝ ድንግል እመቤቴ ድካሜን እዪና ፍርኃት ጭኝቀቴን አርቂልኝና የሕይወትን ፍሬ ሁሌ እንዳፈራ ነይልኝ እናቴ ከዮሐንስ ጋራ //፪// #አዝ

❖✞🍇 #የሕዝቅኤል_የተቈለፈች_መቅደስ_የአምላክ_እናት_በቅዱስ_ኤፍሬም_ሶርያዊ 🍇✞❖ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ✅ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅኤል በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝቶ በምዕ ፵፬፥፪ ላይ "ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ፤ ተዘግቶም ነበር፤ እግዚአብሔርም ይኽ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፤ ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል" በማለት የዘላለማዊ ድንግልናዋን ነገር ተናግራል፡፡ ❖ ይኸውም መቅደስ የቅድስት ድንግል ማርያም፤ በር የድንግልናዋ፤ መቈለፊያው የማኅተመ ድንግልናዋ ምሳሌ፤ አምላክ ሳይከፍታት ገብቶ ሳይከፍታት ሲወጣ ማየቱ እንበለ ዘርዕ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና መወለዱን፤ "አይከፈትም ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል" ብሎ መናገሩ ፱ ወር ከ፭ ቀን በማሕፀንዋ የተሸከመቺው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምም ማኅተመ ድንግልናዋ የማይለወጥ ዘላለማዊት ድንግል መኾኗን ሲገልጽለት ነው። ❖ ይኽነን እውነታ ከብዙ ድንቅ ሃይማኖታዊ ምስጢሮች ጋር በማስተባበር ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እንዲኽ ሲል ገልጾታል፡- ☞ “Leap for joy, young girls…” (ወጣት ልጃገረዶች በደስታ ዝለሉ፤ ድንግል ማርያም በመደነቅ ተመልታለች፤ ምክንያቱም ወጣት ሴቶችን አስገድዶ ክፉ ሥራ እንዲሠሩ የሚያባብለውን ተቃዋሚ ተነሥቶ አስገድዶ አስሮት ያቆመውን ከኀሊውን ወንድ ልጅን ተንበርክካ ወልዳለች፡፡ ለአንተ ለእግዚአብሔር ልጅ ምስጋና ይግባኽ፡፡ እናትኽን ሔዋንን ክፉ ሥራ እንድትሠራ ያባበላት ተቃዋሚ የሚጐዳ ፍሬን እንድትበላ አደረጋት፣ አኹን ግን … ማርያም ሞትን የሚያመርተውን ዛፍ ነቅላ ጥላዋለች፡፡ በዚኽም ለኹሉም ሕይወት የሚሰጥ ፍሬን አቅርባለች፡፡ ❖ በማሕፀኗ ውስጥ እሳት ይኖራል በጒያዋም ውስጥ ኀያል ድንቅ ነገር አለ፦ በጣቶቿ ይኽነን እሳት ያዘች በመዳፏም የሚያቃጥል ፀሓይን ተሸከመች፤ እንዴት ለመናገር ድንቅ የኾነ ነገር ነው!፡፡ ሕፃናትን የሚቀርጸውን (የሚሠራውን) ርሱን ተሸከመች፤ የሰው ዘር ሠሪን ወለደች፤ ኹሉንም ለሚመግበው ለርሱ ወተትን አቀረበች! ይኽነን በድንቅ የተመላ ነገር ማን ሊናገር ይችላል?፡፡ ❖ ማርያም የመደነቅ ምንጭ ናት በነፍሷ አስተዋይ ናት፤ በሰውነቷም ውስጥ ቅዱስ ናት፤ የእሳት ነበልባልን የተሸከመች የርሷ ዐሳብም አንጸባራቂ ነው፡፡ መውለዷን እና እስከአኹንም ድረስ ድንግል ኾና መቆየቷን እንዴት ሊኾን? እንደሚችል በማሰብ እንዴት መደነቅ ወደ ነፍሷ ወይም መገረም ወደ አእምሮዋ ወይም ፍርሀት ከዐሳቧ ሊያልፍ ቻለን?፡፡ ❖ በእጆቿ ውስጥ ሕፃኑን ተሸክማለች ግን በአካሏ ላይ የታተመ የድንግልና ማኅተሞችን እያየች፤ ወተት በጡቶቿ ውስጥ ሞቆ እየፈሰሰ እንኳንም ድንግልናዋ እንዳልተለወጠ በማየት በእያንዳንዱ ቀን በመደነቅ ትመላ ነበር፡፡ አዳማጮች በሚገኙበት ጊዜ በጥበብ በጥንቃቄ (ሕፃናት እሽሩሩ እንደሚባሉት) እንደ ሕፃን ትዘምራለች ግን በሚንቀሳቀሱ ጊዜም እንደ ክብር ጌታ ታመልከዋለች፡፡ ❖ በጭኗ ውስጥ ልጇን ተሸክሟ ነፍሷ በመደነቅ ይመላል፤ ልጇ በመኾኑ ትደሰታለች ግን በደንብ አድርጋ ጌታዋም እንደኾነ ታውቃለች፡፡ እንደ ልጇም እንደ ጌታዋም ተሸክማዋለች፡፡ ከሕፃኗ ጋር እንደነበረች ታይ ነበር ግን ድንግልናዋ እስከ አኹንም ድረስ ቆይቷል፡- ይኽ ዐዲስ አስደማሚ ክስተት የወለደችው ልጅ እግዚአብሔር እንደኾነ እንድትረዳ ጥንካሬን ሰጥቷታል፡፡ ❖ ድንግል ማርያም በመደነቅ ተከብባ በዚኽ በተደበቀ ምስጢር መኻከል በብርሀን ደምቃ ርሱ ማን እንደነበር ዐውቃና ርሷ የተሸከመችው ቡሩኩ ፍሬ የማን ልጅ እንደኾነ ታውቃለች፤ በኹሉም ነገር ውስጥ ብልኅ ነበረች፡፡ በምርኮ የተወለደው ሕዝቅኤል የዳዊት ብላቴና የኾነችውን ድንግልን በትንቢት ዐይን አይቶ ነበር፡፡ እንዲኹም ከእግዚአብሔር በተላከው በርሱ ራእይ ውስጥ የድንግልናዋን ምስል አሳየ (ሕዝ ፵፬፥፪)፡፡ ❖ በከለዳውያን ምድር ትንቢት የማርያም አምሳል አሳየ፣ በነቢያቶች መጽሐፍትም ውስጥ ርሷን አስቀመጠ፤ የርሷንም ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስጠብቋል ስለዚኽም ማንም ሰው ይኽነን በማንበብ ሊረዳ ይችላል፡፡ በካህናት ጉባኤ መኻከል ጌታ ለነቢዩ ተገልጾለት በሩ በጥብቅ እንደተዘጋ “ይኽ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል” በማለት ተናገረ)፡፡ (T.j. Lamy, Sancti Ephream Syri Hymni et Sermones, II (Malines, 1886) 519-590, Brock, hymns on Mary no. 4, p.38-40) ነገረ ማርያም በሊቃውንት ከሚለው መጽሐፌ የተወሰደ ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ 🙏የቅዱስ ኤፍሬም እመቤት ትባርከን፨🙏 ✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ ለወዳጅዎ #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞ ╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮ @EOTC2921 @Orthodox2921 ╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯

‹‹ #መቼም_የማይጾሙ ›› #እና ‹‹ #መቼም_የማይበሉ ›› ✅በቤተክርስቲያናችን ትምህርት ‹‹መቼም የማይጾሙ›› ወይም ‹‹ሁሌም የሚበሉ›› የሚባሉ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም በጾምም ይሁን በፍስክ የሚበሉ ወይም የሚደረጉ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል የሕያው እግዚአብሔርን ቃል መመገብ፣ ለእርሱና ለቅዱሳኑ ምስጋናን ማቅረብ፣ መልካም ነገርን መሰማት፤ ማየት፤ ማሰብ፣ መናገርና መሥራት ይገኙበታል፡፡ አንድ ሰው ሁልጊዜ የእግዚብሔርን ቃል መመገብ ምስጋናውንም ምግብ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ትዕዛዙንም ዘወትር በመፈጸም ለአምላኩ ያለውን ፍቅር ሊገልጽ ይገባዋል፡፡ እነዚህ ጾም ሲገባ ምግብን ተክተው የሚገቡ፣ ጾም ሲወጣ ደግሞ ሥጋን ተክተው የሚወጡ አይደሉም፡፡ ሁል ጊዜ ሙሉ የሕይወት ዘመናችንንም ልናደርጋቸው የሚገቡ ናቸው እንጂ፡፡ ስለዚህ ነው ‹‹መቼም የማይጾሙ›› የተባሉት፡፡ ከእነዚህ መከልከል በራሱ ኃጢአት ነውና፡፡ ✅በተመሳሳይ ‹‹መቼም የማይበሉ›› ወይም ‹‹ሁሌም የሚጾሙ›› የሚባሉ ነገሮችም አሉ፡፡ እነዚህም የኃጢአት ሥራዎችና ወደ ኃጢአትም የሚመሩ ነገሮች ናቸው፡፡ ክፉ ማየት፣ ክፉ መስማት፣ ክፉ ማሰብ፣ ክፉ መናገር፣ ክፉ ማድረግና እነዚህም የመሳሰሉት ነገሮች መቼም መበላት ወይም መደረግ የሌለባቸው ስለሆኑ ሁልጊዜ ከእነዚህ መጾም ያስፈልጋል፡፡ በስህተትም ከእነዚህ የቀመሰ ወይም የበላ ዋናውን ጾም ገድፏልና በቶሎ ወደ ንስሐ ሊቀርብ ይገባዋል፡፡ እነዚህ በጾም ወቅት የሚከለከሉ የጾም ወቅት ሲያልፍ ደግሞ የሚፈቀዱ አይደሉም፡፡ በማንኛውም ጊዜ የሚጾሙ ናቸው እንጂ፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለአባታችን አዳምና ለእናታችን ለሔዋን ‹‹መልካምና ክፉውን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብሉ (ዘፍ 2፡18›› ሲል መቼም ቢሆን አትብሉ ማለቱ እንደሆነ ያለ ነው፡፡ ✅በጾም ወቅት በፈቃዳችን ሥጋችንን ስለምናደክም ‹‹መቼም የማይጾሙትን›› የበለጠ ልናደርግ፣ ‹‹መቼም ከማይበሉት›› ደግሞ የበለጠ ልንከለከል እንችል ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ግን የጾም ወቅት ሲያልፍ ወደ ነበርንበት እንመለስ ማለት አይደለም፡፡ በጾም ወቅት የነበሩንን መልካም ነገሮች ከጾሙም በኋላ ይዘናቸው ልንቀጥል ይገባል እንጂ፡፡ በጾም ወቅት የተውናቸውን የሚጎዱን ነገሮች ደግሞ ከጾም በኋላ መልሰን ልንይዛቸው አይገባም፡፡ እንደተውናቸው ልንቀጥል ይገባል እንጂ፡፡ ሰለዚህ በጾም ወቅት ያለንን ተሞክሮ በማጽናት ‹‹ መቼም የማይጾሙትን›› መቼም አለመጾም፣ ‹‹መቼም የማይበሉትን›› ደግሞ መቼም አለመብላት ይገባናል፡፡ ይህንን ስናደርግ ‹‹የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል። የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ እርሱም፦ እነሆኝ ይላል። ኢሳ 58፡8-9›› እንደተባለው ይሆንልናል፡፡ << #የቀሳውስት_ጾም >> #ወይስ_የክርስቲያኖች_ሁሉ_ጾም? ✅የሐዋርያትን ጾም አንዳንዶች ‹‹የቀሳውስት ጾም›› ሲሉት ይሰማል፡፡ ይህም ከአሰያየሙ ጋር የተያያዘ ብዥታን በመጠቀም ላለመጾም የሚፈልጉ ወገኖች ያመጡት አስተሳሰብ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ‹‹የሐዋርያት›› የሚለውን ቃል ብቻ በመውሰድ ጥንት ይህንን ጾም ሐዋርያት ብቻ እንጂ ሕዝቡ አልጾመውም፤ ዛሬ ደግሞ በሐዋርያት እግር የተተኩ ካህናት (ቄሶች) ናቸውና ጾሙም የእነርሱ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ብዙውን ጊዜም ቀሳውስት አበክረው ስለሚጾሙትና በሕዝቡም ዘንድ ይህ ስለሚታወቅም ጭምር ነው ይህ አስተሳሰብ የመጣው፡፡ ✅ቤተክርስቲያን ግን ይህን የአዋጅ ጾም ጳጳስ፣ ቄስ/መነኩሴ፣ ዲያቆን፣ ሰንበት ተማሪ ምዕመን ሳይል በ40 እና በ80 ቀን የተጠመቀና ዕድሜው ከሰባት ዓመት በላይ የሆነው ሁሉ እንዲጾም አውጃለች፡፡ እኛም እነርሱን ተከትለን፣ በእነርሱ ሥርዓት በመመራት፣ በሐዋርያት ላይ ያደረው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ሀብት በእኛም ላይ እንዲያድርብን በየዓመቱ ጾመ ሐዋርያትን ሌሎችንም አጽዋማት አክብረን መጾም እንደሚገባን በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተወስኗል (ፍት.ነገ. 15፡ 586)፡፡ #የሐዋርያት_ጾም_የእኛም_ጾም_ነው ✅ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል›› እንዳለ (ኤፌ 2፡20) በሐዋርያት መሠረትነት ላይ ለታነጽን ለእኛ ለክርስቲያኖች የሐዋርያት ጾም የእኛም ጾም ነው፡፡ የሐዋርያት ጾም ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ስብከተ ወንጌልን ለመፈጸም በየሀገሩ ከመሰማራታቸው በፊት በሁሉም ነገር እግዚአብሔር እንዲረዳቸው የጾሙት ጾም ነው፡፡ እኛም የሐዋርያትን ጾም ስንጾም ሁል ጊዜ በንስሐ ታጥበን እና ነጽተን ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀን ቀሪ ዘመናችንን እግዚአብሔር አምላክ እንዲባርክልንና ሰላምን ፍቅርን እና ጤናን እንዲሰጠን መጾም ይኖርብናል:: ይህ የሐዋርያት ጾም በሐዋርያት እግር የተተኩ የቤተክርስቲያንን አገልጋዮችም አገልግሎታቸውን እንዲባርክላቸውና ምዕመኑን ወደ መልካም ጎዳና እንዲመሩ የሚጸልዩበት ጾም ነው፡፡ ✅በአጠቃላይ በሐዋርያት ጾም የሐዋርያት ክብራቸውና አገልግሎታቸው ይታሰባል፡፡ ይህን ጾም የምንጾመው የሐዋርያትን በረከት ለመላበስ፣ እነርሱ ድል ያደረጉትን ዓለም እንድናሸንፈው አምላካችንን ለመማጸን ነው፡፡ በዚህ ጾም ሐዋርያት ሁሉን ትተው ጌታን መከተላቸው፣ ዓለምን ዞረው ማስተማራቸውና ስለ ቅዱስ ስሙ በጽናትና በጥብዐት መከራ መቀበላቸው ይዘከራል፡፡ ምዕመናን እና ካህናትም የቅዱሳን ሐዋርያትን መንፈሳዊ ተጋድሎ እያሰብን በዘመኑ ሁሉ በፍቅር በተዋበ የመታዘዝ ፍርሃት የየራሳችንን መዳን እንፈጽም ዘንድ (ፊልጵ. 2፡12) ጾምን በመጾም፣ ጸሎትን በመጸለይ ከእግዚአብሔርና በንፁህ ደሙ ከዋጃት ቅድስት ቤተክርስቲያን ጋር ያለንን ፍጹም አንድነት ልናጸና፣ ራሳችንን ከኃጢአት ከበደል አርቀን በመታዘዝ ጸጋ የጾምን በረከት ልንቀበልበት ይገባል፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን ሐዋርያት ጸሎት ይርዳን። አሜን🙏 ✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ ለወዳጅዎ #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞ ╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮ @EOTC2921 @Orthodox2921 ╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯

🌿🌾✟ #ጾመ_ሐዋርያት ✟🌾🌿 ✅የሐዋርያትን አስተምህሮ የምትከተለው ቅድስት ቤተክርስቲያን ሁሉ በሥርዓት እንዲሆን ስለሚገባ ለጾምም ሥርዓትን ሠርታለች፡፡ በዚህ መሠረት ሰባት የአዋጅ አጽዋማትን አውጃለች፡፡ ከእነዚህም መካከልም ጾመ ሐዋርያት (የሐዋርያት ጾም ወይም በተለምዶ ሥሙ- የሰኔ ጾም) (The Fast of the Holy Apostles) አንዱ ነው፡፡ ይህ ጾም ቅዱሳን ሐዋርያት የሥራቸው መጀመሪያ አድርገው ስለጾሙት አስቀድሞ ‹‹የጰንጤቆስጤ ጾም›› ወይም ‹‹የደቀ መዛሙርት ጾም›› ይባል ነበር፡፡ ከኒቅያ ጉባዔ በኋላ እስከ ዛሬ የምንጠቀምበትን ‹‹የሐዋርያት ጾም›› የሚለውን ስያሜ አግኝቷል፡፡ ሐዋርያትም የጾሙት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲጾሙ አስተምሯቸው ስለነበር ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ እንደጻፈው “እኛና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ የምንጦመው ደቀመዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ስለምንድን ነው?” ብለው በጠየቁት ጊዜ “ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወስድበት ወራት ይመጣል በዚያን ጊዜም ይጦማሉ (ማቴ ፱፥፲፭-፲፮)” በማለት እንዲጾሙ አዝዟቸዋል፡፡ ይህንን አብነት በማድረግ ሐዋርያት ወንጌልን የሚሰብኩትን ዲያቆናትና ቀሳውስት የሚሾሙትም በጾምና በጸሎት ነበር። (የሐዋ ፲፫፥፫፤፬፥፳፭) ✅የሐዋርያት ጾም በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተጻፈው መጽሐፈ ድዲስቅሊያ፣ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተጻፈው መጽሐፈ ቀለሜንጦስ፣ እንዲሁም ቅዱስ አትናቴዎስ ለንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በጻፈው መልእክት ላይ ተብራርቶ ይገኛል፡፡ ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስን ሰፍረውና ቆጥረው ባስረከቡን ሐዋርያውያን አበው መሰረትነት የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ሁሉ የመታዘዝ ምልክት የሆነ የሐዋርያትን ጾም እንጾማለን፡፡ #ጾመ_ሐዋርያት__ቅድመ_ጰራቅሊጦስ ✅ቀደምት የቤተክርስቲያን መጻሕፍት እንደሚያስረዱት ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታችን ዕርገት እስከ ኀምሳኛው ቀን (ለ፲ ቀናት) ድረስ በጾምና በጸሎት ቆይተዋል፡፡ እነዚህንም ፲ቀናት የጾሙት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ እያለ ‹‹ እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል። እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው። ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም›› (ዮሐ ፲፬፡፲፮-፲፰) ብሎ የሰጣቸውን ተስፋ እየተጠባበቁ ነበር፡፡ ✅ይህንን ጾም በመጾም ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ራሳቸውን አዘጋጅተውበታል፡፡ ዛሬም ካህናት ክህነት ከመቀበላቸው በፊት፣ አዳዲስ ተጠማቂዎችም ከጥምቀት በፊት እንዲሁም ክርስቲያኖች ሁሉ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ከመቀበላቸው በፊት የሚጾሙት ይህንን አብነት አድርገው ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ለመቀበል ራስን በጾምና በጸሎት ማዘጋጀት ያስፈልጋልና፡፡ #ጾመ_ሐዋርያት__ድኅረ_ጰራቅሊጦስ ✅ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላም ጾምን የአገልግሎታቸው መጀመሪያ አድርገውታል፡፡ ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ከተቀበሉ በኋላ የጾሙት ስለሁለት ዓላማ ነው፡፡ አንደኛው ስለተሰጣቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ አምላካቸውን ለማመስገን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በዓለሙ ሁሉ ዞረው ለሚሰብኩት ወንጌል ራሳቸውን ለማዘጋጀት ነው፡፡ ስለዚህም ነው መንፈሳዊ አገልግሎትና ስብከት የዚህ ጾም አንኳር ነጥቦች የሆኑት፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ መጾማቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድርገው ነው፡፡ እርሱ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ጌትነቱን ለመመስከር ከወረደ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዶ በዚያ 40 መዓልትና 40 ሌሊት ጾሟልና እነርሱ ደግሞ ኃይል ይሆናቸው ዘንድ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን በበዓለ ጰራቅሊጦስ ዕለት ከተቀበሉ በኋላ ጾምን የሥራቸው ሁሉ መጀመሪያ አድርገዋል፡፡ ✅አንዳንድ መዛግብት በመጀመሪያዎቹ ዘመናት የሐዋርያት ጾም የሚጀምረው ከጰራቅሊጦስ አንድ ሳምንት በኋላ ነበር ይላሉ፡፡ ከዚያም በ258ዓ.ም ከበዓለ ጰራቅሊጦስ እስከ ሐዋርያት በዓል (The Feast of the Holy Apostles) (ሐምሌ 5) ድረስ እንዲሆን አባቶች ደነገጉ በማለት ያስረዳሉ፡፡ ይህም የተረደገው የቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ በኔሮን ቄሳር በሮም አደባባይ ሰማዕትነት የተቀበሉበትን ዕለት አብሮ ለማሰብ እንዲረዳ ነው በማለት ያጠናክሩታል፡፡ መጽሐፈ ድዲስቅሊያ ደግሞ ሐዋርያት 40 ቀን እንደጾሙ ከዚያም በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ እግራቸውን አጥቧቸው ለስብከተ ወንጌል እንደተሰማሩ ያስረዳል፡፡ ‹‹እናንተ ስትጦሙ›› እና ‹‹አንተ ግን ስትጦም›› መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ጾም የፈቃድ ብቻ ሳይሆን ትዕዛዝ መሆኑንም ለሐዋርያቱና ለሚከተለው ሕዝብ ሲያስተምር ‹‹ስትጦሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጦም፥ በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል። ማቴ 6፡16-18›› ብሏል፡፡ ✅በዚህም ትምህርቱ እርሱ የሚወደው ጾም ምን አይነት እንደሆነና እንዲሁም የማኅበርና የግል ጾም መኖሩን ‹‹እናንተ ስትጦሙ›› እና ‹‹አንተ ግን ስትጦም›› ብሎ ለይቶ አስተምሯል፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድም የተወደደ ጾም እንዴት አይነቱ እንደሆነ ነቢያት አስቀድመው ‹‹የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘምድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን?›› ብለው ጽፈዋል፡፡ ኢሳ 58፡6-8

photo content

#የዮሐንስ_ወንጌል_ምዕራፍ_14 1፤ልባችኹ፡አይታወክ፤በእግዚአብሔር፡እመኑ፥በእኔም፡ደግሞ፡እመኑ። 2፤በአባቴ፡ቤት፡ብዙ፡መኖሪያ፡አለ፤እንዲህስ፡ባይኾን፡ባልዃችኹ፡ነበር፤ስፍራ፡አዘጋጅላችኹ፡ዘንድ፡ እኼዳለኹና፤ 3፤ኼጄም፡ስፍራ፡ባዘጋጅላችኹ፥እኔ፡ባለኹበት፡እናንተ፡ደግሞ፡እንድትኾኑ፡ኹለተኛ፡እመጣለኹ፡ወደ፡እኔም፡እወስዳችዃለኹ። 4፤ወደምኼድበትም፡ታውቃላችኹ፥ መንገዱንም፡ታውቃላችኹ። 5፤ቶማስም፦ጌታ፡ሆይ፥ወደምትኼድበት፡አናውቅም፤እንዴትስ፡መንገዱን፡እናውቃለን፧አለው። 6፤ኢየሱስም፦እኔ፡መንገድና፡እውነት፡ሕይወትም፡ነኝ፤በእኔ፡በቀር፡ወደ፡አብ፡የሚመጣ፡የለም። 7፤እኔንስ፡ብታውቁኝ፡አባቴን፡ደግሞ፡ባወቃችኹ፡ነበር።ካኹንም፡ዠምራችኹ፡ታውቁታላችኹ፡አይታችኹትማል፡አለው። 8፤ፊልጶስ፦ጌታ፡ሆይ፥አብን፡አሳየንና፡ይበቃናል፡አለው። 9፤ኢየሱስም፡አለው፦አንተ፡ፊልጶስ፥ይህን፡ያኽል፡ዘመን፡ከእናንተ፡ጋራ፡ስኖር፡አታውቀኝምን፧እኔን፡ያየ፡አብን፡አይቷል፤ እንዴትስ፡አንተ፦አብን፡አሳየን፡ትላለኽ፧ 10፤እኔ፡በአብ፡እንዳለኹ፡አብም፡በእኔ፡እንዳለ፡አታምንምን፧እኔ፡የምነግራችኹን፡ቃል፡ከራሴ፡አልናገረውም፤ነገር፡ግን፥በእኔ፡የሚኖረው፡አብ፡ርሱ፡ሥራውን፡ይሠራል። 11፤እኔ፡በአብ፡እንዳለኹ፡አብም፡በእኔ፡እንዳለ፡እመኑኝ፤ባይኾንስ፡ስለ፡ራሱ፡ስለ፡ሥራው፡እመኑኝ። 12፤እውነት፡እውነት፡እላችዃለኹ፥በእኔ፡የሚያምን፡እኔ፡የማደርገውን፡ሥራ፡ርሱ፡ደግሞ፡ያደርጋል፤ከዚህም፡የሚበልጥ፡ያደርጋል፥ 13፤እኔ፡ወደ፡አብ፡እኼዳለኹና፤አብም፡ስለ፡ወልድ፡እንዲከበር፡በስሜ፡የምትለምኑትን፡ዅሉ፡አደርገዋለኹ። 14፤ማናቸውንም፡ነገር፡በስሜ፡ብትለምኑ፡እኔ፡አደርገዋለኹ። 15-16፤ብትወዱኝ፡ትእዛዜን፡ጠብቁ። እኔም፡አብን፡እለምናለኹ፡ለዘለዓለምም፡ከእናንተ፡ጋራ፡እንዲኖር፡ሌላ፡አጽናኝ፡ይሰጣችዃል፤ 17፤ርሱም፡ዓለም፡የማያየውና፡የማያውቀው፡ስለ፡ኾነ፡ሊቀበለው፡የማይቻለው፡የእውነት፡መንፈስ፡ነው፤ነገር፡ግን፥ከእናንተ፡ዘንድ፡ስለሚኖር፡በውስጣችኹም፡ስለሚኾን፡እናንተ፡ታውቃላችኹ። 18፤ወላጆች፡እንደ፡ሌላቸው፡ልጆች፡አልተዋችኹም፤ወደ፡እናንተ፡እመጣለኹ። 19፤ገና፡ጥቂት፡ዘመን፡አለ፡ከዚህም፡በዃላ፡ዓለም፡አያየኝም፤እናንተ፡ግን፡ታዩኛላችኹ፤እኔ፡ሕያው፡ነኝና፡እናንተ፡ደግሞ፡ሕያዋን፡ትኾናላችኹ። 20፤እኔ፡በአባቴ፡እንዳለኹ፡እናንተም፡በእኔ፡እንዳላችኹ፡እኔም፡በእናንተ፡እንዳለኹ፡በዚያን፡ቀን፡ታውቃላችኹ። 21፤ትእዛዜ፡በርሱ፡ዘንድ፡ያለችው፡የሚጠብቃትም፡የሚወደኝ፡ርሱ፡ነው፤የሚወደኝንም፡አባቴ፡ይወደዋል፡ እኔም፡እወደዋለኹ፡ራሴንም፡እገልጥለታለኹ። 22፤የአስቆሮቱ፡ያይደለ፡ይሁዳ፦ጌታ፡ሆይ፥ለዓለም፡ሳይኾን፡ራስኽን፡ለእኛ፡ልትገልጥ፡ያለኽ፡እንዴት፡ነው፧አለው። 23፤ኢየሱስም፡መለሰ፥አለውም፦ የሚወደኝ፡ቢኖር፡ቃሌን፡ይጠብቃል፤ አባቴም፡ይወደዋል፡ወደ፡ርሱም፡ እንመጣለን፡በርሱም፡ዘንድ፡መኖሪያ፡እናደርጋለን። 24፤የማይወደኝ፡ቃሌን፡አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም፡ቃል፡የላከኝ፡የአብ፡ነው፡እንጂ፡የእኔ፡አይደለም። 25፤ከእናንተ፡ዘንድ፡ስኖር፡ይህን፡ነግሬያችዃለኹ፤ 26፤አብ፡በስሜ፡የሚልከው፡ግን፡መንፈስ፡ቅዱስ፡የኾነው፡አጽናኝ፡ርሱ፡ዅሉን፡ያስተምራችዃል፥እኔም፡የነገርዃችኹን፡ ዅሉ፡ያሳስባችዃል። 27፤ሰላምን፡እተውላችዃለኹ፥ሰላሜን፡እሰጣችዃለኹ፤እኔ፡የምሰጣችኹ፡ዓለም፡እንደሚሰጥ፡አይደለም።ልባችኹ፡አይታወክ፡አይፍራም። 28፤እኔ፡እኼዳለኹ፡ወደ፡እናንተም፡እመጣለኹ፡እንዳልዃችኹ፡ሰማችኹ። የምትወዱኝስ፡ብትኾኑ፡ከእኔ፡አብ፡ይበልጣልና፥ወደ፡አብ፡በመኼዴ፡ደስ፡ባላችኹ፡ነበር። 29፤ከኾነም፡በዃላ፡ታምኑ፡ዘንድ፡አኹን፡አስቀድሞ፡ሳይኾን፡ነግሬያችዃለኹ። 30፤ከእንግዲህ፡ወዲህ፡ከእናንተ፡ጋራ፡ብዙ፡አልናገርም፥የዚህ፡ዓለም፡ገዢ፡ይመጣልና፤በእኔ፡ላይም፡ አንዳች፡የለውም፤ 31፤ነገር፡ግን፥አብን፡እንድወድ፡ዓለም፡ሊያውቅ፥አብም፡እንዳዘዘኝ፥እንዲሁ፡አደርጋለኹ።ተነሡ፤ከዚህ፡እንኺድ።

•✞ #በዓለ_ጰራቅሊጦስ ✞• 🌻🌾🌻🌾🌻🌾🌻🌾🌻🌾 ☞✞ በሐዋርያት ሥራ ምዕ ፩፥፲፬ ላይ እንደተጻፈ የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በአርባኛው ቀን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ቢታንያ በማውጣት “እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” ብሎ ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ ዕውቀትን ገንዘብ እስኪያደርጉ ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲቆዩ አዝዞ በምስጋና ዐረገ፡፡ ☞✞ ስለምን እንዲኽ አዘዛቸው ቢሉ መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው በፊት ፈሪዎች ነበሩና ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ባልተቀበለ ሰውነታቸው አይሁድ መከራ አጽንተውባቸው ሃይማኖታቸውን እንዳይክዱ፡፡ ☞✞ ዳግመኛም ኅሊናቸውን በተመስጦ ለማቆየት፡፡ ሌላው መንፈስ ቅዱስ የሚወርደው በጽርሐ ጽዮን ነውና ከአንዱ ወደ አንዱ ሲዘዋወሩ እንዳይቀርባቸው ነው፡፡ ☞✞ 12ቱ ሐዋርያት፣ 72ቱ አርድእት፣ 36ቱ ቅዱሳት አንስት በማርቆስ እናት በማርያም ቤት ኹነው በይሁዳ ምትክ ማትያስን አስገብተው፤ ሰማይ ምድር የማይወስኑትን አምላክ በማሕፀኗ የተሸከመች የድንግልና ጡቶቿን ያጠባች ቅድስት ድንግል የሌለችበት ጉባኤ ከጸጋ መንፈስ ቅዱስ የተለየ ነውና የመስቀል ሥር ስጦታቸውን “የኢየሱስ እናት ማርያምን” ይዘው በአንድ ልብ ኾነው በጸሎት መትጋት እንደዠመሩ ሉቃስ ጽፏል (የሐዋ ፩፥፲፬)፡፡ ☞✞ ከዚያም ልክ በሦስት ሰዓት “መጽአ ግብተ እምሰማይ ድምፅ ከመ ድምፀ ነፋሰ ዐውሎ” ይላል ከወደ ሰማይ እንደ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ነጒዶ ተሰምቶ ያሉበትንም ቤት መላው ይኽም የሚያስተምረን ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ የኾነች እመቤታችን ያለችበትና የምትጠራበት ጉባኤ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጸጋ እንዳለበት ያሳየናል፤ ይኽም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አስቀድሞ በኤልሳቤጥ ሲታወቅ ገና እመቤታችን ደርሳ ሰላምታን ስትሰጣት ቅዱስ ወንጌል “በኤልሳቤጥ ላይ መንፈስ ቅዱስ መላባት” በማለት እንደመሰከረ እናያለን (ሉቃ ፩፥፵፩)፡፡ ☞✞ ጌታ በዐረገ በ10ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ ስለምን ወረደ ቢሉ፡- ➊ኛ10ሩን ሕዋሳት 10ሩን ቃላት በእውነት ብንጠብቅ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጠን ለማጠየቅ፡፡ ➋ኛ ከ10ኛው መዐርግ የገባን እኛ ነበርንና ከጥንተ ቦታችን ክብራችን እንደተመለስን ለማጠየቅ ነው፡፡ ☞✞ ይኸውም ለሐዋርያት በአምሳለ ነፋስ የተገለጸው መንፈስ ቅዱስ ነው ለምን በነፋስ አምሳል ተገለጸ ቢሉ መተርጉማነ መጻሕፍተ ሐዲሳት ያመሰጥሩታል፦ ✔ነፋስ ረቂቅ ነው መንፈስ ቅዱስም ረቂቅ ነውና፤ ✔ነፋስ ኀያል ነው መንፈስ ቅዱስም ኀያል ነውና፤ ✔ነፋስ ፍሬውን ከገለባው ይለያል መንፈስ ቅዱስም ጻድቃንን ከኃጥኣን ይለያልና፤ ✔ነፋስ በምላት ሳለ አይታወቅም ባሕር ሲገሥፅ ዛፍ ሲያናውፅ ነው እንጂ መንፈስ ቅዱስም በምላት ሳለ አይታወቅም ቋንቋ ሲያናግር ምስጢር ሲያስተረጒም ነውና፤ ✔ነፋስ መንቅሂ ነው መንፈስ ቅዱስም መንቅሂ ነውና፤ ✔ነፋስ መዐዛ ያመጣል መንፈስ ቅዱስም መዐዛ ጸጋን ያመጣልና ነው፡፡ ከዚያም “ወአስተርአይዎሙ ልሳናተ እሳት ክፉላት ከመ እሳት ዘይትከፈል” ይላል እንደ እሳትም የተከፋፈለ ልሳን ኹኖ በያንዳንዳቸው ላይ ተቀምጦባቸዋል፤ ☞✞ ይኸውም ልሳን ላንቃ ማለት ቋንቋን ማውጫ መነጋገሪያ እንደኾነ ኹሉ ሰዎች የሚግባቡበት ትክክለኛ መግባቢያ የኾነ፤ ሊጻፍ ሊሰማ ሊያግባባ የሚችል የቋንቋ ሀብትን መንፈስ ቅዱስ በእሳት ላንቃ አምሳል አሳድሮባቸዋል፡፡ ☞✞ መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል መውረዱ ምሳሌነት ያለው ነው፤ ይኸውም እሳት ምሉእ ነው መንፈስ ቅዱስም ምሉእ ነውና፤ ✔እሳት በምላቱ ሳለ ቡላድ ካልመቱ አይገለጽም መንፈስ ቅዱስም ቋንቋ ሲያናግር ምስጢር ሲያስተረጉም እንጂ ዐድሮ ሳለ አይታወቅምና፤ ✔እሳት ከቡላዱ ሲወጣ በመጠን ነው ኋላ በዕንጨት እያቀጣጠሉ ያሰፉታል መንፈስ ቅዱስም በ፵ በ፹ ቀን በጥምቀት ሲሰጥ በመጠን ነው ኋላ በሥራ ያሰፉታልና፤ ✔እሳት ጣዕምን መዐዛን ያመጣል መንፈስ ቅዱስም ጣዕመ ጸጋን መዐዛ ጸጋን ያመጣልና፤ ✔እሳት በመጠኑ የሞቁት እንደኾነ ሕይወት ይኾናል ከመጠን ዐልፎ ቢሞቁት ያቃጥላል መንፈስ ቅዱስም በሚገባ በተጻፈው የመረመሩት እንደኾነ ሕይወት ይኾናል በማይገባ ከተጻፈው ወጥተው የመረመሩት እንደኾነ ይቀሥፋልና፤ ✔እሳት ያቀረቡለትን ያቃጥላል መንፈስ ቅዱስም የጸለዩትን ጸሎት ያቀረቡለትን መሥዋዕት ይቀበላልና፤ ✔እሳት ውሃ ገደል ካልከለከለው ኹሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋል መንፈስ ቅዱስም ቸርነቱ ካልከለከለው ኹሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋልና፤ ✔እሳት ዱር ይገልጻል መንፈስ ቅዱስም ምስጢርን ይገልጻልና፤ ✔እሳት የበላው መሬት ለእኽል ለተክል ይመቻል መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ሰውነት ለገድል ለትሩፋት ይመቻልና ርሱ ባወቀ በእሳትና በነፋስ አምሳል ወርዷል፡፡ ☞✞ ከዚያም በኹሉም መንፈስ ቅዱስ መልቶባቸው ዓለም በሚሰማው ኹሉም በሚረዳው በ፸፪ቱ ቋንቋ ተናግረዋል፤ በሐዋርያት 72 ቋንቋ አልተከፈለባቸውም፤ የቀሩት ግን ከ15 በታች የወረደ የለም እንጂ 20ም 30ም 40ም 50ም 60ም የተገለጠላቸው አሉ፡፡ ☞✞ እስራኤል ከምርኮ መልስ በኋላ በወደዱት ሀገር በሕጋቸው ይኖራሉ፤ ለበዓለ ፋሲካ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣሉ፤ በዓለ ፋሲካን አክብረው ከዚያ አያይዘው ሰባት ሱባዔ ቈጥረው በ50ኛዪቱ ዕለት በዓለ ሰዊትን ያከብሩ ነበርና በዓለ ፶ን ለማክበር ከየዓለማቱ የመጡት በእጅጉ ተገርመው:- “እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን?፤ የጳርቴና የሜድ የኢላሜጤም ሰዎች በኹለት ወንዝም መኻከል በይሁዳም በቀጰዶቅያም በጳንጦስም በእስያም በፍርግያም በጵንፍልያም በግብጽም በቀሬናም በኩል ባሉት በሊብያ ወረዳዎች የምንኖር በሮሜም የምንቀመጥ አይሁድም ወደ ይሁዲነትም የገባን የቀርጤስና የዐረብ ሰዎች የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን” በማለት በእጅጉ ተደነቁ፡፡ ☞✞ ያን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ተነሥቶ ነቢዩ ኢዩኤል በምዕ 2፡28-29 ላይ “ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፥ ጐበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ደግሞም በዚያ ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ መንፈሴን አፈስሳለሁ” ብሎ የተናገረው መፈጸሙን ጠቅሶ ሰፋ አድርጎ ነገረ ክርስቶስን ቢያስተምራቸው ቃሉን ተቀብለው ሦስት ሺሕ ሰዎች አምነው ተጠምቀዋል፡፡ ☞✞ ሊቃውንትም ይኽነን በመያዝ በተለይ እነቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ዕለቷን “የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን” ብለዋታል፡፡ ☞✞ እመቤታችን በመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በማርቆስ እናት ቤት በሰገነት ላይ በመስቀል ሥር በአደራ የተቀበለቻቸው በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት የሚያምኑ የአደራ ልጆቿን ሐዋርያትን ይዛ እንደተገኘች ዛሬም በልጇ ደም በተመሠረተችው ሐዋርያዊት በኾነችው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበን የልጇን የባሕርይ አምላክነት የርሷን ወላዲተ አምላክነት በመመስከር እንኖራለን፡፡ ☞✞ “ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማሕየዊ ዘሠረጸ እምአብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ ዘነበበ በነቢያት” (ጌታ ማሕየዊ በሚኾን ከአብ በሠረጸ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፤ በነቢያት ዐድሮ የተናገረ ለርሱ ከአብ ከወልድ ጋር እንስገድለት እናመስግነው) አሜን፡፡ [ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ] Channel @EOTC2921 Group @Orthodox2921 •✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ✞•

❖ ደራሲው በመጨረሻ፡- “ኢያሱ መድኀኒትነት ያለው የስምኽን አክሊል ተቀዳጅቶ የጠላቶችን ሀገሮች ወረሰ (ገንዘብ አደረገ)” በማለት ኢያሱን አነሣ ስለምን ቢሉ? ኢያሱ ማለት የስሙ ፍቺ መድኀኒት ማለት ነውና ይኸውም ኢያሱ መድኀኒት መባሉ በዐጭር ቃጥቆ ዘገር ነጥቆ ጦር ነቅንቆ አማሌቃውያንን አጥፍቶ እስራኤልን ከሥጋዊ ጠላት አድኖ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን መድኀኒት መባሉ ሥጋውን ቈርሶ ደሙን አፍስሶ፤ ጠላት ዲያብሎስን ሰራዊቱ አጋንንትን ድል ነሥቶ ምእመናን በኀጢአታቸው ከመጣባቸው ፍዳ አድኖ ነውና የስሙን ነገር ካነሣ ብሎ ለማነጻጸር ያመጣዋል፡፡ ❖ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም የኢያሱን ለኢየሱስ ምሳሌነት እንዲኽ አመሰጥሮታል፡- “በከመ ኢያሱ ዜናዌ ተሰምየ ኢየሱስሀ እምቅድመ ኢየሱስ ናዝራዊ ኢየሱስ ብሂል መድኅን ብሂል …” (የነዌ ልጅ ኢያሱ ከናዝሬቱ ኢየሱስ በፊት መድኅን እንደተባለ፤ ኢየሱስ ማለት መድኀኒት ነውና፤ ኢያሱ ወገኖቹን ከጠላት ጦር እንዳዳናቸው ጌታ ኢየሱስም ወገኖችን ከኀጢአታቸው አዳናቸው (ዘዳ ፴፬፥፱)፤ ኢያሱ ከሙሴ በረከትን እንደተቀበለ ጌታ ኢየሱስም ከአባቱ ዘንድ ክብሩ ተገለጠ (ማቴ ፫፥፲፯)፤ ኢያሱ ከወገኖቹ ጋር የብስ የኾነ የዮርዳኖስን ወንዝ እንደተሻገረ (ኢያ ፫፥፲፯) ጌታ ኢየሱስም የዮርዳኖስን ውሃ በጥምቀቱ ቀደሳት (ማር ፩፥፱-፲፩)፤ ኢያሱ የእስራኤልን የሰውነታቸውን ሸለፈት በስለታም ምላጭ እንደገዘረ (ኢያ ፭፥፯) ጌታ ኢየሱስም በወንጌል ምላጭ የአሕዛብን የበደላቸውን ሸለፈት ገዘረ፤ ኢያሱ በገባዖን ፀሓይን እንዳቆመ ኹለተኛውንም ቀን አንድ ቀን እንዳደረገ (ኢያ ፲፥፲፪-፲፫) ጌታ ኢየሱስም ፀሓይን በቀራንዮ አጨለመ አንዲቱንም ቀን ኹለት ዕለት አደረጋት (ማቴ ፳፯፥፵፭)፤ ኢያሱ ምድረ ርስትን ለወገኖቹ በየነገዳቸው እንዳደላቸው ጌታ ኢየሱስም የገነትን ምድር ለነቢያቱ በየወገናቸው አደላቸው (ኢያ ፲፩፥፳፫፤ ኤፌ ፩፥፲፩)) እንዲል፡፡ ✍ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (መልክአ ኢየሱስ ንባቡና ትርጓሜው የተወሰደ) ✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ ለወዳጅዎ #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞ ╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮ @EOTC2921 @Orthodox2921 ╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯

📖✞ #መልክአ_ኢየሱስ_ትርጓሜ ✞📖 የመልክአ ኢየሱስ ለዝክረ ስምከ ለጌታ ስም የቀረበ ትርጓሜ ✞“ሰላም ለዝክረ ስምከ ስመ መሐላ ዘኢይሔሱ ዘአንበረ ቅድመ እግዚአብሔር በአትሮንሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዳዊት ባሕርየ ከርሡ አክሊለ ስምከ እንዘ ይትቄጸል በርእሱ አህጉረ ጸር ወረሰ ኢያሱ” (የማይከዳ የቃል ኪዳን ስም ለኾነ የስም አጠራርኽ ሰላምታ ይገባል፤ እግዚአብሔር አስቀድሞ በዙፋኑ ያስቀመጠኽ የዳዊት የኾዱ ባሕርይ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ኢያሱ መድኀኒትነት ያለው የስምኽን አክሊል ተቀዳጅቶ የጠላቶችን ሀገሮች ወረሰ (ገንዘብ አደረገ)) ❖ (ትርጓሜ)፡- ሊቁ በዚኽ የመልክአ ኢየሱስ ድንቅ ድርሰቱ ላይ “ነገርን ከሥሩ ውሃን ከጥሩ” እንዲሉ “ኢየሱስ ክርስቶስ” ከሚለው ከስም አጠራሩ በመነሣት ምስጋናውን ይዠምራል፤ “የማይከዳ የቃል ኪዳን ስም” ስለምን አለው? ቢሉ አዳምና ሔዋን ከገነት ከተባረሩ በኋላ እንኳ አዳም የቤተ ፈት ልማድ አላገኘውም፤ ቤተ ፈት በዚኽ ጊዜ እበላ እጠጣ፤ በዚኽ ጊዜ ተድላ ደስታ አድርግ ነበር ብሎ ያዝናል፤ አዳም ግን ፈጣሪዬ አትብላ ያለኝን ዕፀ በለስን በልቼ በደልኍ ብሎ በኀጢአቱ ፲፬ ሱባዔ ፺፰ ዓመት መሪር ልቅሶን አለቀሰ፡- “ወአልቦቱ ካልዕ ኅሊና ላዕለ ኀጢአቱ ዘእንበለ ብካይ ወላህ” (ኀጢአቱን እያሰበ ከማልቀስ ውጪ ሌላ ዐሳብ አልነበረውም) እንዳሉ አሞንዮስና አውሳብዮስ በመቅድመ ወንጌል ❖ ያን ጊዜ የምሕረት ባለቤት አዳምንና ሔዋንን እንደሚቤዣቸው እንደሚያድናቸው የማይታበል ጽኑ ቃል ኪዳንን ገብቶላቸዋል፡- ☞ “ወእምድኅረ ኀሙስ መዋዕል ወመንፈቀ መዓልት እምሕረከ ወእሣሃለከ በብዝኀ ሣህልየ ወምሕረትየ፤ ወእወርድ ውስተ ቤትከ ወአኀድር ውስተ ከርሥከ ወበእንቲኣከ ኦ አዳም እትወለድ ከመ ሕፃን ወበአንቲኣከ ኦ አዳም አሐውር ውስተ ምሥያጥ፤ ወበእንቲኣከ እጸውም ፵ መዓልተ ወ፵ ሌሊተ፤ ወበእንቲኣከ እትዌከፍ ወእትዔገሥ ሕማማተ ወበእንቲኣከ እሰቀል ዲበ ዕፀ መስቀል” (በፍጹም ይቅርታዬ ከዐምስት ቀን ተኩል በኋላ በፍጹም ምሕረቴ ይቅር እልኻለኍ፤ ወደ ቤትኽም ወርጄ በባሕርይኽ ዐድራለኍ፤ አዳም ሆይ ስለ አንተ እንደ ሕፃን እወለዳለኍ፤ ስለ አንተ ወደ ገበያ እኼዳለኍ፤ ስለ አንተም አርባ ቀን አርባ ሌሊት እጾማለኍ፤ ስለ አንተ መከራ መስቀልን በትዕግሥት አቀበላለኍ፤ ስለ አንተም በዕንጨት መስቀል ላይ እሰቀላለኍ) እንዲል (መጽሐፈ ቀሌምንጦስ፣ ፫ኛ መቃ ፬፥፳፫-፳፬፤ ዕዝ ሱቱ ፬፥፩፤ ሲራ ፳፬፥፮፤ ገላ ፬፥፬)፡፡ ❖ በመኾኑም “እትቤዘወከ” ብሎ እንደሚቤዠው እንደሚያድነው ለአዳም የነገረው ሊደርስ ሊፈጸም ዘመኑ ሲፈጸም ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን ተልኮ “ወናሁ ትፀንሲ ወትወልዲ ወልደ ወትሰምዪዮ ስሞ ኢየሱስ” (እነሆም ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ) በማለት የስሙን መድኀኒትነት ነግሯታልና ደራሲው “የማይከዳ የቃል ኪዳን ስም ለኾነ የስም አጠራርኽ ሰላምታ ይገባል” ይለዋል (ሉቃ ፩፥፴፩)፡፡ ❖ መጋቤ ሐዲስ ቅዱስ ገብርኤል ለአረጋዊዉ ለዮሴፍም ኢየሱስ የሚለውን ንባቡንም ትርጓሜውን ሲገልጽለት፡- “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ ከርሷ የተፀነሰው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነውና ዕጮኛኽን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ ልጅም ትወልዳለች፤ ርሱ ሕዝቡን ከኀጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለኽ” በማለት ወገኖቹን በኀጢአታቸው ከመጣባቸው ፍዳ የሚያድናቸውን መድኅነ ዓለም ኢየሱስን ቅድስት ድንግል ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደፀነሰችው ነግሮታልና (ማቴ ፩፥፲፰-፳፫)፡፡ ❖ ከሊቃውንት አንዱ ሶርያዊዉ ቅዱስ ኤፍሬምም ስለዚኽ ነገር በጥልቀት በትርጓሜ ወንጌሉ ላይ ሲገልጸው፡- “The words in the ‘sixth month’ are reckoned in Elizabeth’s pregnancy…” (መልአኩ “በስድስተኛው ወር” የሚለው ኤልሳቤጥ ከፀነሰችበት ወራት ዠምሮ በመቊጠር ነው፤ መልአኩ ወደ አንዲት ድንግል ተላከ ወደ ርሷ ገብቶም “እነሆ ድንግልናሽ ሳይነዋወጥ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” አላት፤ ይኸውም በሥጋ ተገልጦ ሊመጣ ስላለው ስለ አካላዊ ቃል ሲናገር ነው፤ ሲነግራትም “ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” አላት እንጂ “ኢየሱስ የተባለው” አላላትም፤ ይኸውም ወልደ እግዚአብሔር በተዋሐደው ሥጋ የሰው ልጆች የሚድኑበት ስም መኾኑን የሚያመለክት ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ማለት በዕብራይስጥ “መድኅን” ማለት ነውና፤ መልአኩ “ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” ሲላት መድኅን ትዪዋለሽ ማለቱ ነው፤ ለምን? ቢሉ ሕዝቡን ኹሉ ከኀጢአታቸው ያድናቸዋልና) በማለት ተርጒሞታል፡፡ ❖ ክርስቶስ “Χριστός” የጽርዕ ቃል ነው፤ በዕብራይስጥ “መሲሕ” ሲባል፤ በግእዝ ቋንቋ “ቅቡዕ” ማለት ነው፤ ይኸውም ብቻ የትስብእት፤ ብቻ የመለኮት ስም አይደለም፤ ከኹለት አካል አንድ አካል፤ ከኹለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ቢኾን የወጣለት የተዋሕዶ ስም ነው፤ “ቅቡዕ” መባሉም ሥጋ ከአካላዊ ቃል ጋር ቢዋሐድ የባሕርይ አምላክ መኾኑን ያመለክታል፤ ይኸውም የአካል የባሕርይ ተዋሕዶ ነውና ትስብእት ከባሕርይ ልጅ ከባሕርይ አምላክ የባሕርይ ተዋሕዶ ቢዋሐድ ሥጋ የባሕርይ አምላክነትን የባሕርይ ልጅነትን አገኘ፤ በባሕርይ አምላክነት፣ በባሕርይ ልጅነት ከበረ፤ ውሱን ሲኾን ምሉዕ፤ ግዙፍ ሲኾን ረቂቅ፤ መዋቲ ሲኾን ሕያው ኾነ፤ ኀየሰ፣ ወረሰ፣ ነግሠ፣ ዐብየ፣ ከብረ፣ ተለዐለ ተባለ፡፡ ኹሉ የሚቻለው ከሌላ አካል ክብር ከማይሻ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ዕሩይ ከሚኾን ከቃል ጋራ የባሕርይ ተዋሕዶን ቢዋሐድ ሥጋ በተዋሕዶተ ቃል ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተካከለ የባሕርይ አምላክ ኾኗልና፡፡ ❖ አንድም “ስመ መሐላ” ብሎ የያዘውስ ለዳዊት የገባለትን ቃል ኪዳን ነው ብሎ፤ ለዳዊት አስቀድሞ ከባሕርዩ የተከፈለ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን በዙፋኑ እንደሚያስቀምጥለት፡- “መሐለ እግዚአብሔር ለዳዊት በጽድቅ ወኢይኔስሕ እስመ እምፍሬ ከርሥከ አነብር ዲበ መንበርከ” (እግዚአብሔር ለዳዊት እንዲኽ ሲል በእውነት ማለ አይጸጸትምም፤ ከኾድኽ ፍሬ በዙፋንኽ ላይ አስቀምጣለኹና) ብሎታልና፤ ደራሲውም ከዚኽ አያይዞ “እግዚአብሔር አስቀድሞ በዙፋኑ ያስቀመጠኽ የዳዊት የኾዱ ባሕርይ ኢየሱስ ክርስቶስ” በማለት ተናገረ (መዝ ፻፴፩፥፲፩)፡፡ ❖ ይኽማ የተነገረው ለሰሎሞን አይደለም ቢሉ? ለጊዜው ለሰሎሞን ቢኾን ፍጻሜው ለጌታ ነውና፤ ለጊዜው ለሰሎሞን ፍጻሜው ለጌታ መኾኑ እንደምን ነው? ቢሉ ሰሎሞን በጸጋ የገዛቸውን ኹሉ ጌታ በባሕርይ ገዝቷቸዋልና፡፡ አንድም ሰሎሞን በሥጋ የገዛቸውን ኹሉ ጌታ በነፍስ ገዝቷዋልና፡፡ አንድም ሰሎሞን በግድ የገዛቸውን ጌታ በፈቃድ ገዝቷቸዋልና፡፡ አንድም የጌታ መንግሥት መታወቁ ነቢዩ “መንበርከ እግዚኦ ለዓለመ ዓለም” ብሎ በተናገረለት ነውና (መዝ ፵፬፥፮)፡፡ አንድም “ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምኢ እዝነኪ” ብሎ የትንቢት ዙፋን አድርጎ በተናገረላት በምእመን ላይ ነውና (መዝ ፵፬፥፲)፡፡ አንድም “ዲበ መንበረ ዳዊት ትጸንዕ መንግሥቱ ለክርስቶስ” እንዲል ከዳዊት የነሣው ሥጋ እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ የሚያድን የሚገድል ኾኗልና ፡፡

✅✞በዕለተ ዐርብ በጌታችን ስቅለት ዕለት ስለተደረገው ስለዚኽ ታላቅ ተአምር ሊቃውንት እንዲኽ ይገልጹታል፡- ☞ “ጐየ ፀሓይ ወጸልመ ወርኅ ወከዋክብትኒ ተኀብኡ ከመ ኢያብርሁ ለምእመናን በጊዜ ስቅለቱ ቅዱስ እንዘ ፍጹም በገሃሁ ወርኅ ኢያብርሀ…” (ፀሓይ ብርሃኑን ነሣ ጨረቃም ጨለመ፤ ከዋክብትም በከበረ ስቅለቱ ጊዜ ለምእመናን እንዳያበሩ ብርሃናቸውን ነሡ፤ ጨረቃም በምልአቱ ሳለ አላበራም፤ ፀሓይ ብርሃኑን በነሣ ጊዜ ፍጡራን ኹሉ በጨለማ ተያዙ፤ የፈጠራቸው ፈጣሪያቸው እንደ ሌባ እንደ ወንበዴ በዕንጨት ላይ ተሰቅሎ እንዳያዩ ቀኑ ጨለመ፤ ባለሟሉ መልአክም ከሓድያንን ያጠፋቸው ዘንድ ሰይፉን በእጁ መዝዞ ይዞ ከመላእክት መኻከል ወጣ፤ የክርስቶስም ቸርነት በከለከለችው ጊዜ ያ መልአክ የቤተ መቅደሱን መጋረጃ በሰይፉ መታው ቀደደውም፤ ከላይ እስከ ታችም ወደ ኹለት አደረገው (ማቴ ፳፯፥፶፩፤ ማር ፲፭፥፴፰፤ ሉቃ ፳፫፥፵፭)። ✅✞መላእክትም ኹሉ በሰማይ ኹነው ርሱን አይተው በአንድነት ሲቈጡ የአብ ምሕረቱ፣ የወልድ ትዕግሥቱ፣ የመንፈስ ቅዱስ ቸርነቱ ከለከለቻቸው፤ ፀሓይ ብርሃኑን ነሣ፤ በጨለማ ተይዞ ሲድበሰበስ ዓለምንም ተወው፤ ይኽ ኹሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ከሥጋው ከመለየቱ አስቀድሞ ተደረገ) (ቅዱስ አትናቴዎስ) ☞ “እስመ ሶበ ተሰቅለ ክርስቶስ ጸልመ ሰማይ አሜሃ ወፀሓይኒ ሰወረ ብርሃኖ ወወርኅኒ ደመ ኮነ…” (ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ ያን ጊዜ ሰማይ ጨለማ ኾነ፤ ፀሓይም ብርሃኑን ነሣ፤ ጨረቃም ደም ኾነ፤ ምድርም ተነዋወጠች ደንጊያውም ተከፈለ፤ መቃብራትም ተከፈቱ፤ ስለዚኽም ለፍጡራን ከፈጣሪያቸው ጋር ሊታመሙ ተገባቸው (ማቴ ፳፯፥፵፭-፶፩) (ቅዱስ ሱኑትዩ) ☞ “ፀሓይ ጸልመ ወወርኅ ደመ ኮነ ወከዋክብት ወድቁ ፍጡነ ከመ ኢይርአዩ ዕርቃኖ ለዘአልበሶሙ ብርሃነ” (ፀሓይ ጨለመ፤ ጨረቃም ደም ኾነ፤ ከዋክብትም ፈጥነው ወደቁ፤ ብርሃንን ያጐናጸፋቸውን የጌታን ዕርቃን እንዳያሳዩ) (አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ) ✅✞ሊቁ አባ ጊዮርጊስም ምስጢሩን በመጠቅለል በሕማማት ሰላምታው ላይም፡- “ፀሓይ ብሩህ አሜሃ ጊዜ ቀትር ጸልመ ወወርኅኒ ጽዱል ተመሰለ ደመ ትንቢት ከመ ቀደመ፤ ስብሐት ለከ” (ብሩህ የኾነ ፀሓይ ያን ጊዜ በቀትር (በስድስት ሰዓት) ጨለመ፤ ጽዱል የኾነ ጨረቃም ደምን መሰለ፤ አስቀድሞ ትንቢት እንደተነገረ፤ ጌታ ሆይ ምስጋና ይገባኻል) በማለት ከትንቢተ ነቢያት በመነሣት በዚኽ በስድስት ሰዓት ምስጋናው ላይ በሰዓቱ ከተከናወነው ምስጢር በመነሣት አስተምሯል፡፡ ✅✞በመስቀል የተሰቀለው የክብር ባለቤት ሰማይን የፈጠረ ነውና በሰማይ ከላይ የተጠቀሱት ተአምራት ሲደረጉ ምድርንም የፈጠረ ነውና በምድር ደግሞ አራት ተአምራት ማለት የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለኹለት ተቀደደ፤ ምድር ተናውጣ ዐለቶች ተሠንጥቀዋል፤ መቃብራት ተከፍተዋል፤ ከ፭፻ በላይ ሙታን ተነሥተዋል (ማቴ ፳፯፥፵፭፤ ፳፯፥፶፩፤ ፳፯፥፶፪-፶፫)፡፡ ✅✞አንድያ ልጇን በመስቀል ተሰቅሎ አካሉ ደም ለብሶ ስታየው ኹሉ ሲሸሽ በታማኝነት ቀራንዮ ድረስ ከተገኘው ከሚወድደው ደቀ መዝሙር ከዮሐንስ ጋር መሪር ልቅሶን በምታለቅስበት ጊዜ ዮሐንስ ጌታን በእጅጉ ከመውደዱ የተነሣ ኹሉም ከቀራንዮ ሲሸሽ ርሱ ግን ሳይሸሽ በመቅረቱ ጌታም እንዲኽ ለሚወድደው ለዮሐንስ ፍቅሩን ሊገልጽለት ከስጦታ ኹሉ የላቀች ስጦታው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምን “እናትኽ እነኋት” በማለት ሲሰጠው፤ እናቱንም “እነሆ ልጅሽ” በማለት ዐደራ ሰጥቷታል፡፡ ✅✞ይኽ የአደራ ቃል ሊፈጸም ጌታችን ካረገ በኋላ ዐሥራ ዐምስት ዓመት በዮሐንስ ቤት ኑራለች፤ በመኾኑም ዮሐንስን በሃይማኖት በምግባር ለምንመስል ለእኛ ለክርስትያኖች ያደራ እናታችን ያደራ ልጆቿ ነንና በልቡናችን ቤት ዘወትር ከብራ ትኖራለች (ዮሐ ፲፱፥፳፮-፳፯)፡፨ 🙏✞የመድኀኔ ዓለም ይቅርታ ከኹላችን ጋር ይኹን፨✞🙏 ✍ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ ለወዳጅዎ #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞ ╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮ @EOTC2921 @Orthodox2921 ╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯

🌾✞ #የመድኀኔ_ዓለም_ስቅለት ✞🌾 ✅✞ጌታችን ከምድር ከፍ ከፍ ብሎ ስለምን ተሰቀለ? ቢሉ:- “እምከመ ተለዐልኩ እምድር እስሕብ ኲሎ ኀቤየ” (ከምድር ከፍ ከፍ ባልኊ ጊዜ ኹሉን እስባለኊ) ብሎ ነበርና ይኽነን ሊፈጽም ነው (ዮሐ ፲፪፥፴፪)፡፡ ✅✞ዳግመኛም ከምድር ከፍ ከሰማይ ዝቅ ብሎ መሰቀሉ “ኅሩይ ማእከለ እግዚአብሔር ወሰብእ” እንዲል አምላክ ወሰብእ ኾኖ እንዳስታረቀን ለማጠየቅ፡፡ ✅✞በመጨረሻም ምድርን በኪደተ እግሩ እየተመላለሰ እንደ ቀደሳት፤ ዐየራትን ደግሞ ሥብ እያጤሱ አስተራኲሰውት ነበርና አየራትን ለመቀደስ ነው፡፡ ✅✞ንጹሐ ባሕርይ ጌታችንን አይሁድ መስቀሉን አሸክመው ቀራንዮ ወደሚባል ቦታ ከወሰዱት በኋላ ኹለት ወንበዴዎችን በቀኝና በግራ አድርገው ጌታችንን በመኻከል ሰቅለውታል (ማቴ ፳፯፥፴፰)፡፡ በትርጓሜ ወንጌል እንደታተተው ክፉዎች ✅✞አይሁድ ይኽነን ያደረጉበት ምክንያት በክፋት ነው፤ ይኸውም በቀኝ የሚመጡ ሰዎች በቀኝ የተሰቀለውን ወንበዴ አይተው “ይኽ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ወንበዴ ነው” ይሏቸዋል፤ ከዚያም ጌታን “ይኽስ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ይኽስ ከርሱ ልዩ ነውን አንድ ነው እንጂ” ብለው ሰዎችን ለማሳሳት፤ በግራ የሚመጡ ሰዎች በግራ የተሰቀለውን ወንበዴ አይተው “ይኽ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ወንበዴ ነው” ይሏቸዋል፤ ከዚያም ጌታን “ይኽስ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ይኽስ ከርሱ ልዩ ነውን አንድ ነው እንጂ” ብለው ሰዎችን ለማሳሳት ያደረጉት ነው፡፡ ✅✞ዳግመኛም አነገሥንኽ ብለውታልና ቀኛዝማች ግራዝማች ሾምንልኽ ለማለት ለመዘበት፡- በተጨማሪም ነቢዩ ኢሳይያስ በምዕ ፶፫፥፲፪ ላይ “ከዐመፀኞችም ጋር ተቈጥሯልና” የሚለው ትንቢቱን ሊፈጽም ሲኾን ምስጢሩ ግን እኛን ከጻድቃን ጋራ አንድ ያደርገን ዘንድ ርሱ ከበደለኞች ጋር ተቈጥሯል፤ ሌላውም በዕለተ ምጽአት እኛን ኃጥኣንን በግራ ጻድቃንን በቀኝ ታቆማለኽ ሲያሰኛቸው ነበር (ማቴ ፳፭፥፴፫፤ ራእ ፩፥፯)፡፡ ✅✞ይኽነንም በሕማማት ድርሳኑ ላይ ሲገልጹ፡- “ወሰቀልዎ ለእግዚእ ኢየሱስ ዲበ ዕፀ መስቀል እንዘ ገጹ መንገለ ምሥራቅ ወእዴሁ ዘየማን መንገለ ደቡብ ወእዴሁ ዘፀጋም መንገለ ሰሜን…” (ጌታችን ኢየሱስንም በዕንጨት መስቀል ላይ ሰቀሉት፤ ፊቱን ወደ ምሥራቅ ቀኝ እጁን ወደ ደቡብ፤ ግራ እጁን ወደ ሰሜን አድርገው ሰቀሉት … ከርሱም ጋር ኹለቱን ወንበዴዎች አንዱን በቀኝ አንዱን በግራው በመኻከላቸው ጌታችን ኢየሱስን አድርገው ሰቀሉ፤ ሕዝቡም ርሱም እንደነርሱ ወንበዴ ነው ይሉት ዘንድ ሰቀሉት፤ ርሱ ግን ወድዶ ከወንበዴዎች ጋር በዕንጨት መስቀል ተሰቀለ፤ ልዑላን መላእክት ፈርተው በፊቱ ራሳቸውን ዝቅ ዝቅ የሚያደርጉለት ርሱ በሚሰቅሉት ፊት ራሱን ዝቅ አደረገ (ፊልጵ ፪፥፲፤ ራእ ፬፥፲-፲፩)። ✅✞በከሃሊነቱ ሰማይና ምድርን ያጸና ከግርማውም የተነሣ ሰማያትና ምድር የሚንቀጠቀጡለትን ርሱን ደካማ ዕንጨት ተሸከመው (ምሳ ፴፥፬፤ ኢሳ ፵፪፥፭)፤ ርሱ ግን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ከራሱ ያስታርቀን ዘንድ ከሰማይ ዝቅ ብሎ ከምድር ከፍ ብሎ በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቀለ፤ ርሱም ስለእኛ በሥጋው በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቀለ፤ ከኀጢአታችን ይለየን ዘንድ በቸርነቱ ያድነን ዘንድ ተሰቀለ (፩ጴጥ ፪፥፳፬)። ✅✞ርሱ ግን ሰማያትን ይቀድስ ዘንድ በአየር ያሉ አጋንንትን ያወርዳቸው ዘንድ በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቀለ፤ ሙሴ አርዌ ብርትን በገዳም እንደ ሰቀለው ርሱም በዕንጨት ላይ ተሰቀለ ፤ በርሱ ያመነ ኹሉ ይድናል እንጂ እንዳይጐዳ የክብር ባለቤት ርሱ ግን ስለ እኛ በዕንጨት ላይ ተሰቀለ (ዮሐ ፫፥፲፬-፲፭)፤ አውቀውስ ቢኾን የክብር ባለቤት ጌታን ባልሰቀሉት ነበር (፩ቆሮ ፪፥፰)፤ ሰማይ ዙፋኑ ሲኾን ምድርም በእግሮቹ የተረገጠች ስትኾን ስለኛ በዕንጨት ተሰቀለ (ኢሳ ፷፮፥፩)፤ ርሱ ግን ተጠብቆለት ስላለ ስለ ደስታው የመስቀልን መከራ ንቆ አቃልሎ ተቀበለ ኀፍረትንም ናቃት፤ ለተሰቀለው ለርሱ የማይሰግድ ቢኖር የተለየ የተወገዘ ይኹን (ፊልጵ ፪፥፰-፲፩)፤ ርሱ ግን ስለ ዓለሙ ደኅንነት በማእዝነ ምድር ወደ ላይ ወደ ታች ወደ ግራ ወደ ቀኝ ኾኖ እንደ መጋረጃ በዕንጨት ላይ ተሰቀለ፤ እኛን ከጻድቃን ጋራ አንድ ያደርገን ዘንድ ርሱ ከበደለኞች ጋር ተቈጠረ) በማለት በስፋት የነገረ ስቅለቱን ምስጢር አስተምረዋል፡፡ ✅✞በመስቀል ሲሰቀልም በቀኙ የተሰቀለው ጥጦስ በግራ የተሰቀለው ዳክርስ ይባላል፤ በቀኝ የተሰቀለው ጥጦስ ፀሓይ ስትጨልም፣ ጨረቃ ደም ስትኾን፣ ከዋክብት ከብርሃናቸው ሲራቈቱ፣ ድንጋዮች ሲሠነጠቁ፣ መቃብራት ሲከፈቱ፣ ሙታን ሲነሡ፣ የምኩራቡ መጋረጃ ወደ ኹለት ወደ ሦስት ሲቀደድ ሰባቱ ተአምራት ሲደረጉ አይቶ አምላክነቱን ተረድቶ “አቤቱ በመንግሥት ዐስበኝ” እያለ ወደ ርሱ ሲለምን፤ በግራ የተሰቀለው ወንበዴ ሰምቶት እየተዘባበተ “አንተስ ክርስቶስ አይደለኽምን? ራስኽንም እኛንም አድን” ይል ዠመር (ሉቃ ፳፫፥፴፱)፡፡ ✅✞ያን ጊዜ በቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ጌታችን ለቤዛ ዓለም የተሰቀለ እውነተኛ የባሕርይ አምላክነቱን ስለተረዳ በግራ የተሰቀለውን “አንተ እንደዚኽ ባለ ፍርድ ሳለኽ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይኽ ግን ምንም ክፋት አላደረገም” ብሎ ከገሠጸው በኋላ ኀጢአት ሳይኖርበት የተሰቀለውን ንጹሐ ባሕርይ አምላኩን፡- “ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ” (ጌታ ሆይ በመንግሥትኽ በመጣኽ ጊዜ አስበኝ) እያለ ሲለምነው ጌታችንም “እውነት እልኻለኊ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኾናለኽ” ብሎት ተስፋውን ሰጥቶታል፡፡ ✅✞በኹለት ወንበዴዎች መኻከል ከሰቀሉት በኋላ ጲላጦስም “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ጽሕፈት በዕብራይስጥና በሮማይስጥ በግሪክም ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረው፤ (ዮሐ ፲፱፥፲፰-፳፪)፤ የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን “ርሱ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለኽ አትጻፍ” ሲሉት፤ ጲላጦስም “የጻፍኹትን ጽፌአለኊ” ብሎ መልሶላቸዋል። ✅✞ይኽነንም በሕማማት ድርሳኑ ላይ ሲተረጒሙት፡- “ወዝ መጽሐፈ ጌጋይ ዘጸሐፎ ጲላጦስ ወአንበሮ መልዕልተ ርእሱ ይደምስስ ለነ በኲሉ ጊዜ መጽሐፈ ዕዳነ ዘጸሐፉ አጋንንት” (ጲላጦስ ጽፎ ከራሱ በላይ ያኖረው በደሉን የሚናገር ይኽ መጽሐፍ ኹልጊዜ አጋንንት የጻፉትን የዕዳችንን መጽሐፍ ያጠፋልን ዘንድ ነው) በማለት አራቅቀው ገልጠዋል፡፡ ✅✞ጌታችን በሚሰቀልበት ጊዜ ብርሃን ያለበሳቸውን አምላክ ዕርቃኑን ለመሰወር ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ፀሓይና ጨረቃ ብርሃናቸውን ነሥተዋል (ማቴ ፳፯፥፵፭)፡፡ ✅✞ይኽ በጌታ ስቅለት ዕለት እንደሚደረግ አስቀድሞ በነቢዩ አሞጽ ኹለት ጊዜ በትንቢት ተነግሯል፡-ይኸውም ☞ “የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይኾን ጨለማ አይደለምን? ጸዳል የሌለውም ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?” (አሞ ፭፥፳) ☞ በዚያም ቀን ፀሐይ በቀትር እንድትገባ አደርጋለኊ ይላል ጌታ እግዚአብሔር በብርሃንም ቀን ምድሩን አጨልማለኊ” (አሞ ፰፥፱)

🌻✞ #የኢትዮጵያ_ኦርቶዶክስ_ተዋህዶ_ቤተክርስቲያን_ቴሌቭዥን ✞🌻 Channel Name: EOTC Frequency: 12519 MHz Symbol rate: 27500 KS/s Polarity: Vertical(V) Satellite: Eutelsat 8WB FEC: 7/8 🌻✞ #የማህበረ_ቅዱሳን_ቴሌቭዥን ✞🌻 "የምናውቀውን እንናገራለን የአየነውን እንመሰክራለን" Channel Name: EOTCMK Frequency: 11555 MHz Symbol rate: 27500 KS/s Polarity: Vertical(V) Satellite: Nilesat FEC: 7/8 ይህ መረጃ ለሌሎች ክርስቲያን እህት ወንድሞቻችን እንዲዳረስ👉 #Share ያድርጉ፡፡

photo content

❖ ማሕሌታዊዉ ቅዱስ ያሬድም በመዋሥዕት መጽሐፉ ላይ ይኽነን ምስጢር ሲተረጒም "ኢሳይያስ ነቢይ ልዑለ ቃል እም ነቢያት ከልሐ ወይቤ እግዚአብሔር ጸባኦት ይወርድ ብሔረ ግብጽ" (ከነቢያት ይልቅ ድምፀ ታላቅ የሚኾን ነቢዩ ኢሳይያስ አሸናፊ እግዚአብሔር ወደ ግብጽ ምድር ይወርዳል ብሎ አሰምቶ ተናገረ)፤ "ደመና ቀሊል ዘይቤ ኢሳይያስ ይእቲኬ ማርያም ድንግል እንተ ጾረቶ በከርሣ ለወልደ እግዚአብሔር" (ኢሳይያስ ቀላል ደመና ብሎ የተናገረላት የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁን በማሕፀኗ የወሰነችው ድንግል ማርያም ናታ፡፡) በማለት ሙሉ ትርጓሜን ሰጥቶታል፡፡ ❖ ቅዱስ ያሬድም ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ በስደቷ ወቅት በደብረ ቊስቋም ስለማረፏ በድጓው ላይ ሲጽፍ፡- “መንግሥቱ ሰፋኒት ዘእምቅድመ ዓለም ወልደ ቅድስት ማርያም ኀሠሠ ምእራፈ ከመ ድኩም ንጉሥ ዘለዓለም፤ ግሩም እምግሩማን ብርሃነ ሕይወት ዘኢይጸልም፤ ኀደረ ደብረ ቊስቋም” (ቅድመ ዓለም የነበረች ጌትነቱ ምልእት ስፍሕት የኾነች የቅድስት ድንግል ማርያም የባሕርይ ልጅ የዘለዓለም ንጉሥ ሲኾን እንደ ደካማ ማረፊያን ፈለገ፤ ከግሩማን ይልቅ ግሩም፤ የማይጨልም የሕይወት ብርሃን ርሱ በደብረ ቊስቋም ዐደረ) ❖ “መንክር ወመድምም ዘተገብረ በደብረ ቊስቋም መንክር ወመድምም ዘይሴባሕ በአርያም፤ አምላክ ፍጹም ኀደረ ውስቴቱ መድኀኔ ዓለም፤ ዘሀሎ እምቅድም፤ ኀደረ ውስቴቱ ለዝንቱ ደብር ዘአብ ቃል ምስለ እሙ ድንግል ደመና ቀሊል” (በደብረ ቊስቋም የተደረገው የሚያስደንቅ እና የሚያስገርም ነው፤ በአርያም የሚመሰገን ፍጹም የባሕርይ አምላክ መድኀኔ ዓለም በውስጡ ዐደረ፤ ቅድመ ዓለም የነበረ የአብ አካላዊ ቃል ፈጣን ደመና ከተባለች ከድንግል እናቱ ጋር በዚኽ ደብር በውስጡ ዐድሯል) በማለት መስክሮላታል፡፡ ❖ በዘመነ ጽጌ የሚደርሰውን ልዩውን ምስጋና የደረሰው አባ ጽጌ ድንግልም በማሕሌተ ጽጌ ድርሰቱ ላይ:- “ተአምረ ግፍእኪ ለአርእዮ እምገጸ ሄሮድስ መስቴማ አመ ጐየይኪ ማርያም በሐዊረ ፍኖት እለ ደክማ ምስለ እግረ ጽጌኪ ልምሉም ኀበ አእጋርኪ ቆማ ለምድረ ገዳምኪ ቅድስት ቊስቋም ስማ እምፈተውኩ በጺሕየ በሰጊድ እሰዓማ” (ማርያም የግፍሽን ተአምር ለመግለጥ ከጠላት ሄሮድስ ፊት በሸሸሽ ጊዜ ከለመለመች ከልጅሽ እግር ጋር መንገድን በመኼድ የደከሙ እግሮችሽ የቆሙባት ስሟ ቊስቋም የተባለ የተቀደሰች ገዳምሽን እኔም ደርሼ ብሳለማት እመኛለኊ እወድዳለኊ) በማለት ጽኑ ፍቅሩን ገልጧል ፡፡ 🙏እመቤታችን ሆይ በስደትሽ ዓመታት ያነባሽው ዕንባ በልጅሽ ፊት አማላጅ ይኹነን። አሜን🙏 በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ ለወዳጅዎ #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞ ╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮ @EOTC2921 @Orthodox2921 ╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯

#የእመቤታችን_ከልጇ_ጋር_የ፫_ዓመት_ከ፮_ወራት_መሰደድ ❖ መልአኩ ለዮሴፍ በሕልሙ ተገልጾ “ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘኽ ወደ ግብጽ ሽሽ እስክነግርኽም ድረስ በዚያ ተቀመጥ” ባለው ጊዜ ቅዱስ ዮሴፍ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብጽ ኼዷል፤ ቅድስት ድንግል ማርያምም ከልጇ ጋር በግብጽ በረሓ በስደት ያሳለፈችው ፫ ዓመት ከ፮ ወር ሲኾን በዚያም ከልጇ ጋራ ብዙ ጸዋትወ መከራ አግኝቷታል፡፡ ❖ ሊቁ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም መጽሐፉ ከቊ ፻፷፯-፻፷፱ ላይ “አዘክሪ ድንግል ንግደቶ ዘምስሌኪ እንዘ ትጐይዪ ምስሌሁ እምሀገር ለሀገር በመዋዕለ ሄሮድስ ንጉሥ፤ አዘክሪ ድንግል ረኀበ ወጽምዐ ምንዳቤ ወሐዘነ ወኲሎ ዐጸባ ዘበጽሐኪ ምስሌሁ…” (ድንግል ሆይ ርጉም በኾነ በሄሮድስ ዘመን ከርሱ ጋራ ካገር ወደ አገር ስትሸሺ ካንቺ ጋር መሰደዱን አሳስቢ፤ ድንግል ሆይ ረኀቡና ጥሙን፣ ችግሩንና ጒዳቱን ከርሱ ጋራ የደረሰብሽን ጸዋትወ መከራ ኹሉ አሳስቢ፤ ድንግል ሆይ ከዐይኖችሽ የፈሰሰውንና በተወደደ ልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር እንባ አሳስቢ፤ ጥፋትን ያይደለ ይቅርታን አሳስቢ መዐትን ያይደለ ምሕረትን አሳስቢ፤ ለጻድቃን ያይደለ ለኃጥኣን አሳስቢ ለንጹሓን ያይደለ ለተዳደፉት አሳስቢ) በማለት ከልጇ ጋር የደረሰባትን ጸዋትወ መከራ አሳስቧል፡፡ ❖ በስደት ወቅት መከራ ያገኙ የእግሮቿን ነገር ሊቁም በሰቈቃወ ድንግል መጽሐፉ ላይ፡- “እፎ ቈቊዐ በሐዊረ ፍኖት መከየደ እግርኪ ወርኀ ዘይሤአን ለባሲተ ፀሓይ ማርያም ወለተ ብርሃን አመ አጒየይኪ ወልደኪ በጒጕዓ እምገጸ ሄሮድስ ተመን ዘበጽሑኪ ምንዳቤያተ ሶበ ይሰምዕ በእዝን ሰብእ አኮ እምበከየ እብን” (ፀሓይን የምትለብሽ የብርሃን ልጅ ድንግል ማርያም ጨረቃን የሚጫማ እግርሽ መንገድን በመኼድ እንዴት በለዘ? (ራእ ፲፪፥፩) በድንጋጤና በችኮላ ከሄሮድስ ፊት ልጅሽን ባሸሸሽው ጊዜ የደረሱብሽን ችግሮች ሰው በዦሮው ቢሰማ ሰው አይደለም ድንጋይ ባለቀሰ ነበር!) በማለት አሳዛኙኝ መከራ ጽፎታል፡፡ ❖ ሊቁ አባ ጊዮርጊስም በሰዓታቱ ላይ “አጽምዕ ሰማይ ዘእነግረከ ወስምዒ ምድር እምዜና ስደታ ንስቲተ ለእመ መለኮት ክቡር ዘልበ ይከፍል ወኅሊና ያንቀለቅል ሶበ ይትነገር ሕማማ ለድንግል” (ሰማይ የምነግርኽን ስማ፤ ምድርም በሚነገር ጊዜ ልብን የሚከፍልና ኅሊናንም የሚያነዋውጥ የድንግልን መከራ በሚነገር ጊዜ ከክቡር መለኮት እናት ከስደቷ ዜና ጥቂት ስሚ)፡፡ “አመ ወፅአት በፍርሃት እምሀገረ ዳዊት ዘይሁዳ በብሥራተ መልአክ እንግዳ ኢረከበት ማየ በፍኖት ዘታሰትዮ ለወልዳ” (በእንግዳ መልአክ ብሥራት የይሁዳ ክፍል ከምትኾን ከዳዊት ከተማ ከይሁዳ በፍርሀት በወጣች ጊዜ ለልጇ የምታጠጣው ውሃ በመንገድ አላገኘችም) ብሏታል፡፡ ❖ መከራ ያገኛቸው የእግሮቿን ነገር የመልክአ ማርያም ጸሐፊ፦ “ሰላም ለአእጋርኪ እለ ጻመዋ በረዊጽ እምቤተልሔም ዘይሁዳ እስከ ምድረ ግብጽ ማርያም ድንግል ሥርጉተ ነበልባል ዕፅ ለኀዲር በቤተ ናሕስ እንተ መልዕልተ ኰኲሕ ሕኑጽ አጥብብኒ በተግሣጽ ወሱቅኒ እምዳሕጽ” (የይሁዳ ዕጣ ከምትኾን ከቤተልሔም ዠምሮ እስከ ግብጽ ምድር ድረስ በሩጫ ለደከሙ እግሮችሽ ሰላምታ ይገባል፤ በነበልባል ያጌጥሽ ዕፅ ድንግል ማርያም ሆይ በዐለት ላይ የታነጸ በኾነ የግንብ ቤት ለማደር በተግሣጽ ጥበበኛ አድርጊኝ፤ ከመሰነካከልም ደግፊኝ) ይላል፨ ❖ የሄሮድስ ወታደሮች ልጇን እንዳይገድሉባት ብላ ወደ ግብጽ ስትሰደድ ያለ ጫማ በመኼድ እሾኹ፣ ዕንቅፋቱ ያገኛቸውን መርገጫዎቿን:- “ሰላም ለመከየድኪ እለ ረከቦን መከራ እምፍርሃተ ቀተልት ሐራ እንበለ አሣዕን አመ ሖራ (ገዳዮች ከኾኑ ጭፍሮች ፍራቻ የተነሣ ያለመጫሚያ በኼዱ ጊዜ መከራ ላገኛቸው መርገጫዎችሽ ሰላምታ ይገባል) ይለዋል፨ ❖ ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈሰ እግዚአብሔር እየተቃኘ ቅድስት ድንግል ማርያም የባሕርይ አምላክ ዐማኑኤልን ይዛ ወደ ግብጽ የመሰደዷን ነገር አስቀድሞ ተገልጾለት በምዕ ፲፱፥፩ ላይ "እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ" በማለት ከገነት የተሰደድነውን እኛን ወደ ቀደመ ርስታችን ሊመልሰን እንደመጣ ለማጠየቅና፤ ጠላታችን ዲያብሎስን ከሰዎች ልብ አውጥቶ ለመስደድ፤ ወልደ እግዚአብሔር ልመናዋ ፈጥኖ በሚሰማላት "ደመና መፍጠኒት" በተባለች በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ዠርባ ታዝሎ ወደ ግብጽ የመሰደዱን ነገር አስቀድሞ ገልጾታል፡፡ ❖ ይኸውም በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈ ንጉሡ ሄሮድስ ክርስቶስን ለመግደል በፈለገ ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል ለአረጋዊዉ ለዮሴፍ በሕልሙ ተገልጾለት "ተንሥእ ወንሣእ ሕፃነ ወእሞ ወጒየይ ውስተ ብሔረ ግብጽ" (ሕፃኑንና እናቱን ይዘኽ ወደ ግብጽ ሽሽ) ባለው ጊዜ ይኽ ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት ሊፈጸም ምልጃዋ ፈጥኖ በሚደርስ "ደመና መፍጠኒት" በተባለች በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ዠርባ ታዝሎ ወደ ግብጽ በኼደ ጊዜ የግብጽ ጣዖታት ኹሉ እየተሰባበሩ ሲወድቁ፤ በነርሱ ዐድረው ያስቱ የነበሩ አጋንንት ኹሉ ሸሽተዋል፤ በመኾኑም በዚኽ የነገረ ማርያም አስተምህሮ እመቤታችን "ደመና መፍጠኒት" ወይም "ደመና ኢሳይያስ" ተብላ ተጠርታለች፡፡ ❖ ኢትዮጵያዊዉ የነገረ ማርያም ሊቅ አባ ጊዮርጊስም ይኽነን የኢሳይያስን ትንቢት በጥልቀት ሲተረጒም፡-"ሄሮድስ ኀሠሠ ዘኢይትረከብ ወእግዚእ ተግሕሠ ውስተ ምድረ ግብጽ ተጽዒኖ ዲበ ደመና ቀሊል፤በከመ ይቤ ኢሳይያስ ... " (ሄሮድስ የማያገኘውን ፈለገ፤ ጌታም በፈጣን ደመና ተጭኖ ወደ ግብጽ ምድር ኼደ፤ ነቢዩ ኢሳይያስ እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተጭኖ ወደ ግብጽ ምድር ይወርዳል ብሎ እንደተናገረ፤ ቅድስት ድንግል ሆይ ፈጣን ደመና መቸም መች ቢኾን አንቺ ነሽ፤ ሄሮድስ በአዳራሹ ውስጥ ነፋስን ሊዘጋ ወደደ፤ ነፋስን መዝጋት በወዴት ይቻላል፤ ሄሮድስ የፀሓይ ብርሃንን በእጁ ሊጨብጥ ወደደ፤ የፀሓይ ብርሃንን መጨበጥ በወዴት ይቻላል፤ እግዚአብሔር በዠርባሽ ታዝሎ በግብጽ ምድር እንግዳ ኾነ) በማለት ምስጢሩን አምልቶ አጒልቶ አብዝቶ አስፍቶ ተንትኖታል፡፡

🌿🌾✞ #የቁስቋም_ክብር_በኢትዮጵያ_ቀደምት_ሊቃውንት ✞🌾🌿 ❖ ከብዙ የስደት ውጣ ውረድ በኋላ ልጇን ይዛ ከአረጋዊ ዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር ከመዐዲ ወደ ላዕላይ ግብጽ በጀልባ ከካይሮ በስተደቡብ 320 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በላዕላይ ግብጽ በምትገኘው ወደ ደብረ ቊስቋም ገብተው በመንገድ ጒዞ ካገኛቸው ድካም 6 ወር ከ10 ቀናት ዐርፈዋል፡፡ ❖ በደብረ ቁስቋም ሳሉ ሄሮድስ እንደሞተ የጌታ መልአክ በግብፅ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ። የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ኺድ ብሎታል (ማቴ 2፡19-20)። ❖ ይኽቺንም የተቀደሰች ቦታን ጌታችን ባርኳት ወደ ናዝሬት ተመልሰዋል፤ ከብዙ ዘመን በኋላ በኅዳር ስድስት ቀን “አስተጋብኦሙ እግዚእነ ለሐዋርያቲሁ ቅዱሳን ውስተ ዝንቱ ደብረ ቊስቋም ወቀደሰ ታቦተ ወቤተ ክርስቲያን ወሠርዐ ቊርባነ ወመጠዎሙ ሥጋሁ ቅዱሰ ወደሞ ክቡረ” ይላል (በዚኽ በደብረ ቊስቋም ቅዱሳን ሐዋርያቱን ሰበሰባቸው ታቦትንና ቤተ ክርስቲያንንም አክብሮ የቊርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ሰጥቷቸዋል) ይላል፡፡ ❖ በዚኽ ምክንያት ደብረ ቁስቋምን የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በግብጽ የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ይሏታል፤ የግብጽ ኦርቶዶክስ ምእመናን በእጅጉ የሚወዷት ገዳም ስትኾን በ1993 ዓ.ም. ላይ እመቤታችን በገዳሙ ተገልጣ እንደነበር ይናገራሉ፤ በዚኽችም ገዳም 100 መነኮሳት ይገኙበታል፤ ከቦታዋ ክብር የተነሣ "ዳግሚት ቤተልሔም" ይሏታል፤ በገዳሙም ታላቅ ቤተ መጻሕፍት አለ፨ ❖ በጌታ በተባረከችው ይኽቺ ቦታ ላይ በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ቅዱስ ጳኩሚስ ገዳም የገደመ ሲኾን፤ የእስክንድርያ 23ኛ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ በታናሿ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ምትክ ታላቅ ካቴድራል ለመሥራት ባሰበ ጊዜ እመቤታችን ተገልጻለት የልጇ የክርስቶስ ትሕትናው በገዳሙ እንዲታሰብበት ባለበት እንዲኾን ነግራዋለች። ❖ በርካቶች የኢትዮጵያ ሊቃውንት እመቤታችን ከልጇ ጋር ወደ ቊስቋም የመግባቷን ነገር የጻፉ ሲኾን ለምሳሌም አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በሰዓታት መጽሐፉ ላይ በስፋት ሲዘረዝረው፡- [“በሊዓ ሕፃናት ሶበ ኀለየ ሄሮድስ አርዌ ሰማይ ምስለ ዮሴፍ አረጋይ ነገደት ቊስቋመ ናዛዚተ ሐዘን በብካይ”] (የሰማዩ አውሬ ሄሮድስ ሕፃናትን መብላት ባሰበ ጊዜ፤ ከሐዘንና ከልቅሶ የምታረጋጋ ማርያም ከአረጋዊዉ ዮሴፍ ጋራ ወደ ቊስቋም ኼደች (ተሰደደች)) ❖ “አሥረጸት ማርያም አክናፈ ረድኤት አምሳለ ዖፍ ለዐሪገ ቊስቋም ህየ ከመ ትትዐቀብ ዘመነ ወአዝማነ ወመንፈቀ ዘመን በከመ ይቤ መጽሐፍ” (ማርያም ወደ ቊስቋም ተራራ ለመውጣት እንደ ዎፍ የረድኤት ክንፎችን አበቀለች በመጽሐፍ እንደተናገረ በዚያ በዘመንና በዘመናት በዘመን እኩሌታም ትጠበቅ ዘንድ) ❖ “ብጽዐን ለኪ ኦ ደብረ ቊስቋም እምኲሎን አድያም እምናዝሬት እስከ ቤተልሔም ዘተጸወነ ላዕሌኪ መድኀኔ ኲሉ ዓለም” (ከናዝሬት እስከ ቤተ ልሔም ካሉ አውራጆች ኹሉ የዓለም ኹሉ መድኀኒት ወደ አንቺ የተጠጋ የቊስቋም ተራራ ሆይ ክብር ይገባሻል) ❖ “በቃለ ውዳሴ ጥዑም ይደሉ ሰላም ለዕበይኪ ፍጹም አድባረ ቊስቋም ማኅደረ ልዑል ዘአርያም” (በአርያም ያለ የልዑል ማደሪያው የኾንሽ የቊስቋም ተራራ ሆይ ፍጹም ለሚኾን ክብርሽ በሚጣፍጥ የምስጋና ቃል ሰላምታ ማቅረብ ይገባል) በማለት ዘርዝሮ ጽፎላታል፡፡ ❖ ቅዱስ ያሬድም ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ በስደቷ ወቅት በደብረ ቊስቋም ስለማረፏ በድጓው ላይ ሲጽፍ፡- ❖ “መንግሥቱ ሰፋኒት ዘእምቅድመ ዓለም ወልደ ቅድስት ማርያም ኀሠሠ ምእራፈ ከመ ድኩም ንጉሥ ዘለዓለም ግሩም እምግሩማን ብርሃነ ሕይወት ዘኢይጸልም ኀደረ ደብረ ቊስቋም” (ቅድመ ዓለም የነበረች ጌትነቱ ምልእት ስፍሕት የኾነች የቅድስት ድንግል ማርያም የባሕርይ ልጅ የዘለዓለም ንጉሥ ሲኾን እንደ ደካማ ማረፊያን ፈለገ፤ ከግሩማን ይልቅ ግሩም፤ የማይጨልም የሕይወት ብርሃን ርሱ በደብረ ቊስቋም ዐደረ) ❖ “መንክር ወመድምም ዘተገብረ በደብረ ቊስቋም መንክር ወመድምም ዘይሴባሕ በአርያም አምላክ ፍጹም ኀደረ ውስቴቱ መድኀኔ ዓለም ዘሀሎ እምቅድም ኀደረ ውስቴቱ ለዝንቱ ደብር ዘአብ ቃል ምስለ እሙ ድንግል ደመና ቀሊል” (በደብረ ቊስቋም የተደረገው የሚያስደንቅ እና የሚያስገርም ነው፤ በአርያም የሚመሰገን ፍጹም የባሕርይ አምላክ መድኀኔ ዓለም በውስጡ ዐደረ፤ ቅድመ ዓለም የነበረ የአብ አካላዊ ቃል ፈጣን ደመና ከተባለች ከድንግል እናቱ ጋር በዚኽ ደብር በውስጡ ዐድሯል) በማለት መስክሮላታል፡፡ ❖ እኔም ለወንጌል አገልግሎት ወደ ግብጽ ኼጄ በነበረ ጊዜ እመቤታችን ልጇን ይዛ ከስደት ስትመለስ ከአረጋዊ ዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር ኅዳር 6 ከድካም ያረፉበት ይኽቺን ቅድስት ቦታ ስረግጣት መጀመሪያ ያሰብኩት ቅዱሱ አባት አባ ጽጌ ብርሃን በማሕሌተ ጽጌው ላይ፦ “ተአምረ ግፍእኪ ለአርእዮ እምገጸ ሄሮድስ መስቴማ አመ ጐየይኪ ማርያም በሐዊረ ፍኖት እለ ደክማ ምስለ እግረ ጽጌኪ ልምሉም ኀበ አእጋርኪ ቆማ ለምድረ ገዳምኪ ቅድስት ቊስቋም ስማ እምፈተውኩ በጺሕየ በሰጊድ እሰዓማ” (ማርያም የግፍሽን ተአምር ለመግለጥ ከጠላት ሄሮድስ ፊት በሸሸሽ ጊዜ ከለመለመች ከልጅሽ እግር ጋር መንገድን በመኼድ የደከሙ እግሮችሽ የቆሙባት ስሟ ቊስቋም የተባለ የተቀደሰች ገዳምሽን እኔም ደርሼ ብሳለማት እመኛለሁ እወዳለሁ) በማለት የጸለያት ጸሎትን ነበር፡፡ 🙏✟የእመቤታችን በረከት ይደርባችኊ፤ ቦታዋንም ለመሳለም ኹላችኹንም ያብቃችሁ፡፡✟🙏 [ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ] ✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ ለወዳጅዎ #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞ ╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮ @EOTC2921 @Orthodox2921 ╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯

🌾🌾🌾🌾🌾🌾🌾🌾🌾🌾🌾🌾 #የቅዱስ_ጊዮርጊስ_ተጋድሎ_በኢትዮጵያ_ሊቃውንት 🌾🌾🌾🌾🌾🌾🌾🌾🌾🌾🌾🌾 በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ❖ የዚኽም ቅዱስ አባቱ በቀጶዶቅያ መስፍኑ አንስጣስዮስ ሲኾን እናቱ ቴዎብስታ ትባላለች፤ የተወለደውም በልዳ በሶርያ ፍልስጥኤም በ፪፻፹ ዓ.ም. ነው፤ ታናሽ ኾኖ ሳለ አባቱ ዐርፏል፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ፈረስ ግልቢያን ተምሮ ኻያ ዓመት በኾነው ጊዜ ቢሩት ሀገር በመኼድ በዚያ ሀገር ይመለክ የነበረውን መንፈሰ ሰይጣን ያደረበትን የመኰንኑን ልጅ እንዲበላት የተሰጠውን ዘንዶ በክርስቶስ ስም ከገደለው በኋላ እጅ መንሻ ይዞ ወደ ንጉሠ ፋርስ ኼደ፡፡ ❖ በዚያ ሀገር ግን ነገሥታቱ ጣዖታትን በማምለክ ክርስቲያኖችን ሲያሳድዷቸው አይቶ ዐዘነ፤ ልቡም በክርስቶስ ፍቅር ነድዶ ወደ ሀገሬ አልመለስም ስለ ክርስቶስ ስም እሞታለኊ አለና “ክርስቲያናዊ አነ ወአአምን በእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ” (እኔ የክርስቲያን ወገን ነኝ እምነቴም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው) በማለት መሰከረ፡፡ ❖ ከዚያም ንጉሡ ልብሱን ገፍፈው በዕንጨት ላይ እንዲሰቅሉት፤ ዳግመኛ የዘንባባ እሾኽ የመሳሰሉ ፸ የብረት ችንካሮች ሠርተው በነዚያ እንዲቸነክሩትና ዐጥንቱን ኹሉ እንዲቀጠቅጡት አዘዘ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን በትዕግሥት በመኾን “እፎ ኢይኄሊ ከመ አምላኪየ ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅለ ዲበ ዕፀ መስቀል” (ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል እንደተሰቀለ እንዴት አላስብም) አለ፡፡ ❖ ዳግመኛም በውስጡ ረዣዥም ችንካሮች ያሉበት የብረት ጫማን ባጫሙት ጊዜ “ሠጠቅዎ ወመተርዎ ዐሥራዊሁ እስከ ውኅዘ ደሙ ዲበ ምድር ከመ ማይ ወሶበ ስዕነ ሠጊረ ድቡተ ሖረ” ይላል ችንካሮቹ ደሙ እንደ ውሃ በምድር ላይ እስኪፈስስ ድረስ እግሩን ዘልቀው ሥሩን በጣጠሱት፤ መኼድም ባልቻለ ጊዜ አጐንብሶ ኼዷል፤ ከዚያም የፈላ የብረት ጋን ውስጥ ከትተው ሰውነቱ በደም እስኪጥለቀለቅ ድረስ ራሱን በመዶሻ ሲመቱት ወደ ጌታችን ጸለየ፤ ያን ጊዜ “ጊዮርጊስ ሆይ ከአንተ ጋር ነኝና ጽና” የሚል ቃል ከሰማይ መጣለት፤ ቅዱስ ሚካኤልም ተገልጾ ከሕመሙ ፈውሶታል፡፡ ይኽነንም ባዩ ጊዜ ብዙዎች በጌታችን አመኑ፡፡ ❖ ንጉሡም ይኽነን ባየ ጊዜ እጅግ የሚያስጨንቅ መንኰራኲር ለ፵ ቀን አሠርቶ ለቅዱስ ጊዮርጊስ “እመሰ ትሠውዕ ለአጵሎን ትነሥእ ጌራ መንግሥት ወእመሰ ኊልቊ አንተ ከመ ትትልዎ ለክርስቶስ ነጽር ዘንተ መንኰራኲረ ዘግበርኩ ለከ ከመ እግድፍ በውስቴታ ታማስን ሥጋከ” (ለአጵሎን ብትሠዋ የመንግሥትን ዘውድ ትቀዳጃለኽ፤ ግን ክርስቶስን ለማገልገል የቈረጥኽ ብትኾን ሥጋኽን ትፈጭ ዘንድ በውስጧ ልትጣልባት ያዘጋጀኋትን መንኰራኲር ተመልከት) አለው፤ ይኽ ሲኾን ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈጣሪው ክርስቶስን አመሰገነ፡፡ ❖ እነርሱም ወደ መንኰራኲሩ በመወርወር ፵ ሰዎች ያዞሩት ዠመር ከዚያም ሰውነቱ ለዐሥር ክፍል ተከፋፈለ፤ እነርሱም ሥጋውን በጒድጓድ ውስጥ ቀበሩት፤ ክብር ይግባውና ጌታችን መላእክትን አስከትሎ በመምጣት እንደገና ከሞት አስነሣውና ባረከው፡፡ ❖ ርሱም ከሞት ተነሥቶ እንደገና ወደ ከተማ ገብቶ ስለ ክርስቶስ አምላክነት መሰከረ፤ እነርሱም እጅግ ለመስማት የሚከብዱ መከራዎችን አደረጉበትና ሰውነቱን ጨምቀው አንጀቱን ዘረገፉት፤ ከዚያም ሥጋውን አቃጥለው በዕንጨት ቀፎ በማድረግ ይድራስ ወደተባለ ተራራ ወስደው ዐመዱን በትነውት ተመለሱ፤ ክብር ይግባውና ጌታችን መላእክትን አስከትሎ በመውረድ አራቱን ነፋሳተ ምድር የተበተኑትን የቅዱስ ጊዮርጊስን ሥጋዎች እንዲሰበስቡ አዝዞ እንደገና ከሞት አስነሥቶታል፤ ይኽነንም ባዩ ጊዜ ብዙዎች በክርስቶስ አምነው የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጅተዋል፡፡ ❖ በመጨረሻም ብዙ ተጋድሎዎችን ለሰባት ዓመታት ከፈጸመ በኋላ ንጉሡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ራስ በሰይፍ እንዲቈረጥ አዝዞ ወደ መሰየፊያው ቦታ ሲኼድ እሳት ከሰማይ ወርዶ ፸ውን ነገሥታት ያቃጥላቸው ዘንድ መከራውም ከክርስቲያኖች ጸጥ ይል ዘንድ ጸለየ፤ ወዲያውኑም እሳት ከሰማይ ወርዶ ፸ውን ነገሥታት አቃጥሏቸዋል፤ ከዚያም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙ ቃል ኪዳንን ከሰጠው በኋላ በክብር ወደ ሰማይ ወጣ፤ ከዚያም ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ራሱን ዘንበል አድርጎ ሚያዝያ ፳፫ በሰይፍ ቈርጠውት የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጅቷል፡፡ ❖ ከአገልጋዮቹ የቀሩት ሥጋውን ወስደው በንጹሕ ልብስ ጠቅልለው ወደ ሀገሩ ልዳ በመውሰድ ቤተ ክርስቲያን ሠርተው በውስጡ አኖሩት፤ ከርሱም ቊጥር የሌላቸው ብዙዎች ድንቆች ተአምራት ተገልጠዋል፡፡ ❖ ኢትዮጵያዊዉ ሊቅ አባ ጽጌ ብርሃን በማሕሌተ ጽጌ ድርሰታቸው ላይ፦ “ክበበ ጌራ ወርቅ ጽሩይ እምዕንቈ ባሕርይ ዘየሐቱ ዘተጽሕፈ ብኪ ትእምርተ ስሙ ወተዝካረ ሞቱ አክሊለ ጽጌ ማርያም ለጊዮርጊስ ቀጸላ መንግሥቱ አንቲ ኲሎ ታሰግዲ ሎቱ ወለኪኒ ይሰግድ ውእቱ” (የስሙና የሞቱ መታሰቢያ ባንቺ የተጻፈብሽ የሚያበራ ከኾነ ዕንቈ ባሕርይ ይልቅ የጠራ ወርቅ ክበብ ያለው የራስ ቊር የተባለ የጊዮርጊስ የመንግሥቱ የራስ ልብስ ጌጥ ሽልማት የአበባ አክሊል ማርያም ሆይ አንቺ ለርሱ ኹሉን ታሰግጅለታለሽ (ታንበረክኪለታለሽ) ርሱ ግን ላንቺ ይሰግዳል) ይሉታል፨ ❖ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቁ አርከ ሥሉስም የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስን ተጋድሎ፡- “ሰላም ለከ ሰርዌ ሰማዕታት አእላፍ ዘሞገሰ ስምከ በጽሐ መንገለ ኲሉ አጽናፍ በቅድመ ፀሓይ ብሩህ ዘኢየዐርብ ለዘልፍ ሕማምየ ዝሩ ነሢአከ ወጸዊረከ እስትንፋሰ አፍ ጊዮርጊስ ቀሊለ ክንፍ ከራድዮን ዖፍ” (ዘወትር በማይጠልቅ በብሩህ ፀሓይ ፊት በምድር ዳርቻዎች ኹሉ የስምኽ ባለሟልነት የደረሰ የአእላፍ ሰማዕታት አለቃቸው ሰላምታ ለአንተ ይገባል፤ ክንፈ ፈጣን ከራድዮን ዖፍ የተባልኽ ጊዮርጊስ ሆይ የአፍ እስትንፋስን ተቀብለኽና ተሸክመኽ ሕማሜን በትን) እያለ ተማፅኖታል፡፡ ❖ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በተአምኆ ቅዱሳን መጽሐፉ ላይ፦ “ሰላም ለጊዮርጊስ ሰማዕት ዘፀሓየ ጽድቅ ዘተአምሪሁ ከመ ኆጻ ባሕር ዘኢይትኌለቊ ኮከበ ክብር ዘማእከለ ሰማይ ወምድር ዘአርአየ ኀይለ በዲበ ሰሌዳ መንበር ብእሲ አዛል ወመስተጋድል ኀያል ዝሕዙሐ ገድል”፡፡ (ገድሉ የበዛ የተትረፈረፈ ኀያል፤ ተጋዳይ ጐልማሳ (ብርቱ) ሰው፤ በተዘረጋ ዙፋን ላይ ኀይልን ያሳየ፤ በሰማይና በምድር መኻከል ያለ የማይቈጠር የክብር ኮከብ፤ ተአምሩ እንደ ባሕር አሸዋ የበዛ የኾነ፤ የፀሓየ ጽድቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ሰማዕት ለኾነ ለጊዮርጊስ ሰላምታ ይገባል) ይለዋል፨ ❖ የስብሐተ ፍቁር ዘጊዮርጊስ ደራሲ ኢትዮጵያዊዉ ሊቅ፦ "እምብሩር ወወርቅ ይትበደር ሞገሱ ለጊዮርጊስ ቅዱስ በዲበ ጸዐዳ ፈረሱ ለረዲኦትነ ይምጻእ ወያንሶሱ" (ከወርቅና ከብር ይልቅ ሞገሱ የሚበልጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በነጭ ፈረሱ እኛን ለመርዳት ይምጣ፤ ይመላለስም) ይለዋል፨ 👇👇👇👇👇👇👇 ✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ለጓደኞቻችን #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞ ╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮ @EOTC2921 ╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯