fa
Feedback
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን🙏

የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን🙏

رفتن به کانال در Telegram

የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና የጠበቁ የነፍስ ስንቅ የምናገኝበት፦ ✍️"ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም" ፩ኛ ቆሮ. ፰፥፪ #ለተጨማሪ፦👇✞👇 https://www.youtube.com/EOTC2921 https://www.facebook.com/eotc2921 https://www.tiktok.com/@eotc2921 https://www.instagram.com/eotc2921

نمایش بیشتر
4 374
مشترکین
اطلاعاتی وجود ندارد24 ساعت
اطلاعاتی وجود ندارد7 روز
اطلاعاتی وجود ندارد30 روز
آرشیو پست ها
› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹አዎ እኔ ሰው ነኝ ያውም የጌታዬ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ›› አሉት፡፡ ንጉሡም መልሶ ‹‹በዚያ አይሁድ በሰቀሉት ታምናለህን?›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹አዎን እኔ በእርሱ አምናለሁ አላፍርም ስለእኔ የተሰቀለውን በሰው ፊት አምነዋለሁ፡፡ ስለእኔ ብቻ አይደለም ንጉሥ ሆይ ስለ አንተና ካንተ ጋር ስላሉትም ነው እንጂ፡፡ በእርሱ እመኑ የዘላለምን ሕይወት ታገኙ ዘንድ አላችሁ›› አሉት፡፡ ንጉሡም ይህንን በሰማ ጊዜ በጣም ተቆጥቶ ሠራዊቱን ሁሉ ጠርቶ በቶሎ እሳት እንዲያነዱ አዘዛቸው፡፡ የእቶን እሳቱንም ካነደዱ በኋላ ‹‹በሉ ይህንን የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ነኝ የሚለውን ፀጉረ ለባሹን አንስታችሁ ከእሳቱ ውስጥ ጨምሩት›› አላቸው፡፡ አባታችንም ንጉሡና መኳንንቱ ሠራዊቱ ሁሉ እያየአቸው ከእቶኑ እሳት ውስጥ ገቡ፡፡ ነገር ግን እሳቱ እንደ ወንዝ ውኃ ሆነ፡፡ የንጉሡም ሠራዊት ይህንን ከመለከቱ በኋላ ግማሾቹ ‹‹በዚህ ሰው አምላክ አምነናል›› አሉ፡፡ ንጉሡም 77 አዛዦቹን በማዘዝ ‹‹አምነናል›› ያሉትን ሰዎች ራስ ራሶቻቸውን በሰይፍ አስቆረጣቸው፡፡ ቁጥራቸውም አርባ እልፍ ነበር፡፡ ንጉሡም ሰይፉን መዝዞ የአባታችንን ራስ ሊቆርጥ ተወርውሮ ወደ አባታችን ሲሄድ ወዲያው ጽኑ የመብረቅ ነጎድጓድና ንውጽውጽታ ሆነ፡፡ ጌታችንም ወደ አባታችን ዘንድ መጣ፡፡ መብረቁም በአንድ ጊዜ ንጉሡንና ሠራዊቶቹን ሁሉ አጠፋቸው፡፡ የሞቱም ሰዎች ቁጥራቸው አራት መቶ ሺህ ሆነ፡፡ አንድስ እንኳን ሳይቀር ሁሉም አለቁ፡፡ አባታችንም በመብረቅ የሞቱን ሰዎች ባዩ ጊዜ ውስጣቸው በሀዘን አለቀሰ ነፍሶቻቸውን የጽልመት መላእክት ወደ ገሀነመ እሳት ሲያወርዷቸው ተመልክተዋልና፡፡ በዚህም ጊዜ አባታችን ጌታችንን ‹‹እነዚህም ሰዎች ማርልኝ›› አሉት፡፡ ዳግመኛም ‹‹ሰው ስሕተተኛ ነው፣ አንተ ግን መሐሪ ይቅር ባይ ነህና በእኔ ምክንያት በእነዚህ ሰዎቸ አትፍረድባቸው… ›› እያሉ በለመኑት ጊዜ ጌታችን ተሰወረባቸውና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ አባታችንም ወዲያው አጠገባቸው ካለው ገደል እግራቸውን በገመድ አሥረው ቁልቁል ተዘቅዝቀው ተሰቀሉ፡፡ ሰይጣንም መጥቶ ያችን ገመድ በቆረጣት ጊዜ አባታችን በገደሉ ሲወድቁ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እንደ ዐይን ጥቅሻ መጥቶ አባታችንን አቅፎ ያዛቸውና ‹‹በእግርህ ላቁምህ/ ወይስ በራስህ ላቆምህ ትወዳለህ/›› አላቸው፡፡ አባታችንም ገብረ መንፈስ ቅዱስም መልአኩን ‹‹ተወኝ በራሴ ልቁም›› አሉትና መልአኩም በዚያው ትቷቸው ዐረገ፡፡ አባታችንም በጥርሳቸው ድንጋይ ነክሰው እስከ 30 ዓመት ተዘቅዝቀው ሲጸልዩ ኖሩ፡፡ ናላቸው ሁሉ ፈሶ አለቀ፣ አንጀታቸውም ፈሰሰ፣ እንደ ዕንጨትም ቅርፊት ሆኑ፡፡ ከ30 ዓመትም በኋላ ጌታችን ሰባቱን ሊቃነ መላአክትና እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያን አስከትሎ ወደ አባታችን መጣና ሦስት ጊዜ በስማቸው ጠርቶ ‹‹እነዚያን ከሐዲዎች ምሬልሃለሁ›› አላቸው፡፡ አባታችንም ነክሰውት የነበረውን ድንጋይ በጣሉት ጊዜ ጥርሶቻቸው አብረው ተነቅለው ወደቁ፡፡ ጌታችንም በከቡራን እጆቹ ቢዳስሳቸው ሰውነታቸው ታደሰችላቸው፡፡ አባታችንም ጌታችንን ‹‹ምሬልሃለሁ ካልከኝና ከማርክልኝስ ነፍሳቸውን ከሥጋቸው ጋር አዋሕድልኝ›› አሉት፡፡ ጌታችንም አባታችንን ‹‹እንዳልክ እንደወደድክ ይሁንልህ እኔ ሙታንን ልታስነሣ ሥልጣን የሰጠሁህ አይደለምን አሁንም ወደሞቱት ሰዎች ሂድና አማትብባቸው›› አላቸውና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ያንጊዜም አባታችን ወደሞቱት ሰዎች ሄደው በላያቸው ከጸለዩ በኋላ ‹‹እናንት ሁላችሁ በጌታዬ በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ተነሡ›› ቢሏቸው ሙታኑም ወዲያው አፈፍ ብለው ተነሥተው በአባታችን ፊት ቆሙ፡፡ አባታችንም ሃይማኖትን አስተምረው አጥምቀው ክርስቲያን አደረጓቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን ከእነርሱ ተለይተው በመብረቅ ተጭነው ወደ ምድረ ከብድ ተመለሱ፡፡ ዳግመኛም አባታችን እነዚያን ሰዎች ይጎበኟቸው ዘንድ ወደ ዐረብ አገር ሄዱ፡፡ እነዚያ ከሞት አስነሥተው ክርስቲያን ያደረጓቸው ሰዎችም ሃይማኖታቸውን ጥምቀታቸውን አጽንነተው ቤተ ክርስቲያን ሠርተው በጽድቅ ሕይወት እየኖሩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ሆነው ‹‹አምላከ ገብረ መንፈስ ቅዱስ›› እያሉ ሲያመሰግኑ ተመለከቷቸው፡፡ አባታችንም ይህንን አይተው ስለሰዎቹ መዳን ደስ ተሰኝተው ተመልሰው ወደ ምድረ ከብድ መጡ፡፡ ነገር ግን አባታችን ሄደው ሄደው እንደጎበኟቸው ሰዎቹ አላወቁም ነበር፡፡ እነዚያም ክርስቲያኖች እስከዛሬ ድረስ አሉ፡፡ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን! (ምንጭ፦ ገድለ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ተስፋ ገብረሥላሴ 1992 ዓ.ም፣ ስንክሳር ዘወርኃ ጥቅምት)

፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ወደ አባታችን መጥቶ ከባሕሩ ዳር በመቆም ‹‹ወዳጄ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! መላ ኢትዮጵያን ምሬልሃለሁና ተነሥ ከባሕሩ ውጣ›› አላቸው፡፡ አባታችንም አጥንታቸው እንደመርፌ ቀዳዳ ተበሳስቶ ፈጽመው ደክመው ነበርና ጌታችን በክቡራን እጆቹ ሁለንተናቸውን ቢዳስሳቸው እንደቀድሞው ደህና ሆኑ፡፡ ጌታችንም ከባረካቸው በኋላ ወደ ምድረ ከብድ እንዲሄዱ ነገራቸው፡፡ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምድረ ከብድ እንደደረሱ እንደ ዓምድ ተተክለው ሰባት ዓመት ቆመው ጸለዩ፡፡ በዚህም ጊዜ ሰይጣን በቁራ ተመስሎ መጥቶ ሁለት ዐይኖቻቸውን አንቁሮ አጠፋቸው ነገር ግን አባታችን ጸሎታቸውን ሳያቋርጡ ሁለት ሳምንት በጸሎት ቆዩ፡፡ ከ2 ሳምንት በኋላ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል መጥተው በዐይኖቻቸው ላይ እፍ ብለው ብርሃናቸውን ከመለሱላቸው በኋላ አባታችንን ‹‹ከሰማይ ፍጹም ኃይል ይሰጥሃልና ጠላቶችህን ትበቀል ዘንድ ወደ ዝቋላ ሂድ›› ብለዋቸው ዐረጉ፡፡ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስም እንደታዘዙት ወደ ዝቋላ እየሄዱ ሳለ በመንገድ ላይ ከዛፍ ሥር ያረፉ ሦስት ሽማግሌዎችን አገኙ፡፡ አባታችንም ባዩአቸው ጊዜ ለመሰወር ቢያስቡም ሽማግሌዎቹ ግን ይመጡ ዘንድ ጠሯቸውና ‹‹በእግዚአብሔር ዙፋን ተማጽነናል ሦስታችንንም በጀርባህ አዝለህ አንድ አንድ ምዕራፍ ሸኘን›› አሏቸው፡፡ አባታችንም ሽማግሌዎቹን በቀረቧቸው ሰዓት ሽበት የከበባቸው የደከሙ ሽማግሌዎች ሆነው አገኟቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን አንደኛውን ሽማግሌ አዝለው ከአንድ ምዕራፍ አደረሷቸው፡፡ ያም ሽማግሌ ‹‹ከዚህ አሳርፈኝ፣ አንተ ደክመሃል የማትበላ የማትጠጣ ነህና›› አሏቸው፡፡ አባታችንም ‹‹አባ የት ያውቁኛል?› አሏቸው፡፡ ሽማግሌውም ‹‹አሁን ደግሞ ሄደህ ጓደኞቼን አምጣልኝ›› አሏቸው፡፡ አባታችንም የቀሩት ሁለቱ ሽማግሌዎች ካሉበት ደርሰው ሁለቱንም በየተራ እያዘሉ የመጀመሪያውን ካደረሱበት ቦታ አደረሷቸው፡፡ ከዚህም በኋላ እነዚያን ሽማግሌዎች ‹‹አባቶቼ ሆይ! ከየት ነው የመጣችሁት?›› አሏቸው፡፡ ሦስቱም ሰዎች ተነሥተው ቆሙና ለአባታችን በአንድነት በሦስትነት ተገለጡላቸው፡፡ አንድ ሲሆኑ ሦስት ሦስት ሲሆኑ አንድ ሆኑ፡፡ ሥሉስ ቅዱስ ለአብርሃም በመምሬ አድባር ሥር በአንድነት በሦስትነት እንደተገለጡለት ሁሉ አሁንም ለአባታችን ለገብረ መንፈስ ቅዱስ በአንድነት በሦስትነት ተገለጡላቸው፡፡ በጀርባቸውም አዘሏቸው፡፡ የእግዚአብሔርንም ክብር ስላዩ አባታችን ፊታቸው እንደፀሐይ አበራ፡፡ ቅዱሳን መላእክት ወርደው እንደሻሽ ተነጥፈው ሲያመሰግኑ ሰማይና ምድር ተነዋውጠው ተራሮች ኮረብቶች ዓለቶች ተሰነጣጠቁ፡፡ በዚያችም ሰዓት ታላቅ ፍርሃት ሆነ፡፡ አባታችንም ዙሪያቸውን በከበባቸው በምሥጢራት ጎርፍ ተውጠው ተንቀጥቅጠው በግንባራቸው ወደቁና እንደ በድን ሆኑ፡፡ በራእይ ውስጥም ሆነው እነዚያ ሽማግሌዎች አባታችንን እስከ ሰባተኛው ሰማይ እንዳደረሷቸው ተመለከቱ፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ሐዋርያትን እንደ ቅዱስ ጴጥሮስን እንደቀሰቀሳቸው አባታችንንም ቀሰቀሳቸውና ‹‹ወደ ዝቋላ ውረድ መቶ ዓመት ሙሉ አጥንትህን ሥጋህን እየነደፉ የተዋጉህን አጋንንት ታጠፋቸው ዘንድ፡፡ እነሆ እኔ እንደወሰድኩህ ባለማወቃቸው በትዕቢት ላይ ናቸውና ‹በባሕር ውስጥ አለ› ይሉሃል፡፡ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ይረዱሃል፤ መባርቅትም በፊት በኋላ ይከተሉሃል›› አላቸው፡፡ ያንጊዜም አባታችን በመብረቅ ላይ ሆነው እነዚያ አጋንንት ወዳሉበት ወረዱ፡፡ አጋንንቱንም ደመናት ከበቡአቸው፣ መላእክትም በእሳት ሰይፍ መተሩአቸው፣ በመብረቅ አጨዷቸው፤ አመድ ሆነው በነፋስ በተኗቸው፡፡ የእነዚያም አጋንንት ቁጥራቸው ሰባ ሺህ እልፍ ከአንድ ሺህ ነበር፡፡ ሁሉም በአንድ ጊዜ አልቀዋልና ከእነርሱ ሸሽቶ ያመለጠም አልነበረም፡፡ ሰባቱ ሊቃነ መላእክትም ወደ ሰማይ ዐረጉ፡፡ አባታችንም አንበሶችና ነብሮች፣ ድብና ዘንዶ ወዳሉበት ምድረ ከብድ ተመለሱ፡፡ አባታችንም ወደ ምድረ ከብድ ከተመለሱ በኋላ መንፈስ ቅዱስ የጠራቸው ሦስት ቅዱሳን ሁሉም በየአንበሶቻቸው ላይ ተቀምጠው ወደ ምድረ ከብድ መጡ፡፡ እነዚህም ቅዱሳን የዋልድባው አቡነ ሳሙኤል፣ የአዘሎው አቡነ አንበስ እና ከላዕላይ ግብፅ ተነሥቶ የመጣው አቡነ ብንያም ናቸው፡፡ ነገር ግን አባታችን እነዚህን ቅዱሳን ስለተሰወሯቸው ቅዱሳኑ እስከ ሰባት ቀን ድረስ በምህላ ሰነበቱ፡፡ የአባታችን የሚያስፈሩ አንበሶች ወጥተው የቅዱሳኑን አንበሶቻቸውን ገድለው ደማቸውን አፍስሰው ሥጋቸውን በሉ፡፡ ሦስቱም ቅዱሳን በዚህ ፈጽመው ደንግጠው ሳለ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ 60 ነብሮችንና 60 አንበሶችን አስከትለው ተገለጡላቸውና ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን የእግዚአብሔር ቅዱሳኑ አትፍሩ›› አሏቸው፡፡ ቅዱሳኑም ‹‹አባታችን ሆይ! ጸሎትህ ቅድስት እንደሆነች ባወቅን ጊዜ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንባረክ ዘንድ ወደ አንተ መጣን፡፡ ነገር ግን ባላገኘንህ ጊዜ እስከ ሰባት ቀን አለቀስን›› አሏቸው፡፡ ዳግመኛም ‹‹የእርስዎም አንበሶች መጥተው አንበሶቻችንን በሉብን›› አሏቸው፡፡ አባታችንም አንበሶቻውን ‹‹እስከ ዕለተ ሞቴ ድረስ በእግሬ ከረገጥኩት ምድር በቀር እግዚአብሔር ያላዘዛችሁን ለምን በላችሁ? አሁንም የበላችሁትን ትፉ›› አሏቸው፡፡ እነዚያም አንበሶች አፋቸውን ከፈቱና የበሉትን የአንበሶቹን ሥጋቸውን አጥንታቸውን ከደም ጋር ተፉ፤ በሆዳቸውም የቀረ የለም፡፡ አባታችንም ወዲያው ወደ ምሥራቅ ዞረው እግዚአብሔር ካመሰገኑ በኋላ ‹‹አቤቱ አልዓዛርን ያስነሣኸው አንተ ነህና አሁንም እነዚህን አናብስት ከሞት አስነሣቸው፤ ለባሮችህም የድካማቸውን ማረፊያ ይሆኑላቸው ዘንድ የሰጠሃቸውን አትከልክላቸው… ›› እያሉ ጸለዩ፡፡ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ብለው ጸሎታቸውን ከጨረሱ በኋላ የአንበሶቹን ሥጋቸውን በመስቀል ምልክት ባርከው ‹‹በጌታዬ በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ተነሡ›› አሏቸው፡፡ አንበሶቹም እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥነው ተነሡና እንደቀድሞው ሆኑ፡፡ ለአባታችንም እጅ ነሥተውና ሰግደው የእግሩን ትቢያ ላሱ፡፡ አባታችንም ወደጌቶቻቸው መለሳቸው፡፡ እነዚህም ሦስቱ ቅዱሳን በአባታችን ላይ አድሮ ድንቅ ነገርን የሚሠራ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ የዋልድባው አቡነ ሳሙኤልም አባታችንን ‹‹አባት ሆይ በዚህች ቀን ድንቅ ሥራን አየን፣ አርአያህ የእግዚአብሔርን መልአክ አርአያ ይመስላል፣ ቅድስናህ ፍጹም ነው፣ የጸሎትህ ኃይል ሙታንን ያስነሣል፣ የተበሉ አንበሶችን ከአንበሶች ሆድ አወጣህ›› አሏቸው፡፡ ዳግመኛም አባታችን ስለ ቅዱሳኑ ምግብ ወደ እግዚአብሔር በጸለዩ ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ፋኑኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ በእጁ ሦስት ኅብስትና ሦስት ጽዋ ይዞ መጣ፡፡ አባታችንም ሦስቱን ቅዱሳን ‹‹እግዚአብሔር የሰጣችሁን ይህንን ኅብስትና ጽዋ ንሡ ብሉ ጠጡ›› አሏቸው፡፡ ቅዱሳኑም ሥራቸውን እያደነቁ በልተው ጠጥተው ጠገቡ፡፡ በማግሥቱም አባታችን ቅዱሳኑን ‹‹በሰላም ሂዱ›› ብለው መርቀው ሸኟቸውና የእግዚአብሔር ሥራ እያደነቁ ወደየበዓታቸው ተመልሰው ሄዱ፡፡ ከዚህም በኋላ ለአባታችን ጌታችን ተገልጦ ብዙ ምሥጢራትን ከነገራቸው በኋላ ወደ አረማውያን አገር ሄደው እንዲያስተምሩና የሚደርስባቸውንም መከራጭምር ነገራቸው፡፡ አባታችንም ክርስቶስን ፈጽመው ወደማያውቁት ዐረብ አገራት ሄዱ፡፡ የዐረብ ንጉሥም ብዙ ሠራዊቱን አስከትሎ ብዙ ጣዖታን አሶዞ ሲጓዝ አገኙት፡፡ በጣዖታቱ ውስጥ አድረው የነበሩ አጋንንትም አባታችንን ባዩ ጊዜ ወጥተው ሸሹ፣ ጣዖታቱም ከምድር ላይ ወድቀው ተሰባበሩ፡፡ የዐረቡም ንጉሥ ‹‹አንተ ፀጉር ልብሱ ምንድነህ? ሰው ነህን?›

፡ ከዚህም በኋላ አባታችን ወደ ጫካ ገብተው ብቻቸውን የበጋውን ሐሩር የክረምቱን ቁር ታግሰው ምንም ልብስ ሳይለብሱ ራቁታቸውን ሆነው በተጋድሎ ኖሩ፡፡ ከጽኑው ተጋድሎአቸውና ከጫካው ቅዝቃዜ የተነሣ ሰውነታቸው አልቆ ከአጥንታቸው ጋር ተጣበቀ፡፡ ፍራፍሬም ሆነ ምንም ነገር አይመገቡም ውኃም ፈጽሞ አይጠጡም ነበር፡፡ አባታችን በምድረ በዳ እንደሰው ሳይሆን እንደመላእክት ኖሩ፡፡ ቅዱሳን መልእክትም ዘወትር ይጎበኟቸው ነበር፤ ስለምግባቸውም ሰማያዊ ኅብስት አምጥተው ይሰጧቸዋል ነገርግን አባታችን ያንን ኅብስት አይመገቡትም ይልቁንም ጽዋውን ባሸቱት ጊዜ እንዲሁ ይጠግባሉ ይረካሉ፡፡ ነቢይ ክብርህን በማየቴ እጠግባለሁ እንዳለ፡፡ አባታችን በተወለዱበትም ቤት አልኖሩምና እናት አባታቸው የሥጋ ዘመዶቻቸውም አላወቋቸውም በበረሃ ብቻቸውን ኖሩ እንጂ፡፡ ነገር ግን ሰማያውያን ሁሉ ወዳጆቻቸው ሆኑ፤ እመቤታችን ወዳጄ ትላቸዋለች፡፡ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ወገናችን ይሏቸዋል፡፡ መላእክትም ወዳጃችን እያሉ በክንፋቸው ያቅፏቸዋል፡፡ የአባታችን መዓዛቸው ጫካውን ይሞላው ነበር፡፡ በመንፈስ ቅዱስም ኃይል ወደፈለጉት ቦታ በፍጥነት እንደወፍ ይበራሉ፡፡ ስለተሰጣቸውም ጸጋ የበረሃ እንስሳት ሁሉ ያገለግሏቸዋል፡፡ አባታችን ሁልጊዜ እንዲህ ይሉ ነበር፡- ‹‹የሚጣፍጥ ምግብን መውደድ ኃጢአትን ያመጣል፣ ሞትን ያስከትላል፡፡ ክንፍ ያላቸው የሰማይ ወፎች እንኳን በመብል ምክንያት ይጠመዳሉ፣ ምግብ በመሻት ከምድር ላይ ይወድቃሉ በወጥመድም ይያዛሉ፡፡ የሰው ልጅም ምግብን በመውደድ በኃጢአት ይወድቃልና እኔስ ለሰውነቴ ምግብ መጠጥን አልፈልግም፤ ልብስም አልሻም ዕራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን እንደወጣሁ እንዲሁ ዕረቁቴን ወደ መቃብር እመለሳለሁ እንጂ፡፡ ከዚህ ከኃላፊው ዓለም በሞት በተለየሁ ጊዜ መብል መጠጥንና ልብስን ማን ያስከትልልኛል?›› አሉ፡፡ ዳግመኛም ‹‹ሰው ሊደርስ በማይችልበት በረሃ እኖራለሁ፣ ነጣቂ ተኩላዎችና አራዊቶች ባሉበት እነርሱ እንዲበሉኝ ሥጋዬን እጥላለሁ፤ ዳዊት በመዝሙር ‹የጻድቃን ሥጋቸው ለዱር አራዊት ነው› እንዳለ እኔ ክፉ አውሬዎች፣ ተናዳፊ እባቦችና ዘንዶዎች ወዳሉበት እገባለሁ ምግብም እሆናቸው ዘንድ እወዳለሁ›› በማለት አባታችን ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው ይሰጡ ነበር ነገር ግን አራዊቱ ሁሉ እየሰገዱላቸው ይገዙላቸው ከእግራቸውም በታች ይተኙ ነበር፡፡ እንደሚታዘዝ ደቀ መዝሙርም ይታዙላቸው ነበር፤ ለጸሎትም በሚቆሙበት ጊዜ አብረዋቸው ይቆማሉ፡፡ በፊታቸውም ይጫወታሉ፡፡ በአንደኛው ዕለት አባታችን ጸሎታቸውን እንደጨረሱ ሰማይ ተከፍቶ የእሳት ድንኳን ተገልጦ አርባእቱ እንስሳ የእግዚአብሔርን ዙፋን ተሸክመው 24ቱ ካህናተ ሰማይ ማዕጠንት ይዘው፣ ቅዱሳን መላእክትና አለቆቻቸው በየነገዳቸው በዙሪያው ቆመው ጌታችን ለአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአንድነት በሦስትነት እንዳለ ተገለጠላቸው፡፡ አባታችንም ይህንን ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተውና ድግጠው መሬት ላይ ወደቁ፡፡ ጌታችንም ካጸናቸውና ካበረቻው በኋላ ‹‹ዮሐንስ ቀለምሲስ እኔን እንዳየኝ አንተም እኔን ማየት የምትችልበትን ኃይል እሰጥሃለሁ፤ ወዳጄ ሆይ ምን ትሻለህ? የምትጠይቀኝስ ነገር ምንድነው? ልይህ ብለህ በለመንከኝ ጊዜ ተገልጥኩልህ፡፡ ሰማንያ ዓመት በጫካ ኖርክ፣ በረሃዎችን ዞርክ፣ ከአንበሶችና ነብሮች ከአራዊትም ጋር መኖርን አልፈራህም ጨክነህ እስከ ሞት ድረስ ታገስህ፡፡ የመረጥኩህ ወዳጄ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! ምን አደርግልህ ዘንድ ትወዳለህ?›› አላቸው፡፡ አባታችንም ይህንን ቃል ከጌታችን ሲሰሙ ‹‹አምላኬ ሆይ ይህን ልታደርግልኝ አይገባኝም፡፡ በፊትህስ ሞገስን ካገኘሁ የገቦታን ሰዎች ማርልኝ እነርሱ ኃጥአን ናቸውና አንተ ንስሓን ለማይሹ ጻድቃን አልመጣህምና ኃጥአንን ወደ ንስሓ ልትመልስ ነው እንጂ›› አሉት፡፡ ዳግመኛም ‹‹አቤቱ እንደ ክረምት ውኃ እንባቸውን እያፈሰሱ ጥርሳቸውን እያፋጩ በደይን የሚኖሩትን አስባቸው ሰይጣን አስቷቸዋልና በማወቅ ባለማወቅ በሠሩት ማራቸው፣ ይቅር በላቸው›› እያሉ ለመኑት፡፡ ጌታችንም ‹‹ወዳጄ ሆይ የለመንከኝን አልከለክልህም፣ እንደቸርነቴም ስምህን የጠሩትን መታሰቢያህን ያደረጉትን ኃጥአንን መሬልሃለሁ፤ የለመንከኝንም ሁሉ አደርግልህ ዘንድ ኪዳንን ሰጥቼሃለሁ›› አላቸው፡፡ አባታችንም እጅግ ደስ ብሏቸው በግንባራቸው መሬት ላይ ወድቀው ጌታችንን ሲያመሰግኑት ቅዱሳን መላአክትና ሰማያውያን ቅዱሳን ሁሉም አብረው ተደስተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ አባታችንም ይህንን ቃልኪዳን ሲቀበሉ ዕድአቸው 300 ዓመት ነበር፡፡ ጌታችንም የመላእክት አለቆችን ‹‹ስለ ወዳጄ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምልጃ ወደ ገሃነም ሂዱና የኃጥአንን ነፍስ አውጡ፣ ከእስራታቸውም ፍቱአቸው›› አላቸውና እነርሱም የገቦታ ሰዎችን ሦስት ሺህ ነፍሳት ከደይን አውጥተው ወደ ገነት አገቧቸው፡፡ ዳግመኛም እግዚአብሔር አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ‹‹እንደ አንተ ካሉት ሰዎች በቀር በዓለም ያሉ ሰዎች እንዳያውቁህ አደርጋለሁ፤ መላእክት ይጎበኙሃል እንጂ ከካህናት ከመነኮሳት ከምእመናንም ወገን ቢሆን ምንም ያለ ፈቃድህ አያይህም፡፡ ወደጄ ሆይ እንደ ወደድህም እኔን አባቴንና መንፈስ ቅዱስን በሦስትነቴ አየኸኝ፡፡ አሁንም ወደ ኢትዮጵያ ሂድ በዚያም ከደይን የምታወጣቸው ነፍሳት አሉ›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹አምላኬ ሆይ ወደዚያች አገር ማን ያደርሰኛል?›› አሉት፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹እኔ በሥልጣኔ አደርስሃለሁ›› ካላቸው በኋላ ከእርሳቸው ተሰወረ፡፡ አባታችንም የገቦታ ሰዎች ምሕረትን ሲያገኙ አይተው እጅግ ተደሰቱ፡፡ በሌላም ጊዜ አባታችን አራት ሺህ እልፍ እየሰገዱ፣ 300 ጊዜ የቀኝ 300 ጊዜ ደግሞ የግራ ፊታቸውን በድንጋይ እየመቱ፣ መዝሙረ ዳዊትን እየደገሙ፣ 15ቱን መኅልየ ነቢያት፣ መኅልየ ሰለምንንና ውዳሴ ማርያም እየጸለዩ ለኃጥአን ምሕረትን ሲለምኑ ዕንባቸው እንደ ውኃ ይፈስ ነበር፡፡ ጌታችንም ‹‹በተወለድሁባት፣ በተጠመቅሁባትና ከሞት በተነሣሁባት ዕለት እልፍ እልፍ ነፍሳትን እምርልሃለሁ›› አላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን ስድሳ አንበሶችና ስድሳ ነብሮች እየተከተሏቸው ወደ አገራችን ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ብርሃናዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም ከእነዚሁ ተከታዮቻቸው ጋር በነፋስ ሠረገላ ጭኖ ምድረ ከብድ አደረሳቸው፡፡ ዳግመኛም ‹‹ደብር ቅዱስ›› ወደሚባለው ወደ ዝቋላ ወሰዳቸው፡፡ አባታችንም በውኃው ዳር ቆመው ምሥራቁን፣ ምዕራቡን፣ ሰሜኑን፣ ደቡቡን በመለከቱ ጊዜ የኢትዮጵያ ሰዎች ኃጢአታቸው በፊታቸው የተገለጠ ሆነ፡፡ ሰው የገዛ ፊቱን በመሥታወት እንደሚያይ የኃጥአንም ሥራቸው በአባታችን ፊት እንዲሁ የተገለጠ ነውና፡፡ አባታችንም የኢትዮጵያን ሰዎች ኃጢአታቸውን በግልጽ በተመለከቱ ጊዜ ተወርውረው ወደ ባሕሩ በመግባት ተዘቅዝቀው መጸለይ ጀመሩ፡፡ ‹‹ከባሕር እንዳልወጣ፣ በእግሬም እንዳልቆም በሕያው ስምህ ምያለሁ›› ብለው አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ቆዩ፡፡ በ40ኛ ቀናቸው የታዘዘ መልአክ መጥቶ ‹‹ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሃለሁ ብሎሃል›› አላቸው፡፡ አባታችንም መልአኩን ‹‹መላ ኢትዮጵያን ካልማረ ከዚህ ባሕር አልወጣም›› አሉት፡፡ መልአኩም ከእሳቸው ተለይቶ ከሄደ በኋላ አባታችን በዚያ ባሕር ውስጥ መቶ ዓመት ተዘቅዝቀው ሲጸልዩ ኖሩ፡፡ አባታችንም በባሕሩ ውስጥ ተዘቅዝቀው መቶ ዓመት ሲጸልዩ ከኖሩ በኋላ ደማቸው ፈሶ አለቀና ውኃው ደም መሰለ፡፡ ሥጋቸውም አልቆ አጥንቶቻው እንደበረዶ ሆኑ፡፡ ሰባት ሺህ እልፍ ሦስት መቶ የሚሆኑ አጋንንትም ከአራቱም አቅጣጫ እየመጡ ሰውነታቸውን በፍላፃዎቻቸው ይወጓቸው ነበር

✞✞✞ #ገብረ_መንፈስ_ቅዱስ ✞✞ አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን 🌹ጥቅምት 5🌹 ኑሮአቸው እንደሰው ያይደለ በምድረ በዳ እንደመላእክት የኖሩትና በዝቋላ ተራራ ባለው ባሕር ውስጥ 100 ዓመት ተዘቅዝቀው ለኢትዮጵያ ሰዎች ምሕረትን የለመኑት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ታላቅ ቃልኪዳን የተቀበሉበት ዕለት ነው፡፡ + የከበረ ቅዱስ ኪራኮስ ከእናቱ ከቅድስት ሐና ጋር በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡ ኤልያኖስ የተባለው ከሃዲ ንጉሥ በመጀመሪያ አባታችንን ለጣዖቶቹ እንደሰግዱ ሲያስገድዳቸው ትእዛዙን እንዳልተቀበሉት ባወቀ ጊዜ ወደ አደባባይ አወጣቸውና ‹‹አማልክቶቼን እንዳያመልኩ እየጻፈች የምትከለክል ይህች እጅህ ትቆረጥ ዘንድ ይገባል›› አለው፡፡ አቡነ ኪራኮስንም ይዘው እርሳስ አፍልተው በአፋቸው ውስጥ አፈሰሱባቸው፡፡ ደግሞም በብረት አልጋ ላይ ፍሕም ነስንሰው በላዩ አስተኟቸው፡፡ ጨውም በመጨመር ሰውነታቸውን ፈጽመው አቃጠሉት፡፡ አጥንቶቻቸውም እስኪሰበሩ ድረስ በብረት በትሮች ደበደቧቸው፡፡ ጌታችንም ከሕመማቸው ፈወሳቸው፡፡ አቡነ ኪራኮስ በእሥር ቤት ሳሉ ከሃዲው ንጉሥ ወላጅ እናታቸውንም አምጥቶ ለሦስት ሰዓት ያህል በፀጉሯ ሰቅሎ ሥጋዋን ሰነጣጠቀው፡፡ በእሳትም አቃጠላትና ሰማዕትነቷን በዚያው ፈጸመች፡፡ አቡነ ኪራኮስን ግን አምጥተው መርዛማና ተናዳፊ እባቦችና እፉኝቶች ካሉበት ትልቅ ጉድጓድ ከተቷቸው ነገር ግን መርዛማ እባቦቹ አባታችንን አልኳቸውም፡፡ ከወታደሮቹም ውስጥ አንዱ ‹‹በኪራኮስ አምላክ አምኛለሁ፣ የኪራኮስ አምላክ ሆይ ነፍሴን ተቀበላት›› ብሎ መስክሮ አንገቱን ለሰያፊዎቹ አስተካክሎ በመስጠት ተሰየፈና ሰማዕትነት ተቀበለ፡፡ አባታችንንም ከዘይት ጋር ዝፍጥ ከፈላበት ምጣድ ውስጥ ጨመሯቸው፡፡ ሁለተኛም ደረታቸውን በጦር ወጓቸውና ሰማዕትነታቸውን በዚሁ ፈጽመው ነፍሳቸውን ለእግዚአብሔር አስረከቡ፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፤ + + + አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፡- ከደቡባዊ ግብፅ ከቆላው አገር ከንሒሳ የተገኙ ገዳማዊ ናቸው፡፡ አባታቸው ስምዖን ከነገደ ብንያም ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ አቅሌስያ ይባላሉ፡፡ ወላጆቻቸው በእግዚአብሔር ፊት ደጋጎች የነበሩ ቢሆኑም አቅሌስያ መካን ሆና ሆና ልጅ በማጣቷ እያለቀሰች 30 ዘመን ኖራለች፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ሥዕል ካለበት ፊት ለፊት በመቆም እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣት ዘንድ አልቅሳ ስትለምን ያንጊዜ ከሥዕሉ ቃል ወጥቶ ‹‹ሥልጣኑ ከሰማይ ከፍታ ከፍ የሚል ንጽሕናው ከሚካኤል ከገብርኤል የሚተካከል ክህነቱ እንደ መልከጼዴቅ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ እንደ ነቢይ ኤልያስ የሆነ ልጅ እንቺ ተቀበይ›› አላት፡፡ አቅሌስያም በመጋቢት 29 ቀን ፀንሳ በታኅሣሥ 29 ቀን ደም ግባቱ እጅግ የሚያምር ወንድ ልጅ እንደወለደች መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሰው አምሳል መጥቶ ‹‹የዚህ ልጅሽ ስሙ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ይሁን›› አላት፡፡ ወዲያውም ሕፃኑ ተነሥቶ ከእናቱ ጭን ወርዶ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ሦስት ጊዜ ሰገደ፡፡ ዳግመኛም ‹‹ከጨለማ ወደ ብርሃን ለአወጣኸኝ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን›› አለ፡፡ እግዚአብሔር ነቢዩ ኤርሚያስን ‹‹በእናትህ ማኅፀን ቀደስኩህ ከማኅፀን ሳትወጣም የተመረጠ አደረግሁህ›› እንዳለው ገብረ መንፈስ ቅዱስንም ከእናቱ ማኅፀን መርጦታልና የበልአምን አህያ ያናገረ የቢታንያ ድንጋዮችንም አንደበት ሰጥቶ ስሙን እንዲያመሰግኑት ያደረገ አምላክ አሁንም ይህንን ሕፃን አንደበቱን ከፍቶለት ስሙን እንዲያመሰግን አደረገው፡፡ ኤር 1፡1፣ ዘኁ 22፡21-33፣ ሉቃ 19፡40፡፡ ከዚህም በኋላ ይህ ሕፃን በተወለደ ጊዜ ለአምላኩ ሰግዶ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ካመሰገነ በኋላ እናቱ አላቀፈችውም፣ ጡቷንም አልጠባም፡፡ ከዚያ የነበሩ ሁሉ ይህንን በማየታቸው እጅግ ተደንቀው አምላካቸውን አመሰገኑ፡፡ ከ3 ዓመት በኋላም እግዚአብሔር መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን እንዲህ ብሎ አዘዘው፡- ‹‹ሕፃኑን ከእናቱ ክንድ ተቀበል፣ ብዙ ገዳማውያን ወዳሉበት ገዳም ውሰድና ከበራቸው አስቀምጠው፣ አበ ምኔቱንም ሕፃኑን ከበር አንሥተህ ካንተ ዘንድ አኑረው ስለ ልብሱ ስለ ምግቡ አታስብ ሕፃኑ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነውና ምግቡም መንፈሳዊ ነው ይኸውም ከእግዚአብሔር የሚወጣ ቃል ነው፣ ሰው በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ዕወቅ በለው›› በማለት አዘዘው፡፡ ብርሃናዊው መልአክ የራማው ልዑል ቅዱስ ገብርኤልም እንደታዘዘው ከሰማይ ወርዶ ሕፃኑን ከእናቱ ክንድ ወስዶ በክንፎቹ አቅፎ ስሞ እስከ ሰባቱ ሰማይ አውጥቶ በሥሉቅ ቅዱስ ፊት አቅርቦት አካስባረከው፡፡ እግዚአብሔርም መልአኩን ‹‹ወደ እናቴ ወደ ማርያም ውሰደውና ትባርከው›› አለውና ወስዶት እመቤታችንም ባረከችው፡፡ ዳግመኛም ከአዳም ጀምሮ ሄሮድስ በግፍ እስካስፈጃቸው ሕፃናት ያሉት ሁሉም ቅዱሳን ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ ደናግልና መነኮሳት ሁሉም እንዲባርኩት አደረገው መልሶ ከእግዚአብሔር ፊት አቆመው፡፡ መድኅን ጌታም ሕፃን ገብረ መንፈስ ቅዱስን ‹‹በመንግሥቴ ከእኔ ጋር ትነግሣለህና ደስ ይበልህ፣ በርታ የሚደርስብህን ሁሉ ታገሥ ብዙ ነፍሳት በአንተ ምክንያት ይድናሉ፣ ሰላሜ ከአንተ ጋር ይሆናል›› አለው፡፡ ከዚህም በኋላ መልአኩ አባ ዘመደ ብርሃን ወዳለበት ገዳም አወረደውና ሕፃኑን ከበር ላይ አስቀምጦ እርሱ ወደ ውስጥ ገብቶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉን ነገረው፡፡ አባ ዘመደ ብርሃንም ሕፃኑን አስገብቶ በእንክብካቤ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ እያስተማረ አሳደገው፡፡ ሕፃኑም ትምህርቱን በጨረሰ ጊዜ ዲቁና ተቀብሎ እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ጸጋንና ሞገስን የተመላ ሆነ፡፡ ፍጹም የእግዚአብሔር ጸጋ አድሮበታልና ሥራው ሁሉ በዕውቀት የተመላና የተቃና ሆነ፡፡ አባ ዘመድ ብርሃንም በሕፃኑ ላይ ያደረበትን ጸጋ እያየ እጅግ ደስ ይለው ስለነበር እንደ ቅዱስ እንጦንስ አስኬማን ሰጠው፡፡ ከዚህም በኋላ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቅስናን ተቀበሉና በጾም በጸሎት ተጠምደው በታላቅ ተጋድሎ መኖር ጀመሩ፡፡ እንደ ሐዋርያትም የተአምራትና የፈውስ ሀብት ተሰጣቸውና ድውያንን የሚፈውሱ፣ ሙታንን የሚያነሡ፣ አጋንንትን የሚያወጡ ሆኑ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ዳግመኛ ተገልጦላቸው ወደ ሰማይ አሳረጋቸውና ከእግዚአብሔር ፊት አቆማቸው፡፡ ያን ጊዜም ጌታችን ክቡራን የሆኑ እጆቹን ዘርግቶ ከባረካቸው በኋላ ‹‹በጸሎትህ ከሲኦል የምታወጣቸው ብዙ ነፍሳት አሉ፤ ድውያንንም ትፈውሳለህ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ከሰው ተለይተህ ወደ ጫካ ገብተህ ከአንበሶችና ከነብሮች ጋር ኑር›› አላቸው፡፡ አባታችንም ጌታችንን ‹‹የሰጠኸኝ እነዚህ አንበሶችና ነብሮች ምን ይመገባሉ?›› አሉት፡፡ ጌታችንም ‹‹የረገጥከውን መሬት ይልሳሉ በዚያም ይጠግባሉ፡፡ ወደ እኔም እስክትመጣ ድረስ ይኸው ምግብ ይሆናቸዋል›› አላቸው፡፡ ቅዱሳን መላእክትም ይህንን በሰሙ ጊዜ ደስ አላቸው፡፡ ጌታችንም መልአኩን ወደ ቀደመ ቦታቸው ይመልሳቸው ዘንድ አዘዘው፡፡ ከዚህ በኋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከራሳቸው እስከ እግራቸው ድረስ ጠጉር በቀለላቸው፡፡ የጠጉራቸውም ርዝመቱ አንድ ክንድ ከስንዝር ነው፡፡ አባታችንም በታላቅ ተጋድሎ ሲኖሩ በጸጋ ላይ ጸጋ ተጨመረላቸው፡፡ ከዕለታት በአንደዋ ቀን የፈወሳቸው ሕሙማን ብዛታቸው እልፍ ሆነ፡፡ የሀገሩ ሰዎችም ሥራቸውን ስላወቁባቸው አዘኑ፡፡ ‹‹ውዳሴ ከንቱ እንዳይሆንብኝ ተነሥቼ ሰው ወደማያውቀኝ አገር እሄዳለሁ›› ብለው ተነሥተው ሄዱ፡፡ ሕዝቡም አባታችን እንደተሰወሩ ባወቁ ጊዜ በሀዘን ዘለቀሱ፡

#ወዳጄ_ሆይ (ምክረ አበው) ✔ወዳጄ ሆይ ኃጢአት ለመስራት ቀጠሮ ትይዛለህ፤ ፅድቅ ለመስራት ግን ጊዜ የለኝም ትላለህ። ✔ጓደኛህን ለማግኘት ጊዜ አለህ፤ የንስሐ አባትህ ለማግኘት ጊዜ የለህም። ✔ስጋህ ሲራብ ከየትም አምጥተህ (ለምነህም ቢሆን) ትበላለህ፤ ነፍስህ ግን የክርስቶስን ስጋ ከራባት ዘመናት ተቆጥረዋል። #ወዳጄ_ሆይ እባብ አሳተኝ ያለችውና ከፍርድ ያላመለጠችውን ሔዋንን ታስታውሳታለህ? እንግዲያውስ አንተም እንደ እሷ ምክንያት በመደርደር ራስህን ለማጽደቅ አትሞክር፤ ይህም ሲነገርህ በተግባር እንጂ በአፍህ ለመመለስ አትጣር።

"ሰይጣንም የአንቺን ምስጋና ወሬ ሲሰማ በብስጭት ጥርሱን ያፏጫል የምስጋናሽ ወሬ በእርሱ ዘንድ መራጃ ነውና እራሱን ይቆርጠዋል፡፡ ከስምሽ አጠራር የተነሣ መብረቅ በኃይል ሲጮህ እንደ ሰማ ሁሉ ይደነግጣል፡፡ አንቺ ከተወለድሽ ጀምሮ ፈጽሞ ዕረፍት አላገኘም፡፡ ባንቺ ታመመ በልጅሽም ተጨነቀ በአንድ ልጅሽ መስቀል ሥቃይ አገኘው፡፡ ከፍጡራን ወገኖች ሁሉ ይልቅ ሰይጣል አንቺን ይጠላል፡፡" በአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ

​​#ስደትሽን_ሳሥብ ስደትሽን ሳሥብ ስለ አንቺ ልገፋ፣ ለካስ ሥደት አለ ቀን በሰው ሲከፋ፣ ወስዶ ሣያስቀርሽ ወንዝ እና ጅረቱ፣ ምሣሌ ሆነሻል ድንግል ለፍጥረቱ፡፡ #አዝ https://telegram.me/EOTC2921 እንዳልቅበዘበዝ ሁኚ ከአጠገቤ፣ ድንግል ሆይ ሥራሽን መዝግቦታል ልቤ፣ በምሕረት ይለፈኝ በፍጹም ይቅርታ፣ እሺ ባይው ልጅሽ የታቀፍሽው ጌታ፡፡ #አዝ https://telegram.me/EOTC2921 ሡላማጢስ ብሎ ሶለሞን ጠራሽ፣ የሠላም መገኛው አንቺ ስለሆንሽ፣ እንበረከካለሁ እሠግዳለሁ ለአንቺ፣ ጠላት እንዳይጥለኝ ጉልበቴን አበርቺ፡፡ #አዝ https://telegram.me/EOTC2921 የኮቲባ ቁጣ ዛቻ እና ክፋቷ፣ አስተናግዳዋለች ምድር አፏን ከፍታ፣ በአንቺ ላይ ያመጹት በቁጣው ጠፍተዋል፣ ከጥቅልሉ መዝገብ ከእርሱ ተሽረዋል፡፡ #አዝ https://telegram.me/EOTC2921 ለተጠሙት ነፍሳት ያጠጣቸው ጌታ፣ ከጀርባሽ ላይ ሆኖ በዱር ተንገላታ፣ የግብጽን ጣዖታት በግርማው መታቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የአለቆች ጌታቸው፡፡

🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻 🌻የሱፍ አበባ የአምላክ እናት🌻 🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻 👉ጠቢቡ ሰሎሞን በማሕ ፪፥፩‐፪ ላይ በመንፈሰ እግዚአብሔር በመቃኘት የቅድስት ድንግል ማርያምን ንጽሕና በሱፍ አበባ መስሎ ሲያስተምር፡- “አነ ጽጌ ገዳም ጽጌ ደንጐላት ዘውስተ ቈላት፤ ወከመ ጽጌ ደንጐላት በማእከለ አሥዋክ ከማሁ አንቲኒ እንተ ኀቤየ በማእከለ አዋልድ” (እኔ የዱር ጽጌረዳ፤ የቈላም የሱፍ አበባ ነኝ፤ በእሾኽ መኻከል እንዳለ የሱፍ አበባ እንዲኹ ወዳጄ በቆነዣዥት መኻከል ነሽ) በማለት የተናገረውን ምሳሌያዊ ኀይለ ቃል ሊቁ በድርሰቱ ላይ፡- “ወከመ ጽጌ ደንጐላት በማእከለ አሥዋክ ከማሃ አንቲኒ ኦ ወላዲተ አምላክ” (በእሾኽ መኻከል እንዳለ የሱፍ አበባ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ አንቺም እንደ ርሷ ነሽ) ሲል ያቺ ሰሎሞን የተናገረላት የሱፍ አበባ የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ መኾኗን ተርጒሞታል፡፡ 👉ይኸውም ይቺ የሱፍ አበባ እሾኽ ዙሪያዋን ከቧት ሳለ በሾኽ መኻከል እንደምታብብ እንደምታፈራ ቅድስት ድንግል ማርያምም ኀጢአት እንደ እሾኽ በከበባቸው በአይሁድ መኻከል ሳለች ብቻዋን ከኀልዮ (ከማሰብ)፣ ከነቢብ (ከመናገር)፣ ከገቢር (ከመሥራት) ኀጢአት ተጠብቃ በሃይማኖት፣ በምግባር፣ በንጽሕና፣ በቅድስና፣ በድንግልና ጸንታ የሕይወት ፍሬ ክርስቶስን አብባ አፍርታ ተገኝታለችና ነው፡፡ 👉አባ ጊዮርጊስም ይኽነን የሰሎሞንን ቃል በአርጋኖን መጽሐፉ ሲተረጒመው፡- “ጽጌ ደንጐላት እንከ እሰምየኪ እስመ ጽጌ ደንጐላት ዕዉድ በአሥዋክ... ” (በሱፍ ዕንጨት እመስልሻለኊ፤ የሱፍ አበባ በእሾኽ የተከበበ ነውና፤ አንቺም ከዳዊት ግንድ (ባሕርይ) የተገኘች የንጽሕት አበባ ቅንጣት ኾነሽ ሳለ፤ በጒስቁልናቸው የሚመኩ አንገታቸውን የሚያደነድኑ በዐይኖቻቸው የሚጠቃቀሱ በእግሮቻቸው የሚያሸበሽቡ የልብሶቻቸውን ዘርፎች የሚጐትቱ የሚዘፍኑትን የቆነዣዥት አለቆች የሚኾኑ የጽዮንን ልጆች እግዚአብሔር ያዋርዳቸዋል ያጐሳቁላቸዋል ብሎ ነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት እንደተናገረባቸው (ኢሳ ፫፥፲፮‐፲፯)፤ አንቺም አንገተ ደንዳኖች በሚኾኑ በዕብራውያን ቆነዣዥት መኻከል እንደተቀመጥሽ) በማለት ግዙፉነ ክሣድ በኾኑ ኀጢአት እንደ እሾኽ በከበባቸው በአይሁድ ልጆች መኻከል ሳለች ርሷ ብቻ በንጽሕና በቅድስና ጸንታ የመገኘቷን ምስጢር ከሰሎሞንና ከኢሳይያስ ቃል በመጥቀስ ተንትኖታል፡፡ 👉ሊቁ ቅዱስ አባ ሕርያቆስም ከዚኽ ምስጢር በመነሣት በቅዳሴው ላይ “ኦ ድንግል አኮ በተላህዮ ዘልህቂ ከመ አዋልደ ዕብራውያን እለ ያገዝፋ ክሣዶን አላ በቅድስና ወበንጽሕ ውስተ ቤተ መቅደስ ነበርኪ” (ድንግል ሆይ አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ እንደ ዕብራውያን ሴቶች ልጆች በዋዛ ያደግሽ አይደለሽም፤ በንጽሕና በቅድስና በቤተ መቅደስ ኖርሽ እንጂ) በማለት ግዙፋነ ክሣድ በኾኑ በዘፈን፣ በቧልት፣ በጨዋታ፣ ኀጢአትን በመሥራት ይኖሩ ከነበሩ ከዕብራውያት ሴቶች ልጆች ተለይታ በቤተ መቅደስ ማደጓን አስተምሯል፡፡ 👉አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታም በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው ይኽነን የሰሎሞንን ቃል ሲያብራሩ:- “ጽጌ ደንጐላ ዘቈላ ወአኮ ዘደደክ ዘጸገይኪ ጽጌ በማእከለ አይሁድ አሥዋክ ተአምረ ድኂን ማርያም ዘልማድኪ ምሂክ መሀክኒ ለምእመንኪ እምጻዕረ ኩነኔ ድሩክ ተአምኖትየ ኢይኩን በበክ” (በእሾኾች አይሁድ መኻከል የደጋ ያይደለ የቈላ የሱፍ አበባን ያበብሽና ልማድሽ መራራት የኾነ የመዳን ምልክት ማርያም፤ ብርቱ ከኾነ ከጭንቅ የቅጣት ፍርድ ታማኝሽን አድኚኝ፤ በአንቺ ምልጃ መታመኔ ከንቱ ኾኖ እንዳይቀር) በማለት በሱፍ አበባ መመሰሏን አጒልተው ተርጒመዋል፡፡ [🌻የሱፍ አበባ የተባልሽ የአምላኬ የክርስቶስ እናት ሆይ ከማያልቀው በረከትሽ ጥቂቱን በእኔ ላይ አሳድሪ አሜን✞✞✞🌻] ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ 🌻💐🌹 #Join us... 🌹💐🌻 #Share #Share #Share #Share ❀✆✞✆✞✆✞✆✞✆✞✆✞✆✞✆❀ 🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻 🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼 👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇 👉 @EOTC2921 👈 👉 @EOTC2921 👈 👉 @EOTC2921 👈 ☝️☝️☝️☝️☝️☝️☝️☝️☝️☝️☝️ 🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼 🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻🌻

❖ “ሰላም ለአርሴማ ሥርጉተ አፍኣ ወውስጥ በምግባር ፍጹም ወበሃይማኖት ስሉጥ አመ ኮነት ሰማዕተ እንበለ ተምያጥ አሕምሞ ሥጋሃ ኢክህሉ አስዋጥ ወጸበለ እግራ ለሐሱ አናብስት መሠጥ” (በፍጹም ምግባርና በፍጹም ሃይማኖት በውስጥና በውጪ ያጌጠች ለኾነች ለአርሴማ ሰላምታ ይገባል፤ ወደ ኋላ ባለመመለስ ሰማዕትን በኾነች ጊዜ ዐለንጎች ሥጋዋን ማሳመም አልቻሉም፤ ነጣቂዎች አናብስትም የእግሯን ዐቧራ ላሱ) የሰማዕቷ የቅድስት አርሴማ ረድኤት በረከት ይደርብን፤ በቃል ኪዳኗ ትጠብቀን፡፡ 🙏✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር🙏 https://telegram.me/EOTC2921

#ሰማዕቷ_ቅድስት_አርሴማ https://telegram.me/EOTC2921 ✔✞ መስከረም 29 ቀን ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ በሰማዕትነት ያረፈችበት እለት ነው፤ እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን የቅድስት አርሴማ እናት አትኖስያ ትባላለች። ልጂ በማጣት ለረዥም ዘመን ታዝን ታለቅስ ነበር። በኃላም እግዚአብሔር ልመናዋን ሰማት። ይህቺን ክብርት ቅድስት ልጅም ሰጣት። ቅድስት አርሴማ ጥር 6 ነው የተወለደችው፣ 15 አመት ሲሆናት ሊያጋቧት አሰቡ፣ እርሷ ግን ይህን አልወደደችም በድንግልና ገዳም ገብታ በተጋድሎ መኖር ጀመረች። ከዚያም በኃላ እንዲህ ሆነ፤ ከሃዲው ንጉስ ዲዮቅልጢያኖስ ሊያገባት ወደደ። ቅድስት አርሴማ ግን ከደናግሉ ጋር ሸሽታ ወደ አርማኒያ ሄደች። በዚያም በበረሃ ለጥቂት ቀናት ተቀመጠች። በኃላ ላይ ድርጣድስ የሚባል አገር ገዢ በበረሃ እንደሚኖሩ ሰማ፤ ወታደሮቹንም ልኮ አስመጣቸው። የቅድስት አርሴማን መልክ በተመለከተ ጊዜ ፈዞ ደንዝዞ ቀረ፤ የፊቷ ውበት እፁብ ድንቅ ግርማዋ የሚያስደንቅ ልብ የሚያርድ ነበረና ስለዚህም ሊያሰቃያት አልደፈረም። በእንክብካቤ በሰገነት ላይ አኖራት። ሌሎቹን ግን ለጣኦት እንዲሰግዱ ገፋፋቸው። ቅድስት አርሴማ እኔንም አሰቃየኝ እያለች አምርራ ታለቅስ ነበር። ድርጣድስ ብዙ ጊዜ ሊሸነግላት ወደደ፤ እርሷ ግን ትዘልፈው ጣኦቱንም ትረግም ነበር። እርሷ ፀንታ ደናግሉን ታፀና ነበር፤ ትመክራቸው ታረጋጋቸው ነበር። ድርጣድስ ሽንገላው እንደማያዋጣው ባወቀ ጊዜ ማሰቃየት ጀመረ። https://telegram.me/EOTC2921 ✔✞ በመጨረሻም ከብዙ ስቃይ በሗላ መስከረም 29 ቀን አንገቷን ቆርጧት ከእርሷ ጋር 27 ሰማዕታት አብረው ተሰይፈዋል። በአገራችን በስሟ ሰሜን ወሎ ውስጥ ሲሪንቃ ቅድስት አርሴማ የሚያስገርም ገዳም አላት። በዚህ ገዳም 7 ቀን ብቻ ሱባኤ የሚገባ የልቡን መሻት ትፈፅምለታለች። በመዲናችን አድስ አበባም የቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያኖች አሉ። እንዲሁም አስኮ ቃሎ ተራራ ላይ የሚያስገርም ቤተ ክርስቲያን አላት። ይህንን የቃሎ ተራራ ሲወጡ ዝቋላ ትዝ ይላል። መስከረም 29 በደማቅ ተቦተ ህጉ ወጥቶ ተከብሮ ይውላል። ታህሳስ 6 ፍልሰተ አጽሟ ነው። #የቅድስት_አርሴማ_ተጋድሎ_በቀደምት_የኢትዮጵያ_ሊቃውንት፦ https://telegram.me/EOTC2921 ❖ ስለ ቅድስት አርሴማ ተጋድሎ ቀደምት የኢትዮጵያ ሊቃውንት መስክረዋል፤ ሥዕላቷን ሥለዋል፤ መልክእ ደርሰውላታል፤ ገድሏን አጽፈዋል፤ የዚኽች ቅድስት ሰማዕት አባቷ ቴዎድሮስ እናቷ አትኖስያና ይባላሉ፤ በብፅዐት ያገኟት ልጅ በመኾናቸው በተወለደች በሦስት ዓመቷ በእመቤታችን ስም በታነጸች ቤተ ክርስቲያን አድጋለች፤ ሊቁ እንደጠቀሰው እጅግ መልከ መልካም ነበረች ራሷንም በድንግልና ሕይወት ለክርስቶስ ለይታ ነበር፤ በጊዜው ከሓዲው ድዮቅልጥያኖስ መልኳ ውብ የኾነች ድንግል ሊያገባ ፈልጎ ቆንጆ መርጠው ያመጡለት ዘንድ አገልጋዮቹን አዘዛቸው፡፡ ❖ እነርሱም በፍለጋቸው በሮሜ አገር ባለች ቤተ ክርስቲያን ቅድስት አርሴማን በማግኘት ሥዕሏን ሥለው ለንጉሡ ላኩለት፡፡ ርሱም በእጅጉ ተደስቶ እንዲያመጧት በማዘዝ ወደ ሰርጉም እንዲመጡ ለመኳንንቱ ላከ፡፡ ❖ ርሷና ዐብረዋት የነበሩትም ደናግል ይኽነን በሰሙ ጊዜ በማዘን ድንግልናቸውን ይጠብቅላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር በመለመን ከሮም ተነሥተው በስዉር የንጉሥ ድርጣድስ ግዛት ወደነበረችው ወደ አርመን ሸሽተው ኼደዋል፡፡ ቅድስት አርሴማም ወደ አርመንያ ሀገር በገባች ጊዜ ከሓድያኑ በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትን የሚያምኑትን ክርስቲያኖችን ላይ መከራን ሲያጸኑባቸው ተመለከተችና “እኔ በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትን የማምን ክርስቲያን ነኝ” በማለት መሰከረች፡፡ ❖ የመልኳን ደም ግባትም በማየት ድርጣድስም ለራሱ ስለተመኛት አምልኮቷን እንድትተው ብዙ ሽንገላን ሊሸነግሏት ቢሞክሩም አልኾነላቸውም፤ ከዚያም ፈርታ ትክዳለች ብለው በማሰብ ክርስቲያኖች ለአናብስት ወደሚጣሉበት አደባባይ በመውሰድ የተራቡ አናብስትን ሲለቅቋቸው በጸሎቷ ኀይል አናብስቱ ወደ ንጉሡ ወታደሮች በመወርወር ብዙዎችን ገድለዋል፤ ከዚያም ከሥሯ ተንበርክከው ሰግደውላታል፡፡ ❖ ንጉሡ በዚኽ ባይኾንለት በክድ ለጣዖታቱ እንድትሰግድ አሳስሮ አማልክቱ ወዳሉበት ቤተ ጣዖት ሲወስዳት፤ በመስቀል ምልክት ብታማትብ በጣዖታቱ ላይ ዐድረው ሰዎችን የሚያስቱ አጋንንት እየጮኹ ሲወጡ ጣዖታቱ በመላ እየተሰባበሩ ወድቀዋል፤ ከዚያም በረኀብ ለመቅጣት ወደ እስር ቤት ቢያኖሯት መልአኩ ኅብስትን እንደ ኤልያስ መግቧታል፡፡ ❖ ከዚያም ንጉሡ ወዳለበት እየጐተቱ ወሰዷት፤ “ወተንሥአ ንጉሥ እማዕከለ ዐውድ ወአኀዛ ከመ ያብኣ ውስተ ጽርሑ ለአርሴማ ድንግል ወሶቤሃ ኀደረ ኀይለ እግዚአብሔር ላዕለ አርሴማ ቅድስት ወገደፈቶ ውስተ ምድር” ይላል፤ ንጉሡ ይዞ ወደ እልፍኙ ሊያስገባት ከአደባባይ ተነሥቶ ድንግል አርሴማን በያዛት ጊዜ፤ እላይዋ ላይ ባደረው የእግዚአብሔር ኀይል በምድር ላይ ጣለችው። ❖ ያን ጊዜ በዐፍረት ኾኖ ራሷ ይቈረጥ ዘንድ አዘዘ፤ ከዚያም የክብር ባለቤት ጌታችን ተገልጾ ስሟን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳንን ከገባላት በኋላ መስከረም ፳፱ በ፪፻፺ ዓ.ም አንገቷን ተቈርጣ የሰማዕታትን አክሊል ተቀዳጅታለችና፤ በስሟም ቤተ ክርስቲያን ታንጾ ታኅሣሥ ፮ ቅዳሴ ቤቷ ሲከበር፤ የከበረ ሰውነቷ ዛሬ ድረስ በአርመን አለ፡፡ ❖ በኢትዮጵያና በመላው ዓለም ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በስሟ እየታነጹ ከክርስቶስ አምላኳ በተቀበለችው ቃል ኪዳንም ብዙ ሕሙማን እየተፈወሱ በረከቷን እያገኘን እንገኛለን፡፡ በረከቷን ለመሳተፍ በባሕር ማዶ የሰማዕቷን ገድል ከተረጎምኩባቸው ቦታዎች መኻከል በደቡብ አፍሪካ በረስተንበርግ፤ በዱባይ፣ በአውሮፓ በስዊድን በማልታና ስኮትላንድ ግላስኮ ይገኛሉ፨ ❖ ካመሰገኗት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀደምት ሊቃውንት ውስጥ ሊቁ አርከ ሥሉስ እና አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ የሚጠቀሱ ሲኾኑ፦ ❖ ሊቁ አርከ ሥሉስም ይኽነን የቅድስት አርሴማ ተጋድሎ ሲመሰክር፡- “በጾታ ኅሩያን ዕደው እንዘ ተኀብሪ ጾታ እንበለ ትፍርሂ ምንተ ብልኀተ ኲያንው ወሰይፍ ልሳነ መንታ ዘፈጸምኪ ስምዐ በእንተ ኢየሱስ ንጉሠ ኤፍራታ ሰላም ለኪ አርሴማ ምስለ እምኪ አጋታ ወለደናግል ሰላም ምስሌኪ ዘሞታ” (በተመረጡ ወንዶች ወገንነት ተባብረሽ ኹለት አፍ ያለው ሰይፍንና የጦሮችን ስለትን ምንም ሳትፈሪ የኤፍራታ ንጉሥ ስለሚኾን ስለ ኢየሱስ ምስክርነት የፈጸምሽ አርሴማ ከእናትሽ ከአጋታ ጋር ሰላምታ ላንቺ ይገባል፤ ካንቺ ጋር የሞቱ ለኾኑ ደናግል ሰላምታ ይገባል) በማለት በኅብረት አመስግኗቸዋል፡፡ ❖ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በተአምኆ ቅዱሳን ታላቅ መጽሐፉ ላይ፦ “ሰላም ለአርሴማ ቅድስት ከመ በቀልት ዘይመስል ቆማ ወዘከለላ ዘመንፈስ ግርማ ዘፈጸመት ገድላ በጻማ ወበመንግሥተ ሰማይ ዐቢይ ስማ”፡፡ (ገድሏን በሥቃይ የፈጸመች፤ የመንፈስ ግርማ የጋረዳትና ቊመቷ እንደ ዘንባባ የሚመስል ለምትኾን ለቅድስት አርሴማ ሰላምታ ይገባል፤ በመንግሥተ ሰማይም ስሟ ታላቅ ነው) በማለት ያወድሳታል፨ ❖ እኔም በዚኽ ጽሑፌ ላይ ሊቁ አርከ ሥሉስ ለቅድስት ጣጡስ ሰማዕት በሰጣት ምስጋና ለሰማዕቷ አርሴማ በመስጠት አመስግኜያት ጽሑፌን አበቃለሁ፨

✤✣✤#ገዳመ_ጽጌ_ድግል_፤ የአቡነ ጽጌ ድንግል ገዳም በ14ኛው ክፍለ ዘመን የተመሠረተው በታላቁ አባት በአቡነ ጽጌ ድንግል ሲኾን፤ እኝህ ታላቅ አባት እጅግ ሰፊ ኾኖ የሚያምረውንና ዕጹብ ድንቅ የሚያሰኘውን ባለሦስት ክፍል (ቅኔ ማሕሌት፣ ቅድስትና መቅደስ) ያለውን የገዳመ ጽጌን ውቅር ዋሻ ቤተክርስቲያን ያነጹ፣ ከሰባቱ ቅዱሳን ዘጋሥጫ (አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ዘደብረ ጎል፥ አቡነ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፥ አቡነ ያዕቆብ ዘቀዳሚት ግሸን ደብረ ከርቤ፥ አቡነ ገብረ እንድርያስ ዘደብረ ቆዘት፥ አቡነ ዘካርያስ ዘወለቃ፥ አቡነ ዮሴፍ ዘወለቃ፥ የዝቋላው አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዘምስካበ ቅዱሳን ገዘዛ) አንዱ የኾኑና የወርቃማ ዘመን ወርቃማ ደራሲ የኾኑ በዚህም በቤተክርስቲያናችን ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ የምንጸልይበትንና የምናመሰግንበትን ማሕሌተ ጽጌን ባለ ፭ት አርኬና እንደ መዝሙረ ዳዊት በ፻፶ መዝሙር ልክ አድርገው የደረሱና ጸሐፊያቸው በኾኑ ጓደኛቸው አቡነ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ አጽፈው ለትውልድ ያስተላለፉ፤ እንዲሁም ሰቈቃወ ድንግልን ከጓደኛቸው አቡነ ገብረ ኢየሱስ ዘገዳመ መጕና ጋር አብረው የደረሱ ቅዱስ አባት ናቸው፤ እንዲሁም በዘመናቸው ከነበሩት ከጓደኛቸው ከታላቁ አባት አቡነ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ጋር ብዙ ገቢረ ተዓምራትን የሠሩ (የወለቃ ወንዝ ድልድይን ጨምሮ ያነጹ)፥ አሁንም ብዙ ገቢረ ተዓምራትን የሚሠሩ አባት ናቸው፡፡ ገዳሙ የሚገኘው በደቡብ ወሎ ሃገረ ስብከት፥ በወግዲ ወረዳ ልዩ ስሙ ደብረ (ገዳመ) ጽጌ ጫቀታ በሚባል ቦታ፤ ለዐባይ ወንዝ ገባሮች ከኾኑትና በበረሀ ውስጥ ከሚጓዙት አንዱ በኾነው በወለቃ ወንዝ አቅራቢያ ነው፡፡ ገዳሙ ለታላቁ አባት በተሰጠው ቃል ኪዳን መሠረትም አኹንም ድረስ ፈውሰ ሥጋ፥ ፈውሰ ነፍስ እየሰጠ ይገኛል፤ የገዳሙ ፍየሎችና ከብቶችም በአካባቢው ከሚገኙት ነብሮች ጋር አብረው ያለምንም አደጋ ይኖራሉ፡፡ ገዳሙ በግራኝ መሐመድ ወረራ ወቅት 500 መነኰሳት በሰማዕትነት የተሰየፉበት ሲኾን ከዚህ ጀምሮ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ተዘግቶ ቆይቶ በልዑል ራስ ካሣ ኀይሉ አማካይነት ተከፍቶ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፤ በድጋሚ በጣሊያን ወረራ ወቅት አደጋ ደርሶበታል፤ በደርግ ዘመንም የገዳሙ 84 ጋሻ መሬት ስለተወሰደበት እንደገና እስከ ከ1995ዓ.ም. ገዳሙ ዘግቷል፤ ነገር ግን በ1995ዓ.ም. በበጎ አድራጊ ምዕመናን ድጋሚ ሊከፈት ችሏል፡፡ ማሕሌተ ጽጌ የተደረሰበት ይህ ገዳም እስከ 2008ዓ.ም. ማሕሌቱ ሳይቆምበት ቆይቶ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ ማሕሌቱ እየተቆመ ይገኛል፡፡ ለበርካታ ዓመታት የሊቁ የአባ ጽጌ ድንግል በዓለ ዕረፍት መስከረም 27 መከበር አቁሞም ነበር፤ እንደ አምላከ አበው ፈቃድ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ክብረ በዓሉ በገዳም ሥርዐት እየተከበረ ይገኛል፡፡ ወደ ገዳሙ ለመሄድ ለሚፈለጉ ምዕመናን፤ (በተለይ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ የተጓዛችሁ በዛው ለመሄድ ቅርብ ነው፡፡) 1ኛ) ከደሴ ከተማ ለምትነሱ ወግዲ በሚል መኪና ከተሳፈሩ በኋላ ከተወሰኑ የእግር ጕዞ በኋላ ይገኛል፤ 2ኛ) ከጎጃም በመካነ ሰላም ለምትነሱ ወግዲ በሚል መኪና ከተሳፈሩ በኋላ ከተወሰኑ የእግር ጕዞ በኋላ ይገኛል፤ 3ኛ) በመርሐ ቤቴ በሚዳ ለምትነሱ ወግዲ በሚል መኪና ከተሳፈሩ በኋላ ከተወሰኑ የእግር ጕዞ በኋላ ይገኛል፡፡ † በዚሁ አጋጣሚ የታለቁ ሊቅ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በዓለ ጽንሰታቸውም ጥቅምት 3 ስለሚከበር አብሮ ማክበር ይቻላል፡፡ /ከዋልድባ ዋሊ ገጽ የተወሰደ/ (የገዳሙን ኹኔታ የዘገበልንን ወንድማችንን አምላከ አባ ጽጌ ድንግል ወጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ይስጥልን፤ በረድኤት በበረከት ቅዱሳን ሊቃውንቱ ይጎብኙልን፡፡)

✤✤#መስከረም_27_ሊቁ_አባ_ጽጌ_ድንግል (#ጽጌ_ብርሃን)፤ #የማኅሌተ_ጽጌ_ደራሲ¬ ✤✤ የተወለደው በ14ኛው መ.ክ.ዘ. በሰሜን ሸዋ በይፋት(ዊፋት) አውራጃ ውስጥ ሲሆን፤ ነገዱ ታቦተ ጽዮንን ይዘው ከመጡት ከ318 ሌዋውያን ነው፡፡ የቀድሞ እምነቱ አይሁዳዊ ሲኾን ስሙም ዮሐኒ ይባል ነበር፡፡ በወጣትነት ዕድሜው አውሬ ለማደን በይፋት አውራጃ በምትገኝ ልዩ ስሟ ገዳመ ደነስ ወደሚባል ዱር (ጫካ) ሄደ፤ በጫካዋ ውስጥም ፊቷ በጽጌረዳ አበባ የተከበበና ያጌጠ፣ እጅግም ደስ የምታሰኝ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕል አይቶ በሥዕሏ ውበት እየተደነቀ ሲመለከት እንደ እርሱ ያልተጠመቀ አይሁዳዊ ጓደኛው መጥቶ፣ ‹‹ምን እየፈለግህ ነው? የክርስቲያኖችን ሥዕል ነውን?›› ብሎ ለድንግል ማርያም ምስጋና ይግባትና በያዘው በትር ሥዕሏን ሲመታት ወዲያው ተቀሥፎ ሞተ፣ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሩፋኤል በነጭ ወፍ ተመስሎ አንድ መነኵሴ እሰኪመጣ ድረስ፣ ይህችን ሥዕል ጠብቃት ብሎ በሰው አነጋገር ነግሮት ተሠወረ፣ አቡነ ዜና ማርቆስ ደብረ ብስራት ከሚባለው ገዳሙ ወደ ይፋት መጥቶ ከነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት በምዕ. 11፥1 ‹‹ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ (ከዕሤይ ግንድ በትር ትወጣለች /ትገኛለች/ ከሥሩም ቁጥቋጦ ያፈራል››) እያለ ሲያነብ አባ ጽጌ ድንግል በሰማ ጊዜ አባቶቼ አይሁድ የነቢያትን ትንቢት ንባቡን አስተምረውኛል አውቀዋለሁ፤ ትርጕሙን ግን አላውቀውምና ተርጕምልኝ አለው፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስም ሲተረጕምለት እንዲህ አለ፤ ፠ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ፣ የሚለው ከእሴይ ነገድ የሕይወት በትር የኾነች ድንግል ማርያም ትወለዳለች፡፡ ፠ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ የሚለው ንባብ ደግሞ፤ ከእመቤታችን ጌታችን በድንግልና ይወለዳል፤ ጌታችንም ተወልዶ ትንቢቱ ተፈጽሟል ብሎ ተረጐመለት፡፡ ኢሳ. 7፥14፣ ማቴ. 18፥24፡፡ ይህ ሰውም (አባ ጽጌ ድንግልም) በዚህ ትርጕም ደስ ተሰኝቶ አባት ሆይ በመልካም ሁኔታ ተረጐምከው አለውና፣ ሥዕሏ ወዳለችበት ቦታ ወስዶ ታሪኩ ከላይ የተገለጸውን ሁሉ ነገረው፣ አቡነ ዜና ማርቆስም ከሥዕሏ የተደረገውን ተአምር ሰምቶ፣ እጅግ ደስ አለውና አስተምሮ አጥምቆ #ጽጌ_ብርሃን_ ብሎ ሰየመው፡፡ ከዚህ በኋላ ሥዕሏን ከገዳመ ደንስ ደብረ ብሥራት ወደሚባል ገዳሙ ወስዶ በዘመነ ጽጌ ጥቅምት አንድ ቀን በክብር አስቀመጣት የምትከብርትንም ቀን ጥቅምት 3 እና ሰኔ 8 ቀን አደረገ፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስም ጽጌ ብርሃንን ለመዓርገ ምንኵስና አበቃው፤ አባ ጽጌ ድንግል ምንም እንኳን አስቀድሞ ብሉያትን ቢማርም ከአቡነ ዜና ማርቆስ ዘንድ ብሉያትንና ሐዲሳትን ንባባቸውን ከነትርጓሜያቸው ተማረ፡፡ አባ ጽጌ ድንግል ከሰባቱ ቅዱሳን ዘጋሥጫ (አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ዘደብረ ጎል፥ አቡነ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፥ አቡነ ያዕቆብ ዘቀዳሚት ግሸን ደብረ ከርቤ፥ አቡነ ገብረ እንድርያስ ዘደብረ ቆዘት፥ አቡነ ዘካርያስ ዘወለቃ፥ አቡነ ዮሴፍ ዘወለቃ) አንዱ የኾኑና ገባሬ ተዓምራት ወመንክራት የኾኑ የወርቃማ ዘመን ወርቃማ ደራሲ ናቸው፡፡ በወርቃማ ደራሲነታቸው ማኅሌተ ጽጌንና ሰቈቃወ ድንግልን ደርሰዋል፡፡ ሊቁ ሲደርሱም ዋርማ (ሽክና) ሙሉ እንባን እያነቡ ባነቡት እንባ ቀለም እየበጠበጡ እርሳቸው እየደረሱ፤ ጸሓፊያቸውና ጓደኛቸው የኾኑት አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ ደግሞ እየጻፉ ነው፡፡ #ማኅሌተ_ጽጌ_ እመቤታችንንና ፈጣሪ ልጇን በጎ፥ በጎ መዓዛ ባላቸው አበባዎችና ፍሬዎች እየመሰለ የሚያመሰግን ሲኾን፣ በአባቷ በዳዊት መዝሙር መጠን 150 አድርጎ ደረሶታል፤ ፍሬ ከአበባ አበባም ከፍሬ እንደሚገኝ ኹሉ በማኅሌተ ጽጌ እመቤታችንን በአበባ፥ ጌታችን በፍሬ፤ ወይም እመቤታችንን በፍሬ፥ ጌታችንን በአበባ እየመሰለ እጅግ አስደናቂ የሆኑ ታሪኮችን እያጣቀሰ ደርሶታል፡፡ ዘመነ ጽጌ ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ድረስ 40 ቀናት ሲኾን በዚህ ወቅት የሚጾመው ጾም ጾመ ጽጌ ሲባል ጾሙ የፈቃድ ነው፡፡ #ሰቈቃወ_ድንግል፤ ማለት እመቤታችን ከልጇ ከመድኀኔዓለም፥ ከአረጋዊ ዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር በስደቷ ወቅት ያየችውን መከራ፥ ልቅሶ፥ ዋይታ የሚዘከርበት የማኅሌተ ጽጌ አርኬ ነው፡፡ የሰቈቃወ ድንግልን ደራሲ በተመለከተ አባ ጽጌ ድንግል ደረሱት የሚሉ አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አባ ገብረ ኢየሱስ ዘገዳመ መጕና ወይም /አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ/ ወይም /አባ አርከ ሥሉስ/ ነው የደረሱት የሚሉም አሉ፡፡ በገቢረ ተዓምራት አድራጊነታቸውም እንደ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአየር ላይ የሚጓጓዙት በክነፈ ነፋስ፥ በሠረገላ እሳት፥ በደመናት፥ በመባርቅትና በነጐድጓድ ሲኾን በምድር ላይ ደግሞ በአንበሳና በነብር ተጭነው እንዲሄዱ ጸጋው ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ በዘመናቸው ከነበሩት ከጓደኛቸው ከታላቁ አባት አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ጋር ብዙ ገቢረ ተዓምራትን የሠሩ ሲኾን የእግዜር ድልድይ (የወለቃ ወንዝ ድልድይን) ያነጹ፥ ብዙ ድውያንና ሙታንን አብረው ያስነሱ ናቸው፤ አሁንም ብዙ ገቢረ ተዓምራትን የሚሠሩ አባትም ናቸው፡፡ ገዳሙ የተመሠረተው በአባ ጽጌ ድንግል ሲኾን፤ እጅግ ሰፊ ኾኖ የሚያምረና ዕጹብ ድንቅ የሚያሰኝ ባለአራት ክፍል (ቅኔ ማኅሌት፣ ቅድስትና መቅደስ፣ አጽመ ቅዱሳን ማረፊያ) ያለው ነው፡፡ የሚገኘውም በደቡብ ወሎ ወግዲ ወረዳ ነው፡፡ /ምንጭ ገዳሙ ካሳተመው ታሪክና ከቀ.ደ.ሰ. መድኀኔ ዓለምና ደ.ት.ቅ.ገብርኤል ፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሰሌዳ መጽሔት፡፡/ /የቀ.ደ.ሰ. መድኀኔ ዓለምና ደ.ት.ቅ.ገብርኤል ፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት፡፡/

#አበው_ስለ_እመቤታችን ✔"አምላክ ከንጉሥ ሔሮድስ ሴት ልጅ ቢወለድ ኖሮ አልጋ ወራሽ በሆነና ባልተሰደደ ነበር። እርሱ ግን የድሆች ልጅ የሆነችውን ድንግል መረጠ" አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ✔"ታላቁ ተራራ ሆይ ታናሽዋ ብላቴና የተሸከመችህ ራስህን በሚቻላት መጠን አድርገህላት ነው ፣ ታላቁ እሳት ሆይ ታናሽዋ ብላቴና ተሸክማህ ያልተቃጠለችው ኃይልን ትችል ዘንድ አጽንተሃት ነው " ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ✔"ይህ ዓለም የእግዚአብሔርን ልጅ በቀጥታ ከእግዚአብሔር አብ እጅ ለመቀበል የተገባ ሆኖ ስላልተገኘ ፣ ዓለም ከእርስዋ ይቀበል ዘንድ አንድያ ልጁን ለድንግል ማርያም እናት ትሆነው ዘንድ ሠጣት" ቅዱስ አውግስጢኖስ ✔"ሔሮድስ የማይያዘውን ይይዝ ዘንድ ተነሣ ፣ ዓውሎ ነፋስንም በቤቱ አስገብቶ ሊዘጋ ታገለ" አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ✔"ጌታ ሆይ እናትህን ማን ብለን እንጥራት? እናት ብቻ እንዳንላት ድንግል ሆና አገኘናት ፣ ድንግል እንዳንላት ልጅ ታቅፋ አየናት። ጌታ ሆይ እናትህን ለመጥራት እንዲህ የሚያስቸግር ከሆነ አንተን ከቶ ምን ብለን እንጠራሃለን??" ቅዱስ ኤፍሬም ✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ ለጓደኞቻችን #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞ ╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮ @EOTC2921 ╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯

ወርኃ ጽጌ - (ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6) እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕግና ስርአት መሰረት ከመስከረም 26 ቀን እስከ ሕዳር 6 ቀን ያለው 40 ቀን የእመቤታችን ና የልጇን ስደት በማሰብ ወርኃ ጽጌን (ዘመነ ጽጌን) ታከብራለች፡፡ ይህ 40 ቀን የእመቤታችንና የጌታ ስደት የሚታሰብበት ዘመን ነው፡፡ ወቅቱ የአበባና የፍሬ ወቅት በመሆኑ እመቤታችን በአበባ ጌታን በፍሬ እየተመሰሉ ጌታችን በአምልኮት እመቤታችን በፈጣሪ እናትነቷ በተለየ ምስጋና ይመሰገናሉ ፡፡ በዚህ በወርኃ ጽጌ (በዘመነ ጽጌ) የሚጾሙ ክርስቲያኖች ሲኖሩ ጾሙን መንፈሳውያን ሰዎች ሳይታዘዙ በራሳቸው ፈቃድ የሚጾሙት ጾም በመሆኑ (የፈቃድ) የትሩፋት ጾም ይባላል፡፡ በቀኖና ቤተክርስቲያን ከታዘዙት ከ7ቱ አጽዋማት ውጪ የሆነ ትርፍ ጾም ማለት ነው፡፡ ከታዘዘው አትርፎ የጾመ ሰው የመጾሙን ዋጋ ያገኛል፡፡ ብዙ መንፈሳዊ ሥራ የሰራ ሰው ብዙ ክብር እንደሚያገኝ መጽሐፍ ይናገራልና፡፡ ‘’እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ሐጢአትዋ ተሰርዮላታል፡፡ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል’’ (ሉቃ. 7፡47) እንዲል፡፡ የጽጌን ጾም የሚጾሙ ሰዎች በክብርም ከእመቤታችን ጋር ይተባበራሉ፡፡ ነገር ግን የጽጌን ጾም የሚጾሙ ሰዎች ለመመጻደቅ መጾም የለባቸውም፡፡ የማይጾሙ ሰዎችንም መንቀፍና መክሰስ የለባቸውም፡፡ የጽጌ ጾም እንዲጾም በቀኖና ቤተክርስቲያን ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ተደርጎ ስላልተወሰነ የማይጾሙ ሰዎች ሕገ ጾምን እንዳፈረሱ አድርጎ መውሰድ ስሕተት ነው፡፡ ይልቁንም የሚጾሙ ሰዎች ቢችሉ መጾማቸው እንዳይታወቅባቸው ቢያደርጉ የተሻለ ነው፡፡ "ስትጾሙ እንደግብዞች አትጠውልጉ" (ማቴ. 6፥16) የተባለው ለዚህ ዓይነቱ ጾም ነው፡፡ ✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንንለጓደኞቻችን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞ ╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮ @EOTC2921 ╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯

........... #ትዕዛዝ_ለቄሱ! .......... #እናንተ የተወደዳችሁ የቤተክርስትያን ታማኝ አገልጋይ ቀሳውስት ለእናንተ የሚመሆን "ትዕዛዝ ለቄሱ" የምትል ከግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የተገኘች ምክር እነሆ ተተርጉማ ቀርባለች እና በትዕግስት እና በማስተዋል አንብቧት! የእግዚአብሔር ፀጋ ይብዛላችሁ! ........... #ትዕዛዝ_ለቄሱ! .......... #እግዚአብሔርንና ፍጥረትን ሁሉ በፍፁም ልብህ እና በፍፁም ሀሳብህ አፍቅር! #ሰዎችን በጥሩ ምሳሌ እና በሚያፅናና ስብከት አስተምር! #የሀይማኖት መሰረት ከሆነው እና ክርስቲያኖች ከዳኑበት ከእውነተኛው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ካለ እምነት ውጪ አታፈንግጥ! #ጉባኤውን እንደ ተቀጣሪ ሳይሆን እንደ አባት ተንከባከብ! #የታማኝ መጋቢነትን ሽልማት ለማግኘት በእምነት የሆነ አገልግሎት ይኑርህ! #በስራህ ከሚጠፋውና ከሚሻግተው እንጀራህ ይልቅ የማይጠፋውን እና የዘላለም ህይወትን ለማብዛት ለሆነው አገልግሎት ትጋ! #በትህትና ፣ በቅድስና እና በፀጋ በማገልገል ለጉባኤህ ምሳሌ ሁኑ! #በፀጋ እና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሳታቋርጥ እደግ! #እራስህን የኃጢአት ሁሉ ምንጭ ከሆነው ገንዘብን ከማፍቀር አስመልጥ! #መጠጥ መጠጣት እና የስጋ ፈቃዶችን መፈፀም የህሊና ብርሃንን ያጨልምና ሰውን እንደ እንስሳ የምኞቱ ባርያ ስለሚያደርገው ከዚህ ተቆጠጥ! #ቅናት ፣ ፌዝ ፣ ጥላቻን ፣ ሁከት፣ ጠብ ፣ ክፋትን እና ኩራትን ከራስህ ላይ አስወግድ። በዚህም አገልግሎትህ ሳይባክን ዓላማውን ያሳካል! #ግብዝነት ፣ አሉባልታ፣ ወሬ ፣ ፉከራ እና ልታይ ልታይ ማለትን ፈፅመህ አስወግድ። እነዚህ የሚረብሹና ዘግናኝ ድምፆች ስለሆኑ መንፈስ ቅዱስን እና አማኞችን ያሸሻሉ! #በሁለት ገፅ እና ባለሁለት ምላስ ሆኖ በአስመሳይነት መቅረብን፤ እንዲሁም ለማሳመን የሚደረግ የሀሰት ምስክርነትን ፈፅመህ አስወግድ! #ሰዎችን የሚያስፈራና የሚያስጨንቅ አትሁን ነገር ግን ከዚያ ይልቅ ከሁሉ ጋር ተግባቢ እና ትዕግስተኛ ሁን! #እራስን በመቆጣጠር በፅድቅ፣ በምህረት ፣ በትህትና፣ በንፅህና ፣ በፍሬ፣ በመልካም ተፅእኖ፣ በትዕግስትና በፍቅር በእነዚህ በምግባርህ ቢሆን በስራህ ታላቁ መምህርህን ኢየሱስ ክርስቶስን ምሰል! #መፅሐፍ ቅዱስ ፣ የጥንት አባቶች ፅሁፎችን እንዲሁ ቤተክርስቲያን በሁሉም ዘርፍ ያላትን ቀኖናዊ ህጎች ለማጥናት ትጉ ሁን! #የእግዚአብሔርን ጉባኤ፡ በርህራሄ እና በጥበብ በመንከባከብ ወደ ክርስቶስ ደግነት ፣ ርህራሄና ብርታት እንዲያድጉ መምራት አለብህ! #በአክብሮት እና በእውነተኛ ምስክርነት የክርስትና አማኞችን በህይወታቸው ዋና ወደ ሆነው ፀጋ ወደ ፍቅር ማደግን አስተምራቸው። የትእዛዝ ፍጻሜ ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነውና። (1ጢሞ 1:5) #የቤተክርስትያን ምስጢራት ላይ ተጠንቀቁ። ቅዱስ ቁርባን (የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ የሆነ ስጋ እና ደም) እና ሌሎቹን የከበሩ ሀብቶች በገነት እንዳለች ወደ ህይወት ዛፍ እንደምትወስድ መንገድ እያቸው! (ዘፍ 3:24) #ቅዱስ ቁርባንን ንሰሃ ገብተው ለመቀበል ለተዘጋጁ ሰዎች ብቻ አቅርብ ። በልቦናው ክፋትን እንደያዘ እና ሳይገባው ወደ ጌታ ስጋና ደም መጥቶ ከቆረበ በኃጥያቱ እና በፍርዱ ከእርሱ ጋር ተካፋይ ትሆናለህ! #በመንፈሳዊ ህይወት ጥሩ ልምድ ያላቸውና በዕድሜ የገፉ የንሰሃ አባት ይኑርህ። የአንድ ቀን ልምድ እንኳ ብዙ ነውና ከእሳቸው ምክር እና መመርያዎችን ተቀበል! #አንዱ የጉባኤ አባል በኃጢአት ቢታመም ከበሽታው እንዲድን እና መንፈሳዊ ጤንነቱ እስኪመለስ መንከባከብ አለብህ! #እንደዚህ ካደረክ ከእግዚአብሔር ስለፍቅርህ እና ስለአገልግሎትህ ብዙ እጥፍ ሽልማትን ትቀበላለህ። የጌታንም አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ የሚለውን የተወደደ ድምፅ ትሰማላችሁ። (ማቲ 25:21) ❀✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞❀ ©Mahiberekidusan

#ከተዓምረ_ተክለሃይማኖት_በጥቂቱ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን፡፡ በረከታቸው ይደርብንና አቡነ ተክለሃይማኖት በዛፍ ላይ አድሮ ይመለክ የነበረውን ሰይጣን ከዛፉ ላይ እንዳስወጡትና እንዳጠፉት የሚናገር ተአምር ይህ ነው፦ - ‹‹… አቡነ ተክለሃይማኖት ወደ ከተታ አውራጃ በደረሰ ጊዜ የዚያች አገር ሰዎች እንደ እንስሳ ሆነው አገኛቸው። እርሱም "ምን ታመልካላችሁ?" አላቸው። ሰዎቹም የምናመልከው የምንሰግድለት ታላቅ ዛፍ አለ" አሉት። አባታችንም "በሰገዳችሁለት ጊዜ ምን ይመስላችኋል?" አላቸው። እነርሱም "እኔ ፈጠርኳችሁ ፈጣሪያችሁ እኔ ነኝ" ብሎ ከዛፉ ላይ ቃል ይናገረናል፣ ስለዚህ ነገር እኛም እንሰግድለታለን፣ የወደደውን እንሠዋለታለን" አሉት። አቡነ ተክለሃይማኖትም "እሰግድለት ዘንድ እኔንም ከእናንተ ጋራ ውሰዱኝ" አላቸው። እነርሱም "እሺ ነገ እንወስድሃለን" ብለው በነጋታው ለጣዖቶታቸው የሚሰግድ መስሏቸው አቡነ ተክለሃይማኖትን ከእነርሱ ጋራ ወሰዱት። ከዛፉ ዘንድ በደረሱ "እናንተ የዚህች ሀገር ሰዎች ከእኔ ሥራ ልዩ የሆነ ሰው ለምን አመጣችሁብኝ? ይኸውም በመካከችሁ የሚሄድ ተክለሃይማኖት ነው..." እያለ በዛፏ ላይ ያደረ ሰይጣን ጮኸ። አባታችንም ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ወደፈጣሪው ጸለየ። "...አቤቱ በፍጥረትህ ላይ ሰይጣን የሚሠራውን ተንኮል ተመልከት! ሥነ ፍጥረትህን ያጠፋ ዘንድ ይህን ጠላት እንዲሰለጥን አትተወው፣ ይህን ትዕቢተኛ ሰይጣን በእኔ እጅ በሕዝቡ ፊት ታዋርደው ዘንድ አቤቱ እለምንሃለሁ..." እያለ ጸለየ። - ‹‹…ጸሎቱንም ከጨረሰ በኋላ (ሰይጣን አድሮባት በሰዎች ዘንድ ትመለክ ወደነበረችው) ዛፍ ተመልሶ ‹ሰይጣን በአንቺ አድሮ እየተናገረ ሕዝቡን የሚያስትብሽ አንቺ ዛፍ እኔ በምሰግድለት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሻለሁ ሰዎቹ ሁሉ የፈጣሪዬን ኃይል ያዩ ዘንድ ከሥርሽ ተነቅለሽ ወደኔ ነይ› አላት፡፡ በውስጧ አድሮ የነበረውንም ሰይጣን ‹አንተ ቀድሞ እንዳሳትካቸው ዛሬም ጉስቁልናህን ያዩ ዘንድ የዚህችን ሀገር ሰዎች ‹እኔ ቀድሞ በሐሰት አስቻችኋለሁና እንግዲህስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከባሕይር ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ለኢየሱስ ክርስቶስ ስገዱ› በላቸው አለው፡፡ ሰይጣንም ‹እነዚህን ሦስቱን ስም መጥራት አይቻለኝም› አለ፡፡ ተክለ ሃይማኖትም ‹የሦስቱን ስም መጥራት የማይቻልህ ከሆነ እናንተንም እኔንም ለፈጠረ ለሰማይና ለምድር ፈጣሪ ስገዱ ተገዙ› በላቸው አለው፡፡ ሰይጣኑም በዚያ እርሱን ሊያመልኩት ለተሰበሰቡት ሰዎች ‹ቀድሞ እኔን በመሰላችሁኝ ጊዜ በሐሰት ሳስታችሁ ኖርኩ፣ እንግዲህስ ሀገራችሁን ትቼላችሁ ሔድኩ፣ ሰማይንና ምድርን፣ እኔንና እናንተን ለፈጠረ ስገዱ ተገዙ፤ የእኔን ሥራ የሚሠራ ግን ከእኔ ጋራ በገሃነም ይኖራል› ብሎ ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ ሔደ፡፡ ሰዎቹም እንደአንድ ልብ ሆነው ‹በተክለ ሃይማኖት አምላክ አምነናል› አሉ፡፡ እርሱም በሦስቱ ስም አጠመቃቸው፡፡›› - የአቡነ ተክለሃይማኖት ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን። (ምንጭ ገድለ አቡነ ተክለሃይማኖት፣ የደብረ ሊባኖስ እትም ገጽ 110፣ የትንሣኤ እትም ገጽ 84፣ የተስፋ ገብረሥላሴ እትም ገጽ 86) ✞ ✞ ✞ ድንጋይም ያምልክ ዕንጨት፣ ዛፍም ያምልክ ወንዝ....ማንም ሰው የፈለገውን ማመን፣ እምነቱንም በተግባር መግለጽ መብቱ ነው። ባመነበት እምነቱ ግን ጽድቅ ወይም ኩነኔ እንዳለበት ማወቅ አለበት። "...ኢሬቻ የምስጋና በዓል ነው...." ምናምን እያሉ ሰውን ማጃጃል አይቻልም። ምንም መቀባባትና መሸፋፈን አያስፈልገውም-ኢሬቻ ለኢትዮጵያ መርገምን የሚያመጣ ምድሪቷንም የሚያረክስ ለአውሬው መሥዋዕት የሚቀርብበት የባዕድ አምልኮ ነው። ኢሬቻ ራሱን የቻለ እምነት ነው-እነርሱ ማመን መብታቸው ነው ነገር ግን ኢሬቻን ከክርስትና ጋር ማገናኘት እጅግ አጸያፊ ነው፣ እግዚአብሔርንም ማስቆጣት ነው። "ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ።" (ኤፌ 4፡30) እንዲል ቅዱሱ መጽሐፍ እግዚአብሔር በኃጢአት ከሆነ ይታገሳል፣ በክህደት ወይም ለእርሱ ብቻ የሚገባውን ክብር ለሌላ ለባዕድ ነገር ሲሰጥበት ግን ትዕግሥት የለውም፣ የቁጣ በትሩን ይመዛል። ትናንት በሀገረ አሜሪካ እያሉ "ታቦት አያስፈልግም፣ አማላጃችን ኢየሱስ ነው፣ ቅዱሳን አያስፈልጉም ..." በማለት በግልጽ ምንፍቅናን ሲያቀረሹ የኖሩት አባ ወልደትንሳኤ (የአሁኑ "አቡነ" በርናባስ) እኽ.... አሁን ደግሞ "ኢሬቻ የምስጋና በዓል ነው...." ሲሉ ተደምጠዋል። ባለጊዜ ነን የሚሉ ሥልጣን ላይ ያሉ ደናቁርት መሪዎችም "የኢሬቻ በዓል የሁላችንም ነው" ብለዋል። - ኢሬቻ ይመለከተኛል የሚል ሁሉ በዓሉን ማክበር እምነቱንም መከተል መብቱ ነው ነገር ግን "የእኛ እምነት የእናተም እምነት ነው ኑ ከኛ ጋር ለዛፍ ለወንዝ ለሜዳ ለተራራ ስገዱ..." ማለት ግን እግዚአብሔርን አስክዶ ለጣዖት ካሰገደው ከናቡከደነፆር አዋጅ ተለይቶ የማይታይ ነው። የኢሬቻን እምነት በበላይነት የሚያስተባብሩት መምለኬ ጣዖታትም "በዓሉ የሁሉም በዓል ስለሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አብሮን ያክብር" እያሉ ነው። እኛ ኦርቶዶክሳውያንስ ከላይ በተአምሩ እንዳየነው በዛፍ ላይ አድሮ ይመለክ የነበረውን ጣዖት ከምድረ ገጽ ያጠፉት የእነ አቡነ ተክለሃይማኖት ልጆች ነን እንጂ እንደዚህ ዓይነቱ መርገምን ከሚያመጣ ምድሪቷንም ከሚያረክስ ለአውሬው መሥዋዕት ከሚቀርብበት የባዕድ አምልኮ ጋር አንተባበርም። "አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት እንዲሆን እንጂ ለእግዚአብሔር እንዳይሠዉ እላለሁ፤ ከአጋንንትም ጋር ማኅበረተኞች እንድትሆኑ አልወድም" (1ኛ ወደ ቆሮ 10፡20) የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ለሁላችንም የተሰጠን የማስጠንቀቂያና የአደራ መልእክት ነዉ። የቅዱሳን አምላክ በምድር ላይ ከሚፈጸመው እርኩሰት ሁሉ ይጠብቀን፡፡ (በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን)

ክርስቶስን መውደድ እንዴት? (በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ) አንድ በጣም የምንወደው እንግዳ ወደ ቤታችን ሲመጣ እጅግ በጣም ከመደሰታችን የተነሣ የምናደርግለት ኹላ ሊጠፋብን ይችላል፡፡ እንደምንወደው፣ እንደናፈቀን እንነግሯለን፡፡ ከዚያም በላይ የሚወደውን እናቀርብለታለን፡፡ ባይኖረን እንኳን ስላላቀረብንለት እናዝናለን፡፡ ያለንን፣ ቤት ያፈራውን ግን እናቀርብለታለን፡፡ ስለምንወደውና ስለናፈቀን ርሱን የሚያስከፋ ነገር ምንም አናደርግም፡፡ ብናደርግም ወዳጃችንን ኾን ብለን ለማስከፋት ብለን የምናደርገው አይደለም፡፡ እንወዷለን የምንለው እንግዳችንን ትተን ሌላ ሥራ አንሠራም፡፡ በቃላት ብቻ እወድኻለኁ ብንለው፥ ነገር ግን በተግባር እንግዳችንን መውደዳችን ባንገልጥ ግን እንግዳችን ያዝንብናል፡፡ ከቃላችን በላይ ተግባራችንን ስለሚያይም እንደምንወደው ብንነግረውም አያምነንም፡፡ መውደድ የቃላት ጨዋታ ሳይኾን በተግባር የሚገለጥ ነውና፡፡ ልክ እንደዚኹ ፍጹም ሰው ኾኖ፣ ባሕሪያችንን ባሕርይ አድርጐ ወደ እኛ የመጣውን ክርስቶስን እንደምንወደው እየተናገርን፥ ነገር ግን በተግባር የምናሳዝነው ከኾነ መውደዳችን ትክክለኛ መውደድ አይደለም፡፡ ብንወደው ኖሮ ልክ ከላይ እንደገለጥነው እንግዳችን የሚበላ ነገርን እናቀርብለታለን፡፡ የክርስቶስ መብሉስ ምንድነው? እርሱ እራሱ እንዲኽ ሲል ነግሮናል፡- “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” /ዮሐ.4፡34/፡፡ ተርቦ ስናየው የሚበላ ነገርን እንስጠው፤ ተጠምቶ ስናየው የሚጠጣ ነገርን እንስጠው፤ ርሱም ይቀበለናል፡፡ የሚቀበልንም ስለሚወደን ነው፤ ከማንወደው ሰው ስጦታን አንቀበልምና፡፡ ስጦታችን ትንሽ ሊኾን ይችላል፤ ነገር ግን አፍቃሪያችን ነውና ስለ ስጦታችን ታናሽነት አልቀበላችኁም አይለንም፡፡ ስጦታችን በርሱ ዘንድ ትልቅ ነው፡፡ በስንፍና አንያዝ እንጂ ስጦታችን አምስት ሳንቲምም ልትኾን ትችላለች፤ ርሱ ግን ወዳጃችን ነውና አምስት ሳንቲም ናት ብሎ ስጦታችንን አያቃልላትም፡፡ እንደ ድልብ ስጦታ አድርጎ አምስት ሳንቲሟንም ይቀበልልናል እንጂ፡፡ ስጦታችንን የሚቀበለው ድኻ ስለኾነ አይደለም፡፡ ስጦታችንን የሚቀበልልን ስለ ስጦታችን ታላቅነት ሳይኾን ስለ ልቡናችን ኀልዮት (intention) ነው፡፡ ስለዚኽ ስንሰጥ ክርስቶስ ስለተቀበለን ትንሽዋንም ስጦታችንን ይቀበል ዘንድ በቤታችን ታዛ ስለገባ ልናመሰግነው ይገባል፡፡ እውነተኛ ሐሴት ማለትም ይኸው ነው፤ በመቀበል ሳይኾን በመስጠት የምናገኘው፡፡ ወደ ቤታችን፣ ወደ ሕይወታችን የመጣው ለእኛ ሲል ነው፡፡ ነፍሱን አሳልፎ ለሞት የሰጠው ለእኛ ሲል ነው፡፡ ፍቅሩ ግን እዚኽ ላይ አላበቃም፡፡ አኹንም እኛ ጋር እየመጣ ነው፡፡ ሐዋርያው “ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን” ብሏል /2ኛ ቆሮ.5፡20/፡፡ ስለዚህ ተርበውና ተጠምተው ወደ እኛ የሚመጡት ሰዎች የክርስቶስ መልእክተኞች ናቸው ማለት ነው፡፡ የንጉሡን መልእክተኛ፡የሚያባርር ታድያ ማን ሞኝ ነው? ነገር ግን ብዙዎቻችን ሞኞች ኾነናል፡፡ የነገሥታት ንጉሥ የክርስቶስ መልእክተኞችን እያባረርናቸው ነውና፡፡ ክርስቶስን እንወድኻለን እያልን በተግባር ግን እናባርረዋለን፡፡ ከዚኽ የበለጠ ምስኪንነት ከወዴት ይገኛል? ክርስቶስን በቃል እወድኻለኁ እያሉ በተግባር ግን ርሱን ማባረር የማይጠቅም ብቻ ሳይኾን የሚጐዳን ጭምር ነው፡፡ እንኪያስ ተወዳጆች ሆይ! ክርስቶስን በቃልም ገቢርም እንውደደው፡፡ በታላቁ እንግዳችን በክርስቶስ ደስ መሰኛታችንን በተግባር እንግለጠው፡፡ ይኽን እንድናደርግ ርስቱንና መንግሥቱንም እንደ ቸርነቱ እንዲያወርሰን እኛን በመውደዱ ወደ እኛ የመጣው ደግሞም የሚመጣው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!! ✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ለጓደኞቻችን #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞ ╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮ @EOTC2921 ╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯

☞= "ፍፁም ፍቅር" = ባልንጀራውን የሚወድ በባልንጀራው ላይ ክፉ ሥራ አይሠራም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።[ ሮሜ 13፥10] ✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝ ☞"ይቅር ባይነት" በምትጸልዩበትም ጊዜ በሰማያት ያለው አባታችሁ በደላችሁን ይቅር እንዲላችሁ በወንድማችሁ ያለውን በደል ይቅር በሉ። እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።" (ማር. 11፥25-26) ✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝ ☞"በጎነት (ቸርነት)" ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፤ ስለሚበድሉአችሁና ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ። ||ማቴ 5፥44|| ክፉ ላደረገባችሁ ክፉ አትመልሱ፤ የሰደባችሁንም አትስደቡ፤ጠላታችሁንም መርቁ፤ በረከትን ትወርሱ ዘንድ ለዚህ ተጠርታችኃልና።[ 1ኛ ጴጥ.3፥9] ✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝ ☞"ትህትና" ለትዕቢተኞች ጥፋት ፈውስ የላትም፤ ክፉ ተክል በውስጣቸው ሥር ሰድዶአልና። (መ.ሲራክ 3፥26) ራሱን ከሁሉ ዝቅ የምያደርግ እርሱ ታላቅ ይሆናል።{ሉቃስ 9፥48} እግዚአብሔርን በመፍራት ለባልንጀራችሁ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ።// ኤፌሶን 5፥21// ትህትናን በያዘ ልቡና ከራሳችሁ ይልቅ ባልንጀራችሁን አክብሩእንጅ አትታበዩ። ትዕቢትን የሚያደርግ በቤቴ መካከል አይኖርም፤ ዐመፃን የሚናገር በፊቴ አይጸናም። መዝ 100 ፥ 7 ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ኦሪትም ነቢያትም የሚያዝዙት ይህ ነውና። [[ማቴ7፥12]] ✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝ "ለራስህ የምትጠላውን ለማንም አታድርግ።" (መ.ጦቢት 4፥15) አቤቱ አባታችን ሆይ! ማስተዋሉን አድለን፤ እኛ ደካሞች ነንና አንተ አጋዥ ሁነን። ከሁሉ አስቀድመን እንለምንሃለንና ሁሉን እንወድ ዘንድ ንፁህ ልብን ስጠንን፤ የይቅርታ ልብንም ስጠን፤ ነፍሳችን ትህትናን ትላበስ ፤ በጎ ምግባርን ይዘን 30,60,100 ያማረ የሕይወት ፍሬ አፍርተን የመንግሥትህ ወራሾች እንድንሆን ፍቀድልን ሁሉ ይቻልሃልና። ክብር ምስጋና ለስምህ ይሁን አሜን። ✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ለጓደኞቻችን #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞ ╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮ @EOTC2921 ╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯

#ፍቅር ከእግዚአብሔር ቤት መራቅ ስትጀምር ፍቅር ካንተ ትርቃለች። ከምታየው ነገር ጋር ሁሉ ትጣላለህ። የምትጣላውም ከሰዎች ጋ ብቻ አይደለም። ካገኘከው ነገር ጋ እና ከራስህም ጋ ጭምር እንጂ። ከራስህ ጋ ተከራክረህ እራስህን መርታት ከማትችልበት ጭንቀት ውስጥ ትወድቃለህና የምትሞትበትን ጊዜ ታመቻቻለህ። እንደ ይሁዳ ታንቆ ለመሞት አልያም እንደ ሌሎቹ በሌላ ምክንያት እራስህን እስከማጥፋት ድረስ ማንነትህን ትጥላለህ። እራስህን እንደ ሰው መቁጠር ከማትችልበት ከባድ ሙግት ውስጥ ትወድቃለህ። በዚህም ከአምላክህ ጋ እና ከሰዎች በፍቅርና በሰላም መኖር አልችል ትላለህ። ሁልጊዜ ከሰዎች ጋ ክርክርና ጥላቻ ይሆንብሀል። ጠላትን የምታጠፋበት ትልቁ መሳሪያ ፍቅር ብቻ መሆኑን ትዘነጋለህ። ይህን የከበሩ እንቁዎች የማይተካከሉትን ልዩ ፀጋ ማጣት ማለት ሰው ሁኖ ተፈጥሮ ሰው ሁኖ አለመገኘት ነው። የሰውነት መመዘኛው ትልቁ ሚዛን ፍቅር ነው። ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮህ ንሀስ ወይንም እንደሚንሿሿ ፅናፅል ሁኛለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ፣ ሚስጥርንም ሁሉና፣ እውቀትንም ሁሉ ባውቅ፣ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፣ ስጋዬን ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። ፍቅር ይታገሳል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፣ ፍቅር አይቀናም፣ ፍቅር አይመካም፣ አይታበይም፣ የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም አይፈልግም፣ አይበሳጭም፣ በደልን አይቆጥርም፣ ከእውነት ጋ ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም። ሁሉን ይታገሳል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል በሁሉ ይፀናል። ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም። እንዲህም ከሆነ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሶስቱ ፀንተው ይኖራሉ። ከነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው። 1ኛ ቆሮ 13፥1-13 ፍቅር በሰዎችና በመላእክት ልሳን ከመናገር በላይ ነው። ድሆችንም ከመመገብና ስጋችንም ለእሳት አሳልፈን ከመስጠት የላቀ ነው። እውነተኛ ፈቅር የሚታገስ፣ ሁሉን የሚያምን፣ ከእውነት ጋ ደስ የሚለው፣ የማይቀና፣ ቸርነት የሚያደርግ የማይመካ፣ በደልን የማይቆጥር፣ ሁሉን ተስፋ የሚያደርግ ነው። ይህንን ፍቅር የምናገኘው ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋ በመሆን ብቻ ነው። ምክንያቱ ፍቅር ከእግዚአብሔር ነው እራሱ እግዚአብሔርም ደግሞ ፍቅር ነውና። ሐዋርያው ዮሃንስ በመልእክቱ እንዲህ ይላል:-ወዳጆቼ ሆይ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ የሚወደው ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለተወለደ እግዚአብሔርም ስለሚያውቅ እርስ በራሳችን እንዋደድ።1ኛ ዮ 4፥7 ለዚህም ነው ፍቅር የሆነውን እግዚአብሔርን ስትርቅ ፍቅር ደግሞ ከአንተ የምትርቀው። ፍቅር የሕግ ሁሉ ፍፃሜ በመሆኗ ትልቁ ገንዘብ ናት። ፍቅርን የምንገልፀው ሰውን እግዚአብሔርን እንዲሁም ሀገርን በመውደድ ነው። እኛም እንደታማኙ አገልጋይ ጌታ የሰጠንን መክሊት ልናተርፍበት ይገባል። በመክሊታችን ትርፋማ ለመሆን ደግም ፍቅር ትልቁን ሚና ይጫወታል። ስለዚህ ፍቅርን ለብሰን ትህትናን ተጫምተን በማስተዋል መጓዝ አለብን። የፍቅር አምላክ ፍቅርን ያድለን! የአብ_ፀጋ_የወልድ_ፍቅር_የመንፈስ_ቅዱስ_አንድነት አይለየን አሜን። ✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንንበየቀኑ አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ለጓደኞቻችን #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞ ╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮ @EOTC2921 ╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯