cookie

Utilizamos cookies para mejorar tu experiencia de navegación. Al hacer clic en "Aceptar todo", aceptas el uso de cookies.

avatar

የአባቶች ምክር

አስተማሪ የሆኑ የአባቶች ምክሮችን ÷መንፈሳዊ ፅሁፎችን፣ መፅሐፍቶችንና ትምህርቶችን የምናጋራበት ቻናል ነው። ሊንኩን በመጫን ቤተሰብ ይሁኑ! የክርስቶስ ሰላም ይብዛላችሁ!@Father_advice

Mostrar más
Publicaciones publicitarias
2 724
Suscriptores
+524 horas
+357 días
+13830 días

Carga de datos en curso...

Tasa de crecimiento de suscriptores

Carga de datos en curso...

+++ ሦስቱ ዛፎች +++ በአንድ ኮረብታ ጫፍ ላይ የተተከሉ ሦስት ዛፎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ዛፎች የወደፊት ተስፋቸውና ሕልማቸው ምን እንደሆነና ምን መሆን እንደሚፈልጉ መወያየት ጀመሩ፡፡     የመጀመሪያው ዛፍ ‹‹ታላቅ ንጉሥ የሚተኛበት አልጋ ለመሆን እመኛለሁ፡፡ ዙሪያዬን በልዩ ቅርጽ ተሠርቼ ሰው ሁሉ እንዲያከብረኝ ዝናዬ እንዲነገር እፈልጋለሁ›› አለ፡፡     ሁለተኛው ዛፍ ይኼን ሲሰማ የራሱን የተለየ ምኞት ተናገረ፡፡ ‹‹እኔ ደግሞ የምጓጓው ታላቅ መርከብ ሆኜ ለመሠራት ነው! በዓለም ላይ እጅግ ዝነኛ የሆኑ ነገሥታት በእኔ ላይ ተሣፍረው እንዲሔዱና ከጥንካሬዬ የተነሣ ሰዎች እኔ ላይ በመሳፈራቸው ያለ ሥጋት እንዲጓዙ ነው የምፈልገው!›› አለ - መርከብ ሆኖ በባሕር ላይ ሲንሳፈፍ በዓይነ ሕሊናው እየታየው፡፡    ሦስተኛው ዛፍ ግን ‹‹ዛፍነቴን ብተው ያንዘፍዝፈኝ›› አለ፡፡ ‹‹እኔ የምፈልገው ከዚሁ ሳልነቃነቅ ረዥም ዛፍ ሆኜ ወደ ላይ ማደግ ነው፡፡ እጅግ ከፍ ብዬ አድጌ የዛፎች ሁሉ ንጉሥ ሆኜ ፣ ለሰማይ እጅግ ቅርብ ሆኜ ሰዎች በእኔ መሰላልነት ወደ ገነት እንዲገቡና እኔን ባዩ ቁጥር ፈጣሪያቸውን እንዲያስታውሱ እፈልጋለሁ›› አለና ምኞቱን ተናገረ፡፡         ይህን ተነጋግረው እንደጨረሱ አናጢዎች ወደ እነዚህ ዛፎች መጡ         አንደኛው አናጢ የንጉሥ አልጋ ለመሆን የሚመኘውን ዛፍ ቀረብ አለና ካየው በኋላ ‹‹ይኼ ዛፍ ጠንካራ ይመስላል ፤ ወስጄ ለቤት ዕቃ ሠሪዎች እሸጠዋለሁ›› አለ፡፡ ይህን የሰማው ዛፍ ‹የንጉሥ አልጋ› ሆኖ የመሠራት ሕልሙ ዕውን እንደሚሆን በመተማመን ፈነደቀ፡፡  አናጢው ወስዶ የሸጠላቸው እንጨት ሠሪዎች ግን የዛፉን ሕልም ሳይረዱ የንጉሥ አልጋ አድርገው በመሥራት ፈንታ የከብቶች የሣር ድርቆሽ ማስቀመጫ ሣጥን አድርገው ሠሩትና በአንድ በረት ውስጥ ተጣለ፡፡       ሁለተኛው አናጢ የንጉሥ መርከብ እሆናለሁ ብሎ የሚመኘውን ዛፍ ቀረብ ብሎ አየውና ‹‹ይኼ ዛፍ ጠንካራ ይመስላል ፤ መርከብ ወደሚሠሩ ሰዎች ወስጄ ባሳየው ጥሩ ዋጋ ያወጣልኛል›› አለ፡፡ ዛፉ ‹ስዕለቴ ሠመረ› ብሎ ተደሰተ፡፡ ሆኖም መርከብ ሠሪዎቹ ምኞቱን ሳያውቁ ቆራርጠው ቆራርጠው በርከት ያሉ የዓሣ ማጥመጃ ጀልባዎችን ሠሩበት፡፡ መርከብ እሆናለሁ ብሎ የተመኘው ይህ ዛፍ ዓሣ አጥማጆችን ጭኖ እየተንሳፈፈ የንጉሥ መርከብ ሲያልፍ ተመልካች ሆነ፡፡       ሦስተኛውን ዛፍም በመጥረቢያ ሲቆርጡት የዛፎች ንጉሥ ሆኖ ከፍ ብሎ የማደግ ሕልሙን አብረው ቆረጡት፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ አንዲት የጸነሰች ብላቴና ከአንድ አረጋዊ ጋር ቤተልሔም በሚባል የይሁዳ ከተማ መጣች፡፡ በወቅቱ የማደሪያ ሥፍራ ስላልነበር በከብቶች በረት ውስጥ ለማደር ገቡ ፤ ጸንሳ የነበረችውንም ልጇን በበረት ውስጥ ወለደችው፡፡ የመኝታ ሥፍራ ስላልነበር ሕጻኑን የከብቶቹ የሣር ድርቆሽ በሚቀመጥበት ሳጥን ውስጥ አስተኛችው፡፡ የዚያን ቀን ለተወለደው ሕጻን ከሩቅ የመጡ ነገሥታት ሳይቀር ሥጦታን አመጡለት፡፡ የንጉሥ አልጋ መሆን ይመኝ በነበረው ያ ዛፍ ሳጥን ሆኖ ቢሠራም የነገሥታት ንጉሥ መኝታ ሆነ፡፡       ይህ ከሆነ ከሠላሳ ዓመታት በኋላ የዓሣ ማጥመጃ ሆኖ በተሠራው ጀልባ ላይ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ዓሥራ ሦስት ሰዎች ተሳፈሩበት፡፡ የንጉሥ መርከብ ለመሆን የተመኘው ይህ ጀልባ በጀልባነቱ ዓሥራ ሦስት ተሳፋሪዎችን ተሸክሞ ሲማረር በጉዞ መካከል ድንገት ትልቅ ማዕበል ተነሥቶ መርከቧን ያናውጻት ጀመረ፡፡ ተሳፋሪዎቹ ጀልባዋን ለመቆጣጠር ታገሉ፡፡ ከመካከላቸው ግን አንዱ ተሳፋሪ ተኝቶ ነበር፡፡ ሞገዱ እየባሰ ሲመጣ የተኛውን ተሣፋሪ ‹‹ስንጠፋ አይገድህምን?›› ብለው ቀሰቀሱት፡፡ እሱም ተነሥቶ ማዕበሉን ገሠጸው፡፡ ጀልባው ድሮ እንደተመኘው የጫነው የነገሥታትን ንጉሥ እንደሆነ ተረዳ፡፡        ይህ ከሆነ ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ የዛፎች ንጉሥ ለመሆንና ወደ ሰማይ መውጫ መሰላል ለመሆን የተመኘውን ዛፍ አምጥተው ለአንድ ወንጀል ለሌለበት ንጹሕ አሸከሙት ፣ ከተራራ ጫፍ ሲደርሱም ባሸከሙት እንጨት ሰቀሉት፡፡ እንደተሰቀለ ምድር ለሦስት ሰዓታት ጨለመች ... ብዙ ተአምራት ተፈጸሙ፡፡ ይህ ዛፍ እንደተመኘው የዕጽዋት ሁሉ ንጉሥ ሆነ ፤ ሰዎች በእሱ መሰላልነት ወደ ገነት ገቡ ፤ እሱን ያዩ ሁሉ ፈጣሪያቸውን ያስታውሳሉ፡፡          በሁላችንም ሕሊና ውስጥ የእነዚህ ዛፎች ሕልም የተበላሸው ገና ያን ጊዜ ወዳላሰቡት ሥፍራ ሲጣሉ ነበር፡፡ ነገሩ አበቃ ብለን ስናስብ ግን የሦስቱም ምኞት ተሳካ፡፡ ይህ ጥንታዊ ታሪክ ምሳሌ እንጂ እውነተኛ ታሪክ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ ግን አንድ እውነታ አለ፡፡ በሕይወታችን ውስጥ እኛ አበቃልን ስንል እግዚአብሔር ሥራውን ይጀምራል፡፡ ‹‹የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ያለቀ የተቈረጠ ነገርን በምድር ሁሉ መካከል ይፈጽማል።›› ኢሳ. 10፡23 ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
Mostrar todo...
33👍 3😁 1
“አቤቱ ፥ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ ፥ የዘመኔ ቍጥሮች ምን ያህል እንደ ሆኑ ፥ እኔ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደምቀር አውቅ ዘንድ ።”  (መዝ. 38 ፡ 4) ። “በሉ እናንተም ሂዱ እኛም ወደዚያው ነን ፣ ወትሮም መንገደኛ ፊትና ኋላ ነው ፤” ዛሬ የሞተው ሰው ይኑር ብንል አንድ ቀን መሞቱ አይቀርም ። ሞት የማይቀር የሰው ዕጣ ነው  ። የሰው ልጅ አእምሮው ለሞት ስለተሸነፈ ለበሽታ መድኃኒት ሲፈልግ ፣ ለሞት ግን መድኃኒት ለመፈለግ አልተነሣም ። ሁሉን ያስተካከለ ሚዛን ሞት መሆኑን እናያለን ። የድሀውን ሞት ባለጠጋው ፣ የምስኪኑን ሞት ንጉሥ ይሞታል ። የመቃብር ስፍራዎችን ስንጎበኝ ከእኛ የተሻሉ ኃያላንና ጠቢባን መቃብር ውስጥ እንዳሉ እናረጋግጣለን ። ነጭ ይለብሱ የነበሩ ሽቅርቅሮችን ስናስብ ዛሬ አፈር/ጭቃ ውስጥ ተኝተዋል ። መሬትን ለመርገጥ ይጸየፉ የነበሩ ዛሬ ድንጋይ ተጭኗቸዋል ። ቤታቸውን አያምኑት የነበሩ ዛሬ ሁሉን ትተው ላይመለሱ ባዶ እጃቸውን ከቤታቸው ወጥተዋል  ። በሕይወት ዘመናቸው ይጨነቁለት የነበረው ነገር ፣ እኔ ከሌለው ይህ ነገር ምን ይሆናል ? ከሌለሁ እገሌም ቆሞ አይሄድም ሲሉ የነበሩ እነርሱ ሞቱ እንጂ ሕይወት እየቀጠለ ነው ። በሽታዬን አይስማ ቀድሞኝ ይሞታል ብለው ሲታክቱ የነበሩ ሞታቸው ተሰምቶም ነገሮች እየቀጠሉ ነው ። እርግጥ ነው ከሞተ ጋር የሞተ አላየንም ። ሁሉም የራሱን ምጽአት ወይም ዕለተ ሞቱን ይጠብቃል። የሕንዱ የነጻነት መሪ የነበሩት ማኅተማ ጋንዲ፡- “ተስፋ መቍረጥ ሲሰማኝ በታሪክ ሁሉ ምንጊዜም የፍቅር መንገድ ማሸነፉን አስባለሁ ። ጨካኞችና ነፍሰ ገዳዮች ነበሩ ፤ ለጊዜው የማይደፈሩ መስለው ይታያሉ ። ሆኖም በመጨረሻ ሁልጊዜም ይወድቃሉ ። አስታውሱ !! ሁልጊዜ!!” ብለዋል ። ሶቅራጥስም፡- “በዚህች ምድር ሁሉም ነገር ያልፋልና ስታገኝ ከልክ በላይ አትደሰት ፣ ስታጣም አብዝተህ አትከፋ” ብሏል። መጽሐፍ ቅዱስ በእያንዳንዱ ክፍል ይህን ያረጋግጥልናል ። የዘፍጥረት መጽሐፍ ሁሉም ነገር ጅማሬ እንዳለውና ወደ ተጻፈለት ግብ እንደሚጓዝ ይነግረናል ። የዘጸአት መጽሐፍ ኃያላን ሰጥመው ድሆች እንደሚሻገሩ ያወሳል ። የዘሌዋውያን መጽሐፍ በሚያልፍ ዕድሜ የማያልፈውን እግዚአብሔር ስለማገልገል ይተርካል ። የዘኁልቍ መጽሐፍ በእግዚአብሔር የታወቅን ፣ የራስ ጸጉራችንም የተቆጠረ መሆኑን ይተነትናል ። የዘዳግም መጽሐፍ እኛ ስናልፍ ትውልድ እንደሚቀጥል ይገልጻል። የኢያሱ መጽሐፍ ሁሉም ነገር በጊዜው ፍጻሜ እንደሚያገኝ ያስተነትናል ። የመሳፍንት መጽሐፍ ሁሉም መሪ የሆነበት አገር እንደሚፈርስ ያትታል ። የሩት መጽሐፍ ለሚያልፍ ችግር የማያልፍ ሕይወትን ማጣት እንደማይገባ ያስረግጣል ። የሳሙኤል መጽሐፍ አህያ ፈላጊ ሳኦልን ፣ እረኛውን ዳዊት ያከበረውን እግዚአብሔር በመግለጥ ትልልቆች ሁሉ የጀመሩት ከትንሽ መሆኑን ያብራራል ። የነገሥት መጽሐፍ አገርን የሚመራ እግዚአብሔር መሆኑን ይገልጣል ። የዜና መዋዕል መጽሐፍ ስለ አገርና ስለቤተ ክርስቲያን ደግ ደጉን ብቻ ማሰብ እንደሚገባ ያትታል ። የዕዝራ መጽሐፍ እግዚአብሔር ከሰጠን ስጦታዎቻችን አንዱ ደራስያን/መጽሐፍ የሚጽፉ መሆናቸውን ያስተምራል ። የነህምያ መጽሐፍ አገር ፈርሶ በለማ ከተማ ቢኖሩም ልብ እንደማያርፍ ይገልጻል ። የአስቴር መጽሐፍ እኔ የማስፈልገው ለማን ነው ? የሚለውን ጥያቄ ያነሣል ። የኢዮብ መጽሐፍ የተዋረደው ሁሉ የከበረ እንደነበር ይናገራል ። የዳዊት መዝሙር እግዚአብሔርን በሕይወት ውጣ ውረድ ሁሉ መጠጋት እንደሚገባ ያስረግጣል ። የምሳሌ መጽሐፍ ከሰው ጋር መኖር መቻል ትልቅ ጥበብ መሆኑን ይገልጻል ። መጽሐፈ መክብብ ደስታም ኀዘንም ሁሉም ያልፋል ፣ የአሁኑ የመጨረሻ አይደለም ይለናል ። የሶቅራጥስ አሳብም ከዚህ ከመክብብ መጽሐፍ ይቀዳል ። ብዙ ሰው የሚናገረው ነገ አንደበቱ እንደሚታሰር ሆኖ አይደለም ። ብዙ ሰው የሚሮጠው ነገ እንደሚቆም ዘንግቶ ነው ። ብዙ ሰው የሚጨነቀው ሞት የሚባል ጥሪ እንዳለ ረስቶ ነው ። ሰው ሞት እንዳለ እያሰበ ቢራመድ አይደናቀፍም ። ትልቁ ሞኝነት ወዳጅን እየቀበሩ እኔ አልሞትም ብሎ ማሰብ ነው ። ልጅን እየቀበሩ ገና ግፍ የሚሠሩ ወላጆች መኖራቸው ይገርማል ። ሞቱን የሚያስብ ትልቅ ጠቢብ ነው። የቀረን ዘመን በጣም አጭር ነው ። የምንዘገየው ለጥቂት ቀን ነው ። ስለዚህ አንደበታችንን መጠበቅ አለብን ። ዘግይቶ የተፈታው አንደበት ቀድሞ ይዘጋልና ለአንደበታችን ጠንቃቃ መሆን ይገባናል ። ነቢዩ በየቀኑ ካለው ተናግሮ አናጋሪ ማረፍ ስለፈለገ “ጥቂት ተወኝ” ብሎ ለመነ ። “እኔ መንገደኛ ተሸኝቶ አዳሪ ፣ ምን ክፉ አናገረኝ እንግዲህ ከቀሪ ፤ @father_advice
Mostrar todo...
12👍 4
Photo unavailableShow in Telegram
"ራስን በሐሰት አትውቀስ ራስን መክሰስ ትህትና አይደለም ታላቁ ትህትና ሰዎች ሲወቅሱህ መታገስ ነው።"       /ቅዱስ ስራኘዮን/
Mostrar todo...
26👍 5
ክረምትና ሞት “ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።” (መዝ. 45፡2 ።) የዓለምን ከንቱነት ለመግለጥ የአገራችን ሰዎች እንዲህ ብለው ይገጥማሉ፡- ምን ጌታ ቢሆኑ ፣ ባለ ዋርዳ በቅሎ ፣ ባለ ማር እሸት ፣ አሽከር ቢያደገድግ ፣ ቀንና ሌሊት ፣ ድጓ ቢተረጎም ፣ ቢነበብ ዳዊት ፣ በቅሎ ቢያሰግሩት ፣ ተጎንደር ይፋት መቅረቱን አይቀርም ክረምትና ሞት ። ክረምት ጊዜውን ጠብቆ ይመጣል ፣ ይቀራል ተብሎ አይታሰብም ። ሞትም እንደ ክረምት በጊዜው ይመጣል ። ቢዘገይም ይቀራል ተብሎ አይታመንም ። የትኛውም የኑሮ ደረጃ ሞትን አያስቀረውም ። ሁሉም ወደዚያው ነው ። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ውጭ ስሜ ትልቅ ነው ፣ ጀርባዬ ጥብቅ ነው ፣ ጎተራዬ ሙሉ ፣ አሽከሬ እልፍ ነው ብሎ መመካት አይገባም ። በማንኛውም ጊዜ ተነሥቼ ከአዲስ አበባ ኒውዮርክ ፣ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ የምበርር ነኝ ብለን ብንመካም ከሞት የሚሸሽግ ዋሻ እስካሁን አልተገኘም ። ክረምት የደረቀውን መሬት ያረሰርሳል ፣ ሞትም ጻድቃንን ከወዳጅ እግዚአብሔር ጋር ያገናኛል ። ያን ቀንም እንባ ከዓይን ይታበሳል ! በዚህ ዓለም ላይ ከሚያደናግሩ ነገሮች አንዱ የተራሮች መሰወር ነው ። ነቢዩ፡- “ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም” ብሏል ። በእስራኤል ዘንድ ትልቁ ተራራ ፣ የክብር ሰው ዳዊት ነው ። ዳዊትም ተራሮች ነበሩት ። ሰዎች “የእኔ ጀግና እገሌ ነው ፣ የእኔ ምሳሌ እገሊት ናት” ይላሉ ። እንደ ተራራ የገዘፉ ፣ ከሩቅ የሚታዩ ፣ ይጎድላሉ ተብለው የማይሰጉ ፣ የተጠለላቸውን የማያስነኩ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ ። ተራሮች የሚሰወሩበት ጊዜ ግን ጥቂት አይደለም ። በጉቦና በሌብነት ምክንያት ተሠሩ የተባሉ ሕንፃዎች ይሰወራሉ ። በውኃ ጥም ሲሰቃዩ የነበሩ የገጠር ሰዎችን ለማርካት የተቆፈሩ የውኃ ጉድጓዶች ይሰወራሉ ። የእንጦጦ ተራራን ሽቅብ ስናየው እንውላለን ። ይህ ተራራ ድንገት ቢሰወርና ከጀርባው ያለ ከተማ ቢታየን ከመደሰት እንደነግጣለን ። የከፍታዎች መለኪያ ሲጠራ “ከባሕር ጠለል በላይ…” ተብሎ ነው ። አሁን ግን ተራሮች ወደ ባሕር ልብ ተሰወሩ ። ብዙ ሰው የገዛ አእምሮውን የሚጠራጠረው ፣ አለሁ ወይስ የለሁም ብሎ ራሱን የሚደበድበው ተራሮች ሲሰወሩበት ነው ። ቆይ መጣሁ ብለውን ገብተው ፣ በገቡበት ቤት በጓሮ በር የጠፉ ሰዎች ቆመን እንድንውል ፣ በኀዘን እንድንጎዳ አድርገውናል ። ለአገር ምሳሌ ፣ ለትውልድ አርአያ የሚሆኑ ሰዎች ከስፍራቸው ሲታጡ ደንግጠናል ። በዝምታቸው የምናከብራቸው ሲናገሩ “ምነው ዝም ብለው በቀሩ” ብለናል ። እንደ ተራራ የገዘፉብን ብዙ ሰዎች ናቸው ። ከቦታቸው ታጥተው ወንዝ ለወንዝ ሲሄዱ ፣ በጎሣ በሽታ ሲለከፉ እናዝናለን ። ብዙ ያወራንላቸው ፣ “የእኔ ትልቅ” ብለን የእወቁልኝ ማስታወቂያ የሠራንላቸው አንሰው ሲገኙ ፣ ከእነርሱ መውረድ በላይ የእኛ ማመን ያበሳጨናል ። ይህ ዘመን ተራሮች የሚሰወሩበት ዘመን ነው ። መደልደል ቢሆን እሺ እንላለን ። ወደ ባሕር ልብ ፣ ከልኬት ቍጥር ውጭ ሲሆኑብን ዓለምን እንፈራለን ። ፈላስፎችን የተከተሉ ፣ ምድራዊ ዝነኞችን ያፈቀሩ ፣ በውጫዊ ነገር ለሰው የዘፈኑ ይደነግጣሉ ፣ ይፈራሉ ። ሁሉ ሲንሸራተት ፣ በከፍታው ነዋሪ የሆነ ፣ የዘመናት ዘመን የሆነ ፣ ለዘመኑ ዘመን የሌለው መድኃኔ ዓለም ግን ከፍርሃት ያድናል ። የታመናቸው ሊጥሉን ፣ ያየናቸው ሊሰወሩብን ይችላሉ ። የእውነት መዝገበ ቃላት ያደረግናቸው ፣ “እነርሱ ካሉማ ጨለማም ብርሃን ነው” ብለን የዘመርንላቸው ሊሰወሩ ፣ ሊታጠፉ ፣ በበሉበት ግብር ሊቀሩ ይችላሉ ። ክርስቶስን ካላየን ከክርስቶስ ርስት መድረስ አይቻልም ። የነፍስ መንገድ ረጅም ነውና እርሱን ብቻ መሪ ካላደረግን ፍርሃት ቶሎ ይከበናል ። እግዚአብሔር ረዳታችን ከሆነ ግን ያመነው ቢከዳን ፣ ያከበርነው ቢያዋርደን ጉዞው ይቀጥላል ። @father_advice
Mostrar todo...
👍 9 4🔥 2🙏 1
Photo unavailableShow in Telegram
"ሰዎች አንድ ሰው ተነሥቶ ሌላውን ሲገድል ወንጀለኛ ነህ ይሉታል። አንድ ላይ ተሰባስበው ብዙ ሰዎችን ሲገድሉ ግን ውጊያ ይሉትና መግደላቸውን ጀግንነት ይሉታል" ቅዱስ ቆጵሮሳዊ
Mostrar todo...
👍 24 9😢 5
“አንኳኩቼ አላገኘሁም” አትበል፡፡ ብቻ የለመንከው፣ ደጅ የጠናኸው አንተ የምትወደው ሳይሆን እግዚአብሔር የሚወድልህ ይሁን፡፡ ወደ እግዚአብሔር የተዘረጋ እጅ ፈጽሞ ባዶውን አይመለስም፡፡ ስለዚህ ራስህን፣ ልመናህን ምን ዓይነት እንደሆነ ፈትሽ እንጂ አንኳኩቼ አላገኘሁም አትበል፡፡ እንኳንስ ንጹሐ ባሕርይ የሆነው እግዚአብሔር ክፋት የሚስማማው ምድራዊ አባትም ለልጁ ጀሮውን አይደፍንም፡፡ አስቀድሞ ሕያዊት ነፍስን “እፍ” ብሎ እንዲሁ የሰጠን ጌታ፣ ኋላም ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድ ልጁን ሳይራራ ከሰጠን እንደምን በዚህ ይታማል? እንደምንስ አይሰጠንም እንላለን? /ሮሜ.8፥32/፡፡ ልጁን የሰጠው እኮ ጭራሽ “ስጠን” ብለው ላልለመኑ አሕዛብም ጭምር ነው፡፡ ታድያ እንዲህ የምንለምን እኛማ እንዴት አብልጦ አይሰጠንም? የሚበልጠውን ሰጥቶን ሳለስ እንደምን ትንሹን አይሰጠንም እንላለን? ስለዚህ ከእኛ የሚጠበቀውን ሳናደርግ “እግዚአብሔር ጸሎቴን አይሰማም” የሚል የሰነፎች አባባል የምንናገር አንሁን፡፡ ጆሮን የፈጠረ ይሰማል!” #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ (ሰማዕትነት አያምልጣችሁ መጽሐፍ #በገብረ_እግዚአብሔር_ኪደ ገጽ 178
Mostrar todo...
27👍 5🥰 4
ምክረ አበው ከወድሞች አንዱ ወደ አረጋዊ መጣና " አባ ፣ ደካማ ነኝና ጸልዩልኝ " አለው፡፡ አረጋዊም እንዲህ አለው " በሸተኛን ይቀባ ዘንድ በእጁ ቅባት የሚይዝና ሌላውን የሚቀባ ሰው እርሱም ደኀና ሆኖ ይቀባል፡፡ እንዲሁም እኛም ለሌላው ስንጸልይ ለራሳችን መድኃኒትና ፍስሐ ይሆነናል፡፡ ስለዚህ ወንድሜ ሆይ ፣ አንዳችን ለሌላችን ልንጸልይና እርስ በርሳችን በጸሎት ልንተሳሰብ ይገባናል፤ ሐዋርያው " ትድኑ ዘንድ ለወንድሞቻችሁ ጸልዩ " ብሎ እንዳዘዘን፡፡ @father_advice
Mostrar todo...
28❤‍🔥 1
በወደቀው ላይ ምሳር አናብዛ የወደቀ ሰው የሚፈልገው የሚያነሣው እጅ እንጂ ስለ ውድቀቱ ጥናት የሚሠራበት ፈራጅ አይደለም ። የራሳችን ችግር ተራራ አህሎ ፣ የሰዎች ውጣ ውረድ አንሶ የሚታየን ጊዜ ብዙ ነው ። ኃጢአትን በሚመለከት የራሳችን ትልቅ በደል ቅንጣት ፣ የሰዎች ትንሽ ስህተት ቁልል ሁኖ ይታየናል ። ሰዎችን ከደረሰባቸው ችግር በላይ የሚከብዳቸው በየጊዜው የሚያስተናግዱት የሌሎች የፍርድ ቃል ነው ። ደካማ ሰዎች የሰውን መታመም ፣ መቸገርና መዋረድ ሲያዩ እነርሱ ቅዱስ ፣ ያ ሰው ርኩስ መስሎ ይታያቸዋል ። ይህች ዓለም ግን ለክርስቶስ ሕመምን ፣ ረሀብን ፣ ጥማትን ፣ ውርደትን የከፈለች ዓለም ናት ። እውነተኛው ፍርድ ያለው በሰማይ ነው ። ውድቀት የራሱ ሆነ ድምፅ አለው ። ሰውን ውድቀቱ የሚናገረውን ያህል የእኛ ቃል ሊናገረውና ሊገሥጸው አይችልም። በሰው ቍስል እንጨት መስደድ ለተቀባዩ ከባድ ፣ ላቀባዩ ግን ቀላል ነው ። በእኛ ቍስል ላይ ግን የሐኪም እጅ ፣ የመድኃኒት ጠብታ ሲያርፍ እንሳቀቃለን ። በሰዎች ቍስል ላይ ሌላ ቍስል ለመጨመር ግን አንፈራም ። በራሳችን ላይ ግን የመፍትሔ እጆችንና ሥራዮችን ሳይቀር እንሸሻለን ። ለሰው መርዝን በደስታ እንበጠብጣለን ፣ ለእኛ ግን መድኃኒቱንም አጥብቀን እንመረምራለን ። “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ማለት ተጠንቀቅለት ፣ ይቅርታ አድርግለት ፣ አስብለት ማለት ነው ። በእኛ አገር ብዙ ችግር አለ ። ትልቁ ችግራችን “ምን ይሉኛል?” የሚለው ከንቱ ስጋት ነው ። ያልተገነባው ማንነታችን በሚሉን ነገርና በሚሰጡን ክፉ ስም ይፈራርሳል ። ቀላል ሰው በጥቂት ምስጋና ደመና ይነካል ፣ በጥቂት ነቀፋ መቀመቅ ይወርዳል ። አራት አምስት ልጅ የቀበሩ የሚያሳስባቸው ከራሳቸው መጎዳት ፣ ከልጆቻቸው ማለቅ በላይ “ምን ይሉኛል?” የሚለው ፍርሃት ነው ። ለሁሉም ነገር አስተንትኖ መስጠት ግዳጅ የሚመስለው የአገሬ ሰው ፣ የራሱን ትቶ በሰው ቤት ላይ የሚውል የሚያድረው ወገኔ ፈውሱ መቼ ይሆን! ይህችን ጽሑፍ በምንጽፍባትና በምናነብባት ቅጽበት በሰው ላይ ነገር የሚሠሩ ፣ የስም ጥላሸት የሚቀቡ ብርቱ ሥራ እንደ ያዘ ተጠምደዋል ። በልመና ስንዴ መኖራችን አያሳቅቀንም ። ለልመናም ብቁ አይደላችሁም ተብለን ገሸሽ ሲያደርጉን እናኮርፋለን እንጂ ይህን ታሪክ ለመለወጥ ወኔ ያጥረናል ። በሰው ቍስል ላይ መፍረድ ትልቅ ጭካኔ ነው ። ጨካኝ ብለን የምንጠራቸው ሰይፍ የሚዙ ፣ ጥይት የሚተኩሱ ሰዎችን ነው ። ትልቁ ጭካኔ ግን በሰው ቍስል ላይ መፍረድ ነው ። ጫካ ላይ ቆመው ሰውን የሚያስጨንቁትን ብቻ ሳይሆን በከተማ ያሉትን ግፍ የማይፈሩ ጠበቃና ዳኞችን ፣ ሐኪምና ባለሙያዎችን አሸባሪ ብለን ለመጥራት ድፍረት ያስፈልገናል ። ሁሉም በአቅሙ የሚበድልባት አገር መፍጠራችን በእውነት ያሳዝናል ። አዎ በሰው ቍስል መፍረድ ትልቁ የአንደበት ውድቀት ነው ። የወደቀን ሰው እንዲነሣ ከማገዝ ውጭ ምንም ዓይነት አሉታዊ ድምፅ ማሰማት አይገባንም ። ሃይማኖት ማለት የወደቀውን አዳም የፈለገ ፣ የበዳይን ሞት ሞቶ የካሰውን አምላክ ማመን ነው ። ሰዎች የሚወድቁት አንዳንዴ መንገዱ ጠፍቷቸው ነው ፣ ሌላ ጊዜ የሚዘሉት መስሎአቸው ገደሉ ሰፍቶባቸው ነው ፣ አንዳንዴም እነሣለሁ ሲሉ ይወድቃሉ ፣ አተርፋለሁ ሲሉ ይከስራሉ ፣ አስደስታለሁ ሲሉ ያሳዝናሉ ። አላዋቂነታቸውም የውድታቸው ምክንያት ይሆናል ። ለመማር ፣ በርታ ለመባል ዕድሉን ባለማግኘታቸው ሰሰዎች ይወድቃሉ ። የእግዚአብሔር እጆች የወደቀን ለማንሣት ተዘርግተዋል ። እኛ ባናነሣቸው እንኳ በወደቁት ላይ ምሣር ማብዛት አይገባንም ። ምሣር ወይም መጥረቢያ የምናበዛበት ዛፍ ትላንት በልምላሜው ደስ ያሰኘን ፣ በአበባው ተስፋ የሰጠን ፣ በፍሬው ያጠገበን ፣ በጥላው ያሳረፈን ፣ በውዝዋዜው አየሩን የቀዘፈልን ፣ በውበቱ ቤታችንን ውድ ያደረገልን ነው ። ይህ ዛፍ ሲወድቅ ግን ሁሉም መጥረቢያ ይዞ ይከተክተዋል ። ሰው ዛፍ አይደለም ፣ ወድቆ አይቀርም ፣ ይነሣል ። ዛፍ ሲያድግ ድምፅ የለውም ፣ ሲወድቅ ግን ድምፁ ይሰማል ። ስናድግ ብዙ ሰው እንዳላየ ያልፈናል ፣ ቅናቱ ዱዳ ያደርገዋል ። ስንወድቅ ግን ሁሉ ይሰማዋል ። በወደቀው ዛፍ የቆሙት ቢስቁ ያ የወደቀ ዛፍ የመጥረቢያ እጀታ ሁኖ ሊቆርጣቸው እንደሚመጣ ቋሚዎች ይዘነጋሉ ። ዛሬ እያስጨነቁን ያሉት ትላንት ወደቁ ብለን የሳቅንባቸው ፣ ወይም ገፍትረን የጣልናቸው ወገኖች ናቸው ። ንስሐ እስካልገባን በገመድነው ጅራፍ እየተገረፍን እንኖራለን @father_advice
Mostrar todo...
😢 10👍 6🥰 3
Photo unavailableShow in Telegram
#የታገሰ_ከምርጡ_ፍሬ_ይበላል! አንድ ጊዜ አንዲት ድኃ ሴት የወይን ተክል ባለበት ማሳ በኩል እያለፈች ነበር። ማሳው በሚያማምሩና በበሰሉ የወይን ዘለላዎች የተሞላ ነበር። ሴቷ ጠምቷት ስለነበር የወይኑን ማሳ እያየች "ከእነዚህ የበሰሉ ፍሬዎች አንዱን ወለላ የሚሰጠኝ ባገኝ..." ብላ ተመኘች የወይን ማሳው ባለቤት በመንገዱ በኩል እያለፈ ስለነበር አያት፤ እንዳያትም ሰላም ካላት በኋላ "ምን እያየሽ ነው የኔ ውድ? የወይን ዘለላ ትፈልጊያለሽ?" ብሎ ጠየቃት። "አዎ እፈልጋለሁ" አለችው "ግን መውሰድ አልችልም" ባለቤቱ ወደ ማሳው ገብቶ፣ በማሳው መሐል ጠፋ። ጠበቀችው፣በጣም እንደዘገዬ ሲታወቃት ግን ምን አልባት ረስቶታል ማለት ነው ብላ መንቀሳቀስ ጀመረች። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የማሳው ባለቤት ሲመጣ ሴቷ ሄዳለች። ነገር ግን ከርቀት ስላያት ጠራት። እንደተመለሰችም "ስለዘገየሁ ይቅርታ። ግን ለምን ሄድሽ? የዘገየሁት እኮ እጅግ ምርጡን ዘለላ እየፈለግኩልሽ ስለነበር ነው። ይሄው ሙሉ ቅርጫት አመጣሁልሽ!" አላት ቅርጫቱንም ሰጣት። ሴቷ ትንሽ አፈረች፣ አንገቷን ደፍታም ቅርጫቱን አነሳች። የማሳውን ባለቤት አመስግናም ሄደች። ይህ ታሪክ ለሁሉም ሰው የሚሆን አንድ ትልቅ ትምህርት አለው። ብዙ ጊዜ በጸሎት አንድ ነገር እንጠይቅና ወዲያው ግን ምላሽ አናገኝም። ከዚያም እግዚአብሔር ለእኛ አይጨነቅም ብለን እናስባለን። ከሆነ ጊዜ በኋላ ሲመጣ ግን የዘገየው ለካ ለእኛ ጥቅም ነው። ምላሹም እጅግ የተባረከና ከጠበቅነውና ከጠየቅነው በላይ ይሆናል።
Mostrar todo...
🙏 26 15👍 9
Photo unavailableShow in Telegram
ማቴዎስ 7 ¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯ ²⁴ ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። ²⁵ ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። ²⁶ ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ²⁷ ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፥ ወደቀም፥ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ። ²⁸ ኢየሱስም ይህን ነገር በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን ²⁹ እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና።
Mostrar todo...
19