cookie

Utilizamos cookies para mejorar tu experiencia de navegación. Al hacer clic en "Aceptar todo", aceptas el uso de cookies.

avatar

ስንክሳር ወግጻዌ (Addis)2014ዓ.ም

በየቀኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በስንክሳር የሚታሰቡ የቅዱሳን ታሪክ፣ የቅዱሳን ገድላት እና የየቀኑ የቅዳሴ ወንጌል ምስባክ (ግጻዌ) ይቀርብበታል።

Mostrar más
Publicaciones publicitarias
228
Suscriptores
Sin datos24 horas
Sin datos7 días
Sin datos30 días

Carga de datos en curso...

Tasa de crecimiento de suscriptores

Carga de datos en curso...

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አሜን"። ❤ ❤ ጥር ፲፰ (18) ቀን። ❤ እንኳን ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በ34 ዓ.ም በሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ ላተጠመቀ ለመጀመሪያው ለአፍሪካ ሐዋርያ ለሆነ ለሐዋርያች ለቅዱስ አቤላክ (ባኮስ) ከሞት ለተሰወረበት በዓል በሰላም አደረሰን። + + + ❤ የመጀመሪያው የአፍሪካ ሐዋርያ ቅዱስ አቤላክ (ባኮስ)፡- ይኽም ጃንደረባ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ንግሥት የሆነችው የህንደኬ የገንዘቧ ሁሉ ኃላፊና አዛዥ የነበረ ነው፡፡ ከአባቱ እብነ መላክ ከእናቱ ስሂነ ሕይወት ታኅሣሥ29 ቀን ተወለደ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ለበዓለ ፋሲካ በቤተ መቅደስ ይሰግዱ እንደነበረው ሁሉ ይኽም ጃንደረባ ከ4ሺህ ማይልስ በላይ ተጉዞ ኢየሩሳሌምን ተሳልሞ በመለስ ላይ ነበረ፡፡ ❤ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ በተለይም ስለ ጌታችን መከራ መስቀል በዝርዝር የሚናገረውን ክፍል 53ኛውን ምዕራፍ ያነብ ነበር ነገር ግን ጃንደረባው ስለማን እንደሚናገር አልገባውም ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር በአካባቢው ወንጌልን ይሰብክ የነበረውን ሐዋርያውን ቅዱስ ፊሊጶስን ላከለት፡፡ እርሱም ጃንደረባው ያነበው የነበረውን መጽሐፍ ተረጎመለት፣ የከበረች ወንጌልን ሰበከለት፣ በመጨረሻም አጠመቀው፡፡ ሐዋርያው ባጠመቀውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በጃንደረባው ላይ ወረደ፡፡ ሐዋ 8፡26-40፡፡ ❤ ይህን ለእኛ ለኢትዮጵያውን እጅግ የሚያኮራን ታሪካችን ነው፡፡ ዛሬ በእጃችን ላይ በመገኘው መጽሐፍ ውስጥ ባይኖርም በቆዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች ላይ ግን ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ ጃንደረባውን ባጠመቀውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በኢትዮጵያው ጃንደረባ ላይ እንደወረደ ተጽፏል፡፡ (v 39.cord.alexand. in bible reg. angl-aliqu plures codd.mss) ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ ጃንደረባውን ያጠመቀበት ወንዝ "ቤተ ሳሮን" በተባለችውና እስከዛሬም ድረስ ከኢየሩሳሌም20 ማይልስ ርቀት በምትገኘው መንደር በኬብሮን መካከል ባለው ኮረብታ ሥር የሚመነጭ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን የታሪክ ጸሐፊ የሆነው ሊቁ ቅዱስ ጀሮም ጃንደረባውን "የኢትዮጵያውያን ሐዋርያ" በማለት ይጠራዋል፡፡ በሰፊው ለኢትዮጵያውያን ወንጌልን የሰበከ እርሱ ነውና፡፡ ❤ ጌታችን የመረጣቸው የከበሩ ሐዋርያት እንኳን ወንጌልን በዓለም ለመስበክ ገና ከኢየሩሳሌም ባልወጡበት ወቅት በ34ዓ.ም ነው። ቅድስት አገራችን ኢትዮጵያ በክርስቶስ አምና ወንጌልን የተቀበለችው፡፡ በምድሪቱም ላይ ወንጌል መነገር የጀመረው ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ሐዋርያው ባኮስ (አቤላክ) ከኢየሩሳሌም ወንጌልን ተምሮና ተጠምቆ ወደ አክሱም እንደተመለሰ በመጀመሪያ ያጠመቀ ንግሥቲቷ ሕንደኬን ነው፡፡ ከእርሷም በኋላ መኳንንቱና መሳፍንቱ ሁሉ አምነው በባኮ እጅ ተጠመቁ ይኸውም በ34 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚህም በኋላ ባኮስ እስከ ኑብያ ድረስ ሄዶ ወንጌልን ሰብኮ ብዙዎችን አሳምኖ አጥምቋል፡፡ በዚህም ጊዜ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በባኮስ እየተሰጠ የነበረውን የወንጌል ብርሃን የበለጠ እንዲበራ አድርጓል፡፡ ከጃንደረባውም ጋር ሆነው በብዙ ቦታዎች አብረው ወንጌልን ሰብከው አምልኮተ ጣዖትን አጥፍተዋል፡፡ ❤ ከዚህም በኋላ ባኮስ ወደ የመን በመሄድ በዚያም ክርስትናን በማስተማር ብዙዎችን አሳምኖ ካጠመቀ በኋላ ወደ ፐርሺያ ከዚያም ወደ ሕንድ፡ በመሄድ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሟል፡፡ በመጨረሻም ጥንት ታፕሮባና (taprobana)፡ ዛሬ ሲሎን በምትባለው ደሴት ወንጌልን በማስተማር ላይ እያለ በሰማዕትነት እንዳረፈ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ (lives of the most eminent fathers of the church, page 87) በሌላም በኩል ሐዋርያው ባኮስ (አቤላክ) ከመጠመቁ በፊት 35ዓመት ከተጠመቀ በኋላ ደግሞ 41 ዓመት ኖሮ በኢየሩሳሌምም 3ዓመት ተቀምጦ ወንጌልን ዞሮ ካስተማረ በኋላ በመጨረሻ በ79 ዓመቱ ጥር 18 ቀን በሰሜን ተራራዎች ላይ ቅዱስ ያሬድ በተሰወረበት ቦታ እንደተሰወረ ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ ጽፈዋል፡፡ ምንጭ፦መዝገበ ቅዱሳንና ቅዱሳት በዓላት።
Mostrar todo...
❤ ቅድስት እናታችን ጸበለ ማርያም ከነቢያት፣ ከሐዋርያትና ከሰማዕታት ዕድል የተሰጣት እናት ናት፡፡ እንደነቢያት የሚመጣውን ሁሉ እንዳለፈ አድርጋ ትናገራለች፡፡ ዳግመኛም የትምህርታቸውን ፍለጋ ስለተከተለችና ለሕጋቸው ስለተገዛች ከሐዋርያት ጋር ዕድል ተሰጣት፡፡ ሦስተኛ ግድ ሳይሏት በፈቃዷ ስለተቀበለቻቸው ግርፋቶቿና ስላገኛት መከራ የሰማዕታት ዕድል ተሰጣት፡፡ ከደናግል መነኰሳትም ዕድል ተሰጣት መነኵሲትም ድንግልም ናትና፡፡ ቅድስት እናታችን ጸበለ ማርያም መልካም የሆነውን ተጋድሎዋን ከፈጸመችና ጌታችን ታላቅ ቃልኪዳን ከገባላት በኋላ በሰላም ዐርፋለች፡፡ እንደ ንግሥት ዕሌኒም የሞቷን መስቀል ተሸክማ ተጠብቆላት ወዳለ ተስፋዋ በክብር ሄደች፡፡ ዕረፍቷ መስከረም 18 ነው፡፡ ጥር 18 የልደቷ ዓመታዊ በዓሏ ነው። ገዳሟ የሚገኘው ጃማ ወረዳ ልዩ ስሙ አህያ ፈጅ ከሚባለው አካባቢ ነው። ከእናታችን ቅድስት እናታችን ጸበለ ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን፣ በጸሎቷ ይማረን!። ምንጭ፦ ገድለ ቅድስት ጸበለ ማርያም፣ ደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት የንህበት ቅድስት ጸበለ ማርያም ቤ/ክ ያሳተመው።
Mostrar todo...
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤ ❤ ጥር ፲፰ (18) ቀን። ❤ እንኳን ለኢትዮጵያዊቷ ጻድቅ ጌታችን በደሃ ሰው ተመስሎ ተገልጦ ቁራሽ እንጀራ ለለመናትን በኋላም በጀርባዋ አዝላ ለሸኘችው፤ በጎኗ ተኝታ ለማታውቅ፤ በጌታችን 40 ጾም ወራት ከሰንበት በቀር ምንም የማትቀምስ፤ ነብሮች የእግሯን ትቢያ ይልሱላት ለነበረች ለታላቋ እናትን ለቅድስት ጸበለ ማርያም ለልደቷ በዓል፣ ለኢትዮጵያዊው ጻድቅ ኤርትራ ጠረፍ መረብ ወንዝ አካባቢ የሚገኘው ሩሑብ ገዳም ለተመሠረተ ከአቡነ ሐራ ድንግል ጋር ተመሳሳይ ታሪክ ላላቸው፣ልክ እንደ አቡነ ሐራ ድንግል በቃላቸው ገዝተው ነብርንና ሚዳቋን ላስማሙ ለታላቁ አባት ለአቡነ ለአቡነ ቴዎድሮስ ዘአዳይቦ ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን። + + + ❤ አቡነ ቴዎድሮስ ዘአዳይቦ፦ አባታቸው ፈያት ገብረ ክርስቶስ እናታቸው መክብበ ድንግል ይባላሉ። ነገር ግን አቡነ ቴዎድሮስን ወላጆቻቸው በሕገ እግዚአብሔር በሥርዓተ ጋብቻ ጸንተው ኖረው የወለዷቸው አይደሉም። ❤ መክበብ ድንግል ዕንጨት እየለቀመች ሳለ ፈያት ገብረ ክርስቶስ በዚያ ሲያልፍ አግኝቷት በግብር አወቋትና ፀነሰች። ሰሎሜ የምትባለው ደገኛ ሴትም ይኽንን በመንፈስ ቅዱስ መነጽርነት አይታ መክብበ ድንግል እንደፀነሰች ተመለከተች በወቅቱ የነበሩትና ታሪካቸውን ቀደም ብለን ያየናቸው ታላላቆቹ ቅዱሳን አቡነ አዎስጣቴዎስና ልጃቸው አቡነ አብሳዲም ይኽን የመክበብ ድንግልን መደፈርና መፀነስ ዐውቀው አቡነ አምስጣቴዎስ "አረከሳት" ሲል አቡነ አብሳዲ ደግሞ "ቀደሳት ቀደሳት እንጂ አላረከሳትም"... በማለት ከመክብበ ድንግል የሚወለዱት ጻድቁ አቡነ ቴዎድሮስ መሆናቸውን ተናገሩ። መክብበ ድንግልም የብርሃን ዓምድ አዝላ ታየቻቸው። ❤ ከዚኽም በኋላ አቡነ ቴዎድሮስ በኤርትራ ልዩ ስሙ ዓዲ ተምሾ በሚባል ቦታ ተወለዱ። እርሳቸውም የእናታቸውን የመክብበ ድንግል ጡት ሳይጠቡ አደጉ ነገር ግን እንደ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሚዳቋ እያጠባቻቸው እንዳደጉ ገድላቸው ይናግራል። ❤ አባታችንም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተምረው ካደጉ በኋላ በቅዱስ ወንጌል "ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?" ማቴ 19፡26 ማር 8፡36። ተብሎ የተጻፈውን የወንጌል ቃል አስበው የነፍሳቸውን ድኅነት በመሻት መንነው ከሰው ተነጥለው ወደሚኖሩበት በረሓ ገቡ። በዚያም ከዓለም ተለይተው በታላቅ ተጋድሎ ኖረው የምንኵስናን ሥራ ሁሉ ፈጽሙ በአቡነ አብሳዲ እጅ መነኰሱ። አቡነ ቴዎድሮስ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጥናት ምሥጢራትን ካወቁና በአቡነ አብሳዲ እጅ ከመነኰሱ በኋላ በጽኑ ተጋድሎ ኖረዋል። ❤ ከዚኸም በኋላ አቡነ ቴዎድሮስ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እያደጉ ሔደው ከብቃት ደረጃ ላይ ሲደርሱ አቡነ አብሳዲ የአቡነ ቴዎድሮስን ማረፊያ በመንፈስ ቅዱስ ተረድተው "አንተ በመንፈስ አባቴ ነህ አሁን ግን እግዚአብሔር ካዘጋጀልህ የተጋድሎ ቦታህና ማረፊያ ወደሆነችው ርሒብ ሒድ" አሏቸው። ይኸችም ርሑም የተባለች የአቡነ ቴዎድሮስ ገዳም ዙሪያዋ እሳት መሀሏ ገነት የሆነች ለምለም ቦታ ናት አባታችንም ወደዚህች በአታቸው ሔደው እንዲያገለግሉ አቡነ አብሳዲ ላኳቸው፡ ❤ ቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስም የአቡነ አብሳዲን ቃል ተቀብለው ወደ ተነገራቸው ቦታ ርሑብ) ሔደው በዚያም በታላቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ መኖር ጀመሩ። ርሑ ማለት ሰፊ ቦታ እንደማለት ነው። ገዳማቸውንም ገድመው በርካታ መናንያንን አፍርተዋል። እርሳቸውም በተሰጣቸው መንፈሳዊ ጸጋ ለገዳሙ መነኰሳት መቊነን ያመጡ የነበረው ከሩቅ ቦታ በደመና ተጭነው እየተመላለሱ ነበር፣ በወቅቱ የነበሩ መነኰሳትም ይህን አይተው እጅግ ይገረሙና ለቅዱሳን ጸጋ የሚስጠውን ልዑል እግዚአብሔርን ያመሰግኑ እንደነበር ገድላቸው ይናገራል፡፡ ❤ ከዚኽም በኋላ ቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስ በመንፈሳዊ ተጋድሏችው ጸንተው እስከ መጨረሻ ድረስ እግዚአብሔርን አገልግለው የዕረፍታቸው ጊዜ ሲደርስ ጌታችን መድኃኔዓለም ክርስቶስ ተገለጠላቸውና ከዚህ ዓለም ድካም ወደ ዘለዓለማዊ ዕረፍት ሊወስዳቸው እንደመጣ ነገሯቸው ታላቅ ቃልኪዳን ገባላቸው። የተጋድሏቸውን ዋጋ አስቦ በቸርነቱ "ስለ ፍጹም ድንግልናህ ዓለምንና በውስጧ ያለውን ነገር ስለናቅህ ስለ ምንኵስናህ" በማለት አክሊላትን አቀዳጃቸው ዳግመኛም ገዳማቸውን የተሳለመ እና የገዳማቸው ጽላሎት ያረፈበትን እስከ 12 ትውልድ ድረስ እንደሚምርላቸው ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል። ❤ የቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስን ገድላቸውን በእምነት የሰማ፣ የተሳለመ እንዲሁም መጽሐፈ ገድላቸውን አዝሎ የተማጸነ ሁሉ ልጅ እንደሚያገኝ የታወቀ ነው አሁንም ድረስ በርካታ መውለድ ያልቻሉ እናቶች ገድላቸውን እያዘሉ ልጅ ይወልዳሉ። እንዲሁም ገዳሙ ውስጥ በምትገኘውና የጻድቁ የእጃቸው ምርኩዝ በነበረችው በመቋሚያቸው እጣቢ እጅግ በርካታ ምእመናን ከተለያዩ ደዌያትና ሕማማት ተፈውሰዋል። ከመካነ መቃብራቸውም ላይ የፈለቀው ጠበል እጅግ ፈዋሽ ነው። ገዳማቸው የሚገኘው ኤርትራ ጠረፍ መረብ ወንዝ አካባቢ ሲሆን ከኣዲ ነብሪ ኢድ ወደ ዓዲ ክልተ በመኪና ከተጓዙ በኋላ ከዚያ የአራት ሰዓት የእግር መንገድ ርቀት ላይ ነው። ❤ በቱርኮችና በዐረቦች ታግዞ የእነርሱንም ሠራዊት አስከትሎ 15 ዓመት ሙሉ የሀገራችንን ሊቃውንት ሲያሳርድ ገዳማትን ሲያቃጥል የኖረው የሰይጣን መልእክተኛ ግራኝ አህመድ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ሔዶ በወርቅ በዕንቍ ተጊጠው የተሠሩ እጅግ በርካታ ገዳማትንና አብያተ ክርስቲያናትን ሲያቃጥል በተለየ ተኣምር ግን ሊያቃጥላቸው ካልቻላቸው ገዳማት ውስጥ አንዱ ይኸ የአቡነ ቴዎድሮስ ገዳም ነው። ግራኝም ማቀጣጠያ እየጨመረ እሳቱን ለኮሶ ገዳሙን ለማቃጠል ብዙ ቢደክምም ይኽንን ገዳም ግን ለማቃጠል አልችል ብሎ ትቶት እንደሔደ ገድላቸው ይናገራል። ❤ የአቡነ ቴዎድሮስ በዓለ ዕረፍታቸው ጥር 18 ሲሆን መስከረም 18 ቀንም ከአባታችን ኤዎስጣቴዎስ በዓል ጋር ክብረ በዓላቸው በገዳሙ በድምቀት ይከበራል። ከዕለታትም በአንደኛው ቀን በገዳማቸው ውስጥ የጻድቁን በዓል ለማክበር ከተሰበሰቡት አገልጋዮች ውስጥ አንድ መነኵሴ ደክሟቸው በቅዳሴ ሰዓት ተኝተው ሳለ ጻድቁ አቡነ ቴዎድሮስ በአካል ተገልጠው በመቋሚያቸው ቀስቅስው"አንተ ደካማ ክብረ በዓሌ በሚከበርበት ቀን ለምን ትተኛለህ ?"ብለው ከዕንቅልፋቸው እንደ ቀስቀሷቸው የገዳሞ አባቶች ይናገራሉ ። ከአቡነ ቴዎድሮስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን። ምንጭ በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን መጽሐፍ የተወስደ። + + + ❤ ቅድስት ጸበለ ማርያም፦ ትውልዷ በጎንደር ጠቅላይ ግዛት ቀሐ አካባቢ ነው፡፡ ወላጆቿ አባቷ እንድርያስና እናቷ መስቀል ክብራ ፈሪሃ እግዚአብሔርንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እያስተማሩ በሃይማኖት በምግባር ኮትኮተው አሳደጓት፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ተከስተ ብርሃን የተባለ ደገኛ ባሕታዊ ወደ አባቷ ቤት መጥቶ ባደረበት መንፈስ ቅዱስ ኀይል የቅድስት ጸበለ ማርያምን ጸጋ አወቀ፡፡ ለወላጆቿም "ይኽቺ ልጅ ወደፊት ነፍሳት የሚድኑባት የከበረች ትሆናለች" ብሎ በእርሷ ላይ ትንቢት ተናገረ፡፡
Mostrar todo...
❤ ቅድስት ጸበለ ማርያም ለአቅመ ሔዋን ስትደርስ ወላጆቿ በጋብቻ ሕግ እንድትወሰን ፈለጉ፡፡ ነገር ግን ቅድስት ጸበለ ማርያም "ቅዱስ ጳውሎስ ለእግዚአብሔር አጭቶኛልና ፈጣሪዬን በድንግልና ለማገልገል ተስያለሁ" በማለት ተቃወመቻቸው፡፡ ወደ አንድ ደገኛ ባሕታዊም ዘንድ ሄዳ በጸሎቱ ከዚህ ነገር እንዲያድናት ተማጸነችው፡፡ እርሱም ፈቃደ እግዚአብሔርን በጸሎት ከጠየቀላት በኋላ ማድረግ የሚገባትንና ወደፊት የሚገጥማትን ሁሉ ነገራት፡፡ እርሷም ለዕጣን እንዲሆን ጌጧን ሁሉ አውጥታ ሸጠችና "መሥዋዕቴን አሳርግልኝ" ብላ ለባሕታዊው ሰጠችው፡፡ እርሱም ከጸለየላት በኋላ የጸሎቱን ምላሽ ነገራት፡፡ ❤ ወላጆቿም ያለፈቃዷ በሕግ ቢያጋቧትም ቅድስት ጸበለ ማርያም ግን በሌሊት ማንም ሳያያት ከጫጉላ ቤት ወጥታ ሄዳ በልዳው ፀሐይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ወደተሠራች ቤተ ክርስቲያን ሔዳ እያለቀሰች ጸሎት አደረገች፡፡ እመቤታችንም ከቅዱሳን ሚካኤል ወገብርኤል እንዲሁም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተገለጠችላትና እንዲጠብቋት ነገረቻቸው፡፡ ቤተሰቦቿም እንዳያዝኑባት ፈርታ ተመልሳ ወደ ባሏ ዘንድ ብትገባም ባሏ በግብር እንዳያውቃት መላእክቱ ይጠብቋት ነበር፡፡ ባሏንም ሰውነቷ እንደእሳት ያቃጥለው ነበር፡፡ እርሱም አእምሮውን ከሳተ ከ3 ቀን በኋላ ሲነቃ የደረሰበትን ለቤተዘመዶቹ ባስረዳቸው ጊዜ "ከገዳም የመጣች ከሆነች ለእኛ ልትሆን አይገባም" አሉና አስጊጠውና ሸልመው መልሰው ወደ ቤተሰቦቿ ላኳት፡፡ አባቷም ዳግመኛ ወደባሏ እንድትመለስ በማስገደድ ብዙ አሰቃቂ ግርፋት ቢገርፋትም በተአምራት ምንም እንዳላገኛት ሆነች፡፡ ❤ ከዚኽም በኋላ ወጥታ ወደ ምድረ በዳ ሄደች፡፡ ወደ ገዳምም ሄዳ ዋሻ ውስጥ ገብታ ስትጸልይ አድራ አረፍ ስትል ነብር መጥቶ የእግሯን ትቢያ ይልሳት ነበር፡፡ ከዚያም ወጥታ ንህበት ወደሚባል ሀገር መጥታ ቶማስ ከሚባል መነኵሴ ጋር በታላቅ ተጋድሎ ኖረች፡፡ ቆማ ስትጸልይ እንባዋ መሬቱን ያርስ ነበር ነገር ግን ሰው እንዳያውቅባት አፈር በላዩ ትጨምርበታለች፡፡ በአንድ ዕለትም በቤተ ክርስቲያን ቆማ ስትጸልይ በሁለቱ ማዕዘን የተቀበሩ ምውታን ሲጮኹ ሰማቻቸው፣ እነርሱ ግን በሲኦል ነበሩ፡፡ ጩኸታቸውንም በሰማች ጊዜ በእንባዋ ላይ እንባን በጸሎቷም ላይ ጸሎትን ጨምራ ስለእነርሱ ለመነች፡፡ ስለእነርሱም ሱባኤ ያዘች፡፡ በባሕርይው ቸርና ይቅርባይ የሆነ ልዑል እግዚአብሔርም ጸሎቷን ሰምቶ እነዚያን ነፍሳት ማረላት፡፡ ❤ ቅድስት ጸበለ ማርያም በምግባርና በትሩፋት በጾም በጸሎት ጸንታ ከኖረች በኋላ የምንኩስና ቀንበርን ትሸከም (በመንናኔ ትኖር) ዘንድ በብሕትውና ወደሚኖረው ታላቁ አባት ወደ አቡነ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ ዘንድ ሄደች፡፡ እርሱም ማኅሌተ ጽጌን ከአባ ጽጌ ድንግል ጋር የደረሰው ነው፡፡ ❤ አቡነ ገብረ ማርያምም ካስተማራትና በኋላ አመነኰሳትና ስሟን "ጸበለ ማርያም" ብሎ ሰየማት፡፡ ከዚኽም በኋላ ተጋድሎዋን እጅግ በማብዛት ትኅርምትን ገንዘብ አደረገች፡፡ ከዕንጨት ፍሬዎች ውጭ የማትመገብ ሆነች፡፡ በተቀደሰችው የጌታችን 40 ጾም ወራት ግን ከሰንበት በቀር እርሱንም ፈጽሞ አትቀምስም፣ እስከ ፋሲካም ድረስ ከበዓቷ ስለማትወጣ ማንም አያያትም ነበር፡፡ ❤ ከመነኰሰችም ጊዜ ጀምሮ በጎኗ ተኝታ አታውቅም፡፡ ባመማት ጊዜም ተቀምጣ ታንቀላፋ ነበር፡፡ በውርጭ ቅዝቃዜ መከራን እየተቀበለች በባሕር ውስጥም ቆማ እየጸለየች ታድራለች፡፡ በስግደቷም በቀን እስከ 8 እልፍ ትሰግድ ነበር፡፡ ከወንድሟ ቶማስም የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ተማረች፡፡ የዮሐንስን ወንጌልና የራእዩን መጽሐፍ ዘወትር በማንበብ ትጸልያለች፡፡ የእመቤታችን በዓል በሆነ ጊዜ አርጋኖን ውዳሴዋን በቀን ሦስት ጊዜ ታነባለች፣ አንቀጸ ብርሃንንም በየሰባቱ ጊዜ ትጸልያለች፡፡ የዳዊትንም መዝሙር በፈጸመች ጊዜ የጌታችንን መከራ ግርፋት እያሰበች ራሷን ሺህ ጊዜ ትገርፋለች፡፡ ዳግመኛም አገዛዛቸው መልካም ይሆን ዘንድ ስለ ጳጳሱና ስለ ንጉሡ አንድ አንድ ሺህ ጊዜ፣ ስለ መነኰሳትም ሺህ ጊዜ፣ ስለኃጥአንም ሺህ ጊዜ ራሷን ትገርፋለች፡፡ ዳግመኛም ነጭ ዕጣን በእጇ ይዛ ሰባት ቀን እስኪሆን ድረስ ዕንባዋን ታፈስበታለች፣ ያም ነጭ ዕጣን ከዕንባዋ ብዛት የተነሣ ጥቁር ይሆናል፡፡ በዓል በሚሆንበት በሰባተኛው ቀን አስቀድማ ዐውቃ በመሠዊያ ያሳርገው ዘንድ ያን ዕጣን ለቄሱ ትሰጠዋለች፡፡ እግዚአብሔርም እንደሱራፌል የጽናሕ መዐዛና እንደኪሩቤል ዕጣን ሽታ አድርጎ ከቄሱ እጅ ሲቀበል በግልጽ ታያለች፡፡ ❤ ቅድስት እናታችን እሾህ ያለው የብረት ዛንዠር በወገቧ ትታጠቃለች፡፡ በወገቧና በጭኖቿ ያሰረችው ርጥብ የላም ቁርበት ከአጥንቶቿ ጋር ይጣበቃል፡፡ በደረቀም ጊዜ ሥጋዋ እየተቆራረጠ ይወድቃል፣ በምድርም ውስጥ ትቀብረዋለች፡፡ አምስት ጊዜም እንደዚህ እያደረገች ራሷን ጎዳች፣ ከዳነም መልሳ ታቆስለዋለች፡፡ በዚህም ጊዜ ጌታችን ተገለጠላትና "ወዳጄ ጸበለ ማርያም ሆይ! ሰላም ለአንቺ ይሁን" አላት፡፡ ዳግመኛም "በእንዲህ ያለ የቁስል መከራ መሠቃየት ይበቃሻል" ካላት በኋላ ተሰወረ፡፡ እርሷ ግን ሰባት ጊዜ እስኪሆናት ድረስ ይህንን አደረገች፡፡ በዚህም ጊዜ ሥጋዋ እጅግ ታመመ፡፡ ሥጋዋ እንደ ድንጋይ ደርቆ ቢቀር የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ እንደተላለፈች ዐውቃ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ተወች፡፡ ❤ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ቅድስት ጸበለ ማርያም እየጸለየች ሳለ የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቆሰለ ችግረኛ ደሃ ሰው ተመስሎ ለቅድስት ጸበለ ማርያም ተገልጦ ወደ እርሷ በመምጣት ቁራሽ እንጀራ ለመናት፡፡ እርሷም ፈጥና ይዛ መጥታ ሰጠችው። እንጀራውንም ተቀብሎ ሲያበቃ "በመንገድ ብዛት ደክሜአለሁና በጀርባሽ አዝለሽ ትሸኚኝ ዘንድ እወዳለሁ" አላት፡፡ እርሷም ለድሆች አዛኝ ናትና አዝላው የድንጋይ መወርወሪያ ያህል እንደወሰደችው ቁስሉ ይድን ጀመር፡፡ ወዲያውም ቁስሉ ድኖ ምንም እንዳላገኘው ፍጹም ደህነኛ ሰው ሆነ፡፡ ያንጊዜም ፊቱ እንደፀሐይ አበራ፣ ሁለንተናውም ተለወጠ፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችን ከጀርባዋ ወርዶ በፊት ለፊቷ ቆመና "የከበርሽ አገልጋዬ ጸበለ ማርያም ሆይ! ምን እንዳድርግልሽ ትወጃለሽ?" አላት፡፡ እርሷም ከድንጋጤዋ የተነሣ እንደበድን ሆና መሬት ላይ ወደቀች፡፡ ጌታችንም አበረታትና እጇን ይዞ አነሣትና "የልብሽን መሻት ለምኚኝ" አላት፡፡ እርሷም "አምላኬ ሆይ ! በፊትህስ ሞገስ ካገኘሁ በሲኦል ያሉ ነፍሳትን ይቅር በላቸው" አለችው፡፡ በዚኽም ምክንያት በጌታችን ቸርነትና በእርሷም አማላጅነት ብዙ ነፍሳት ከሲኦል ወጡ፡፡ ጌታችንም ሰላምታ ሰጥቷት በክብር ዐረገ፡፡ ❤ ዳግመኛም ጌታችን ለቅድስት ጸበለ ማርያም ሦስት በትሮችን ሰጥቷት በእነርሱ እየተመረኮዘች እስከሲኦል ድረስ ትሄድና ነፍሳትን ታወጣና ታስምር እንደነበር ራሷ ተናገረች፡፡ ዳግመኛም ስትናገር "ሰማያውያን ብዙ ስሞች አወጡልኝ፣ "የወይን ፍሬ" እያሉ ይጠሩኛል፣ "የበረከት ፍሬ" የሚሉኝም አሉ፣ "የገነት ፍሬም" ይሉኛል" አለች፡፡ ዳግመኛም ከልዑል ዘንድ ብዙ ጸጋዎች እንደተሰጣት በሕይወት ሳለች ለአንደ ደገኛ ቄስ ነገረችው፡፡ ❤ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አምላክን በድንግልና የወለደች ክብርት እመቤታችን ለቅድስት ጸበለ ማርያም ተገለጠችላትና "ስሜን የተሸከምሽ ጸበለ ማርያም ሆይ! ሰላም ለአንቺ ይሁን" አለቻት፡፡ እመቤታችንም ብዙ ምሥጢርን ከነገረቻት በኋላ ጡቶቿንም አጠባቻትና በጸጋ የከበረች አደረገቻት፡፡ በስሟም ብዙ ተአምራትን የምታደርግ ሆነች፡፡
Mostrar todo...
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አሜን"። ❤ ❤ ጥር ፲፰ (18) ቀን። ❤ እንኳን ለፀሓየ ልዳ ለኮከበ ፋርስ ለሰማዕታት አለቃ ለቅዱስ ጊዮርጊስ (ለዝርወተ ዐፅሙ) ዐፅሙ ተቃጠጥሎ ተደቁሶ በይድራስ ተራራ በነፋስ ከተበተነ በኋላ ከሞት ለተነሳበት ዓመታዊ መታሰቢያ በዓል፣ ና በገድል ለተጸመደ ለከበረ አባት ለቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ መምህሩ ቁጥሩ ከሠለስቱ ምዕት ለሆነ ለአገረ ንጺቢን ኤጲስቆጶስ ለአባ ያዕቆብ ለዕረፍት በዓል በሰላም በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚህ ቀን ከሚታሰቡ፦ ከአራት ቀኖች በኋላ ጌታች ከመቃብር ያነሳ ከአልዓዛር እኅቶች ከቅድስት ማርያምና ከቅድስት ማርታ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። + + + ❤ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዝርወተ አፅሙ፦ በዚች ቀን ሰባ ነገሥታት ማሰቃየት በሰለቻቸው ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ መጭመቂያ ሆኖ ከተሠራ የስቃይ መሣሪያ ላይ አውጥተው ሰውነቱን እንዲሰነጥቁት ንጉሥ ዱድያኖስ አዘዘ፡፡ አንጀቱ ሁሉ ወጥቶ ከምድር ላይ እስኪዘረግፉት ድረስ እንዲህ አደረጉበት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከስቃይ ብዛት የተነሳ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች ሥጋውንም በሙሉ በእሳት አቃጠሉት አመድም ሆነ፡፡ ❤ ከሐዲው ንጉሥ ዱዲያኖስ የተቃጠለውን የሥጋውን አመድ አፍሰው በቀፎ አድርገው ይድራስ ወደሚባል ተራራ ወስደው ምዕመናን ራሩን አመዱን እንኳን እንዳያገኙት በነፋስ እንዲዘሩት አዘዘ፡፡ ደብረ ይድራስ ማለት ምድረ በዳ ማለት ነው፡፡ ወታደሮቹም የሥጋውን አመድ በተራራ ላይ ነስንሰው የተመለሱበት፣ የሥጋው አመድ ያረፈበት ዕፅዋት ሁሉ ጊዮርጊስ ጊዮርጊስ ያሉበት፣ ጌታችን ከመላእክት ጋር ተገልጦ አራቱን የምድር ነፋሳትንም የቅዱስ ጊዮርጊስ የሥጋውን ትቢያ እንዲሰበስብ አዞ። "የኔ ሆይ! የመረጥኩህ ወዳጄ ጊዮርጊስ ከሞት ተነሥ አትፍራ፤ እኔ አዝዤሀለሁና" ሲል ኀያሉን ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ጠራው። ያን ጊዜ ልዑል ንዑድ ጊዮርጊስም ከጫጉላ ቤት እንደሚወጣ ሙሽራ ምንም ሕማም ሳይኖርበት ተነሣ። ❤ መድኃኒታችንም ባረከው። "አትፍራ፤ ይኸንን ከሀዲ ንጉሥም እስክታሳፍረው ድረስ እኔ አጸናሀለሁ። ከእንዲህስ ወዲህ አምላኩ ከእጃችን ሊያአድነው አይችሉም እንዳይሉ እነዚህን ከሐድያን ነገሥታትና የረከሱ ጣዖታቸውን ታሳፍራቸው ዘንድ ተነሣና ወደ አገር ውጣ፤ ሰላሜ ለዘለዓለም ከአንተ ጋር ይሁን" አለው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ተናግሮ ሳመው። በፍጹም ምስጋናም ወደ ሰማይ ዐረገ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጌታች ይህንንም ቃል ኪዳን የተቀበለበት ቀን ነው፡፡ ምንጭ፦ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ። + + + ❤ አባ ያዕቆብ ዘንጽቢን፦ ይህም ቅዱስ ተወልዶ ያደገው በንጽቢን ከተማ ነው እርሱ ግን ሶርያዊ ነው ከታናሽነቱም የምንኵስና ልብስ መልበስን መረጠ ከጠጕር የተሠራ ማቅንም ለበሰ በጾም በጸሎት ተወስኖ በቀን በሌሊት በበጋ በሐሩር በክረምት ቊር የሚጋደል ሆነ ያንንም ማቅ ከቶ ከሥጋው ላይ አያወጣውም ነበር ምግቡም ቅጠላቅጠል ነው የሚጠጣውም የዝናብ ውኃ ብቻ ነው ስለዚህ ሥጋው ብሩህ ሆነ ነፍሱም እጅግ በራች። ❤ እግዚአብሔርም ሀብተ ትንቢት ድንቆች ተአምራቶችንም የመሥራት ጸጋን ሰጠው ለሰዎችም ከመሆኑ በፊት የሚሆነውን ይነግራቸውና እንዲሁም ይሆናል። ተአምራቱም እጅግ ብዙ ነው በአንዲትም ቀን ሴቶች በውኃ ምንጭ ላይ ያለማፈር ሲጫወቱና ሲሣለቁ አያቸው የውኃውንም ምንጭ አደረቀ የራሳቸውንም ጠጒር ነጭ ሽበትን አደረገ በተጸጸቱና የውኃውን ምንጭ እንዲመልስላቸው እየሰገዱ በለመኑት ጊዜ የውኃቸውን ምንጭ መለሰላቸው እንዳይታበዩም ይገሠጹ ዘንድ የራሳቸውን ጠጒር ነጭ እንደሆነ ተወው። ❤ በአንዲት ዕለትም በጐዳና አልፎ ሲሔድ አንዱን ሰው አስተኝተው ሰዎችን አገኛቸው መገነዣ ልብስም ይሰጣቸው ዘንድ ቅዱሱን ለመኑት እርሱ ግን በጸሎቱ ሰውዬውን ምውት አደረገው ሰዎችም ወደርሱ በተሰበሰቡ ጊዜ ሙቶ አገኙት ተጸጽተውም ሁለተኛ ያድንላቸው ዘንድ ለመኑት አዳነላቸውም። ትሩፋቱና ደግነቱም በተሰማ ጊዜ መርጠው በአገረ ንጽቢን ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት የክብር ባለቤት የክርስቶስን መንጋዎች ከአርዮሳውያ ተኵላዎች በበጎ አጠባበቅ ጠበቀ። ❤ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስም የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱን የከበሩ አባቶች በኒቅያ ከተማ በሰበሰባቸው ጊዜ ይህ አባት አብሮ አለ ከእርሳቸውም ጋር አርዮስን አውግዞ ከክርስቲያን አንድነት ለየው የቤተ ክርስቲያንንም ሥርዓትና በሁሉ ምእመናን ዘንድ የታወቀች የሃይማኖት ጸሎትን ሠራ። ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በደረሰ ጊዜ የሞተውን ሰው በጉባኤው ውስጥ አስነሥቷል። ❤ የፋርስ ንጉሥም መጥቶ አገረ ንጽቢንን በከበባት ጊዜ ይህ ቅዱስ ያዕቆብ የጭጋግ ደመና በሠራዊቱ ላይ አመጣ ትንኞችም ፈረሶቻቸውንና ጐበዛዝቶችን ነደፏቸው ፈረሶችም ማሠሪያቸውን ቆርጠው ፈረጠጡ የፋርስ ንጉሥም አይቶ ታላቅ ፍርሀትን ፈራ ተነሥቶም ሽሽቶ ወደኋላው ተመለሰ። ነፍሱን የመንጋዎቹንም ነፍስ ጽድልት ብርህት አድርጎ ገድሉንም በፈጸመ ጊዜ ጥር18 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ያዕቆብ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጥር 18 ስንክሳር። + + + ❤ የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦ "እስመ ኀልቀ ከመ ጢስ መዋዕልየ። ወነቅጻ(ጸ) ከመ ሣዕር አዕፅምትየ። ተቀሠፍኩ ወየብሰ ከመ ሣዕር ልብየ"። መዝ 101፥3-4። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 11፥19-33። + + + ❤ የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦ "ወእምኵሉ ያድኅኖሙ እግዚአብሔር። እግዚአብሔር የዐቅዐብ ኵሎ አዕፅምቲሆሙ። ወኢይትቀጠቀጥ አሐዱ እምውስቴቶሙ"። መዝ 33፥19-20። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 8፥35-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 3፥1-7 እና የሐዋ ሥራ 17፥30-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 5፥42-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ወይም የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ጊዮርጊስ ዝርወተ ዐፅም በዓልና የቅዱስ ባኮስ (አቤላክ) የስዋሬ በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
Mostrar todo...
Elige un Plan Diferente

Tu plan actual sólo permite el análisis de 5 canales. Para obtener más, elige otro plan.