🕊
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †
[ † እንኳን ለመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ዓመታዊ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ † ]
† 🕊 ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ 🕊 †
ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: [ሉቃ.፩፥፮]
የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ [አድናቆት] ይገባል !
እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ ፺ [90] የዘካርያስ ፻ [100] ደግሞ ደርሶ ነበር:: ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት [ኢሳ.፵፥፫] (40:3) , [ሚል.፫፥፩] (3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::
ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም ፳፮ [26] ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ፮ [6] ወራት ራሷን ሠወረች:: በ፮ [6] ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::
የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በሁዋላ በዚህች ቀን [ሰኔ ፴] (30) ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ
+ የቅዱሳኑ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ
+ በማሕጸን ሳለ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት
+ በበርኀ ያደገና በገዳማዊ ቅድስና ያጌጠ
+ እሥራኤልን ለንስሃ ያጠመቀ
+ የጌታችንን መንገድ የጠረገ
+ ጌታውን ያጠመቀና
+ ስለ እውነት አንገቱን የተቆረጠ ታላቅ ሰው ነው::
ስለዚሕም ቤተ ክርስቲያን ነቢይ: ሐዋርያ: ሰማዕት: ጻድቅ: ገዳማዊ: መጥምቀ መለኮት: ጸያሔ ፍኖት: ቃለ ዐዋዲ ብላ ታከብረዋለች::
† 🕊 አባ ጌራን ሕንዳዊ 🕊 †
ዳግመኛ በዚህች ቀን ሕንድ ካፈራቻቸው ታላላቅ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት ጻድቁ አባ ጌራን ይታሰባሉ:: የእኒህ ቅዱስ ታሪክ አሳዛኝ ነው:: ቅዱሱ በሕንድ ተወልደው: በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አድገው: ገና በወጣትነታቸው መንነው: ደሴት ውስጥ ወደሚገኝ አንድ በርሃ ገብተዋል:: ከገድላቸው ጽናት: ከቅድስናቸውም ብዛት የተነሳ በሃገረ ሕንድ ሰይጣን እንዳይገባ: ጠብ ክርክር እንዲጠፋ: ሰው ሁሉ በፍቅርና በሰላም እንዲኖር ማድረግ ችለው በጣም ተወዳጅ ነበሩ::
በዚህ የተበሳጨ ሰይጣን ግን ባልጠረጠሩት መንገድ መጣባቸው:: አንዲት ሴት ወደ እርሳቸው መጥታ [የንጉሡ ልጅ ነኝ በሚል] አስጠግተዋት ነበር:: አንድ ሌሊት ላይ ግን አውሬ ያባረራት በመምሰል ሩጣ ወደ ቤታቸው ገብታ አቀፈቻቸው:: በዚያ ቅጽበት ፍጡር ደካማ ነውና ታላቁ አባ ጌራን ተሰነካከሉ:: ከአፍታ በሁዋላ የሆነውን ሲያውቁ ደም አለቀሱ::
ልብሳቸውን ቀደው: እንባቸው እንደ ዥረት እየፈሰሰ አለቀሱ:: ራሳቸውን በትልቅ ድንጋይ እየቀጠቀጡት የጭንቅላታቸውና የደረታቸው አጥንቶች ተሰባበሩ:: እርሱ እግዚአብሔር መሐሪ ነውና ይቅር ብሎ: የቅድስና ስም ሰጥቶ በዚሕች ቀን ወደ ገነት አሳርጉዋቸዋል:: ለዚህ ነው መጽሐፉ "ጻድቅ ፯ [7] ጊዜ ይወድቃልና: ይነሣማል" ያለው:: [ምሳ.፳፬፥፲፮] (24:16)
አምላካችን ከቅዱሱ ቤተሰብና ከጻድቁ አባ ጌራን በረከት ይክፈለን::
🕊
[ † ሰኔ ፴ [ 30 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት [ልደቱ]
፪. ቅዱሳን ዘካርያስና ኤልሳቤጥ [ወላጆቹ]
፫. አባ ጌራን መስተጋድል [ሕንዳዊ]
፬. ቅዱሳት ደናግል ማርያና ማርታ [ከ፴፮ (36) ቱ ቅዱሳት አንስት-የአልዓዛር እህቶች]
[ † ወርኀዊ በዓላት ]
፩. ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ [ሐዋርያ]
፪. አባ ሣሉሲ ክቡር
፫. ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
፬. ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
" ደግሞም አንተ ሕጻን ሆይ የልዑል ነቢይ ትባላለህ:: መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሔዳለህና:: እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ:: ይሕም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው::" [ሉቃ.፩፥፸፮]
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
subscribe&share እያረጋችሁ
https://www.youtube.com/@bonny1221
ይህ የተለግራም ግሩፕ ሊንክ ነው👇👇👇
https://t.me/Dnwonde
channel
https://t.me/orthodoxchallenge
https://www.facebook.com/DeaconWondalemAlemayehu/