ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ
Ir al canal en Telegram
ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።
Mostrar más611
Suscriptores
Sin datos24 horas
-17 días
-930 días
Archivo de publicaciones
🌼 ቅዱስ ዮሐንስ በተለያዩ ስሞች ይጠራል፡፡ በሕይወቱና በኑሮው ሁሉ ጌታችንን ለመምሰል ይጥር ነበርና ጌታችንም እጅግ ይወደው ስለነበር "ፍቁረ እግዚእ" ተባለ፡፡ የታላቁ ያዕቆብ ታናሽ ወንድም ስለሆነና አባቱም ዘብድዮስ ስለሚባል "ዮሐንስ ወልደ ዘብድዮስ" ተባለ፡፡ ለጌታችን ባለው ቅናትና ከወንድሙ ጋር ሆነው ባሳዩት የኃይል ሥራ እንዲሁም የጌታችንን አምላክነት በመግለጡ "ወልደ ነጎድጓድ" ተብሏል፡፡ ነገረ መለኮትን ከሌሎቹ በበለጠ ሁኔታ አስፍቶና አምልቶ በማስተማሩ "ነባቤ መለኮት ወይም ታኦሎጎስ" ተብሏል፡፡ ኃላፊውንና መጻዒውን ጊዜ በራእዩ ስለገለጠ "አቡቀለምሲስ" ተባለ፣ ይህም በግሪክኛ ባለራእይ ማለት ነው፡፡ የጌታችንን መከራ መስቀሉን እያስታወሰ 70 ዘመን ሙሉ እያለቀሰ ስለኖረና ፊቱም በሀዘን ስለተቋጠረ "ቁጽረ ገጽ" ተብሏል፡፡ ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያስትፈን። በጸሎቱ ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን።
✝ ✝ ✝
🌼 #የእስክንድርያ_ሊቀ_ጳጳሳት_አባ_መቃርስ፦ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ከቍጥራቸው ውስጥ ነው። ይህም አባት ከታናሽነቱ ጀምሮ በገድል የተጠመደ ሆነ የምንኲስናንም ልብስ ሊለብስ ወዶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ወጣ። በዚያም በመጀመሪያው አባት በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መነኰሰ በምንኲስና ያለውንም ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ።
🌼 ይህምእርሱም ሁልጊዜ መጻሕፍትን የሚያነብና ትርጓሜያቸውንም የሚያስረዳ ሁኗልና በትሩፋት ስራ ከፍ ከፍ ባለ ጊዜ ቅስና ተሾመ። ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤልም በዐረፈ ጊዜ ኤጲስቆጶሳቱ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔዱ። ከእርሳቸውም ጋር ሃይማኖታቸው የቀና ብዙዎች አዋቂዎች ካህናት ነበሩ በአስቄጥስ ገዳም ከሚኖሩ ከታላላቅ መነኰሳትም ጋራ ስብሰባ አድርገው ለዚች ለከበረች ሹመት ስለሚገባው ሰው እየመረመሩ ብዙ ቀኖች ተቀመጡ።
🌼 ከዚህም በኋላ የተሻለና ለዚች ለከበረች ሹመት የሚገባ ይህን አባ መቃርስን አግኝተው ሊቀ ጵጵስና ሊሾሙት ሁሉም በአንድ ምክር ተስማው። ስለ ትሩፋቱና ስለ ተጋድሎው በአስቄጥስ ገዳም የሚኖሩ ብዙ መነኰሳት ምስክሮች ሁነዋልና ይዘውትም ሊሔዱ ያለ ፍቃዱ ይዘው አሰሩት እርሱ ግን እንዲህ እያለ ይጮህ ነበር። "እኔ ለዚች ለከበረች ሹመት የማልገባ ነኝ እናቴ ሁለት ባሎችን አግብታ ስለነበር" ይህንንም ያለው እንዲተዉት እንጂ እናቱ ግን በአንድ ባል ብቻ የኖረች ሌላ የማታውቅ ንጽሕት እንደሆነች ስለርሷ ብዙዎች ምስክሮች ሁነዋልና። ስለዚህ እርሱ የተናገረውን ምክንያት አልተቀበሉትም።
🌼 ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ወስደው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት ከዚያም ወደ ምስር አውጥተው በመዓልቃ በሚገኘው አምላክን በወለደች በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሹመቱ ደብዳቤ በዮናኒ በቅብጥ በአረብ ቋንቋ ተነበበች።
🌼 ከዚህም በኋላ በሹመቱ ወራት በጎ ስራ ትሩፋትን ተጋድሎውን አብዝቶ የሚሰራ ሆነ ። ሁል ጊዜም ለህዝቡ እግዚአብሔርን እንዲፈሩ ያስተምራቸዋል ስለ ነፍሳቸውም ድኀነት ይገሥጻቸው ነበር።
🌼 በሹመቱ ወራትም ከራሱ ከሚገባው ከግብሩ ለቤተ ክርስቲያን ይሰጣል ለድኆችና ለችግረኞችም ይመጸውታል እንጂ ከቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ምንም ምን አልወሰደም። በሹመቱም ሃያ ሰባት ዓመት ኖረ እግዚአብሔርንም አገልግሎ ደስ አሰኝቶ በሰላም በፍቅር ሳለ ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ መቃርስ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የመስከረም 4 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
🌼 "#ሰላም_ለመቃርስ_በእስክንድርያ_ዘተአምነ። መርዔተ ክርስቶስ ይርዓይ መሲሐውያነ። ለእለ ኀረይዎ ሕዝብ ዘይሰመዩ ኄራነ። ጸሊዖ ሢመተ እንዘ ውእቱ ኢኮነ። ወልደ ዳግሚት ብእሲት ይቤሎሙ አነ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመስከረም_4።
🌼 "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼
🌼 #መስከረም ፬ (4) ቀን።
🌼 እንኳን #ለሐዋርያው_ለወንጌላዊው ለወልደ ነጎድጓድ #ለቅዱስ_ዮሐንስ_ለልደት_በዓል፣ #ለነዌ_ልጅ_ለቅዱስ_ኢያሱ ለመታሰቢያ በዓሉና ለእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #ለአባ_መቃርስ_ዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #በአንጾኪያ_በሰማዕትነት_ከዐረፉ_ከ_2መቶ_ሰዎች ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝️ ✝️ ✝️
🌼 #ቅዱስ_ዮሐንስ_ወንጌላዊ፡- ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልን ለመስበክ ዕጣ የደረሰው እስያ ስለነበር ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን አስከትሎ ሄደ፡፡ ይኽችውም ኤፌሶን በጥንቱ በታናሽ እስያ በዛሬው የቱርክ ግዛት ውስጥ ከተማ ናት፡፡ ዛሬ ኢያዞሎክ ተብላ የጥንት ታሪኳ ጠፍቷል፡፡ አስቀድሞ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን ሰብኮባታል፡፡ ደቀ መዝሙሩን ቅዱስ ጢሞቴዎስንም በከተማዋ ላይ ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ እርሱም በግፍ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ቅዱስ ዮሐንስን እየረዳው በከተማዋ ብዙ አገልግሏል፡፡ በኋላ ግን በግፍ ገድለውታል፡፡
🌼 ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ኤፌሶን ለመሄድ በመርከብ ሲሳፈር መርከቡ በማዕበል ተሰበረ፡፡ ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን ማዕበሉ ወደ አንዲት ደሴት አደረሰው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን በመርከቡ ስባሪ ተንጠልጥሎ በባሕሩ ማዕበል መካከል 40 ቀንና 40 ሌሊት ከኖረ በኋላ ማዕበሉ ተፍቶ አብሮኮሮስ ካለበት ደሴት አደረሰውና ተያይዘው ኤፌሶን ከተማ ገቡ። የከተማይቱም ሰዎች እጅግ ክፉዎች ስለነበሩ መጀመሪያ ላይ ቅዱስ ወንጌልን መስበክ አልቻሉም ነበር፡፡ እነርሱም እጅግ ክፉዎች መሆናቸውን ስላወቀ ቅዱስ ዮሐንስ ገና ዕጣው ሲደርሰው በሀዘን አልቅሶ ነበር፡፡ አሁንም ከተማው በገቡ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ምክንያት በመፍጠር ሮምና ለምትባል ሴት የውሽባ ቤቷ እሳት አንዳጅ ሆኖ አብሮኮሮስም ዕቃ አጣቢ ሆነው ተቀጠሩ፡፡ የቀጠረቻቸው ሴትም እጅግ ታሠቃያቸው ጀመር፡፡ ባሮቿ እንደሆኑ ተስማምተው ስለጻፉላት ትደበድባቸውም ነበር፡፡ እነርሱም በታላቅ ጉስቁልና ውስጥ እየኖሩ እያለ በአንዲት ዕለት የአገረ ገዥው ልጅ ለመታጠብ ወደ ውሽባው ቤት ገባ፡፡ በውሽባ ቤቱም የሰይጣን ኃይል ስለነበረበት የመኰንኑን ልጅ አንቆ ገደለው፡፡ የአገሪቱም ሰዎች ሁሉ ለሞተው የመኰንን ልጅ ሊያለቅሱ ሲሰበሰቡ ቅዱስ ዮሐንስም አብሮ ቆሞ ሲመለከት ሮምና መጥታ "በጌታዬ ልጅ ሞት ልትደሰት መጣህን" እያለች ረገመችው፡፡ እርሱም "አይዞሽ አትዘኚ" አላትና ወደ ሞተው ልጅ ቀርቦ በመስቀል ምልክት ካማተበበት በኋላ በፊቱ እፍ አለበት፡፡ የሞተውም ልጅ ድኖ ተነሣ፡፡ የሀገሪቱም ሰዎች እጅግ ደነገጡ፡፡ ሮምናም ደንግጣ "እግዚአብሔር የሚሉት አምላክ አንተ ነህን" ብላ ጠየቀችው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም "በፍጹም እኔ አምላክ አይደለሁም፣ እኔ የእርሱ አገልጋዩና ሐዋርያው ነኝ እንጂ" አላት፡፡ ሮምናም ስለበደለቻቸው በደል ሁሉ መሪር ዕንባን እያለቀሰች ይቅር እንዲሏት ለመነቻቸው፡፡ እነርሱም አረጋጉዋት፡፡ ከሕዝቡም ውስጥ ብዙዎቹ በጌታችን አመኑ፡፡
🌼 ቅዱስ ዮሐንስም ሌሎች ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ ወንጌልን እየሰበከ ከጣዖት አገልጋዮች በቀር ሁሉንም አሳምኖ አጠመቃቸው፡፡ አገልጋዮችን ኤጲስቆጶሳትን፣ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ከሾመላቸው በኋላ ወደ ሌሎች አቅራቢያ አገሮች ሄደ፡፡
በመጨረሻም በከሃዲውና በጨካኙ በድምጥያኖስ ዘመን በጣዖት አምላኪዎች ተከሶ ለፍርድ ቀረበ፡፡ በፈላ ውኃ ካሠቃዩት በኋለ በፍጥሞ ደሴት አጋዙት፡፡ በዚያም ሳለ ራእዩን ተመልክቶ ጻፈው፡፡ ድምጥያኖስም ከተገደለ በኋላ ከግዞቱ ተመልሶ ሦስቱን መልእክታቱንና ቅዱስ ወንጌሉን ጽፏል፡፡
🌼 ጌታችንም አስቀድሞ ሞትን እንደማይቀምስ ለዮሐንስ ቃል ገብቶለት ነበርና (ዮሐ 21፡22) ጥር 4 ቀን እንደ ኤልያስና ሄኖክ ሞትን እንዳያይ ወደ ብሔረ ሕያዋን ወስዶታል፡፡ ጌታችን ለዮሐንስ ያልነገረው እርሱም ያላስተማረው ምሥጢር የለም፡፡ ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር "በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ..." ብሎ የጌታችን ነገር ተመራምሮ ለመድረስ ሲል በመሀል መልአኩን በዮርዳኖስ ባሕር ላይ ሲሄድ አገኘው፡፡ መልአኩም የዮርዳኖስን ባሕር በእንቁላል ቅርፊት እየጨለፈ ወደ ውጭ ሲያፈስ ተመለከተው፡፡ ዮሐንስም ተገርሞ "ምን ማድረግህ ነው" አለው፡፡ መልአኩም "የዮርዳኖስን ባሕር ቀድቼ እየደፋሁ ልጨርሰው ነው" ሲለው ዮሐንስም መልሶ "ታዲያ በእንቁላል ስባሪ ነውን?" አለው፡፡ መልአኩም "አዎን" አለው፡፡ ዮሐንስም "በከንቱ ደከምክ" አለው፡፡ ይህን ጊዜ መልአኩም መልሶ "አንተስ እንጂ ደግሞ የአምላክን መገኘት፣ አኗኗሩንም ተመራምረህ በጥበብ ለማግኘት ብለህ "በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ.." ብለህ ጀምረህ የለምን? አንተ ጌታን ተመራምረህ ካገኘህና ከደረስክበት እኔም የዮርዳኖስን ወንዝ በዚህ እንቁላል ቅርፊት ቀድቼ እጨርሰዋለሁ" አለው፡፡ ዮሐንስም ይህን ጊዜ ደንግጦ ዝቅ ብሎ "ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ…" ብሎ ሀሳቡን ለወጠና ሌላ ታሪክ ቀጠለ፡፡
🌼 ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ክርስቲያኖችን ሁሉ ወክሎ እመቤታችንን በአደራ የተቀበለ እርሱም ለእመቤታችን በአደራ የተሰጠ ሲሆን እመቤታችንን ከወሰዳት በኋላ ለ15 ዓመት እየተንከባከበ ጠብቋታል፡፡ እናቱም በሕፃንነቱ ስለሞተች እመቤታችን ናት እየተንከባከበች ያሳደገችው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በመልኩም ከጌታችን ጋር ይመሳሰል ነበር፡፡
🌼 ቅዱስ ዮሐንስ ሥዕል የመሳል ተሰጥኦም ነበረው፡፡ ጌታችን በተሰቀለበት ዘመን የነበረው ጢባርዮስ ቄሳር ልጁ በሽተኛ ነበር፡፡ የጌታችንን የማዳን ሥራ እየሰማ እነ ጲላጦስም ስለጌታችን የሚጽፉለትን ይሰማ ስለነበር ልጁን ከጌታችን መቃብር ላይ እንዲያኖሩለት ላከው፡፡ ልጁም ፈጥኖ ተፈወሰለት፡፡ ጢባርዮስ ቄሳርም በልጁ መዳን ምክንያት የጌታችንን ውለታ ማስቀመጥ ፈልጎ የጌታችንን ሥዕሉን የሚሥልለትን ሲያጠያይቅ ቅዱስ ዮሐንስን አገናኙት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ጌታችንን ልክ በዕለተ ዓርብ እንደተሰቀለ አድርጎ በመሣል ለጢባርዮስ ቄሳር ሰጠው፡፡ ሲሥለውም በመጀመሪያ ጌታችንን ልክ እንደተሰቀለ አድርጎ ራቁቱን ነበር የሳለው፡፡ ዮሐንስ የሳለው የጌታችን ሥዕልም አፍ አውጥቶ "በመጀመሪያ አይሁድ በኢየሩሳሌም ራቁቴን ሰቀሉኝ፣ አሁን ደግሞ አንተ ድጋሚ በሮም ራቁቴን ትሰቅለኝን?" ብሎ ተናገረው፡፡ ዮሐንስም እጅግ ደንግጦ "እንዴት አድርጌ ልሳልህ?" ብሎ የሳለውን ሥዕል ቢጠይቀው ሥዕሉም "ከለሜዳ አልብሰህ ሳለኝ" አለው፡፡ ዮሐንስም እንዳለው ከለሜዳ አልብሶ ከሳለው በኋላ ሥዕሉን ትኩር ብሎ ተመልክቶ ቢስመው ከንፈሩ አንድ ቀን ተኩል ያህል ተጣብቆ ቆይቷል፡፡ ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጠቀምባቸውን የጌታችንን ስነ ስቅለት የሚያሳዩ ሥዕሎች መገኛቸው ይህ ወንጌላዊው ዮሐንስ የሳለው ሥዕል ነው፡፡
🌼 "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼
🌼 #መስከረም ፬ (4) ቀን።
🌼 እንኳን #ከግብጽ_ለኢትዮጵያ_ሊቀ_ጳጳስ ተሾመው ለመጡ በመላው ዓለም እና በኢትዮጵያ ብዙ የዋሻ እና የሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን ላነጹ #ለብፁዓዊ_አቡነ_ሙሴ ዘድባ ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
🌼 #ብፁዕ_አቡነ_ሙሴ_ዘድባ፦ በአባታቸው የእቤታችን ጠባቂ የአረጋዊ ቅዱስ ዮሴፍ የልጅ ልጅ ሲሆኑ፤ በእናቸው በኩል ድንግል ማርያም ከልጇ ጋር በቃና ዘገሊላ ሰርግ የተገኘችበት የዶኪማስ የልጅ ልጅ ናቸው። የአባታቸው ስም ቅዱስ ዮስጦስ ሲባል፤ የእናታቸው ስም ቅድስት ጵስርስቅላ (ሶልያና፡ማርያም) ይባላል።
🌼 በሊቀ መላእክት በቅዱስ ገብርኤል አብሳሪነት ታኅሣሥ 8 ቀን ተወለዱ። በዚህች ቀን ከእናታቸው እቅፍ በመውረድ "ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን፤ ከጨለማ ወደ ብርርሃን ላወጣኸኝ" ብለው ፈጣርያቸውን አመስግነዋል። በ40 ኛው ቀን የጌታ ሐዋርያት ቅዱሳን ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ፊሊጶስና እንድርያስ ሆነው ጥር 18 ክርስትናን አቡነ ሙሴን አነሱዎቸው።
🌼 በ3 ዓመታቸው ወላጆቻቸው ለቤተ ክርስቲያን ሰጧቸው። ቅዱስ ፋኑኤልና ቅዱስ ዮናኤል ሕብስት ሰማያዊ እያመጡ ይመግቧቸው ነበር። ከዚህ በኋላ መምህራቸው ዝክረ ጻድቅ ብሉያትንና ሐዲሳትን አስተማራቸው። በወንጌላዊው በቅዱስ ማርቆስ እጅ ዲቁና ተሾሙ። እመቤታችን ማርያምም ለብፁዓዊ ሙሴ ልፋፈ ጽድቅ፣ ሰኔ ጎልጎታን፣ ባርቶስና ራዕየ ማርያምን ሰታቸዋለች። ወገባቸውን ከጠጉር በተሰራ መታጠቂያ ይታጠቁ ነበር። አቡነ ዘበሰማያትም በጀመሩ ጊዜ ሰባቱ ሰማያት ተከፍተውላቸው ከአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ጀምሮ ሁሉንም ቅዱሳን በግልጥ ያያሉ። ሲሰግዱ እንባቸው ደረታቸውና እግራቸውን እያራሰ በመሬት ይፈሳል። በዓለም ብዙ የዋሻ ቤተ ክርስቲን አንጸዋል።
🌼 የህንፃ ሥራ ከመደመራቸው በፊት 40 ቀን ይጾማሉ። ሁለቱ መላእክት ቅዱስ ፍርክኤልና ቅዱስ ፍናኤል እየረዷቸው መቅደስን ያንጻሉ። የዋሻ ቤተ መቅደስ ሥራ ጎን ለጎን መስቀልና ሌሎች ንዋየ ቅዱሳት ይሠራሉ። የሚሠሯቸው መቅደሶች ከፊሉ የሚታዩ ምዕመናን የሚገለገሉባቸው ሲሆን የቀሩት የማይታዩ ስውራን የሚገለገሉበት ነው።
አቡነ ሙሴ ጵጵስና የተሾሙት በ 12ቱ ሐዋርያት በአንድነት ነው። ዘመናቸውን ሁሉ ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር በመሆን የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስን መንበር አጥነዋል። በድንግልናቸው በንጽሕናቸው የከበሩ 12 ክንፍ የተጎናጸፉ ናቸው። ጥቂቶች ለማየት የታደሉትን ብሔረ ብፁዓን ሄደው አይተዋል።
🌼 አቡነ ሙሴ በግብፅና በእስራኤል መካከል ሲካር በሚባል ቦታ ካገለገሉ በኋላ ጣዖታትን ለማሳፈር ወደ መቄዶንያ ሄደው ጣዖት አምላኪውን ንጉሥ ገሰጹት። ንጉሥ ተቆጥቶ አጥንታቸው እስኪሰበር ድረስ በብረት አስደብድቦ በብረት አልጋ ላይ አስተኝቶ እሳት አነደደባቸው። ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ግን ዳሰው ፈወሷቸው። በማግስቱ ወደ ፍርድ አደባባይ ቢወስዷቸው ምንም እንዳልሆኑ ንጉሡ በማየቱ በንዴት ሰውነታቸውን በሰይፍ አስቆራረጠ። ከሰውነታቸው ደም፣ ውሃ፣ ወተትና መዓር ወጣ። ጌታችንም አድኗቸው "በስምህ የተማፀነውን መልካም ነገር አደርግታለሁ" ብሎ ቃል ኪዳን ገባላቸው።
🌼 በግብጽ አንስጣስዮስ ቴዎዶስዮስ ተብለው ሢነግሡ መላእክት የአባቱ የዳዊት መንግሥት ቅባት ቀቧቸው፤ የመንግሥት ልብስ አለበሷቸው፤ የመንግሥት ሥርዓት ሁሉ ሰጧቸው። የጣዖታትን ቤት አፍርሱ "ቤተ ክርስቲያንን ሥሩ" በማለት ኅዳር 12 ቀን አዋጅ ነጋሪን ላኩ። ጌታችን በግብፅ ተሶዶ ሳለ ለአረጋዊ ቅዱስ ዮሴፍ የተናገረው ትንቢት ተፈፀመ "ከልጅህ የሚወለድ በግብፅ ያሉትን ጣዖቶች አፍርሶ ሃይማኖትን ያጸናል" ብሎ ነበር። እዲሁም ቅድስት አርሴማ ሳትወለድ በስሟ የተሰየመውን ታቦት በግብፅ ያገኙና ያከበሩ ናቸው (ገድለ አርሴማ 7ኛ ተአምር)።
🌼 በግብፅ ደብረ ምጥማቅ ማርያም በመጀመሪያ ሰርተው የቀደሱት አቡነ ሙሴ ናቸው። በተጨማሪ ብዙ የሕንጻ ቤተ ክርስቲያንና የዋሻ ቤተ ክርስቲያን አንጸዋል። እንደ ቅዱሳን ብዙ ድንቅ ተአምር አድርገዋል። ለምሳሌ አውሬ ገድሏቸው ተጠራቅሞ የነበረ አፅም ላይ ጸልየው አራት ሺህ የሞቱ ሰዎችን ከሞት አስነስዋል። 40 ዓመት በንግሥና ከቆዩ በኋላ ከብዙ ተከታዮቻቸው ጋር ወደ አስቄጥስ ገዳም ለምነና ስጓዙ በበረሃው ተርበው ለወደቁት ወደ እግዚአብሔር ሲጸልዩ መና ወርዶላቸው መግበዋል አስቄጥስ ገዳም ሲደርሶ አቡነ መቃርስ ነበሩ የተቀበሏቸው፡፡
🌼 በአስቄጥስ በአቡነ እንጦንስ ስም የመጀመሪያውን ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ከፈፀሙ በኋላ አቡነ እንጦንስንና አቡነ መቃርስ በምንኵስና ልብስ፣ በመላእክት አስኬማ፣ በቅንዓት፣ በቀሚስና በቆብዕ ላይ ለ40 ቀን ጸልየው ጥር 22 ቀንተክለ ማርያም ብለው ሰይመው አመነኰሷቸው። በዚያውም አቡነ መቃርስ ከበታቻቸው ሾሙ። በአስቄጥስ ብዙ ተከታዮቻቸውን አመንኵሰው ቀድሞ ወደ፡ሠሯቸው ቤተ መቅደሶች ይልኳቸው ነበር። የቀሩት ደግሞ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ አብረዋቸው መጥተዋል።
🌼 የኢትዮጵያ የመጀመርያው ጳጳስ አቡነ ሰላማ በማረፋቸው ነገሥታት አብርሃ ወአጽብሃ ጳጳስ እንዲልኩላቸው ከእጅ መንሻ ጋር ወደ ግብፅ ላኩ። አቡነ አትናቴዎስ ፈቃደ እግዚአብሔር ጠይቀው አቡነ ሙሴ ከአስቄጥስ ገዳም ለኢትዮጵያውያን አባት እዲሆኑ አቡነ ሚናስ ብለው ሾሙ። ከሦስት ሺህ ልጆቻቸው ጋር ሆነው ብዙ ቅርስ ይዘው አባታችን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ሕዝቡ በደስታ ተቀበሏቸው። ብዙ መጽሐፍትን ከአረብኛ ወደ ግእዝ ቋንቋ ተርጉመው ጽፈዋል። ይጽፉበት የነበረው ብዕር አድሮ በማግስቱ ለምልሞ አብቦ ይገኛል። ቀለም ይበጠብጡበት የነበረው የቀንድ ዋንጫም ከመሬት ተጣብቆ ያገኙት ነበር። በእጃቸው ሲያላቅቁት ከመሬት ጠበል ይፈልቃል፣ በጠበሉም ህሙማንን ፈውሰውበታል።
🌼 በኢትዮጵያ 5መቶ የዋሻ ቤተ ክስቲያን ያነጹ ሲሆን በአጠቃላይ በመላው ዓለም ከ10 ሺህ በላይ ቤተ ክርስቲያ ሰርተዋል፣ አንጸዋል (መለከት መጽሔት 2007 ዓ.ም)። በእንቁና በእብነ በረድ ከሠራቸው ቤተ ክርስቲያኖች መካከል በአራራት ደብር (ከምድር ጥፋት በኋላ የኖኅ መርከብ መጀመርያ ያረፈችበት) በጻድቁ ኖኅ ስም፣ አብርሃም ሥላሴን በድንኳኑ ባስተናገደበት ስፍራ በቅድስት ሥላሴ ስም፣ በሕንድ (በሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ መቃብር ቦታ) በቅዱስ ቶማስ ስም፣ በአርማንያና በፋርስ (በሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስጋውን ባሳረፉበት ቦታ) በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም።
🌼 በኢትዮጵያ በአቡነ ሙሴ ከታነጹት ቤተ ክርስቲያ ውስጥ የተወሰኑት፦
1.የድባ መቅደሰ ማርያም አቡነ ሙሴ አንድነት ገዳም (ባለ ሰባት መቅደስ ፎቅ)፣ የረፍታቸው ቦታ፣ በትረ ሙሴያቸውና የእጅ መስቀላቸው ያለበት (ሰሜን ወሎ ዳውንት)
2.አእማድ ቅድስት ሥላሴ ገዳም (መቄት) እንደ አቡነ አሮን መንክራዊ ጣራው ክፍት ሆኖ ዝናብ የማይገባው፣
🌼 በመጨረሻ ብፁዕ አቡነ ሙሴ በቤተ ሚናስ ቤተመቅደስ የድባ መቅደሰ ማርያም አቡነ ሙሴ ገዳም መሰከረም 4 በዕለተ እሁድ ዐረፋ። ወርሃዊ በዓላቸው ወር በገባ በ4 ነው። በተለይ ጋብቻን የሚቀድሱ፣ ክህነት የሚባርኩ፣ መናንያንን የሚያጸኑ አረጋዊን አባት ናቸው። ከአባታችን ከብፁዕ አቡነ ሙሴ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትንና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸውም ይማረን!። ምንጭ፦ የድባ መቅደሰ ማርያም አቡነ ሙሴ አንድነት ያሳተመው መጽሔት ላይ የተወሰደ።
🌼 ያን ጊዜም ሳሙኤል መጣ ንጉሥ ኢጋቦም በበረሃ ውስጥ ወደአነፃት ቤተ ክርስታያን ወሰደው እርሷም ገዳማውያን የሚሰበሰቡባት ተሰውራ የምትትኖር ናት ወደርሷም በደረሱ ጊዜ ቅዱሳን ተሰብስበው መሥዋዕትን ሲያሳርጉ አገኙና በአንድነት ሥጋውንና ደሙን ተቀበሉ ሰንብትም ከሆን በኋላ ከቅዱሳን መቃብር በረከትን ሊቀበሉ ከአባ ሳሙኤል ጋራ አብረው ሔዱ ከዚያም ደርሶ አባ ሙሴ ሰገደ ወዲያውም ዐረፈ አባ ሳሙኤልም ቀበረው ገድሉንም ጻፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ሙሴ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የመስከረም 2 ስንክሳር።
✝️ ✝️ ✝️
🌼 "#ሰላም_ለሙሴ_ዘረሰየ እምዓለም ተፈልጦ። ቈጽለ ሆሣዕና አራዘ ወፍሬ ዘይቶን ሥብጦ። በብዙኅ መከራ አምድኅረ ሰይጣን አስፈጦ። #እግዚአብሔር መሐሪ መንገደ ገዳም ሜጦ። ኀበ ሥጋሁ የዓርፍ ወነፍሶ ይትሜጦ። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመስከረም_3።
✝️ ✝️ ✝️
🌼 #የዕለቱ_ምስባክ፦ "እስመ አድኀንካ ለነፍስየ እሞት። ወለአዕይንትየኒ እምአንብዕ። ወለእገርየኒ እምዳኅዕ"። መዝ 55፥13-14። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ተሰ 3፥13-ፍ.ም፣ 2ኛ ዮሐ 1፥8-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 20፥28-31። የሚነበበው ወንጌል 18፥18-23። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የአባ አንበስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta) Saints Of The Orthodox Tewahedo Church.:
🌼 "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼
🌼 #መስከረም ፫ (3) ቀን።
🌼 እንኳን #ለገዳመ_ሲሐቱ_ለአባ_ሙሴ ለዕረፍት በዓል፣ የከበረ አባት #ሊቀ_ጳጳሳት_አባ+ዲዮናስዮስ ከተሾመ በሁለተኛው ዓመት በእስክንድርያ ከተማ ነፍስ ከሥጋዋ ጋር ትሞታለች በዕለተ ትንሣኤም ከሥጋዋ ጋር አብራ ትነሣለች ስለሚሉ ክፉዎች #የኤጲስቆጶሳት_የአንድነት_ጉባዔ ለተደረገበት ቀን በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከሰማዕት_ከአባ_ዲዮስቆሮስ፣ ሰማዕት ከሆነ ከሊቀ ጳጳሳት #አባ_ዲዮናስዮስ፣ #ከዲያቆን_በትንከል፣ ከብዙዎች የፋርስ ሰማዕታት ከዕረፍታቸው መታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝️ ✝️ ✝️
🌼 በዚች ቀን የከበረ አባት ሊቀ ጳጳሳት #አባ_ዲዮናስዮስ ከተሾመ በሁለተኛው ዓመት በእስክንድርያ ከተማ የኤጲስቆጶሳት የአንድነት ጉባዔ ተደረገ።
🌼 ይህም ጉባዔ የሆነው ነፍስ ከሥጋዋ ጋር ትሞታለች በዕለተ ትንሣኤም ከሥጋዋ ጋር አብራ ትነሣለች ስለሚሉ ክፉዎች በዐረቢያ አገር ስለ ተነሡ ሰዎች ነው። እነርሱም ለከፋችና ብልሹ ለሆነች ሃይማኖታቸው የፈጠራ ድርሰትን ደርሰው በእስክንድርያ ከተማ ወደሚኖሩ ሰዎች ላኩ።
🌼 አባታችን ሊቀ ጳጳሳት አባ ዲዮስናስዮስም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ ከዚህ ከክፉ ሥራም እንዲመለሱ አስተማራቸው ገሠጻቸውም እነርሱ ግን አልሰሙትም አልተመለሱም። ስለዚህም በእነርሱ ላይ ይህን ጉባዔ ሰብሰቦ ተከራከራቸው ስሕተታቸውንም ገልጾ አስረዳቸው እነርሱ ግን ሰይጣን አሳውሮአቸዋልና ተጸጽተው አልተመለሱም ይህም ጉባኤ ረግሞ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ለይቶ አሳደዳቸው።
🌼 ይህም አባት ዲዮናስዮስ ስለርሳቸው ድርሳናትን ደረሰ በውስጣቸውም እንዲህ የሚል "በዚህ በቸርነቱ ስጦታ ውስጥ የእግዚአብሔር ፍቅር የጎላ የተረዳ ሆነ ነፍስ ረቂቅ ስለሆነች እንደ መላእክት በሕይወት እንድትኖር እንጂ እንዳትሞት እንዳትጠፋ ማድረጉ ነው።
🌼 ከሥጋዋም በምትወጣ ጊዜ ስለ በጎ ሥራዋ እንደሚገባት መጠን ወደ ሕይወት ቦታዋ ይወስዷታል ወይም እንደ ሥራዋ ክፉነት ወደ ሥቃይ ይወስዷታል። በትንሣኤ ቀንም ንቃሕ መዋቲ ተብሎ ዓዋጅ ሲነገር በፈጣሪያቸው ትእዛዝ የሙታን በድኖች ሲነሡ ነፍሳት እንዲህ ይሆናሉ እያንዳንዲቱ ነፍስ ከሥጋዋ ተዋሕዳ አብራ ትነሣለች"። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አባቶቻችን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
✝️ ✝️ ✝️
🌼 #የገዳመ_ሲሐት_አባ_ሙሴ፦ ይህም ቅዱስ ከመነኰሰ ጀምሮ ዓለምን ትቶ ከበረሀ ገብቶ በጾም በጸሎት በመጠመድ ተጋደለ። እግዚአብሔር ዘይቶንና የተምር አትክልት ያለባትን የአትክልት ቦታ በማየት ልቡን ብሩህ እስከ አደረገለት ድረስ በወሩ መባቻም ከዘንባባ ዕንጨትና ከዘይቶን የወደቀውን ፍሬ ወስዶ ይበላል። ምግቡም ታናሽ ወፍ በሚመገበው መጠን ልክ ነው ልብሱም ከዘንባባ ቅጠል የተሠራ ሰሌን ነው። ስለዚህ ለሚያስጨንቅ ለክረምት ቅዝቃዜና ለበጋ ቃጠሎ የተጋለጠ ከዚህም ጋር በጾምና በጸሎት የተጠመደ ነው ።
🌼 ነገር ግን መጻሕፍትን የሚያውቅ አይደለም የዱር አራዊትም በየወገናቸው ወደርሱ ይመጡ ነበር እርሱም ያረጋጋቸዋል። የጸሎት ጊዜም ሲደርስ በእጁ ሲጠቅሳቸው ይሔዳሉ። ድርቅ የሆነ እንደሆነም ሊያነጋግሩት እንደሚሹ ሁነው መጥተው በፊቱ ይቆማሉ እርሱም የሚሹትን በመንፈስ ቅዱስ አውቆ በጸሎቱ ዝናብን ያወርድላቸዋል። እንዲሁም እያደረገ ከእርሳቸው ጋር አርባ አምስት ዓመት ኖረ ።
🌼 ሰይጣንም ቀናበት ዘመኑ በአለፈና እጅግ በአረጀ ሽማግሌ አምሳል በጥቂት በጥቂት ሲያዘግም ከበዓቱ ውስጥ ሁኖ አየው ለዚህ ቅዱስ አባ ሙሴም ገዳማዊ መናኒ መስሎት ወደርሱ ሒዶ አምጥቶ ወደ በዓቱ አስገባው አራዊት ግን በሽማግሌ የተመሰለውን ሰይጣን በአዩት ጊዜ ከእርሱ ሸሹ።
🌼 ከዚህ በኋላ አባ ሙሴን አገሩንና ሃይማኖቱን ጠየቀው እርሱም ሁሉን ነገረው ደግሞ አባ ሙሴ ኑሮው እንዴት እንደሆነ ሽማግሌውን ጠየቀው ። በሽማግሌ የተመለሰ ሰይጣንም እንዲህ ብሎ መለሰለት "እኔ በዓለም ኃጢአት በመሥራት ብዙ ዘመናት ኖርኩ አንዲት ሴት ልጅንም ወለድኩ ። ከዚያም የዓለምን ኃላፊነትና ጠፊነት አሰብኩ ከዓለምም ወጥቼ በበረሀ ውስጥ አርባ ዓመት ኖርኩ። ልጄን ያገባት እንደሌለ በአሰብኩ ጊዜ በዚህ ነገር ምክንያት ወዳንተ መጣሁ ከአንተ በቀር የሚያገባት የለምና በሞትኩም ጊዜ የምትቀብረኝ አንተ ነህ ብዙ ስፍራዎችና የአታክልት ቦታዎችም ስላሉኝ ሁሉንም እንተ ትወርሳለህ"።
🌼 አባ ሙሴም ሰምቶ ደነገጠ "እኔ መነኲሴ ስሆን ይህን እንዴት አደርጋለሁ" አለ የተመረጡ ጻድቃን ሲሆኑ ሚስቶች የነበሩአቸው አብርሃምን ሙሴን ዳዊትን ከብሉያት መጻሕፍት ምስክር ማስረጃ አድርጎ አመጣለት በዚህም ወደ ተንኰሉ ልቡን አዘነበለው።
በውስጡ ያጌጠች ሴት ልጅ ያለችበትን የተሸለመ አዳራሽ አሳየውና ከዚያም በኋላ እንደሞተ ሆነ አባ ሙሴም አይቶ በለዩ አለቀሰ ገንዞም ቀበረው።
🌼 ልጅቷ ወዳለችበት ለመግባት በፈለገ ጊዜ ጥቅል ነፋስ ነፍሶ የኋሊት ጣለው ከዚህ በኋላ ልቡ ሲመለስለት አዳራሹንም ልጅቷንም የአትክልት ቦታዎችንም አጣ ፈጽሞ እያደነቀ ወደ ማደሪያው ተመለሰ ከዕንጨቱም ፍሬ ምግቡን ሊመገብ ፈለገ በአፉም ውስጥ መራራ ሆነበት በረኃብም ስለ ተጨነቀ ወደ ዱር ወጥቶ ሔደ።
🌼 ከዚህም በኋላ በአህያው ላይ ተቀምጦ ወደ እስክንድርያ በሚሔድ በሽማግሌ ነጋዴ አምሳል ሰይጣን ተገናኝው መብልና መጠጥም ይዞ ነበር አባ ሙሴንም ከርሱ ጋር ወሰደው ወዳንድ አገርም አድርሶ በዚያ ተወው ።
🌼 ዳግመኛም በገዳማዊት በመናኒነት በምትኖር አምሳል ሰይጣን ታየው እርሷም ውኃ የምትቀዳ መስላ ነው ሥራውን ጠየቀችው ሰይጣን እንደ ፈተነው ሁሉን ነገራት በልቧም ሳቀችበት ወደ ቤቷም ወስዳው አብልታ አጠጥታ ከዚያ በኋላ የጋብቻን ነገር አሳሰበችው ብዙ ገንዘብም እንዳላት እርሷም የሟች ንጉሥ እንደሆነት ነገረችው። ልቡም እንደአዘነበለ አይታ "እኔ አይሁዳዊት ነኝ እኛም ብዙዎች ነን" ሃይማኖቱንም እስከካደ ድረስ በብዙ ተንኰል ተስፍ አስደረገችው ።
🌼 ዳግመኛም እንዲህ አለችው "ና ወደ በረሀ እንውጣና ያኖርኩትን ገንዘብ እንውሰድ" ብላ ውኃ ወደሌለበት በረሀ ወሰደችው ከተራራ በላይም ወጥታ ተለወጠችበት እንዲህም አለችው "እኔ ብዙዎችን ያሳትኩ ሰይጣን አንተነንም ከገዳምህ አስመጣሁህ ሃይማኖትህንም አስካድኩህ እነሆ በዚህ በረሀም ሙተህ ነፍስህ ወደገሃነም ትወርዳለች" ይህንንም ብሎ ሰይጣን ከርሱ ተሠወረ። በተመለሰም ጊዜ በቀኝም በግራም መንገድ አጣ የሚጠጣውም ውኃን አላገኘም ምድር ጠበበችው በምድር ላይም ወድቆ በፊቱ ውስጥም አፈርን በተነ ነፍሱም ከሥጋው ለመለየት እስከደረሰች ደረስ ተንከባለለ ጭኸ መሐሪና ይቅር ባይ ሰውን የሚወድ እግዚአብሔር ራራለት ያጽናናው ዘንድ መልአኩን ላከለት እርሱም "ኃጢአትህ ተሠረየልህ እስከ ሰባት ቀንም ታርፍለህ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሳሙኤልም ይቀብርሃል" ብሎ አጽናናው ሰላምታም ሰጥቶት ዐረገ ።
🌼 "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼
🌼 #መስከረም ፫ (3) ቀን።
🌼 እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ ታላቁ የሥውራ ቅዱሳን መኖርያ የሆነው ገዳም #ደብረ_ሐዘሎው ለመሰረቱ፤ አንበሳ እንደ ፈረስ ያገለግላቸው ለነበሩ #ለታላቁ_አባት_ለአቡነ_አንበስ ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን።
✝️ ✝️ ✝️
🌼 #አባ_አንበስ፦ እኚህ አባት ከቅድስናቸው የተነሣ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱት በአንበሳ ላይ ተጭኖ ነው፡፡ ተአምራትን በማድረግና ወንጌልን በማስተማር በጾም ጸሎት አብዝቶ የደከመ ሲሆን ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሌት ተቀን በጸሎት ይተጉ የነበረ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ አቡነ አንበስ ትውልዳቸው ትግራይ አድዋ በእንጭጮ ወረዳ ነው፡፡ በስማቸው ትግራይ አድዋ "እንጭጮ አቡነ አንበስ ገዳም" እና በትግራይ ሽሬ ሁለት ትላልቅ ገዳማት አሏቸው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድርሰቱ ደጋግሞ የጠቀሳቸው ሲሆን የያሬድንም የድርሰቱን የአቋቋም ሥርዓት ያመጡት አቡነ አንበስ ናቸው፡፡
🌼 አቡነ አንበስ በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና በአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ጊዜ የነበሩ ሲሆን እሳቸውንም አንበሶች ያገለግሏቸው ነበር፡፡ ጻድቁ አቡነ አንበስ ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጋር የተገናኘ ትልቅ ታሪክ አላቸው፡፡ የላዕላይ ግብጹ አባ ብንያም፣ በአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ እና የሐዘሎው አቡነ አንበስ እነዚህ 3ቱ ቅዱሳን ከየአሉበት በአንበሳቸው ተጭነው ምድረ ከብድ አቡዬ ዘንድ እንደደረሱ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንበሶች የ3ቱንም ቅዱሳን አንበሶች ዋጡዋቸው፣ አቡዬም በዚህ አዝነው ከበዓታቸው ወጥተው አንበሶቻቸውን "ትፉ" ብለው የበሉአቸውን አንበሶቻቸውን አስተፍተዋቸው ለ3ቱም ቅዱሳን የተበሉባቸውን አንበሶቻቸውን መልሰውላቸዋል፡፡
🌼 ይኸውም የሆነው እኝዲህ ነው፡- አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዝቋላ 7ቱ ሊቃነ መላእክት እየረዷቸው 70 ሺህ እልፍ አጋንንትን በእሳት ሰይፍ ፈጅተው ካጠፏቸው በኋላ ወደ ምድረ ከብድ ተመለሱ፡፡ ከዚህም በኋላ መንፈስ ቅዱስ የጠራቸው ሦስቱ ቅዱሳን አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ አቡነ አንበስ ዘሐዘሎ እና የላዕላይ ግብጹ አቡነ ብንያም በአንበሶቻቸው ሆነው ወደ ጻድቁ አባት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዘንድ ምድረ ከብድ ገዳም መጡ፡፡ አባታችን ግን ስለተሰወራቸው እስከ 7 ቀን ድረስ በምህላ ሰነበቱ፡፡ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንበሶችም መጥተው የ3ቱን ቅዱሳን አንበሶች በልተውባቸው ተሰወሩ፡፡ 3ቱም ቅዱሳን ፈጽመው ደነገጡ፡፡ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስም የቅዱሳኑን ሀዘንና ድንጋጤ ተመልክተው በታላቅና በሚያስፈራ ግርማ ሆነው ስልሳ ነብሮችንና ስልሳ አንበሶችን አስከትለው ተገለጡላቸው፡፡ ቅዱሳኑም ከአቡነ ገብረ መንፈስቅዱስ ግርማ የተነሣ ስለደነገጡ እንዳይፈሩም አረጋጉአቸው፡፡
🌼 ከዚህም በኃላ አባታችን "በምን ምክንያት ወደዚህ ገዳም ወደ እኔ መጣችሁ?" አሏቸው፡፡ ሦስቱ ቅዱሳን እንዲህ አሉ፡- "ጸሎትህ ቅድስት እንደሆነች ባወቅን ጊዜ ወደ አንተ መጣን፤ አንተ በሁሉ ርእሰ ባሕታውያን ነህና የእግዚአብሔርን ሥራ ትነግረን ዘንድ መጣን፤ ባላገኘንህም ጊዜ እስከ 7ቀን አለቀስን" አሉት፡፡
🌼 ዳግመኛም "አንበሶችህ መጥተው አንበሶቻችንን ደማቸውን ጠጡ ቆዳቸውንም በጥፍራቸው በጣጠሱ" ብለው ነገሯቸው፡፡ አባታችንም ይህንን ሲሰሙ አንበሶቻቸውን "እስከ ዕለቴ ሞቴ ድረስ በእግሬ ከረገጥኩት ትቢያ በቀር ምንም እንዳትበሉ ታዛችሁ የለምን? እግዚአብሔር ያላዘዛችሁትን ለምን በላችሁ? በሉ አሁንም የበላችሁትን ትፉ" አላቸው፡፡ እነዚያም አንበሶች አፋቸውን ከፍተው አንዳች ሳያስቀሩ አጥንታቸውን ሥጋቸውን በሙሉ ተፉአቸው፡፡ ጻዲቁ አባታችንም ወደ ምሥራቅ ተመልሰው እግዚአብሔርን ከለመኑ በኋላ በአንበሶቹ ሥጋ ላይ ባረኩና "በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ተነሡ" አሏቸው፡፡ አንበሶቹም እንደ ዐይን ፈጥነው ተነሥተው እንደ ቀድሞው ሆኑ፡፡ ከአባታችን ከአቡነ አንበስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸውም ይማረን። ምንጭ፦ ከገድላት አንደበት።
🌼 "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼
🌼 #መስከረም ፪ (2) ቀን።
🌼 እንኳን #ለታላቁ_ነብይ_ሰማዕት_ሐዋርያ_ካህን #ለመጥምቀ_መለኮት_ለሰማዕቱ_ለቅዱስ_ዮሐንስ ሕግ አፍራሽ በሆነ በንጉሥ ሄሮድስ እጅ አንገቱን በመሰየፍ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል በሰላም አደረሰን። በዚች ቀን በጨማሪ ከሚታሰቡ፦ በግብጽ ውስጥ ታዕዳ ከሚባል አገር በሰማዕትነት ከዐረፈ #ከቅዱስ_ዳስያ፣ #ከሰማዕት_ዲዲሞስና #ቅድስት_መሪና ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
🌼 #የታላቁ_ነብይ_ሰማዕት_ሐዋርያ_ካህን፣ #የመጥምቀ_መለኮት_የቅዱስ_ዮሐንስ_ሰማዕትነት፦ ይህም እንዲህ ነው ፊሊጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ነቢዩ ቅዱስ ዮሐንስ በገሠጸው ጊዜ ፊሊጶስ ወንድሙ ስለሆነ ቅዱስ ዮሐንስም የወንድህን ሚስት ልታገባ አይገባህም ይለው ነበርና።
🌼 ቅዱስ ዮሐንስም ሄሮድስን የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ስለማግባቱና ሌላም ያደርገው ስለነበረ ክፉ ሥራ ሁሉ ይገሥጸው ነበር። ደግሞም በተግሣጽ ላይ ተግሣጽን ጨመረ። ስለዚህም ቅዱስ ዮሐንስን ተቀየመውና በግዞት ቤት አኖረው።
🌼 ሄሮድስም ቅዱስ ዮሐንስን ይፈራው ነበር ጻድቅ ቅዱስ ሰው እንደሆነ ያውቅ ነበርና ብዙ ይጠባበቀውም ነበር። ሄሮድስ የተወለደባትን ቀን በዓል የሚያከብርባት ዕለት ነበረች መኳንንቱን አለቆቹን መሣፍንቱን ሹሞቹን በገሊላ አገር ያሉትን ታላላቅ ሰዎች ግብር አገባ።
🌼 የሄሮድያዳ ልጅም ወደ አዳራሹ ገብታ ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው ከእርሱ ጋር በማዕድ የነበሩትንም ንጉሡም ያቺን ብላቴና "የምትሺውን ለምኚኝ እሰጥሻለሁ" አላት። እስከ መንግሥቱ እኩሌታ ድረስም ቢሆን የለመነችውን ሊሰጣት ማለላት። ወጥታም እናቷን "ምን ልለምነው" አለቻት እናቷም "የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ" አለቻት።
🌼 ያን ጊዜም እየሮጠች ወደ ንጉሡ ገብታ "የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በውጭት አሁን እንድትሰጠኝ እሻለሁ" ብላ ለመነችው። ንጉሡም ስለ መሐላው አብረውት ስለ ነበሩትም ሰዎች አዘነ እምቢ ሊላት ግን አልወደደም።
🌼 ያን ጊዜም ባለወጎችን ላከ በእሥር ቤትም ሳለ የቅዱስ ዮሐንስን ራስ ቆረጡ ራሱንም በወጭት አምጥተው ለዚያች ብላቴና ሰጡአት እርሷም ወስዳ ለእናቷ ሰጠች።
🌼 በዚያችም ቀን የቅዱስ ዮሐንስ ራስ ከሄሮድያዳ ከእጆቿ ላይ ወደ አየር ስለ በረች ታላቅ ድንጋፄ ሆነ። "ደግሞም ሄሮድስ ሆይ የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም" እያለች በመጮኸ ዘልፋዋለችና።
🌼 ደቀ መዛሙርቱም በሰሙ ጊዜ መጥተው በድኑን ወስደው ቀበሩት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበረ በአጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
🌼 #ቅዱስ_ዳስያ፦ ይህም ቅዱስ በግብጽ ውስጥ ታዕዳ ከሚባል አገር ነው። ቅዱስንም የእንዴናው አገረ ገዥ አርያኖስ አሠቃየው ጽኑ ሥቃይንም ከአሠቃየው በኋላ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ። የቅዱስ ዳስያ በረከቱም ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን። ምንጭ፦ የመስከረም 2 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
🌼 #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወእመኒ ነሣእኩ ክንፈ ከመ ንስር። ወሠረርኩ እስከ ማኅለቅተ ባሕር። ህየኒ እዴከ ትመርሀኒ ወታነብረኒ የማንከ"። መዝ 138፥9። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 14፥1-13።
✝ ✝ ✝
🌼 #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ወይርአዩ አሕዛብ በቅድመ አዕይንቲነ። በቀለ ደሞሙ ለአግብርቲከ ዘተክዕወ። ይባዕ ቅድሜከ ገዐሮሙ ለሙቁሓን"። መዝ78፥10-11። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 6፥1-11፣ 1ኛ ዮሐ 3፥10-16 እና የሐዋ ሥራ 13፥24-28። የሚነበበው ወንጌል ማር 6፥14-29። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
🌼 "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼
🌼 #መስከረም ፩ (1) ቀን።
🌼 እንኳን #ለርእሰ_ዐውደ_ዓመት_ለቅዱስ ዮሐንስ፤ #ከዘመነ_ቅዱስ_ማቴዎስ_ወደ_ዘመነ_ቅዱስ_ማርቆስ አሸጋግሮ እግዚአብሔር አምላክን በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
🌼 #የተባረከ_የመስከረም_ወር_የግብፅና #የኢትዮጵያ_ዓመታት_ወሮች_ርእስ_ነው። የቀኑ ሰዓትም ከሌሊት ሰዓት የተስተካከለ ዐሥራ ሁለት ነው። ከዚህ በኋላ እያነሰ ይሔዳል። አሁንም በፍጹም ንጽሕና ታላቅ በዓልን አድርገን ልናከብር ይገባናል።
🌼 ይህች ዕለት ከሌሎች ዕለታት ተለይታ የተባረከች ናትና ከክፉ ሥራዎችም ሁሉ ተለይተን እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝባቸውን አዳዲስ የሆኑ በጎ ሥራዎችን እንሥራ። ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ "እነሆ የቀደሙት ሥራዎች አልፈው ሁሉ በክርስቶስ ሐዲስ ሆነ" እንዳለ። ይህም ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዲሁ የጐላ የተረዳ ሆነ እርሱም በክርስቶስ ልጅነትን በመስጠት ይቅርታውንና ቸርነቱን አደለን።
🌼 ኢሳይያስም እንዲህ አለ "በኔ ህልውና ያለ ያዋሐደኝ ሕይወቴ መንፈስ ቅዱስ ስለርሱ ድኆችን በልብ ያዘኑ ሰዎችን ደስ አሰኛቸው ዘንድ ለተማረኩም ሰዎች ነፃ መውጣትን አስተምራቸው ዘንድ ዕውሮችም ያዩ ዘንድ እግዚአብሔር የወሰነውን ዘመን የተመረጠ እለው ዘንድ ፍዳ የሚደረግባትንም ቀን ደግ እላት ዘንድ ያዘኑትንም ሰዎች ደስ አሰኛቸው ዘንድ ላከኝ"።
🌼 ነቢዩ ዳዊትም ዳግመኛ እንዲህ አለ "የምሕረትህንም ዓመት እህል ትባርካለህ። ምድረ በዳዎችም ከበረከትህ ጠሎችን ይጠግባሉ። ምንጭ፦ የመስከረም 1 ስንክሳር።
🌼 አዲሱ ዓመት ዘመነ #ቅዱስ_ማርቆስ የንስሐ፣ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመተሳሰብ፤
ከአገራችን ኢትዮጵያ የእርስ በርእስ ጦርነት የሚወገድበት ይሁንልን።
✝ ✝ ✝
🌼 #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወትባረክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ። ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም። ወይረውዩ አድባረ በድው"። መዝ 64፥11-12 ወይም 146፥6። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 4፥17-23።
✝ ✝ ✝
🌼 #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "አድኅንኒ እምእለ ሮዱኒ እስመ ይኄይሉኒ። ወአውጽነ እሞሕቅ ለነፍስየ። ከመ እግነይ ለስምከ እግዚኦ"። መዝ 141፥6-7። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ቆሮ 6፥1-11፣ ያዕ 5፥8-13 እና የሐዋ ሥራ 5፥12-16። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 11፥1-20። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱሳን ሐዋርያት ወይም የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም አዲስ ዓመት፣ የመልአኩ የቅዱስ ራጉኤል የሲሞት በዓል፣ የሐዋርያው በርተሎሜዎስም የዕረፍት በዓልና የታላቁ አባት የአባ ሚልኪ የዕረፍት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
🌼 አባ ሚልኪም ከመነኰሰ አርባ አምስት ዓመታት ሲሆነው እንዲህ የሚል ቃል ከሰማይ ወደርሱ መጣ "እነሆ የምታርፍበት ቀን ቀርቧል ከሦስት ቀን በቀር አልቀረህም ወደ ዘላለምም ተድላ ደስታ ትሔዳለህ"።
ያን ጊዜም ልጆቹን ሁለ ጠርቶ ሰይጣን ከሚያመጣው ስሕተት እንዲርቁና እንዲጠብቁ በፍርሃትም ሁነው እግዚአብሔርን እንዲአገለግሉ አዘዛቸው። ከሦስት ቀንም በኋላ ቅዱሳን አባቶች መነኰሳት አባ እንጦንስ አባ መቃርስ አባ ሲኖዳ አባ ብሶይ አባ ጳኵሚስ ወደርሱ መጥተው እንዲህ አሉት "ወንድማችን ወደእኛ ና ከእኛ ጋርም ፍጹም ተድላ ደስታ ባለበት በእግዚአብሔር መንግሥት ደስ ይበልህ" ይህንንም ሲሉት ነፍሱ ከሥጋው ወጣች። መላእክትም "በዓለም ውስጥ በገድል በትሩፋት የደከመ ለዘላለሙ በሕይወት ይኖራል" እያሉ በክብር በምስጋና ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት አወጡት።
🌼 ከዚህም በኋላ ጳጳሳት ኤጲስቆጶሳት ሁሉም ካህናት ተሰብስበው ገነዙት በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ቀበሩት ከመቃብሩም ቍጥር የሌላቸው ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ አባ ሚሊኪ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
✝️ ✝️ ✝️
🌼 #የታላቂቱ_አገር_የእስክንድርያ_ሊቀ_ጳጳሳት #አባ_ሜልዮስ፦ እርሱም ለአባታችን ሐዋርያና ወንጌላዊ ለሆነ ማርቆስ ሦስተኛ ነው።
🌼 ይህም አባት የሮሜ ንጉሥ አስባስያኖስ በነገሠ በዐሥራ አምስት ዓመት ተሾመ ይኸውም የክብር ባለቤት ጌታችን በዐረገ በአርባ ዓመት ነው ክብር ይግባውና የክርስቶስን መንጋዎች በበጎ አጠባበቅ ጠበቃቸው በሹመቱም ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ። እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም በፍቅር አንድነት ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ሚልዮስ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የመስከረም 1 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
🌼 "#ሰላም_ለምልኪ_እምዐቢይተ_ቊልዝም_ዘኮነ። ዘሠናየ ልሕቀ ወዘአዳመ ተሐፅነ። እምእግዚአብሔር ከሀሊ ነሢኦ ሥልጣነ። በኃይለ ጸሎቱ ቀነየ ሰይጣነ። እንዘ ያፀውሮ ገብላተ ወስቊረ ዕብነ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመስከረም_1።
🌼 መምጣቱም በዘገየ ጊዜ ፈለጉት ግን አላገኙትም። እያለቀሱም ተመልሰው ለአባቱና ለእናቱ ነገሩአቸው እነርሱም የመረረ ልቅሶን አለቀሱ ከለቅሶ ብዛትም የተነሣ የእናቱ ዐይኖቿ ታወሩ ለሞትም አደረሳት። ይህ አባ ሚልኪ ግን ጡር ወደምትባል ገዳም ሔደ ይቺም ስሙ አባ አውጊን ለሚባል ለእናቱ ወንድም ገዳሙ ናት።
🌼 ይህም አባ አውጊን ብዙ ትሩፋትን የሚሠራ ጻድቅ ሰው ነው በእርሱም ሥር የተመረጡ ሰባ ሁለት መነኰሳት ነዋሪዎች አሉ። አባ ሚልኪም ከእግሩ በታች ሰግዶ "አባቴ ሆይ በጥላህ ሥር እንድኖር የምንኲስናንም ልብስ ታለብሰኝ ዘንድ እሻለሁ" አለው። አባ አውጊንም ከወዴት አገር ነህ ብሎ ጠየቀው እርሱ አባ ሚልኪም አገሩ ቊልዝም ለአባ አውጊንም የእኀቱ ልጅ መሆኑን ነገረው ሰምቶም ፈጽሞ ደስ አለው።
🌼 ሦስት ዓመትም በአመክሮ አቆየው ከዚህም በኋላ የምንኲስናን ልብስ አለበሰው ዜናው በፋርስ አገር ሁሉ እስቲሰማ ትጋትንና ተጋድሎን አበዛ። እግዚአብሔርም የመፈወስን ሀብት ሰጥቶት አጋንንትን ከሰዎች ላይ አሰወጥቶ ይሰዳቸዋል።
🌼 ከዕለታትም በአንዲቱ ዕለት የዳዊትን መዝሙር እያነበበ ብቻውን ሲጓዝ ታላቅ ጒድጓድ ወዳለበት ደረሰ በአጠገቡም የበለስ ዛፍ አለ ብዙ እረኞችም በዚያ ያለቅሱ ነበር። አባ ሚልኪም "ምን ያስለቅሳችኋል" አላቸው። እረኞችም እንዲህ ብለው መለሱለት "የአገረ ገዢው ልጅ ከእኛ ጋራ ከበለስ ፍሬ ሲበላ ታላቅ ዘንዶ ወጥቶ ልጁን ውጦ ወደ ጒድጓድ ተመለሰ" አሉት። እረኞችም እየነገሩት ሳለ የሕፃኑ አባት ልብሱን በመቅደድ ፊቱንም በመጽፋት ከብዙ ሰዎች ጋር መጣ ቅዱስ ሚልኪንም ስለ ልጁ ማለደው። አባ ሚልኪም "ልጄ ሆይ በእግዚአብሔር ታመን እንጂ አትፍራ የጌትነቱንም ድንቅ ሥራ ታያለህ" አለው።
🌼 ያን ጊዜም ፈቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ረጅም ጸሎትን ጸለየ ጸሎቱንም በጨርሰ ጊዜ ዘንዶውን ጠርቶ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሕፃኑን ይተፋው ዘንድ አዘዘው ምንም ሕማም ሳይነካው ጒዳትም ከቶ ሳያገኘው ወዲያውኑ ተፋው በከይሲውም አድሮ ያለ ሰይጣን እንዲህ ብሎ ጮኸ "የቊልዝም ሰው ሚልኪ ከአንተ የተነሣ ወዴት ልሒድ" ይህንንም ብሎ እንደ ጢስ ተበተነ።
🌼 የሕፃኑም አባት ይህን ድንቅ ሥራ ልጁም እንደ ዳነ በአየ ጊዜ እጅግ ደስ አለው። ለቅዱስ አባ ሚልኪም ብዙ ወርቅትና ብር አመጣ አባ ሚልኪም "መቀበልን አይሆንም" አለ "ግን በጽድቅ ሥራ አንድ እንድንሆን ገዳምን ሥራ" አለው። አገር ገዢው የሕፃኑ አባትም ደስ አለው ሦስት መቶ የመነኰሳት ቤቶችን ሠራ ዙሪያውንም በግንብ አጠረ መዝጊያውንም ከብረት ሠራ።
🌼 ቤተክርስቲያንንም ሲሠሩ ሦስት መቶ ሰዎች ሊአንቀሳቅሷት የማይችሉ ለማዕዘን የምትሆን ደንጊያን አገኙ በጻድቁ በአባ ሚልኪ ጸሎትም ራስዋ ተነሥታ እንደሚፈልጓት ሁና ተሠራች።
🌼 ከዚህም በኋላ በዚያ ገዳም ሦስት መቶ ሰዎች ተሰብስበው የተመረጡ መነኰሳትን ሆኑ። የቅዱስ አባ ሚልኪም ዜናው በሀገሩ ሁሉ ተሰምቶ በየዓይነቱ ደዌ ያለባቸውን በክፉዎች አጋንንትም የተያዙትን ወደርሱ የሚያመጡአቸው ሆኑ ሁሉም በጸሎቱ ይፈወሱ ነበር።
በዚሁ ጻድቅ ጸሎትና ምልጃ የፋርስና የሮም ሰዎች ተጠብቀው የሚኖሩ ሆኑ።
🌼 ከዚህም በኋላ አባ ሚልኪ ከዋሻ ውስጥ ገብቶ የዋሻውን በር ዘጋ በልቡም "እስከ ዕድሜዬ ፍጻሜ ከዚህ ዋሻ አልወጣም" ብሎ ቃል ገባ። የበጎ ሥራ ጠላት ሰይጣንም እንዲህ ብሎ ዛተበት "ጠብቀኝ እኔ ከዚህ ከበዓትህ አስወጥቼ የተሳልከውን ቃል አፈርሳለሁ" ይህንንም ብሎ ሒዶ በሮም ንጉሥ ልጅ ላይ አድሮ አሳበዳት እርሷም እየጮኸች እንዲህ አለች "ከቊልዝማዊው ሚልኪ በቀር የሚያድነኝ የለም"።
🌼 ንጉሥ አባቷም ሰምቶ ከወታደሮቹ ውስጥ አራት መቶ ሰዎችን ላከ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው "በሁሉ ቦታ ተግታችሁ አባ ሚልኪን ፈልጋችሁ ወደ እኔ አምጡት እኔም በጎ የሆነ ዋጋችሁን እከፍላችኋለሁ። ይህ ካልሆነ ግን ራሶቻችሁን በሰይፍ ልቆርጥ ምያለሁ"።
🌼 የተላኩ ወታደሮችም ፈልገው በጭንቅ አገኙትና ለብፁዕ አባ ሚልኪ የንጉሡን መልእክት ልጁን ጋኔን እንደአደረባት የምትናገረውንም ነገር ነገሩት። እርሱም "እኔ ሽማግሌ ሰው ነኝ ወደ ሮም አገር ለመሔድ አልችልም" አላቸው። እነርሱም "አባታችን ሆይ አንተ ከእኛ ጋር ካልሔድክ ንጉሥ በሰይፍ ቆርጦ እንደሚገድለን ነግሮናል" አሉት። ሰምቶም እጅግ አዘነ እንዲህም አላቸው "ልጆቼ ሒዱ እኛ እርስ በርሳችን በሮም ከተማ መግቢያ እንገናኛለን"።
🌼 ቃሉንም ሰምተው ሔዱ በዓመቱም ፍጻሜ ከሮሜ ከተማ መግቢያ መድረሳቸውን በመንፈስ ቅዱስ አውቆ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ያን ጊዜም ደመና ተሸክማ ከሮሜ ከተማ መግቢያ አደረሰችው። የንጉሥ መልእክተኞችም በአዩት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው። ለንጉሡም የከበረ አባ ሚልኪ መምጣቱን ነገሩት። እርሱም ወጥቶ በክብር ተቀብሎ ወደ እልፍኙ አስገባው ስለ ልጁ ስለ ደዌዋ ነገረው ቅዱስ አባ ሚልኪም አምጧት ብሎ አዘዘ። በአመጧትም ጊዜ ጋኔኑ ጥሎ አረፋ አስደፈቃት ሞተች ብለው እስከሚጠራጠሩ። ያን ጊዜም አባ ሚልኪ ተነሥቶ ጸለየ በፊቷ ላይም ውኃን ረጨ ዘይትንም ቀባት ሰይጣንንም ከርሷ ይወጣ ዘንድ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዘዘው። ያን ጊዜም በጥቁር ባርያ አምሳል ከእርሷ ወጣ።
🌼 ቅዱስ አባ ሚልኪም ሰይጣንን በሥውር ይዞ በቤት ውስጥ ዘጋበት በዚያም አሠረው። ንጉሡም ይህን ድንቅ ሥራ አይቶ ከእግሩ በታች ሰገደ ለገዳሙ ለሚአስፈልገው ነገር እንዲሆነው ብሎ ብዙ ወርቅና ብርን አመጣለት እርሱም መቀበልን እምቢ አለ።
ንጉሡም "አባቴ ሆይ ከዚህ ተቀመጥ እኔም ገዳም እሠራልሃለሁ" አለው አባ ሚልኪም "ልጆቼን መተው አይሆንልኝም" አለው ግን በሽተኞችን እየፈወሰ በሮሜ ከተማ ጥቂት ቀኖች ተቀመጠ።
🌼 ወደ አገሩ ይመለስ ዘንድ ተነሥቶ በወጣ ጊዜ ንጉሡም ከመኳንንቱ ጋራ ሊሸኘው ተነሣ። ከንጉሥ ግቢ በስተውጭ የንጉሥ ፈረሶች የሚጠጡበት ታላቅ የደንጊያ ገንዳ የተበሳ ታላቅ ደንጊያን አባ ሚልኪ አይቶ ንጉሡን "ይህን ገንዳ ይህንንም የተበሳ ታላቅ ደንጊያ ለገዳም አገልግሎት እሻዋለሁና ስጠኝ" አለው። ንጉሡም "ዐሥራ አራት ሰዎች ከምድር ከፍ ሊአደርጉት የማይቻላቸው ወደ ገዳምህ እንዴት ይደርሳል ተሸክሞ ወደ ፈለግከው ቦታ የሚያደርስ ኃይል ካለህ እኔ ሰጠሁህ" አለው።
🌼 ያን ጊዜም ቅዱስ አባ ሚልኪ ሰይጣንን ከአሠረበት ቦታ አምጥቶ ያንን የተበሳ ደንጊያ በአንገቱ ውስጥ አንጠለጠለ ገንዳውንም ተሸክሞ በፊት በፊቱ ተገልጦ እንዲጓዝ አዘዘው። ሰይጣንም እነዚያን ገንዳዎች የተበሳውንም ደንጊያ ተሸክሞ በፊት በፊቱ ይጓዝ ጀመረ። ንጉሡና የተሰበሰቡት ሕዝብ አይተው እጅግ አደነቁ ለሚፈሩት ለሚያመልኩት ይህን ያህል ጸጋ የሚሰጥ ምስጉን እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።
🌼 የከበረ አባ ሚልኪም እነዚያን ደንጊያዎች ሰይጣንን አሸክሞ ወደ ገዳሙ አደረሰው በገዳሙም ደጃፍ አጠገብ እንዲአስቀምጣቸው አዘዘው እስከዛሬም በዚያ ይኖራሉ። ሰይጣንንም ዳግመኛ ወጥቶ እንዳይፈትነው በዓለት ዋሻ ውስጥ ዘግቶ በመስቀል ምልክት ለዘላለሙ አሸገው።
🌼 "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼
🌼 #የተባረከ_የመስከረም_ወር_የግብፅና_የኢትዮጵያ ዓመታት ወሮች ርእስ ነው። #የቀኑ_ሰዓትም_ከሌሊት_ሰዓት_የተስተካከለ_ዐሥራ_ሁለት ነው። ከዚህ በኋላ እያነሰ ይሔዳል።
🌼 #መስከረም ፩ (1) ቀን።
🌼 እንኳን #ከተስዓቱ_ሊቃነ_መላእክት አንዱ ለሆነው #ለቅዱስ_ራጉኤል_ለበዓለ_ሲመቱ፣ ለሐዋርያው #ለቅዱስ_ለርተሎሜዎስ ለዕረፍቱ በዓል፣ #ለቅዱስ_ኢዮብ በፈሳሽ ውኃ ታጥቦ ከደዌው ሁሉ ለዳነበት ቀን፣ #ለታላቁ_አባት_ለቊልዝም ሰው ለሆነ ፍፁም ጻድቅ ሰይጣን አስሮ ዐሥራ አራት ሰው ሊይዙት የማችሉትን ደንጊያ ላሸከመው #ለአባ_ሚልኪ ለዕረፍት በዓል በተጨማሪ በጤና በሰላም አደረሰን። በዚች ከሚታሰበው፦ ከሦስተኛ የእስክድርያ ሊቀ ጳጳስ #ከአባ_ሚልዮስ_በዓለ_ዕረፍትና ከቅዱስ ቀን እግዚአብሔር አምላክ ረድኤት በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
🌼 በዚችም ቀን #ከተስዓቱ_ሊቃነ_መላእክት አንዱ የከበረ #መልአክ_ቅዱስ_ራጉኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው። እርሱም ስለሚነድ እሳትና ስለ ኃጥአን ሁሉ በጥፋት ውኃ መደምሰስ ለሄኖክ ያስገነዘበው ነው። የዚህም ብርሃናዊ መልአክ የቅዱስ ራጉኤል አማላጅነቱ ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።
🌼 #ሐዋርያው_ቅዱስ_በርተሎሜዎስ፦ ለዚህም ሐዋርያ ሒዶ ያስተምር ዘንድ እልዋህ በሚባል አገር ዕጣው ወጣ። እርሱም ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በአንድነት ሔደ የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አስተማሩ ልባቸውንም የሚያስደነግጥ ድንቆች ተአምራትን በፊታቸው ከአደረጉ በኋላ እግዚአብሔር ወደ ማወቅ መለሷቸው።
🌼 ከዚህም በኋላ ወደ ከተማው ውስጥ ገብቶ ያስተምር ዘንድ ምክንያት አደረገ ቅዱስ ጴጥሮስም እንደ ባሪያ ሸጠው። ባለ ጸጋ ለሆነ መኰንንም በወይን አትክልት ውስጥ የሚያገለግል ሆነ ድንቅ ተአምርን በማድረግ የተቆረጡ የወይን ቅርጫፎች በሠራተኞች እጅ ላይ ሳሉ አፈሩ። የአገረ ገዥውም ልጅ በሞተ ጊዜ ከሞተ አሥነሣው የአገር ሰዎችም ሁሉ አመኑ እግዚአብሔርንም ወደ ማወቅ ተመለሱ።
🌼 ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በርበር ወደሚባል አገር ሔዶ ያስተምር ዘንድ ሐዋርያ ቅዱስ በርተሎሜዎስን አዘዘው እንዲረዳውም ሐዋርያ ቅዱስ እንድርያስን ከደቀ መዝሙሩ ጋር ላከለት። የዚያች አገር ሰዎች ግን እጅግ የከፉ ስለሆኑ በፊታቸው ድንቆች ተአምራቶችን እያደረጉላቸው ሐዋርያትን አልተቀበሏቸውም።
🌼 ጌታችንም ሰውን ከሚበሉ አገር አንዱን ገጸ ከልብ ይታዘዝላቸው ዘንድ በሚያዙት ሁሉ ትእዛዛቸውን እንዳይተላለፍ አዘዘው። ሐዋርያትም ወደዚያች አገር ሁለተኛ ይዘውት ገቡ የአገር ሰዎችም ሐዋርያትን ይበሏቸው ዘንድ ነጣቂዎች የሆኑ አራዊትን አወጡ። ያን ጊዜም ያ ገጸ ከልብ በአራዊቱ ላይ ተነሥቶ እየነጠቀ በላቸው ይህንንም ገጸ ከልብ ከመፍራት የተነሣ ከሰዎች በድንጋጤ የሞቱ ብዙዎች ናቸው።
🌼 የአገሩ ሰዎች ሁሉም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ከሐዋርያትም እግር በታች ሰገዱ የሚሉአቸው ሁሉ የሚደርጉ ታዛዦች ሆኑ። ሐዋርያትም ቤተ ክርስቲያን ሠርተውላቸው ካህናትንም ሹመውላቸው ከእነርሱም ዘንድ ወጥተው እግዚአብሔር እያመሰገኑ ሔዱ።
🌼 ሐዋርያ ቅዱስ በርተሎሜዎስም እግዚአብሔርን የማያውቁ ሰዎች ወደሚኖሩበት በባሕር ዳርቻ ወዳሉ አገሮች ሔዶ የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰበከላቸው በፊታቸውም ተአምራትን አደረገ ሁሉም የጌታችን በሆነች በቀናች ሃይማኖት አመኑ።
🌼 ሐዋርያ ቅዱስ በርተሎሜዎስም ከዝሙት ርቀው ንጹሐን እንዲሆኑ ሰዎችን የሚያዝዝ ሆነ። ንጉሥ አግሪጳም ስለርሱ በሰማ ጊዜ በከበረ ሐዋርያ በቅዱስ በርተሎሜዎስ ላይ እጅግ ተቆጣ። በማቅ ከረጢት ውስጥ እንዲአደርጉትና አሸዋ ሞልተው ከባሕር እንዲጥሉት አዘወ። እንዲሁም ይህን አደረጉበት ምስክርነቱንና ተጋድሎውንም መስከረም 1 ቀን ፈጸመ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባታችን በሐዋርያ ቅዱስ በርተሎሜዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
🌼 በዚችም ዕለት #ቅዱስ_ኢዮብ_በፈሳሽ_ውኃ ታጥቦ ከደዌው ሁሉ ተፈወሰ። ይህም ለሰዎች ልማዳቸው ሆኖ ዓመቱ ዙሮ ሲመጣ ፈሳሹ ውኃም በመላ ጊዜ በአዲስ ውኃ ይጠመቃሉ በእርሱም ይባረካሉ። የጻድቁ ኢዮብ በረከትም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
+ + +
🌼 #የቊልዝም_ሰው_የሆነ_ፍጽም_ጻድቅ #አባ_ሚልኪ፦ የዚህም ጻድቅ ወላጆቹ ከቊልዝም አገር ከታላላቆች ወገን ናቸው። እርሷም ከላይኛው ግብጹ አውራጃ ውስጥ ናት እነርሱም በብርና በወርቅ የበለጸጉ ናቸው ለድኖችና ለችግረኞች ምጽዋትን የሚሰጡ እግዚአብሔርንም እጅግ የሚወዱ ናቸው።
🌼 ነገር ግን ልጅ አልነበራቸውም ከዕለታትም በአንዲቱ ከመምህር ዘንድ የሚማሩ ልጆችን አዩ በእጆቻቸውም ሠሌዳዎችን ይዘዋል። በሠሌዳዎቹም ውስጥ እንዲህ የሚል ጽሑፍ አለ "እኛ የሕያው እግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን በሕይወታቸው ሳሉ ያስተማሩን አባቶቻችንን አስባቸው አቤቱ ነፍሶቻቸውንም ከተመረጡ ቅዱሳን ጻድቃንና ሰማዕት አሳርፍ"። የአባ ሚልኪ አባትም ከልጆች አንደበት ይህን ቃል በሰማ ጊዜ "ከዚህ ዓለም ከሔድኩ በኋላ ልጅ የሌለኝ እኔን ማን ያስበኛል ወዮልኝ" እያለ እጅግ በማዘን ተከዘ።
🌼 ከዚህም በኋላ በጾም በጸሎት ምጽዋትንም በመስጠት ከሚስቱ ጋር ምህላ ያዘ። የክብር ባለቤት እግዚአብሔርም ልመናቸውን ሰምቶ ወንድና ሴት ሁለት ልጆችን በአንዲት ጊዜ ሰጣቸው በእነርሱም ፈጽሞ ደስ አላቸው። ወደ ክርስትናም በአስገቧቸው ጊዜ ወንዱን ልጅ ሚልኪ አሉት እኀቱን ስፍና አሏት ትርጓሜዋ ርግብ ማለት ነው በመልካም አስተዳደግ አሳደጓቸው።
🌼 ለሚልኪ ሰባት ዓመት ሲሆነው አባቱ ወስዶ ለመምህር ሰጠው የብሊያትንና የሐዲሳት መጻሕፍትን ሁሉ ተማረ መንፈስ ቅዱስም አደረበት። ከሕፃናቱም ጋር አይጫወትም አይስቅም በቀንም በሌሊትም አዘውትሮ መጸሕፍትን ያነባል እንጂ።
🌼 ዕድሜውም ዐሥራ ዘጠኝ ዓመት በሆነው ጊዜ ወላጆቹ ጠርተው ስለ ጋብቻ ሚስት አብግቶ መታሰቢያችው ይሆን ዘንድ ተናገሩት። እርሱም ይህን አልወደደም ነገር ግን በተንኰል "እሺ ቃላችሁን ተቀብዬ ያዘዛችሁኝን ሁሉ አደርጋለሁ" አላቸው እርሱ ግን ከዓለም ሸሽቶ ያመልጥ ዘንድ ያስባል።
🌼 ከዚህም በኋላ አባቱን እንዲህ አለው "አባቴ ሆይ ከእኔ ጋራ ለተማሩ ልጆች ለባልንጀሮቼም ምሳ ላደርግላቸው እሻለሁ ምሳንም በባልንጀሮቹ ያዘጋጅላቸው ዘንድ አባቱ አንድ ሺህ የወርቅ ዲናርን ሰጠው። ዳግመኛም ለሚያስፈልገው ሥራ እንዲገለግሉ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችን አዘዘለት።
🌼 ከዚህም በኋላ በፈረስ ተቀምጦ ከአባቱ ፊት ወጣ ሎሌዎቹንም እንዲህ አላቸው "መቶ የወርቅ ዲናርን ወስዳችሁ በፍጥነት ምሳ አዘጋጁልን ልጆች ባልንጀሮቼን እኔ ብቻዬን ሒጄ እጠራቸዋለሁ"። ዘመዶቹም ሰምተው ተመለሱ እርሱም ብቻውን ሒዶ ያንን ወርቅ ለድኖችና ለምስኪኖች በተነ ፈረሱንም ለአንድ ድኃ ሰጠ በላዩ ካለ ልብስ በቀር ምንም ምን አላስቀረም።
❤ ይህ የከበረ አባ በርሱማ በዚህ የጽና ተጋድሎ ሠላሳ ዓመታትን በፈጸመ ጊዜ እግዚአብሔርንም አገልግሎ ከዚህ በኋላ ጳጒሜን አምስት በዚች ቀን በሺህ ሠላሳ ሦስት ዓመተ ሰማዕታት በሰላም በፍቅር አንድነት አረፈ።
❤ ከዚህ አስቀድሞ ደቀ መዝሙሩ ቀሲስ ዮሐንስ በልቡ እንዲህ አለ "ከአባታችን በርሱማ በኋላ እንግዲህ ስዎችን ማን ያጽናናቸዋል"። ደቀ መዝሙሩ ያሰበውን በመንፈስ ቅዱስ አውቆ በንጹሕ አንደበቱ እንዲህ ብሎ መለሰለት። "ልጄ ዮሐንስ ሆይ የቶባል ልጅ አባ በርሱማ ብሎ ስሜን የሚጠራኝን ሁሉ ከእሳቸው እንደማልርቅ ዕወቅ እኔ እነሆኝ ብዬ የክብር ባለቤት ከሆነ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የሚሻውን ሁሉ እፈጽምለታለሁ"።
❤ ከዚህም በኋላ ወደ ግራው ተመልክቶ እነሆ ፈለጉብን ተመራመሩን ከክፋ ሥራ ምንም ምን በእኛ ላይ አላገኙም አለ። ከዚህም በኋላ ደግሞ ደቀ መዝሙሩ አብርሃምን "ቢላዋ ወይም መቊረጭት ስጠኝ" አለው መቁረጫውንም ተቀብሎ ምላሱን ቆርጦ ጣላትና እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው የሚያስፈራኝ ምንድነው የሚለውን መዝሙር እስከ መጨረሻው ይዘምር ጀመር።
❤ ከዚህም በኋላ አዳኝ በሆነ መስቀል ምልክት ፊቱን አማተበ ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ ብርሃናውያን መላእክትም የከበረች ንጽሕት ነፍሱን ተድላ ደስታ ወደ ሚገኝባት ገነት አሳረጓት።
❤ መነኰሳቱም ከበግ ጸጒር በተሠራ ንጽሕ በሆነ በነጭ ባና ገነዙት ተሸክመውም ወስደው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት። ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሰማንያኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስ መጣ ከእርሱ ጋርም ኤጲስቆጶሳት ቀሳውስትና ዲያቆናት የምስር አገር ታላላቆችና ብዙ የክርስቲያን ወገኖች በአንድነት ሁነው በመዘመርና በማመስገን በታላቅ ክብር ሥጋውን ገንዘው ቀበሩት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ በርሱማ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #የምስር_አገር_ኤጲስቆጶስ_አባ_ያዕቆብ፦ ይህም ተጋዳይ የሆነ አባት ገና በታናሽነቱ የምንኵስናን ልብስ ይለብስ ዘንድ ነፍሱ ወደደች። ከሀገሩም ወጥቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደና በአባ ዮሐንስ ሐጺር በዓት ውስጥ ኖረ በዚያም ጽኑዕ በሆነ ገድል ብዙ ዘመናት ተጠምዶ ኖረ።
❤ ከዚህም በኋላ በአባ ዮሐንስ ሐጺር ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊቀ ዲያቆናት አድርገው ሾሙት የደግነቱ፣ የትሩፋቱና የቅድስናውም ዜና ተሰማ። በእግዚአብሔርም ፈቃድ በምስር አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት። በሹመቱ ወንበርም በተቀመጠ ጊዜ ጾምን ጸሎትን ጨመረ ስለ ሹመቱም ተጋድሎውንና አገልግሎቱን ከቀድሞው አበዛ እንጂ ቸልል አላለም። ሕዝቡንም ሁልጊዜ ያስተምራቸዋል መጻሕፍትንም ያነብላቸዋል ከእነርሱ ሥውር የሆነውንም ይተረጒምላቸዋል።
❤ ኃጢአትን በመሥራት የሚኖሩትን ይገሥጻቸዋል፤ በንስሐ እስከሚመለሱም ሥጋውንና ደሙን ከመቀበል ያርቃቸዋል። በጎ ተጋድሎውንም በፈጸመ ጊዜ ጥቂት ታመመ መንጋዎቹንም ጠርቶ በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ አዘዛቸው ደግሞ ካህናቱን ጠርቶ በጸሎትና በቅዳሴ ጊዜ ቸለል እንዳይሉ አዘዛቸው። ሁለተኛም "ሥጋውንና ደሙን ለማክበር በንጽሕና እግዚአብሔርን በመፍራት ሁናችሁ ካላገለገላችሁ ከደማችሁ ንጹሕ ነኝ" አላቸው።
❤ ከዚህም በኋላ ፊቱንና ደረቱን በመስቀል ምልክት አማተበ እጆቹንም ዘረጋ ዐይኖቹንም ራሱ ከደነና ጳጒሜን 5 ቀን በሰላም ዐረፈ በአማሩ ልብሶችም ገነዙት ታላቅ ልቅሶንም አልቅሰው በክብር በምስጋና በማወደስ ቀበሩት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ያዕቆብ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጳጒሜን 5 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለበርሱማ_ትርሲተ_ዓለም_ዘገደፈ። እስከ ኢያጥረየ አሐደ ዐጽፈ። ወዲበ ዝኒ ወሰከ ፃማ ተጋድሎ ትሩፈ። ከመ ያጽምዕ አመ ደኃሪ ምስለ ቅዱሳን ምዕራፈ። ማዕከለ ሥጋሁ ወምድር ኢገብራ መንጸፈ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የጳጒሜን_5።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ላዕለ ተኵላ ወከይሲ ትፄዐን። ወትከይድ አንበሳ ወከይሴ። እስመ ብየ ተወከለ አድኅኖ"። መዝ 90፥13-14። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 11፥32-ፍ.ም፣ 2ኛ ጴጥ 1፥19-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 13፥1-12። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 5፥1-17 ወይም ማር16፥15-19። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የነቢዩ ቅዱስ አሞጽና የአባ በርሱማ የዕረፍት በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
