ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ
Ir al canal en Telegram
ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።
Mostrar más609
Suscriptores
-124 horas
-37 días
-1130 días
Archivo de publicaciones
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አሜን"። ❤
❤ #ጥር ፳፭ (25) ቀን።
❤ እንኳን ለኢትዮጽያዊ ጻድቅ #ለአቡነ_ተክለ_ሃይማኖት_ለአጎት_ልጅ ለታላቁ አባት ከበሬ ጋር ተጠምደው በማረስ ሰማዕትነት ለተቀበሉት #ለአቡነ_ሕፃን_ሞዐ_ለልደታቸው በዓልና ለታላቁ ሰማዕት #ለቅዱስ_መርቆሬዎስ በሥዕሉ ላይ አድሮ ቅዱሳን ለሆኑ #ባስልዮስንና_ጎርጎርዮስን በመርዳት ከሃዲውን ንጉሥ ዑልያኖስን ለገደለባት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #ሰማዕቱ_ቅዱስ_መርቆሬዎስ_ያደረገው ተአምር፦ በቀጰዶቅያና በቂሳሪያ በተሾመ በኢጲስቆጶስ ቅዱስ ባስልዮስ ዘመን ዑልያኖስ በነገሠ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ካደ። ከቅዱስ ባስልዮስ ተአምራት በአንዷ ውስጥ እንደተጻፈው ከሓዲ ዑልያኖስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑትን ከባድ ሥቃይ አደረሰባቸው። በቅዱስ ባስልዮስ ላይም ተቈጣ፤ አሰረውም። በክርስቲያኖች ላይ ከባድ ሥራ ባበዛባቸው ጊዜ ቅዱስ ባስልዮስ ስለ ከሐዲ ዑልያኖስ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ይለምን ጀመረ። ወደ ቅዱስ መርቆሬዎስ ለመነ።
❤ እግዚአብሔር ጸሎቱን ሰማና ታላቁን ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስን ላከለት። በፈረስ ተጭኖ መጣና ከሓዲ ዑልያኖስን አንገቱን በጦር ወጋው። በፋርስ ምድር በውጊያ በክፉ አሟሟት ሞተ። ቅዱስ ባስልዮስ ይህን ራእይ በቅዱስ መርቆሬዎስ ሥዕል ላይ ባየ ጊዜ ፈጽሞ ደስ አለው። የታላቁ ሰማዕት የቅዱስ መርቆሬዎስ አካለ ሥጋ ያለበት ቦታ ተገልጦለት እየጸለየና እያደነቀ ገባ። ያን ጊዜ የቅዱስ መርቆሬዎስ ሰይፍና ጦር ከቅዱስ መርቆሬዎስ ሥዕል ሥር ያለበት ቦታ እስኪሞላ ድረስ ከእነርሱ ብዙ ደም እየፈሰሰ ወደ ቦታቸው ተመለሱ።
❤ ያን ጊዜ ቅዱስ ባስልዮስ ጮኸ። "የክርስቶስ ሰማዕት ሆይ፤ የእውነት ጠላት የሆነውን ዑልያኖስን ገደልከውን?" አለ። ቅዱስ መርቆሬዎስ በቅዱስ ባስልዮስ ፊት "አወን ገደልኩት" እያለ በሥዕሉ ላይ ራሱን ዘንበል አደረገ። ቅዱስ ባስልዮስ የእግዚአብሔርን ክብርና ምስጋና የኢየሱስ ክርስቶስ ሰማዕት የሆነውን የቅዱስ መርቆሬዎስን ብዙ ተአምርና ድንቅ ድንቅ ሥራ አደነቀ። የሰማዕቱ የቅዱስ መርቆሬዎስ ጸሎቱና በረቱ ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን። ምንጭ፦ የቅዱስ መርቆሬዎስ ገድል ተአምር 2።
✝ ✝ ✝
❤ #አቡነ_ሕፃን_ሞዐ፡- በአባታቸው አርከሌድስ እናታቸው ትቤ ጽዮን ይባላሉ፡፡ የተወለዱት ጥር25 ነው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ እና ከእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር የሥጋ ዝምድና አላቸው፡፡ ይኸውም አባታቸው አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ወንድማማቾቸ ናቸው፡፡ አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ሌሎች ሌሎች አራት ወንድሞች አሏቸው፡፡
❤ እነርሱም እንድርያስ፣ ዘርዐ አብርሃም፣ ቀሲስ ዮናስ እና ቀሲስ ዮሐንስ ናቸው፡፡ አርከሌድስ ሕፃን ሞዐን ይወልዳል፣ ጸጋ ዘአብ ተክለ ሃይማኖትን ይወልዳል፣ እንድርያስ ሳሙኤል ዘወገግን፣ዘርዐ አብርሃም ታላቁ አኖሬዎዮስን፣ ቀሲስ ዮናስ ገላውዲዮስንና የፈጠጋሩን ማትያስን፣ እና ቀሲስ ዮሐንስ ዜና ማርቆስን ይወልዳሉ፡፡ እነዚህ የከበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን በእናታቸውም ወገን ቢሆን እንዲሁ በዝምድና የተቆራኙ ናቸው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ በሌላኛው ስማቸው ሕፃን ዘደብረ በግዕ ተብለውም ይጠራሉ፡፡ ይኸውም የደብረ በግዕን ገዳም የመሠረቱት እርሳቸው ስለሆኑ ነው፡፡
❤ ከአራባ ሰባቱ የአገራችን ቀደምት ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ በመንዝና በተጉለት የሚገኙ ታላላቅ ገዳማትን አብዛኞቹን የመሠረቷቸው አቡነ ሕፃን ሞዐ ናቸው፡፡ ጻድቁ በክፉዎች ወሬና ሴራ ምክንያት ከበሬ ጋር ተጠምደው ሰማዕትነት የተቀበሉ አባት ናቸው፡፡ ከበሬ ጋር ሲታረሱ ውለው በእጅጉ ከደከማቸ በኋላ በኃይል የተነፈሱባት ምድሪቱ ዛሬም ድረስ ልክ እንደሰው የሚሞቅ ትንፋሽ ታወጣለች፡፡ ያም በጻድቁ እስትንፋስ አምሳል ከመሬት ውስጥ የሚወጣው እስትንፋስ ለአስም በሽታ መድኃኒት ሆኖ ብዙዎችን እየፈወ ነው፡፡ ገዳማቸው ከደብረ ብርሃን ከተማ በእግር የሁለት ሰዓት መንገድ ርቀት ይገኛል፡፡ ይኸውም ከወንይዬ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አጠገብ ነው፡፡ ጻድቁ ጥር 25 ቀን ልደታቸው፣ ጥቅምት25 ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ዕለት ሲሆን ሐምሌ25 ደግሞ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ምንጭ፦ ከገድላት አንደበት።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ጥር ፳፬ (24) ቀን።
❤ እንኳን #ከደቡባዊ_ግብጽ ከታችኛው ምድር አውራጃ ከንሒሳ ከተማ ለሆነ #ለቅዱስ_ለአባ_ኖብ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለልደት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በፍቅር አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #ቅዱስ_አባ_ኖብ፦ይህም ቅዱስ ከደቡባዊ ግብጽ ከታችኛው ምድር አውራጃ ከንሒሳ ከተማ ነው።
ወላጆቹ ቅዱሳን ንጹሐንና የሚራሩ ነበሩ። ይህንንም ቅዱስ ኖብን በወለዱት ጊዜ ዐሥራ ሁለት ዓመት እስኪሆነው ፈሪሀ እግዚአብሔርን እያስተማሩ አሳደጉት። ቤተ ክርስቲያንን የመጻሕፍትን ቃል መስማትንና መማርን የሚወድ ሆነ።
❤ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የክርስቲያን ወገኖችን ዲዮቅልጥያኖስ በአሠቃያቸው ጊዜ ይህ ቅዱስ ደሙን ስለ ጌታችን ሊአፈስ አሰበ ያን ጊዜም ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ ቄሱንም ምእመናንን እንዲህ እያለ ሲያስተምራቸውና ሲያበረታቸው "ጣዖታትን ከምታመልኩ ክብር ይግባውና ስለ መድኃኒታችን ስለ ክርስቶስ ነፍሳችሁን ለሞት አሳልፋችሁ ብትሰጡ ለእናንተ መልካም ነው" ሲላቸው ሰማው። ይህም ቅዱስ እያዘነና እየተከዘ ወደ ቤቱ ተመለሰ አባቱም የተወለትን ወርቁንና ብሩን ልብሶችን ሁሉ ተመልክቶ እንዲህ አለ ሁሉ ነገር የዚህ ዓለም ፍላጎቱም ሁሉ እንደ ሚያልፍ እነሆ ተጽፏል። ከዚህም በኋላ ገንዘቡን ሁሉ ወስዶ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጠ።
❤ ከዚህም በኋላ ወደ ሀገረ ገምኑዲ ሔደ በእግሩም ሲጓዝ በባሕሩ ዳርቻ ሉስዮስ የሚባለውን መኰንን አገኘው በፊቱም ቁሞ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመነ። መኰንኑም ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለት በእርሱ ላይም የሚደርሰውን ሁሉ ነግሮት አጽናናው።
❤ ከዚህም በኋላ መኰንኑ ወደ ሰሜን አገር ሲጓዝ የከበረ ኖብን ከእርሱ ጋራ በመርከብ ወሰደው በመርከቡም ምሰሶ ላይ ዘቅዝቆ ሰቀለው መኰንኑም ሊበላና ሊጠጣ ተቀመጠ በመኰንኑም እጅ የነበረው ጽዋ ወዲያውኑ እንደ ደንጊያ ሆነ የወታደሮቹም ዐይኖቻቸው ታወሩ የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ወርዶ አባ ኖብን ፈትቶ ከተሰቀለበት አወረደው በአፍንጫውና በአፉ የወረደውንም ደሙን አሻሸለት።
❤ ከዚህ በኋላም መልካም ነፋስ ነፍሶ መርከቢቱ ተጓዘች። ወደ አትሪብ ከተማም ደረሱ ወታደሮችም ይህን ድንቅ ተአምር አይተው ትጥቃቸውን ፈተው በመኰንኑ ፊት ጣሉ። ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመኑ ሰማዕታትም ሆነው ራሳቸውን ቆረጡአቸው የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ። መኰንኑም በአትሪብ ከተማ ቅዱስ አባ ኖብን ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው በብረት ዐልጋ ላይም አስተኝተው ከበታቹ እሳትን አነደዱ በጸለየ ጊዜም እግዚአብሔር ከእሳት አዳነው።
❤ ከዚህም በኋላ በመጋዝ መገዙት ሕዋሳቱንም ቆራረጡ የእግዚአብሔር መልአክም ወርዶ አዳነው ያለ ጉዳትም በጤና አስነሣው። ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ከተማ ወሰዱት በዚያም ብዙ አሠቃዩት በላዩም እባቦችን ሰደዱ ግን አልቀረቡትም ከእባቦችም አንዱ ሒዶ በመኰንኑ አንገት ተጠመጠመ ያስጥሉትም ዘንድ ሟርተኞቹን አዘዛቸው ግን አልተቻላቸውም ከዚህም በኋላ ያድነው ዘንድ ቅዱስ አባ ኖብን ለመነው ቅዱሱም ከይሲውን ትቶት ከአንገቱ እንዲወርድ አዘዘው።
❤ መኰንኑም ሁለተኛ በእሳት እንዲአቃጥሉት ሟርተኞችንና ሥራየኞችን አዘዛቸው እሳቱም ምንም አልነካውም። አቅፋሐስ ከሚባል አገርም ዮልዮስ መጣ ከእርሱም እንደ ተረዳ ገድሉን ጻፈ። መኰንኑም ማሠቃየቱን በሰለቸ ጊዜ አንገቱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ።
❤ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ተገልጾለት አጽናናው እንዲህ ብሎም ቃል ኪዳን ሰጠው "ሥጋህ በሚኖርበት ቦታ ከእርሱ ታላቅ ፈውስ ይሆናል እንዲሁም በመከራው ጊዜ ስምህን በመጥራት ከእግዚአብሔር ርዳታ ለሚሻ ሁሉ ድኅነት ይደረግለታል። መታሰቢያህንም ለሚያደርግ ሁሉ የተራበ ለሚያጠግብ፣ የተጠማም ለሚያጠጣ፣ ለቤተ ክርስቲያንም በስምህ መባ ለሚሰጠው፣ የገድልህንም መጽሐፍ ለሚጽፍ ኃጢአቱን ይቅር እለዋለሁ መንግሥተ ሰማያትንም አወርሰዋለሁ"።
❤ ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡ ተጋድሎውንም ፈጸመ ሥጋውንም ቅዱስ ዮልዮሰ አንሥቶ ከሁለት አገልጋዮቹ ጋራ ንሒሳ ወደ ሚባል አገሩ ላከው። የመከራውም ወራት በተፈጸመ ጊዜ አብያተ ክርስቲያናትን ሠሩለት በውስጣቸውም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ አባ ኖብ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፦ የሐምሌ 24 ስንክሳር።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አሜን"። ❤
❤ #ጥር ፳፬ (24) ቀን።
❤ እንኳን #ለታላቁ_አባት_ለሐዲስ_ሐዋርያ ለፀሐይ ዘኢትዮጵያ #ለአቡነ_ተክለሃይማኖት በቁመትና በጸሎት ብዛት አንዲቱ የእግሩ አገዳ ለተሰበረበት (#ለስብረተ_አፅማቸው) ዓመታዊ መታሰቢያ በዓልና ለኢትዮጵያዊው ጻድቅ እንደ ነዳይ ሆነው ለምነው ያገኙትን ለጦም አዳሪዎች በመመጽወት ለሚታወቁት #ለአቡነ_እጨጌ_መርሐ_ክርስቶስ (ዘሸዋ) ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #የአቡነ_ተክለ_ሃይማኖት_ስብረተ_አፅም፦ "...ከበዐቱ ሳይወጣ ሌሊትና ቀን ቆመ። አልተቀመጠም ወደ ግራና ወደ ቀኝም አልተንቀሳቀሰም። ውኃም ቅጠልም ቢሆን ከቅዳሜና ከእሑድ በቀር በዚያ ወራት ምንም ምን አልቀመሰም። እህል ግን ከመነኰሰ ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ አልቀመሰም። ፀሓይንም ጨረቃንም ከዋክብትን በጋና ክረምትንም ቡቃያና አበባንም ፍሬውንም አላየም። ዓይኖች ሳሉት እንደ ዕውር ጆሮዎች ሳሉት እንደ ደንቆሮ የሚናገር የተከናወነ አንደበት እያለው እንደ ዲዳ ሆነ። ከምስጋና በቀር ምንም ምን አይናገርም። ሌሊትና ቀንም እግዚአብሔርን አመሰገነ። ዓለምንም እንደ ትቢያና እንደ ጉድፍ ቆጠረው ከክርስቶስ ጋር እንደተሰቀለ ሆነ ልቡናውም ዘወትር ወደ ዓየር የተመሰጠ ነበር። እንዲህ ባለም ገድል ብዙ ዘመን (22ዓመታት) ኖረ። ቁመትንም ካበዛ ወዲህ አንዲቱ የእግሩ አገዳ ተሰበረች ደቀ መዛሙርቱ አንሥተው አክብረው በሰበን ጠቅልለው ከመንበሩ እግር በታች ቀበሯት። ከዚህም ባንዲት እግሩ ሰባት ዓመት ቆመ። ከነዚህም አራቱን ዓመት ውሃው አልጠጣም"። ምንጭ፦ ገድለ ተክለ ሃይማኖት ምዕ 53፥8-11።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #እጨጌ_መርሐ_ክርስቶስ (ዘሸዋ)፡- ትውልዳቸው አገራቸው ሸዋ ሚዳ ሲሆን ለገዳማት ብዙ የደከሙ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ በተለይም በእጅጉ የሚታወቁበት አንድ ገድል አላቸው፡፡ ይኸውም እንደ ነዳይ ሆነው ለምነው ያገኙትን ለጦም አዳሪዎች በመመጽወት ይታወቃሉ፡፡ ከባለ ሀብቶች ለምነው ያገኙትን ለድሆች ይመጸውቱትና በቀረው ቤተ ክርስቲያን ይሠሩበታል፡፡ አስደናቂ ገድላቸውና ዐፅማቸው በደብረ ሊባኖስ ይገኛል፡፡ በትግራይም ትልቅ ገዳም አላቸው። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አሜን"። ❤
❤ #ጥር ፳፫ (23) ቀን።
❤ እንኳን #ከሰባ_ሁለቱ_አርድእት_ለአንዱ ለሐዋርያው #ቅዱስ_ጳውሎስ_ደቀ_መዝሙሩ (በመንፈስ ልጁ) ለሆነው #ለቅዱስ_ጢሞቴዎስ ለዕረፍት በዓልና ለጻድቁ ንጉሥ #ለቅዱስ_ቴዎዶስዮስ ለመታሰቢያ በዓሉ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከከበሩ ሰማዕታት ከቅዱሳን ጌርሎስና አትናቴዎስ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #ቅዱስ_ጢሞቴዎስ፦ የዚህም ቅዱስ ልደቱና እድገቱ ልስጥራን ከሚባል አገር ነው አባቱም ከዋክብትን የሚያመልክ ዮናናዊ ነው እናቱ ግን በኦሪት ሕግ ጥላ ሥር ያለች ናት። የከበረ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም በልስጥራን አገር በሰበከ ጊዜ ይህ ጢሞቴዎስ ስብቱንና ትምህርቱን ሰማ እግዚአብሔርም በቅዱስ ጳውሎስ እጅ የሚደያደርጋቸውን ድንቆች ተአምራቶችን አይቶ እሊህም ተአምራቶች አስተዋዮችን አይቶ እሊህም ተአምራቶች አስተዋዮችና ጥበበኞች የሚደነግጡባቸው ናቸው ስለዚህም ወደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ሒዶ በእርሱ ትምህርት በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቆ የሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ ሆነ ወደ ብዙ አገሮችም ተከትሎት በመሔድ ከእርሱ ጋር ደከመ ታላቅ መከራና ብዙ ኀዘንም ደርሶበታል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በኤፊሶን ውስጥ በአንዲት አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾመው።
❤ በዚያንም ጊዜ ወደርሷ ገብቶ ለሰዎቿ በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰበከ ብዙዎችንም ወደ ቀናች ሃይማኖት መልሶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ከዚህም በኋላ በዙሪያዋ ወዳሉ ብዙዎች አገሮች በርቀትም ለሚገኙ አገሮችም የከበረ ወንጌልን ሰበከላቸው። የከበረ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ሁለት መጻሕፍቶችን ጽፎ ወደርሱ ልኳል እርሳቸውም ሕዝቡን የሚያስተምርባቸው ራሱም ከቢጽ ሐሳውያን የሚጠብቅባቸው ቅስና ወይም ዲቁና ሊሾም የሚገባውንና የማይገባውን የሚለይበት ክህነት በማይገባው እጁን እንዳይጭን የሚያስጠነቅቁ ናቸው ጢሞቴዎስን ደግሞ ለርሱ ተወዳጅ ልጁ አድርጎ ይጠራዋል መልእክቶቹንም በእርሱ እጅ ወደ አገሮች ልኳል።
❤ በላያቸው የተሾመባቸውን የክርስቶስን መንጋዎች ፈጽሞ በጠበቀ ጊዜ በትምህርቶቹ በተግሣጾቹና በድርሰቶቹ ልቡናቸውን ብሩህ አደረገ አይሁድንና ዮናናውያንን ይገሥጻቸውና ይዘልፋቸው ነበር እነርሱም ቀንተውበት ሁሉም በጠላትነት ተነሡበት ተሰብስበውም ጥር 23 ቀን ገደሉት ምእመናንም ሥጋውን አንሥተው ቀበሩት ጻድቅ ቈስጠንጢኖስም እስከ ነገሠ በዚያው ኖረ እርሱም ስለ ሥጋው አስቦ ወደ ቊስጥንጥንያ ከተማ በጥር ወር በሃያ ሰባት ቀን አፈለሰው በዚያችም ቀን በዓል አደረገለት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያ ቅዱስ ጢሞቴዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጥር 23 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለጢሞቴዎስ_ዘተሠይመ_ቀዋሜ። በመልእክተ ጳውሎስ መምህረ ሮሜ። ለዮናናውያን ኮኖሙ ዘላፌ ወለአይሁድ ረጋሜ። እስከ አድምዐ እዴሆሙ ዘስምዐ ሞቱ ፍጻሜ። እንተ ተወሰነ ሎቱ ሶበ በጽሐ ዕድሜ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የጥር_23።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወበመንፈስ አዚዝ አፅንዐኒ። ከመ እምሐሮሙ ለኃጥአን ፍኖተከ። ወረሲዓን ይትመየጡ ኀቤከ። መዝ 50፥12-13። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ጢሞ 1፥1-10፣ 1ኛ ጴጥ 3፥13-18 እና የሐዋ ሥራ 16፥1-13። የሚነበበው ወንጌል 12፥17-35። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱሳን ሐዋርያት ቅዳሴ ነው። መልካም የሐዋርያው የቅዱስ ጢሞቴዎስ የዕረፍት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "እምክቡዳን አቅርንት ዘእምኔሆሙ። አውልደ ንግሥት ለክብር። ወትቀውም ንግሥት በየማንከ"። መዝ 44፥8-9። የሚነበበው ማቴ 11፥28-ፍ.ም።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ጻድቅሰ ከመ በቀልት ይፈሪ። ወይበዝኅ ከመ ዘግባ ዘሊባኖስ። ትኩላን እሙንቱ ውስተ ቤተ እግዚአብሔር"። መዝ 91፥12-13 የሚነበቡት መልዕክታት ኤፌ 7፥10-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 4፥4-12፣ እና የሐዋ ሥራ 15፥1-4 ወይም 28፥1-11። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 6፥5-19። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ወይም የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ዑራኤልና የሲመት በዓልና የአባ እንጦንስ የዕረፍት ለሁላችንም ይሁንልን።
ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta):
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አሜን"። ❤
❤ #ጥር ፳፪ (22) ቀን።
❤ እንኳን #ለሊቀ_መላእክት_ለቅዱስ_ዑራኤል ለሢመቱ (ለተሾመበት) ዓመታዊ መታሰቢያ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #ሊቀ_መላእክት_ቅዱስ_ዑራኤል፡- ኢዮር፣ ራማ እና ኤረር የተባሉ ሦስት የመላእክት ከተሞች አሉ፡፡ እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክት ከፈጠራቸው በኋላ በነገድ 100 በአለቃ 10 አድርጎ በሦስቱ ሰማያት አስፍሯቸዋል፡፡ ኢዮርን በ4፣ ራማን በ3፣ ኤረርንም በ3 ከፍሎ ነው በዓሥሩ ከተማ ያሰፈራቸው፡፡
❤ በዚህም መሠረት ኢዮርን ላይና ታች አድርጎ በ4 ከተማ ከፍሏታል፡፡ በእርሷ ያሉትን መላእክትን በ40 ነገድ 4 አለቃ አድርጎ ከፈላቸው፡፡ የመጀመሪያው ነገድ "አጋእዝት" ይባላሉ፡፡ አለቃቸው ሣጥናኤል ነበር፤ እርሱም የመላእክትን ሁሉ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ያሳርግ ነበር፡፡ ከክብሩ ሲዋረድ ቅዱስ ሚካኤል በምትኩ ተሹሞበታል፡፡ ሁለተኛው ነገድ "ኪሩቤል" ይባላሉ፡፡ እነርሱም መንበረ ሥላሴን ይሸከማሉ፡፡ የቀሳውስት አምሳል ናቸው፡፡ አለቆቻቸው ገጸ ሰብና ገጸ አንበስ ናቸው፡፡ በሦስተኛው ከተማ በኢዮር ያሉት "ሱራፌል" ይባላሉ፡፡ የዲያቆናት አምሳል ናቸው፡፡
❤ በትንቢተ ኢሳያስ በምዕራፍ 6 ላይ የተገለጹትና ኢሳያስን ከለምጹ እንዲፈወስ ያደረጉት ናቸው፡፡ አለቆቻቸው ገጸ ላህምና ገጸ ንስር ናቸው፡፡ (በነገራችን ላይ "ከሩቤል" ወይም "ሱራፌል" የሚባሉ የግለሰብ መጠሪያ ስሞች ስህተት ናቸው፡፡ አንደኛ እነዚህ ስሞች የብዙ መላእክት መጠሪያን የሚወክሉ ናቸው፡፡ ለአንዱ ሲሆን "ኪሩብ፣ ሱራፊ" ይባላል፡፡ "ኪሩቤል" ወይም "ሱራፌል" ማለት ግን የብዙ ቁጥራቸው መጠሪያ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የቅዱሳን መላእክትን ስም እንዳለ በቁሙ ወስዶ ለግል መጠሪያ ስም ማዋል ተገቢ አይደለም፡፡ "ወለተ ሚካኤል፣ ክብፈ ገብርኤል…." እየተባሉ ይሰየማሉ እንጂ ቀጥታ "ሚካኤል"፣ "ገብርኤል" እያሉ ሰዎችን መሰየም ስህተት ነው፡፡ 4ኛው ከተማ በኢዮር ያሉት ኃይላት ይባላሉ፡፡ የእሳት ሰይፍ ይዘው በሥሉስ ቅዱስ ፊት የሚቆሙ ናቸው፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት የዛሉና የደከሙ ክርስቲያኖችን የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ አለቃቸውም ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡
❤ ዳግመኛም እግዚአብሔር በራማ ያሉትን መላእክት በ30 ነገድ በ3 አለቃ አድርጎ ከፈላቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ "አርባብ" ይባላሉ፡፡ የሥላሴ እልፍኝ አስከልካዮች ናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን መንበር በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ ሁለተኞቹ በራማ ከተማ ያሉት "መናብርት" ይባላሉ፡፡ ለእግዚአብሔርን እጅግ ቅርብ የሆኑ ናቸው፡፡ የመብረቅ ጋሻቸውን የእሳት ጦራቸውን ይዘው የሥላሴ ጋሻ ጃግሬዎች ሆነው በተጠንቀቅ ይቆማሉ፡፡ የሰውን ችግር ለእግዚአብሔር ያቀርባሉ፡፡ መዝ 88፡6፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሦስተኞቹ በራማ ከተማ ያሉት "ሥልጣናት" ይባላሉ፡፡ መላውን ፍጥረት ለመጠበቅ ሥልጣን የተሰጣቸውና የምጽአት ዕለት አዋጅ ነጋሪዎች ናቸው፡፡ ዳን 12፡1፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ሱርያል ነው፡፡
❤ ዳግመኛም እግዚአብሔር በኤረር ያሉትን መላእክት በ30 ነገድ በ3 አለቃ አድርጎ ከፈላቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ "መኳንንት" ይባላሉ፡፡ የሥላሴ የእሳት ባለ ቀስት ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ልዩ ጠባቂዎች ናቸው፤ በተለይ በአደጋ ጊዜ ሎጥን እንዳዳኑት ፈጥነው ይደርሳሉ፡፡ በዕለተ ምጽዓት የሰውን ሁሉ ዐፅም ሰብስበው ለትንሣኤ ዘጉባኤ ያበቃሉ፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ሰዳካኤል ነው፡፡ ሁለተኛዎቹ "ሊቃናት" ይላሉ፡፡ የሥላሴ የእሳት ፈረሶች ናቸው፡፡ በእሳት ፈረስ ይመላለሳሉ፡፡ እነዚህም 24ቱ ካህናተ ሰማይ ሲሆኑ አለቃቸው ቅዱስ ሰላታኤል ነው፡፡ በኤረር ከተማ የሰፈሩት ሦስተኛዎቹ "መላእክት" ይባላሉ፡፡ ፍጥረትን ሁሉ የሚጠብቁ ናቸው፡፡ አለቃቸው ቅዱስ አናንኤል ነው፡፡ በእነዚህ የማይጠበቅ ፍጥረት የለም፡፡ ከአዝርእት ጀምሮ ሁሉን ይጠብቃሉ፡፡
❤ ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ "በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ 7 መላእክትን አየሁ" (ራዕ 8፥2) እንዳለ ሊቃነ መላእክት በቁጥር 7 ናቸው፡፡ እነርሱም፡- ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ሩፋኤል፣ ቅዱስ ራጉኤል፣ ቅዱስ ዑራኤል፣ ቅዱስ ፋኑኤል እና ቅዱስ አፍኒን ናቸው፡፡ "ዑራኤል" የሚለው ስም "ዑር" እና "ኤል" ከሚሉ ሁለት ቃላት የተመሠረተ ስም ነው፡፡ "ዑራኤል" ማለት ትርጉሙ "የብርሃን ጌታ፣ የአምላክ ብርሃን" ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ዑራኤል ከ7ቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ በመብረቅና በነጎድጓድ ላይ የተሾመ መልአክ ነው፡፡
❤ በመሆኑም መጽሐፈ ሄኖክ እንደሚገልጸው መባርቅት ለጥጋብና ለበረከት እንዲበርቁ ነጎድጓድም ለሰላም እንዲሆን ያሰማራል፡፡ ምሥጢረ ሰማይንና ሰማያዊውን ዕውቀት ሁሉ ለሄኖክ የገለጸለት መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ የፀሐይን፣ የጨረቃን፣ የከዋክብትንና የሰማይ ሠራዊትን ብርሃንን የሚመራው ይኸው ገናና መልአክ ነው፡፡ መጽሐፈ ሄኖክ 28፡13፡፡ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ሆኖ በተሰቀለ ጊዜ ክቡር ደሙን በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ በብርሃነ መነሳንስ በዓለም ላይ የረጨው ይኸው ገናና መልአክ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡
❤ ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል ጽዋ ጥበብን አጠጥቶ ሰማያዊውን ምሥጢር የገለጠለት መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ ዕውቀት ተሠውሮበት ለነበረው ለኢትዮጵያዊው ሊቅ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም በእመቤታችን ትእዛዝ ጽዋ ጥበብን አጠጥቶ ሰማያዊውን ምሥጢር የገለጠለት ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ "ዑራኤል የተባለ መልአክ ሊረዳኝ መጣ"፡፡ መጽሐፈ ዕዝራ 2፡1፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር የሕይወትና የይቅርታ ዝናም በምድራችን ላይ ያዘንብ ዘንድ እንዲሁም የእርሻችንን አዝመራ በዝናም አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ ለምግብነት እንዲበቃ ከፈጣሪ ዘንድ ምሕረትን የሚለምን መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡
❤ ሊቁ አባ ጊዮርጊስም በመልአኩ አማላጂነት እጅግ ብዙ ድርሰቶችን የደረሱት መልአኩ ጽዋ ሕይወትን ካጠጣቸው በኋላ ነው፡፡ በመጀመሪያም አባ ጊዮርጊስ የተወለዱት በቅዱስ ዑራኤል አብሳሪነት ነው፡፡ በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ የተመሠረቱ አብዛኞቹ ቅዱሳት ገዳማት በቅዱስ ዑራኤል መሪነት ነው፡፡ ድርሳኑ ላይ የማይጠቅሳቸው የሀገራችን የከበሩ ቅዱሳት ገዳማትና ቅዱሳን ነገሥታት የሉም፡፡
የብርሃን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክን ከልጇ ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስትሰደድ መንገድ እየመራ ወደ ግብጽ እና ወደ አገራችንን ኢትዮጵያ ያመጣቸው ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ እመቤታችንን ከተወደደ ልጇ ጋር በደመና ጭኖ መላ ኢትዮጵያን ካስጎበኛት በኋላ ቅድስት አገራችንን ለእመቤታችን የዓሥራት አገር እንድትሆን ያደረገው መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡
❤ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል በዓመት 3 ዓበይት በዓላት አሉት፡፡ ጥር 22 በዓለ ሲመቱ ነው፡፡ መጋቢት 27 የጌታችንን ክቡር የሆነ ወርቀ ደሙን ለዓለም የረጨበት ነው፡፡ ሐምሌ 22 ቀን ቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበትና ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል የዕውቀትን ጽዋ ያጠጣበት ዕለት ነው፡፡ ከሊቀ መላእክት ከቅዱስ ዑራኤል እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። አማላጅነቱ አይለየን! በጸሎቱ ይማረን!። ምንጭ፦ ከገድላት አንደበት።
❤ ሮሜ አገር በደረሰችም ጊዜ ልጃቸው ስለዳነችላቸው ንጉሡና መኳንንቱ የአገሩም ሰዎች ሁሉ ተደስተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ ከዚህም በኋላ አባቷ በገዳም ስለነበራት ቆይታ ልጁን ጠየቃት፡፡ እርሷም "ያ በጸሎቱ ያዳነኝ አባ ኢላርዮን የሚባል መነኩሴ አብዝቶ ይወደኛል፤ አቅፎም ይስመኛል" አለችው፡፡ ንጉሡም ይህንን ሲሰማ ልቡ ታወከና "መነኵሴ እንዴት ሴትን ለመሳም ይገባዋል" አለ፡፡ በዚህም ጊዜ "በእኔ ላይ ይጸልይ ዘንድ አገሬንም ይባርክ ዘንድ ልጄን ያዳናትን አባ ኢላርዮንን ወደኔ ላኩልኝ" ብሎ ደብዳቤ ጽፎ ወደ አስቄጥስ ገዳም ላከ፡፡ አረጋውያኑም ቅድስት ኢላርያ ጠርተው ወደ ንጉሡ አገር ሄዳ እንድትባርከው አዘዟት፡፡ እርሷም ይተዋት ዘንድ እያለቀሰች ብትለምናቸውም እነርሱ ግን "ይህ ንጉሥ ክርስቲያኖችን የሚወድ ጻድቅ ነው፣ ቅዱሳት መጻሕፍትም እንደሚያዙን ትእዛዙን መተላለፍ የለብንም" ብለው አስገድደው ላኳት፡፡ ወደ ንጉሡም በደረሰች ጊዜ ሁሉም በክብር ተቀብለው ተሳለሟት፡፡ ንጉሡና ንግሥቲቱም ለብቻቸው ሆነው ወደ ውስጠኛ ክፍል አስገቧትና ንጉሡ እንዲህ ብሎ ጠየቃት፡- "ልጄን ትስማት እንደነበር በሰማሁ ጊዜ በሀሳቤ ታውኬያለሁ፤ መነኵሴ ሴትን መ ሳም አይገባውምና ይህን ነገር ትገልጥልኝ ዘንድ እወዳለሁ" አላት፡፡
❤ የከበረች ቅድስት ኢላርያም "በነገርኳችሁ ጊዜ ወደ አስጥስ ገዳም መሄድን ላትከለክሉኝ የከበረ ወንጌልን አምጥታችሁ ማሉልኝ" አለቻቸው፡፡ እነርሱም ማሉላት፡፡ በዚህም ጊዜ እርሷ ማለት ልጃቸው ኢላርያ መሆኗን ነገረቻቸው፡፡ እንዴት ከቤተ መንግሥት እንደወጣችም አስረዳቻቸውና በአካሏ ላይ ያለውን ምልክት አሳየቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ በቤተ መንግሥቱ ታላቅ ጩኸት ሆነ፡፡ አቅፈውም እየሳሟት አለቀሱ፡፡ "ከእኛ ዘንድ እንድትሄጂ ከቶ አንተውሽም" አሏት፡፡ እርሷም "በከበረ ወንጌል የማላቸሁትን መሐላ አስቡ" አለቻቸው፡፡ እሺ ብለው ግን እስከ 40 ቀን አብራቸው እንድትቆይ ለመኗት 40 ቀን አብራቸው ቆየች፡፡
❤ ቅድስት ኢላርያም ወደ አስቄጥስ ገዳም ከተመለሰች በኋላ ንጉሡ ዘይኑን ለገዳሙ መነኮሳት ለፍላጎታቸው ይሆን ዘንድ የግብጽን ምድር ግብር እንዲሰጧቸው አዘዘ፡፡ በዚያም ወራት በአባ መቃርስ ገዳም 400 የመነኮሳት ቤቶች ተሠሩ፡፡ በአባ ዮሐንስ ገዳም 700 በአባ ሙሴ ገዳም 300 ቤቶቸ ተሠሩ፡፡ ከዚህም በኋላ ቅድስት ኢላርያ 5 ዓመት ኖራ በሰላም ዐረፈች፡፡ ከዕረፍቷም አስቀድሞ እርሷ ሴት እንደሆነች ያወቀ የለም፡፡ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ኢላርያ ጸሎት ይማረን በከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጥር 21 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ትሴብሖ ኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር። ወሰብሒዮ ለአምላክኪ ጽዮን። እስመ አጽንዐ መናሥግተ ኆኃትኪ"። መዝ 147፥1-2። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ1፥27-ፍ.ም።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "በከመ ሰማዕነ ከማሁ ርኢነ። በሀገረ እግዚአ ኃያላን በሀገረ አምላክነ። እግዚአብሔር ሣረራ ለዓለም"። መዝ 47፥8-9። የሚነበቡት መልዕክታት ገላ 4፥1-12፣ 2ኛ ዮሐ 1፥1-7 እና የሐዋ ሥራ 7፥30-35። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥47-57። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የዕረፍት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ በቀበሩዋትም ጊዜ ከዚያ ሦስት ቀን ኖሩ ዕረፍቷም የሆነው እሑድ ቀን በጥር ወር በሃያ አንድ በዚች ቀን ነበረ ጌታችንም ብርሃናውያን መላእክትን ላከ እነርሱም ሥጋዋን ከመቃብር ወስደው በገነት ውስጥ በዕፀ ሕይወት ሥር አኖሩዋት።
❤ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ ግን ያን ጊዜ አልነበረም በደመና ላይ ተጭኖ እርሱ ሲመጣ መላእክት ሲአሳርጓት እመቤታችንን አገኛት መላእክትም "ለአምላክ እናት ለእመቤታችን ድንግል ማርያም ና እጅ ንሣ" አሉት እርሱም ሰገደላትና ተሳለማት ከእርሷም ተባረከ ከዚህም በኋላ ወደ ሐዋርያት ደረሰ። እነርሱም እመቤታችን ማርያምን እንደ አረፈችና እንደ ቀበሩዋትም ነገሩት ቶማስም "ሥጋዋን እስከማይ አላምንም" አላቸው። ሥጋዋንም ያሳዩት ዘንድ ወደ መቃብርዋ በአደረሱት ጊዜ በመቃብር ወስጥ ሥጋዋን አላገኙም ደንግጠውም አደነቁ ያን ጊዜ ከመላእክት ጋር ወደ ሰማይ ስታርግ እመቤታችንን እንዳገኛት ቅዱስ ቶማስ ነገራቸው። ሐዋርያትም ይህን በሰሙ ጊዜ የእመቤታችንን ዕርገቷን ስለ አላዩ እጅግ አዘኑ ሥጋዋን በምድር ውስጥ ይተው ዘንድ እንዳልወደደ መንፈስ ቅዱስ አስገነዘባቸው። ከዚህም በኋላ አንድ ጊዜ ደግሞ እርሷን ያሳያቸው ዘንድ እንዳለው ጌታችን ቃል ኪዳን በማድረግ ተስፋ ሰጣቸው እነርሱም እሰሰከ ነሐሴ ዐሥራ ስድስት በተስፋ ኖሩ።
❤ የእመቤታችን የዕድሜዋ ዘመን ስሳ አራት ዓመት ነው በአባትና እናቷ ቤት ሦስት ዓመት ከሰባት ወር በቤተ መቅደስም ዐሥራ ሁለት ዓመት በዮሴፍ ቤት ሠላሳ አራት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን ዕረገት በኋላ በወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ ቤት ዐሥራ አራት ዓመት ነው። የሕይወት የድኅነት አለኝታ የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በጸሎቷም ከክፉ ነገር ይጠብቀን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጥር 21 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ #አቡነ_ጎርጎርዮስ_ዘኑሲስ፡- ይኸውም የቅዱስ ባስልዮስ ወንድም ነው፡፡ አገሩ ቂሳርያ ሲሆን የተሾመው ኑሲስ በተባለች ደሴት ላይ ነው፡፡ መናፍቁ ሰባልዮስ "አንድ ገጽ" በማለቱ ሌሎቹ መናፍቃንም መቅዶንዮስና አቡሊናርዮስ "መንፈስ ቅዱስ ህጹፅ" እና "ወልድ ሥጋ እንጂ ነፍስ አልነሳም" በማለታቸው በ381 ዓ.ም 150ው ሊቃውንት በቍስጥንጥንያ ተሰብስበው መናፍቃኑን ተከራክረው እረተው ሃይማኖትን ሲያጸኑ ከጢሞቲዎስ ጋር አንድ ላይ የጉባኤው አፈ ጉባዔ የነበረው ሊቁ ጎርጎሪዮስ ዘኑሲስ ነበር፡፡ እርሱም በጉባኤው ላይ እነ መቅዶንዮስንና አቡሊናርዮስን ተከራክሮ በመርታት መልስ አሳጥቷቸዋል፡፡ ሃይማኖትንም አጽንቷል፡፡
❤ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ቅዳሴ ሲቀድስ ጌታችን በርግብ አምሳል ሲወርድ ያየው ስለነበር ዘወትር እያለቀሰ ይቀድሳል፡፡ ከተጋድሎውም ጽናት የተነሣ ታማሚ ሆኖ ነበር፡፡ በኤጲስ ቆጶስነት ተሹሞ 33 ዓመት ኖሯል፡፡ ከተጋድሎውም ብዛት ድካም አጋጥሞት ነበርና አንድ ቀን ወንድሙ ባስልዮስ ሊጠይቀው መጣ፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስም እንደልማዱ ሊቀድስ ወደ መሠዊያው በወጣ ጊዜ እመቤታችን ተገለጠችለትና "ዕረፍትህ በዕረፍቴ ቀን ነውና ዛሬ ወደእኔ ትመጣለህ" አለችው፡፡ ጎርጎርዮስም የቁርባኑን ቅዳሴ ሲጨርስ ሕዝቡን በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ ለመምከር ተነሣ ነገር ግን ከድካምና ሕመም ብዛት ሰውነቱ መቆም ስላልቻለ ወንደሙን ባስልዮስን "ዛሬ አንተ አስተምራቸው" አለው፡፡ ወዲያውም እንደሚያንቀላፋ ሆነና ዐረፍ አለ፡፡ በቀሰቀሱትም ጊዜ በሞት ዐርፎ አገኙት፡፡ ይኸውን ጥር 21 ቀን ነው፡፡
❤ በስሙ የተጠራ አንድ ቅዳሴና ገድለ ዜና አለው፡፡ በትንቢት ተናጋሪነቱ፣ በደራሲነቱና በመምህርነቱ መጽሐፍ "ጎርጎርዮስ ዐቃቤ ሥራይ ቁስለ መድኃኒት ዘነፍስ" ይለዋል፡፡ ከሃዲው ንጉሥ ዑልያኖስ ወንድማማቾቹን ባስልዮስንና ጎርጎርዮስን በጸሎታቸው ሰዓት ደርሶባቸው እነርሱን ገድሎ መሥዋዕታቸውን ሊበላባቸው ሲመጣባቸው የቅዱስ መርቆሬዎስን ሥዕል በጸሎት ቢማጸኑ ሥዕሉ በገዘፈ ሥጋ ሆኖ በተአምራት ዑልያኖስን በጦር ወግቶ ገድሎላቸዋል፡፡
✝ ✝ ✝
❤ #ቅድስት_ኢላርያ፡- ይኽችም ቅድስት የሮሜው አገር ንጉሥ የዘይኑን ልጅ ናት፡፡ እርሱም እግዚአብሔርን የሚወድ ሃይማኖቱ የቀና ነው፡፡ ልጁ ቅድስት ኢላርያንም ፈሪሃ እግዚአብሔርንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እያስተማረ አሳደጋት፡፡ ከሁለት ሴቶቹ ለጆቹ በቀር ወንድ ልጅ የለውም ነበር፡፡
❤ ቅድስት ኢላርያም ዕድሜዋ ከፍ ሲል ዓለምን ፍጹም ንቃለችና የምንኵስናን ልብስ የመላእክትንም አስኬማ ትለብስ ዘንድ ወደደች፡፡ ከቤተ መንግሥትም ተደብቃ ወጥታ የወንድ ልብስ በመልበስ ወደ ግብጽ አገር ሄደች፡፡ ወደ አስቄጥስ ገዳምም ገብታ ስሙ አባ ባውሚን የሚባል ፍጹም ሽማግሌ ጻድቅ ሰውን አግኝታ የምንኩስና ሀሳቧን ነገረችው፡፡ እርሷም ሴት እንደሆነች ስትነግረው ምሥጢሯን ጠብቆ ለብቻዋ ከዋሻ ውስጥ አስገባት፡፡ እየጎበኛትም ልትሠራው የሚገባትን ሁሉ ያስተምራት ነበር፡፡ እንዲህም ሆና በዚያ ዋሻ ውስጥ 12 ዓመት ኖረች፡፡ ቅድስት ኢላርያ ፂም ስለሌላት ለአረጋውያን መነኮሳት ጃንደረባ ትመስላቸው ነበር፡፡ በወንድ ስም አጠራርም አባ ኢላርዮን ብለው ይጠሯት ነበር፡፡
❤ ከአባቷ ዘንድ ያለችው ታናሽ እኅቷ ርኩስ መንፈስ አደረባትና ብዙ አሠቃያት፡፡ ያድኗትም ዘንድ አባቷ ብዙ በመድከም ገንዘቡን አወጣ ነገር ግን ልትድን አልቻለችም፡፡ መኳንንቶቹም ወደ ግብጽ አስጥስ ገዳም እንዲልካት ለንጉሡ ነገሩት-በዚያ ያሉ መነኮሳት ክብራቸውና ጸጋቸው በሮም አገሮች ሁሉ ታውቋልና፡፡ ንጉሡም የታመመችውን ልጁን ከብዙ ሠራዊት ጋር ወደ ግብጽ ላካት፡፡ ለመነኮሳቱም "… ሁለት ሴቶች ልጆችን ወለድኩ ነገር ግን አንደኛዋ ጥላኝ ጠፋች፣ ሁለተኛዋንም ርኩስ መንፈስ ይዞ መጨወቻ አደረገብኝ፡፡ ቅዱሳን አባቶቼ ሆይ ልጄን በጸሎታቸሁ ትፈውሱልኝ ዘንድ ቅድስናችሁን እለምናለሁ" የምትል ደብዳቤ ጽፎ ላከላቸው፡፡ መነኮሳቱም የንጉሡን ደብዳቤ ካነበቡ በኋላ በልጅቱ ላይ ጸለዩ፡፡ ነገር ግን ያደረባት ርኩስ መንፈስ ሊለቃት አልቻለም፡፡
❤ ከዚህም በኋላ አረጋውያኑ መነኮሳት ጃንደረባ የሚሏትን ኢላርያን ጠርተው እስካዳናት ድረስ የንጉሡን ልጅ ወስደህ "በላይዋ ላይ ጸልይ" ብለው ሰጧት፡፡ እርሷም "ይህ ለእናንተ እንጂ ለእኔ አይቻለኝም" ብትላቸውም ግድ አሏት፡፡
ከዚህም በኋላ ቅድስት ኢላርያ የታመመችውን ልጅ ወደ በዓቷ ወስዳ ጸሎት አደረገችላት፡፡ ሰይጣኑም ወዲያው ጥሏት ሸሸ፡፡ በጥቂት ቀንም ውስጥ ፈጽማ ዳነች፡፡ ቅድስት ኢላርያም እኅቷ እንደሆነች ታውቃለችና አቅፋ ትስማት ነበር ስለ ፍቅሯና ናፍቆቷም ወደ ውጭ እየወጣች ታለቅስ ነበር ነገር ግን ታማ የነበረችው እኅቷ አላወቀቻትም፡፡ ቅድስት ኢላርያም በጸሎቷ ከፈወሰቻ በኋላ ወደ አረጋውያኑ መነኰሳት ወስዳ "እነሆ በጸሎታች እግዚአብሔር ፈውሷታልና ወደ ንጉሡ አባቷ መልሷት" ብላ ሰጠቻቸው፡፡ እነርሱም እጅግ ደስ ብሏቸው ወደ አባቷ መለሷት፡፡
ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta):
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አሜን"። ❤
❤ #ጥር ፳፩ 21 ቀን።
❤ እንኳን #አምላክን_ለወለደች_ለእናታችን #ለእመቤታች_ለቅድስት_ድንግል_ማርያም ለዕረፍቷ በዓል (ለአስተርእዮ ማርያም)፣ ለኑሲስ ኤጲስቆጶስ #ለቅዱስ_ባስልዮስ_ወንድም_ለከበረ_ለቅዱስ_ጎርጎርዮስ ዕረፍት በዓልና ለሮሜ አገር ንጉሥ ለዘይኑን ልጅ ለከበረች #ለቅድስት_ኢላርያ_ለዕረፍት በዓል በሰላምና በጤና እግዚአብሔር አምላክ አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #እመቤታችንንም_ከመጥምቁ #ቅዱስ_ዮሐንስ ጋር በደብረ ማሕው ከተገለጠችበት፣ #ከነቢዩ_ከቅዱስ_ኤርምያስ፣ #ከዮሐንስና_ከአባ_እስክንድር፣ በዋሻ ከሚኖሩ #ከቅዱስ_ኒቆላዎስና_ከኤጲስቆጶስ_ከአባ_ፊቅጦር ከሁሉም ከመታሰቢያቸው፣ በናፍቁ ንጉሥ በመርቅያን ዘመን በሰማዕትነት ከዐረፉ #ከቅዱሳን_ጳውሎስና_ከቀሲስ_ሲላስ ዕረፍት እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #የእመቤታችን_የቅድስት_ድንግል_ማርያም ዕረፍት፦ ያን ጊዜ እመቤታችን በልጅዋ በጌታችን በፈጣሪያችንና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከበረ መቃብሩ ቦታ ትጸልይ ነበር ከዚህም ዓለም እንደምትለይ መንፈስ ቅዱስ ነገራት ከዚህም በኋላ ከደብረ ዘይት ደናግል መጡ ጌታችን ነግሮዋቸዋልና እርሷም ነገረቻቸው። በዚያንም ጊዜ እመቤታችን እንዲህ ብላ ጸለየች "ልጄ ወዳጄም ጌታዬና ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ልመናዬን ተቀብለህ ደቀ መዝሙርህን ዮሐንስን በዚያች ሰዓት አምጣው። እንዲህም ሕያዋን እንደሆኑ ሐዋርያትን ሁሉንም ነፍሳቸውንም የለየሃቸውን አምጣቸው አንተ የሕያዋንና የሙታን አምላክ ነህና ላንተም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን"።
❤ በዚያንም ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ትእዛዝ ከኤፌሶን አገር ዮሐንስን ደመና ተሸክማ ወደ እመቤታችን ማርያም አደረሰችው ሰገደላትና በፊቷ ቁሞ እንዲህ አላት "ሰላምታ ይገባሻል ጌታችን ፈጣሪያችንንና መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለድሺው ጸጋን የተመላሽ ደስ ይበልሽ አንቺ ከዚህ ዓለም ሕይወት ትሒጂአለሽና። ይህም ስሙ ክቡር ምስጉን የሆነ ጌታችንና ፈጣሪያችን ድንቆች ተአምራቶችን በአንቺ ላይ ገለጠ በኋላ ነው"። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ይህን በሰማች ጊዜ እጅግ ደስ አላት እግዚአብሔርንም እንዲህ ብላ አመሰገነችው "ፈጣሪዬ ጌታዬ ላንተ ምስጋና ይሁን አንተ የለመንኩህን ሰጥተኸኛልና አሁንም ነፍሴን ተቀበለው ወደ ሰማይ ወደ አንተ ሊሳርጓት ከሚመጡ መላእክቶችህ ጋር በመምጣትህ የምለምንህን ሁሉ ስጠኝ"።
❤ በዚያንም ጊዜ ከሰማይ እንዲህ የሚል ቃል መጣ "እነሆ አሁን መላእክት ይደርሳሉ ሐዋርያትም ሁሉ ከምድር ዳርቻ በደመና ተጭነው ለሰማይና ለምድር ጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ወደ ሆነች ወደ ቅድስት ድንግል ይደርሳሉ"። ወዲያውኑ ሁሉም ሐዋርያት የሞቱትም ከመቃብራቸው ተነሥተው ወደ እመቤታችን ደርሰው ሰገዱላት "አምላካችን ከአንቺ የተወለደ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ እርሱ ከዚህ ዓለም ለይቶ ቃል ኪዳን እንደሰጠሽ በክብር በምስጋና ከርሱ ጋር የሳርግሻልና" አሏት።
❤ በዚያንም ጊዜ እመቤታችን በዐልጋዋ ላይ ተቀመጠች ሐዋርያትም እንዲህ አለቻቸው "ፈጣሪዬ ፈጣሪያችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመጣ እናንተንም እንዳየኋችሁ እንደማየው አሁን አውቅሁ ከዚህ ከሥጋዬም ወጥቼ ወደዘላለም ሕይወት እሔዳለሁ ነገር ግን ትነግሩኝ ዘንድ እሻለሁ ከዚህም ዓለም እንደምለይ ከወዴት አወቃችሁ?"። "ጴጥሮንና ሐዋርያት ሁሉም ወዳንቺ እንመጣ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አዘዘን በደመና ላይም በተጫን ጊዜ ወዳንቺ እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥንን ደረስን" አሏት።
❤ እመቤታችን ማርያምም ይህን ነገር ከሐዋርያት በሰማች ጊዜ ድምጿን ከፍ አድርጋ "ክርስቶስ ሆይ ክቡር ምስጉን የሆነ ስምህን ፈጽሜ አመሰግናለሁ። የእኔ የአገልጋይህን መከራ ተመልክተህ ድንቅ ኃይልን አድርገህልኛልና ከእንግዲህ ወዲያ ትውልድ ሁሉ ያከብሩኛል ያመሰግኑኛል"። ጸሎቷንና ምስጋናዋን ስትጨርስ ሐዋርያትን እንዲህ አለቻቸው "ዕጣን አምጥታችሁ በማጠን የጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስ ስሙን ጥሩት" እነርሱም እንዳዘዘቻቸው አደረጉ። በዚያንም ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እልፍ አእላፋት መላእክት አጅበው እያመሰገኑት መጣና አረጋጋት ያዘጋጀላትንም ተድላ ደስታ ነገራት በዚያንም ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተደረጉ ዕውሮች አይተዋልና ሐንካሶች ቀንተው ሒደዋልና ደንቆሮዎች ሰምተዋልና ለምጻሞች ነጹ አጋንንትም ከሰዎች ወጥተው ሔዱ ዲዳዎች ተናገሩ በሽታና ደዌ ያለበት ሁሉ ዳነ እመቤታችን ድንግል ማርያም ወዳለችበት ቤት በቀረቡ ጊዜ ከደዌያቸው ይፈወሳሉና።
❤ ከዚህም በኋላ እመቤታችን ተወዳጅ ልጅዋን እንዲህ አለችው "በአየር ውስጥ ተበትነው ከሚኖሩ ከሚያስደነግጡ ግሩማን መላእክት የተነሣ ከእሳት ባሕርም እፈራለሁ" ጌታችንም "እርሳቸው ለማንም በአንቺ ላይ ስልጣን የለውም" አላት። ከሥጋዋም የምትለይበት ጊዜ ሲደርስ ሐዋርያትና ደናግል ትባርካቸው ዘንድ እያለቀሱ ለመኑዋት እጅዋን በላያቸው ዘርግታ ባረከቻቸው በዚያንም ጊዜ ጌታችን ንጽሕት ነፍሷን ከሥጋዋ ለይቶ በመለኮታዊ እጆቹ ይዞ በብርሃን ልብስ አጐናጽፎ ወደ ከፍተኛ መኖሪያ ከእርሱ ጋር አሳረጋት ሥጋዋን ግን እንደሚገባ ገንዘው ወደ ጌቴሴማኒ ተሸክመው እንዲወስዷት ሐዋርያትን አዘዛቸው።
❤ ነፍሷ ከሥጋዋ ከመውጣቷ በፊት በሰው አንደበት ይህ ነው ተብሎ የማይነገር ብርሃንን እያያች ነበር በክብር ባለቤት ጌታችን ክርስቶስም "እንግዲህ ሥጋሽን ተድላ ወዳለበት ገነት አፈልሳለሁ ዳግመኛም ሥጋሽን ከነፍስሽ ጋር አዋህጄ አስነሥቼ መላእክት በውስጡ በፊትሽ ሁነው በሚያመሰግኑበት ተመሳሳይ በሌለው ተድላ ደስታ በአለበት ማደሪያ አኖርሻለሁ" አላት። እመቤታችንም እንዲህ አለች "አቤቱ በረቀቀ ጥበብህ ይህን ሁሉ የሠራህ አመሰግንሃለሁ ሁለተኛም ልመናዬን ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ በስሜ ወዳንተ የሚለምነውን ሁሉ ልመናውን ተቀበለው በመከራም ውስጥ ሁኖ ስሜን ጠርቶ ወዳንተ የሚለምነውን ከመከራው ሁሉ አድነው በሰማይም በምድርም በሥራው ላይ ሁሉ አንተ ከሀሊ ነህና መታሰቢያዬን በውስጧ የሚያደርጉባትን ቦታ ሁሉ ባርክ በእኔ ስም የሚያቀርቡትን የሁሉንም መሥዋዕታቸውን ተቀበል"። ጌታችንም እንዲህ ብሎ መለሰላት "የለመንሺኝን ሁሉ አደርግልሻለሁ ደስ ይበልሽ ከእኔ ከአባቴ ከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ጸጋ ክብር ባለሟልነት ተሰጥቶሻልና ስምሽንም ጠርቶ የሚለምን ሁሉ በዚህም ዓለም በሚመጣውም ዓለም አይጠፋም"።
❤ እመቤታችንም ከአረፈች በኋላ ጌታችን እንዳዘዘ ወደ ጌቴሴማኒ ሊወስዷት ሐዋርያት ገንዘው ተሸከሟት። አይሁድም በሰሙ ጊዜ ሥጋዋን ሊአቃጥሉ ወጡ ከእርሳቸው አንዱ ስሙ ታውፋንያ ከምድር ላይ ይጥላት ዘንድ የእመቤታችንን ዐልጋዋን ያዘ ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ እጆቹን በእሳት ሰይፍ ቀጣውና እጆቹ በዐልጋዋ ላይ ተንጠለጠሉ። ያን ጊዜ በጌታችን አምኖ ወደ እመቤታችን እያለቀሰ እንዲህ ብሎ ለመነ "የእውነተኛ አምላክ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እናት አንቺ በእውነት ድንግል የሆንሽ በእኔ ላይ ይቅርታ ታደርጊ ዘንድ እለምንሻለሁ" በሐዋርያትም ልመና እጆቹ ተመልሰው እንደቀድሞው ደኅነኞች ሆኑ።
ጥር ፳ /20/በዚች ዕለት ወንጌልን ይሰብኩ ዘንድ በሽተኞችንም ይፈውሱ ዘንድ ጌታችን መርጦ ከላካቸው ከሰብዓ ሁለቱ አርድእት አንዱ የከበረ ሐዋርያ አብሮኮሮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ በጽርሐ ጽዮን ከሐዋርያት ጋር ሁኖ ሳለ የአጽናኝ መንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተሞላ። እርሱንም ሐዋርያት መርጠውት ከሰባቱ ዲያቆናት ጋር የተቆጠረ ሆነ እነርሱ መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸው ዕውቀትም ያላቸው እንደሆኑ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ስለርሳቸው ምስክር ሆነ። ከዚህም በኋላ ለወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙሩ ሆነ ከእርሱም ጋር ወደ ብዙ አገሮች ሔደ በቢታንያ አገር በኒቆምድያ ከተማ ላይ በአንብሮተ እድ ኤጲስቆጶስነት ሾመው። እርሱም የክብር ባለቤት የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት አስተማረ ከዮናናውያንም ብዙዎችን መልሶ ወደ ቀናች ሃይማኖት አስገባቸው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው የወንጌልንም ትእዛዞች እንዲጠብቁ አስተማራቸው ቤተ ክርስቲያንንም ሠርቶ ቀሳውስትን ዲያቆናትን ሾመላቸው። ከዚህም በኋላ ያቺን አገር ወደሚከቧት አገሮች ወጣ በውስጣቸውም የከበረ ወንጌልን ሰበከ ብዙዎችንም ከስሕተት መለሳቸው አይሁድንም የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ነገር ግን ብዙ መከራና ስደት ደርሶበታል ስለ ክርስቶስ ስም ተጋድሎውንም ሲፈጽም ጌታችንንም አገልግሎ በመልካም ሽምግልና አረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ሐዋርያ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አሜን"። ❤
❤ #ጥር ፲፰ (18) ቀን።
❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጃንደረባ_በ34 ዓ.ም #ሐዋርያው_ቅዱስ_ፊሊጶስ_ላተጠመቀ ለመጀመሪያው ለአፍሪካ ሐዋርያ ለሆነ ለሐዋርያች #ለቅዱስ_አቤላክ (ባኮስ) ከሞት ለተሰወረበት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #የመጀመሪያው_የአፍሪካ_ሐዋርያ_ቅዱስ_አቤላክ (ባኮስ)፡- ይኽም ጃንደረባ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ንግሥት የሆነችው የህንደኬ የገንዘቧ ሁሉ ኃላፊና አዛዥ የነበረ ነው፡፡ ከአባቱ እብነ መላክ ከእናቱ ስሂነ ሕይወት ታኅሣሥ29 ቀን ተወለደ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ለበዓለ ፋሲካ በቤተ መቅደስ ይሰግዱ እንደነበረው ሁሉ ይኽም ጃንደረባ ከ4ሺህ ማይልስ በላይ ተጉዞ ኢየሩሳሌምን ተሳልሞ በመለስ ላይ ነበረ፡፡
❤ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ በተለይም ስለ ጌታችን መከራ መስቀል በዝርዝር የሚናገረውን ክፍል 53ኛውን ምዕራፍ ያነብ ነበር ነገር ግን ጃንደረባው ስለማን እንደሚናገር አልገባውም ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር በአካባቢው ወንጌልን ይሰብክ የነበረውን ሐዋርያውን ቅዱስ ፊሊጶስን ላከለት፡፡ እርሱም ጃንደረባው ያነበው የነበረውን መጽሐፍ ተረጎመለት፣ የከበረች ወንጌልን ሰበከለት፣ በመጨረሻም አጠመቀው፡፡ ሐዋርያው ባጠመቀውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በጃንደረባው ላይ ወረደ፡፡ ሐዋ 8፡26-40፡፡
❤ ይህን ለእኛ ለኢትዮጵያውን እጅግ የሚያኮራን ታሪካችን ነው፡፡ ዛሬ በእጃችን ላይ በመገኘው መጽሐፍ ውስጥ ባይኖርም በቆዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች ላይ ግን ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ ጃንደረባውን ባጠመቀውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በኢትዮጵያው ጃንደረባ ላይ እንደወረደ ተጽፏል፡፡ (v 39.cord.alexand. in bible reg. angl-aliqu plures codd.mss)
ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ ጃንደረባውን ያጠመቀበት ወንዝ "ቤተ ሳሮን" በተባለችውና እስከዛሬም ድረስ ከኢየሩሳሌም20 ማይልስ ርቀት በምትገኘው መንደር በኬብሮን መካከል ባለው ኮረብታ ሥር የሚመነጭ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን የታሪክ ጸሐፊ የሆነው ሊቁ ቅዱስ ጀሮም ጃንደረባውን "የኢትዮጵያውያን ሐዋርያ" በማለት ይጠራዋል፡፡ በሰፊው ለኢትዮጵያውያን ወንጌልን የሰበከ እርሱ ነውና፡፡
❤ ጌታችን የመረጣቸው የከበሩ ሐዋርያት እንኳን ወንጌልን በዓለም ለመስበክ ገና ከኢየሩሳሌም ባልወጡበት ወቅት በ34ዓ.ም ነው። ቅድስት አገራችን ኢትዮጵያ በክርስቶስ አምና ወንጌልን የተቀበለችው፡፡ በምድሪቱም ላይ ወንጌል መነገር የጀመረው ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ሐዋርያው ባኮስ (አቤላክ) ከኢየሩሳሌም ወንጌልን ተምሮና ተጠምቆ ወደ አክሱም እንደተመለሰ በመጀመሪያ ያጠመቀ ንግሥቲቷ ሕንደኬን ነው፡፡ ከእርሷም በኋላ መኳንንቱና መሳፍንቱ ሁሉ አምነው በባኮ እጅ ተጠመቁ ይኸውም በ34 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚህም በኋላ ባኮስ እስከ ኑብያ ድረስ ሄዶ ወንጌልን ሰብኮ ብዙዎችን አሳምኖ አጥምቋል፡፡ በዚህም ጊዜ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በባኮስ እየተሰጠ የነበረውን የወንጌል ብርሃን የበለጠ እንዲበራ አድርጓል፡፡ ከጃንደረባውም ጋር ሆነው በብዙ ቦታዎች አብረው ወንጌልን ሰብከው አምልኮተ ጣዖትን አጥፍተዋል፡፡
❤ ከዚህም በኋላ ባኮስ ወደ የመን በመሄድ በዚያም ክርስትናን በማስተማር ብዙዎችን አሳምኖ ካጠመቀ በኋላ ወደ ፐርሺያ ከዚያም ወደ ሕንድ፡ በመሄድ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሟል፡፡ በመጨረሻም ጥንት ታፕሮባና (taprobana)፡ ዛሬ ሲሎን በምትባለው ደሴት ወንጌልን በማስተማር ላይ እያለ በሰማዕትነት እንዳረፈ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ (lives of the most eminent fathers of the church, page 87) በሌላም በኩል ሐዋርያው ባኮስ (አቤላክ) ከመጠመቁ በፊት 35ዓመት ከተጠመቀ በኋላ ደግሞ 41 ዓመት ኖሮ በኢየሩሳሌምም 3ዓመት ተቀምጦ ወንጌልን ዞሮ ካስተማረ በኋላ በመጨረሻ በ79 ዓመቱ ጥር 18 ቀን በሰሜን ተራራዎች ላይ ቅዱስ ያሬድ በተሰወረበት ቦታ እንደተሰወረ ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ ጽፈዋል፡፡ ምንጭ፦መዝገበ ቅዱሳንና ቅዱሳት በዓላት።
