ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ
Ir al canal en Telegram
ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።
Mostrar más601
Suscriptores
-124 horas
-97 días
-1930 días
Archivo de publicaciones
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
✍️"የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል ከመከራም ሥጋት ያርፋል"
📖ምሳ 1፥33
#ስንክሳር
ዘሰኔ #አስራ ሁለት (፲፪)
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
✍️"የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል ከመከራም ሥጋት ያርፋል"
📖ምሳ 1፥33
#ስንክሳር
ዘሰኔ #አስራ አንድ (፲፩)
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ሰኔ ፱ (9) ቀን።
❤ እንኳን ልበ አምላክ የተባለውን ታላቁን ንጉሥ መዝሙረኛው #ቅዱስ_ዳዊት_ቀብቶ_ላነገሰው ለታላቁ #ነቢይ_ለቅዱስ_ሳሙኤል_ለዕረፍቱ_መታሰቢያ በዐልና #ለቅዱስ_ሉክያኖስ ከሌሎች #አራት_ሰማዕታት ጋር ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡት፦ #ከቅዱሳን_ከዮሐንስና #ከጳጳስ_አርልክሳ_ከዕረፍታቸው_መታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
+ + +
❤ #ነቢዩ_ቅዱስ_ሳሙኤል፦ የዚህ ቅዱስ አባቱ ሕልቃና ይባላል የእናቱም ስሟ ሐና ነው እርሱም ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ወገን ናቸው ሐናም መካን ነበረች ክብር ይግባውና ወደ እግዚአብሔር እያለቀሰች አዘውትራ ስለ ማለች ይህን የተባረከ ልጅ ሰጣት በቤቷም ሦስት ዓመት አሳደገችው።
❤ ከዚህም በኋላ ገና ስትፀንሰው እንደተሳለች ወደ እግዚአብሔር መቅደስ አቀረበችው ካህኑ ኤሊንም በመላላክ የሚያገለግለው ሆነ። የካህኑ ልጆች ግን ክፉዎች ነበሩ እግዚአብሔርንም አይፈሩም ነበር በቅዱስ መሥዋዕቱም ላይ በደሉ። ይህ ሕፃን ሳሙኤል ግን በኤሊ ፊት ለእግዚአብሔር ሲያገለግል ኖረ በነዚያ ወራቶችም ቃለ እግዚአብሔር ውድ ነበር የሚታይ ራእይም አልነበረም።
❤ ከዚህም በኋላ በአንዲት ሌሊት እንዲህ ሆነ ኤሊ በመኝታው ተኝቶ ሳለ ዐይኖቹንም መፍዘዝ ጀምረው ነበር ማየትም አይችልም ነበር። የእግዚአብሔርንም መብራት አብርቶ ለማሳደር ገና አላዘጋጁም ነበር ሳሙኤል ግን በቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ማደሪያ ታቦት አጠገብ ተኝቶ ነበር። እግዚአብሔርም "ሳሙኤል ሳሙኤል ሳሙኤል" ብሎ ጠራው እነሆ እኔ አለሁ አለ። ወደ ኤሊም ፈጥኖ ሔደ "ስለጠራኸኝ እነሆ እኔ መጣሁ" አለው። ኤሊም "አልጠራሁህም ተመልሰህ ተኛ" አለው ሒዶም ተኛ። እግዚአብሔርም ዳግመኛ "ሳሙኤል ሳሙኤል ሳሙኤል" ብሎ ጠራው ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ ኤሊ ሔደ ስለ ጠራኸኝ እነሆ መጣሁ" አለው ኤሊም "አልጠራሁህም ተመልሰህ ተኛ" አለው።
❤ ሳሙኤልም ከዚህ አስቀድሞ እግዚአብሔርን በራእይ ገና አላወቀውም ነበር ቃለ እግዚአብሔርም አልተገለጠለትም ነበር። ዳግመኛም እግዚአብሔር ሳሙኤልን ሦስት ጊዜ ጠራው ተነሥቶም ወደ ኤሊ ሔደ "ስለጠራኸኝ እነሆ መጣሁ" አለው ኤሊም ያንን ልጅ እግዚአብሔር እንደጠራው አሰበ። "ልጄ ተመልሰህ ተኛ የሚጠራህ ካለ እኔ ባሪያህ እሰማለሁና ጌታዬ ተናገር በለው" አለው ሳሙኤልም ሒዶ በመኝታው ተኛ። እግዚአብሔር መጥቶ እንደ መጀመሪያው በፊቱ ቁሞ ጠራው። ሳሙኤልም "እኔ ባሪያህ እሰማለሁና ጌታዬ በል ተናገር" አለው እግዚአብሔርም ሳሙኤል "የሰማው ሁሉ ሁለቱን ጆሮዎቹን ይይዝ ዘንድ እንሆ እኔ በእስራኤል ላይ የተናገርሁት ቃሌን አደርጋለሁ። በዚያችም ቀን በኤሊና በወገኑ ላይ የተናገርኹትን ሁሉ አጸናለሁ እጀምራለሁ እፈጽማለሁም። ልጆቹ እግዚአብሔርን ቃል አቃልለዋልና እርሱም አልገሠጻቸውምና በልጆቹ ኃጢአት እኔ ወገኑን በዘላለም እንደ ምበቀለው ነገርሁት። ስለዚህ ነገር በዕጣንም ቢሆን በመሥዋዕትም በመሆን የኤሊ የወገኑ ኃጢአት እስከ ዘላለሙ ድረስ እንዳይሠረይ ራሴ እንዲህ ብሎ ማልሁ"። በኤሊ ወገኖችና ልጆች ላይ እግዚአብሔር የተናገረው ሁሉ ተፈጸመ።
❤ ከዚህም በኋላ የቂስ ልጅ ሳኦልን ቀብቶ ለእስራኤል ልጆች ያነግሠው ዘንድ እግዚአብሔር ሳሙኤልን አዘዘው እንዲአነግሥላቸው ለምነዋልና። ሳኦልም የልዑል ትዕዛዝ በተላለፈ ጊዜ ዳግመኛ ለእስራኤል ንጉሥ ሊሆን የዕሴይ ልጅ ቅዱስ ዳዊትን ይቀባው ዘንድ ይህን ነቢይ ሳሙኤልን ዳግመኛ አዘዘው።
❤ ይህም ነቢይ ሳሙኤል በሕይወት በኖረበት ዘመን ሁሉ እስራኤልን አስተዳደራቸው። ከዚህም በኋላ ሰኔ 9 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በነቢዩ ቅዱስ ሳሙኤል ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
+ + +
❤ #ቅዱስ_ሉክያኖስና_አራቱ_ሰማዕታት፦ ይህም ቅዱስ አስቀድሞ የጣዖት ካህን ነበር የሰማዕታትንም መከራቸውን በእሳት ሲአቃጥሏቸውና ሕዋሳታቸውን ሲቆራርጧቸው ሲሰቅሏቸው ከእሳት ምድጃ ውስጥም ሲጥሏቸው ምንም ምን ጉዳት እንዳልደረሰባቸው በአየ ጊዜ ከዚህ ሥራ የተነሣ አደነቀ ክብር ይግባውና በጌታችን አመነ ያገለግላቸው የነበሩ ጣዖታት ከእሳት ቢጥሏቸው ፈጥነው ይቃጠላሉ እንጂ ይህን ሥራ ሊሠሩ እንደማይችሉ ተረድቷልና። ዳግመኛም እንዲህ አለ "ይህን ድንቅ ሥራ የሚሠራ አምላክስ በእውነት እርሱ አምላክ ነው"።
❤ ከዚህ በኋላም በንጉሥ ፊት "እኔ ክርስቲያን ነኝ ክብር ይግባውና በክርስቶስ አምናለሁ" ብሎ በግልጥ ጮኾ ተናገረ። ንጉሡም ወደርሱ አቅርቦ ጣዖት ማምለክን እንዳይተው መከረው ወደ አምልኮ ጣዖት ይመለስ እንደሆነ ብሎ ብዙ ቃል ኪዳኖችን ገባለት። እርሱም ግን አልሰማውም ሥቃዩንም አልፈራም ከዚህም በኋላ ንጉሡ ጽኑዕ ሥቃይን ሊአሠቃየው ጀመረ ዘቅዝቀው እንዲሰቅሉት መንጋጋውንም በደንጊያ አሰንዲሰብሩት ታላቅ ግርፋትንም እንዲገርፉት አዘዘ።
❤ ከዚህም በኋላም አራት ክርስቲያን እሥረኞች ቀረቡና ከእርሱ ጋራ አቆሟቸው ንጉሡም "ለአማልክት ዕጣን ዕጠኑ ይህ ካልሆነ ግን ታላቅ ሥቃይን አሠቃያችኋለሁ" አላቸው። እነርሱም ለስሕተቱ አልታዘዙለትም በላያቸውም ተቆጥቶ በእሳት ምድጃ ውስጥ ጨመራቸው ያንጊዜ ዝናብ ዘነበ እሳቱንም አጠፋው።
❤ ቅዱስ ሉክዮስን ግን "እንደ አምላክህ እሰቅልሃለሁ" ብሎ በዕንጨት መስቀል ላይ እንዲሰቅሉት አዘዘ በረጃጅም ችንካሮችም ሥጋውን ሁሉ ቸነከሩት ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ። እንዚያን አራቱን ሰዎችም ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጡአቸው የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሉክያኖስና በከበሩ አራት ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ቴድረሰን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሰኔ 9 ስንክሳር።
+ + +
❤ "#ሰላም_ለሉክያኖስ_ዘአድምዐ_ተወድሶ። ምስለ ፬ቱ ዕደው ሥቃያተ ስምዕ በተዓግሦ። ሶበ ለአማልክት ኢሦዐ መሥዋዕተ ልዑል አስተኀይሶ። እለ ቀነውዎ እስከ ይመጡ ነፍሶ። እስመ በአዕባን ቀጥቀጡ መንከሶ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሰኔ_9።
+ + +
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወሳሙኤልኒ ምስለ እለ ይጼውዑ ስሙ። ይጼውዕዎ ለእግዚአብሔር ውእቱኒ ይሰጠዎሙ። ወይትናገሮሙ በዐምደ ደመና"። መዝ 98፥6-7። የሚበቡት መልዕክታት ዕብ 11፥32-ፍ.ም፣ 2ኛ ጴጥ 3፥1-7 እና የሐዋ ሥራ 13፥16-24። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 10፥32-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የነቢዩ ቅዱስ ሳሙኤል የዕረፍት በዓልና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ አባታችንም ካዐረፉ በኋላ በደብረ ምዕዋን ቅድስት ሥላሴ ደብረ ናዝሬት ከአባታቸው ከአቡነ ብፁዐ ኣምላክ ጋር ተቀበሩ። የአቡነ ብፁዕ አምላክ እና የአቡነ በኩረ ድንግል ገዳም ደቀ መሐሪ ጎደይቲ አካባቢ ይኛል። እነርሰም ካረፉ በኋላ እየተገለጡ በጠበላቸው አጋንንት ያደሩባቸውን ሰዎች ሁለ እየፈወሱ፣ በመቃብራቸው አፈር ሙት እያስነሡ የተለያዩ ድንቅ ድንቅ ተኣምራት ሲሠሩ ታይተዋል። የሠሯቸውም ተዓምራት ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደለም። ከአባታችን ከአቡነ በኩረ ድንግል እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን። ምንጭ፦ በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን።
❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ሰኔ ፱ (9) ቀን።
❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ_ኤርትራ_አገር የሚገኘው #ደብረ_ምዕዋን ለመሰረቱ ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ብፁዕ_አምላክ_ደቀ_መዝሙር ለሆኑት #ለአቡነ_በኵረ_ድንግል_ዘደብረ_ምዕዋን_ለዕረፍታቸው_በዐል በሰላም አደረሰን።
+ + +
❤ #አቡነ_በኵረ_ድንግል፦ የአቡነ ብፁዐ አምላክ ረድእ የነበሩ ሲሆን እርሳቸውም ካረፉ በኋላ ተመርጠው በደብረ ምዕዋን ገዳም ላይ አበ ምኔት ሆነው ተሾመው ብዙ አገልግለዋል" ጻድቁ በምድረ ኤርትራ በምንኩስና እና በብሕትውና ጸንተው ለትልቅ ሰማያዊ ክብር የበቁ ታላቅ ጻድቅ ናቸው። በዓለ ዕረፍታቸው ሰኔ 9 ነው።
❤ የአቡነ በኵረ ድንግል፦ አባታቸው ማርቆስ እናታቸው እግዚእ ክብራ የሚባሉ ሲሆን ጻድቁ ገና በእናታቸው ማሕፀን ሳሉ ብዙ ተኣምራት ይሠሩ ነበር" ሲወለዱም የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ከነልጇ (ምስለ ፍቁር ወልዳ) በልባቸው ላይ ተሥላ ተገኝታለች" በማሕፃን ሳሉ ተመርጠዋልና በአኵሱም ሲወለዱ እንደሌሎቹ ቅዱሳን አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ›› ብለው ስመ ሥላሴን ጠርተው አመሰገኑ። በዚያ የነበሩና ይህንን የተመለከቱ ሰዎችም ባዩትና በሰሙት ነገር እጅግ ተደነቁ።
❤ በ40ኛው ቀናቸውም በጥምቀት የሥላሴን ልጅነት እንዲቀበሉ ወላጆቻቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዷቸው በወቅቱ የነበሩት ጳጳሱ አቡነ ሰላማ ሕፃኑ ትልቅ መነኵሴና የአቡነ ብፁዐ አምላክ ደቀ መዝሙር እንደሚሆን ተገልጾላቸው ትንቢት ተናገሩ። ዳግመኛም ጳጳሱ ቅብዓ ሜሮን ሊቀቡት ሲሉ ሥዕለ ማርያም ከነልጇ በሕፃኑ ደረት ላይ ተሥላ አይተዋት ደነገጡ ወዲያውም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ተገልጸ ሳይፈሩ ሥርዓተ ጥምቀቱን እንዲፈጽሙ አዘዛቸው ዳግመኛም ..… "ስሙን በኵረ ድንግል በለው ትርጉሙም በልቡ ላይ ያየኸው ሥዕል ነው" ብሎ ነገራቸው" ሕፃኑም ከተጠመቀ በኋላ እመቤታችን ከነልጇ ጋር ተገልጻ በትእምርተ መስቀል ባረከችው ያ ትእምርተ መስቀልም ዳግመኛ በሰውነታቸው ላይ ተሳለ።
❤ ከዚህም በኋላ አቡነ በኵረ ድንግል አድገው ቤተሰቦቻቸውን እየረዱ በእረኝነት እያገለገሉ በመልካም አስተዳደግ አደጉ" ዕድሜአቸው ለትምህርት እንደደረሰ ወላጆቻቸው ለንቡረ እድ ዮፍታሔ ሰጧቸውና አስተማሯቸው። ከቋንቋዎች ግእዝ፣ ዐረብ ዕብራይስጥ፣ ጽርዕ እና ሮማይስጥ ተማሩ፤ ብሉይንና ሐዲስን እንዲሁም ቅዱሳት መጻሕፍትን ሁሉ አጠናቀው ተማሩ። ቅኔ ድጓ ጾመ ድጓ እና የቅዱስ ያሬድን ዜማዎችም በሚገባ አጠኑ። ትምህርታቸውንም ከጨረሱ በኋላ መምህራቸው ወደ ሊቀ ጳጳስ ወሰዱአቸው በልባቸው ያለች የእመቤታችን ሥዕልም ለጳጳሱ ተገልጣ "ይህ የምወደው ልጄ ስለሆነ በልቡ ተሳልሁ ስለዚህ ዲቁና ቅስና ስጠው፣ ኤጲስ ቆጵስነትም ሹመው" አለቻቸው። ጳጳሱም ባዩትና በሰሙት ነገር ተደንቀው ተነሥተው እንደተባሉት በሦስቱ መዕረግ ሾሟቸው። ከሹመታቸውም በኋላ በአከባቢው ያሉ ሰዎች አቡነ በኩረ ድንግልን ብርሃን ለብሰው ስላዩዋቸው በጣም ተደነቁ።
❤ ከዚህም በኋላ አቡነ በኵረ ድንግል ለአቅመ አዳም ሲደርሱ ወላጆቻቸው በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ሚስት ሲያጩላቸው አቡነ በረ ድንግል ግን "እኔስ ፍላጎቴ በድንግልና መኖር እንጂ ማግባት አይደለም" ብለው ሌሊት ተነሥተው ከቤታቸው ጠፍተው ወደ እግዚአብሔር ቤት ሔደው "አቤቱ ጌታ ሆይ! ከዘለዓለም እሳት ከዲያብሎስ እሥራት ሰውረኝ መጥፎውን ሐሳብ ከእኔ አርቀህ ፍቃድህን እፈጽም ዘንድ እርዳኝ የእመቤታችን ሥዕል ከነልጇ በልቤ አለና ወደ ጋብቻ ዓለም ለመግባት ኅሊናዬ አልፈቀደልኝም ስለዚህ ፍቃድህ ቢሆንልኝ እንደ መላእክት ንጹሕ ሁኜ እንድኖር እለምንሃለሁ፣ አንተ ድኃና ምስኪን የማትንቅ አምላክ መሆንህን ዐውቃለሁና…" እያሉ ጸለዩ። እየጸለዩ ሳለ ክብርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤል አስከትላ ተገለጠችላቸውና "ልጄ ሆይ! ጸሎትህ ተሰምቷልና ወደ ደብረ ዳሞ ወደ አባትህ ሒድ፣ እንዲሁም ደግሞ ወደ ደብረ ናዝሬት ወደ ብፁዐ አምላክ ዘንድ ሒድ የብዙዎች አባትም ትሆናለህ" በማላት ከባረከቻቸው በኋላ ተሰወረች።
❤ ከዚህም በኋላ ጻድቁ መጋቢት 9 ቀን በቦታቸው ሆነው በተመስጦ እየጸለዩ ሳሉ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል በደመና ተሸክሞ ወስዶ ደብረ ዳሞ የቅዱሳን ማረፍያ ቦታ አደረሳቸው። እመቤታችን እንደነገረቻቸው በገዳሙ አስቀድማ እንደነገረቻቸው ለረጅም ዓመታት በትሕትና ካገለገሉ በኋላ ወደ አባታቸው ወደ አቡነ ብፁዐ አምላክ ከረጅም ጉዞ በኋላ መጡ። አቡነ ብፁዐ አምላክም አስቀድመው መምጣታቸውን ያውቁ ነበርና አሁን ሲያገኗቸው እግዚአብሔርን አመስግነው በታላቅ ደስታና ትሕትና ተቀበሏቸው።
❤ በገዳማቸውም በትሕትና እያገለገለ ከቆዩ በኋላ አንድ ቀን አቡነ ብፁዐ አምላክ "ዛሬ በእጅህ ቍርባን እንድንቀበል አንተ ቀድስ" አሏቸው። አቡነ በኩረ ድንግልም ቅዳሴ ገብተው አሐዱ አብ ቅዱስ… ብለው ሲጀምሩ ከመሬት ወደላይ 5 ሜትር ያህል ከፍ ብለው ታዩ፤ ይኽንንም አይተው አቡነ ብፁዐ አምላክ በጣም ተደንቀው እግዚአብሔርን አመሰገኑ። አቡነ በኵረ ድንግልም በእንዲህ ያለ ሕይወት አባታቸውን አቡነ ብፁዐ አምላክን ካገለገሉ በኋላ አቡነ ብፁዐ አምላክ ታኅሣሥ 9 ቀን የገዳማት መነኰሳትን ሰብስበው "ዛሬ ለሁላችሁ መሪ የሚሆን ትሑትና ደግ መምህር እሰጣችኋለሁ ከእኔ በታች እርሳቸውን ስሟቸው ታዘዙአቸውም" ብለው ነገሯቸው።
❤ ዳግመኛም አባታችን አቡነ ብፁዐ አምላክ የዕረፍታቸው ጊዜ ሲደርስ የገዳሙን መነኰሳት ሰብስበው ከእርሳቸው በኋላ አባት እንዲሆኗቸው አቡነ በኵረ ድንግልን እጃቸውን ጭነው ባርከው ሾሟቸው። ከዚህም በኋላ አቡነ በኵረ ድንግል በጾም በጸሎት በስግደት ለገዳሙና በገዳሙ ለሚኖሩ መነኰሳት ሁሉ በትሕትና እያገለገሉ በታላቅ ተጋድሎ ኖሩ። የገዳሙ መነኰሳትም በጣም ወደዷቸው። ተጋድሏቸውንና አገልግሎታቸውንም በፈጸሙ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአቡነ በኵረ ድንግል እንዲህ የሚል ቃልኪዳን ገባላቸው።
❤ "በስምህ ዝክር የሚዘክር ስምህን የሚጠራ በዕረፍትህ ቀን የታመሙትንና የታሰሩትን የጎበኘ በስምህ የተራበ ያበላ ያጠጣ የታረዘ ያለበሰ የልጁን ስም በስምህ የጠራ ይህን ሁሉ ያደረገውን እምረዋለሁ ክፉም አይነካውም፤ በደብረ ምዕዋን በአባትህ በብፁዐ አምላክ ቦታ በአንተም ቦታ የተቀበረ በቦታው ቅዱስ ቍርባን የተቀበለ ክፉ አያገኘውም፣ እምረዋለሁ፣ ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌምም አስገበዋለሁ ብሔረ ሕያዋንና ብሔረ ብፁዓንንም አወርሰዋለሁ…" የሚሉ ታላላቅ የምሕረት ኪዳናትን ከእግዚአብሔር ከተቀበሉ በኋላ ሰኔ 9 ቀን ትንሽ የራስ ምታት ሕመም ጀመራቸው። የገዳሙ መነኰሳትና ሌሎቹም ታላላቅ ቅዱሳን አባቶች እንደእነ አቡነ ዮሐንስ ዘደብረ ቢዘን ያሉት እንደየ ደረጃቸው ከያሉበት ተሰበሰቡ። በዚህም ጊዜ ሥሉስ ቅዱስ ተገልጸውላቸው ድጋሚ ቃልኪዳን ገብተውላቸው አረጋጓቸውና ቅድስት ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች።
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
✍️"የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል ከመከራም ሥጋት ያርፋል"
📖ምሳ 1፥33
#ስንክሳር
ዘሰኔ #ዘጠኝ (፱)
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
✍️"የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል ከመከራም ሥጋት ያርፋል"
📖ምሳ 1፥33
#ስንክሳር
ዘሰኔ #ስምንት (፰)
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ሰኔ ፰ (8) ቀን።
❤ እንኳን #አምላክን_ለወለደች_በሁለት_ወገን #ድንግል_ለሆነች_ለእመቤታችን_ለቅድስት_ድንግል ማርያም ለታወቀችው በውኃ ምንጭ ዘንድ ላለች #ለቤተ_ክርስቲያንዋ_ለቅዳሴ_ቤት ከእመቤታችን #ከሠላሳ_ሦስቱ_በዓል_አንዱ_ለሆነ_በዐል (እርሱም #ጌታችን ከእርሷ ጋር ወደ ግብጽ አገር ተሰዶ ሲመለስ ያፈለቀው የተባረከ መታጠቢያ ውሃ (ጠበል) ነው፣ ለርማኖስ እናት #ለቅድስት_ትምዳ_ለዕረፍቷ መታሰቢያ በዐል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡት፦ ከአንድ ሽህ ሁለት ሰማዕታት ከመታሰቢያቸው፣ ከቅዱሳን ከአትካሮንና ከአውሎጊስ ከበዓላቸው መታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
+ + +
❤በዚች ቀን #አምላክን_የወለደች_በሁለት_ወገን #ድንግል_የሆነች_የእመቤታችን_የቅድስት_ድንግል #ማርያም የታወቀችው በውኃ ምንጭ ዘንድ ያለች የቤተ #ክርስቲያንዋ_ለቅዳሴ_ነው። እርሱም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሷ ጋር ወደ ግብጽ አገር ተሰዶ ሲመለስ ያፈለቀው የተባረከ መታጠቢያ ነው።
❤ ይህም እንዲህ ነው ለጻድቁ ዮሴፍ የእግዚአብሔር መልአክ በሕልም ተገልጾለት "ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ አገር ሒድ" አለው። ዮሴፍም ነቅቶ ተነሣ ክብር ይግባውና ሕፃኑን ጌታችንን እናቱንና እኅቷ ሰሎሜን ይዞ ወደ ግብጽ አገር ሔዱ በዚያም በውስጧ ባሉ በብዙ አገሮች እየዞሩ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ኖሩ።
❤ ኄሮድስም ከሞተ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ ሁለተኛ ተገለጠለት "ወደ እስራኤል አገር ሕፃኑንና እናቱን ይዞ እንዲመለስ" አዘዘው። በሚመለሱም ጊዜ ወደ መዓልቃ ደረሱ ከዚያም ወደ መጣርያ አገር ደረሱ ይቺም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውኃ ያፈለቀባትና የመታጠቢያ ቦታ የሆነች ናት እርሷም እስከ ዛሬ አለች ሰዎችም ከአገሩ ሁሉ ከየነገዱ ሁሉ መጥተው አምላክን ወደ ወለደችና በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ወደ ጸናች ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም ይለምናሉ ከተባረከውም የውኃ ምንጭ ታጥበው ከደዌያቸው ሁሉ ይድናሉ በዛሬዪቱ ሰኔ 8 ቀን ከከበረች ቤተ ክርስቲያንም ይባረካሉ።
❤ እርሷን እመቤታችንን ለመረጣትና ለወደዳት በሥጋም እናቱ ላደረጋት ስለርሷም ዘመድ ለሆነንና ወደርሱ ላቀረበን ወራሾቹም ላደረገን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሰኔ 8 ስንክሳር።
+ + +
❤ "ሰላም ዕብል ለቅዳሴ ቤትኪ ሕንፅት። ኀበ አንቅዐ ወሌድኪ ማየ በረከት። ማርያም ድንግል በስምከመ በቊዔት። እስመ ይትወሀብ ለዘጸለየ በኵሉ ዕለት። ሠናይ ሀብት ወፍጹም ፍት"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሰኔ_8።
+ + +
❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "እፎ እስፋሕ ለከ ሥጋየ። በምድረ በድው ኀበ አልቦ ዕፅ ወማይ። ከመዝ በመቅደስከ አስተርአይኩከ"። መዝ62፥1-2"። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ4፥14-17።
+ + +
❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ወአስተዮሙ ከመ ዘእምቀላይ ብዙኅ። ወአውኃዘ ማየ ከመ ዘእምአፍላግ። ወአውጽአ ማየ እምዕብን"። መዝ 77፥15-16። የሚነበቡት መልዕክታት ኤፌ 2፥13-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 1፥10-13 እና የሐዋ ሥራ 7፥44-51። የሚነበበው ወንጌልን ዮሐ 4፥1-15። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓልና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
✍️"የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል ከመከራም ሥጋት ያርፋል"
📖ምሳ 1፥33
#ስንክሳር
ዘሰኔ #ሰባት (፯)
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ሰኔ ፯ (7) ቀን።
❤ እንኳን #አምላክን_ለወለደች_ለእመቤታችን #ለድንግል_ማርያም_ቤተ ክርስቲያን_ለተከፈተበትና ለከበረችበት፣ ቀሊን ከምትባል አገር ቅዱስና ቡሩክ ድል አድራጊም ለሆነ #ለአባ_አበስኪሮን_ሰማዕትነት ለተቀበሉበት #ለዕረፍታቸው_በዐል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚህ ቀን ከሚታሰቡ፦ መኰንን አርማንዮስ ካሠቃያቸው #ከአስራ_ስድስት_ሺህ_ሰማዕታት ከዕረፍታቸው መታሰቢያና ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
+ + + #በዚች_ዕለት_አምላክን_የወለደች_የእመቤታችን_የድንግል_ማርያም_ቤተ_ክርስቲያን_የተከፈተበትና_የከበረችበት ነው። እርሷም ዌላ በሚባል አደባባይ ያለች ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ተዘግታ የኖረች ነበረች። ይኸውም በአንድ ሽህ ሃያ ዓመተ ሰማዕታት ነው። ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ሰው ለሆነ ሕይወትና መድኃኒት አድርጎ እርሷን ለሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።
+ + +
❤ #አባ_አበስኪሮስ፦ ይህም ቅዱስ ከእንዴናው ገዥ ከአርያኖስ ጭፍራ ውስጥ ነበር የከሀዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ ስለ አምልኮ ጣዖት የሆነች ትእዛዝ በደረሰችው ጊዜ። ወዲያውኑ ይህ በሕዝብ መካከል ተነሥቶ ንጉሡን ረገመው ጣዖታቱንም ሰደበ ወታደር ስለ ሆነም ያሠቃየው ዘንድ ማንም አልደፈረም ነገር ግን በንጉሥ አዳራሽ ውስጥ አሠሩት።
❤ መኰነንኑም ወደ አገረ አስዩጥ በሔደ ጊዜ ወደ ንጉሥ ላከው ከእርሱም ጋራ ሌሎች ወልደፍዮስ፣ አርማንዮስ፣ አርኪያስ፣ ጴጥሮስና ቀራንዮስ የተባሉ ነበሩ እሊህም ክብር ይግባውና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደማቸውን ሊአፈሱ ከአባ አበስኪሮስ ጋር ተስማሙ። በንጉሡም ፊት በቆሙ ጊዜ በጌታችን ታመኑ ንጉሡም ትጥቃቸውን ይቆርጡ ዘንድ በየአይነቱ በሆነ ሥቃይም እንዲአሠቃዩአቸው አዘዘ ንጉሡ እንዳዘዘም አደረጉባቸው። ከእኒህ ከአምስቱ ግን ራሶቻቸውን የቆረጡአቸው አሉ የሰቀሉአቸውም አሉ እንዲህም ገድላቸውን ፈጽመው የሕይወት አክሊል ተቀበሉ።
❤ የከበረ አበስኪሮስን ግን ታላቅ ግርፋትን እንዲገርፉት አዘዘ ከዚያም በኋላ ከራሱ እስከ አንገቱ ቆዳውን እንዲገፉ በፈረስ ጅራትም አሥረው በከተማው ውስጥ እንዲጐትቱት አዘዘ። ይህንም ሁሉ አደረጉበት። ከዚህም በኋላ በብረት ምጣድ ውስጥ አድርገው በላዩ አፉን ዘግተው ተሸክመው ወስደው በውሽባ ቤት ማንደጃ ውስጥ ጨመሩት በሥቃዩም ውስጥ ሁሉ የእግዚአብሔር መልአክ ወደርሱ ይመጣና ያጽናናው ነበር ያስታግሠውም ነበር ያለ ምንም ጉዳት አድኖ በደኅና ያስነሣው ነበር።
❤ ከማሠቃየቱም በደከመ ጊዜ ከሥራየኞች ሁሉ የሚበልጥ በሥራዩም ወደ አየር ወጥቶ ከአጋንንት ጋራ የሚነጋገር ሥራየኛ አመጣለት። እርሱም የውሽባ ቤቱን ዘግተው ሽንት እንዲረጩበት አዘዘ እንዲሁም አደረጉ። እባብንም ይዞ በላዩ አሾከሾከና ለሁለት ክፍልም ሁኖ ተሠነጠቀ መርዙንና ሆድ ዕቃውን ወስዶ በብረት ወጭት አድርጎ አበሰላቸው በውሽባ ቤቱ ውስጥ ወደ አባ አበስኪሮን አቅርቦ ያንን መርዝ ይበላ ዘንድ ሰጠው ቅዱሱም በላ ግን ምንም ምን ጉዳት አልደረሰበትም። ያም መሠርይ "የመኳንንተ ጽልመት አለቃቸው ሆይ በዚህ ክርስቲያናዊ ላይ ኃይልህን አድርግ" ብሎ ጮኸ ምንም ምን ጥፋት ባልደረሰበት ጊዜ መሠርዩ አደነቀ። ቅዱስ አበስኪሮንም መሠርዩን "የሚራዳህ ሰይጣንህስ በክብር ባለበት በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል አንተን ይቀጣሃል" አለው። ወዲያውኑ ጥሎ የሚያንከባልለው ክፉ ሰይጣን ተጫነበት ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ታመነ ድረስ አሠቃየው። መኰንኑም የመሠርዩን ራስ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና በሰማዕትነት ሞተ። በቅዱስ አበስኪሮን ላይ ግን ቁጣና ብስጭትን በመጨመር ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው አባለ ዘሩንም እንዲቆርጡ አዘዘ እርሱ ግን በመከራው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግን ነበር። ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘና ሰኔ 7 ቀን ቆረጡት የድል አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
❤ ከቅዱስ አበስኪሮን ተአምራትም አንዱን እንነግራችኋለን በግብጽ ደቡብ በስሙ የታነፀች ቤተ ክርስቲያን ነበረች ካህናቷም ክፉ ሥራ የሚሠሩ ክፉዎች ነበሩ ቅዱስ አበስኪሮንም ከክፋታቸው ተመልሰው ንስሓ ቢገቡ ብሎ ጠበቃቸው። ባልተመለሱ ጊዜ ግን የንዳድ በሽታ አምጥቶ ሁሉም በአንዲት ጊዜ ሞተ።
❤ ከዚህም በኋላ ቅዱስ አበስኪሮን በፈረስ ተቀምጦ የላዕላይ ግብጽ የሆነች ብያሁ ወደምትባል አገር ደረሰ የአገር ሰዎችም በደጃቸው ተቀምጠው ሳይተኙ በጨረቃ ብርሃን እርስ በርሳቸው ያወሩ ነበር። የከበረ አበስኪሮንም ከፊታቸው ደርሶ "ሰላም ለእናንተ ይሁን" አላቸው በአዩትም ጊዜ የሰላምታውን አጸፋ እየመለሱ ተነሥተው ተቀበሉት ሁለተኛም "ያቺን የሚሻትን ምድር እያመለከታቸው ከምድራችሁ ጥቂት እንድትሰጡኝ እሻለሁ" አላቸው። እነርሱም "ጌታችን እንደወደድክ ይሁንልህ" አሉት መቶ የወርቅ ዲናርም ሰጥቷቸው ተሠወራቸው። እነርሱም ከዚህ ራእይ የተነሣ አደነቁ።
❤ ከተኙ በኋላም ቤተ ክርስቲያኒቱን አፍልሶ ከግብጽ ደቡብ ወደ ላይ ግብጽ ብያሁ ወደምትባል አገር በመቶ የወርቅ ዲናር ወደ ገዛት ምድር ከንዋየ ቅዱሳቷ ሁሉና ከዐፀዷ ጋር አምጥቶ በዚያ አቆማት። የአገር ሰዎችም በጥዋት ነቅተው ወደ ውጭ በወጡ ጊዜ ቤተ ክርስቲያቱን በደጃቸው አገኙዋት እጅግ ፈጽሞም አደነቁ ምስጉን እግዚአብሔርንም አመሰገኑት። ከዚያች ጊዜ ጀምሮ ድንቅ ተአምር የሚደረግባት ሆነ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ በአባ በአበስኪሮን ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሰኔ 7 ስንክሳር።
+ + +
❤ "#ሰላም_ዕብል_ለርኅወተ_ቤትኪ_ዮም። ከመ ኤልያስ አርኀወ ኆኅተ ዝናም። በስሱ አውራኅ ወበሠላስ ዓም። ማርያም ሥመሪ አርኅዎቶ ለሕሊናየ ሕቱም። ከመ ላዕሌሁ ይትከዐው ምስለ ጽድቅ ሰላም"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሰኔ 7።
+ + +
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ያበድሮን እግዚአብሔር ለአናቅጸ ጽዮን። እምኵሉ ተዓይኒሁ ለያዕቆብ። ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር"። መዝ 86፥2-3። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ቆሮ 6፥11-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 1፥6-10 እና የሐዋ ሥራ 12፥10-21። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 17፥14-22። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን ማርያም ቅዳሴ ነው፡፡ መልካም በዓል የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዐልና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ ሰኔ ፯ (7) ቀን።
❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ ለታላቁ አባት #አቡነ_ተክለ_ሃይማኖት_ከሾሟቸውና_በሀገራችን ለስብከተ ወንጌል ካሰማሯቸው #ከ47ቱ ቅዱሳን አንዱ ለሆኑት #ለአቡነ_ማቴዎስ_ዘእንደርታ_ለዕረፍታቸው መታሰቢያ በዐልና ለታላቁ አባት #ለጻድቁ_ለሐዋርያም ለደራሲም ለመላእክት በዐል የሚቀደሰው ከ14_ቅዳሴ አንዱ የሆነ በስሙ የተሰየመው ቅዳሴ ለደረሰ ለተከራካሪ መምህርም #ለያዕቆብ_ዘሥሩግ_ለዕረፍት_በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
+ + +
❤ #አቡነ_ማቴዎስ፦ እኚህ ጻድቅ ትውልድ አገራቸው እንደርታ ሲሆን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሾሟቸውና በሀገራችን ለስብከተ ወንጌል ካሰማሯቸው ከ 47ቱ ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው። ጻድቁ መላ ሰውነታቸው እንደ እሳት ያቃጥል ነበር። ወንጌልን በመስበክና በተአምራታቸው ድውያንን እየፈወሱ ብዙ ያገለገሉ ታላቅ አባት ናቸው። መዝገበ ቅዱሳንና ቅዱሳን በዓላት ላይ።
+ + +
❤ #አቡነ_ያዕቆብ_ዘሥሩግ፦ አገሩ ሶርያ ሲሆን አባቱ ሊቀ ካህናት ነበር። በኤጲስ ቆጶስነት የተሾመባት አገር በጤግሮስና በኤፍራጥስ መካከል በምትገኝ ሥሩግ በምትባል አገር ስለሆነ ያዕቆብ ዘሥሩግ ተባለ። በ 3 ዓመቱ እናቱ ቤተ መቅደስ ስትወስደው መልአክ እጁን ይዞ በሊቀ ጳጳሱ እጅ እንዲቆርብ አድርጎታል። በዚህም ጊዜ ምሥጢራት ሁሉ ተገልጠውለታል። ገና በ 7 ዓመቱ ስለ ሦስት ነገሮች በእጅጉ ያለቅስ ነበር። "ነፍሴ ከሥጋዬ ተለይታ ስትወጣ ከጌታችን ጋር ስትገናኝና መጨረሻውን ፍርድ ስሰማ እነዚህን ሦስት ነገሮች በእጅጉ እፈራለሁ" እያለ ያለቅስ ነበር።
❤ በ 12 ዓመቱ ብሉይንና ሐዲስን አጠናቆ ተመምሮ ጨርሷል። ጸጋውን ዐውቀው 5 ቱ ታዋቂ ሊቃነ ጳጳሳት መጥተው እጅ ነስተውት አዲስ ድርሰት ድረስልን ቢሉት እርሱም በፍጹም ትሕትና "በእናንተ ፊት እንኳን አዲስ ድርሰት ልደርስ ቀርቶ የተደረሰውንም መናገር አልችልም"። አላቸው። እርሱ በነበረበት ዘመን በሮማው መናፍቅ ልዮን አማካኝነት ቤተ ክርስቲያን ለመጀመርያ ጊዜ ለሁለት የተከፈለችበት ጊዜ ነበርና እነ ዲዮስቆሮስ "የውሾች ጉባኤ" ከተባለው ከኬልቄዶን ጉባኤ ተለይተው ሃይማኖትን ሲያጸኑ ልዮንንም ማውገዛቸውን ያዕቆብ ሲሰማ በዲዮስቆሮስ ጽናት በእጅጉ ተደስቶ ደብዳቤ ጽፎ አመስግኖታል። እነ ልዮንን ግን አውግዞ እረግሟቸዋል። ልዮንም ተከታይ ባገኘ ብሎ "እኔን ምሰል" በማለት ለያዕቆብ ደብዳቤ ጻፈለት። ያዕቆብም "ሳጥናኤል ከመላእክት ጋር ምን አንድ አደረገው? አንተ ርኩስ ነህ፤ የዲዮስቆሮስን ጥርስ አስወልቀህ፣ ጢሞን አስነጭተህ፣ ሃይማኖትህን የቀየርህ ከሁለት ዓለም ስደተኛ ጋር አልተባበርም፣ ይልቅስ ንስሓ ግባ፣ ንስሓ ባትገባ ግን አንተ ዲያብሎስ ነህ ተከታዮችህም አጋንንት ናቸው። በማለት መልሱን ጽፎለታል። እምቢ ብሎ በክህደቱ ቢጸናበትም አውግዞ እረግሞ ንጽሕናውን ቅድስናው እንደ መላእክት ነው የተባለለት ያዕቆብ ዘሥሩግ ጻድቅም ሐዋርያም ደራሲም ተከራካሪ መምህርም ነው። ሦስት ድርሰቶች ያሉት ሲሆን በስሙ የተጠራው ቅዳሴም አለው። ዕረፍቱ ሰኔ 7 ቀን ነው። ከአባታችን ከአቡነ ያዕቆብ ዘሥሩግ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎቱም ይማረን።
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
✍️"የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል ከመከራም ሥጋት ያርፋል"
📖ምሳ 1፥33
#ስንክሳር
ዘሰኔ #ስድስት (፮)
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ውድ የፍኖተ-ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በሙሉ በነገው ዕለት ማለትም በ06/10/15 የሰንበት ትምህርት ቤታችን 11ኛ አመት የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ልደትሽ ልደታችን ነው በሚል መርሐ ግብር የማታ ጉባዬ አገልግሎት ሁላችንም የአዳጊና ወጣት ክፍል አባላት በሰዓቱ ተገኝተን በአንድነት እንድናገለግል በእግዚአብሔር ስም እናሳስባለን ላልሰሙ አባላትም መልዕክቱን በማስተላለፍ እንገኝ
ሰዓት ከ 11:00 ሰዓት ጀምሮ
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
✍️"የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል ከመከራም ሥጋት ያርፋል"
📖ምሳ 1፥33
#ስንክሳር
ዘሰኔ #አምስት (፭)
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
✍️"የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል ከመከራም ሥጋት ያርፋል"
📖ምሳ 1፥33
#ስንክሳር
ዘሰኔ #አራት (፬)
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።❤
❤ #ሰኔ ፪ (2) ቀን።
❤ እንኳን #የመጥምቀ_መለኮት_ለቅዱስ_ዮሐንስ ሥጋ ከቀናተኛው ከነቢዩ #ከቅዱስ_ኤልያስ ደቀ መዝሙር ከሆነው #ከነቢዩ_ከቅዱስ_ኤልሳዕ_ሥጋ ጋር በአንድነት ለተገኘ መታሰቢያ በዐል። በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚህ ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከቅዱሳን_ቆርሎስና_ከአክሌጥስ_ከመታሰቢያቸው ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
+ + +
❤ #የመጥምቁ_የቅዱስ_ዮሐንስና_የነቢዩ #ቅዱስ_ኤልያስ_ሥጋ_በአንድነት_መገኘት፦ ከሀዲው ንጉሥ ዑልያኖስ የጥጦስ ልጅ አስባስያኖስ ከአፈረሰው በኋላ በዘመኑ በኢየሩሳሌም የአይሁድ ምኵራባቸውን ሊሠራ በወደደ ጊዜ እርሱ በቅዱስ ወንጌል ደንጊያ በደንጊያ ላይ ተቀምጦ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም የተባለውን የእግዚአብሔር ቃል ሊሽር ፈልጎ መሥራት በጀመረ ጊዜ ሦስት ጊዜ ፈረሰበት። አይሁድም እንዲህ አሉት "የደጋግ ክርስቲያኖች ዐፅሞቻቸው በዚህ ቦታ ስለሚኖሩ ከዚህ ካላወጣሃቸውና ካላቃጠልካቸው በዚህ ቦታ ምኵራብ አይሠራም"።
❤ በዚያንም ጊዜ የቅዱሳንን ዐፅሞቻቸውን አውጥተው በእሳት እንዲአቃጥሉት አዘዘ በአፈለሱም ጊዜ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስና የነቢዩ ኤልሳዕን ሥጋቸውን ምእምናንም መጥተው ለወታደሮች ብዙ ገንዘብ ሰጡ ንጉሡም ሰምቶ እንዳያጠፋቸው በዚያች አገር እንዲያስቀሩ ከአማሏቸው በኋላ የቅዱሳንን ሥጋ ወሰዱ።
❤ የዑልያኖስም ዜናው እንዲህ ሆነ የጳጳሳት አለቆች ባስልዮስና ጎርጎርዮስ በአሠራቸው ጊዜ እነርሱ በቅዱስ መርቆሬዎስ ሥዕል ዘንድ እያለቀሱ ጸለዩ። የክብር ባለቤት የሆነ የጌታችንን የከበረ ስሙን ሰድቧልና ያን ጊዜ እግዚአብሔር ቅዱስ መርቆሬዎስ በከአካለ ነፍስ ላከው ዑልያኖስንም በጦር ወጋው ከደሙም ዘግኖ "ኢየሱስ የሰጠኸኝን ነፍስ ተቀበል" እያለ ወደ አየር ረጨ ወዲያውኑም በክፋ አሟሟት ሞተ።
❤ የከበሩ የቅዱሳን የዮሐንስና የኤልሳዕ ሥጋ ግን እሊህ ሰዎች በእስክንድርያ ከተማ ወደ ሊቀ ጳጳሳቱ አባ አትናቴዎስ አደረሱ። እርሱም በእርሳቸው ታላቅ ደስታ ደስ አለው ቤተ ክርስቲያንም እስኪሠራላቸው ድረስ በርሱ ዘንድ አኖራቸው። በአንዲት ዕለትም አባ አትናቴዎስ በአባቶቹ ቦታዎች ላይ ስለ ጸሐፊው ቴዎፍሎስም አብሮት ሳለ "እግዚአብሔር መልካም ዘመን ቢሰጠኝ ሥጋቸውን በውስጧ አኖር ዘንድ ለቅዱሳን መጥምቁ ዮሐንስና ለነቢዩ ኤልሳዕ በስማቸው በዚህ ቦታ ቤተ ክርስቲያ እሠራለሁ" አለ ቴዎፍሎስም ሰማው።
❤ አባ ቴዎፍሎስም በተሾመ ጊዜ አባ አትናቴዎስ የተናገረውን ያንን ቃል አስቦ ቤተ ክርስቲያን ሠራ። ከርሱ ጋራም ብዙዎች ካህናትና የክርስቲያን ወገኖችን ይዞ የቅዱሳን የመጥምቁ ዮሐንስና የነቢዩ ኤልሳን ሥጋቸውን ወዳለበት ሔደ በታላቅ ክብርም ተሸክመው አምጥተው ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገቡ። ሥጋቸውንም ይዘው በሚጓዙበት ጊዜ በጐዳናቸው አቅራቢያ ቤት ካለበት ቦታ ደረሱ በውስጡም በምጥ ተይዛ አራት ቀናት እየጮኸች ለሞት የተቃረበች ሴት ነበረች። እርሷም አረማዊት ነበረች በቅዱሳኑም ሥጋ ዘንድ ካህናቱ የሚያመሰግኑትን ሰምታ በቤቷ መስኮት ተመለከተች "ይህ ምንድን ነው?" ብላ ጠየቀች። "የቅዱሳን የመጥምቁ ዮሐንስና ነቢዩ ኤልሳዕ ሥጋቸው ነው" እርሷም "ከዚህ ሥቃይ ከዳንኩ ክርስቲያን እሆናለሁ" አለች ገና ቃሏ ከአፋዋ ሳይፈጸም ያን ጊዜ መልካም ሕፃን ወለደች ስሙንም ዮሐንስ ብላ ጠራችው። ከዚህም በኋላ ከቤተ ሰቦቿ ሁሉ ጋራ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀች።
❤ የቅዱሳኑንም ሥጋቸውን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት ከእርሳቸውም ታላላቅ ድንቆችና ተአምራት ተገለጠ። በቅዳሴ ቤተ ክርስቲያኑም ጊዜ ከሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ ጋራ ብዙዎች ሰዎች ቅዱሳን መጥምቁ ዮሐንስንና ነቢዩ ኤልሳዕን ሲዞሩ አዩአቸው በቀድሞ መልካቸው ያውቋቸዋልና የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ መልክ ሁለመናው ጸጒር ሲሆን ጽሕሙ በደረቱ ላይ የወረደ ነበር ቅዱስ ኤልሳዕም ቁመቱ ረጅም ራሱ በራ ነበር።
❤ ከዚህም በኋላ ኤጲስቆጶሱ አባ መቃርስ በሰማዕትነት በዐረፈ ጊዜ ሥጋውን ከቅዱሳን ዮሐንስና ኤልሳዕ ሥጋ ጋራ አደረጉ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስና በነቢዩ ቅዱስ ኤልሳዕ በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸው ከእኛ ለዘላለሙ ይኑር አሜን። ምንጭ፦ የሰኔ 2 ስንክሳር።
+ + +
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ናሁ ሠናይ ወናሁ አዳም። ሶበ ይሔልው አኃው ኅቡረ። ከመ ዕረፍት ዘይውኅዝ እምርእሱ እስከ ጽሕሙ"። መዝ 132፥1-2። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 14፥29-ፍ.ም፣ ያዕ 5፥12-17 እና የሐዋ ሥራ 13፥24-32። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 11፥1-16። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የበዐልና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ ሰኔ ፪ (2) ቀን።
❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቃን #ለአቡነ_ተክለ_ሃይማኖት_ለአክስት_ልጅ እንደ ነቢዩ ኤልያስ እሳት ከሰማይ አውርደው በሸዋ ክፍለ አገር ፈንታሌ ተራራ ላይ ሰሪቲ ለምትባ ጠንቋይ እየተላላኩ ሕዝቡን የሚያስቱና የሚያሰቃዩ አራት መቶ ሰባ ሽህ ሦስት መቶ አጋንንት በአንድ ጊዜ ላጠፋ ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ቀውስጦስ_ዘመሐግሉ ለመታሰቢያ በዐላቸው በሰላም አደረሰን።
+ + +
❤ #አቡነ_ቀውስጦስ፦ ጻድቁ የተወለዱት ሸዋ ክፍለ አገር በወግዳና ቡልጋ ውስጥ ሲሆን አባታቸው ቅዱስ ገላውዴዎስ እናቸው ቅድስት እምነ ጽዮን ይባላሉ። የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እናት እግዚእ ኃርያ እና እምነጽዮን ታናሽና ታላቅ እህትማማቾች ናቸው።
❤ ቅዱስ ገላውዴዎስና ቅድስት እምነ ጽዮን እግዚአብሔር የተባረከ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ለዓመታት በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስዕል ፊት ሲጸልዩና ሲለምኑ እመቤታችን በስዕሏ ላይ አድራ አናገረቻቸው፤ እንዲህም አለቻቸው፦ " አንድ ልጅ አስቀድማችሁ ትወልዳላችሁ፤ የሚወለደውም እኔ በተወለድኩበት ግንቦት1 ቀን ዕረፍቱም በእኔ ዕረፍት ቀን ጥር21 ነው እሱም የሰማያዊ ንጉሥ ጭፍራ ይሆናል" አለቻቸው። በቃሏ መሰረትም ግንቦት1 ቀን ጻድቁ አቡነ ቀውስጦስ ተወለዱ።
❤ ጻድቁ አባታችን አቡነ ቀውስጦስ የዚህን ዓለም ተድላ፣ ደስታና ጠዐም ንቀው ፈለገ ሐዋርያትን ተከትለው በሸዋ፣ በከፋና በጅማ ዞረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በማስተማር አረማውያን፣ ነገሥታትና ባላባቶች የሚደርስባቸውን መከራና እንግልት በመታገስ በተጋድሎ ፀንተው ብዙውን ሕዝብ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ከኃጢያት ወደ ጽድቅ መልሰዋል። በተለይም በሸዋ ክፍለ አገር ፈንታሌ ተራራ ላይ ሰሪቲ ለምትባ ጠንቋይ እየተላላኩ ሕዝቡን የሚያስቱና የሚያሰቃዩ ፬፻፸ሺ፫፻ (አራት መቶ ሰባ ሽህ ሦስት መቶ) አጋንንትን እንደ ነቢዩ ኤልያስ በጸሎታቸው ከሰማይ እሳት አውርደው ተራራውን ደምስሰው አጋንንቱን አቃጥለዋል። ሕዝቡንም ለጣዖትና ለጠንቋይ ከመገዛት አድነውታል።
❤ ጻድቁ አባታችን አቡነ ቀውስጦስ በብዙ ተጋድሎ ሲኖሩ በሰማዕትነት ያርፉ ዘንድ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚተጉ እንጂ የዚህን ዓለም መንግሥት ሀብትና ስልጣን የማይሹ እውነተኛ መናኝ ነበሩና የታናሽ ወንድማቸው የአፄ ይኩኖ አምላክ ልጅ አፄ አምደ ጽዮን የአባቱን እቁባት በማግባቲ "ይህንን ልታደርግ አይገባህም"። ብለው እንደ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ቢገስጹት ዐሥራ አንድ አሽከሮቹን በሌሊት ልኮ ከበዩ ወደ እንሳሮ አገር ካስወሰዳቸው በኋላ ኮሶ አረህ ከሚባለው አፋፍ ላይ በእኩለ ሌሊት በጦር ጎናቸውን አስወግቶ ደማቸውን አስፈሰሰ። ደማቸውም እስከ ታላቁ ወንዝ ጀማ ድረስ ሆነ። የፈሰሰው ደማቸውም ቀይ ብርሃን ሲሆን የሌሊቱ ጨለማ ከፀሐይ ሰባት እጅ የሚበልጥ ብርሃን በአውራጃዎቹ ሁሉ ታየ። በዚህ የተነሳ እስከ ዛሬ ድረስ አገሩ ቀን ተብሎ ይጠራል።
❤ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ሳትለይ በስቃይ ላይ ሳሉም በዘመናቸው ሁሉ ስለነበራቸው ተጋድሎ፣ ንፅህናና ምናኔ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምንና ቅዱሳን መላእክትን አሰከትሎ በክበበ ትስብእት በግርማ መለኮት መጣና ቃል ኪዳን ሰጣቸው። እንዲህም አላቸው፦ "እኔ ለአንተ አይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን መንግሥተ ሰማያትን አዘጋጀውልህ። በዘመንህ ስላሳለፍከው ክርስቲያናዊ ፍፁም ተጋድሎህ ሰባት የብርሃን አክሊል (ዘውዶችን) ያዘጋጀውልህ ሲሆን ሁለቱ እንደ እነ ነቢዩ ኤልያስና ነቢዩ ሳሙኤል ለሆነ ንጽህናህ፣ ሁለቱ እንደ እነ ቅዱስ ጴጥሮስና ጳውሎስ ለሆነ የወንጌል ስብከትህ፣ ሁለቱ እንደ እነ ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅዱስ ፊቅጦር በትዕግሥት ስለተጋደልክ፣ አንዷ ስለ ልብህ ርህራኄ ናት ብሎ አጎናፅፏችኋል። እንዲሁም ስለ እኔ ምስክርነት የሞትክባት ምድር እንደ ዳዊት አገር እንደ ኢየሩሳሌም ትሁንል ወደእርሷ የሄደውንም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ወደ መቃብሬ ጎልጎታ እንደሄደ እቆጥርለታለሁ። ብዙ ኃጢያት የሥራ ሰው ንስሐ ገብቶ በዚያች አገር በስምህ ጥቂት ምጽዋት ቢሰጥ እኔ ኃጢያቱን እደመስስለታለሁ፤ በጠበልህም ቢጠመቅ በደሉን አጠፋለታለሁ ደምህ በምድሪቱ ፈሷልና፤ በዕረፍትህ ዕለት ለቤተ ክርስቲያንህ ለቅዱስ ቁርባን ስንዴ፣ ወይንና ዕጣን ያቀረበ ኃጢያት የሰራ ተነሳሂ (ንስሃ የገባ) ሰው ቅዱስ ሥጋውንና ክብር ደሙን እንደተቀበለ ንፁህ ሰው አደርገዋለሁ፣ ለስምህ መታሰቢያ በታነጸው ቤተ መቅደስ በንጽህና ቅዱስ ሥጋውንና ክብር ደሙን የሚቀበል (የሚቆርብ) ሰው ራሱን፤ ቤተሰቡንና ባልንጀሮቹን ያድናል"።
❤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለጻድቁ አባታችን አቡነ ቀውስጦስ ይህንን ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው ዐረገ። ቅዱሳን መላእክትም ነፍሳቸውን ከስጋቸው በክብር ለዩ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በሰማይ መካከል ነፍሳቸውን በፈገግታ ተቀበለች። የዕረፍታቸውም ዕለት እመቤታችን ባለፈችበት ጥር 21ቀን በመሆኑ እመቤታችንም "መታሰቢያህን ለሚያደርጉ ሁሉ በልጄ በረከት እበርካቸዋለሁ" ብላ ቃል ኪዳን ገባችላቸው። ጻድቁ አባታችን አቡነ ቀውስጦስ ባረፉበት ዕለትም ብዙዎች ከዴዌአቸው ተፈውሰዋል። የጻድቁ አባታችን በረከትና ፈውስ አሁንም ድረስ ደማቸው በፈሰበትና አፅማቸው ባረፈበት ቦታ ሁሉ እየታየ ብዙ ምዕመናን ፈውስ ነፍስና ፈውሰ ሥጋ እያገኙበት ነው።
❤ ገዳመ ቀውስጦስ የሚገኘው ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 120ኪ.ሜ ርቀት ላይ ሲሆን ወደ ደብረ ሊባኖስ በሚወስደው መንገድ ሙከጥሪ ከተማ ሲደርሱ ወደቀኝ በመታጠፍ ሜጤና ባዩ በሚባለው አካባቢ ልዩ ስሙ ተግባሬ (መገንጠያ) ከሚባል ቦታ ነው። ከጻድቁ አቡነ ቀውስጦስ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ ገድለ አቡነ ቀውስጦስ (በአጭሩ) ከሚለው መጽሐፍ።
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
✍️"የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል ከመከራም ሥጋት ያርፋል"
📖ምሳ 1፥33
#ስንክሳር
ዘሰኔ #ሁለት (፪)
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
