ch
Feedback
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን🙏

የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን🙏

前往频道在 Telegram

የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና የጠበቁ የነፍስ ስንቅ የምናገኝበት፦ ✍️"ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም" ፩ኛ ቆሮ. ፰፥፪ #ለተጨማሪ፦👇✞👇 https://www.youtube.com/EOTC2921 https://www.facebook.com/eotc2921 https://www.tiktok.com/@eotc2921 https://www.instagram.com/eotc2921

显示更多
4 374
订阅者
无数据24 小时
无数据7 天
无数据30 天
帖子存档
🌿🍇✞ #ቅድስት_ክርስቶስ_ሠምራ ✞🍇🌿 ግንቦት ፲፪ እንኳን ለቅድስት ክርስቶስ ሠምራ አመታዊ የመታሰቢያ ክብረ በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን አሜን። ✅ኢትዮጵያዊቷ ጻድቅ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በሸዋ ክፍለ ሀገር በቡልጋ አውራጃ ልዩ ስሟ ቅዱስ ጌየ በተባለች ሀገር እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ደጋግ ሰዎች በግንቦት ፲፪ ቀን ተወለደች፡፡የአባቷ ስም ቅዱስ ደረሳኒ የእናቷም ስም ቅድስት ዕሌኒ ይባላል፡፡ አኒህም ሰዎች ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን ከወለዱ በኋላ በደም ግባቷና በጠባይዋ እየተደሰቱ የእግዚአብሔርን ሕግጋትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በማስተማር አሳደጓት፡፡ባደገችና ለአቅመ ሔዋን በደረሰች ጊዜ የንጉሥ ባለሟል ለሆነ ስሙ ሠምረ ጊዮርጊስ ለተባለ ሰው በሕግ አጋቧት፡፡ ✅ከዚህ በኋላ ከሕግ ባሏ ከሠምረ ጊዮርጊስ አስራ አንድ ልጆችን ወለደች ከእነዚህም መካከል ዘጠኙ ወንዶች ሁለቱ ሴቶች ነበሩ፡፡ በዚያ ዘመን የነበረው ንጉሥ ገብረ-መስቀል በጸሎትሽ አስቢኝ በማለት 174 አገልጋዮችን፣ ብዙ ፈረስና በቅሎ እንዲሁም ለነገሥታት ሚስቶች የሚገባ ከሐርና ከወርቅ የተሠራ ልብስና የወርቅ ጫማ ላከላት፡፡ ነገር ግን እሷ ይህን ሁሉ ክብር አልፈለገችም ይልቁንም ለዓላማዬ እንቅፋት ወይም ውዳሴ ከንቱ ይሆንብኛል እንደዚሁም ወርቁ ጌጡ ተሸጦ ለነዳያን ይመጸወታል፤ ነገር ግን እነዚህን አገልጋዮች ምን አደርጋቸዋለው እያለች ወደ እግዚአብሔር አመለከተች፡፡ ✅ከጥቂት ቀናት በኋላ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ፊቱ እንደ ፀሐይ እያበራ ሦስት ኅብስት በእጁ ይዞ የእግዚአብሔር ባለሟል ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እነሆ ይህን ኅብስት ተመገቢ እግዚአብሔር በቸርነቱ ብዛት ሰጥቶሻል አላት፡፡ እሷም ፈጣሪዋን አመስግና ኅብስቱን ከመልአኩ እጅ ተቀብላ ተመገበች መዓዛ ጣዕሙም ሰውነቷን አለመለመው፡፡ በዚህም የተነሳ እስከ ሦስት ቀን እህል ሳትበላ ውኃ ሳትጠጣ ቆየች፤ ኃይለ መንፈስ ቅዱስ በሰውነቷ አድሮባታልና፡፡ ✅ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፣ ከአገልጋዮቿ መካከል አንዷ ምግባሯ የከፋ ነበርና በጣም ስላበሳጨቻት በዚያች አገልጋይ አፍ ውስጥ የእሳት ትንታግ ጨመረችባት ያም የእሳት ትንታግ እስከ ጉሮሮዋ ዘለቀና አገልጋይዋን ገደላት፡፡ በዚህ ጊዜ ብጽዕት ክርስቶስ ሠምራ ደንግጣ ወደ ሌላ ክፍል ገባችና ኃጢአቷን ለእግዚአብሔር እየተናዘዘች እጅግ በጣም አዝና ጥፋቷ እንደ ጸጸታትና እግዚአብሔር አምላክም በእጇ የሞተችውን አገልጋይዋን ከሥጋዋ አዋህዶ ቢያስነሳላት ያላትን ገንዘብና ሀብት ትታ ባላት ዘመኗ ሁሉ አገልጋዩ እንደምትሆን ብጽዓት/ስዕለት/ አደረገች። እግዚአብሔርም ጸሎቷን ሰምቶ አገልጋይዋን አስነሳለት፡፡ እሷም' ልመናዬን ቸል ያላለ ቸርነቱንም ከእኔ ከባሪያው ያላራቀ አምላክ ይክበር ይመስገን ብላ በታላቅ ምስጋና እግዚአብሔርን አመሰገነች፡፡ ✅ከዚህ በኋላ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ አስቀድማ የገባችውን ቃል አስባ ልብሰ ምንኩስናዋን አዘጋጀች፡፡ ከዛም አገልጋዮቿን ጠርታ ወደ ቤተክርስቲያን እንሄድ ዘንድ ተዘጋጁ አለቻቸውና አብረዋት ሄዱ፡፡ ከዚያም እንደ ደረሱ አንድ አገልጋይዋንና ሕፃን ልጅዋን አስቀርታ ሌሎቹን ወደ ቤት መለሰቻቸውና የሚያልፈውን ዓለም በማያልፈው ዓለም ለመተካት ጉዞዋን ጀመረች፡፡ ✅ጉዞ ወደ #ደብረ_ሊባኖስ ያ በልስላሴና በእንክብካቤ የኖረ እግር ከመንገዱ ብዛት እንደዚሁም ከእንቅፋቱ የተነሳ ፈለግ ሲያወጣ ሥጋውን እየቆረጠች ስትጥለው ደሙ እንደ ጎርፍ ውኃ ይወርድ ነበር፡፡ በዚህ ዓይነት ችግርና የፀሐይ ሀሩር ከአሰበችው ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ደረሰች በዚያም አስቀድማ ያዘጋጀችውን ልብሰ ምንኩስናዋን ለብሳ ከሴቶች ገዳም ገባች፡፡ ✅ይዛው የተሰደደችውን ሕፃን ግን ወንድ ስለሆነ ከደጅ ላይ አስቀምጣው ገባች ሕፃኑ ግን ምርር ብሎ ያለቅስ ነበር ምክንያቱም ከእናቱ ከመለየቱ በተጨማሪ ጊዜው ጨልሞ ነበር፡፡ ከመነኮሳቱ አንዲቷ ሕፃኑ ሲያለቅስ ከሚያድር ብላ ወደ በአቷ ልታስገባው ስትል የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ነጥቆ ወስዶ ሄሮድስ ካስፈጃቸው ሕፃናት ጋር በገነት አስቀመጠው፡፡ ታኅሳስ ፳፱ ቀን ተወልዶ በ ፫ ዓመቱ ታኅሳስ ፲፪ ቀን ብሔረ ብጹአን ገባ፡፡ ✅የምንኩስና ሕይወት ከዕለታት በአንደኛው ቀን እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ቆማ ስትጸልይ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ በክንፉ ተሸክሞ ከጣና ደሴት አደረሳት፡፡ ከዚያም ሰውነቷ ተበሳስቶ የባህር ዓሳ መመላለሻ እስከሚሆን ድረስ እንደ ተተከለ ዓምድ ሆና ሳትወጣ በባህሩ ውስጥ ፲፪ ዓመት ቆማ ስትጸልይ ኖራለች፡፡ ✅ከዕለታት አንድ ቀን በጣና ማዶ መዕቀበ እግዚእ የሚባል አንድ ሰው ነበረና መልአከ ጽልመት ወደ እሱ ዘንድ መጥተው ፈጣሪውን ክደህ ይህን ዕፅ በሰውነትህ ብትቀብር ሞትና እርጅና አያገኝህም አለው፡፡ እሱም እሽታውን ስለገለፀ መልአከ ጽልመት በሰውነቱ ዕፁን ቀብሮለት ሄደ፡፡ ✅ዳግመኛም ከዕለታት አንድ ቀን ወደ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ዘንድ መጥቶ "ሰላም እልሻለው በጸሎትሽም ተማጽኛለሁ የፈጠረኝን እግዚአብሔርን እስከ መካድ ደርሼ ብዙ ኃጢአት ሰርቻለውና" አላት፡፡ በዚያን ጊዜ ፈጥና ተነስታ ወደ ቤተክርስቲያን ሄደችና ስለዚህ ሰው በፍጹም ኀዘን በመሆን ወደ ፈጣሪዋ አመለከተች፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታችን መጥቶ ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ለዚህ ሰው ምህረት አይገባውም፤ የምገድል የማድን የምቀስፍ ይቅር የምል አምላክ እኔ እያለሁ ፈጣሪውን ክዶ በሰይጣን ምክር ተማምኖአልና አላት፡፡ ✅በዚህ ጊዜ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በእግሩ ስር ተደፍታ አንተ መዓትህ የራቀ ምህረትህ የበዛ ፈጣሪ ሆይ ማርልኝ ሁሉ ይቻልሃልና ስትል አጥብቃ ለመነችው፡፡ ሁሉን የፈጠረ ጌታ እግዚአብሔር እለ፦ "በአንቺ ፍቅር ምሬልሻለው አላት፡፡" ከዚህ በኋላ ማእቀበ እግዚእን ጠርታ ኃጢአትህን ይቅር ብሎሃል አለችው፡፡ ከዚህ በኋላ ከራስ ጸጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ የተቀበረውን ዕፅ ሰውነቱን ፍቃ ስታወጣለት ደሙ እንደ ቦይ ውኃ ወረደ በዚያው ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ ከማኅበረ ሰማዕታት ጋር አንድ ሆነች፡፡ ✅ከዚህ በኋላ ለቅድስት ክርስቶስ ሠምራ እግዚአብሔር አምላካችን ስድስት ክንፎች በሰውነቷ ላይ ማለትም ሦስቱ በቀኝ ጎኗ ሦስቱ በግራ ጎኗ በቀሉ በዚህም እግዚአብሔርን ፈጽሞ አመሰገነች፡፡ ✅ከዕለታት በአንደኛው ቀን እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ጌታችንን እንዲህ ስትል ጠየቀችው፡፡ አቤቱ ፈጣሪዬ ፈቃድህ ቢሆን የአዳም ልጆች ከስቃይ ከኩነኔ ይድኑ ዘንድ ዲያቢሎስን ይቅር ትለው ዘንድ እለምንሀለው፡፡ የኃጥእን መመለሱን እንጂ ጥፋቱን አትወድምና አለችው፡፡ ይህን ባለችው ጊዜ ጌታም መልሶ ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ሌሎች ከአንቺ በፊት የነበሩ ከአንቺም በኋላ የሚመጡ የማያስቡትን እጅግ የሚያስደንቅ ልመና አቀረብሽ አላት፤ ይህን ካለ በኋላ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን ጠርቶ ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ዲያቢሎስን ማርልኝ ስትል ልመና አቅርባለችና እሺ ካላት ታመጣው ዘንድ ወደ ሲኦል ይዘሃት ሂድ አለው፡፡ ከሲኦል እንደ ደረሰች ለዲያቢሎስ ልተስታርቀው እንደመጣች ነገረችው እሱ ግን ጭራሽ አጁዋን ይዞ ወደ ሲኦል ወረወራት በዚህ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል በያዘው ሰይፍ አስጣላትና በቅዱስ ሚካኤል ክንፍና ለእሷም በተሰጣት ክንፈ ረድኤት ከሲኦል ዓስር ሺህ(10,000) የሚያክሉ ነፍሳትን ይዘው ወጡ፡፡

🌿🌾✞ #ቅዱስ_ያሬድ ✞🌾🌿 [ግንቦት ፲፩ የቅዱስ ያሬድ ዓመታዊ በዓል] ✅ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ አባቱ አብዩድ (ይሥሐቅ) እናቱ ክርስቲና (ታውክልያ) ሲባሉ የተወለደውም በ፭፻፭ ዓ.ም. በአክሱም ነው፡፡ ሰባት ዓመት ሲመላው አባቱ ስላረፈ፤ እናቱ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንዲያስተምረው ለአባ ጌዴዎን ሰጠችው፡፡ ነገር ግን ማጥናት ስላልቻለ አባ ጌዴዎን ይቈጣው ነበርና ሸሽቶ ከዱር ውስጥ ገባ፤ ከዐዘኑም ብዛት የተነሣ በዛፍ ሥር ተጠልሎ ሳለ አንዲት ታናሽ ትል ከዛፍ እኩሌታ ደርሶ ሲወድቅ ሲነሣ በመጨረሻም በጭንቅ ከዛፉ ላይ ሲወጣ በማየቱ እግዚአብሔር በዚኽች ታናሽ ፍጥረት እንዳስተማረው በመረዳት ይቅርታ ጠይቆ ወደ መምህሩ ተመልሷል፡፡ ✅“ወእምዝ ሶበ ሰአለ ኀበ እግዚአብሔር በብካይ ብዙኅ ተርኅወ ልቡናሁ ወተምህረ በሐጺር ዕለት መጻሕፍተ ብሉይ ወሐዲስ” ይላል ከዚኽ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ እግዚአብሔር በለመነ ጊዜ ልቡናው ብሩህ ኾኖለት በዐጭር ጊዜ ውስጥ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ተምሮ በመጨረስ ዲቁናን ተሾመ፤ እስከ ርሱ ዘመን በማነብነብ እንጂ በከፍተኛ ድምፅ የመዝሙር ማሕሌት አልነበረም፤ እግዚአብሔርም ለዚኽ አባት የመላእክትን ዝማሬ ሊያሳየው ስለወደደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እስከ ሦስተኛው ሰማይ እንደተነጠቀ ኹሉ ሊቁም ተነጥቆ የኻያ አራቱ ካህናተ ሰማይን የምስጋና ዝማሬ ሰምቶ ተመለሰ፡፡ ✅ቅዱስ ያሬድ ከአርያም ወርዶ ወደ ምድር እንደ ደረሰ ወደ አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ገብቶ፡- “ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ” (ለአብ ምስጋና ይገባል፣ ለወልድም ምስጋና ይገባል፣ ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል፡፡ ከጽዮን አስቀድሞ ሰማይን ፈጠረ ዳግመኛም ለሙሴ የድንኳኑን ሥራ እንዴት እንደሚሠራ አሳየው) ሲል ዘምሮ ይቺኑ መዝሙር ከሰማይ መላእክት አገኘኹት፣ በማለት አርያም በሚል ሥያሜ ጠርቷታል፡፡ ✅ይኽነኑ ድርሳነ ዜማ የጻድቁ ካሌብ ልጅ ንጉሥ ገብረ መስቀል በሰማ ጊዜ ጫማውን ሳይጫማ ንግሥቲቱም ደንገጡሮቿን አጃቢዎቿን ሳታስከትል መኳንንቱ፣ ካህናቱና መምህራኑ እነሱን ተከትለው እየተጣደፉ ወደ ዐደባባዩ በመኼድ በተመስጦ ሲሰሙት ውለዋል፡፡ ✅ቅዱስ ያሬድ ዐምስት የዜማ መጻሕፍትን የደረሰ ሲኾን እነርሱም ፩ኛ) ድጓ ፪ኛ) ጾመ ድጓ ፫ኛ) ምዕራፍ ፬ኛ) ዝማሬ ፭ኛ)መዋሥዕት ናቸው፡፡ ✅እነዚኽንም ታላላቅ ድርሰቶቹን በሦስት የዜማ ስልቶች ማለት በግእዝ፣ በዕዝል፣ በአራራይ አዘጋጅቷቸዋል፡፡ “ወአሐተ ዕለተ እንዘ ይዜምር ያሬድ ቀዊሞ ታሕተ እገሪሁ ለንጉሥ ገብረ መስቀል ወእንዘ ያጸምዕ ንጉሥ ቃሎ ለያሬድ ተከለ በትረ ኀጺን ውስተ መከየደ እግሩ ለያሬድ” ይላል፤ ከዕለታት ባንዳቸው ቅዱስ ያሬድ በተመስጦ ልዑል እግዚብሔርን በዝማሬ ሲያመሰግን ንጉሥ ገብረ መስቀል ሳያውቁት ልባቸው በጣዕመ ዜማው በመመሰጡ የብረት ዘንጉን በቅዱስ ያሬድ እግር ላይ ተክለውታል፤ ከእግሩም ብዙ ደም ቢፈስስም ቅዱስ ያሬድ ግን ማሕሌቱን እስከሚፈጽም ድረስ ምንም አልሰማውም ነበር፡፡ ✅ንጉሡም የደሙን መፍሰስ አይቶ ደንግጦ ቅዱስ ያሬድን “የደምኽ ዋጋ የፈለግኸውን ንገረኝ” አለው፤ ቅዱስ ያሬድም ተምኔቱ ወደ ገዳም መኼድ እንደኾነ ነገረው፤ ያን ጊዜ ንጉሡ እያዘነ አሰናብቶታል፡፡ ✅“ወእምዝ ቦአ ያሬድ ውስተ ቤተ ክርስቲያን ወቆመ ቅድመ ታቦተ ጽዮን” ይላል ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ በታቦተ ጽዮን ፊት በመቆም የአንቀጸ ብርሃንን ምስጋና ከመዠመሪያው እስከ መጨረሻው በተናገረ ጊዜ በእግዚአብሔር ኀይል ክንድ ያኽል ከምድር ከፍ ከፍ አለ፤ ከዚኽ በኋላ ወደ ሰሜን ተራራዎች ወደ ገዳም ሲኼድ የአኲስም ጽዮን ካህናት እስከ ተከዜ ወንዝ ድረስ ሸኙት ርሱም እጅግ ባማረ ጣዕመ ዜማ ድምፁን ከፍ አድርጎ “ሰላም እግዚአብሔር ኲሉ ባቲ ተሃሉ ወትረ ምስለ ኲልክሙ” (በኹሉ ላይ ጸንታ የምትኖር የእግዚአብሔር ሰላም ዘወትር ከኹላችኊ ጋር ትኑር) ብሎ የስንብት መዝሙርን ዘመረ፤ ካህናቱም ይኽነን ቃል ሰምተው መሪር እንባን አለቀሱና ተሰነባበቱ፡፡ ✅በትርጓሜ ቅዳሴ ማርያም መቅድም ላይ እንደምናነብበው ቅዱስ ያሬድ ማይ ኪራህ በተባለው ቦታ ተሰውሮ ጸዋትወ ዜማን ሲያስተምር እመቤታችን ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬምን የብህንሳውን አባ ሕርያቆስን በአካለ ነፍስ እንዲመጡ አድርጋ ኤፍሬም ውዳሴዬን፤ ሕርያቆስ ቅዳሴዬን ነግራችኹት ቅዱስ ያሬድ በዜማ ይድረስልኝ ብላ ነግረውት በዜማ ደርሶታል፤ ይኽም ሊታወቅ ሥረይ በቅዳሴ ማርያም ይበዛል፡፡ ✅ርሱም ጸዋትወ ዜማን ለደቀ መዛሙርቱ እያስተማረ መላእክት ዘወትር እየጐበኙት በጾም በጸሎት ተወስኖ በተጋድሎ ለኻያ ኹለት ዓመት ጸንቶ ኖረ፤ በመጨረሻም ጌታችንም ለቅዱስ ያሬድ ተገልጾለት “ኦ ፍቁርየ ቀዳሚኒ በከመ ሰመርኩ ትርአይ ሥርዐተ ስብሐተ መላእክት ዘበሰማያት ወአስተኀለፍከ ዘንተ ማሕሌተ ዲበ ምድር... ” (ወዳጄ ሆይ ቀድሞ በሰማይ ያለ የመላእክትን ሥርዐተ ማሕሌት እንድታይና ወደ ምድርም አስተላልፈኽ ይኽነኑ ዜማ እንድትመሠርት እንደ ወደድኊ ኹሉ እኔ ዳግም ተመልሼ በምመጣበት ጊዜ ከካህናተ ሰማይና ሄሮድስ ደማቸውን ካፈሰሰው ሕፃናት ጋር በደብረ ጽዮን ትዘምር ዘንድ ሰማያዊ የክብር አክሊልና የብርሃን ልብስ ተዘጋጅቶልኻል” ብሎት ቃል ኪዳንን ሰጥቶት በክብር ዐረገ፡፡ የቅዱስ ያሬድ መታሰቢያውም ግንቦት ዐሥራ አንድ ነው፡፡ ✅ሊቁ አርከ ሥሉስም የቅዱስ ያሬድን ነገር በአርኬው ላይ፦ “ሰላም ለያሬድ ስብሐተ መላእክት ለሕዋጼ እንተ አዕረገ በልቡ ኅሊና መንፈስ ረዋጼ ለትምህርተ መጽሐፍ ገብአ እምኀበ ኮነ ነፋጼ በብዙኅ ጻማ ዘአልቦ ሑጻጼ መልዕልተ ጒንደ ዖም ነጺሮ እንዘ የዐርግ ዕጼ” (የመላእክትን ምስጋና ለመጐብኘት ከመንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ ፈጣን ዐሳብን ወደ ልቡናው ያሳረገ ለኾነ፤ ጒድለት በሌለበት በብዙ ድካምም ወደ ዛፍ ግንድ ጫፍ ላይ ትል ሲወጣ ተመልክቶ፤ ኰብልሎ ከኼደበት መጻሕፍትን ለመማር የተመለሰ ለኾነ ለያሬድ ሰላምታ ይገባል) በማለት ሊቁ ማሕሌታይን አመስግኖታል፡፡ ✅ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በተአምኆ ቅዱሳን መጽሐፉ ላይ ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ሊቁ ቅዱስ ያሬድን ሲያወድስ፡- “ሰላም ለያሬድ ቀሲስ ዘጽጉብ እክለ መንፈስ ቅዱስ፤ ዘአስተጋብአ ምድራሳተ እምኲሎሙ መጻሕፍት ወአሰርገዋ በሐዋዝ ስብሐት ወበጥዑም ማሕሌት ለብሔረ ኢትዮጵያ በስብሐት ሃሌ ሉያ ዘከዐወ ቃለ መለኮት ዲቤሃ ከመ አስራበ ወርቅ ንጹሐ”፡፡ (የመንፈስ ቅዱስን ምግብን የጠገበ፤ ከመጻሕፍት ኹሉ ትርጓሜያተ ድርሰትን ያሰባሰበ፤ ሃሌ ሉያ በሚል ምስጋና የኢትዮጵያ ሀገርን በጥዑም ማሕሌትና በሚያምር ምስጋና ያስጌጠ፤ የመለኮት ቃልን በላይዋ ላይ እንደ ንጹሕ የወርቅ ሻሻቴ ያፈሰሰ ለኾነ ለካህኑ ያሬድ ሰላምታ ይገባል) ይለዋል፡፡ [የጽሑፉ ምንጭ፡- አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ የደረሰው ተአምኆ ቅዱሳን ንባቡና ትርጓሜው በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ የተጻፈ፤ ከገጽ 232-235]፡፡ 🙏የቅዱስ ያሬድ ረድኤት በረከት ይደርብን።🙏

#የኢትዮጵያ_አስገራሚ_እውነታዎች ~~~✔🍇 #ክፍል-1🍇✔~~~ ✅ #ኢትዮጵያ ማለት “ለአምላክ የሚሰጥ የወርቅ ሥጦታ” ማለት ነው ትርጉሙ። ሲተነተንም #ኢት=ማለት አምላክ፣ ፈጣሪ፣ እግዚአብሔር ማለት ሲሆን #ዮጵ=ማለት ቢጫ ወርቅ፣ ውድ ወርቅ፣ ልዩ ወርቅ ማለት ነው። ✅ኢትዮጵያ ማለት እኔና እናንተ በምናውቃት ልክ ብቻ ያለች ሀገር አይደለችም። ✅ኢትዮጵያ ከምድር ሀገራት ሁሉ እጅግ ምስጢራዊና ረቂቅ ሀገር ናት። ይሄን ስላችሁ ደግሞ በግምት ወይም በስሜት ተገፍቼ አይደለም። በብዙ ማስረጃዎች ነው እንጅ። #1ኛ) ሊቀ ነብያት ሙሴን የአመራርነት ጥበብ ያስተማረው #ኢትዮጵያዊው_ ዮቶር ነው። ስለዚህ ለእስራኤል ከፈርዖን ነጻ መውጣት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና አለበት ማለት ነው። የዮቶር እርስት ውብ ሀገር ኢትዮጵያ ነች። #2ኛ) አሁንም የሊቀ ነብያት ሙሴ ሚስት #ሲጳራ ኢትዮጵያዊት ነች። ሐበሻዊት ሲጳራ የኢትዮጵያዊው የዮቶር ልጅ ነች። ሙሴ ይቺን ሴት በማግባቱ ወንድሙ አሮንና እህቱ ማርያም ያጉረመርሙበት ነበር። #3ኛ)የመጀመሪያው ካህን መልከጼዴቅ ኢትዮጵያዊ ነው ይህ ካህን በክርስትና አስተምህሮ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ተደርጎ ይቆጠራል። #4ኛ) በሀገረ እስራኤል የራሷ ቦታ ያላት (ዴር ሡልጣን) ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ ነች። ይሄንን ቦታ ምዕራባዊያንና አንዳንድ የምስራቅ ሀገራት ለመውሰድ ቢሞክሩም እንዳልተሳካላቸው ታሪክ ይዘክራል። #5ኛ) ከባቢሎን ዘመን አስቀድሞ የነበረው ብቸኛው የሰው ልጅ ቋንቋ (ግዕዝ) የሚገኘው ኢትዮጵያ/ቤተ ክርስትያን/ ውስጥ ነው። ይሄን ቋንቋ እኛ የቋንቋው ባለቤቶች ብናቃልለውም ቅሉ ዓለም ግን እጅግ የሚያከብረው ትልቅና ቀዳሚ ልሣን ነው። ይሄንን ደግሞ ራሳቸው ምዕራባዊያን ይመሰክራሉ። በዚህ ቋንቋ ብዙ እልፍ ድርሳናትና ምስጢራት ተከትበዋል። #6ኛ) ጻዲቁ አባታችን የሄኖክ የልጅ ልጅ #ኖኅ የተቀበረው ኢትዮጵያ/ጎንደር/ ውስጥ ነው። የሰው ልጅ ከሰማይ ከተጣሉት መላዕክት (ኔፍሊሞች) በተማረው ምድራዊ ጥበብ ምክንያት ልቦናው ከፈጣሪው ራቀ። ለምሳሌ ኮኮብ ቆጠራ፣ በአንገት የሚታሰሩ በጆሮ የሚንጠለጠሉ በእጅና እግር ጣቶች የሚታሰሩ ከንፈርንና ገላን የሚቀቡ ሁሉም ምድራዊ ጌጣጌቶች የመጡት ከወደቁት መላዕክት ወይም ከኔፍሊሞች ነው። እነዚህ መላዕክት የሰውን ልጅ ከፈጣሪው እንዲርቅ ዝሙትን፣ መዳራትን፣ ያለ አግባብ መብላትና መጠጣትን አስተማሩት። ✅በዚህም ምክንያት የሰው ልጅ ኅልቆ መሳፍርት ሀጢያትን በመስራቱ እግዚአብሔር ምድርን በንፍር ውኃ መላት። ሁሉም አለቁ። ኖኅና ቤተሰቦቹ ብቻ ቀሩ። ይህ ሰው መቃብሩ የሚገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። #7ኛ) ኖኅ ራሱንና ልጆቹን ከንፍር ውኃ ያዳነባት መርከቡን ያሳረፋት #ኢትዮጵያ_ጣና አካባቢ ከሚገኘው አራራት ተራራ ላይ ነው። #8ኛ) የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረው ከአራት ባህሪያተ ስጋ ነው። ከእነዚህም መካከል ደግሞ የተፈጠረበት እሳት ውኃና ነፋስ የተገኘው ከኢትዮጵያ ነው። ከዚህም በመነሳት አንዳንዶች #አዳምና_ሄዋን_ኢትዮጵያዊያን ናቸው ይላሉ። እውነት ነው። ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ነች። #ኢትዮጵያን_መጽሐፍ_ቅዱስ_ምን_አላት❓ ✅"እናንተም #ኢትዮጵያውያን ደግሞ በሰይፌ ትገደላላችኹ።" (ትንቢተ ሶፎንያስ ምዕ፡2፥12) ✅ የዔዴን ገነትን ከሚያጠጡ 4 ወንዞች(ፊሶን፣ግዮን፣ጤግሮስና ኤፍራጥስ) "የኹለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ ርሱም #የኢትዮጵያን ምድር ዅሉ ይከባ፟ል።"(ኦሪት ዘፍጥረት ምዕ፡2፥13) ✅"የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ #ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችኹምን ይላል እግዚአብሔር፦" (ትንቢተ አሞጽ ምዕ፡9፥7) ✅ " #የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየኹ፤" (ትንቢተ ዕንባቆም ምዕ፡3፥7) ✅ ይላል እግዚአብሔር፦ " #ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ፥"(ትንቢተ ሶፎንያስ ምዕ፡3፥10) ✅ "ሙሴም #ኢትዮጵያዪቱን አግብቷልና፥"(ኦሪት ዘኍልቍ ምዕ፡12፥1) ✅ " #ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።"(መዝሙረ ዳዊት ምዕ፡67፥31) ✅ "በእውኑ #ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን፤" (ትንቢተ ኤርምያስ ምዕ፡13፥23) ✅ "አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥኽ፤ #ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠኻቸው።"(መዝሙረ ዳዊት ምዕ፡73፥14) ✅ " #በኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ ላለች፥...መርከቦችንም በውሃ ላይ ለምትልክ ምድር ወዮላት! "(ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ፡18፥1-2) "የአባይን ውሃ በማንኪያ.." እንዲሉ አበው የኢትዮጵያን እጅግ ረቂቅ ምስጢር በጥቂቱ እንጂ ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም። ✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ለጓደኞቻችን #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞ ╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮ @EOTC2921 @Orthodox2921 ╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯

#ቢፈልግባትም_መልካሙ_ገበሬ •••✞✞✞•••✞✞✞•••✞✞✞••• ቢፈልግባትም መልካሙ ገበሬ አልተገኘባትም ከበለስዋ ፍሬ፤ #አዝ••• ለስልሶላት ነበር ሀይማኖት መሬቱ፤ ተቀጥሮላት ነበር አጥር ስርዓቱ፤ ተነቅሎላት ነበር ድንጋይ ፈተናዋ፤ ፍሬ ግን ታጣባት በመጨረሻዋ፤ #አዝ••• ፍሬ የሌለባት ቅጠል ስለሆነች፤ ተካይዋን በምግባር ስላላስደሰተች፤ መልካሙን ገበሬ ሊቆርጣት ተነሳ፤ ሌሎች እንዳይጠፉ በእርሷ የተነሳ፤ #አዝ••• ለንስሐ የሚሆን እድሜ እንዲሰጣት፤ ጠባቂ መልዐኳ ተማጸነላት፤ ምክር እና ተግሳጽ ይጨመርላት፤ ታፈራ እንደሆነ ለዓመት እንያት፤ #አዝ••• ልመናውን ሰምቶ ጌታውም ፈቀደ፤ ጥቂት እድሜ ሊሰጥ ሊታገስ ወደደ፤ ዳግመኛ ሲመጣ ፍሬ ካላፈራች፤ ተቆርጣ ወደ ቶን እሳት ትጣላለች፤

🌿🌾 #ይቺን_ዓመት_ተወኝ!🌾🌿 ✔ከዓመት እስከ ዓመት፦ ፍሬን ሳላፈራ፥ ደረቅ እንደሆንኩኝ፤ ✔በራድ ወይም ትኩስ፦ ሁለቱንም ሳልሆን፥ እንዲያው ለብ እንዳልኩኝ፤ ✔አለሁኝ በቤትህ፦ ለሙ መሬትህን፥ እያጎሳቆልኩኝ፤ ✔አውቃለሁ አምላኬ፦ ፍሬዬን ለመልቀም፥ እንዳመላለስኩህ፤ ✔ዛሬም ሳላፈራ፦ እሾህን አብቅዬ፥ ደርቄ ጠበቅሁህ፤ ✔ያልተደረገልኝ፦ ያላፈሰሰክብኝ፥ ያልሰጠኸኝ የለም፤ ✔ነገር ግን ይህ ሁሉ፦ አላርምህ አለኝ፥ አልለየኝም ከዓለም፤ ✔የማትሰለቸኝ ሆይ፦ ተነሥቼ እስክቆም፥ እባክህ ታገሠኝ፤ ✔የእኔን ክፋት ተወው፦ መልአክህን ሰምተህ፥ ይህችን ዓመት ተወኝ፤ ✔አውቃለሁ ታውቃለህ፦ ቀጠሮን ሰጥቼ፥ እንደማላከብር፤ ✔ብዙ ጊዜ አቅጄ፦ ብዙ ጊዜ ዝቼ፥ በወሬ እንደምቀር፤ ✔ዘንድሮስ…! እንዳልኩኝ፦ አምና ይሄን ጊዜ፥ ሰምተኸኝ ነበረ፤ ✔ምንም ሳልለወጥ፦ ዘንድሮዬ› አልፎ፥ በአዲስ ተቀየረ፤ ✔ፍሬ የማይወጣኝ፦ እኔን በመኮትኮት፥ እጆችህ ደከሙ፤ ✔እኔ ግን አለሁኝ፦ ዛሬም አልበቃኝም፥ በኃጢአት መታመሙ፤ ✔የቃልህን ውኃ በድንጋይ ልጅህ ላይ፦ ሳታክት ስታፈስ፥ ዘመን ተቆጠረ፤ ✔ወደ ልቤ ሳይሰርግ፦ ሕይወቴን ሳይለውጥ፦ እንዲያው ፈስሶ ቀረ፤ ✔ቃልህን ጠግቤ፦ እያገሳሁት ነው፥ ሌሎች እስኪሰሙ፤ ✔በቃልህ መኖር ግን፦ አልያዝህ አለኝ፥ ከበደኝ ቀለሙ፤ ✔ብዙ ጥቅስ አገኘሁ፦ ከቅዱስ መጽሐፍህ፥ ገልጬ አይቼ፤ ✔ከራሴ ላይ ብቻ፦ አንድ ጥቅስ አጣሁኝ፥ በበደል ተኝቼ፤ ✔ውጤቴ ደካማ፦ ትምህርት የማይሠርጸኝ፥ ተማሪ ብሆንም፤ ✔ይህችን ዓመት ተወኝ፦ ደግሞ ትንሽ ልማር፥ ታገሠኝ አሁንም፤ ✔እባክህ አልቆረጥ፦ በቅዱስ መሬትህ፥ ልቆይ ፍቀድልኝ፤ ✔ያፈሩት ቅዱሳን፦ የፍሬያቸው ሽታ፥ መዓዛ እንዲደርሰኝ፤ ✔የተሸከምከኝ ሆይ፦ ዛሬም ተሸከመኝ፥ አትሰልቸኝ አደራ፤ ✔ማን ይታገሠኛል፦ ጠላት እየሆንኩት፥ አይሠሩ ስሠራ፤ ✔አታውጣኝ ከቤትህ፦ ብዙ ቦታ አልይዝም፥ ፍሬ ስለሌለኝ፤ ✔ስፍራ የማያሻኝ፦ ቤት የማላጣብብ፥ ፍሬ አልባ በለስ ነኝ፤ ✔ቦታስ የሚይዙት፦ ባለ ምግባሮቹ፥ ቅዱሳንህ ናቸው፤ ✔ልክ እንደ ዘንባባ፦ የተንዠረገገ፥ ተጋድሎ ጽድቃቸው፤ ✔ከሊባኖስ ዝግባ፦ እጅጉን የበዛ፥ ገድል ትሩፋታቸው፤ ✔እኔ አይደለሁም፦ ቦታስ የምትይዘው፥ የአንተው እናት ናት፤ ✔ሥሮቿ በምድር፦ ጫፎቿ በሰማይ፥ ሲደርሱ ያየናት፤ ✔ይቺን ዓመት ተወኝ፦ ከሥርዋ እሆናለሁ፥ ባፈራ ምናልባት፤... ✔ይቺን ዓመት ተወኝ፦ እባክህ አምላኬ፥ አንድ ዓመት ምንህ ናት፤ ✔ሺህ ዓመት አንድ ቀን፦ አይደለም ወይ ለአንተ፥ ዓመት ኢምንት ናት!፤ ✔ይሄ ዓመት አልፎ፦ ዳግም ‹ዓመት ሥጠኝ›፥ እስከምልህ ድረስ፤ ✔እባክህን ጌታ፦ ይቺን ዓመት ተወኝ፥ የወጉን እንዳደርስ!። ✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ለጓደኞቻችን #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞ ╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮ @EOTC2921 @Orthodox2921 ╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯

🌿🌾🍇 ሉቃስ ምዕ፡13፤1-9 🍇🌾🌿 #ንስሓ_ባትገቡ_ዅላችኹ_እንዲሁ_ትጠፋላችኹ 1፤በዚያን፡ጊዜም፡ሰዎች፡መጥተው፡ጲላጦስ፡ደማቸውን፡ከመሥዋዕታቸው፡ጋራ፡ስላደባለቀው፡ስለገሊላ፡ሰዎች፡አወሩለት። 2፤ኢየሱስም፡መልሶ፡እንዲህ፡አላቸው፦እነዚህ፡የገሊላ፡ሰዎች፡ይህ፡ስለ፡ደረሰባቸው፥ከገሊላ፡ሰዎች፡ዅሉ፡ይልቅ፡ኀጢአተኛዎች፡የኾኑ፡ይመስሏችዃልን፧ 3፤እላችዃለኹ፥አይደለም፤ነገር፡ግን፥ንስሓ፡ባትገቡ፡ዅላችኹ፡እንዲሁ፡ትጠፋላችኹ። 4፤ወይስ፡በሰሌሆም፡ግንቡ፡የወደቀባቸውና፡የገደላቸው፡እነዚያ፡ዐሥራ፡ስምንት፡ሰዎች፡በኢየሩሳሌም፡ከሚኖሩት፡ዅሉ፡ይልቅ፡በደለኛዎች፡ይመስሏችዃልን፧አይደለም፥እላችዃለኹ፤ 5፤ነገር፡ግን፥ንስሓ፡ባትገቡ፡ዅላችኹ፡እንደዚሁ፡ትጠፋላችኹ። 6፤ይህንም፡ምሳሌ፡አለ፦ላንድ፡ሰው፡በወይኑ፡አትክልት፡የተተከለች፡በለስ፡ነበረችው፥ፍሬም፡ሊፈልግባት፡መጥቶ፡ምንም፡አላገኘም። 7፤የወይን፡አትክልት፡ሠራተኛውንም፦ እንሆ፥ከዚች፡በለስ፡ፍሬ፡ልፈልግ፡ሦስት፡ዓመት፡እየመጣኹ፡ምንም፡አላገኘኹም፤ ቍረጣት፤ስለ፡ምን፡ደግሞ፡መሬቱን፡ታጐሳቍላለች፧አለው። 8፤ርሱ፡ግን፡መልሶ፦ጌታ፡ሆይ፥ዙሪያዋን፡እስክኰተኵትላትና፡ፋንድያ፡እስካፈስላት፡ድረስ፡በዚች፡ዓመት፡ደግሞ፡ተዋት። 9፤ወደ፡ፊትም፡ብታፈራ፥ደኅና፡ነው፤ያለዚያ፡ግን፡ትቈርጣታለኽ፡አለው። 🙏✞ ሁላችንም ሳናፈራ እንዳንቆረጥ ንስሐ ገብተን በፊቱ መልካም ፍሬን ካስገኙት ተርታ እንድንሆን የአምላካችን ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን። ✞🙏

❖ ይኽቺ ሥላሴ የገቡባት ኀይመተ አብርሃም (የአብርሃም ድንኳን) የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት፤ ይኸውም ሥላሴ ወደ አብርሃም ድንኳን እንደገቡ ኹሉ፤ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያምም፤ አብ ለአጽንኦ፣ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፣ ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ለመዋሐድ ዐድረዋል (ሉቃ ፩፥፴፭)፤ በመኾኑም አማናዊቷ የሥላሴ ማደሪያ የአብርሃም ድንኳን እመቤታችን ብቻ ናት፡፡ ❖ ሊቁም በነገረ ማርያም ይኽነን ምስጢር ሲገልጽ "ወይእቲ ኀይመት ትትሜሰል በድንግል ወዕደው አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እሙንቱ፤ አብ አጽንኣ፣ ወወልድ ተሰብአ እምኔሃ፣ ወመንፈስ ቅዱስ ቀደሳ ከመ ትጹር አምላከ በከርሣ" (ያቺ ድንኳንም በድንግል ትመሰላለች፤ ሰዎቹም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው፤ አብ አጸናት፣ ወልድም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፣ መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ቃል አምላክን ትሸከም ዘንድ ለያት) በማለት ተርጉሞታል፨ ❖ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ በሰላምታ መጽሐፉ ላይ መጽሐፉ፦ "ኀይመተ አብርሃም አብ ሰላም ለኪ፤ ዘኮንኪ ከመ ተድባብ ሰላም ለኪ" (እንደ ጥላ የኾንሽ የአባት አብርሃም ድንኳን ሰላምታ ይገባሻል) በማለት አመስግኗታል፡፡ ❖ ይኽ አብርሃም የተቀበለውን የተስፋ ቃል ሊቃውንት ሲተረጒሙት "ኦ አኃውየ በይነ መኑ እንከ ዘይቤ እግዚአብሔር ለአብርሃም አመ ከመ ዮም እገብእ ኀቤከ አኮኑ እግዝእትነ ማርያም ይእቲ ዘወፅአት እምነ ሥርው ለአዳም ..." (ወንድሞቼ ሆይ እግዚአብሔር አብርሃምን እንደዛሬው ኹሉ ወደአንተ ተመልሼ እመጣለኍ ያለው ስለማን ይመስላችኋል? ከአዳም ሥር ወጥታ፤ ከኖኅ አብራክ ተገኝታ፤ ወደ አብርሃም አብራክ ልትከፈል፤ ሥላሴ በአብርሃም ቤት በእንግድነት ተገኝተው፤ ከአብርሃም ዘር ከእመቤታችን የእግዚአብሔርን ልጅ ሰው መኾን ስለርሷ የተናገሩላት እመቤታችን ድንግል ማርያም አይደለችምን፤ ስለዚኽ እግዚአብሔር ስለ እመቤታችን ጥንታዊ የልደቷን አመጣጥ በየጊዜው ምልክት እንደሚሰጥ ልብ አድርገን ማስተዋል ይገባናል) በማለት አብራርተው ተርጒመዋል፡፡ ❖ ሊቁ አባ ሕርያስቆስም በቅዳሴው በቊ ፴፪ ላይ "ተናግዶቱ ለአብርሃም" (የአብርሃም እንግድነቱ አንቺ ነሽ) በማለት ምስጢሩን ጠቅልሎ የገለጠውን ይኽነን ድንቅ ምስጢር፤ ሊቁ በነገረ ማርያም ላይ በስፋትና በጥልቀት፡- "ወዓዲ ኀይመት ዘአብርሃም ዘውስቴታ ተአንገደ እግዚአብሔር አኮ ከማሁ ዘኮነቶ ምጽላለ በእንተ ምዕር አላ ኮነቶ እመ ወተከድነ ሥጋሃ ወረሰዮ አሐደ ምስለ መለኮቱ" (ዳግመኛም እግዚአብሔር (በሦስትነት) በዕንግድነት ያረፈባት የአብርሃም ድንኳን አንቺ ነሽ፤ ለጥቂት ጊዜ ብቻ መጠለያን፣ መጠጊያን የኾነቺው አይደለም፤ እናትን ኾናው ሥጋዋን ተዋሕዶ ከመለኮቱ አንድ አደረገው እንጂ) በማለት በአብርሃም ድንኳን ብትመሰልም እንኳ ክብሯ ከፍ ያለ፤ ለዘላለም የአምላክ ማረፊያውና እናቱ መኾኗን አብራርቶ ገልጧል፡፡ ❖ ሊቅነትን ከንግሥና ጋር ያስተባበረው ዐጼ ዘርዐ ያዕቆብ በመጽሐፈ ሥላሴ መጽሐፉ ላይ፦ "ኦ ብእሲ ዘትትከሓድ አይኑ ዕለት ለአግዚአብሔር ሰገዱ ሎቱ ምስለ መላእክቲሁ በዕሪና እምነ ኩሉ ፍጡራኒሁ..." (ሥላሴን የምትክድ አንተ ሰው ሆይ ከፍጡሮች ወገን በመላ እግዚአብሔርን ከመላእክቱ ጋር በአንዲት ዕሪና የሰገዱለት በማናቸው ዕለት ነው? በማናቸው ዕለት እግዚአብሔር ከፈጠራቸው መላእክቱ ጋር ተካክሎ እግሩን ታጠበ? በማናቸው ዕለት በሰው መጠለያ በታች ከፈጠራቸው መላእክት ጋር ተካክሎ ተጠለለ? በማናቸው ዕለት ከፈጠራቸው መላእክት ጋር ተካክሎ እግዚአብሔር በላ? በማናቸው ዕለት ከአዳም ልጆች ወገን ሰው ወደ ፈጣሪው በለመነ ጊዜ መላእክቱ ከፈጣሪያቸው ከእግዚአብሔር ጋር ተካክለው እንዲኽ አድርግ መቼ አሉ? አንተ ሥላሴን የካድኽ ከሓዲ ፍጡራን መላእክትን ፈጣሪ ከኾኑ ከሥላሴ ጋር በመተካከል እንዲሰገድላቸው ለምን ታመጣቸዋለኽ? ፈጡራን መላእክትን ፈጣሪ ከኾኑ ከሥላሴ ጋር ተካክለው በአብርሃም ቤት እንደተጠለሉ፤ እግራቸውን እንደታጠቡ፤ ዐብረው እንደበሉ አድርገኽ ለምን ታስተካክላለኽ? አንተ ከእኛ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አንድነት የኾንኽ ክርስቲያን አንዱ እግዚአብሔር ነው፤ ኹለቱ መላእክት ናቸው አትበል) በማለት አስፍቶ ይጽፋል፨ ✞ በቤተ አብርሃም የገቡ ሥሉስ ቅዱስ ሆይ ዘወትር በቤተ ልቡናችን ውስጥ ግቡልን ✞ ✍ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ

🌿🌾🍇 ✞✞✞ #ስላሴ ✞✞✞ 🍇🌾🌿 ❖ አብርሃም ከደግነቱ ብዛት እንግዳን ከመውደዱ የተነሣ ድንኳኑን በተመሳቀለ ጎዳና ሠርቶ የወጣ የወረደውን ያለፈ ያገደመውን ሲቀበል የሚኖር በሥራው ኹሉ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ጻድቅ ነበር (ዘፍ 18:1-10)፡፡ ጽድቁም ሊታወቅ ስድስት ሰዓት ላይ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ፤ በመምሬ ዛፍ ሥር እግዚአብሔር በአንድነት በሦስትነት ተገለጸለት ዐይኑን አቅንቶ ሲመለከት፤ ሥላሴ በአምሳለ ዕደው ቆመው አይቶ፤ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፤ ወደ ምድርም ሰገደ። ❖ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ሰለዚኽ ነገር በድጓው ላይ፦ "ዮም አብርሃም ሰገደ ለፈጣሪሁ ሶበ ነጸረ ዋሕደ በሥላሴሁ" (ዋሕደ ባሕርይ የኾነ እግዚአብሔርን በአካላዊ ሦስትነቱ ባየው ጊዜ አብርሃም ዛሬ ለፈጣሪው ሰገደ) ይላል፨ ❖ የተገለጡለት ሰዓቱ ቀትር (ስድስት) ሰዓት በዕንጨት ሥር በሰው አምሳል መኾኑ ቀደምት ሊቃውንት ሲያራቅቁት በአብ፣ በመንፈስ ቅዱስ፣ በራሱም ፈቃድ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ዘመኑ ሲፈጸም የአብርሃምን ባሕርይ ተዋሕዶ ፍጹም ሰው ኾኖ በስድስት ሰዓት በዕንጨት መስቀል ላይ ለቤዛ ዓለም የሚሰቀል መኾኑን ያጠይቃል ይላሉ፨ ❖ ይኽነን ይዞ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በሕማማት ሰላምታው፦ "ለአብርሃም አብ ቀዳሚ ዘአስተርአይኮ ክርስቶስ ቀትረ ታሕተ ዕፀ ድርስ ተሰቀልከ ከመ እቡስ ስብሐት ለከ" (ምስጋና የተገባኽ ጌታ ድርስ በሚባል የዛፍ ዐይነት ሥር በስድስት ሰዓት ለአባታችን አብርሃም ቀድሞ የተገለጥኽለት ክርስቶስ ሆይ እንደ በደለኛ ተሰቀልኽ) ይላል፨ ❖ ከዚኽ በኋላ "አቤቱ በፊትኽስ ሞገስ አግኝቼ እንደኾነ ባሪያኽን አትለፈኝ ብዬ እለምናለኍ፤ ጥቂት ውሃ ይምጣላችኍ፤ እግራችኹን ታጠቡ፤ ከዚኽችም ዛፍ በታች ዕረፉ…" በማለት ተናግሯል፡፡ "በፊትኽ ሞገስን አግኝቼ" ብሎ አንድነታቸውን፤ "ውሃ ይምጣላችኍ፣ ዕረፉ፣ ትኼዳላችሁ" ብሎ የሦስትነታቸውን ምስጢር ገልጾአል፡፡ ❖ ይኸው ሊቅ ያሬድ ይኽነን ይዞ በድጓ ላይ፦ "ይቤሎሙ ዮም አብርሃም ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አመጽእ ማየ ወአሐጽብ እገሪክሙ ወእርከብ ሞገሰ በቅድሜክሙ" (አብርሃም ዛሬ አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስን ባለሟልነትን በፊታችሁ አገኝ ዘንድ ውሃን አምጥቼ እግራችኹን አጥባለሁ አላቸው) ይላል ❖ ይኽቺ አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፍለው በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገን እግዚአብሔር የተገለጠባት ዛፍ፤ አንድነት ሦስትነት በጐላ በተረዳ ነገር የታወቀባት ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድን በድንግልና የወለደች የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ መኾኗን፤ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ እንዚራ ስብሐት መጽሐፉ ላይ "አንቲ ውእቱ ዕፀ ድርስ ዘለአብርሃም በርስአኒሁ ዘብኪ አጽለለ እግዚአብሔር በሥላሴሁ" (ለአብርሃው በእርጅናው ወቅት፤ እግዚአብሔርን በሦስትነት ያስጠለለብሽ የወይራ ዕንጨት አንቺ ነሽ) በማለት ሲገልጥ፤ ❖ ዳግመኛም በዚኹ መጽሐፉ፡- "እንቲ ውእቱ ዕፀት ዘነበርኪ ጥቃ ኀይመት፣ ዘብኪ አጽለሉ ሠለስቱ አጋዕዝት" (ባንቺ ሦስቱ ጌቶች (ሥላሴ) የተጠለሉብሽ በድንኳን አጠገብ የቆምሽ ዕንጨት አንቺ ነሽ) በማለት በአንድነቱ ምንታዌ (ኹለትነት)፣ በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት) ለሌለበት አምላክ የሦስትነቱ የአንድነቱ ምስጢር መገለጫ የሥላሴ ማደሪያ መኾኗን መስክሯል፡፡ ❖ ከዚኽም ምስጢር የተነሣ አብርሃምም ሳራን “ሦስት መስፈሪያ የተሠለቀ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፤ ለውሺውም እንጎቻም አድርጊ” በማለት የተገለጸለትን የሦስትነት የአንድነት ምስጢርን አጒልቶ ተናግሯል፡፡ ❖ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ይኽነን ይዞ በሕማማት ሰላምታው ላይ፦ "ግናይ ለክሙ ሥሉስ ቅዱስ ነገሥተ ሰብዐቱ አብያት እለ በላዕክሙ ውሣጤ ኀይመት አሐደ ኅብስተ ትሥልስት" (ከሦስት መስፈሪያ ዶቄት የተጋገረ አንድነት ያለው ኅብስትን በድንኳን ውስጥ የተመገባችሁ የሰባት ቤቶች (ሰማያት) ነገሥት ሆይ ለእናንተ መገዛት (ምስጋና) ይገባል) ይላል፨ ❖ አብርሃምም በደስታ ኾኖ መዐር፣ ወተት፣ ያዘጋጀውን ጥጃ አመጣላቸው፤ እነርሱም ደስ ይበለው ብለው በግብር አምላካዊ ተመግበዋል፤ መላእክት ሎጥ ቤት፤ ቅዱስ ሩፋኤል ጦቢት ቤት ተመገበ የተባለው አንድ ነው፤ እሳት ቅቤ በላ እንደማለት ብቻ ነው፨ ❖ ይኸውም ወተትና መዐር መመገባቸው ኦሪትን ወንጌልን መሥራታቸውን ሲያጠይቁ ነው፤ መዐር የኦሪት፤ ቅቤ የወንጌል ምሳሌ ነው፨ ማር ለጊዜው ሲይዝ የሚለቅ አይመስልም፤ ግን ይለቃል ኦሪትም ስትሠራ የምታልፍ አትመስልም ነበር ግን በኽዋላ ዐልፋለች፨ ወተት የወንጌል ምሳሌ ነው፤ ይኽ ወተት ለጊዜው የሚለቅቅ ይመስላል በኽዋላ ሲያጥቡት አይለቅም ወንጌልም ለጊዜው ስትሠራ የምታልፍ ትመስል ነበር፤ በኽዋላ ግን ጸንታ የምትኖር ኾናለችና በማለት መተርጉማን ያራቅቁታል፡ ከሦስቱ አንዱ እግዚአብሔር ወልድ አብርሃምን "የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለኍ፤ ሚስትኽ ሳራም ልጅን ታገኛለች" በማለት ዘመኑ ሲፈጸም እግዚአብሔር ወልድ ከቤተ አብርሃም ከተገኘች ከእመቤታችን የመወለዱንና፤ በሳራ የተመሰለች ወንጌል ምእመናንን እንደምታስገኝ በምስጢር ገልጾለታል፤ ቅዱስ ጳውሎስም አካላዊ ቃል በሰጠው ተስፋ መሠረት ከነገደ አብርሃም የመወለዱን ነገር ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ "በሕይወታቸው ኹሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ኹሉ ነጻ እንዲያወጣ፤ በሥጋና በደም እንዲኹም ተካፈለ፣ የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም" በማለት ገልጾታል (ዕብ ፪፥፲፭-፲፮)፡፡

​​✞✟ #ምሬሀለው_በለኝ ✟✞ ምሬሀለው በለኝ ስለ ድንግል ማርያም(2) መሀሪው መዳኒአለም ይቅር ባይ እንዳንተ የለም //2// በሀጥያት ድንኳን ውስጥ ይብቃ መቀመጤ የቀናውን መንፋስ አድሰው በውስጤ የምህረት አይኖችህ ይዩኝ በይቅርታ ስለ ድንግል ማርያም እስራቴን ፍታ(2) #አዝ----------✞---✞---✞------- ቸል በማለቴ የደምህን ዋጋ ተመልሼ ገባሁ ከጥፋት መንጋጋ ሰላሜ ደፍርሶ ተቅበዝባዥ ሆኛለው ስለ እናት ብለህ ማረኝ እልሀለው ስለ ድንግል ማርያም ማረኝ እልሀለው #አዝ----------✞---✞---✞------- በከንቱ መሻቴን ስጋ ነብሴን ቀብሮ አቅም አጥቻለው አጥንቴ ተሰብሮ ከበረዶ ይልቅ ነጭ እንድታደርገኝ ስለ ድንግል ማርያም ከሀጥያቴ ጠበኝ/2 #አዝ----------✞---✞---✞------- ከንፋሮቼን ከፍተህ ልቁም ለምስጋና አንተን የጋረደኝ ጣሪያዬ ይነሳና አልብሰኝ ፅድቅህን ይቅር መራቆቴ ስለድንግል ማርያም መልሰኝ ከቤቴ(2) #አዝ----------✞---✞---✞------- ✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ለጓደኞቻችን #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞ ╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮ @EOTC2921 @Orthodox2921 ╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯

........ ➲➨በዚህ ድርጊት ቅድስና እና ንጽሕና ይጠፋል፡፡ ዓይነ ጥላና የዝሙት መንፈስ ይህንን ጠባይ ከልጅነታቸው ጊዜ ጀምሮ በማውረስ እስከ አሁን ሕይወታቸውን በማቃወስ የሚጫወትባቸው አሉ፡፡ የዚህ አንዱና ዋነኛው ችግር የተፈጥሮን ሩካቤ ሳያውቁ ግለ ወሲብን ማጣጣም ነገ በትዳር መሃል ባለው ሕገ ሩካቤ ጣዕም ይቸገራሉ፡፡ ➲➨ሁለተኛ የወጣቶች ግለ ወሲብ ነው፡፡ ይህም ወጣቶች በወሲብ ፊልም፣ በመጠጥ፣በሱስ እና በሌሎችም ነገሮች በመገፋፋት፣አጋንንት ተጨምሮበት የሚፈጽሙት ግለ ወሲብ ነው፡፡ ይህ አብዛኛውን ጊዜ ዓይነ ጥላ ሴቷን ከወንድ፣ወንዱን ከሴት አላስቀርብ እያለ የሚገረግርባቸው ወጣቶች የሚፈጽሙት ነው፡፡ እራሳቸውን ከተቃራኒ ጾታ በማራቅ ደስታን ለማግኘት ዓይነ ጥላቸው በግለ ወሲብ እንዲጠቁ እና እራሳቸውን እንዲደብቁ ያደርጋቸዋል፡፡እንዲሁም የፍትወት እሳት ድንገት ሲያቃጥላቸው ለማብረድ፣እርካታን ለማግኘት የሚያውቁትን ሰው በሕሊና በማሰብ፣ በምስል በመከሰት ይፈጽማል፡፡ ➲➨ሦስተኛው የባለ ትዳሮችና የእጮኛሞች ግለ ወሲብ ነው፡፡ ባል እና ሚስት፣እጮኛሞች በሥራ ምክንያት ሲራራቁ፣ሲጣሉ፣ሲኳረፉ፣ሲለያዩ የሚፈጽሙት ነው፡፡ ይህ ደግሞ አጋንንቱ የጸብ ወይም የጥል ጊዜያቸውን ለማስረዘም እና ሩካቤያቸውን ለማሰልቸት ይጠቀምበታል፡፡ አንዳንዴም ባለ ትዳሮች ከትዳራቸው ውጪ ያለን ሰው በሕሊና፣በምናብ በማሰብ ይፈጽሙታል፡፡ ይህ ድርጊት ደግሞ ከእውነተኛው ዝሙት ልዩነት የለውም፡፡ ➲➨አራተኛ ሰዎች ሰይጣንን ያስለመዱት ግን ሰይጣን መልሶ የሚጫወትባቸው ግለ ወሲብ ነው፡፡ ይህም ሰይጣንና የእኛ አባቶች የማያውቁት በዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ የሚፈጸም ግለ ወሲብ ነው፡፡ አንደኛው በስካይ ፒ የሚፈጸም ግለ ወሲብ ነው፡፡ ከእውነተኛው ሩካቤ ብዙም የማይለይ ነው፡፡ እውነት የሚያስመስለው ሁለቱም እየተያዩ ስለሚፈጽሙ ደስታውና እርካታው የገሐዱን ሩካቤ ይመስላቸዋል፡፡ ሁለተኛው ሰይጣን የማያውቀው ግን እኛ ያስለመድነው ፎን ሴክስ እና ቻት ሴክስ የሚባል ነው፡፡ ስለ እውነት እናውራ ከተባለ ፎን ሴክስ፣ቻት ሴክስ እና በስካይ ፒ የሚፈጸም ግለ ወሲብ እኛ ሰይጣንን ያስለመድነው እንጂ እሱ እኛን ያስለመደን አይደለም፡፡ በተለይ ፎን እና ቻት ሴክስ ከምናውቃቸውና ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር የሚፈጸም ስለሆነ እራስን በእግዚአብሔር ፊት ማርከስ እና መናቅ ካልሆነ በስተቀር በራሳችን የምናመጣው ጣጣ ነው፡፡ ➲➨ተወዳጆች ሆይ ዓይነ ጥላና የዝሙት መንፈስ ውስጣችን ካለ ይህ ክፉ ድርጊት እንደ ኮሶ በመጣባት ለጸያፍ ሕይወት ይዳርገናል፡፡ የዚህ ድርጊት መጨረሻው ደናግሎች ድንግልናቸውን፣ ቅድስናቸውን፣ ንጽህናቸውን ያጎድፍባቸዋል፡፡ ወጣቶችንና ባለ ትዳሮችን ደግሞ ከተፈጥሮ ሩካቤ በማስፈንገጥ የሞራል ውድቀት ውስጥ ይከታቸዋል፡፡ ➲➨ወዳጆቼ በግለ ወሲብ ምከንያት በተለይም በወንዶች ላይ ዘርን ያለቦታው ማፍሰስን ያስከትላል፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ ኃጢአት ነው፡፡ ላዘውም ኃጢአተ አውናን፡፡ ምናልባት ብዙዎች እርግዝናን ከመከላከል ጋር በማያያዝ የሚፈጽሙት ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን ተግባረ አውናን በመሆኑ ያስቀጣል፡፡ የከበረውን የወንድ ዘር ያለ ቦታው ማፍሰ ተገቢ ስላልሆነ፡፡ ዘርን በግለ ወሲብ ማፍሰስ በወገባችን ያለን ልጅ በሚዳ ላይ እንደመጣል ነው፡፡ ሆን ተብሎ ዘርን ማፍሰስ ትልቅ ኃጢአት ነው፡፡ በግለ ወሲብ ጊዜ ዘርን ማፍሰስ የእርካታ ምልክት ቢሆንም በእኛ ደስታ ውስጥ ማለትም በሚፈሰው ዘር ውስጥ ያሉት ልጆች ናቸው፡፡ የሚሳዝነው ወልደን ካሳደግናቸው ልጆች ዘርን ከማህጸን ውጪና በግለ ወሲብ በማፍሰሳችን የማናውቃቸው የበተናቸው ልጆች ይበልጣሉ፡፡ ➲➨ወዳጆቼ የሰው ልጅ ዘር በእግዚአብሔር ዘንድ ክብር ነው፡፡ እግዚአብሔር ልጆችን በማህጸን ለመፍጠር የሚጠቀምበት አንዱ የሰው ልጅ ዘር ነው፡፡ ይህ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ጥበብ የሚገለጥበትን የሰው ዘር ያለ ቦታው ማፍሰስ ተገቢ አይደለም፡፡ አባቶቻችን ይህን ድርጊት ‹‹ኃጢአተ አውናን›› በማለት ይገልጹታል፡፡ ➲➨የይሁዳ ልጅ ዔር የሚባል ልጅ ነበረው፡፡ እሱም ትዕማር የምትባል ልጅ አግብቶ ይኖር ነበር፡፡ የይሁዳ ልጅ ዔር ግን በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ ክፉ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ዔርን ቀሰፈው ሞተም፡፡ ይሁዳም የዔርን ወንድም ልጁ አውናንን ‹‹ወደ ወንድምህ ሚስት ግባ፣አግባትም፣ለወንድምህ ዘር አቁምለት›› አለው፡፡ አውናንም እንደ ወንድሙ ዔር ክፉ ነበርና ለወንድሙ ዘር እንዳይተካለት ከትዕማር ጋር ሩካቤ ሥጋ ሲፈጽም ዘሩን ከማህጸንዋ ውጪ በምድር ላይ ያፈሰው ነበር፡፡ በማህጸን ጽንስን የሚጠቀልለው እግዚአብሔር የአውናንን ተንኮልና ግፍ ተመለከተ፡፡ በአጸያፊ ድርጊቱ እግዚአብሔር አውናንን ቀሰፈው እንደ ወንድሙ ዔር ሞተ፡፡ /ዘፍ 38÷6-10/ ➲➨እግዚአብሔር በሐዲስ ኪዳን ንስሐን ባይሰጠን ኖሮ፣በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ባይታረቀን ኖሮ ዘርን ከማህጸን ውጪና በግለ ወሲብ እያፈሰስን፣ዘርን ያለ ቦታው ስናውለው፣ስንጥለው እንደ አውናን በተቀሰፍን ነበር፡፡ ምህረቱ እና ቸርነቱ ይዞን ይኸው ከነ በደላችን አለን፡፡ በዓለማችን ላይ በሕይወት ካሉት የሰው ልጆች ይልቅ የመፈጠር ዕድል እያላቸው ግን ባልባሌ ቦታ በሚፈስ ዘር ልጆች የመሆናቸው እድል የተጨናገፉ ይበልጣሉ፡፡ ስለዚህ ስንት ጳጳሳት፣አገር መሪዎች፣ለወገንና ለአገር የሚጠቅሙ ሰዎች የሚሆኑትን ዘርን ያለ ቦታው በማፍሰስ ምክንያት እያጠፋን ስለሆነ ከዚህ ደርጊት ልንታቀብ ይገባል፡፡ ➲➨ለዚህም ነው እኛን "ያልተቀሰፈው እግዚአብሔር የታገሰው ትውልድ" ያልኩት፡፡ ምክንያቱም አውናን ተፈጥሮአዊ ሩካቤን እየፈጸመ በተንኮሉ ዘሩን ከማሕጸን ውጪ ያፈስ ስለነበር ነው እግዚአብሔር የቀሰፈውና የሞተው፡፡ እኛ ግን ተፈጥሮአችን ባልሆነና ለባሕርያችን የማይስማማውን ግለ ወሲብን እየፈጸምን አለመቀሰፋችን እግዚአብሔር የንስሐ እድል እየሰጠንና ለንስሐ እያጨን መሆኑን ያስረዳል፡፡ ‹‹ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት አልፈቅድ›› ያለው ለዚህ ነው፡፡ /ሕዝ 33÷11/ ➲➨ተወዳጆች ሆይ ከዚህ ጸያፍ እና አጋንንታዊ ተግባር ለመላቀቅ ድርጊቱን የሚጸየፍ ሕሊና፣ለንስሐ የጀገነ ልቦና ያስፈልገናል፡፡ እንዲሁን ንስሐ፣ጾም፣ ጸሎት በተለይም ስግደት ያስፈልገናል፡፡ በተረፈ መምህራንንና አባቶችን፣ ካህናትንና የንስሐ አባቶቻችን በማማከር፣ እግዚአብሔርን በመማጸን ከዚህ ሰይጣናዊ ተግባር ለመላቀቅ መሞከር ሳይሆን መተግበር አለብን፡፡ ➲➨እባካችሁ በልጅነታችን የገባው ዓይነ ጥላና የዝሙት መንፈስ በግለ ወሲብ እንዳይጫወትብን፣ ነገአችንን እንዳያበላሽብን፣ ከወደደን በሞቱ ሕይወቱን ከሰጠን ከአምላካችን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዳያቆራርጠን አጋንንቱን ልንነቃበት ይገቃል፣ እስከ ዛሬ የተጫወተብን ይበቃል፡፡ ‹‹ከትውልዱ ማን አስተዋለ›› ት.ኢሳ 58÷3 ከተማርንበት ለወዳጆቻችን #Share በማድረግ እናሳውቃቸው፨ ✟✞ አምላካችን ሆይ ጥበብና ማስተዋሉን፤ ልብና ልቦናውን፤ ጥንካሬና ብርታቱን እምነትና የዋህነቱን፤ ትግስትና ፍቅሩን•••ለኛ ለባሮችህ ትሰጠን ዘንድ አማላጅ በምትሆን በቅድስተ ቅዱሳን በእመአምላክ በንፅህት ቅድስት ድንግል ማርያም፤ እንዲሁም አንተ ባከበርካቸው ቅዱሳን ፀሎትና ቃልኪዳን ማረን ይቅር በለን፡፡ አቤቱ ፈጣሪያችን ሆይ እኛ ሀጢያተኛ ባሮችህን ለንሰሀ ሞት አብቃን፡፡ •••✞ አሜን ✟ አሜን ✟ አሜን ✞•••

#ኃጢአተ_አውናን__ግለ_ወሲብ_በወንዶች_እና_በሴቶች_ላይ❌➮➮➱ ▮ያልተቀሰፈው እግዚአብሔር የታገሰው ትውልድ❕‼▮ ✞✟ #የቅዱሳን_አምላክ_ሥሉስ_ቅዱስ_ምስጢሩን_ይግለጥልን፡፡ ✟✞ ➲➨በዚህ ትምህርት በዘመናችን በአሳዛኝ ሁኔታ ወጣቱን እየተፈታተነ የዲያብሎስ እስረኛ ያደረገውን ችግር እንመለከታለን፡፡ ወዳጆቼ ዕድሜ ዘመናችንን የጥንት ጠላታችን የሰይጣን መጫወቻ እንዳንሆን ሐፍረትን ለጊዜው ገፈፍ አድርገን ፍሬ ፍሬው እንማማራለን፡፡ ምክንያቱን በግለ ወሲብ የሚጠቁ ወንድም እህቶቻችን ችግራቸውን ለሰው ለማማከር፣ንስሐ ለመግባት አንዱ ችግራው ሐፍረት ስለሆነ፡፡ ስለዚህ ‹‹ወይ ቄሱ›› ከማለት ተላቃችሁ የዓይነ ጥላውን የተንኮል ምስጢር አንብቡ፡፡ ➲➨ዓይነ ጥላ እግዚአብሔር በሰጠን ሳይሆን እራሱ በቀደደልን የክፋት እና የጨለማ መንገድን በመምራት ብሎም ሕይወትን በማበላሸት ተወዳዳሪ የለውም፡፡ የዚህ መንፈስ አንዱ ጠባዩ አፈንጋጭነቱ ነው፡፡ ይህንን የማፈንገጥ ጠባይ በእኛ ሕይወት ውስጥ በማስለጥ ኢ-ሩካቤ እና ከተፈጥሮ ውጪ የሆኑ ማወሰቦችን ያለማምደናል፡፡ ከዚህ ቀደም እንዳየነው ዓይነ ጥላ ከማሕፀን፣ ከአራስነት እና ከጊዜ በኃላ ወደ ሕይወታችን በመግባት በራሱ ተንኮል በመቃኘት፣ከተፈጥሮ ያፈነገጠ ሕይወት እንዲኖረን ያደርገናል፡፡ በዚህ ጠባዩ የእሱን መርገም፣በእኛ ሕይወት በመድገም የእርግማን ትውልድ ያደርገናል፡፡ ከሁሉም የሚከፋው በመናፍስቱ የሚመጣ ግለ ወሲብ ነው፡፡ ምክንያቱም መልሶ በማገርሸት ይጠምደናል፡፡ ➲➨ግለ ወሲብ በሰው ልጆች ሕይወት ጥንታዊ ኃጢአት ከሆነው አንዱ ነው፡፡ ግለ ወሲብ በሰው ልጆች ዘንድ መቼ እንደተጀመረ ጥንታዊ የታሪክ ዳራውን ስናይ ቀደምት ጀማሪዎቹ ሮማዎች ናቸው፡፡ ዘመኑም ከክርስቶስ ልደት በፊት በ4000 ዓመተ ዓለም ገደማ ነው፡፡ ግለ ወሲብ በሮማ ኢምፓየር በዓለም ላይ እጅጉን እንደተስፋፋ የታሪክ መዛግብት ይነግረናል፡፡ ከሮማ በመቀጠል ግብጾች ከክርስቶስ ልደት በፊት በ3000 ዓመተ ዓለም እንደ ጀመሩ ተመዝግቧል፡፡ ጥንታውያን ሮማዎችም ሆኖ ግብጾች ግለ ወሲብን ከማህበራዊ እድገታቸው ጋር በማያያዝ ለፍትወት ማብረጃ እና ለወሊድ መቆጣጠሪያ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ➲➨ይህንን ያወቀው ቅዱሳ ጳውሎስ በሮም ለሚኖሩ ክርስትያኖች እንዲማሩበት እንዲጠነቀቁበት ‹‹ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የማይገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባ ለወጡ፤ወንዶቹ ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታው ተቃጠሉ›› በማለት ጽፎላቸዋል፡፡/ሮሜ፡ 1÷26-27/ ልብ ካልን ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን መልእክት የጻፈው ከጥንት ጀምሮ በሮም ግለ ወሲብና ግብረ ሰዶም ስለ ተስፋፋ ክርስትያኖች ከዚህ ጸያፍ ድርጊት እንዲታቀቡ ለማሳሰብ እንደ ሆነ ግልጽ ነው፡፡ ➲➨ወዳጆቼ ግለ ወሲብን ጠላት ሰይጣን ገና የሰው ልጆች ተፈጥረው በአግባቡ መብዛት ባልጀመሩበት ዘመን ነው ወደ ሕይወታቸው ያሰረጸው፡፡ በዚህ መልኩ ሰይጣን ያመጣውን፣ለሰዎች ያስለመደውን ግለ ወሲብ በዘመናችን በማስፋፋት ዛሬ ላይ አድርሶታል፣ ብዙዎችን አሰቃይቶበታል እያሰቃየም ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ ግለ ወሲብ ማለት ተፈጥሮአችን ባልሆነ መልኩና መንገድ እርካታን ለማግኘት የምንጠቀምበት የሰይጣን ወጥመድ ነው፡፡ ድርጊቱም የራስን አካል በራስ አካል ማርካት ነው፡፡ ግለ ወሲብ በወንዶችም በሴቶችም ላይ ይጸናል፡፡ ግለ ወሲብ በሁለት መንገድ ወደኛ ይመጣል፡፡ አንደኛው በርኩሳን መናፍስት እንደ ዓይነ ጥላና እንደ ዝሙት መንፈስ ባሉ ይመጣል፡፡ ሁለተኛው በፊልም በምናያቸው፣በምናነባቸውና ዘልማድ በምናደርጋቸው ትእይንቶች ይመጣሉ፡፡ ግለ ወሲብ ከልጅነት እስከ ወጣትነት ባለ እድሜ ውስጥ የሚጠናወት አስከፊ ተግባር ነው፡፡ ልዩ ልክፍትም ነው፡፡ ምክንያቱም ግለ ወሲብን ወንዶቹም ሴቶቹም ከለመዱት በቀላሉ ለመላቀቅ ይቸገራሉ፡፡ ለብዙዎች ግለ ወሲብን ለመተው ሺሻን መተው ይቀላቸዋል፡፡ መንፈሳዊ ነን የሚሉትም በዚህ ችግር ክፉኛ ይጠቃሉ፡፡ ➲➨ይህ ድርጊት እግዚአብሔር ቆርጦ ካልጣለልን በስተቀር አንዳንዱቹ በምክር፣ በንስሐ፣በጸበል መተው ይቸገራሉ፡፡ ድርጊቱም እንደ ኮሶ ሲጣባ፣ግራ የሚያጋባ ሕይወት ውስጥ ይከተናል፡፡ ሌላ ችግሩ ግለ ወሲብን በእጁ መፈጸም የጀመረ ሰው ምናልባት ትቶት ወደ ትዳር ዓለም ውስጥ ሲገባ ትልቅ ችግር ይገጥመዋል፡፡ እራስን በራስ ማወሰብ ለምዶ የተፈጥሮ የሆነው ሕጋዊ ሩካቤ እምብዛም ላያስደስተው ይችላል፡፡ ብዙ ወንዶችና ሴቶች በእጅ የሚፈጸም ግለ ወሲብን ከትዳር በፊት ይፈጽሙታል፡፡ ይህም በተግባር የሚፈጸመውን ሩካቤ በመፍራት፣በራሳቸው ሕይወት የግላቸውን ይፈጽማሉ፡፡ ➲➨የግለ ወሲብ አንዱ ችግር ዘርን ያለ አግባብ ያለቦታው በማፍሰስ በኃጢአት ላይ ኃጢአትን መጨመር ነው፡፡ ወዳጄ ስንት ለአገርና ለወግን ለቤተ ክርስትያን የሚጠቅሙ ዘሮች ያለ ቦታቸው ወድቀዋል፡፡ አንተ ያለ ቦታው የምታፈሰው ዘር ምናልባት ባለ ትዳሮች ልጃቸው አንዲሆን የሚመኙት ነው፡፡ ይህን መጨረሻው ላይ በዝርዝር እናያለን፡፡ ➲➨ሴቶች ደንግልናቸውን ከመጠበቅና ደፍረውም ተፈጥሮአዊ ሩካቤን ለመፈጸም ከመፍራት አንጻር ግለ ወሲብን በአልጋቸው ላይ ይፈጽማሉ፡፡ ግን በእነዚህ ሁሉ ድርጊቶች የዝሙት መንፈስ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ ዝሙትን አልፈጽምም ብለን የሥጋ ንጽህናችንን ብትጠብቅም በግለ ውሲብ በመፈተን ንጽህናችንን እናጎድላለን ‹‹ሴቶቻቸውም ለባሕሪያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕሪያቸው በማይገባው ለወጡ›› የተባለው ይሄም ነው፡፡ /ሮሜ 1÷26/ ➲➨ሰይጣን መናልባትም ኃጢአት እስከ ማይመስል ድረስ እየመከረ፣በግለ ወሲብ እያሰከረ ትውልዱን ይጫወትበታል፡፡ ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙትን ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹እናንተ ከአባታችሁ ከዲያቢሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ›› በማለት በእጅጉ ይገስጸናል፡፡ ዮሐ 8÷44 ➲➨ዓይነ ጥላና የዝሙት መንፈስ እኛን በግለ ወሲብ በመጥመዱ በማስለመዱ ሁለት ጥቅም ያገኛል፡፡ በተለይ ሰውን ከተፈጥሮ ውጭ ዓይን አፋር የሚያደርግ ዓይነ ጥላ ግለ ወሲብን ያስለምዳል፡፡ አንደኛው ተፈጥሮአችን ባልሆነና በማይስማማን መልኩ እርካታን እያገኘን ግለ ወሲብን በማቆራኘት ከተፈጥሮ ሩካቤ ማስወጣት ሲሆን ሁለተኛው በግለ ወሲብ ምክንያት የኃጢአታችንን ሒሳብ ከፍ በማድረግ ከፈጣሪ ማጣለት እና መቆራረጥ ነው፡፡ ሰይጣን በግለ ወሲብ እነዚህን ሰይጣናዊ ጥቅም ስለሚያገኝ ነው ግለ ወሲብን ለመተው ከባድ የሚሆንብን፡፡ ➲➨ሁለተኛው በፊልም በምናያቸው፣ በምናነባቸውና ዘልማድ በምናደርጋቸው ትእይንቶች የሚመጣው ግለ ወሲብ የብዙ ሰው ልማድ ሆኗል፡፡ ይህ ክፉ ሰይጣናዊ ልማድ በአሁን ሰዓት ያልታወቀበት ግን ብዙ ወጣቶች የሚሰቃይበት ሆኗል፡፡ ➲➨ወዳጆቼ ከኃጢአት ሁሉ ክፉ ኃጢአት አንድ ድርጊት ልማድ ሲሆን ነው፡፡ ልማድ ከሆነ ንስሐ፣ምክር፣ትምህርት በቀላሉ ላያላቅቁን ይችላሉ፡፡ ልማድ ከሆነ ደግሞ ድፍረት ይሆንና የድፍረት ኃጢአት ሆኖ ስንተገብረው ምንም ላይመስለን ይችላል፡፡ እንደ ዳዊት ‹‹የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኛ ባሪያህን ጠብቅ፤ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ፣ ከታላቅም ኃጢአት እነጻለሁ›› ብለን ልንጸልይ ይገባል፡፡ /መዝ 19÷13/ ➲➨ግለ ወሲብን ከአፈጻጸሙ አንጻር በአራት ከፍለን እናያቸዋልን፡፡ አንደኛ የደናግል ግለ ወሲብ ነው፡፡ እንዳየነው በውስጣችን ያለው ዓይነ ጥላና የዝሙት መንፈስ ሩካቤ ብንፈጽም ድንግልናየን አጣለሁ ግን ደግሞ በፍትወት እሰቃያለሁ የሚሉትን ሰዎችን የሚያጠቃ ነው፡፡ ወንዶችና ሴቶች ለድንግልናቸው እንጂ ለቅድስናቸው ካለመጠንቀቅ ይፈፅሙታል። .......

•✞✞✞ #እመቤቴ_ስልሽ ✞✞✞• እመቤቴ ስልሽ ነይልኝ ለልጅሽ፣ ቅረቢኝ በህይወቴ እናቴ ስጠራሽ፡፡/፪/ #አዝ••••••• ኑሮዬ ተዛብቶብኝ ደክሜኣለሁ እናቴ፣ እኔን ቅረቢኝና ልፅናና በህይወቴ፣ በደሳሳ ጎጆዬ በቤቴ ገብተሽልኝ፣ በኔ የነገሰውን ሀዘኔን ለውጪልኝ፡፡ #አዝ••••••• እሻለሁ ፍቅርሽን እናትነትሽን፣ ዘወትር ከጎንህ ነኝ ብለሽ አረጋጊኝ፣ ስምሽን ለዘላለም እጠራለሁኝ እኔ፣ ለመንገዴ መሪ ነሽ ለአይኔ ብርሃኔ፡፡ #አዝ••••••• በድቅድቁ ጨለማ እኔ እንዳልወድቅብሽ በቀኝ እና ከግራ ደግፊኝ እባክሽ፣ ኑሪ ከልጅሽ ጋራ እመአምላክ በዘመኔ፣ አደራ አትራቂኝ ጠበቃ ሁኝ ለኔ፡፡ #አዝ••••••• ከኔ ጋራ ስትሆኚ ድምፅሽም ያፅናናኛል፣ ከሀዘን ከትካዜ እናቴ ያስረሳኛል፣ በኖርሁበት ኑሪልኝ በምጓዝበት ሁሉ፣ የአንድዬ እናት ስጠራሽ ነይ ቤዛዊተ ኩሉ፡፡ #አዝ••••••• ✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ለጓደኞቻችን #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞ ╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮ @EOTC2921 @Orthodox2921 ╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯

•✞✞✞ #ግን_መቼ_ነው ? ? ? ✞✞✞• ☞መቼ ነው ፣ እውነተኛ ክርስቲያን የምሆነው? ? ☞መቼ ነው ፣ እግዚአብሔርን መፍራት የምጀምረው? ? ☞መቼ ነው ፣ እግዚአብሔርን ማመስገን የምጀምረው? ? እስከመቼስ ነው በዋዛ በፈዛዛ ጊዜየን የምጨርሰው? ? ☞በከንቱ ጊዜዬን እጨርሳለሁ እፍፍፍ መቼ ነው ፣ እግዚአብሔር በሰጠኝ ነገር ደስተኛ የምሆነው ? ? ሁልግዜ አማርረዋለሁ ግን ለምን? ☞ኦ አምላኬ እዳስተውል እርዳኝ መቼ ነው ፣ ሰውን እደራሴ አድርጌ የምወደው? ? ☞መቼ ነው ፣ ለጠሉኝ ሁሉ መልካም የማደርገው ? ? እኮ መቼ? ☞መቼ ነው? እግዚአብሔር ለምን እደፈጠረኝ የምረዳው? ? ☞እኔማ ሁሌም በአለም ከንቱነት ጠፋሁ አለም አታለለችኝ ☞መቼ ነው ፣ እግዚአብሔር እንደፈለገው መኖር የምጀምረው ? ? ☞እኮ መቼ? እድሜዬን አንድም ቀን መልካም ሳልሰራበት..? ☞መቼ ነው፣ ክፉ ንግግር ከመናገር ተንኮል ከመስራት የምቆጠበው ? ? ☞መቼ ነው ፣ለፆም ለፀሎትና ለስግደት በሙሉ ልቤ ሆኘ የማገለግለው እኮ መቼ? ? ☞መቼ ነው፣ ለመልካም ስራ ምሳሌ የምሆነው? ? ☞መቼ ነው ፣ ይህን ከንቱ አለም ከልቤ የማወጣው ? ? ? እኮ መቼ ? ☞መቼ ነው ፣ እኔ ማለት ትቼ እህት ወንድሞቼ ወገኖቼ ማለት የምጀምረው ? ሁሌም እራስ ወዳድ እፍፍፍፍ.... ☞መቼ ነው ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የማከብረው ? ?? ☞እኮ መቼ ነው እንደ ቃሉ የምኖረው ? ☞እስከመቼስ ነው የሚፈልገውን ነገር ትቼ የሚጠላውን ነገር የምከተለው እፍፍፍ.... ☞መቼ ነው ፣ ጥሩ እና ለጋሽ አዛኝ የምሆነው? ? ☞መቼ ነው ፣ በፍቅር መኖር የምጀምረው ? ? ? ሁልጊዜ ልቤ በጥላቻ ተሞልቷል... ☞መቼ ነው ሰውን ከመበደል ከማስቀየም የምቆጠበው? ?? ☞መቼ ነው ከራስ ወዳድነት የምላቀቀው ? ? ? ☞መቼ ነው ተመስገን አምላኬ የምለው? ? ? ☞ኦ አምላኬ አንተ እርዳኝ እኔስ ግራ ገባኝ ??? አምላኬ ሆይ ጥበብና ማስተዋሉን፤ ልብና ልቦናውን፤ ጥንካሬና ብርታቱን እምነትና የዋህነቱን፤ ትግስትና ፍቅሩን•••ለኛ ለባሮችህ ትሰጠን ዘንድ አማላጅ በምትሆን በቅድስተ ቅዱሳን በእመአምላክ በንፅህት ቅድስት ድንግል ማርያም፤ እንዲሁም አንተ ባከበርካቸው ቅዱሳን ፀሎትና ቃልኪዳን ማረን ይቅር በለን፡፡ አቤቱ ሆይ እኛ ሀጢያተኛ ባሮችህን ለንሰሀ ሞት አብቃን፡፡ •••✞ አሜን ✞ አሜን ✞ አሜን ✞•••

ነይ ነይ እምዬ ማርያም @EOTC2921.m4a1.10 MB

መመኪያዬ_እርስቴ_የሆነች.m4a9.71 KB

ሰባቱ መብራቶች.m4a1.06 MB

ሰላም ለኪ እንዘንሰግድ.m4a9.29 KB

♥ ከንፈሮችሽም የደስታ ምንጮች ናቸው፤ አንደበትሽም የምስጋና መፍለቂያ ነው፤ እጅግ በጣም አማርሽ፤ ቁመትሽም እንደ ዘንባባ ዛፍ ነው፤ የልብሶችሽ መዐዛም አፈው በመባል እንደሚታወቀው ሽቱ፤ የአፍንጫሽ መዐዛም እንደ ወይን አበባ ሽታ የሚኾንልሽ ድንግል ሆይ ደስታሽን እወደዋለኊ (ማሕ ፯፥፰) የአፍሽም አከፋፈት እንደ ቀናንሞስ አበባ የጣፈጠ ነው፤ ከሊባኖስ ዕንጨቶች ኹሉ ጋር (ማሕ ፬፥፲፬)) በማለት እንደ ሰሎሞን ርሱም የፈጣሪውን እናት አመስግኗል፡፡ ♥ የፈጣሪያችን እናት ቅድስት ድንግል የተወለደችበትን ግንቦት አንድን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን “ልደታ ለማርያም” በማለት ከጥንት ዠምሮ በታላቅ መንፈሳዊ ሐሤት በቅዳሴ፣ በማሕሌት የምታከብርላት ሲኾን፤ በተለያዩ ክፍላተ ዓለማት ያሉ ክርስቲያኖችም ይኽነን በዓል “The Nativity of the blessed Virgin Mary” (የተባረከችው የድንግል ማርያም ልደት (መወለድ)) በማለት ያስባሉ። ♥ በጥንት ምሥራቃውያን (እንደ ቤዛንታይን ባሉ) ዘንድ ዐዲሱ ዓመት ልክ እንደኛ መስከረም ወር “September” ላይ ይውል ስለነበር ከዚኽ አያይዘው መስከረም ፰ (September 8) ያከብሩት የነበረ እንደነበር ታሪክ ሲያስረዳ ይኽነን ይዘው በዚኽ ዕለትም የሚያከብሩት ብዙዎች የዓለማት ሀገራት አሉ፡፡ ✍ ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ [ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን፤ ነገረ ማርያም በሊቃውንት ክፍል አንድ ከሚለው መጽሐፌ የተወሰደ] #የአምላክ_እናት_በረከቷ_በእኛ_በአደራ_ልጆቿ_ላይ_በዝቶ_ይደር፡፡

ፈጣሪያችን ክርስቶስን በድንቅ ተአምር ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ የወለደችልን ምክንያተ ድኂን ርግበ ሰሎሞን የተባለች የቅድስት ድንግልን የመፀነሷን ነገር በአድናቆት ገልጸዋል፡፡ ♥ “ወእምድኅረ ስድስቱ አውራኅ ተዐውቀ ፅንሳ ለሐና” ይላል፤ ከስድስት ወርም በኋላ የሐና ፅንሷ እየታወቀ ሲመጣ ጎረቤቶቿ መፅነሷን ይረዱ ዘንድ በአድናቆት ማሕፀኗን ይዳስሱ ነበር፤ በተለይም ዐይኗ የታወረ የሐና ዘመዷ የአርሳባን ልጅ የምትኾን አንዲት ሴት የሐናን ማሕፀን ዳስሳ ዐይኗን ብትነካው በርቶላት በታላቅ ደስታ ኾና “ብፅዓን ለኪ ኦ ሐና እስመ እም ፍጥረተ ዓለም አልቦ ዘከማኪ ዘይፌውስ በከርሡ አዕይንተ ዕውራን” (ሐና ሆይ ብፅዓን ይገባሻል ዓለም ከተፈጠረ ዠምሮ እንዳንቺ በማሕፀኑ የዕውራንን ዐይን የሚያበራ የለምና) በማለት አመስግናታለች፤ ከዚኽ በኋላ ዝናዋ በሀገሩ ኹሉ ተሰምቶ ሕሙማን ኹሉ ማሕፀኗን እየዳሰሱ ይፈወሱ ነበር፡፡ ♥ አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው ላይ ይኽነን ሲገልጹ፦ ✍ “ጸግይየ ሣዕረ ዘኪሩቤል ልሳነ ተአምረኪ በነጊር እመ ኢፈጸምኩ አነ ባሕቱ አአኲት ማርያም ዘጾረተኪ ማሕፀነ እንዘ ሀለወት ፀኒሳ ኪያኪ ርጢነ ለለገሰስዋ ላቲ ትፌውስ ዱያነ” ♥ (ሳርን የኾንኊ እኔ የኪሩቤል አንደበትን ገንዘብ አድርጌ ታምርሽን በመንገር በማስተማር ባልፈጽምም ነገር ግን ማርያም የተሸከመቺሽን ማሕፀን አመሰግናለኊ፤ መድኀኒት አንቺን ፀንሳ ሳለች ርሷን የዳሰሷትን ድዉያንን ኹሉ ትፈውስ ነበር) በማለት እመ መድኅነ ዓለም ገና ሳትወለድ የተሠራውን ድንቅ ተአምር አመስግነዋል፡፡ ♥ ይኽ የቅድስት ድንግል ማርያም የፅንሰት በዓል በመላው ዓለም የሚታወቅ ሲኾን ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት የኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የአምላክ እናት የተፀነሰችበት ይኽነን በዓል ነሐሴ ፯ ቀን በታላቅ ድምቀት በማሕሌት፣ በቅዳሴ የምታስበው ሲኾን በዓሉም “ፅንሰታ ለማርያም” በመባል ይታወቃል። ♥ በዓለም ላይ ያሉ ክርስቲያኖች ደግሞ በዓሉን “The conception of the Theotokos” (የአምላክ እናት መፀነስ) በማለት ሲያከብሩት ወሩን ግን የልደት በዓልን ለማክበር በሚዘጋጁበት በታኅሣሥ አድርገው በ፱ኛው ቀን “December 9” ላይ ያስቡታል ፡፡ ♥ በእጅጉ የሚደንቀው ደግሞ “ሳሚናስ ወልደ ጦሊቅ ዘይነብር ውስተ ቤተ ዶይቅ” ይላል ሳሚናስ የሚባል የጦሊቅ ልጅ ከኤዶቅ ካጐቱ ቤት ኼዶ ሞተ፤ ሐናም በሀገራቸው ልማድ የአልጋውን ሸንኮር ይዛ እየዞረች ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ፈጥኖ ተነሥቶ “ሰላም ለኪ ኦ ሐና እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ” (ሰማይና ምድርን ለፈጠረው አምላክ አያቱን የተባልሽ ሐና ሰላም ላንቺ ይኹን) አላት። ♥ ከዚያ የነበሩ አይሁድም በመደናገጥ “ሳሚናስ ምን አየኽ? ምን ትላለኽ?” አሉት፤ ርሱም “ከዚች ከሐና ማሕፀን የምትወለደው ሕፃን ሰማይ ምድርን የፈጠረ አምላክን ትወልዳለች እያሉ መላእክት ኹሉ ሲያመሰግኗት ሰማኋቸው፤ እኔንም ያነሣችኝ ርሷ ናት” አላቸው፤ እነርሱም ይኽነን በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን ከማመስገን ይልቅ በቅናትና በክፋት ተመልተው ሐና በማሕፀን ባለ ፅንሷ ካዳነች በኛ ላይ ልትሠለጥን አይደለምን? “ንዑ ንገሮሙ ለሐና ወለኢያቄም” ሳትወልድ አስቀድመን ሐናና ኢያቄምን በድንጋይ ወግረን እንግደላቸው ብለው ተነሣሡባቸው። ♥ ያን ጊዜ ታላቁ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለኢያቄም ተገልጾ ሐናን ሊባኖስ ወደሚባል ተራራ እንዲወስዳት ነገረው፤ ጠቢቡ ሰሎሞን በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝቶ እመቤታችን በሊባኖስ ተራራ እንደምትወለድ ተገልጾለት፡- ✍“ንዒ እምሊባኖስ መርዓት ንዒ እምሊባኖስ ንዒ ወተወፅኢ እምቅድመ ሃይማኖት እምርእሰ ሳኔር ወኤርሞን አምግበበ አናብስት ወእምአድባረ አናምርት” (ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ነዪ ከሊባኖስ ነዪ ከአማና ራስ ከሳኔር ከኤርሞን ራስ ከአንበሶች መኖሪያ ከነብሮችም ተራራ) በማለት የተናገረው ትንቢት ሊፈጸም ቅድስት ድንግል ማርያም በ፭ ሺሕ ፬፻፹፭ (5485) ዓመተ ዓለም በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች (ማሕ ፬፥፲)፡፡ ♥ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማሕሌተ ጽጌ የነገረ ማርያም መጽሐፋቸው ላይም፦ “ለንጉሠ ነገሥት ሰሎሞን ከመ ተፈሥሐ ልቡ በዕለተ ወፃእኪ መርዓት ለአንበሳ ትንቢት እምግቡ ማእከለ ማኅበር ፍሡሓን ተአምረኪ እንዘ እነቡ እዜምር ለኪ ጽጌ ሐና ወፍኖተ ነፈርዐጽ እሌቡ ከመ ጣዕዋ ሐሊበ ዘይጠቡ” ♥ (ትንቢት ከተነገረለት ከአንበሳ ጉድጓድ፤ ድንግል ሙሽራ በተገኘሽ ጊዜ የንጉሦች ንጉሥ የሰሎሞን ልቡ እንደተደሰተ፤ ደስ ባላቸው በመላእክት አንድነት ፊት ታምርሽን እየተናገርኊ የሐና አበባ ማርያም እዘምርሻለኊ፤ ወተትን ጠብቶ እንደሚዘልል እንቦሳም ዝለል ዝለል ይለኛል) በማለት ሰሎሞን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቶ ታላቅ ደስታን ለኹላችን እንደሰጠን አብራርተው ገልጠዋል፡፡ ♥ ይኽ የእመቤታችን ልደት ለሰማያውያን መላእክትና ለደቂቀ አዳም ደስታ ሲኾን አካላዊ ቃል ክርስቶስ ከርሷ ተወልዶ ዲያብሎስ ፭ሺሕ፭፻ ዘመን በሲኦል ያኖራቸውን ነፍሳት ወደ ገነት የሚያስገባቸው ነውና፤ ሰይጣን በተቃራኒው ልደቷ እንዳላስደሰተው ሲገልጹ፦ ✍ “ተፈሥሐት ምድር ወሰማይ አንፈርዐጸ በዕለተ ጸገዩኪ አብላስ ወአውጽኡ ሠርጸ ተአምረ ሕይወት ማርያም ዘአልብኪ ቢጸ እስከ ፈርሀ መልአከ ሞት ወሰይጣን ደንገጸ ዜና ልደትኪ ነጐድጓድ እስከ (ውስተ) ሲኦል ደምፀ” (በለሶች (ኢያቄምና ሐና) ቡቃያ አንቺን ባስገኙሽ ጊዜ ምድር ደስ አላት ሰማይም ደስ አለው፤ ጓደኛ (ምሳሌ) የሌለሽ የድኅነት ምልክት ማርያም፤ መልአከ ሞት እስከ ፈራና ሰይጣንም እስከ ደነገጠ ድረስ የመወለድሽ ዜና እስከ ሲኦል ድረስ (በሲኦል) ተሰማ) በማለት አስተምረዋል፡፡ ♥ ጠቢቡ ሰሎሞን አስቀድሞ በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝቶ በማሕልዩ ላይ “መኑ ይእቲ ዛቲ እንተ ትሔውጽ ከመ ጎሕ ሠናይት ከመ ወርኅ ወብርህት ከመ ፀሓይ” (ይኽቺ እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጐበኝ እንደ ጨረቃ የተዋበች፤ እንደ ፀሓይም የጠራች ዐላማ ይዞ እንደተሰለፈ ሰራዊት የምታስፈራ ማን ናት?) በማለት እንደ ፀሓይ የሞቀ እንደ ጨረቃ የደመቀ ንጽሕናዋና ቅድስናዋ የመልኳ ደም ግባት በነቢያት ትንቢት አስቀድሞ የተጐበኘላት የእውነት ፀሓይ የክርስቶስ እናት የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብርና ደም ግባቷን እንደተናገረ በሊባኖስ ተራራ በግንቦት ፩ በተወለደች ጊዜ ፊቷ በእጅጉ ያበራ ነበር፤ መዐዛዋም ከሽቱ ኹሉ ይበልጥ ነበር፡፡ ♥ ኢትዮጵያዊዉ ሊቅ ቅዱስ ያሬድም የመዐዛዋን አስደናቂነት በሰሎሞንን ቃል በመነሣት የመዐዛዋን ነገር ሲያደንቅ፡- ✍ “ወእወዲ ውስተ አፉየ እምፍሬ ከርሥኪ…” (ከማሕፀንሽም ፍሬ ወደ አፌ እጨምራለኊ፤ የፍሬሽ ደምም ለጉሮሮዬ የጣፈጠ ነው፤ የሽቱሽ መዐዛም ለአፍንጫዬ ያማረ ነው፤ የድንግልናሽ ክብርም ልቡናዬን እንደ ከረመ ንጹሕ ወይን ደስ ያሰኘዋል፤ ስለ አንቺ ያለኝ ደስታ ምን ያኽል ነው፤ አነጋገርሽ ያማረ ነው፤ ቃልሽም የጣፈጠ ነው።