ar
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

الذهاب إلى القناة على Telegram

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

إظهار المزيد
608
المشتركون
-124 ساعات
-37 أيام
-1130 أيام
أرشيف المشاركات
❤ ሃያ ዓመትም ሲሆነው አባቱ ወደ ንጉሥ አቀረበውና ንጉሡም በአባቱ ፈንታ ምስፍና ሾመው አባቱ በዕድሜው ሸምግሎ ነበርና። ከጥቂት ወራትም በኋላ ጣዖታትን የማያመልኩ ክርስቲያኖችን ሁሉ ይገድል ዘንድ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ምልክትን ወደ እንጽና አገር መኰንን ደረሰ። መኰንኑም ክርስቲያኖችን እየፈለገ ወደ ሻው ከተማ ደረሰ ያን ጊዜ ክብር ይግባውና ክርስቶስን እንደሚአመልከው ክፉዎች ሰዎች ይህን ቅዱስ ፊቅጦርን ወነጀሉት ያን ጊዜም እንዲአመጡት አዘዘና በአመጡት ጊዜ ለጣዖታት እንዲሠዋ አስገደደው እምቢ በአለውም ጊዜ በወህኒ ቤት እንደመአሥሩት አዘዘ። ❤ በዚያም እያለ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ሰማይ አወጣው የወህኒ ቤት ጠባቂዎችም በአጡት ጊዜ ተሸበሩ። ከሰባት ቀኖችም በኋላ አግኝተውት ወደ መኰንኑ ወሰዱት መኰንኑ ግን ራራለትና ወደ ንጉሡ ሰደደው ንጉሡም እግዚአብሔርን ከማምለክ ይመልሰው ዘንድ በማባበል ብዙ ሽነገለው። መመለስም በተሳነው ጊዜ አውጣኪያኖስ ወደሚባል መኰንን ሰደደው። እንዲህም ብሎ አዘዘው "እንሆ ፊቅጦርን ወደአንተ ልኬዋለሁ ያንተን ምክር ከሰማ ለአማልክት ይሠዋ ካልሰማህ ግን ግደለው እንጂ አትራራለት"። አለው። ❤ ከዚህም በኋላ ወደ መኰንኑ ሊወስዱት እጆቹንና እግሮቹን አሠሩ በአፉም የብረት ልጓም አግብተው በመርከብ አሳፈሩት የእግዚአብሔርም መልአክ ወርዶ ከማሠሪያው ፈትቶ ወደ መኰንኑ አደረሰው ቅዱስ ፊቅጦርም መኰንኑንና ከሀዲውን ንጉሥ ሊረግም ጀመረ መኰንኑም ተቆጣ ጽኑዕ ሥቃይንም አሠቃይቶ በወህኒ ቤት አሠረው። በዚያም ሳለ ክብር ይግባውና መድኃኒታችን በብርሃን ሠረገላ ላይ ሁኖ ተገለጠለትና ቃል ኪዳን ሰጠው ከዚያችም ቀን ጀምሮ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ብዙ በሽተኞችን የሚፈውስ ሆነ። ❤ መኰንኑም ይህን ሰምቶ ተቆጣ ወደርሱ አስመጣውና ይመለሰው ዘንድ ደግሞ ሸነገለው ቅዱስ ፊቅጦር ግን የረከሱ አማልክቶቹን ረገመ በዚያንም ጊዜ በፈረስ ጅራት ላይ አሥረው የአንድ ቀን መንገድ ያህል እንዲጐትቱት ከዚያም ከውሽባ ቤት እሳት ማንደጃ ውስጥ እንዲጨመሰሩት አዘዘ እንዲህም መልካም ተጋድሎውን ፈጸመ። ሥጋውን ግን ከዚያ ውሽባ ቤት አላወጡትም በመሰላል ወርደው በአማሩ ልብሶች ገንዘው በሽቱዎች አጣፈጡት እንጂ በላዩ ቤተ ክርስቲያንን ሠሩ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ፊቅጦር በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የታኅሣሥ5 ስንክሳር።                                                          ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ተንሥኡ ላዕሌየ ሰማዕት ዐመፃ። ወዘኢየአምር ነበቡ ላዕሌየ። ፈደዩኒ እኪተ ህየንተ ሠናይት"። መዝ 34፥11-12። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 10፥11-ፍ.ም ወይም ገላ 3፥21-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 5፥9-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 16፥14-16። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 10፥35-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ነቢዩ ናሆም የዕረፍት በዓልና የነቢያት (የገና) የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።

ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta): ❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤          ❤ #ታኅሣሥ ፭ (5) ቀን። ❤ እንኳን #ዐሥራ_ሁለቱ_ደቂቀ_ነቢያት አንዱ ለሆነው ለኬልቅዩ ልጅ ለታላቁ ነቢይ #ለቅዱስ_ናሆም_ለዕረፍት_በዓል፣ ከሮም አገር ለሆነች #ለቅድስት_አውጋንያ ሰማዕትነት ለተቀበለችበት ለዕረፍቷ በዓልና አስዩጥ አውራጃ ሻው ከሚባል ከተማ ለሆነ #ለቅዱስ_ፊቅጦር_ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከቅዱስ_ኤስድሮስ_ሰማዕት፣ #ቅዱሳን_ከፊንጦስ፣ #ከሐናንያ_ከባርክዮስ_ከዮሐንስ_ከተጋዳይዋ #ከቅድስት_አውጋንያ_አባት_ከፊልጶስና ከሰማዕት #ቅዱስ_ኤላውትሮስ ከመታሰቢያቸው   እግዚአብሔር አምላክ በረከትን ረድኤትና ያሳትፈን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #ነቢዩ_ቅዱስ_ናሆም፦ ከስምዖን ነገድ የሆነ ይህ ጻድቅ ነቢይ ከነቢዩ ሙሴ በትንቢት ዐሥራ ሰባተኛ ነው። በካህኑ ዮዳሄ በነገሥታቱ በኢዮአስ፣ በአስሜስያስ፣ በልጁ በኦዝያን ዘመን ትንቢት ተናገረ ስለ ክህደታቸውና ጣዖታትን ስለ ማምለካቸውም የእስራኤልን ልጆች ገሠጻቸው። እግዚአብሔርም ምንም መሐሪና ይቅር ባይ ምሕረቱም የበዛ ቢሆን ካልተመለሱ ጠላቶቹን ይበቀላቸው ዘንድ እንደ አለው ለሚቃወሙትም የፍርድ ቀን እንደሚጠብቃቸው በትንቢት ገለጠ። ❤ ዳግመኛም ስለ ከበረ የወንጌል ትምህርትና ስለ ሐዋርያት እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ "የምሥራች የሚናገሩ ሰዎች እግራቸው እንሆ በተራራ ላይ ቁሟል ሰላምንም ይናገራሉ"። ስለነነዌም ውኃና እሳት ያጠፋአት ዘንድ እንዳላቸው ትንቢት ተናገረ እንደ ቃሉ ሆነ ከዕውነት መንገድ ተመልሰው በበደሉ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር በውስጡ ታላቅ ንውጽውጽታ አድርጎ እሳትም አውርዶ እኩሌታዋን አቃጥሏልና። በንስሐ ጸንተው ወደ እግዚአብሔር የተመለሱትን ግን ከክፉ ነገር ከቶ ምንም ምን አልደረሰባቸውም። የትንቢቱንም ወራት ሲፈጸም እግዚአብሔርም አገልግሎ በዚች ቀን ታኅሣሥ5  በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ነቢይ በቅዱስ ናሆም ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                                                                                                          ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅድስት_አውጋንያ፦ የዚችም ቅድስት የአባቷ ስም ፊልጶስ ነው እርሱም የእስክንድርያ አገር ገዥ ነበር ጣዖትንም ያመልካል ስሙ መምድያኖስ የሚባል የሮም ንጉሥም ለጣዖት የሚሰግድ ነው ይቺም ቅድስት አውጋንያ በእስክድርያ ከተማ ተወለደች እናቷም ክርስቲያን ስለሆነች በሥውር የክርስቲያን ሃይማኖትን አስተማረቻት። ❤ በአደገችም ጊዜ ታላላቆች መኳንንት አጯት አባቷም ይህን በነገራት ጊዜ "አባቴ ሆይ መጀመሪያ ወደ እስክንድርያ ገዳም እንድገባና እንድጎበኝ ተራሮችን በማየት ዐይኖቼ አይተው ደስ ይለኝ ዘንድ ፍቀድልኝ" አለችው አባቷም ሰምቶ ሁለት ጃንደረቦችን ጨምሮ የወደደችውን ታደርግ ዘንድ ፈቀደላት። በወጣችም ጊዜ የመነኰሳትን ገዳማት ሁሉ ዞረች ስሙ ቴዎድሮስ የሚባል ጻድቅ ደግ ኤጲስቆጶስ ወደሚኖርባትም ቤተ ክርስቲያን ደረሰች ቀረብ ብላም በልቧ ያለውን ሁሉ ነገረችው ካጃንደረቦቿም ጋር ተጠምቃ በዚያ መነኰሰች በወንድ አምሳልም ሁና ስሟን አባ አውጋንዮስ አሰኘች እርሷ ሴት እንደሆነች ማንም አላወቀም። ወደ አባቷም ባልተመለሰች ጊዜ በቦታው ሁሉ ፈለጋት ሲአጣትም በርሷ አምሳል ጣዖት ሠርቶ ማታና ጧት እየሰገደላት ኖረ። ❤ አንድ ዓመትም ከኖረች በኋላ የዚያ ቦታ አበ ምኔት አረፈ መነኰሳቱም መረጧትና አበ ምኔት አድርገው ሾሟት እግዚአብሔርም አጋንንትን ታስወጣ ዘንድ የዕውራንን ዐይኖች ትገልጥ ዘንድ ደዌውን ሁሉ ታድን ዘንድ ሀብተ ፈውስን ሰጣት። ❤ ከዚህም በኋላ ሰይጣን በአንዲት ሴት ልብ ክፉ አሳብ አሳደረባት ከአዳነቻት በኋላ ወንድ መስላታለችና "ገዳምህንና ምንኵስናህን ትተህ ለእኔ ባል ሁነኝ ብዙ ገንዘብ አለኝና" አለቻት። አባ አውጋንዮስ የተባለችው ቅድስቷም "እናቴ ሆይ ከእኔ ዘንድ ሒጂ ሰይጣን በከንቱ አድክሞሻል" አለቻት በአሳፈረቻትም ጊዜ ወደ እስክንድርያ ገዥ ሒዳ እንዲህ አለችው "እኔ ወደ ዕገሌ ቦታ በሔድኩ ጊዜ ሊደፍረኝ ሽቶ ወጣት መነኵሴ በሌሊት ወደእኔ መጣ ወደ አገልጋዮቼም ስጮህ ከእኔ ዘንድ ወጥቶ ሸሸ"። መኰንኑም በሰማ ጊዜ ይኸውም የቅድስት አውጋንያ አባቷ የሆነ መነኰሳቱን ሁሉ አሥረው ያመጧቸው ዘንድ አዘዘ በአደረሷቸውም ጊዜ እንዲአሠቃያቸው ለሌላ መኰንን አሳልፎ ሰጣቸው ከሥቃይም ጽናት የተነሣ ከእርሳቸው የሞቱ አሉ። ❤ የመነኰሳቱንም መጐሳቈል በአየች ጊዜ መኰንን አባቷን እንዲህ አለችው "ጌታዬ ሆይ ምሥጢሬን ዕውነቱን እነግርህ ዘንድ የምፈልገውንም እንዳትከለክለኝ ማልልኝ" አለችው። በማለላትም ጊዜ ወደ ሥውር ቦታ ወስዳ ምስጢርዋን ሁሉ ገለጠችለትና ልጁ አውጋንያ እርሷ እንደሆነች አስረዳችው። መኰንኑም አይቶ "በእውነት አንቺ ልጄ አውጋንያ ነሽ እኔም በአምላክሽ አመንኩ" አላት። በዚያንም ጊዜ መነኰሳቱን ይፈቷቸው ዘንድ በመሠቃየት የሞቱትንም ይቀብሩአቸው ዘንድ አዘዘ ወዲውኑ ከቤተሰቦቹ ሁሉ ጋር ተጠምቆ ሁሉም ክርስቲያን ሆኑ። ❤ የእስክንድርያ ሰዎችም የሃይማኖቱን ጽናት በአዩ ጊዜ በወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ ወንበር ላይ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት ክብር ይግባውና የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት እያስተማረ ብዙ ዓመታትን ኖረ። ከዚህም በኋላ በእርሱ ላይ ሌላ ከሀዲ መኰንን ተነሥቶ ይህን ሊቀ ጳጳሳት ፊልጶስን በሥውር ይገድሉት ዘንድ ጭፍሮቹን ላከ በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ ገደሉት የሰማዕትነት አክሊል አገኘ። ❤ የሮሜ ሊቀ ጳጳሳትም የቅድስት አውጋንያን ዜና በሰማ ጊዜ ወደርሱ ወስዶ እርሱ በሠራው ገዳም ላይ እመ ምኔት አድርጎ ሾማት የመነኰሳይያቱም ብዛት ሦስት ሺህ ሦስት መቶ ነው እነዚያንም ከእርሷ ጋር የኖሩ ሁለት ጃንደረቦች በሁለት አገሮች ላይ ኤጲስቆጶስትነት ሾማቸው። ከዚህም በኋላ ሌላ ከሀዲ መኰንን በተሾመ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነፍሷን ለሞት አሳልፋ እስከ ሰጠች ድረስ ቅድስት አውጋንያን ይዞ በጽኑ ሥቃይ አሠቃያት የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለች። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት አውጋንያ በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                                                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_ፊቅጦር፦ የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም መርመር የእናቱ ስም ማርታ ይባላል እነርሱም ያለ ፍርሀት እግዚአብሔርን የሚያመልኩት እውነተኞች ጻድቃን ናቸው ነገር ግን ልጅ አልነበራቸውምና ክብር ይግባውና ጌታችንን እየለመኑ ኖሩ ለድኆችም ምጽዋትን ይሰጡ ነበር። እግዚአብሔርም ልመናቸውን ተቀብለ ይቺ የተባረከች ማርታም ይህን ሊቅ ፊቅጦርን ፀንሳ ግንቦት ዘጠኝ ቀን ወለደችው እግዚአብሔርን በመፍራትም ሠርተው ቀጥተው አሳደጉት።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #ታኅሣሥ ፭ (5)። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ ለእግዚአብሔር ሕግ ለሚቀና ገድለኛ ለሆነ ለንጹሕ ድንግል ለቅዱስ አባት #ለአባ_ገብረ_ናዝራዊ_ለዕረፍት_ዓመታዊ ክብረ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ገብረ_ናዝራዊ፦ የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ በወገን የከበሩ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ናቸው አባቱም የቤተ ክርስቲያንን ሕጓንና ሥርዓቷን የሚጠብቅ ካህን ነው እናቱም ፈጣሪዋን የምትወድ ደግ ሴት ናት። ይህም ቅዱስ በተወለደ ጊዜ በዕውቀት እግዚአብሔርን በመፍራት በመማር አደገ ከዚህም በኋላ ዲቁናን በተሾመ ጊዜ የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍትን የሚያነብ ሆነ በኦሪትም ውስጥ "የሰንበትን ቀን የሻረና ሥራ የሠራባት በሞት ይቀጣ" የሚል አገኘ። ከወንጌልም ውስጥ እንዲህ የሚል አገኘ "ከእነዚህ ትእዛዛት ታንሳለች ብሎ የሚያስተምር አንዲቱን የሻረ ለሰውም እንዲህ ብሎ የሚያስተምር በመንግሥተ ሰማይ የተለየ ይሆናል የሚያደርግና የሚያስተም ግን እርሱ በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይሆናል" ዳግመኛም መድኃኒታችን "አባትና እናቱን ያልተው ሰውነቱንም ለመከራ አሳልፎ ያልጣላት ሊአገለግለኝ ደቀ መዝሙሬም ሊሆነኝ አይችልም" ያለውን አስተዋለ። ❤ ከዚህም በኋላ ወደ አቡነ ጎርጎርዮስ ሔደ እርሱም ጽጋጃ በሚባል ገዳም የአቡነ አኖሬዎስ ልጅ ነው በዚያም መንኵሶ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት እየተጋ ኖረ። ከዚህም በኋላ ቅስና ተሾመ ከዚያም ወደ ትግራይ አገር ሔዶ ከአባ ያዕቆብ ጋር ተገናኝቶ በቅዱሳት መጻሕፍት ቃሎች ተነጋገሩ። ከዚህም በኋላ ሀሳብን ገለጠለት አባ ያዕቆብም "እንዴት ይቻላል" አለው አባ ገብረ ናዝራዊም "እግዚአብሔር ይረዳኛል" አለ። ከአባ ያዕቆብም ጒልት ተቀብሎ እርስበርሳቸው በእግዚአብሔር ፈቃድ ተለያዩ። ❤ ከዚህም በኋላ ተስፋፍቶ ገዳምን ሠራ ብዙ ሰዎችም ወደርሱ ተሰብስበው መነኰሳትን ሆኑ ስለሰንበታትና በዓላትም አከባበር እንደሚገባ ሥርዓትን ሠራ። ለመነኰሳትም ከመድኃኒታችን ከልደቱና ከጥምቀቱ በዓል ከሰንበታትና ከበዓለ ሃምሳ በቀር በየሰሞኑ ሁሉ እስከ ማታ ያለ ማቋረጥ መጾም እንደሚገባቸው ሥርዓትን ሠራ። ዳግመኛም የሌላውን ገንዘብ እንዳይነኩ እንዳይረግሙ በሕያው እግዚአብሔርም ስም እንዳይምሉም ለልጆቹ ይህን ሁሉ ያስተምራቸው ነበር። ለእርሱ ግን ለሚጸልየው ጸሎት ልክ የለውም ነቢይ ዳዊት "እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ አመሰግነዋለሁ። ምስጋናውም ዘወትር በአፌ ውስጥ አለ" ያለውን አስቦ ዳግመኛም "ትእዛዝህን በማሰብ እጫወታለሁ ሕግህን እሻለሁ ትእዛዞችህንም አስተምራለሁ ቃልህም አልረሳም" ያለውን አስቦ። ❤ ዳግመኛም ከሰባውና ደም ካለው ጣዕም ካላቸውም መብሎች ሁሉ ይከለከላል የጌታውን መከራ ለነፍሱ ያሳስባታልና ዕንባው ያለ ማቋረጥ ይፈስ ነበር ያለ ማቋረጥም ይሰግዳል ያመሰግናልም እንግዳና መጻተኛውን ይቀበላል "በጽዮን ዘር በኢየሩሳሌም ቤቶች ያለሐት ብፁዕ ነው" ያለውን የነቢይ ቃል አስቦ ድኆችንና ችግረኞችን ይጎበኛቸዋል። ለዚህም አባት ትሩፋቱ ብዙ ነው ደጋግ ተአምራትንም በማድረግ በሰው ልቡናም ተሠውሮ ያለውን በማወቅ ብዙ የተለያዩ ሀብቶች ተሰጥተውታል ለልጆቹም የቀናች ሃይማኖትን አስተማራቸው በእርሷም እንዲጸኑ አዘዛቸው ከዚህም በኋላ በሸመገለ ጊዜ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በዚች ቀን ታኅሣሥ5 ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት በአባ ገብረ ናዝራዊ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የታኅሣሥ 5 ስንክሳር።

ታሕሳስ 4 /፬/ በዚህችም ዕለት ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ አረፈ። እንድርያስ ማለት ጽኑዕ፣ በኩር ማለት ሲሆን የቅዱስ ጴጥሮስ ወንድም ነው። የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ደቀመዝሙር ሳለ ዮሐንስ ጌታችን
ታሕሳስ 4 /፬/ በዚህችም ዕለት ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ አረፈ። እንድርያስ ማለት ጽኑዕ፣ በኩር ማለት ሲሆን የቅዱስ ጴጥሮስ ወንድም ነው።  የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ደቀመዝሙር ሳለ ዮሐንስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አሳይቶት ከእርሱ ጋር ዋለ። በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ። እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ። ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት። ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉትም አይቶ። ምን ትፈልጋላችሁ? አላቸው።እርሱም፦ ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ ትርጓሜው መምህር ሆይ ማለት ነው።መጥታችሁ እዩ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ። ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ። ጴጥሮስንም ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ያመጣው እርሱ ነው። ቅዱስ እንድርያስ መጀመሪያ የስብከት ሥራውን በፍልስጥኤም ጀመረ፡፡ የቤተክርስቲያን ፀሐፊ የነበረው አወሳብዮስ እንደገለጠው እንድርያስ በሩስያ ወንጌልን ሰብኳል፡፡ ቀጥሎም በቢታንያ፣ በገላትያ፣ በሩማንያ፣ በመቄዶንያ፣ በታናሽ እስያ፣ በግሪክ አገር አስተምሯል፡፡ የቁስጥንጥንያን ቤተክርስቲያን የመሠረተና የቁስጥንጥንያ የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ መሆኑ ይነገራል፡፡ በመጨረሻም ግሪክ ውስጥ ምትራ/ ጳጥሪስ በምትባለዋ ሀገር ሲያስተምር በጣኦት አምላኪዎች እጅ /X/ የሚመስል ቅርጽ ባለው መስቀል ተሰቅሎ በድንጋይ ተወግሮ በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ የቅዱሱ በረከት ይደርብን ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር

ታህሳስ 3 /፫/
በዚች ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት ሲሆናት ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ነው ። እርሷ ለእግዚአብሔር የስእለት ልጅ ነበረችና ። እናቷ ቅድስት ሐና ልጅ የሌላት ስለሆነች በቤተ እግዚአብሔር ውስጥ ከሴቶች ተለይታ ርቃ ትኖር ነበር ሽማግሌ ከሆነ ከኢያቄም ከባሏ ጋርም እጅግ የምታዝን ሆነች ። እግዚአብሔርም ኀዘናቸውን ሰማ ቅድስት ሐናም እንዲህ ብላ ለእግዚአብሔር ተሳለች የሰጠህኝን ፍሬ ለእግዚአብሔር አገልጋይ አደርገዋለሁ ። ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምንም በወለደቻት ጊዜ ሦስት ዓመት በቤቷ ውስጥ አሳደገቻት ከዚህም በኋላ ከደናግል ጋር ትኖር ዘንድ ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደቻት በቤተ መቅደስም ምግቧን ከመላእክት እጅ እየተቀበለች ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረች ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም መጥቶ ከእርሷ ሥጋን እስከ ነሣ ድረስ ። ከሴቶች ሁሉ የተመረጠች ይቺ ናት በቤተ መቅደስም በመኖር ዐሥራ ሁለት ዓመት ሲፈጸምላት እርሷ ለእግዚአብሔር የተሰጠች የስዕለት ልጅ ናትና ለሚጠብቃት ይሰጧት ዘንድ ካህናት እርስበርሳቸው ተማከሩ በሴቶች ላይ የሚደርስ በርሷ ላይም ይደርስባታል ብለው ስለፈሩ በቤተ መቅደስ ውስጥ ይተዋት ዘንድ ለእነርሱ ትክክል መስሎ አልታያቸውም ስለዚህም ሊጠብቃት ለሚገባው በእርሷ ላይ እጮኛ ሊአኖሩ ወደዱ ። ከዚህም አስቀድሞ ሊቀ ካህናት ዘካርያስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልጄ ማርያም ሆይ አንቺ እንዳደግሽና ለአካለ መጠን እንደደረስሽ ዕወቂ ልትታጪ ትወጃለሽን እግዚአብሔርን የሚፈራ መልካም የሆነ የተባረከ ጐልማሳ እንፈልግልሽን ወይም በሕይወትሽ ዘመን ሁሉ በቤተ መቅደስ ተቀምጠሽ እግዚአብሔርን ልታገለግዪው የምትሺ ከሆነ በሴቶች ላይ የሚደርሰው በሚደርስብሽ ወራት ወደ ቤተ መቅደስ ደጅ ከመግባት ትጠበቂ ዘንድ በኦሪቱ የተጻፈውን የርግማን ሥርዓት በአንቺ ላይ እንሠራለን አላት ። ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምም እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋዩ በፊታችሁ ነኝ አባትና እናት የሉኝም ስሙ ቡሩክ ምስጉን ከሆነ ከእግዚአብሔር በታች በእናትና አባት ፈንታ እናንት ናችሁና የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንደምታውቁ አድርጉ ብላ መለሰች ። ካህናቱና ማኅበሩም ሁሉ ዘካርያስን ወደ ቤተ መቅደስ ገብተህ ስለዚች ብላቴና ማርያም ወደ እግዚአብሔር ጸልይ አሉት ዘካርያስም ገብቶ ሲጸልይ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና እንዲህ አለው ። ዘካርያስ ሆይ ወጥተህ ከዳዊት ወገን ሚስቶቻቸው የሞቱባቸውን ሁሉ ወንዶች ሰብስብ የየአንዳንዱንም በትር ከስሙ ጋር ውሰድ ወደ ቤተ መቅደስም በምሽት አግብተህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይበት በነጋ ጊዜም በትሮቻቸውን አውጣ እግዚአብሔርም በበትሩ ላይ ምልክት ለገለጠልህ ለዚያ ሰው ማርያምን ተቀብሎ ሊጠብቃት ይገባዋል ። ካህኑ ዘካርያስም ወጥቶ አንድነት ለተሰበሰቡት ሕዝብ የእግዚአብሔር መልአክ የነገረውን ነገራቸው በዚያንም ጊዜ ከዳዊት ወገን ጐልማሳም ቢሆን ሽማግሌም ቢሆን ሚስቱ የሞተችበት ሁሉ በኢየሩሳሌም ወደአለ ቤተ መቅደስ ይሒድ እያሉ ዓዋጅን ዙረው የሚናገሩ በእስራኤል አገር ሁሉ ላከ ። ከዳዊት ወገን የሆነ ጠራቢው ዮሴፍም በሰማ ጊዜ በትሩን ይዞ ከናዝሬት ወደ ኢየሩሳሌም ሔደ ካህኑ ዘካርያስም የሁሉንም በትሮች ተቀብሎ ስማቸውን በላያቸው ጻፈ ቁጥራቸውም አንድ ሽህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አምስት ሆነ ዘካርያስም በትሮችን ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ እንዲሁም ሰዎች ሁሉ ከቤተ መቅደስ ውጭ ቁመው ይጸልዩ ነበር ዘካርያስም ጸሎቱን በፈፀመ ጊዜ ለየአንዳንዱ በትራቸውን አውጥቶ ሰጠ ጠራቢው ዮሴፍም በትሩን ሊቀበል በቀረበ ጊዜ ከእርሷ ነጭ ርግብ የመሰለች ተገለጠች እየበረረችም ሒዳ በጠራቢው ዮሴፍ ራስ ላይ ተቀመጠች ካህናቱና ሕዝቡ ሁሉ አይተው እጅግ አደነቁ ምስጉን የሆነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ። ዘካርያስም ዮሴፍን ዮሴፍ ሆይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ እንደ ተናገረ ድንግል ማርያምን ወደ ቤትህ ወስደህ ጠብቃት አለው ዮሴፍም ቅድስት ድንግል ማርያምን ከካህናት እጅ ተቀበላት በእርሱም ዘንድ ኖረች ። ከዚህም በኋላ የመላእክት አለቃ ገብርኤል ስለ እግዚአብሔር ልጅ ከእርሷ ሰው ሁኖ ስለመወለዱ በዮሴፍ ቤት አበሠራት ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአማላጅነቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን ። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ምንጭ:- መጽሐፈ ስንክሳር

👉 ከመዝ ነበርኪ ውስተ ቤተመቅደስ ወመላእክት ያመጽኡ ወትረ ሲሳየኪ ከመ ነበርኪ ፲ወ፪ተ ዓመተ እንተ ትትናዘዚ እምኀበ መላዕክት ስቴኪኒ ስቴኪኒ ስቴ ህይወት ውእቱ ወመብልዕከኒ ኀብስት ሰማያዊ 👉       ትርጉሙም 👉 እንዲህ ኹነሽ በቤተመቅደስ ኖርሽ፤መላዕክትም ዘወትር ምግብሽን ያመጡ ነበር፤መላዕክት እየጎበኙሽ እንደዚህ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖርሽ 👉        ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ✝ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ✝ 🙏 እንኳን ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል (በዓታ ለማርያም ) ወደ ቤተመቅደስ የገባችበት ዓመታዊ በዓል አው ለታላቁ ኢትዮጵያዊ ፃድቅ ለአቡነ ዜና ማርቆስ ዓመታዊ በዓል አው ለሊቀ መላዕክት ለቅዱስ ፋኑኤል ዓመታዊ መታሰቢያ በስላም አደረሳችሁ አደረስን 🙏 ✤ ታኅሣሥ ፫(3) በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ቅድስት ሃና ወቅዱስ ኢያቄም ፋኑኤል ሊቀ መላዕክት ለዕረፍት ለቅዱስ ለአቡነ ዜና ማርቆስ አው ወክብራን ነገሥት ዕረፍቱ ለአፄ ሚኒሊክ ንጉሥ ነገሥት ዘኢትዮጵያ 👉 ✤ ዘነግህ ምስባክ ✤ እበውእ ቤተከ ምስለ መባዕየ ወእሁብ ብፅአትየ ዘነበብኩ በአፉየ ዘእቤ በከናፍርየ አመ ምንዳቤየ ✤ ትርጉም ✤ የሚቃጠል መባእ ጋራ ወደ ቤት እገባለሁ መከራዬን ጊዜ በአፌ የተናገርሁትን ከንፈሮቼም ያሉት ስእለቴን             መዝ ፷፭-፲፫                    65  13 ✤ ወንጌል ✤ ማቴ ም ፩ ቁ ፩-፲፯            1     1  17 ✝ የቅዳሴ ምንባባት ✝ ዕብ ም ፱ ቁ ፩-፲፩ ፪ ዮሐ ም ፩ ቁ ፭-፰ ግብ.ሐዋ ም ፩ ቁ ፲፪-፲፭ ❖ ምስባክ ❖ ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ዘአጽምዒ እዝነኪ ርስዒ ሕዝበኪ ወቤተ አቡኪ እስመ ፈተወ ንጉሥ ሥነኪ 🙏 ትርጉም 🙏 ልጄ ሆይ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ ንጉሥ ውበትሽን ወዶአል              መዝ ፵፬-፲                     44  10 ❖ ወንጌል ❖ ሉቃ ም ፩ ቁ ፴፱-፶፮           1     39  56 ❖ ቅዳሴ ❖ ዘእግዝእትነ " ድንግል ሆይ አንገታቸውን እንደ ሚያገዝፉ እንደ ዕብራውያን ሴቶች ልጆች በዋዛ ያደግሽ አይደለም በንጽሕና በቅድስና በቤተመቅደስ ኖርሽ እንጂ "         ቅዳሴ ማርያም            ም ፩ ቁ ፴፱                1     39 ✝ በዓሉ በዓል ምህረት በዓለ ፀጋ ያድርግልን ፆሙን ፆመ በረከት ያድርግልን ፆሙን ለማበርከት ያብቃን አምላካችን መድኃኒታችን ዘላለም ሥላሴ በቸርነቱ ይማረን ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በምልጇዋ ትጠብቅን ፍቅሯን በልባችን ጣዕሙን በአንደበታችን ታሳደርብን ከበዓሏ እግዝትነ ማርያም በዓታ በረከት ትክፈልን በዕፀ መስቀሉ ይባረክን ይጠብቅን ቤተክርስቲያን ቅድስት በረድኤት ይጠብቅልን በየሰዓቱ በየደቂቃው ጠባቂ መላዕክት አያሳጣን ሊቀ መላዕክት ከቅዱስ ሩፋኤል በምልጃዋ አይለየን ከአባታችን ከአቡነ ዜና ማርቆስ በረከት ይክፈልን።

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤          ❤ #ታኅሣሥ ፪ (2) ቀን። ❤ እንኳን #ለሠለስቱ_ደቂቅ_ለአናንያ_ለአዛርያና_ለሚሳኤል #እግዚአብሔር_ኃይል_ላደረገላቸው ለመታሰቢያ በዓላቸው፣ #ለቅዱስ_አውክያኖስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓልና ከላይኛው ግብጽ ከሚኖሩ ሰዎች ወገን ለሆነ #ለቅዱስ_አባት_ለአባ_ሖር ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከቅዱስ_ፋሲለደስ አገልጋዮቹና ዘመዶቹ ከሆኑ #ከሰባት_ሺህ_ሠላሳ_ሦስት_ከሆኑ_ሰማዕታት ከመታሰቢያቸው፣ #ከአብላፍታን፣ ከዐረብ ወገን ከሆነ #ከሰማዕት_አንበስና_ከመነኰስ_ናትናኤል ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                                        ✝ ✝ ✝ ❤ #ሠለስቱ_ደቂቅ፦ በዚች ቀን ናቡከደነፆር ከአባታቸው ጋር ለማረካቸው ሦስቱ ለሆኑ ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮአቄም ልጆች እግዚአብሔር ኃልን አደረገላቸው። እሊህም አናንያ አዛርያ ሚሳኤል ናቸው በቤቱም ውስጥ አሳድጎ በባቢሎን አገሮች ውስጥ ሾማቸው። ❤ ከዚህም በኋላ ናቡከደነፆር የወርቅ ምስል በሠራ ጊዜ መኳንንቱንና በግዛቱ ውስጥ ያሉትን ሁሉ በዚያ ምስል እንዲሰግዱ አዘዘ እሊህ ቅዱሳን ግን መስገድን እምቢ አሉ በወነጀሏቸውም ጊዜ ከቀድሞው ሰባት እጅ ወደ አነደዱት የእሳት ማንደጃ ውስጥ ይጨምሯአቸው  ዘንድ ንጉሥ አዘዘ። በእሳቱ መካከል ረጅም ጸሎትን ጸለዩ የእግዚአብሔር መልአክም ቅዱስ ገብኤልም ወርዶ እንደ ቀዘቀዘ ነፋስ አደረገው። ❤ ንጉሥ ናቡከደነፆርም ይህን ድንቅ ተአምር በአየ ጊዜ አደነቀ ለእግዚአብሔርም በመገዛት ሰገደ እነርሱንም ከእሳት ማንደጃ ውስጥ አወጣቸው እጅግም አከበራቸው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ ቅዱሳን በሠለስቱ ደቂቅ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_አውክያኖስ፦ እርሱም ሃይማኖቱን ጠብቆ ሰዎች አባለ ዘሩን እስከ ቆረጡት ድረስ ተጋድሎውን የፈጸመ ነው እግዚአብሔርም አመሰገነው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አውክያኖስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ሖር፦ ይህም አባት ደግነት ያለው መነኰስ በመሆን ጽኑዕ ገድልን ተጋደለ በአምልኮቱና በተጋድሎው ከቅዱሳን ሁሉ ተለይቶ በብዙዎች ላይ ከፍ ከፍ አለ ለብቻ መኖርን ስለወደደ ወደ በረሀ ወጥቶ በገድል ተጠምዶ ብዙ ዘመናት ኖረ። የበጎ ሥራ ጠላት የሆነ ሰይጣንም ቀንቶበት በግልጥ ታየውና "በበረሀ ውስጥ ግን አንተ ድል ትነሣናለህ በዚህ ሰው የለምና ጽኑ ኃይለኛ ከሆንክ ወደ እስክንድርያ ከተማ ና" ብሎ ተናገረው። ❤ አባ ሖርም ይህን በሰማ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኃይል ተማምኖ ወደ እስክንድርያ ከተማ ሒዶ ለእሥረኞችና ለችግረኞች ደካሞች ውኃ የሚቀዳ ሆነ በአንዲት ዕለት ሦስት ፈረሶች በከተማው ውስጥ እየዘለሉ ሲያልፉ አንዱ ፈረስ አንዱን ሕፃን ረገጠውና ወዲያውኑ ሞተ ሰይጣንም በሰዎች ልብ አደረና "ይህን ሕፃን ያለዚህ አረጋዊ መነኵሴ የገደለው የለም" ብለው አሰቡ አባ ሖርም መጣና ሕፃኑን አንሥቶ ታቀፈው በልቡም በመጸለይ ክብር ይግባውና ወደ እግዚአብሔር ማለደ በመስቀል ምልክትም በላዩ አማተበ የሕፃኑም ነፍስ ተመለሰች ድኖም ተነሣ ለአባቱም ሰጠው ወደ ከተማ ውጭ ሸሽቶ በመሔድ ወደ በዓቱ ገባ ፈልገውም አላገኙትም ጽድቅንና ትሩፋትንም በመሥራት ብዙ ዘመናት በገድል ተጠምዶ ኖረ። ❤ የሚሞትበት ጊዜ ሲቀርብ ብዙዎች ቅዱሳንን ሲጠሩት አያቸው እጅግም ደስ አለው ልጆቹንም ሰብስቦ በምንኵስና ሥርዓት ጸንተው ትሩፋትን እንዲሠሩ አዘዛቸው ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እርሱ እንደሚሔድ ነገራቸው እርሱም እጅግ አዘኑ ጥቂት ቀንም ታሞ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት በአባ ሖር ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የታኅሣሥ2 ስንክሳር።                             ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለሖር_በምንሀብ_ፍቱን። እስከ ተለዓለ ጥቀ ላዕለ ብዙኃን። ሶበ ተንሥኡ ላዕሌሁ በምክረ ጸላኢ ሰይጣን። ከመ ኢቀተሎ እስከ አእመሩ አብዳን። በኃይለ ጸሎቱ አንሥኦ ለምውት ሕፃን"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የታኅሣሥ_2።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "እገኒ ለከ እግዚኦ በኲሉ ልብየ። ወእነግር ኲሎ ስብሐቲከ። እትፌሣሕ ወእትሐሠይ ብከ"። መዝ 9፥1-2 ወይም መዝ 65፥12-13። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 6፥35-39 ወይም ማቴ 19፥10-15።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ደቂቀ እጓለ እምሕያው እስከ ማዕዜኑ ታከብዱ ልበክሙ። ለምንት ታፈቅሩ ከንቶ ወተኀሡ ሐሰተ። አእምሩ ከመ ተሰብሐ እግዚአብሔር በጻድቁ"። መዝ 4፥2-3 የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 2፥1-ፍ.ም፣ 1ኛ ዮሐ 5፥1-6፣ የሐዋ ሥራ  5፥31-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእነ ነው። መልካም በዓልና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።

ታህሣሥ 1 /፩/
በዚችም ቀን የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ዮሐንስ አረፈ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳኛ ነው። ይህም የከበረ ቀሲስ የሆነ የገምኑዲ አገር ሰው ነው በዘመኑም የቅዱሳን ሰማዕታት የሰርጊስና የባኮስ ቤተ ክርስቲያናቸው ተሠራች ዳግመኛም የአቡቂርና የዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን በምስር መሰብሰቢያ ቅጽር አጠገብ ተሠራች ያነፃቸውም ስሙ እንድርያስ የሚባል እግዚአብሔርን የሚፈራ ያዕቆባዊ አንድ የግብጽ ሰው ነው። እርሱም ለመርዋን ልጅ ለገዢው ለንጉሥ አብደል ጸሐፊው ነው። ይህም አባ ዮሐንስ የወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስን ቤተ ክርስቲያን በእስክንድርያ አገር በታወቀ ቃምስ በሚባል ቦታ የሠራ ነው። በዚህ በንጉሥ አብደል ዘመንም ሦስት ዓመት ያህል ጽኑ ረኃብ ሆነ ይህም አባት ለድኆች ለጦም አዳሪዎችና ለችግረኞች የሚያስብ ሆነ በየሳምንቱም አራት ጊዜ ወርቅና ብር እንጀራም ይሰጣቸዋል አብዝቶ የሚራራ መመጽወትን የሚወድ በጎ ሥራዎችን የሚሠራ ነውና። በዘመኑም ንጉሥ ይዜድ ሙቶ በርሱ ፈንታ መርዋን ነገሠ ይህም አባት በማርቆስ ወንበር ዘጠኝ ዓመት ኖረ በሰላምም አረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ምንጭ:- መጽሐፈ ስንክሳር

                            ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_ቀሌምንጦስ፦ ይህም ቅዱስ ከመንግሥት ልጆች ወገን የሆነ ለሮሜ ንጉሥ የጭፍራ አለቃ ለሆነ ለቀውስጦስ ልጁ ነው ደጎች የሆኑ አባትና እናቱም ቅዱስ ጴጥሮስ የወንጌል ትምህርት በሰበከ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ገንዘባቸውንም ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች ምጽዋት አድርገው ሰጡ። ❤ ከዚህም በኋላ መኰንኑ ቀውስጦስ ወደ ንጉሥ  ሔዶ በዚያው በዘገየ ጊዜ ወንድሙ የመኰንኑን የቀውስጦስን ሚስት ሊአገባት አሰበ እርሷም በአወቀች ጊዜ አባታቸው እስቲመለስ ወደ አቴና ሔዳ ጥበብን ታስተምራቸወሰ ዘንድ ቀሌምንጦስንና ታናሽ ወንድሙን ይዛ በመርከብ ተሳፈረች። በዚያንም ጊዜ ብርቱ ነፋስ በመንፈሱ ማዕበል ተነሥቶ መርከቡ ተሰበረ ቀሌምንጦስም በመርከቡ ስባሪ ተንጠለጠለ የባሕሩም ሞገድ ወደ እስክንድርያ አገር አደረሰውና በዚያ ጥቂት ቀኖች ኖረ። በዚያንም ወቅት የከበረ ሐዋርያ ቅዱስ ጴጥሮስ ቃል ጠራውና ወደ እስክንድርያ አገር እንዲሔድ አዘዘው በሔደም ጊዜ በውስጥዋ የወንጌልን ቃል ሰበከ ከዚህ ከቅዱስ ቀሌምንጦስ በቀር ከአገር ሰው አንድ እንኳን ያመነ የለም እርሱ የቅዱስ ሐዋርያ ጴጥሮስን ትምህርት በሰማ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ የክርስቶስን ጥምቀትን ተጠመቀ። ❤ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም የጌታችንን የመለኮቱን ምሥጢር ለሚያመልኩትም የሚሰጣቸውን ብልጽግናውንና ክብሩን በስሙም ኃይል ድንቅ ተአምራትም እንደሚደረግ ገለጠለት። ከዚችም ዕለት ጀምሮ ቀሌምንጦስ ቅዱስ ጴጥሮስን ተከተለው ደቀ መዝመሩም ሆነ እርሱም የሐዋርያትን ገድላቸውን ከዐላውያን ነገሥታትና መኳንንት የደረሰባቸውን ሥቃይ ሁሉ ጻፈ። ከዚህም በኋላ በብዙ አገሮች ውስጥ አስተማረ ሐዋርያትም በጉባኤ ተነጋግረው የሠሩአቸውን የሥርዓት መጻሕፍትን ለርሱ ሰጡት። ❤ ከዚህም በኋላ በሮሜ አገር ሊቀ ጵጵስና ተሾመ በትምህርቱም ከሰዎቿ ብዙዎችን እግዚአብሔርን ወደማወቅ መለሳቸው። ስለርሱም ከሀዲ ንጉሥ ጠራብሎስ ሰምቶ ጭፍራ ልኮ ወደርሱ አስመጥቶ "ክርስቶስን ክደህ ለአማልክት ስገድ" አለው ትእዛዙንም ባልሰማ ጊዜ በዚያ ያሠቃዩት ዘንድ ወደ አንዲት አገር ሰደደው እርሱ በላዩ እንዳይነሡበት ከአገር ሰዎችና ከዘመዶቹ የተነሣ ፈርቷልና መኰንኑንም ጽኑዕ ሥቃይን እንዲአሠቃየው አዘዘው። ❤ የዚያችም አገር መኰንን በመርከቦች ውስጥ የሚኖር እግሮች ያሉት ከባድ ብረት በአንገቱ ውስጥ አንጠልጥሎ ከባሕር ውስጥ አሠጠመው ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ ወንጌልን እንደ ሰበኩ ሐዋርያትም በመንግሥተ ሰማያት የምስክርነት አክሊል ተቀበለ። ❤ እንዲህም ሆነ አንዲት ዓመትም ስትፈጸም ባሕሩ ተገልጦ እንደተኛ ሁኖ የቅዱስ ቀሌምንጦስ ሥጋ በጥልቁ ባሕር ውስጥ ታየ። እርሱም ሕይወት ያለው ይመስል ነበር ሰዎችም ገብተው ከእርሱ ተባረኩ የከበረ የደንጊያ ሣጥንም አምጥተው ሥጋውን በውስጡ አድርገው አንሥተው ከባሕር ውስጥ ሊአወጡት ፈለጉ ግን ከቦታው ሊአንቀሳቅሱት አልቻሉም ከባሕር ውስጥ መውጣትን እንዳልፈለገ አወቁ በዚያም ትተውት ወደ ቤቶቻቸው ሔዱ። ከዚህም በኋላ በመታሰቢያው ቀን በየዓመቱ ያቺ ባሕር ከቅዱስ ቀሌምንጦስ ሥጋ ላይ የምትገለጥ ሆነች ምእመናንም ሁሉ ገብተው ከእርሱ ይባረካሉ መታሰቢያውንም በማድረግ በዓሉን ያከብራሉ ከዚያም በኋላ ወጥተው ወደቤታቸው ይገባሉ። ❤ ከአስደናቂዎች ተአምራቶቹም ከተጻፋት ያዩ ይህን ተናገሩ በአንዲት ዓመት ከሥጋው ሊባረኩ በገቡ ጊዜ የቅዱስ ቀሌምንጦስ ሥጋው ካለበት ሣጥን ዘንድ ሲወጡ ታናሽ ሕፃን እንደረሱ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚወዱት ቅዱሳኑ ክብራቸውን ከርሱ የተቀበሉትንም ጸጋ ይገልጥ ዘንድ ወዷልና። ወላጆቹም ከወጡ በኋላ ሕፃኑን ፈለጉት ግን አላገኙትም ባሕሩም በላዩ ተከድኖ ነበር ሙቶ በባሕር ውስጥ ያሉ አራዊት የበሉት መስሏቸው አለቀሱለት እንደ ሥርዓቱም በማዕጠንትና በቊርባን ቅዳሴ መታሰቢያውን አደረጉ። ❤ በዳግመኛውም ዓመት ያቺ ባሕር ተገለጣ እንደ ልማዳቸው ገቡ ሕፃኑንም በሕይወት ሁኖ በቅዱስ ቀሌምንጦስ የሥጋ ሣጥን ዘንድ ቁሞ አገኙት "በዚህ ባሕር ውስጥ አኗኗርህ እንዴት ነበር ምን ትበላ ነበር የባሕር አራዊትስ እንዴት አልበሉህም" ብለው ጠየቁት። እርሱም ቅዱስ ቀሌምንጦስ ያበላኝ ነበር እግዚአብሔርም በባሕር ካሉ አራዊት ይጠብቀኝ ነበር" ብሎ መለሰ ሰምተውም እጅግ አደነቁ በቅዱሳኑና ስለ ከበረ ስሙ ደማቸውን በአፈሰሱ ሰማዕታት የሚመሰገን ምስጉን እግዚአብሔርን አመሰገኑት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው ቅዱስ ቀሌምንጦስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የኅዳር 29 ስንክሳር።                            ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለከ_ቀሌምንጦስ_አቡነ። አበ መንፈስነ። ከመ ናጽንዕ ዘልፈ ዘትምህርትከ አሚነ። ጽሒፎሙ ሐዋርያት ኃደጉ ለነ። #ምስለ_ቀሌምንጦስ እንዘ ይብሉ መልእክተ ፈኖነ። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የኅዳር _29።                                                       ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ምስሌከ ቀዳማዊ በዕለተ ኃይል። ወብርሃኖሙ ለቅዱሳን። ወለድኩከ እምከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽባሕ"። መዝ 109፥3። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 2፥1-8።

ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta): ❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #ኅዳር ፳፱ (29) ቀን። ❤ እንኳን #ከሰባ_ሁለት_አርድእት አንዱ ለአንዱ ለሆነው #ለሐዋርያው_ቅዱስ_ጴጥሮስ ደቀ መዝሙር #ለቅዱስ_ቀሌምንጦስ_ለዕረፍት_በዓል፣ ለእስክንድር ዐሥራ ሰባተኛ ሊቀ ጳጳሳት #ለተፍጻሜተ_ሰማዕት_ለቅዱስ_ጴጥሮስ_ለዕረፍት_በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደአሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከጌታችን_ልደት_ወራዊ መታሰቢያ (በዓለ ወልድ) በዓልና በከሀዲው ንጉሥ በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በሰማዕትነት ከዐረፉ #ከአርባ_ሰባት_አእላፋት ከመታሰቢያቸው በዓል እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                         ✝ ✝ ✝ ❤ #ተፍጻሜተ_ሰማዕት_ቅዱስ_ጴጥሮስ፦ የዚህ አባት ወላጅ አባቱ በእስክድርያ አገር ሊቀ ካህናት ስሙ ቴዎድሮስነው እናቱም ስም ሶፍያ እነርሱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ጻድቃን ነበሩ፡፡ ነገር ግን ልጅ ስላልነበራቸው እጅግ ያዝኑ ነበር፡፡ ሶፍያም በአምስተኛኛው ቀን የቅዱሳን ሐዋርያትን የቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስን በዓል ለማክበር ወደ ቤተ ክርስቲያን ስትሄድ ሌሎቹ ሰዎች ከልጃቸው ጋር ለበዓሉ ሲሄዱ አይታ አዘነች፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሄዳ እግዚአብሔርን ልጅ እንዲሰጣት በቅዱሳን ሐዋርያቱ ስም ለመነችው፡፡ በዚያችም ሌሊት የከበሩ ሁለቱ ሐዋርያት ተገለጡላትና "የከበረ ልጅ ትወልጃለሽ ስሙንም ጴጥሮስ በይው" አሏት፡፡ እርሷም ከወለደች በኋላ ስሙን ጴጥሮስ አለችው፡፡ ❤ ሰባት ዓመትም በሆነው ጊዜ የሃይማኖትን ምሥጢር ይማር ዘንድ ወስዳ ለሊቀ ጳጳሳቱ ለአባ ቴዎናስ ሰጠችው፡፡ ሊቀ ጳጳሳቱም በሥርዓት አሳደጉትና ከእርሳቸው ጋር የሚያገለግል ሆነ፡፡ እርሳቸውም ከማረፋቸው በፊት ጴጥሮስ በእሳቸው ቦታ እንዲሾም ተናገሩ፡፡ ካረፉም በኋላ ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ተሾመና በታላቅ ተጋድሎ እየኖረ አገልግሎቱን በሚገባ አከናወነ፡፡ በእርሱም ዘመን የአንጾኪያዋ ታላቅ ሰማዕት ቅድስት ሣራ ልጆቿን ልታስጠምቅ ወደ እርሱ መጣች፡፡ እርሷም የከሀዲው የዲዮቅልጥያኖስ ባለሟል የሆነ የአንዱ መኳንንት ሚስት ነበረች፡፡ በሏ ንጉሡን በመፍራት ሃይማኖቱን ሲክድ እርሷ ግን በእምነቷ ጸናች፡፡ሁለት ልጆችንም ስትወልድ የክርስትና ጥምቀትን ልታስጠምቃቸው አልቻለችም፡፡ ምክንያቱም በአንጾከያ አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ወድመው ነበር፡፡ ወደ እስክንድርያም ሄዳ በአቡነ ጴጥሮስ እጅ ልታስጠምቃቸው አሽከሮቿን ይዛ ተነሣችና በመርከብ ተሳፈረች፡፡ በመሀልም ኃይለኛ ማዕበል ተነሥቶ መርከቢቱ ልትሰምጥ ሆነ፡፡ ቅድስት ሣራም ልጆቿ ሳይጠመቁ እንዳይሞቱ በማለት ጸሎት ካደረገች በኋላ የቀኙን ጡቷን በምላጭ ቀዳ በደሟ የልጆቿን ግንባር በመስቀል ምልክት አደረገችባቸው፡፡ በጀርባቸውና በደረታቸውም ላይ እንዲሁ አድርጋ በባሕሩ ውስጥ አጠመቀቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ታላቅ ፀጥታ ሆነና ማዕበሉ ጠፋ፡፡ ❤ እስክንድርያም ደርሳ ከአባ ጴጥሮስ ዘንድ ልጆቿን ልታስጠምቅ አቀረበቻቸው፡፡ ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስም ብዙ ልጆችን እያጠመቀ በተራ ደግሞ የቅድስት ሣራን ልጆች ሊያጠምቅ ሲል ውኃው እየረጋበት እምቢ አለው፡፡ እስከ ሦስት ጊዜም እንዲሁ ሆነ፡፡ ምን እንደሆነ ቅድስት ሣራን ሲጠይቃት ያደረገችውን ነገረችው፡፡ ይህንንም ሲሰማ እጅግ በመደነቅ "አንዲት ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ትላለች እንዲህም ትሠራለች" ብሎ ጌታችንን አመሰገነው፡፡ እርሷም ፈርታ ይቅር በሉኝ ብላ እግሩ ላይ ስትወድቅ እርሱም "አይዞሽ አትፍሪ፣ ሃይማኖትሽ ፍጹም ነው፣ አንቺ ባጠመቅሻቸው ጊዜ በመለኮታዊ እጆቹ ያጠመቃቸው ባለቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው" አላት፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ሥጋ ወደሙን ከነልጆቿ አቀብሏትና ወደ አንጾኪያ ተመለሰች፡፡ ❤ ሌላው በቅዱስ ጴጥሮስ ዘመን የተፈጸመው ነገር የአርዮስ መነሳት ነው፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችንን "ወልድ ፍጡር ነው" ብሎ የተነሣውንና ሰይጣን በልቡ ያደረውን አርዮስን ከስህተቱ ይመለስ ዘንድ ቅዱስ ጴጥሮስ ብዙ መከረው፡፡ ነገር ግን አርዮስ እምቢ ቢለው እረግሞ አውግዞታል፡፡ የንጉሡን አማልክት እንዳያመልኩ በሁሉ ቦታ ቅዱስ ጴጥሮስ እያስተማረ መሆኑን ከሃዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ሰማ፡፡ ወታደሮቹንም ልኮ አስሮ አስመጣው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ሕዝቡ ስለ እርሱ ሊሞት የተዘጋጀ መሆኑን በተመለከተ ጊዜ ነፍሱን አሳልፎ ሊሰጥ ወደደ፡፡ ሕዝቡንም በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ ካስተማራቸው በኋላ አጽናንቶ አሰናበታቸው፡፡ አርዮስም ቅዱስ ጴጥሮስ በንጉሡ ትእዛዝ እንደሚሞት ካወቀ በኋላ ከውግዘቱ እንዲፈታው አኪላስንና እለ እስክንድሮስን አማላጅ አድርጎ ላካቸው፡፡ እነርሱም አርዮስን ከውግዘቱ እንዲፈታው ሄደው ቅዱስ ጴጥሮስ ለመኑት ነገር ግን እርሱ ከውግዘቱ ላይ ሌላ ውግዘት ጨመረበት፡፡ ❤ ጌታችንም ልብሱ የተቀደደ ልጅ ሆኖ ተገልጦለት "አርዮስ ልብሴን ቀደደብኝ" ብሎኛል ብሎ ለእነ አኪላስ አስረዳቸው፡፡ ይህም ከባሕርይ አባቴ ለየኝ ማለቱ ነው፡፡ ሁለተኛም "ከአርዮስ ተጠበቁ፣ በክህነት ሥራም አትሳተፉ እርሱ ለክብር ባለቤት ለክርስቶስ ጠላቱ ነውና" አላቸው፡፡ ይህንንም ከነገራቸው በኋላ ሕዝቡ ሳያየው ሊገድለው ካለው ንጉሥ ከዲዮቅልጥያኖስ ጋር ስለሞቱ በስውር ተማከረ፡፡ ይኸውም ሕዝቡ ሳይሰማ እንዴት ይገድሉት ዘንድ ነው፡፡ ንጉሡም አስቀድሞ በእስር ቤት አቆይቶ ልዩ ልዩ በሆኑ ጽኑ ማሠቃያዎች አሠቃይቶት ነበር፡፡ አሁንም ቅዱስ ጴጥሮስ በእስር ቤት ሳለ መስኮቱን ሲያንኳኳላቸው ወታደሮቹ ሰው ሳያይና ሳይሰማ በስውር መጥተው አንገቱን እንዲቆርጡት ተማከረ፡፡ ጌታችንንም በጸሎቱ "የደሜ መፍሰስ ለጣዖታት አምልኮ መጨረሻ ይሁን ከሁሉ ዓለምም ይጥፋ…" ብሎ ለመነው፡፡ ወዲያውም ከሰማይ "አሜን ይሁን ይደረግ" የሚል ድምፅ መጣለት፡፡ ይህንንም ድምፅ በእስር ቤቱ አቅራቢያ የነበረች አንዲት ድንግል ብላቴና ሰምታ ለሕዝቡ ተናግራለች፡፡ ❤ አባ ጴጥሮስም ጸሎቱን ከጨረሰ በኋላ የሚሰይፉትን ወታደሮች ጠርቶ "የታዘዛችሁትን ፈጽሙ" አላቸውና መጥተው ሰየፉት፡፡ በማግስቱም ሕዝቡ ቅዱስ ጴጥሮስ በሰማዕትነት ማረፉን በሰሙ ጊዜ ወደ እስር ቤቱ መጥተው ሥጋውን አንሥተው ወደ ቤተ ክርስቲያን አግብተው በወንበሩ ላይ አስቀመጡት፡፡ ይህም ቅዱስ ጴጥሮስን በሕይወት እያለ ከዚህ በፊት በወንበሩ ላይ ሲቀመጥ ማንም አይቶት አያውቅም ነበርና ነው፡፡ አንድ ቀን "በወንበርህ ላይ የማትቀመጥ ለምድነው?" ብለው ጠይቀውት ነበር፡፡ እርሱም "እኔ እግዚአብሔር በወንበሩ ላይ ተቀምጦ አያለሁና ስለዚህ በዚህ ወንበር ላይ መቀመጥን እፈራለሁ" ብሏቸዋል፡፡ ❤ ግንዘቱንም አከናውነው ከተመረጡ ሊቃነ ጳጳሳት ከሥጋቸው ጋር ሥጋውን አኖሩ እርሱም በወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ ወንበር በሹመት የኖረው ዐሥራ አራት ዓመት ነው የተሾመውም ዲዮቅልጥያኖስ በነገሠ በሃያ ስድስት ዓመት ነው ከሥጋውም ብዙ ድንቅ ተአምራት ተገለጡ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም  በቅዱስ አባት በአባ ጴጥሮስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

❤ አባታችን ከሰማይ መስቀል የወረደላቸው ሲሆን ዛሬም በገዳማቸው የሔደ ሰው በወረደው በእጃቸው መስቀል እየተዳበሰ ቆመው በጸለዩበት ባሕር በጠበላቸው ይጠመቃል፡፡ በተጨማሪም ይይዙት በነበረውም  መቋሚያቸው በመዳበስ በረከትን ማግኘት ይቻላል፡፡ ቆመው ከጸለዩበት ባሕር ውስጥ ደረቅ አሸዋ ይወጣል፡፡ አባ ዮሐንስ 500 ዓመት ከኖሩ በኋላ ዕረፍተ ዘመናቸው ሲደርስ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከ15 ነቢያት፣ ከ12 ሐዋርያት፣ ሄሮድስ ያስፈጃቸው ከመቶ አርባ አራት ሺ ሕፃናት፣ ከአብርሃም ከይስሐቅ፣ ከዕቆብ ጋር ሁሉንም ነገደ መላእክትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ሁሉ አስከትሎ መጥቶ ታላቅ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ "ስምህን የጠራ ገዳምህን የረገጠ፣ መባ የሰጠ፣ ቤተ ክርስትያንህን የሠራ ያሠራ የረዳ፣ ገድልህን የሰማ ያሰማ ያስተረጎመ፣ መታሰቢያን ያደረገ እስከ 10 ትውልድ እምርልሀለው፤ ንስሀ ሳይገባ አይሞትም፣ ልጅ መውለድ ባይችል እኔ ልጅ እሰጠዋለሁ፤ ገድልህን በቤትህ ያስቀመጠ እርኩስ መንፈስ፣ ክፉ አጋንንት ቸነፈር ወባ መልአከ ጽልመት አይነካውም፡፡ በገዳምህ መነኵሴ ቢቀበር በሰማይ ክንፍ አበቅልለታለሁ፤ አይሁድም አረማዊም ያላመነ ያልተጠመቀ በገዳምህ መጥቶ ቢያርፍ ይቅር እልልሃለሁ፣ እንደ መቃብሬ ጉልጎታ እንደተቀበረ አድርጌ እቆጥርልሃለሁ…" የሚል ቃል ኪዳን ከሰጣቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ❤ ቅዱስ አባታችንም በ 500 ዓመታቸው ሐምሌ 29 ቀን ዐርፈው በጎንድ ተክለ ሃይማኖት ተቀብረዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር የሚገኘውን ይህንን ገዳም ጻድቁ ራሳቸው ናቸው የመሠረቱት፡፡ ነገር ግን የገዳሙን ስያሜ በአባታቸው በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም አድርገውታል፡፡ አቡነ ዮሐንስ ካረፉ በኋላ በእርግማናቸው መሠረት በመንዝና በይፋት ብርዱ ድርቁ ስለበዛባቸው አንድ ብቁ ባሕታዊ ከበዓታቸው ወጥተው "በሐሜታችሁ ምክንያት እጨ ዮሐንስ ስለረገማችሁ ነው የእርሱን ዐፅም ካላመጣችሁ ብርዱ ውርጩ ድርቁም አይጠፋላችሁም" አሏቸው፡፡ ሕዝቡም አባታችን በጉንድ አቡነ  ተክለ ሃይማኖት ከተቀበሩ ከ 134 ዓመት በኋላ በቅዱሳን እየተመሩ ሄደው በሌሊት ግማሽ ዐፅማቸውን አምጥተው በሀገራቸው አምጥተው ስላስቀመጡ ብርዱና ውርጩ በመንዝ እየቀነሰላቸው መጥቷል፡፡ ❤ ዛሬም በሀገሩ ብርዱና ውርጭ ሲበዛ የጻድቁን ታቦት ሲያወጡ ውርጩ ይጠፋል፡፡ ጠገሮ በሚባለው ገዳማቸው ውስጥ የሚገኘው ጠበላቸው እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ ግማሽ ዐፅማቸውን ከጉንደ ተክለሃይማኖት አምጥተው አርባ ሐራ መድኃኔዓለም አጠገብ በላይ በፍሩክታ ኪዳነምሕረት መጋቢት 18 ፍልሰተ ዐፅማቸው ተከናወነ፡፡ ምድሪቷም ተባረከች፣ የዘሩትንም አበቀለች፣ ውርጩም ብርዱም ቀነሰ፣ ዝናብ አልዘንብ ሲል ወይም ሰብል የሚጨርስ አንበጣ ሲመጣ ታቦታቸው ወጥቶ ምህላ ይያዛል ወድያውም መቅሰፍት ይርቃል፣ ዝናብም ይዘንባል፡፡ ጻድቁ ደመናን፣ ጨረቃንና ፀሐይን በእጃቸው እየያዙ ይጸልዩ ነበር፡፡ በጠገሮ፣ በአዘሎ፣ በፍርኩታና በሌሎቹም ታላላቅ ቦታቦዎች ላይ በእያንዳንዱ ገዳም ሃምሳ ሃምሳ ዓመት በጸሎት ኖረው በአጠቃላይ በ500 ዓመታቸው ነው ያረፉት፡፡ ዐፅማቸው መንዝ ከአርባ ሐራ መድኃኔዓለም አጠገብ ፍርኩታ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡ ከአባታች ከእጨጌ አቡነ ዮሐንስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸውም ይማረን። ምንጭ፦ ገድለ እጨጌ (እጨ) አቡነ ዮሐንስ ዘጠገሮና መዝገበ ቅዱሳን መጽሐፍ።

ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta): ❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤          ❤ #ኅዳር ፳፱ (29) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያኑ_ጻድቃን በጸሎታቸው የተከዜን ባሕር ለሁለት ለከፈሉ #ለአቡነ_ገብረ_መስቀል_ዘለጋሶ ለመታሰቢያቸው በዓል፣ የአየር አጋንንት ከእናቱ ጋራ ተገናግቶ የተወለደው መጥቆራ ተብሎ ይጠራ የነበረው #አቡነ_ተክለሃይማኖትና_አቡነ_ዜና_ማርቆስም_በጸሎታቸው ወደ እግዚአብሔር ለምነው በመስቀሉ ኃይል ድል ካደረጉት በኋላ ወደ ሰው አርአያነት እንዲለወጥ አድገውት ሥሙን ለውጠው አመንኵሰው ለታላቅ የቅድስና ደረጃ ለአበቁቱ #ለአቡነ_ፄዋለ_ጽጽቅ ለዕረፍት በዓል፣ ለታላቁ አባት በፀሐይ ላይ 50 ዓመት፣ በጨረቃ ላይ 50 ዓመት፣ በደመና ላይ 50 እንዲሁም ዓለምን በክንፋቸው በመዞር በደመና ላይ 50 ለኖሩ ከሰው ተወልደው ከመላእክት ለተደመሩ ጻድቅ #ለእጨጌ (እጨ) #ለአቡነ_ዮሐንስ_ዘጠገሮ ለልደታቸው በዓል መታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_ገብረ_መስቀል_ዘለጋሶ፦ ትውልድ አገራቸው ትግራይ አድዋ ሲሆን የአቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌ ሉያ ልጅ ናቸው። አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌ ሉያ ያሳደጓቸው የቆብ አባታቸው ሲሆኑ ያመነኰሷቸው ግን አቡነ እንጦንዮስ ዘደብረ ተንኮክ ናቸው። አቡነ ገብረ መስቀል ዘለጋሶ በጸሎታቸው የተከዜን ባሕር በሁለት የከፈሉ ታላቅ አባት ናቸው። በምናኔ ሕይወት 80 ዓመት ሲቆዩ የሴት ፊት ሳያዩና ዓለምን ሳያውቁ ነው የኖሩት። በትግራይ ሽሬ ዘለጋሶ የተባለውን ትልቅ ገዳም ቆርቁረው በዚያው ዐርፈው ተቀብረዋል። ከአቡነ ገብረ መስቀል ዘለጋሶ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳንና ቅዱሳን በዓላት።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_ፄዋለ_ጽድቅ፡- ይኸውም ቅዱስ አባት ቀድሞ መጥቆራ ተብሎ ይጠራ የነበረ አጋንንት የነበረ ነው፡፡ አባቱም "ፈረጎ" የተባለ የአየር አጋንንት ሲሆን እናቱን ደፍሮ ተገናኛትና መጥቆራ ተወለደ፡፡ እርሱም እጅግ ኃይለኛ ነበርና እነ አቡነ ተክለሃይማኖትንና አቡነ ዜና ማርቆስን ሳይቀር በእጅጉ ይፈትናቸውና ይበረታባቸው ነበር፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖትና አቡነ ዜና ማርቆስም በጸሎታቸው ወደ እግዚአብሔር ለምነው በመስቀሉ ኃይል ድል ካደረጉት በኋላ ወደ ሰው አርአያነት እንዲለወጥ አድገውት አመንኵሰው ለታላቅ የቅድስና ደረጃ አብቅተውታል፡፡ ስሙንም "አቡነ ፄዋለ ጽድቅ" አሉት፡፡ እርሱም በጾም በጸሎት ተወስኖ በእጅጉ በታላቅ ተጋድሎ ኖሮ ከብቃት ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ በሞት ሊያርፍ ሲል ጌታችን ተገልጦለት ታላቅ ቃልኪዳን ገብቶለታል፡፡ በሀገራችን በስሙ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶለት ጽላት ተቀርጾለት ይገኛል፡፡ ከአቡነ ፄዋለ ጽድቅ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከቱን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን። ምንጭ፦ ከገድላት አንደበት።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #እጨጌ (እጨ) #አቡነ_ዮሐንስ_ዘጠገሮ፦  ጻድቁ አባታችን የተወለዱት በኢየሩሳሌም አውራጃ ልዩ ስሙ ሳሬራ በሚባል ቦታ ነው፡፡ የካቲት 28 ቀን ተፀንሰው ህዳር 28 ቀን ተወለዱ፡፡ ነገር ግን በዓለ የልደታቸው በዓል የሚከበረው ከወራዊ በዓላቸው ጋራ ኅዳር 29 ቀን ነው።  አባታቸው ድላሶር እናታቸው እምነ ጽዮን ይባላሉ፡፡ ሲወለዱ በወላጆቻቸው ቤት ውስጥ ብርሃን ወርዷል፡፡ ወላጆቻቸውም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ አባታችን ገና በተወለዱ በ5 ዓመታቸው ወላጆቻቸው ወደ እግዚአብሔር ቤት ይዘዋቸው የእመቤታችንን ሥዕል ተመልክተው በደስታ ተመልተው ሳቁ፡፡ አምላክን የወለደች የብርሃን እናቱ እመቤታችንም ከምሥሉ ወጥታ "በምን አውቀኸኝ ነው?" ብላ አቅፋ ሳመችውና "ከእንግዲ ወዲህ የልጄ አገልጋይ ትሆናለህ ኑሮህም እንደ መላእክት ይሆናል በአንተ ምክንያት ብዙ ሰዎች ይድናሉ በምድር ላይም 500 ዓመት ትኖራለህ…" ብላ ባርካው ተሰወረች፡፡ ❤ ከዚያችም ቀን ጀምሮ አባ ዮሐንስ ለክርስቶስ ተላልፎ ተሰጠ፡፡ 50 ዓመትም በበረሃ ሲጋደል ኖሮ ከ50 ዓመት በኋላ በደመና ተጭኖ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል መሪነት ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ጻድቁ አባታችን በአቡነ ተክለሃይማኖት ዘመን መጨረሻ የመጡ ሲሆን ምንኵስና ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተቀብለው በዚያው በድብረ ሊባኖስ ገዳም ለ50 ዓመት በጾምና በጸሎት በተጋድሎ ኖዋል፡፡ ከዚኽም በኋላ አባ ዮሐንስ ወደ ተዘጋጀላቸው ምድር በቅዱስ ገብርኤል አሳሳቢነት ወደ ጠገሮ መጡ፡፡ ይኽም ጠገሮ ያለው ገዳማቸው በሰሜን ሸዋ በመንዝና ይፋት ክልል መዘዞ በሚባል ቦታ ሲደርሱ በእግር አንድ ሰዓት ከተጓዙ በኃላ ይገኛል፡፡ ❤ ሕዝቡ በተለምዶ እጨ ዮሐንስ እያለ ይጠራቸዋል እንጂ ስማቸው እጨጌ ዮሐንስ ነው፡፡ አቡነ እጨጌ ዮሐንስ መስቀል ከሰማይ የወረደላቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ መስቀሉም ሁልጊዜ ተአምር ይሠራል፡፡ በልደታቸው ቀን ኅዳር 29 ቀን መስቀሉ ከመቅደሱ ወጥቶ በካህናቱ ታጅቦ ወደ ጸበሉ ሲወርድ ከየት እንደመጣ ሳይታሰብ ደመና መጥቶ ከመስቀሉ ላይ ብቻ እረቦና እንደ ጃንጥላ ተዘርግቶ አብሮ ወደ ጸበሉ ይወርዳል፡፡ እዛው ቆይቶ መስቀሉ ሲመለስም አብሮ አጅቦ ይመለስና መስቀሉ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲገባ ደመናው ወዴት እንደተበተነ ሳይታወቅ ይጠፋል፡፡ ይህ በዘመናችንም ጭምር እየታየ ያለ ታላቅ ተአምር ነው፡፡  ❤ አባታችን በታላቀ ተጋድሎ ሣሉ ሰይጣን የሀገሩን ሰዎች በጠላትነት እንዲነሡባቸው አደረገ፡፡ ሰዎቹም አባታችንን እንዴት እንደሚያጠፏቸው ይማከሩ ጀመር፡፡ ሊገድሏቸው ፈልገው ቅድስናቸው በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነውና ፈሩ፡፡ ከዚህም በኋላ "ለምን ከመንደራችን ከወንድ ያረገዘች ሴት ፈልገን እሳቸው አስረገዟት ብለን በሐሰት እንከሳቸው?" ብለው ተማከሩ፡፡ ብዙ ወርቅና ብርም ለአንዲት ሴት ሰጥተው በሐሰት ከእርሱ አርግዣለሁ ብላ እንድትመሰክር አደረጓት፡፡ አባታችንም በሕዝብ ፊት በሐሰት ተከሰሱ፡፡ ጻድቁም "አንቺ ሴት ከእኔ ነው ያረገሽው?" አሏት እርሷም "አዎ ከአንተ ነው ልትክድ ነው እንዴ?" አለቻቸው፡፡ አባታችንም በዚህ አዝነው "በአንቺና በእኔ መካከል እግዚአብሔር ይፍረድ" ሲሉ ያች ሴት ወዲያው ለሁለት ተሰንጥቃ ሞተች፡፡ የአገሩ ሰዎችም እጅግ ፈሩ፡፡ አባታችንም ምድሪቱን እረገሟት፡፡ "የተዘራው ዘር አይብቀልብሽ፣ የተተከለው አይፅደቅ፣ ብርድና ውርጭ ይፈራረቅብሽ" ብለው እረግመዋት በደመና ተጭነው ወደ ሰሜን ጎንደር እስቴ ጉንደ ተክለተሃማኖት ሔዱ፡፡ ❤ አቡነ ዮሐንስ በመላው ኢትዮጵያ ወንጌልን እየተዘዋወሩ ያስተማሩ ሲሆን ከቅድስናቸው የተነሣ በፀሐይ ላይ 50 ዓመት፣ በጨረቃ ላይ 50 ዓመት፣ በደመና ላይ 50 እንዲሁም ዓለምን በክንፋቸው በመዞር በደመና ላይ 50 የኖሩ ከሰው ተወልደው ከመላእክት የተደመሩ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ በይፋት ጠግሮ በዓለወልድ፣ በአፋር አዘሎ፣ በመንዝ ፍርኩታ ኪዳነምሕረት፣ በደብረ ሊባኖስ፣ በጎንድ ተክለ ሃይማኖት በሌሎችም ቦታዎች በመዘዋወር በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡

ሕዳር 28/፳፰/ በዚች ቀን የሀገረ ኒቅዮስ ኤጲስቆጶስ ቅዱስ ሰረባሞን በሰማዕትነት አረፈ ። ይህም ቅዱስ በተወለደ ጊዜ በአባቱ ስም ስምዖን ብለው ጠሩት አባቱም ሲሞት ክርስቲያን ይሆን ዘንድ ወደደ
ሕዳር 28/፳፰/
በዚች ቀን የሀገረ ኒቅዮስ ኤጲስቆጶስ ቅዱስ ሰረባሞን በሰማዕትነት አረፈ ። ይህም ቅዱስ በተወለደ ጊዜ በአባቱ ስም ስምዖን ብለው ጠሩት አባቱም ሲሞት ክርስቲያን ይሆን ዘንድ ወደደ ። መልአክም ተገለጸለትና ወደ ኤጲስቆጶስ አባ ዮሐንስ እንዲሔድ አዘዘው እንዳዘዘውም ሔደ ። እርሱም የጌታችንን ሰው የመሆኑን ምሥጢር ገለጠለት ግን ዘመዶቹ የሆኑ አይሁድን ስለፈራ በኢየሩሳሌም አገር የክርስትና ጥምቀትን ሊአጠምቀው አልደፈረም ። ኤጲስቆጶሱም ስለርሱ ምን እንደሚያደርግ ሲያስብ እመቤታችን ተገልጣለት ወደ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎናስ እንዲልከው አዘዘችው ። ሰረባሞንም እየተጓዘ ሳለ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ ቀደም ብሎ በሰው አምሳል ወደ ቴዎናስ ቀርቦ ስለ ቅዱስ ሰረባሞን አስረዳው ሰረባሞንም በደረሰ ጊዜ የእግዚአብሔርን ሕግ አስተምሮ የከበረች የክርስትና ጥምቀትን አጠመቀው ። ከዚህም በኋላ ኒቅዮስ ለሚባል አገር ኤጲስቆጶስነት ሾመው። እግዚአብሔርም ከሀገረ ስብከቱ ጣዖታትን ደመሰሰ ዳግመኛም አብን ወልድን መንፈስ ቅዱስን አንድ አካል የሚያደርግ የሰባልዮስን ስድብ አስወገደ ። ዲዮቅልጥያኖስም ስለ ቅዱስ ሰረባሞን በሰማ ጊዜ በብዙ ዓይነት ሥቃይ አሠቃየው። ሕዝቡ ሁሉ በእርሱ ምክንያት በጌታችን እንዳያምኑ ንጉሡ ፈርቶ ወደ ላይኛው ግብጽ ሰደደው በዚያ  ቅዱስ ሰረባሞንንም  ለሀገሩ ደቡብ ወደ ሆነ ቦታ ወስደው ራሱን በሰይፍ ቆረጡት ምእመናንም መጥተው ሥጋውን ወስደው በክብር ገነዙትና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት ከሥጋውም ድንቆች ተአምራት ሆኑ። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ምንጭ፦ ስንክሳር