cookie

نحن نستخدم ملفات تعريف الارتباط لتحسين تجربة التصفح الخاصة بك. بالنقر على "قبول الكل"، أنت توافق على استخدام ملفات تعريف الارتباط.

avatar

የማርያም ልጆች ®

በቦሌ ኆኅተ ብርሃን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰ/ት/ቤት ስር የተካተተ የአከባቢው ወጣቶች የዓርብ ጉባኤ ተማሪዎች መማማሪያ ትክክለኛ ገጽ ። ትምህርቶች ፣ መዝሙር እና የተለያዩ ሃይማኖት ቀመስ ጽሑፎችን ከዚህ ያገኛሉ ለጥያቄ እና አስተያየት @kimi_king

إظهار المزيد
مشاركات الإعلانات
359
المشتركون
لا توجد بيانات24 ساعات
-27 أيام
-130 أيام

جاري تحميل البيانات...

معدل نمو المشترك

جاري تحميل البيانات...

††† እንኳን ለመናኙ ንጉሥ ቅዱስ አፄ ካሌብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። ††† ††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! ††† ††† መናኙ ንጉሥ ካሌብ ††† ††† ቅዱሱን ንጉሥ አፄ ካሌብን በዓለም ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በትልቁ ያከብሩታል:: ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አክሱም አካባቢ ካልሆነ ከነ ስም አጠራሩ እንኳ እየተዘነጋ ይመስለኛል:: ነገር ግን ውለታው : ምናኔውና ቅድስናው የማይረሳ ነውና እንኳን በእምነት የሚመስሉን ይቅርና የማይመስሉን ምሥራቅ ኦርቶዶክሶችና ካቶሊኮች ዓመታዊ በዓሉን በወርኀ ጥቅምት ያከብራሉ:: ከአክሱም ነገሥታት በኃይሉም ሆነ በሃይማኖታዊ ቅድስናው አፄ ካሌብ ዋናው ነው:: ቅዱሱ የነገሠው በ485 ዓ/ም አካባቢ ሲሆን እስከ 515 ዓ/ም ድረስ በዙፋኑ ላይ ቆይቷል:: ከመልካም ትዳሩ አፄ ገብረ መስቀልን ጨምሮ ልጆችን ወልዷል:: ††† ስለ ቅዱስ አፄ ካሌብ እስኪ እነዚህን ነገሮች ብቻ እናንሳ:- 1.በንግሥና ዙፋን ከመቀመጡ በፊት የሚገባውን መንፈሳዊ ትምሕርት ጠንቅቆ ተምሯል:: 2.ሃይማኖቱ የጠራና እጅግ የሚደነቅ ነበር:: በእርሱ ዘመን ሃይማኖት ለነገሥታቱ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ ነበር:: እርሱ ግን እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ አምልኳል:: 3.ለእመቤታችንና ለቸር ልጇ የነበረው ጥልቅ ፍቅር የተገለጠና የሚያስቀና ነበር:: 4.ገና በዙፋኑ ሳለ ጸሎትን ያዘወትር ነበር:: 5.ዛሬም ድረስ ሁሉም ክርስቲያኖች የማይረሱትን መንፈሳዊ ቅንዓትን አሳይቷል:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- *በወቅቱ ዐመፀኛው የአይሁድ መሪ ፊንሐስ በሃገረ ናግራን (የአሁኗ የመን) ውስጥ የነበሩ ክርስቲያኖችን ክርስቶስን ካዱ በሚል ጨፈጨፋቸው:: ከተማዋንም ለአርባ ቀናት በእሳት አነደዳት:: ዜናው በመላው ዓለም ሲሰማ በርካቶቹ ቢያዝኑም የተረፉትን ለመታደግ የሞከረ አልነበረም:: ቅዱስ አፄ ካሌብ ግን የሆነውን ሲሰማ ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብቶ በግንባሩ ሰገደ:: ወደ ፈጣሪም ጸለየ:- "ጌታዬ ሆይ! የክርስቲያኖችን ደም እመልስ ዘንድ እርዳኝ? እኔ በጦሬ ብዛት አልመካም:: እኔ ተሸንፌ ክርስትና ከሚናቅ እዚሁ ግደለኝ" ብሎ በበርሃ ላሉ መነኮሳት እንዲጸልዩ ላከባቸው:: ጊዜ ሳያጠፋ በመርከብና በፈረስ : በበቅሎና በግመል ናግራን (የመን) ደረሰ:: ፊንሐስን ገድሎ ሠራዊቱንም ማርኮ ክርስቲያኖችን ነጻ አወጣ:: ደምና እንባቸውንም አበሰ:: አብያተ መቅደሶችን አንጾላቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ:: ወዲያው እንደተመለሰ ወደ አክሱም ጽዮን ገብቶ "ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ስላደረክልኝ የምሰጥህ ሰውነቴን እንጂ ሐብቴን አይደለም" ብሎ መንግስቱን ለልጁ ገብረ መስቀል አውርሶ ከዙፋኑ ወጣ:: የወርቅ አክሊሉን ወደ ኢየሩሳሌም ልኮ እርሱ በአባ ጰንጠሌዎን እጅ መንኩሶ መነነ:: (በፎቶው ላይ የምታዩት አፄ ቅዱስ ካሌብ የመነነበት : አክሱም አካባቢ የሚገኝ የአባ ጰንጠሌዎን ገዳም ነው) ከዚሕች ዓለም ከአንዲት ረዋት (ኩባያ) : ከአንዲት ሰሌንና ከአንዲት ቀሚስ በቀር የወሰደው አልነበረም:: ከዚያም በበዓቱ ውስጥ በጾምና በጸሎት ተወስኖ አንድም ሰው ሳያይ በሰባ ዓመቱ (በ529 ዓ/ም) ዐርፏል:: ጌታችንም በሰማይ ክብርን አጐናጽፎታል:: ††† ለቅዱስ አፄ ካሌብ የተለመነ አምላክ ለእኛም ይለመነን:: በጻድቁም ጸሎት ከመከራ ይሠውረን:: ††† ግንቦት 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት 1.ቅዱስ አፄ ካሌብ (መናኙ ንጉሠ ኢትዮጵያ) 2.ቅዱስ አሞንዮስ ገዳማዊ (ታላቁ አሞኒ ዘቶና) 3.ቅድስት ሳድዥ የዋሂት 4.አባ ሖር ጻድቅ 5.አባ ዳርማ ገዳማዊ 6.ቅዱስ ዘካርያስ አንጾኪያዊ 7.አባ በትረ ወንጌል ዘደብረ ሊባኖስ ††† ወርኀዊ በዓላት 1.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት (ሰማዕት) 2.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር 3.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ ††† "አቤቱ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል:: በማዳንህ እጅግ ሐሴትን ያደርጋል:: የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው:: የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም:: በበጐ በረከት ደርሰህለታልና:: ከከበረ ዕንቁ የሆነ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ:: ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም:: ለረጅም ዘመን ለዘላለሙ:: በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው::" ††† (መዝ. ፳፥፩-፭) ††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
إظهار الكل...
++"+ በተኩላና በእባብ ላይ ትጫማለህ:: አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ:: በእኔ ተማምኗልና አስጥለዋለሁ:: ስሜንም አውቁዋልና እጋርደዋለሁ:: ይጠራኛል እመልስለትማለሁ:: በመከራውም ጊዜ ከእርሱ ጋር እሆናለሁ:: አድነዋለሁ: አከብረውማለሁ:: ረጅም እድሜን አጠግበዋለሁ:: ማዳኔንም አሳየዋለሁ:: +"+ (መዝ. 90:13-16) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
إظهار الكل...
✞✝✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✝✞ ❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖ ❖ ግንቦት 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት +✝+ አባ ዓቢየ እግዚእ +✝+ ❖ጐንደር ከተማ ነዋሪ ከሆኑ: ወይም ከተማዋን የሚያውቁዋት ከሆነ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎ:: (እንደ ወትሮው ሁሉ) ከተማዋ ውስጥ ጅብና እባብን የመሠሉ አራዊት ነዋሪውን ሲገድሉ: ወይም ሲያቆስሉ ተመልክተው: ካልሆነም በታሪክ ሰምተው ያውቃሉ? ☞ መልስዎ "በጭራሽ አላውቅም" እንደሚሆን እገምታለሁ:: (ምክንያቱም ሆኖ አያውቅማ!) +ነገሬን እንዲረዱኝ ሌሎች የሃገራችን ዋና ዋና ከተሞችን ልብ ይበሉልኝ:: እንኳን በሌሊት በቀንም አራዊቱ አይጠፉባቸውም:: "ታዲያ ጐንደር ከተማ ውስጥ ጅብ የማይገባው: እባብና ጊንጥ ሰው የማይገድለው ግን ለምን?" ካሉ በጻድቁ በአባ ዓቢየ እግዚእ ቃል ኪዳን ምክንያት ነው:: (ሁሉም የሃገራችን ከተሞች የተባረኩ መሆናቸውን ሳንዘነጋ ማለት ነው) +ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- +አባ ዓቢየ እግዚእ የተወለዱት በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ትግራይ ተንቤን (መረታ) ውስጥ ነው:: የተባረኩ ወላጆቻቸው ያፍቅረነ እግዚእና ጽርሐ ቅድሳት ይባላሉ:: አጥምቀው 'ዓቢየ እግዚእ' ሲሉ ስም ያወጡላቸው የወቅቱ ዻዻስ ሰላማ መተርጉመ መጻሕፍት ናቸው:: ትርጉሙም "በጌታ ዘንድ ታላቅ ሰው" ማለት ነው:: +ዓቢየ እግዚእ በሕጻንነታቸው ሌሊት ሌሊት ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሲጸልዩ አድረው ቀን ቀን እየተማሩ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቁ:: ገና በወጣትነታቸው ወደ ታላቁ መነኮስ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ደብረ በንኮል ሔደው መንኩሰዋል:: +በገዳሙ በጾም: በጸሎትና በስግደት ተወስነው ከኖሩ በኋላ ወደ ዋልድባ ሔደው የተሰወረች ቤተ ክርስቲያን አግኝተዋል:: በጊዜው በ40 ቀን አንዲት ቅጠል ብቻ ለቁመተ ሥጋ ይበሉ ነበር:: +ከዚያም ወደ ሃገራቸው ተንቤን ተመልሰው ዛሬም ድረስ ድንቅ ሆኖ የሚታየውን ገዳም መሥርተው ብዙ መናንያንን አፍርተዋል:: ዓቢየ እግዚእ ገዳማዊና ጻድቅ ብቻ ሳይሆን ሐዋርያዊ አባትም ነበሩ:: ከትግራይ እስከ ደንቢያ ደግሞ ሃገረ ስብከታቸው ነው:: +አንድ ጊዜ ደቀ መዛሙርትን አስከትለው ለስብከት ሲንቀሳቀሱ ተከዜ ወንዝ አካባቢ ደረሱ:: ቀኑ ነሐሴ 10 ነውና ተከዜ እስከ ገደፉ ሞልቶ ለ3 ቀናት ባለመጉደሉ ከ1,000 በላይ ሰዎች ሲያለቅሱ ደረሱ:: ጻድቁ ባካባቢው የነበሩት ኢ- አማንያን (አሕዛብ) ቢሆኑም ራርተዋልና "አምላከ ሙሴ" ብለው ጸልየው ወደ ጥልቁ ውስጥ ገቡ:: +ቅዱስ ሚካኤል አብሯቸው ነበርና ተከዜ ግራና ቀኝ ተከፍሎ መሃሉ የብስ ሆነ:: ይሕን ድንቅ ያዩ ከ1,000 በላይ አሕዛብም አምነው በጻድቁ እጅ ተጠምቀዋል:: ይሕም ዘወትር ነሐሴ 10 ቀን በቤተ ክርስቲያናቸው (ጐንደር) ይከበራል:: +ከዚያም እያስተማሩ ጐንደር ደረሱ:: ያኔ ጐንደር በቀሃና አንገረብ ወንዞች የታጠረች አንዲት መንደር ነበረች:: ጻድቁ ቀን ቀን እየሰበኩ ማታ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናቸው የታነጸበት ሥፍራ ላይ ሲጸልዩ ያድሩ ነበር:: +በዚያ ዘመን ጐንደር ውስጥ ጅብ: እባብና መሠል አራዊት ገብተው ሕዝቡን ጨረሱት:: ይሕንን የተመለከቱት አባ ዓቢየ እግዚእ ወደ እግዚአብሔር አለቀሱ:: በፍጹም ልባቸውም ስለ ሕዝቡ ለመኑ:: +የለመኑትን የማይነሳ ጌታ ወደ ጻድቁ ቀርቦ "በስምሕ የተማጸኑ: በቃል ኪዳንህ ያመኑ: በምድር አራዊት አይሠለጥኑባቸውም:: በሰማይም እሳትን አያዩም:: ጐንደርንም አራዊት ገብተው ሰውን አይጐዱም::" ብሏቸው አርጓል:: +ጻድቁም የወንጌል አገልግሎታቸውን ፈጽመው ወደ ገዳማቸው ተንቤን ተመልሰዋል:: ይሔው እኛ ምን ብንከፋ: ጻድቁንም ብንረሳቸው እግዚአብሔር ግን ዛሬም በጻድቁ ምልጃ ከተማዋን ጠብቆ ይኖራል:: ነገን ደግሞ እርሱ ያውቃል:: ዛሬ ቤተ ክርስቲያኑ የታነጸበት ቦታ (ጎንደር ቀበሌ 09 ኪዳነ ምሕረት) ጻድቁ የጸለዩበት ቦታ ነው:: እንኳን በወርሃዊ በዓላቸው (በ19) ይቅርና በዓመታዊ በዓላቸው (ግንቦት 19) ለንግስ የሚመጣው ሰው ቁጥር ያስተዛዝባል:: +አባ ዓቢየ እግዚእ በገዳማቸው ተንቤን ለብዙ ዘመናት በቅድስና ኑረው: 3 ሙታንን አስነስተው: ብዙ ድውያንን ፈውሰው: ብሔረ ብጹዓንን ጎብኝተው: የድኅነት ቃል ኪዳንም ተቀብለው: በ140 ዓመታቸው ግንቦት 19 ቀን አርፈዋል:: የጻድቁ ክብር ለሁሉ ነውና እባካችሁ እናስባቸው:: +<< ተአምሪሁ ለጻድቅ አቡነ ዓቢየ እግዚእ - - - ጸሎቱ ወበረከቱ የሃሉ ምስለ ኩልነ ሕዝበ ክርስቲያን ለዓለመ ዓለም:: አሜን:: >>+ +<< ከበዙ ተአምራቱ አንዱን >>+ =>ጻድቁ አባ ዓቢየ እግዚእ በገዳማቸው #ተንቤን (መረታ) ሳሉ አንዲት መበለት መጥታ "አባቴ! የምጠጣውን ጸበል ባርከህ ስጠኝ?" አለቻቸው:: ጻድቁም በውሃው ላይ ጸሎትን አድርሰው : በመስቀላቸው ባርከው ሰጧት:: +ወደ ባልንጀራዋ ስትደርስ ግን ሐሳቧን ቀየረችና "ልጠጣው" ብላ የተቀበለችውን ማይ (ጸበል) ልትጠመቅበት (ልትጸበልበት) ወሰነች:: ባልንጀራዋንም "በላዬ ላይ አፍሺልኝ" ስትል አዘዘቻት:: +ባልንጀራዋም "እሺ" ብላ ልታፈስላት (ልትጸብላት) በፋጋ (ግማሽ ቅል) ያለውን ጸበል አነሳች:: ልታፈሰው ስትዘቀዝቀው ግን ከሆነው ነገር የተነሳ 2ቱም ደነገጡ:: ጸበሉ የረጋ ደም ወደ መሆን በቅጽበት ተለውጧልና:: +ፍጹም ፍርሃት የወደቀባቸው ሴቶቹ እየተሯሯጡ ወደ አባ ዓቢየ እግዚእ በዓት ደረሱ:: ከውጭ ሆነውም "አባ! አባ! የሰጠኸን ጸበልኮ የረጋ ደም ሆነ" አሏቸው:: ጻድቁም እንዳላዋቂ "ምን አጠፋችሁ?" ሲሉ ጠየቁ:: +"አባታችን! ምንም አላጠፋንም:: ብቻ አፍሺልኝ ብየ ስሰጣት እንዲህ ሆነ" ስትል አንዷ መለሰች:: ጻድቁ ግን በየውሃት "ልጆቼ! ሁሌም : 'ምንም አላጠፋንም' አይባልም:: ሰው ሆኖ የማይበድል የለምና:: + . . . አንቺም ልጄ! እኔን ያልሺኝ 'የምጠጣው ጸበል ስጠኝ' ነበር:: ግን ልትጸበይበት ወደድሽ:: ስሕተትሽ ከዚህ ይጀምራል:: (የቅዳሴ ጸበል ለመጸበል አይሆንምና) ¤በዚያ ላይ "አልቦ ዓቢይ ኃጢአት ከመ ወልጦ ቃል . . . ከውሸት በላይ ከባድ ኃጢአት የለም::" (ዮሐ. 8:44) + . . . በተጨማሪ ደግሞ ያለ ስልጣኗ እህትሽን 'አጥምቂኝ' አልሻት:: ስለነዚህ ነገሮች ጸበሉ ተለውጦባቹሃል" ብለው ወደ ጸበሉ በመስቀል አማተቡ:: "እፍ" ሲሉትም የረጋ ደም የነበረው ማይ ወደ ጸበልነቱ ተመለሰ:: ይህንን ያዩ ሴቶቹ በግንባራቸው ተደፍተው ለጻድቁ ሰገዱ:: =>ጸሎቱ ወበረከቱ የሃሉ ምስለ ኩልነ ሕዝበ ክርስቲያን ለዓለመ ዓለም:: አሜን:: ❖አምላካችን በወዳጆቹ ምልጃ ሃገራችንን ከክፉው ሁሉ ይሠውርልን:: ❖ግንቦት 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.አባ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ (ኢትዮዽያዊ) 2.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም (የ12ቱ ሐዋርያት መቃብር ከጌታ የተገለጠላቸው ኢትዮዽያዊ) 3.አቡነ ብስጣውሮስ ዘሐይቅ እስጢፋኖስ (ኢትዮዽያዊ) 4.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት ታላቁ (7 ጊዜ ሙቶ የተነሳ) 5."805,007" ሰማዕታት (በአንድ ቀን ብቻ የተገደሉ) 6.አባ ይስሐቅ ገዳማዊ ❖ወርኃዊ በዓላት 1፡ ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት 2፡ ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት 3፡ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ 4፡ አባ ስነ ኢየሱስ ጻድቅ
إظهار الكل...
†✝† እንኩዋን ለጥንተ በዓለ ዸራቅሊጦስ (መንፈስ ቅዱስ) እና ለጻድቁ አባ ገዐርጊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †✝† †✝† በዓለ ዸራቅሊጦስ †✝† ✝✞✝ ከዚሕ በፊት እንደተመለከትነው የጌታችን ዓበይት በዓላቱ 2 ጊዜ (ማለትም ጥንተ በዓልና የቀመር በዓል ተብለው) ይከበራሉ:: ዛሬም ከ1,978 ዓመታት በፊት አምላካችን መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ መውረዱን እናስባለን:: ††† ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- +ቸር አምላክ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል *ከልዑል ማዕርጉ ወርዶ: *በማሕጸነ ድንግል ተጸንሶ: *በኅቱም ድንግልና ተወልዶ: *ከኃጢአት በቀር በግዕዘ ሕጻናት አድጐ: *በ30 ዘመኑ ተጠምቆ: *ቅድስት ሕግ ወንጌልን አስተምሮ: *በፈቃዱ ሙቶ: *በባሕርይ ስልጣኑ ተነስቶ: *በአርባኛው ቀን ያርጋል:: +ታዲያ ደቀ መዛሙርቱን የቅዱስ መንፈሱን ጸጋ ተስፋ እንዲያደርጉ ነግሯቸው ነበርና በተነሳ በ50ኛው ቀን: በዐረገ በ10 ቀን ተስፋውን ፈጸመላቸው:: +እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ እንድትይዝ በአንድ ላይ ሰብስባ ለክብረ መንፈስ ቅዱስ አብቅታቸዋለች:: 120ው ቤተሰብ ከጌታችን እናት ጋር ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ በአውሎ ንፋስ አርአያ ወርዶ በአምሳለ እሳት አደረባቸው:: +ቅዱሳን ሐዋርያት ፈሪዎች የነበሩ ደፋሮች: አሮጌ ሕሊና የነበራቸው ሐዲሶች ሆኑ:: በአዕምሮ ጐለመሱ: ቁዋንቁዋ ተናገሩ: ምሥጢርም ተረጐሙ:: በቅጽበትም ብሉይ ከሐዲስ በልቡናቸው ውስጥ ተሞላ:: +ሐዋርያቱ ቅዱስ መንፈስን ተቀብለው ዓለምን በወንጌል ዕርፈ መስቀል አርሰዋል:: አልጫውን ዓለም ጨው ሆነው አጣፍጠዋል:: ሳይሳሱም አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተዋል:: "ኪያሁ መንፈሰ ነሢኦሙ ለለአሐዱ: ሐዋርያት ለሰቢክ አሕጉራተ ዓለም ዖዱ: ሰማዕትኒ ለሕማም ነገዱ::" እንዳለ ደራሲ:: +በዚህ ቀን 2 ነገሮች በትኩረት ይነገራሉ:- 1."የመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክነት:-" *እርሱ ከአብ የሠረጸ: ቅድመ ዓለም የነበረ: በባሕርይ ስልጣኑ ከአብና ከወልድ ጋር እኩል የሆነ: የራሱ ፍጹም አካል ያለው ፍጹም አምላካችን ነውና:: 2."ቅድስት ቤተ ክርስቲያን:-" *አብ ያሰባት: ወልድ በደሙ የቀደሳት: መንፈስ ቅዱስ በጸጋው ያጸናት የክርስቲያኖች አማናዊት አንድነት: አንድም ቤት ናትና:: ዛሬ በጉባዔ ተመስርታለች:: ††† አባ ገዐርጊ ††† =>በዚችም ዕለት የአባ አብርሃም ጓደኛ የከበረ አባ ገዐርጊ አረፈ።ይህም ቅዱስ የክርስቲያን ወገን ነው ወላጆቹ ደጎች ጻድቃን ናቸው።በአደገም ጊዜ የወላጆቹን ከብቶች የሚጠብቅ እረኛ ሆነ።ሁል ጊዜም የምንኵስና ልብስ ይለብስ ዘንድ በልቡ ይመኝ ነበር። ዐሥራ አራት ዓመትም በሆነው ጊዜ የእግዚአብሔር ጸጋ አነሣሳችው በጎቹንም ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ።እየተጓዘም ሳለ ከሩቅ የብርሃን ምሰሶ አየ ወደ ወንዝ እስከ ደረሰ ድረስ ወደ ርሱ ሔደ ከዚህም በኃላ ያ የብርሃን ምሰሶ ከእርሱ ተሰወረ። ያንንም ወንዝ በተሻገረ ጊዜ በሽማግሌ አምሳል ሰይጣን ተገለጠለትና ልጄ ሆይ ዕወቅ ስለ አንተ ልብሱን ቀዶ አባትህን አየሁት እርሱም ያዝናል ያለቅሳል ተመልሰህ የአባትህን ልብ ልትአጽናና ይገባሃል።የዱር አውሬ ነጥቆ የበላህ መስሎታልና አለው። አባ ገዐርጊም ደንግጦ አንድ ሰዓት ያህል ቆመ ከዚህም በኃላ የከበረ ወንጌል ከእኔ ሊሆን አይገባውም ደቀ መዝሙሬም ሊሆን አይችልም ብሏል ብሎ አሰበ።ይህንንም በአለ ጊዜ ሰይጣን እንደ ጢስ ሆኖ ተበተነ።አባ ገዐርጊም ሰይጣን እንደ ሆነ አወቀ በዚያን ጊዜም ያ የብርሃን ምሰሶ ደግሞ ተገለጠለት የእግዚአብሔርም መልአክ በመነኵሴ አምሳል አብሮት ተጓዘ ቅዱሱም መልአኩን ተከተለው እርሱም ከአባ አርዮን ገዳም አደረሰው።አባ ገዐርጊም ከአንድ ጻድቅ ሰው መነኵሴ ጋራ በዚያ ዐሥራ አራት ዓመት ወጥሳይቀምስ ወይን ሳይጠጣ የአትክልት ፍሬም ቢሆን በዚህ በዐሥራ አራት ዓመት ያህል ከሚቀመጥ በቀር አልተኛም። ተጋድሎውንም በጨመረ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና እንዲህ አለው ሥጋህ እንዳይደክም በመካከለኛ ገድል ተጋደል ብሎሃል ጌታ።ከዚህም በኃላ ሊሠራው የሚገባውን ሥርዓት ሠራለት ።ሁል ጊዜም እስከሚመሽ እንዲጾም ትንሽም እንጀራን እንዲበላ ከአራት ሰዓት እስከ መንፈቀ ሌሊት ስለ ሥጋው ዕረፍት እንዲተኛ በቀረው ሌሊት እስቲነጋ ተግቶ እንዲጸልይ። በዚህም ተጋድሎ ብዙ ዘመናት እየተጋደለ በኖረ ጊዜ በበረሀ ውስጥ ብቻውን ሊኖር ወዶ በጫካ ውስጥ እየተመላለሰ ሁለት ዓመት ኖረ።ከዚህም በኃላ ጌታ ተገለጾለት ወደ ቦታው እንዲመለስ አዘዘው።ያን ጊዜም አምላካዊት ኃይል ከከበሩ መክሲሞስና ደማቴዎስ ገዳም አደረሰችው እርሷም ለደብሩ አቅራቢያ ናት። ወደ ደብሩም በተመለሰ ጊዜ በዚያን ወቅት አብርሃም ከዓለም ወደዚያ ገዳም መጥቶ ሁለቱም ተገናኙና በአንድነት ተስማምተው የአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት ወደ ሆነ ወደ አባ ዮሐንስ ደረሱ።እርሱም ቦታ ሰጥቷቸው በውስጡ ኖሩ ያ ቦታም እስከ ዛሬ ታውቆ ይኖራል ። ያቺም ዋሻ በግቢግ ትባላለች የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐለት የሆነ ጣሪያዋን ሠንጥቆ ወደ እነርሱ የወረዳበት ናት ።እነርሱም ሰገዱለት ሰላምታም ሰጥቷቸው አጽናንቷቸው ከእርሳቸው ዘንድ ዐረገ።በዚያችም ጌታችን በወረደበት መስኮት ብርሃንን አዩ እስከ ዛሬም የተከፈተች ሁና ትኖራለች። እሊህ ቅድሳንም ለመነኰሰኘሳት የሚሆን ብዙ ድርሳናትንና ብዙ ተግሣጻትን ደረሱ።ለአባቶቹ የሚታዘዘውንና የሚገዛውን አመሰገኑት።ከዚህም በኃላ አባ አብርሃም ጥር ሁለት ቀን አረፈ።ከእርሱ በኃላም የከበረ አባ ገዐርጊ በዚች በግንቦት ወር በዐሥራ ስምንት ቀን አረፈ።መላ ዕድሜውም ሰባ ሁለት ዓመት ሆነ።በዓለም ዐሥራ አራት ዓመት በምንኩስና ኃምሳ ስምንት ዓመት ነው።ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትሁን አሜን። =>በዚችም ዕለት የሰማዕት ሲኖዳ መታሰቢያው ነው በረከቱ ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን። =>አምላከ ገዐርጊ ከቅዱስ መንፈሱ ጸጋ ለኃጥአን ባሮቹ ያድለን:: =>ግንቦት 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱሳን ሐዋርያት ወአርድእት 2.አባ ገዐርጊ ገዳማዊ 3.ቅዱስ ሲኖዳ ሰማዕት =>ወርሐዊ በዓላት 1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ 2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን) 3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ 4.ማር ያዕቆብ ግብፃዊ =>+"+ በዓለ ሃምሳም የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ ድንገት እንደሚነጥቅ አውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ:: ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው:: እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው:: በእያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው:: በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው:: መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር:: +"+ (ሐዋ. 2:1-4) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>> https://t.me/zikirekdusn
إظهار الكل...
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ)

በዚህ ቻናል ዲ/ዮርዳኖስ የሚያስተምራቸው ወቅታዊ እና የነገረ ቅዱሳን (ዝክረ ቅዱሳን ትምህርቶችን ከእርሱ በመቀበል እናስተላልፋለን):: "ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/

🌿እንኳን ለታላቁ የቤተ ክርስቲያን ጠበቃ ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። ✝በስመ አብ፡ ወወልድ፡ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ♱ቅዱስ ኤዺፋንዮስ 📝ሊቁ ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ጽድቅ ከቅድስና : ድርሰት ከጥብቅና የተሳካለት አባት ነው:: "ኤዺፋንያ" ማለት የመለኮት መገለጥ ሲሆን "ኤዺፋንዮስ" ማለት ደግሞ ምሥጢረ መለኮት የተገለጠለት ማለት ነው። 💡ቅዱስ ኤዺፋንዮስ የተወለደው ክርስቶስን ከሚጠሉ አይሁዳውያን ቤተሰቦች ቤተ ገብርኤል ውስጥ ነው። ቤተሰቦቹ ከአንድ አህያ በቀር ምንም የሌላቸው ድሆች ነበሩ። በዚያ ላይ በልጅነቱ አባቱ በመሞቱ ከእናቱና ከአንዲት እህቱ ጋር በረሃብ ሊያልቁ ሆነ። ሕጻኑ ኤዺፋንዮስ በአህያው እንዳይሠራ አህያው ክፉ ነበርና ሊሸጠው ገበያ አወጣው። 📝ፊላታዎስ ከሚባል ክርስቲያን ጋር ለግዢ ሲደራደሩ አህያው የኤዺፋንዮስን ኩላሊቱን ረግጦት ለሞት አደረሰው:: በዚህ ጊዜ አብሮት ያለው ክርስቲያኑ በትእምርተ መስቀል አማትቦ አዳነው:: በፈንታው ግን አህያው ሞተ:: ሕጻኑ ኤዺፋንዮስ እያደነቀ ሔደ። 📝ከቆይታ በኋላ ሀብታም አጎቱ ገንዘቡን አውርሶት በመሞቱ ገና በ16 ዓመቱ ባለጠጋ ሆነ:: ያቺ ገበያ ላይ ያያት ተአምር ግን በልቡ ውስጥ ትመላለስ ነበር። 💡አንድ ቀን ደግሞ ሉክያኖስ ከሚባል ክርስቲያን ጋር ሲሔዱ ነዳይ አገኙ:: ባለጠጋው ኤዺፋንዮስ አለፈው:: ያ ድሃ ክርስቲያን ግን የለበሳትን አውልቆ መጸወተው:: በዚሕ ጊዜ መልዐኩ መጥቶ የብርሃን ልብስ ሲያለብሰው ኤዺፋንዮስ ተመለከተ። 📝ኤዺፋንዮስ ጊዜ አላጠፋም:: ከእህቱ ጋር በክርስቶስ አምኖ ተጠመቀ:: ሃብት ንበረቱን ግማሹን መጸወተ:: በተረፈው ደግሞ መጻሕፍትን ገዝቶ ወደ አባ ኢላርዮን ገዳም ገባ:: በዚያም መናንያኑ እስኪያደንቁት ድረስ በፍጹም ትጋትና ቅድስና ተጋደለ። በጸሎቱ ዝናም አዘነመ : ድውያንን ፈወሰ : ብዙ ተአምራትንም አደረገ። 📝 እግዚአብሔርም ደግሞ ለሌላ አገልግሎት ሽቶታልና በቆዽሮስ ደሴት ላይ ዻዻስ ሆኖ ተሾመ:: ብሉይ ከሐዲስ የወሰነ ሊቅ ነውና ብዙ መጻሕፍትን ተረጎመ:: በሺሕ የሚቆጠሩ ድርሳናትን ደረሰ:: በአፍም በመጽሐፍም ብሎ መናፍቃንንና አይሁድን ምላሽ በማሳጣቱ ቤተ ክርስቲያን "ጠበቃየ" ትለዋለች። 📝ከደረሳቸው መጻሕፍት መካከል "ሃይማኖተ አበው ዘኤዺፋንዮስ : መጽሐፈ ቅዳሴውና አክሲማሮስ (ስነ ፍጥረት)" ዛሬም በቅርብ ይገኛሉ:: ሊቁ ቅዱስ ኤዺፋንዮስ በመልካም እረኝነትና በሚደነቅ ቅድስና ተመላልሶ በ406 ዓ.ም. ዐርፏል:: እድሜውም 96 ዓመት ያህል ነበር። 🤲አምላካችን ከቅዱሱ ሊቅ በረከት ያድለን! 🗓 ግንቦት 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት 1. ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ) 2. ቅዱስ ኢላርዮን ገዳማዊ 3. አባ ሉክያኖስ ጻድቅ 4. ቅዱስ ፊላታዎስ ክርስቲያናዊ 🗓 ወርኀዊ በዓላት 1. ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት) 2. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ) 3. ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ 4. አባ ገሪማ ዘመደራ 5. አባ ዸላሞን ፈላሢ 6. አባ ለትጹን የዋህ 📖"የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል። እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው። እኛ ግን የማይጠፋውን። ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም። ነፋስን እንደሚጐስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም። ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጐሰምሁ አስገዛዋለሁ።'' (1ቆሮ. 9:25) ✨ወስብሐት ለእግዚአብሔር✨
إظهار الكل...
👍 1
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ❖ ግንቦት 1 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት +"+ ቅዱስ ናትናኤል +"+ +በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ዘግይቶ ሰማዕትነትን የተቀበለ ይህ ቅዱስ ሐዋርያ ነው:: +ቅዱሱ ሐዋርያ የተወለደው ከእሥራኤላውያን ወላጆቹ ጌታችን በተወለደበት ዘመን አካባቢ ነው:: ይህ በምን ይታወቃል ቢሉ እርሱ ሕጻን እያለ ሔሮድስ 144,000 ሕጻናትን ሲፈጅ እርሱ ግን በእግዚአብሔር ጥበብ ተርፏል:: እናቱ በቅርጫት ውስጥ አድርጋ የበለስ ዛፍ ላይ አስቀምጣው ተደብቃ ታጠባው ነበር:: +ለሐዋርያው ወላጆቹ ያወጡለት ስም ስምዖን ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ናትናኤል ብሎታል:: በባልንጀሮቹ ሐዋርያት ደግሞ የቃናው ስምዖን (ገሊላ ቃና አካባቢ ስላደገ): አንዳንዴም ቀናተኛው ስምዖን ይሉት ነበር:: ምሑረ ኦሪት ነበርና ዘወትር ለሕግ ይቀና ነበር:: +በገሊላ ቃና ሰርግ የደገሰው ዶኪማስ የቅዱስ ናትናኤል የአጎት ልጅ ነው:: ጌታና ደቀ መዛሙርቱን ዶኪማስ የጠራበት አንዱ ምክንያትም ይሔው ነው:: +ቅዱስ ናትናኤል ኦሪትን ከገማልያል ተምሮ: ከበለስ ቁጭ ብሎ ይተክዝ ነበር:: "መሲሕ ምነው ቀረህ" እያለም ይተክዝ ነበር:: ማዕምረ ኅቡዓት አምላካችን ክርስቶስ ይህንን አውቆ በፊልዾስ አማካኝነት ጠርቶታል:: +ናትናኤል ለጊዜው ተከራክሮ ነበር:: በኋላ ግን የጌታችንን ማንነት በደቂቃዎች ተረድቶ አምኗል:: ጌታችንም "ክዳት ሽንገላ በልቡ ውስጥ የሌለበት ንጹሕ እሥራኤላዊ" ሲል አመስግኖታል:: +ሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል ከጌታችን እግር ሥር ምስጢረ መንግስተ ሰማያትን ተምሮ: በጸጋ መንፈስ ቅዱስም ሰክሮ ብዙ አሕዛብን ከጨለማ (ጣኦት አምልኮ) ወደ ብርሃን (አሚነ ክርስቶስ) መልሷል:: እጅግ ብዙ መከራንም ተቀብሏል:: +የጌታችን ወንድም የተባለ ቅዱስ ያዕቆብ በአይሁድ ከተገደለ በኋላም ቅዱስ ናትናኤል የኢየሩሳሌም 2ኛ ኤዺስ ቆዾስ ሆኖ አገልግሏል:: ከአይሁድም ዘንድ ብዙ መከራ ደርሶበታል:: በመጨረሻም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት አልፏል:: በገድለ ሐዋርያት ላይ እንደተጠቀሰው ቅዱሱ ሰማዕት የሆነው በ150 ዓመቱ ነው:: ያ ማለት ደግሞ ከሐዋርያት አባቶች በመጨረሻ ያረፈው እርሱ ነው ያሰኛል:: ❖እግዚአብሔር በቅዱስ ናትናኤል ምልጃ ሃገራችንን ከጥፋት: ሕዝቦቿንም ከመቅሰፍት ይሰውርልን:: ከበረከቱም አይለየን:: =>ግንቦት 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ (ቀናተኛው ስምዖን) 2.ቅዱስ ሚናስ ባሕታዊ 3.ቅዱስ ቀርጢኖስ ሰማዕት 4."400" ቅዱሳን ሰማዕታት =>ወርሐዊ በዓላት 1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ 2.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት) 3.ቅዱስ ሚናስ ግብፃዊ 4.ቅድስት እንባ መሪና 5.ቅድስት ክርስጢና =>+"+ ጌታ ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ 'ተንኰል የሌለበት በእውነት የእሥራኤል ሰው እነሆ' አለ:: ናትናኤልም 'ከወዴት ታውቀኛለህ?' አለው:: ጌታ ኢየሱስም መልሶ 'ፊልዾስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች ሳለህ አየሁህ' አለው:: ናትናኤልም መልሶ 'መምሕር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ:: አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ' አለው:: +"+ (ዮሐ. 1:48-51) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>> https://t.me/zikirekdusn
إظهار الكل...
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ)

በዚህ ቻናል ዲ/ዮርዳኖስ የሚያስተምራቸው ወቅታዊ እና የነገረ ቅዱሳን (ዝክረ ቅዱሳን ትምህርቶችን ከእርሱ በመቀበል እናስተላልፋለን):: "ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/

✝✝✝ እንኩዋን የመነኮሳት አባት ለተባለው "ቅዱስ ዻኩሚስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✝✝✝ +*" ቅዱስ ዻኩሚስ (አባ ባኹም) "*+ =>ዛሬን አያድርገውና ምንኩስና ማለት መላእክትን መስሎ የሚኖርበት ሕይወት ነበር:: ምንኩስና በእግዚአብሔር ፈቃድ በአባ እንጦንስ ቢመሠረትም ሕይወቱን በማስፋፋት ደረጃ የቅዱስ ዻኩሚስን ያሕል የደከመና የተሳካለት ግን የለም:: +ቅዱሱ በትውልዱ ግብፃዊ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን ከቀደመ ሕይወቱ ጋር በተያያዘ የሚተረክ ነገር በመጽሐፈ ገድሉ ላይ አለ:: ዻኩሚስ ወደ ምንኩስናው ዓለም የመጣ በታላቁ አባ ዸላሞን አማካኝነት ነው:: ለተወሰነ ጊዜም መንፈሳዊ አባቱን እየረዳ ሕይወተ መነኮሳትን አጥንቷል:: +በመንፈሳዊ ሕይወቱና በተጋድሎ እየበረታና እየደረጀ ሲሔድ ከአባ ዸላሞን ተለይቶ : ማሕበር መስርቶ ለመኖር አምላኩን ጠይቆ ፈቃድ በማግኘቱ በሕግ የሚመራ የመጀመሪያውን ገዳም መሥርቷል:: +ቅዱስ ዻኩሚስ ጸሎቱ አጋንንትን ከአካባቢው አያስቀርባቸውም ነበር:: አካሉ አልቆ በአጥንቶቹ እስኪቆም ድረስ ጾሟል:: ዓርብ ዓርብ የጌታችንን ሕማማት እያሰበ ከእንባ ጋር ይሰግዳል:: እንባውና ላበቱ ከፊቱ እየወረደ አካባቢው ጭቃ ይሆን ነበር:: ጌታችንም መስቀል ተሸክሞ ይታየው ነበር:: +ስለ ክብሩም መላእክት ወደ ሰማይ ወስደው ገነትና ሲዖልን አሳይተውታል:: አባታችን ቅዱስ ዻኩሚስ ከርሕራሔው የተነሳ አጋንንት ያደሩባቸውን ሰዎች ሲያገኝ በቀጥታ ከመፈወስ ይልቅ ደዌውን : ርኩሳን መናፍስቱንም ወደ እርሱ እንዲገለበጡ ያዛቸው ነበር:: +ከዚያም በጾም : በጸሎትና በስግደት ያማስናቸዋል:: ያኔ በግዳቸው እየጮሁ ሲወጡ ደጉ አባት "ምነው ትንሽ ቆዩ እንጂ" ይላቸዋል:: +አጋንንቱም እያደነቁ "ከገነት ካስወጣነው ከአዳም በቀር እንዲህ ዓይነት ፍጡርስ ዓይተን አናውቅም" ብለው እንደ ጢስ በነዋል:: አጋንንት ስለሚፈሩት "አርበኛው መነኩሴ" ይሉታል:: <<< የቅዱስ ዻኩሚስ ፍሬዎች >>> 1.በግብፅ በርካታ ገዳማትን አቁዋቁሟል:: 2.ለሁሉም ገዳማት አበ ምኔቶችን ሹሞ እየዞረ ይጠብቃቸው ነበር:: 3.የመጀመሪያውን ሥርዓተ መነኮሳት አዘጋጅቷል:: 4.መነኮሳት ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ሹመት እንዳይሾሙ ከልክሏል:: 5.መነኮሳት ከገዳማቸው በፍፁም እንዳይወጡ ከልክሏል:: 6.ከግብፅ ውጪ ምንኩስናን ያስፋፉ አባቶችን አስተምሮ አመንኩሷል:: (ለምሳሌ በኢትዮዽያ ምንኩስናን ያስፋፉት አቡነ አረጋዊ የዚህ አባት ደቀ መዝሙር ናቸው) +ከዚሕም ባለፈ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል:: ቅዱስ ዻኩሚስ ጫማ ሳይጫማ: እሾህን ሳይሰቀቅ ይረግጥም ነበር:: የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ እጥፍ ሆኖ የበዛለት ቅዱሱ መነኮስ ወደ ወደደው እግዚአብሔር በዚህች ቀን ሔዷል:: =>የጻድቁ መነኮስ ጸጋና በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን:: =>ግንቦት 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ አባ ዻኩሚስ (አበ መነኮሳት ሣልሳዊ) 2.አባ ሲማኮስ ሰማዕት =>ወርሐዊ በዓላት 1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል) 2.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ 3.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ 4.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው) 5.አባ ስምዖን ገዳማዊ 6.አባ ዮሐንስ ጻድቅ 7.እናታችን ቅድስት ነሣሒት =>+"+ ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም:: በእናት ማሕጸን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ:: ሰውም የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ:: ስለ መንግስተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ:: ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው:: +"+ (ማቴ. 19:11) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>> https://t.me/zikirekdusn
إظهار الكل...
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ)

በዚህ ቻናል ዲ/ዮርዳኖስ የሚያስተምራቸው ወቅታዊ እና የነገረ ቅዱሳን (ዝክረ ቅዱሳን ትምህርቶችን ከእርሱ በመቀበል እናስተላልፋለን):: "ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ❖ ግንቦት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት +"+ ቅዱስ አርሳኒ +"+ =>ቅድስት ሃይማኖት እዚህ ዛሬ እኛ ጋር የደረሰችው በበርካታ ሰማዕታትና ጻድቃን ደም ነው:: ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግድግዳዎቿ እንጨትና ድንጋይ እንዳይመስሏችሁ:: አጽመ ቅዱሳን ነው እንጂ:: +ቅዱሳን ልዑለ ባሕርይ ክርስቶስን እንደ እኔ እና እንደ ዘመኑ ትውልድ በከንፈራቸው የሚሸነግሉ አልነበሩም:: እነርሱ በፍጹም ልባቸው ስለ ፍቅሩ ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጡ እንጂ:: በቅድስናቸው ከተመሰከረላቸው ቀደምት ቅዱሳን አንዱ ደግም ቅዱስ አርሳንዮስ ነው:: +ቅዱሱ የተወለደው በ345 ዓ/ም ሮም ውስጥ ነው:: በወጣትነቱ ይሕ ቀረህ የማይሉት የጥበብና የፍልስፍና ሰው ነበር:: በተለይ በትልቁ የሮም ቄሳር ቴዎዶስዮስ ዘመን በቤተ መንግስት አካባቢ የተከበረና የንጉሡ ልጆች መምሕር ነበር:: አኖሬዎስና አርቃዴዎስን ቀጥቶ ያሳደጋቸውም እርሱ ነበር:: +በድንግልና እስከ 40 ዓመቱ ድረስ ሮም ውስጥ ቆየ:: ከዚህ በኋላ ግን ስለ ሰማያዊ ነገሮች ሲያስብ መልዐኩ በሕልም ወደ ግብፅ ሒድ አለው:: በመጀመሪያ ወደ እስክንድርያ ቀጥሎ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሒዶ መነኮሰ:: በቆይታ ግን ብሕትውና ምርጫው ሆነ:: +ቅዱስ አርሳኒ በእነዚሕ ነገሮቹ ይታወቃል:- 1.በምንም ምክንያት ከማንም ጋር አያወራም:: (ለ60 ዓመታት በአርምሞ ኑሯል) 2.በቤተ መቅደሱ ግድግዳ ተጠግቶ እንባውን ሲያፈስ የርሱን አካል አርሶ በመሬት ላይ ሲፈስ ይታይ ነበር:: ከእንባው ብዛት ቅንድቦቹ ተላልጠው አልቀው ነበር:: 3.በርካታ ድርሳናትን ደርሷል:: ብዙዎቹ ዛሬም ግብጽ ውስጥ አሉ:: 4.ሸንጎበቱን ወደ ደረቱ አዘንብሎ ስለሚቆም ማንንም ቀና ብሎ አያይም ነበር:: 5.ለጸሎት አመሻሽ 11:00 አካባቢ ላይ ይቆምና ጸሎቱን የሚጨርስ ፀሐይ ግንባሩን ስትመታው ነው:: 6.ሁል ጊዜ ራሱን "አንተ ሰነፍ (ሐካይ) እያለ ይገስጽ ነበር:: 7.በገዳማውያን ታሪክ የርሱን ያሕል በቁመቱ ረዥም አልተገኘም ይባላል:: የራሱ ጸጉር በጀርባው የወረደ ሲሆን ጽሕሙን በስዕሉ ላይ እንደምታዩት ነጭና እስከ መታጠቂያው የወረደ ነበር:: +እነዚህ ግን በጣም ጥቂቶቹ ናቸው:: +ቅዱስ አርሳንዮስ አካሉ በተጋድሎ ደቆ: ለ60 ዓመታት በግሩም መንፈሳዊነት ኑሮ በ100 ዓመቱ በዚሕች ዕለት ዐርፏል:: ❖አምላካችን እግዚአብሔር ከታላቁ የቅድስና ሰው አርሳኒ በረከት አይለየን:: =>ግንቦት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ አርሳንዮስ - አርሳኒ (ጠቢብ ገዳማዊ) =>ወርኀዊ በዓላት 1.እግዚአብሔር አብ 2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላዕክት 3."99ኙ" ነገደ መላዕክት 4.ቅዱስ አስከናፍር 5."13ቱ" ግኁሳን አባቶች 6.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ =>+"+ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል:: ደግሞ ተገርቷል:: ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም:: የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው:: በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን:: በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን:: ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ:: ወንድሞቼ ሆይ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም:: +"+ (ያዕ. 3:7-11) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>> https://t.me/zikirekdusn
إظهار الكل...
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ)

በዚህ ቻናል ዲ/ዮርዳኖስ የሚያስተምራቸው ወቅታዊ እና የነገረ ቅዱሳን (ዝክረ ቅዱሳን ትምህርቶችን ከእርሱ በመቀበል እናስተላልፋለን):: "ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖ ❖ ግንቦት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት +°✝ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ✝°+ =>ለቤተ ክርስቲያን የብርሃን ምሰሶ ስለሆነላት ስለ ታላቁ ሐዋርያዊ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? እንደ እኔ ያለ ኃጥእ: ለባሴ ሥጋና ገባሬ ንስሃ ስለሱ ሊናገር አይቻለውምና:: አባቶቻችን እንደ ነገሩን ስለ አፈ ወርቅ ለመናገር አፈ ወርቅ መሆን ያስፈልጋል:: ግን እስኪ በቅዱሱ አባት ምልጃ ጥቂት ልሞክር:: << ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ማን ነው? >> +ነገዱ ከሶርያ: የተወለደው በ347 ዓ/ም በእስክንድርያ ሲሆን አባቱ አስፋኒዶስ እናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ:: እነርሱ ደግ ቢሆኑ ይህንን እንቁ ልጅ እግዚአብሔር ሰጣቸው:: ዮሐንስ ለክርስቲያን እንደሚገባ በትምሕርትና በጥበብ አደገ:: ገና በሕጻንነቱ ወደ ግሪክ ሔዶ የዘመኑን ሳይንስ (ፍልስፍና) ከአፉ እስከ ገደፉ ተምሮ ተመልሷል:: +ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮችም አንዱ ይሔው ነው:: በዘመናዊም ሆነ በመንፈሳዊ ትምሕርት ይህ ቀረህ የማይሉት ሊቅ የሆነው ገና በ15 ዓመቱ ነበር:: በ2 ወገን የተሳለ ሰይፍ በመሆኑ ስንኳን በሕይወተ ሥጋ እያለ ዛሬም ለንፉቃን ትልቅ የራስ ምታት ነው:: +ቅዱሱ ገና በ16 ዓመቱ ሃብት: ንብረት: ውበት: ክብርና እውቀት የሞላለት ቢሆንም ያለውን ሁሉ ለነዳያን ሰጥቶ መጻሕፍትን ብቻ ሰብስቦ ከባልንጀራው ቅዱስ ባስልዮስ ጋር በርሃ ገባ:: ሰውነቱን በጾምና በጸሎት እየቀጣ በበርሃ ሲኖር ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ወደ እርሱ መጡ:: ሊቀ ሐዋርያት የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ ስልጣን ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ወንጌሉን ሰጥተው ተሰወሩት:: +ከዚህች እለት በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ባሕረ ምስጢራት ሆነ:: ብሉይ ከሐዲስ: ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራዕየ ዮሐንስ ድረስ በአንድምታ ትርጉዋሜ ተነተናቸው:: በተለይ ሐዲስ ኪዳንን እየመላለሰ አመሰጠረው:: ቅዱስ ሕሊናው ሳይታክት: ንጹሕ እጆቹ ሳይዝሉ የጻፋቸው ድርሳናት: መልዕክታትና ትርጉዋሜያት ቢቆጠሩ አሥር ሺህ ሞሉ:: በእውነት ለዚህ አንክሮ ይገባል! የሚገርመው ይህን ሁሉ ሲሰራ እድሜው ገና ለጋ: ማዕርጉም ዲቁና ነበር:: +ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ቅስና ተሹሞ በስብከተ ወንጌል ብዙ ቦታዎችን አዳረሰ:: በቅድስናው ወደውታልና የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት:: አፈ ወርቅ ሲናገርም ሆነ ሲያስተምር እንኳን የሚያወራ ኮሽ የሚል የለም:: ከጣዕመ ትምሕርቱ የተነሳ ሕዝቡ በተደሞ ይሰሙት ነበር:: +ሲያስተምር ምድራዊው ሰው ይቅርና ልዑላኑ መላእክት ተሰብስበው ያደንቁት ነበር:: አንዴም እመቤታችን በሕዝብ መካከል " አፈ-ወርቅ" ብላ ጠርታዋለች:: ለዛም ነው አፈ-ወርቅ የሚባለው:: ቅዱሱ በሥልጣነ ቃሉ መልዐከ ሞትን ገስፆ 10 ዓመት አቁሞታል:: +ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለሰው ፊት አያደላም:: በርሱ ዘንድ ንጉሥና ደሃ ነዳይ እኩል ነው:: ለሞት ያበቃውም ይሔው ነበር:: ምክንያቱም የወቅቱ ንግስት አውዶክስያ ያንዲት ድሃ መበለትን መሬት ቀምታ አልመልስም በማለቷ መክሮ አወገዛት:: እርሷ ግን ከኃጥአንና መናፍቃን ጋር መክራ 2 ጊዜ አጋዘችው:: +በተሰደደበት ፍሬ አፍርቶ: አስተምሮና አሳምኖ በ407 ዓ/ ም አርፏል:: ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ሳይጠግቡት እንደናፈቁት በ60 ዓመቱ አጡት:: በወቅቱ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ:: +አንድ ቀን የዘመኑ ደግ ንጉሥ አርቃድዮስ ግብር አገባ (ግብዣ አዘጋጀ):: በዚያች ሌሊት ደግሞ ቅዱሱ ሊቅ ታጥቆ ሲጸልይ ሳለ: አባ ማርዳሪ የሚባል ጻድቅ ደግሞ ከሰማይ 12ቱ ሊቃነ መላእክት (እነ ቅዱስ ሚካኤል) በግርማ ሲወርዱ ተመለከተ:: +ደንግጦ "ወዴት ናችሁ ጌቶቼ" ቢላቸው "ቁስጥንጥንያ: ወደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንሔዳለን:: እርሱ እመቤታችንን እንደሚያመሰግናት ጌታ ነግሮናልና" አሉት:: "እባካችሁ እኔም የአፈ ወርቅ ምስጋናው እንገለጥልኝ መርቁኝ" አላቸው:: ሊቃነ መላእክቱም መርቀውት ጐዳናቸውን ቀጠሉ:: +በማግስቱ በቤተ መንግስት ውስጥ ሊቃውንቱ: መሳፍንቱ: ዻዻሳቱ: ሕዝቡ ሁሉ ተሰብስበው ከድግሱ በሉ:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ግን በመንበሩ ተቀምጦ ነበር እንጂ አልበላም:: ድግሱ ሲጠናቀቅ ንጉሡ አርቃድዮስ ሊቁን "ጥያቄ አለኝ" ብሎ በጉባኤ መካከል ጠየቀው:: +"ምነው ወንጌላዊ ማቴዎስ 'ኢያዕመራ ዮሴፍ እስከ አመ ወለደት ወለደ ዘበኩራ-የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም' ማለቱ (ማቴ. 1:25) ስለ ምን ነው?" ቢለው ቅዱሱ ተነስቶ: በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይተረጉምለት ጀመር:: +"ድንግል ማርያም ንጹሕ ብርሌን ትመስላለች:: ብርሌ የተለያየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ቢያስገቡበት ቀለሙ አብሮ ይቀያየራል:: እመቤታችንም ጌታን ጸንሳለችና ሕብረ መለኮቱ ሲለዋወጥ መልኳ አብሮ ሲለዋወጥ እያየ ዮሴፍ ይደነግጥ ነበር:: +'እርሷ ማን ናት? በማሕጸኗ ያለውስ ማን ነው' እያለ ይጨነቅ ነበር:: ጌታን ከወለደች በኋላ ግን አንድ ሕብረ መልክ ሆናለችና:: አስቀድሞ ማን እንደ ነበረች አላወቀም:: +አሁን ግን እርሷም ወላዲተ አምላክ: ልጇም አምላክ ዘበአማን መሆኗን አወቀ ማለት ነው" እያለ ሲተረጉም ሰምተው ሁሉም ሲያደንቁ: በዚያ የነበረች ስዕለ አድኅኖ "አፈ ወርቅ! ልሳነ ወርቅ! አፈ በረከት!" ስትል ተናገረች:: +ያን ጊዜ አርቃድዮስ የወርቅ ልሳን በሊቁና በስዕሏ ላይ አደረገ:: አፈ ወርቅ ግን ባጭር ታጥቆ "እሰግድ ለኪ! እሰግድ ለኪ! ወእዌድሰኪ . . ." ብሎ ዛሬ በተአምረ ማርያም የምናውቀውን ምስጋና ሰተት አድርጐ አደረሰላት:: ይህንን ምስጋናም ሊቃነ መላእክቱ ሰምተው እያደነቁ ወደ ሰማይ ወጥተዋል:: +ሊቁ ባረፈ በ35 ዓመቱ: በትንሹ ቴዎዶስዮስ ዘመን: ሥጋው ፈልሷል:: ወደ ቁስጥንጥንያ ሲደርስም ከናፍቆት የተነሳ ታላቅ ዝማሬና እንባ ተደርጓል:: አፈ ወርቅም ቀና ብሎ ሕዝቡን ባርኳል:: ✔ቅዱሱ ሲጠራ እንዲሕ ነው:- *ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ *አፈ በረከት *አፈ መዐር (ማር) *አፈ ሶከር (ስኳር) *አፈ አፈው (ሽቱ) *ልሳነ ወርቅ *የዓለም ሁሉ መምሕር *ርዕሰ ሊቃውንት *ዓምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ) *ሐዲስ ዳንኤል *ሊቀ ዻዻሳት ዘበርትዕ (እውነተኛው) *መምሕር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ *ጥዑመ ቃል - - - +እግዚአብሔር ከቅዱሱ በረከት አብዝቶ: አብዝቶ: አብዝቶ ይክፈለን:: +ዳግመኛ በዚህ ቀን ታላቁ ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥጋቸው ፈልሷል:: ይሕ የተደረገው ጻድቁ ከረፉ ከ56 ዓመታት በኋላ ነው:: በዕለቱም ድንቅ ድንቅ ተአምራት ተፈጽመዋል:: +እናታችን ርሕርሕቷ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ደግሞ በዚሕ ቀን ስሟን ለጠራና መታሠቢያዋን ላደረገ የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብላለች:: ❖ቸር አምላካቸው ከሁለቱም ብሩሃን ቅዱሳኑ ክብር ያድለን::
إظهار الكل...
❖ግንቦት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ (የዓለም ሁሉ መምሕር) 2አቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ጻድቅ (ፍልሠታቸው) 3.ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ (ቃል ኪዳን የተቀበለችበት) 4.አባ አብርሃም ዘደብረ ሊባኖስ 5.ቅዱስ ዕንባቆም ነቢይ 6.እስክንድር ንጉሠ ኢትዮዽያ 7.ቅዱስ መስቀል (የተአምር በዓሉ) 8.አባታችን ያሬድ (የማቱሳላ አባት) 9.ቅዱስ ሚናስ ዲያቆን❖ወርኃዊ በዓላት 1፡ ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት2፡ ቅዱስ ድሜጥሮስ 3፡ ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ 4፡ ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድሌዎስ 5፡ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ 6፡ ቅዱስ ላሊበላ 7፡ ቅድስት መስቀል ክብራ ++"+ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም:: መብራትንም አብርተው በዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያናሩታል:: በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል:: መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ:: +"+ (ማቴ. 5:13-16) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>> https://t.me/zikirekdusn
إظهار الكل...
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ)

በዚህ ቻናል ዲ/ዮርዳኖስ የሚያስተምራቸው ወቅታዊ እና የነገረ ቅዱሳን (ዝክረ ቅዱሳን ትምህርቶችን ከእርሱ በመቀበል እናስተላልፋለን):: "ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/