+ ተአምረ ማርያምና አንዳንድ ጉዳዮች +
(ክፍል አንድ)
ተአምረ ማርያምን በተመለከተ ሲነሡ የነበሩ ጉዳዮችን መቼም ሁሉም ሰው ያውቃቸዋል፡፡ ከመቅድሙ ጀምሮ ‘እንዴት ድንግል ማርያም ከዓለም አስቀድሞ ታስባ ትኖር ነበር ይባላል?’ ‘እንዴት ተአምርዋን የሰማ ሥጋውን ደሙን እንደተቀበለ ይሆንለታል ይባላል?’ ‘ለሥዕልዋ ያልሰገደ ከቆመበት ቦታ ይጥፋ የሚል እርግማን እንዴት በሐዲስ ኪዳን ይነገራል?’ ‘የድንግል ማርያም ባሪያዎች ለመሆን እንሽቀዳደም እንጂ 16ቱን ትእዛዛት በመጠበቅ አይደለም እንዴት ይባላል?’ የሚሉ ጥያቄዎች ከፕሮቴስታንቶች አንዳንዶቹ ሲያነሡ አይተናል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የተነሡትን አንዳንድ ጥያቄዎች እንደመግቢያ እንመልከታቸውና በጉዳዩ ላይ ያለውን ዝርዝር ጉዳይና ዘላቂ መፍትሔ ደግሞ አስከትለን ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
‘‘እንዴት ድንግል ማርያም ከዓለም አስቀድሞ ታስባ ትኖር ነበር ይባላል?’’ የሚለው ጥያቄ ማንም ቢያነሣው ላያስደንቅ ይችላል፡፡ ‘ጸጋ ብቻ’ /Sola gratia/ በሚል አስተምህሮ እግዚአብሔር አስቀድሞ የወሰናቸው ሰዎች ብቻ እንደሚድኑ የሚያምነውን አስተምህሮ /Predestinationን/ እንደ መሠረተ እምነቱ የሚያስተምር ፕሮቴስታንቲዝምን የሚከተሉ የካልቪን ተከታይ የሆኑ ሰዎች /በእርግጥ አንዳንዶቹ አሁን አንቀበለውም እያሉ ነው/ እንዴት ቀድማ ታስባ ትኖራለች የሚል ጥያቄ ሲያነሡ መስማት ትንሽ ያስገርማል፡፡ እኛ ባናምንበትም እንዲያው ድንግል ማርያም ሌላው ቢቀር እነርሱ የሚያምኑበት ‘የPredestination አካል’ የምትሆንበትን ዕድል እንኳን ሊኖር እንደሚችል ቢያስቡ ጥሩ ነበር፡፡
ምክንያቱም የመጀመሪያዋ ክርስቲያን እንደመሆንዋ የተመረጡ /elect/ ከሚሏቸው ውስጥ በመቆጠር እድልዋ ቀዳሚ ናትና ከዓለም አስቀድማ ልትታሰብ ትችል ነበር፡፡
በመሠረቱ እንኳንስ ድንግል ማርያም ማንኛውም ፍጡር በአምላክ ሕሊና ታስቦ ይኖር ነበረ፡፡ ይህም ከፍጡሩ ማንነት አንጻር ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ሁሉን አስቀድሞ ማወቅ ጋር የተያያዘ ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ እንኳን ድንግል ማርያም እኛ ለሁላችን እንኳን ‘ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን ፤ በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን’’ ተብሎ ተነግሮልናል፡፡ ኤፌ. 1፡4
የድንግል ማርያም ጎልቶ የሚነገረው ስለ አንድ ምክንያት ነው፡፡ እግዚአብሔር ከዓለም አስቀድሞ የሰው ልጅን መውደቅ የሚያውቅ እንደመሆኑ የሰውን ልጅም እንዴት እንደሚያድነው ያውቃል፡፡ እንዴት እንደሚያድነው ከዓለም አስቀድሞ ካወቀ ደግሞ በማዳኑ ሥራ ውስጥ እጅግ ወሳኝ የሆነችውን ድንግል ማርያምንም ከዓለም አስቀድሞ ያውቃታል ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‘በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ’ ብሎ ክርስቶስ በደሙ የሚያደርገው ቤዛነት ከዓለም መፈጠር በፊት እንደታወቀ ተናግሯል፡፡ 1ጴጥ. 1፡20 የክርስቶስ በከበረ ደሙ እኛን ማዳኑ ዓለም ሳይፈጠር ከታወቀ ከእርስዋ ሥጋና ደምን ነሥቶ የሚወለድባት ድንግል ማርያም በአምላክ ሕሊና የማትታሰብበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡
በጉባኤ ኒቅያ ‘ጥበብ ጌታ ፈጠረኝ እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ’ የሚለውን አርዮስ የካደበት ምሳ. 8፡23 ላይ ያለው ቃል የተብራራው ‘ፈጠረኝ የሚለው ቃል የተዋሐደውን ሥጋ የሚያጠይቅ ነው’ (ወጥበብኒ ዘትብል ፈጠረኒ እግዚእ ያኤምር በእንተ ዘፈጠረ ለርእሱ ሥጋ በከርሰ ማርያም) ተብሎ ነው፡፡ /ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ 76፡15/ ጥበብ ፈጠረኝ ማለትዋ ቅድመ ዓለም ሥጋን ስለመልበሱ የታወቀ መሆኑን የሚያስረዳ መሆኑ በኒቅያ ጉባኤ እንደ ማስረጃ ከቀረበ ድንግል ማርያም ከዓለም አስቀድሞ በአምላክ ሕሊና ታስባ ለመኖርዋም ትልቁ ማስረጃ ይኼው ጥቅስ ይሆናል፡፡ (ለዝርዝሩ ‘የብርሃን እናት’ ገጽ 324ን ይመልከቱ)
ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ያሳተመው የብዙ ምሁራን የነገረ ማርያም ጥናቶች ስብስብ መጽሐፍ ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ይላል፡፡ ‘Mariology is a new creation or, perhaps, a new way of looking at creation. For this reason, the idea arose quite logically that Mary was chosen in eternity to be the Mother of God, and She is associated with Wisdom, who says in Proverbs 8:23 : Ages ago I was set up, at first, before the beginning of the earth’ ‘ነገረ ማርያም አዲስ ፍጥረት ወይም (ምናልባት) ሥነ ፍጥረትን በአዲስ መንገድ መመልከቻ መነጽር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ማርያም የአምላክ እናት ለመሆን ቅድመ ዓለም የተመረጠች የመሆንዋ ሃሳብ ከበቂ አመክንዮ ጋር ይነሣል፡፡ እርስዋም ‘የመንገዱ መጀመሪያ አድርጎ ፈጠረኝ ፤ ምድርን ሳይፈጥር አስቀድሞ ከዓለም በፊት ሠራኝ’ ከምትለው ጥበብ ጋር ተያይዛ ትነሣለች’ /The Oxford Handbook of Mary, Oxford University, UK 2019 Press 2/
ሁለተኛው ጥያቄ ‘ተአምርዋን የሰማ ሥጋ ወደሙን እንደተቀበለ ይሆንለታል’ የሚለውን ቃል በመጥቀስ ‘እንዴት የክርስቶስ ሥጋና ደም ከተአምረ ማርያም ጋር ሊተካከል ይችላል?’ የሚል ጥያቄ ነው፡፡ ይህም ጥያቄ ከፕሮቴስታንት አቅጣጫ መነሣቱ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ እኔ መረጃ አጥሮኝ ካልሆነ በቀር ከመቼ ወዲህ ነው አንድ ፕሮቴስታንት የሥጋ ወደሙ ተቆርቋሪ የሆነው? የአስተምህሮ ለውጥ ተደርጎ እንደሆነ አላውቅም፡፡ በብዙ ለዘመናት ጸንቶ እንደተቃወመው ግን ፕሮቴስታንቲዝም በክርስቶስ ሥጋና ደም አማናዊነት ጨርሶ አያምንም፡፡ ጌታችን ‘ይህ ሥጋዬ ነው ይህ ደሜ’ ነው ብሎ የሠጠውን ምሥጢረ ቁርባንም ‘አብሮ ከሚበላ የመታሰቢያ ማዕድነት ያለፈ ፋይዳ የለውም’ በሚል አቋም የፕሮቴስታንቱ ዓለም ከካቶሊክና ኦርቶዶክሱ ዓለም ጋር ሲሟገት የአምስት መቶ ዓመት ዕድሜውን እንዳሳለፈ ሁላችን የምንስማማባቸው የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ እነርሱ እንደሚሉት ሥጋ ወደሙ ተራ የመታሰቢያ ማዕድ ከሆነ ደግሞ እውነትም ከመብላት መስማት የተሻለ ጥቅም አለውና ይህንን ቃል ሊቃወሙ የሚችሉበት መሠረት አይኖራቸውም፡፡
የተአምረ ማርያም መቅድም ግን ጉዳዩን የሚጀምረው ተአምርዋን መስማት ምንኛ ከሥጋ ወደሙ ያነሠ መሆኑን በመግለጽ ነው፡፡ ሰው ‘ሥጋውንና ደሙን ይቀበል ፤ ሥጋ ወደሙን ለመቀበል የሚከለክል የታወቀ ምክንያት ከገጠመው ግን ተአምርዋን ሰምቶ ይሒድ’ የሚለው ንግግር ሥጋ ወደሙን ለመቀበል የማይችል ሰው ተአምርዋን መስማት እንደሚችል ያስረዳል፡፡ ተአምረ ማርያም ከሥጋ ወደሙ እኩል ቢሆን ኖሮ ሰውዬውን ሥጋ ወደሙን ከመቀበል የከለከለው ምክንያት ተአምርዋንም ከመስማት ይከለክለው ነበር፡፡ ለምሳሌ ‘በአካል መጥተህ እንድታገኘኝ ነገር ግን በአካል ለመምጣት ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ባትችል ቢያንስ በስልክ ደውልልኝ ፤ ከደወልህልኝ እንደ መጣህ እቆጥረዋለሁ’ ብለህ ለወዳጅህ ነገርኸው፡፡ ይህ ዓረፍተ ነገር በአካል መምጣትና በስልክ መደወልን እኩል ያደርጋል ማለት አይደለም፡፡