cookie

We use cookies to improve your browsing experience. By clicking «Accept all», you agree to the use of cookies.

avatar

ኢ.ዜ.አ

The Ethiopian News Agency dispatches text news, audio and video stories about local and international events to media enterprises and the public. www.ena.et facebook.com/ethiopianewsagency Call +1(202) 205-9932 Ext 13

Show more
Advertising posts
410Subscribers
No data24 hours
No data7 days
No data30 days
Posts Archive
ሐሙስ ሚያዝያ 5/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ ኢሰመኮ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት ርምጃና ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ጥቃት የረድኤት ድርጅት ሠራተኞችን ጨምሮ ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል ሲል ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በክልሉ የተፈጠረው ኹኔታ መፍትሄ ካላገኘ፣ "ለከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስጋት" መኾኑን የጠቀሰው ኢሰመኮ፣ ሁሉም አካላት ችግሩን "በምክክርና መግባባት" እንዲፈቱትና መንግሥትም የፖሊሲ ውሳኔውን ለባለድርሻዎች እንዲያስረዳ ጠይቋል። ኢሰመኮ፣ ጸጥታ ኃይሎች "ያልተመጣጠነና ሕይወት የሚያጠፋ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ" እና መንግሥትም ስለደረሰው ጉዳት ምርመራ አድርጎ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ ጥሪ አድርጓል። 2፤ የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ኡመር የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ከፌደራልና ክልል ጸጥታ ኃይሎች ጋር በሚዋሃዱበት ሁኔታ ዙሪያ ትናንት ከክልሉ ልዩ ኃይል ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ጋር መወያየታቸውን የክልሉ ኮምንኬሽን ቢሮ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ቢሮው፣ ሙስጠፋና የክልሉ ጸጥታ ኃላፊዎች በመንግሥት ውሳኔ ዙሪያ ለልዩ ኃይሉ አመራሮች ማብራሪያ እንደሰጡና በጉዳዩ ላይ መግባባት ላይ እንደተደረሰ ጨምሮ ገልጧል። 3፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምሥራቅ በለሳ ወረዳ የአምቡላንስ ሹፌርና አዋላጅ ነርስ በኾኑ ኹለት ሠራተኞቹ ላይ ማንነታቸው ያልታወቀ ታጣቂዎች ሚያዝያ 1 ቀን ጥቃት እንዳደረሱ አስታውቋል። ኹለቱ ሠራተኞች አይባሽካ ቀበሌ ውስጥ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው በምጥ የተያዘችን አንዲት እናት ጤና ጣቢያ ለማድረስ ሲጓዙ መኾኑና የጠቀሰው ማኅበሩ፣ ሠራተኞቹ ሕክምና ላይ መኾናቸውን ገልጧል። ማኅበሩ ጥቃቱን አውግዞ፣ ታጣቂ ኃይሎች ከመሰል ጥቃት እንዲቆጠቡ ተማጽኗል። 4፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአማራ ክልል ለዕርዳታ ፈላጊዎች የምግብ ዕርዳታ ሥርጭት ማቆሙን መግለጡን ሮይተርስ ዘግቧል። ድርጅቱ በክልሉ የዕርዳታ ምግብ ሥርጭት ለማቆም የተገደድኩት፣ በክልሉ ባለው የጸጥታ ኹኔታ ሳቢያ ነው ማለቱን ዘገባው ጠቅሷል። ድርጅቱ ይህንኑ ውሳኔውን የገለጸው፣ የካቶሊክ ተራድዖ ድርጅት ኹለት ሠራተኞቹ በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ አካባቢ በተከሰተ ግጭት መገደላቸውን መግለጡን ተከትሎ ነው። 5፤ "አራት ኪሎ ሜዲያ" የተሰኘው የዩትዩብ ጣቢያ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው ባሕርዳር ውስጥ ትናንት በቁጥጥር ስር መዋሉን ጣቢያው አስታውቋል። ዳዊትን ይዘው የወሰዱት የመከላከያ ሠራዊት አባላት መኾናቸውን ጣቢያው ገልጧል። ዳዊት ቀደም ሲል "የአል ዓይን ኒውስ" ጣቢያ ጋዜጠኛ የነበረ ሲሆን፣ ባኹኑ ወቅት ደሞ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ማኅበር የሥራ አመራር ቦርድ አባል ጭምር እንደኾነ ተገልጣል። 6፤ በቱኒዝያ ጥቁር አፍሪካዊያን ፍልሰተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች የደኅንነት ስጋት እንደተጋረጠባቸው በመግለጽ በተመድ የስደተኞች ኮሚሽን መስሪያ ቤት ያደረጉትን ሰልፍ ፖሊስ በአስለቃሽ ጭስ በትኖ 80 ሰልፈኞችን ማሰሩን የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ዘግቧል። ሰልፈኞቹና ጥገኝነት ጠያቂዎቹ ኮሚሽኑ ከአገሪቱ ባስቸኳይ እንዲያስወጣቸው መጠየቃቸውን ዘገባው ጠቅሷል። አፍሪካዊያን ፍልሰተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች የደኅንነት ስጋታቸው የተባባሰው፣ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ካይስ ሳዒድ ጥቁር አፍሪካዊያን ፍልሰተኞች በብዛት መግባታቸው የቱኒዚያን ዓረባዊ ማንነት ለማጥፋት ያለመ ሴራ እንደኾነ በመግለጽ ፖሊስ "ሕገወጥ" ፍልሰተኞችን እንዲያባርር ባለፈው የካቲት ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ ነበር።
Show all...
ረቡዕ ሚያዝያ 4/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ ትናንት በአማራ ክልል የኮምቦልቻ ከተማ የጸጥታ ዕዝ ከምሽቱ 3:00 ሰዓት በኋላ ማንኛውም ሰው መንቀሳቀስ እንደማይችል ገደብ መጣሉን አስታውቋል። የጸጥታ ዕዙ፣ በከተማዋ አድማ መጥራት ወይም ማስተባበር፣ ያልተፈቀዱ ስብሰባዎችን ማድረግና ጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የከለከለ ሲሆን፣ ከጸጥታ አካላት ተሽከርካሪዎች ውጭ ባጃጅና ሌሎች ተሽከርካሪዎች ከምሽት 1:00 ሰዓት በኋላ እንዳይንቀሳቀሱ ገደብ ጥሏል። መጠጥና ምግብ ቤቶችም ከምሽቱ 1:00 ሰዓት በኋላ አገልግሎት እንዳይሰጡ ተከልክለዋል። 2፤ በአማራ ክልል የወልድያ ከተማ የጸጥታ ዕዝ ከጸጥታ ሰዎች ውጭ ከምሽቱ 3:00 እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት በከተማዋ የማንኛውንም ሰው እንቅስቃሴ ማገዱን አስታውቋል። በከተማዋ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ፣ ጥይት መተኮስ፣ አድማ መቀስቀስ፣ የጸጥታ አካላትን አልባሳት መልበስ፣ ያልተፈቀዱ ስብሰባዎችን ማድረግ፣ ወታደራዊ ሥልጠና መስጠትን ከልክሏል። ቡና ቤቶች፣ ካፍቴሪያዎችና ምግብ ቤቶች ከምሽቱ 2:00 ሰዓት በኋላ አገልግሎት እንዳይሰጡ፣ ባጃጆችም ከምሽቱ 1:00 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት ድረስ እንዳይንቀሳቀሱ ጭምር ዕዙ አግዷል። 3፤ እናት ፓርቲ፣ መኢአድና ኢሕአፓ መንግሥት የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን ማፍረስ በሚመስል መልኩ በክልሉ ከጀመረው "ግብታዊ እንቅስቃሴ" እንዲቆጠብና የሰሞኑ "የጥፋት ጉዞ እንዲገታ" አዲስ ባወጡት የጋራ መግለጫ ጠይቀዋል። መንግሥት አገራዊ ምክክር ተደርጎ የሕገመንግሥት ማሻሻያ እስኪደረግ ድረስ፣ አገሪቱን "ወደ ሁለንተናዊ ቀውስ እየከተታት ያለውን አካሄድ እንዲያቆም" ፓርቲዎቹ ጥሪ አድርገዋል። የክልሉ ልዩ ኃይል መሳሪያዎቹን ወደ ግምጃ ቤት እንዲያስገባ በጽሁፍ ትዕዛዝ ተላልፎለታል ያሉት ፓርቲዎቹ፣ የመንግሥት ርምጃ "ግልጽነት በጎደለው" ኹኔታ እየተካሄደ መኾኑንና አካሄዱ "አገሪቱን ወደ ሁለንተናዊ ቀውስ የሚያስገባ" መኾኑን ገልጸዋል። 4፤የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮንዶሚኒየዬም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ላይ ተፈጸመ በተባለው የማጭበርበር ወንጀል ከተከሰሱ 11 ግለሰቦች መካከል 5ቱን በነጻ እንዳሰናበተ የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ዛሬ በነጻ ከተሰናበቱት መካከል፣ የከተማዋ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የቀድሞ ሃላፊ ሙሉቀን ሃብቱ እንደሚገኙበት ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ቀሪዎቹ አምስት ተከሳሾች በገንዘብ ዋስትና ከእስር ተለቀው ጉዳያቸውን በውጭ እንዲከታተሉ የተወሰነላቸው ሲሆን፣ በቀጣዩ ግንቦት 2 ቀን የመከላከያ ምስክሮቻቸውን እንዲያሰሙ እንደተቀጠሩ ተገልጧል። አንድ ተከሳሽ ግን በሌለበት የጥፋተኛነት ውሳኔ ተወስኖበታል ተብሏል። 5፤ በደቡብ ክልል ቡታጅራ ከተማ የክልሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከጉራጌ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከታሠሩ ግለሰቦች መካከል ለ17ቱ የዋስትና መብት እንደፈቀደላቸው ተገለፀ ። ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸውን ከጠበቀላቸው ታሳሪዎች መካከል፣ የጉራጌ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አለማየሁ ገብረ መስቀል እና የዞኑ የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ፍስሃ ዳምጠው እንደሚገኙበት ጠቅሷል።
Show all...
#NewsAlert በአማራ ክልል የወልድያ ከተማ የሰላምና ጸጥታ ዕዝ ላልተወሰነ ጊዜ በከተማዋ የሰዓት እላፊ ገደቦችንና ክልከላዎችን ጥሏል። ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ የገቡ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላትና አመራሮች ወደተዘጋጀላቸው ማረፊያ እንዲገቡ ያሳሰበው የጸጥታ ዕዙ፣ በተናጥልና በቡድን ጦር መሳሪያ ይዘው እንዳይንቀሳቀሱና ጥይት እንዳይተኩሱ መከልከሉን ጨምሮ ገልጧል። የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላትን ያስከዳ ወይም ከመንግሥት የጸጥታ ኃይል ጦር መሳሪያ የገዛ ወይም የለወጠ ማንኛውም ሰው በሕግ እንደሚጠየቅም የጸጥታ ዕዙ አስጠንቅቋል። የጸጥታ ዕዙ ለጸጥታ ጥበቃ ከተመደቡ ሰዎች ውጭ፣ ከምሽቱ 12:00 እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት በከተማዋ የማንኛውንም ሰው እንቅስቃሴ ማገዱን፣ በማናቸውም ጊዜና ቦታ ጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ፣ ጥይት መተኮስ፣ አመጽና አድማ መቀስቀስ ወይም ማስተባበር፣ የክልሉን ልዩ ኃይል፣ የክልሉንና ፌደራል ፖሊስ ወይም የመከላከያ ሠራዊት አልባሳትን መልበስ፣ ያልተፈቀዱ ስብሰባዎችን ማድረግ፣ ወታደራዊ ሥልጠና መስጠት፣ በሕግ ተፈላጊ ግለሰቦችን መደበቅ ወይም መረጃ ሰጥቶ ማስመለጥ የመሳሰሉት ድርጊቶች የተከለከሉ መኾኑንም አስታውቋል። ቡና ቤቶች፣ ካፍቴሪያዎችና ምግብ ቤቶች ከምሽቱ 2:00 ሰዓት በኋላ አገልግሎት እንዳይሰጡ፣ ባጃጆችም ከምሽቱ 1:00 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት ድረስ እንዳይንቀሳቀሱ ጭምር ዕዙ ከልክሏል።
Show all...
#NewsAlert በትግራይ ክልል ሽራሮ ከተማ ከሚገኝ የዓለም ምግብ ድርጅት የዕርዳታ መጋዘን ውስጥ ለ100 ሺህ ተረጅዎች የሚበቃ ሰብዓዊ ዕርዳታ መዘረፉን ድርጅቱ በቅርቡ እንደደረሰበት ከሁለት የረድዔት ድርጅት ሠራተኞች ሰምቻለሁ ሲል አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል። ዕርዳታውን የለገሰው የአሜሪካው ዓለማቀፍ የተራድዖ ድርጅት መኾኑንና ዕርዳታውን ማን እንደዘረፈው ግን እስካሁን እንዳልታወቀ ምንጮቹ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል። ድርጅቱ በትክክል ከየትኛው መጋዘኑ ዕርዳታ እንደተዘረፈ ባይጠቅስም፣ በኢትዮጵያ የድርጅቱ ኃላፊ ክላውድ ጂቢዳር ግን ለድርጅቱ አጋሮች በጻፉት ደብዳቤ በአገር ውስጥ ገበያዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ምግብ ለሽያጭ መቅረቡ ድርጅቱን እንዳሳሰበው መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ኹኔታው በድርጅቱ ስምና ወደፊት የምግብ ዕርዳታ ልገሳ ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት ላይ ስጋት እንደሚደቅን ኃላፊው መግለጣቸውንና፣ "ዕርዳታ እንዳይዘረፍና ላልታለመለት ዓላማ እንዳይውል አስቸኳይ ርምጃዎችን መውሰድ መውሰድ እንደሚያስፈልግ" በደብዳቤያቸው መጠቆማቸው በዘገባው ተጠቅሷል።
Show all...
ማክሰኞ ሚያዝያ 3/2015 ዓ.ም ዕለታዊ ዜናዎች 1፤ በአማራ ክልል የደብረብርሃንና ደሴ ከተሞች የጸጥታ ዕዞች የተለያዩ ጸጥታ-ነክ ገደቦችንና ክልከላዎችን ተጥለዋል። በከተሞቹ ከተጣሉት ክልከላዎችና ገደቦች መካከል፣ ከመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ውጪ ጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስለ፣ እውቅና የሌላቸው ስብሰባዎችን ማድረግ፣ አድማዎችን ማድረግ፣ ማስተባበር መቀስቀስ እና መታወቂያ ሳይዙ መንቀሳቀስ ይገኙበታል። በደብረብርሃን ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮችም ላልተወሰነ ጊዜ ከመጠለያ ጣቢያዎች ውጭ እንዳይንቀሳቀሱ ገደብ ተጥሏል። 2፤ ትናንት ምሽት በባሕርዳር ከተማ አባይ ማዶ ቀበሌ ባንድ የሆቴልና መጠጥ መሸጫ በደረሰ የቦምብ አደጋ ሦስት ሰዎች ሞተው 10 ሰዎች መቁሰላቸውን ቪኦኤ ዘግቧል። በአካባቢው የሚገኘው አዲስ ዓለም ሆስፒታል ከ10 በላይ በአደጋው የቆሰሉ ሰዎች ለሕክምና ገብተው እንደነበር መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን መልሶ ከማደራጅት ውሳኔ ጋር በተያያዘ፣ በከተማዋ ከዕሁድ'ለት ጀምሮ አገልግሎት ሰጪና የንግድ ተቋማት ዝግ እንደኾኑ ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል። 3፤ በአማራ ክልል የካቶሊክ ተራድዖ ድርጅት ዕሁድ'ለት በቆቦ ከተማ በነበረ የከባድ መሳሪያ ተኩስ የተገደሉበት ሠራተኞቹ ቾል ቶንጊክ የተባሉ የጸጥታ ሃላፊው እና አማረ ክንደያ የተባሉ ሹፌሩ እንደኾኑ መናገሩን የውጭ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ሁለቱ የድርጅቱ ሠራተኞች የተገደሉት፣ ከአካባቢው ወደ አዲስ አበባ በመንቀሳቀስ ላይ ሳሉ መኾኑን ገልጧል። ኾኖም ሁለቱ ግለሰቦች በምን አኳኋን ሊገደሉ እንደቻሉ ገና እንዳላወቀ ድርጅቱ አስታውቋል። 4፤ የፌደራሉ ጤና ሚንስቴር ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ዛሬ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ጉብኝት እንደሚያደርግ የትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ዘግቧል። የልዑካን ቡድኑን የሚመሩት የጤና ሚንስትር ደኤታው እንደኾኑ ዘገባው ጠቅሷል። ባለፉት ጥቂት ቀናት የትምህርት ሚንስቴር ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በመቀሌ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣናት ጋር መምከሩ ይታወሳል። 5፤ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ዛሬ ሞቃዲሾ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የቻይናው ሲጂቲኤን ዘግቧል። ጉተሬዝ በሱማሊያ ጉብኝት ያደርጋሉ የተባለው፣ በአገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ከ8 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ሱማሊያዊያን የድርቅ ተጎጅዎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊ በኾኑበት ወቅት ላይ ነው። 6፤ የኬንያው ፕሬዝዳንት ሩቶ እና ተቃዋሚያቸው ራይላ ኦዲንጋ ለአገሪቱ መረጋጋት ሲሉ የብሄራዊ አንድነት መንግሥት ለመመስረቱ እንዲደራደሩ ግፊት እየተደረገባቸው መኾኑን ደይሊ ኔሽን አስነብቧል። ከብሄራዊ አንድነት መንግሥት ሌላ፣ ሁለተኛው አማራጭ በመንግሥት ውስጥ ለተቃዋሚ ፓርቲው ሊቀመንበር ራሱን የቻለ ቢሮ ማቋቋም መኾኑን ዘገባው አመልክቷል። ፕሬዝዳንቱ ሁለተኛውን አማራጭ ቢደግፉትም፣ ኦዱንጋ ግን ውድቅ አድርገውታል። ሁለቱ አማራጮቹ የቀረቡት፣ በቅርቡ ወደ ኬንያ አቅንተው የነበሩት የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልዑክ ሴናተር ክሪስ ኩንስ እና የኬንያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪዎች አማካኝነት ነው። ኦዲንጋ፣ አሸናፊው ሁሉንም ጠቅልሎ የሚወስድበትን የምርጫ ሥርዓት የሚቀይር ሕገመንግሥታዊ ማሻሻያ እንዲደረግ ሃሳብም አቅርበዋል።
Show all...
#NewsAlert የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ቢሮ በአማራ ክልል ለሕይወት አስጊ በኾነ ሕመም ላይ የሚገኙ ታማሚዎችን ከቦታ ቦታ በሚያጓጉዙ አምቡላንሶች እና የጤና ባለሙያዎች ላይ በቅርብ ጊዜያት የተፈጸሙ ጥቃቶች አሳስበውኛል ሲል ዛሬ ከቀትር በኋላ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የጤና ሠራተኞች፣ አምቡላንሶችና ሆስፒታሎች ዒላማ መኾን እንደሌለባቸው የገለጠው ማኅበሩ፣ የጤና ሠራተኞች፣ አምቡላንሶችና ሆስፒታሎች በማናቸውም ጊዜ ሊከበሩ እና ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገባቸው ናቸው ብሏል።
Show all...
ሐሙስ መጋቢት 28/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ አብን ገዥው ፓርቲ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን "በግዴታ ትጥቅ ለማስፈታት" እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነው ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከሷል። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው፣ ገዥው ፓርቲ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች "በክልሉ ልዩ ኃይል እና በፌደራል የጸጥታ ተቋማት መካከል ከፍተኛ ውጥረት መፍጠሩን" ተረድቻለሁ ብሏል። መንግሥት የጋራ መግባባትና መተማመን ሳይፈጠር የክልሉን ልዩ ኃይል "በድንገትና ያለበቂ የጸጥታ ዋስትና ለማፍረስ" ያሳለፈው ውሳኔና ውሳኔውን ለመተግበር የሚያደርገው እንቅስቃሴ "ኃላፊነት የጎደለው" እና በክልሉና በአገር ዓቀፍ ደረጃ "ከፍተኛ አለመረጋጋት የሚፈጥር፣ ክልሉንና አገሪቱን ወደሌላ የቀውስ አዙሪት የሚከት አደገኛ አካሄድ" መኾኑን ፓርቲው ገልጧል። ገዥው ፓርቲ ውሳኔውን "በአፋጣኝ እንዲቀለብስና ከክልሉ መንግሥትና ሕዝብ ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት እንዲያደርግ" አብን አሳስቧል። 2፤ በአማራ ክልል ከባሕርዳር ወደ ጎንደር በሚወስደው ዋና መንገድ ተሽከርካሪዎች ለሁለት ሰዓታት ያህል መንገድ ተዘግቶባቸው እንደነበር ዶይቸቨለ አሽከርካሪዎች ገለፁ። ሰሜን ወሎ ዞን ጎብዬ በተባለች ከተማ ዛሬ የጥይት ተኩስ ሲሰማ መዋሉን ተገለፀ። ኾኖም ከሁለት ሰዓታት በኋላ፣ አሽከርካሪዎች መታወቂያ እያሳዩና እየተፈተሹ በሁለቱም አቅጣጫ ማለፍ እንደቻሉ መናገራቸውን ሰመተናል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ የክልሉ መንግሥት መንገዱ ተዘግቶ ነበር ስለተባለው መረጃ ያለው ነገር የለም። 3፤ የትምህርት ሚንስትር ደኤታ ሳሙኤል ክፍሌ የመሩት ልዑካን ቡድን ዛሬ መቀሌ መግባቱን የትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ዘግቧል። ልዑኩ፣ መቀሌ የገባው፣ በክልሉ የሚገኙ ለሁለት ዓመታት ትምህርት መስጠት ያቋረጡ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሌሎች ትምህርት ቤቶች ባሉበት ሁኔታ ዙሪያ፣ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲኹም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት መጀመሩን ዘገባው ጠቅሷል። በልዑካን ቡድኑ ከተካተቱ አባላት መካከል፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጣሰው ወልደሃና እና የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኝ ይገኙበታል ተብሏል። 4፤ የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አደም ፋራህ የመሩት ልዑካን ቡድን በጅቡቲ ይፋዊ ጉብኝት እያደረገ መኾኑን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። አደም ከጅቡቲው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሞሐሙድ ዓሊ የሱፍ እና ከፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ እንደተወያዩና ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የላኩትን ደብዳቤ ለፕሬዝዳንት ጌሌ እንደሰጡ ኢምባሲው ገልጧል። 5፤ የሱዳን ወታደራዊ አመራሮችና የፖለቲካ ኃይሎች ዛሬ የሲቪል ሽግግር መንግሥት ማቋቋሚያውን ረቂቅ ሰነድ ለመፈረም ይዘው የነበረውን ቀጠሮ ለሁለተኛ ጊዜ አራዝመዋል። ከመጋቢት 23 ወደ መጋቢት 28 የተራዘመው የስምምነት ሰነዱን የመፈረሙ ቀጠሮ ዛሬ በድጋሚ የተራዘመው፣ የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ምክትል ሊቀመንበር ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ የሚመሩት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ወደፊት ከአገሪቱ ብሄራዊ ጦር ሠራዊት ጋር በሚዋሃድበት የጊዜ ገደብ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ስላልተቻለ እንደኾነ የሱዳን ዜና ምንጮች ዘግበዋል። 6፤ ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ቡድን (ሲፒጄ) ባለፈው ወር በኬንያ በተካሄዱ ጸረ-መንግሥት የተቃውሞ ሰልፎች ወቅት በጋዜጠኞች ላይ ለደረሱ ጥቃቶች ተጠያቂነት እንዲሰፍን ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። የአገሪቱ ባለሥልጣናት በተቃውሞ ሰልፉ ይዘግቡ በነበሩ ጋዜጠኞች ላይ ፖሊሶች ያደረሷቸውን ወከባዎችና አካላዊ ጥቃቶች በጥልቀትና ተዓማኒ በኾነ መንገድ መርምረው ጥፋተኞቹን ለሕግ እንዲያቀርቡ ጥሪ አድርጓል። የመብት ተሟጋቹ ቡድን፣ የተቃውሞ ሰልፎቹን ለመዘገብ የወጡ ሁለት ጋዜጠኞችም ለአጭር ጊዜ ታስረው እንደነበር መረዳቱን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል። 7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ9566 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ0357 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ2303 ሳንቲም እና መሸጫው 65 ብር ከ5148 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ0393 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ2201 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል።
Show all...
ሐሙስ መጋቢት 28/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የኢትዮጵያ ስጋ ላኪዎች ከዛሬ ጀምሮ ስጋ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚያቆሙ ማስታወቃቸውን ሰመቸናል። የኢትዮጵያ ስጋ አምራችና ላኪዎች ማኅበር መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ስወራ ችግርን ሊፈታ አለመቻሉን ጠቅሶ፣ ላኪዎች ስጋ መላክ እንደሚያቆሙ ለግብርና ሚንስቴር ደብዳቤ መጻፉ ታውቋል። ማኅበሩ በደብዳቤው የዘርፉ ችግር አድርጎ የጠቀሰው፣ የኤክስፖርት ቄራዎችን ተከራይተው ምርት ወደ ውጭ የሚልኩ ኩባንያዎች የውጭ ምንዛሬ በመሰወር ሥራ ላይ በመሠማራት ሕግ አክብረው የሚሠሩ ስጋ ላኪ ኩባንያዎችን ከገበያ እያስወጡ ነው የሚል ነው። ቁጥራቸው ከ30 እስከ 40 የሚገመቱ የኤክስፖርት ቄራዎችን ተከራይተው ስጋ የሚልኩ ኩባንያዎች ዋነኛ ዓላማቸው፣ በላኪነት ሽፋን ከብሄራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደኾነ ይነገራል። 2፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተካሄደባቸው ክልሎች በመንግሥትና ሕወሃት መካከል የሰላም ስምምነት ከተደረሰ ወዱህ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ ማድረግ እንደሚቀጥል ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ኮሚሽነ ይህንኑ ተልዕኮውን ለመቀጠል፣ ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን አሠራር ለመዘርጋት ዕቅድ መያዙን ገልጧል። 3፤ ባይቶና አባይ ትግራይ ፓርቲ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ተወካይ የለኝም ሲል ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ባይቶና ፓርቲ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ እንደተወከለ አድርገው መረጃ ያሰራጩት ሕውሃት በፓርቲው ውስጥ ያደራጃቸው ግለሰቦች ናቸው በማለት ፓርቲው ገልጧል። ባይቶና ትናንት ሥራውን በይፋ በጀመረውና 27 አባላት ባሉት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ውስጥ፣ ሁለት ቢሮዎችን የመምራት ሃላፊነት እንደተሰጠው የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቦ ነበር። 4፤ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ሲያደርግ የሰነበተው የኤርትራ ወታደራዊና የደኅንነት ልዐካን ቡድን ትናንት ጉብኝቱን ማጠናቀቁን በኢትዮጵያ የኤርትራ ኢምባሲ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በጉብኝቱ ማጠናቀቂያ ለልዑኩ በተደረገ ግብዣ ላይ፣ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከጀርባው በተወጋበት ወቅት የኤርትራ ሕዝብና ሠራዊት ያደረገለትን ድጋፍ መቼም አይረሳም ማለታቸውን ኢምባሲው ጠቅሷል። የኤርትራ ደኅንነት ሚንስትር ጀኔራል አብርሃ ካሳ በበኩላቸው፣ ሕወሃት በኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሲሰነዝር፣ ኤርትራ አደጋውን ከመመከትና ያንኑ ተከትሎ የተፈጸሙ ወታደራዊ ጥቃቶችን ከማክሸፍ ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበራትም በማለት መናገራቸውን ኢምባሲው ገልጧል። 5፤ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለደቡብ ሱዳን ያቋቋመውን የሰብዓዊ መብቶች ተቆጣጣሪ ኮሚሽን የጊዜ ቆይታን ላንድ ዓመት አራዝሟል። ምክር ቤት የኮሚሽኑን የጊዜ ቆይታ ያራዘመው፣ ኮሚሽኑ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈጽሙ ሲቪልና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ተጠያቂ መኾን አለባቸው በማለት ሰኞ'ለት ሪፖርት ማውጣቱን ተከትሎ ነው። ምክር ቤቱ ኮሚሽኑን ያቋቋመው ከሰባት ዓመታት በፊት ሲሆን፣ የጊዜ ቆይታውን ያደሰው ደሞ በዓመታዊ ጉባዔ ማጠናቀቂያ ላይ ነው። የደቡብ ሱዳን መንግሥት የኮሚሽኑ ቆይታ እንዳይታደስ ጥረት አድርጎ ነበር።
Show all...
በአዲስ አበባ 200 ሺህ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱት በህገ-ወጥ ቦሎ ነው ተባለ፡፡ የተሽከርካሪ እና አሽከርካሪ ቁጥጥር ባለስልጣን እንዳስታወቀው በህጋዊ መንገድ ከምርመራ ተቋማት ቦሎ የሚወስዱ ተሽከርካሪዎች 48 ከመቶ ብቻ ናቸው ብሏል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራቶች በህጋዊ መንገድ ከምርመራ ተቋማት ፍቃድ አግኝተው ቦሎ የወሰዱ ተሽከርካሪዎች 330ሺህ ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡ የአሽከርካሪ እና ተሸከርካሪ ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ደምሴ እንደተናገሩት፣ አሁን ላይ በአዲስ አበባ ደረጃ 650ሺህ ተሸከርካሪዎች እንደተመዘገቡ ገልጸው በየአመቱ ቦሎ የሚወስዱ ተሽከርካሪዎች ግን 450ሺህ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡ የተቀሩት ተሽከርካሪዎች አመታዊ ተሽከርካሪ ምርመራ የት እየሄዱ እንደሚያደርጉና ቦሎም ከየት እንደሚወስዱ አይታወቅም ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ደረጃ እውቅና ተሰጥቷቸው ተሽከርካሪ ምርመራ የሚያደርጉ ከ50 በላይ የምርመራ ተቋት እንዳሉ የተነገረ ሲሆን፣አብዛኛዎቹ የአቅም ክፍተት እንዳለባቸው ተጠቅሟል፡፡ የአሽከርካሪ እና ተሸከርካሪ ቁጥጥር ባለስልጣን እነዚህ ችግሮም ለመቅረፍ ከምርመራ ተቋማቱ ጋር በመቀናጀት አዲስ አሰራር መዘርጋቱንም ነው የገለጸው፡፡ በዚህም ተሽከርካሪዎች አመታዊ የቴክኒክ ምርመራ በቴክኖሎጂ በታገዘ የምረመራ አገልግሎት የሚሰጣቸው ይሆናልም ተብሏል፡፡
Show all...
ማክሰኞ መጋቢት 26/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የጸጥታና ደኅንነት ግብረ ኃይል " በመንግሥት ባለስልጣናትና በከተሞች ላይ በጦር መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ደርሼባቸዋለሁ" ያላቸውን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አውያለሁ አለ። ምሁራን፣ የመገናኛ ብዙኀን ባለቤቶችና የማኅበረሰብ አንቂዎች የታቀፉባቸው ናቸው የተባሉት ኅቡዕ ቡድኖች፣ ጥቃቱን ሊፈጽሙ ያቀዱት በአዲስ አበባ፣ ባሕርዳር፣ አዳማ እና ድሬዳዋ እንደነበር ግብረ ኃይሉ ገልጧል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል፣ ዶ/ር ወንደወሰን አሠፋ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው፣ ፕሮፌሰር ማዕረጉ ቢያበይን እና ዶ/ር መሠረት ወርቁ የተባሉ ተጠርጣሪዎች እንደሚገኙበትና በአንዳንዶቸ ተጠርጣሪዎች እጅ ጦር መሳሪያዎች እንደተያዙ አመልክቷል። ተጠርጣሪዎቹ " የአማራ ሕዝብ በከፍተኛ ጭቆና ውስጥ ይገኛል" በማለት፣ "ሕዝብን በሐይማኖት፣ በብሄርና በጽንፈኛ የፖለቲካ ዓላማ ዙሪያ ደጋፊ ለማሰባሰብ ሲሞክሩ ነበር" ተብሏል። 2፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ከኦሮሚያ ክልል የተመረጡትን አባሉን ዶ/ር ጫላ ዋታን ያለመከሰስ መብት በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ አንስቷል። ጫላ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው፣ የሁሌ ቦራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት ከመንግሥት የግዥ ሥርዓት ውጭ ፈጽመውታል ተብለው በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል መኾኑን ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳቡን ያቀረበው የሕግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ አስረድቷል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ የወንጀል ተጠርጣሪው ጫላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ስለመዋላቸው አልታወቀም። 3፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሌሊሴ ደሳለኝን የከፍተኛው ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ዘሃራ ኡመርን የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ኾነው እንዲሾሙ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ በሁለት ድምጸ ተዓቅቦ አጽድቋል። ሌሊሴ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉና ፌደራል ፍርድ ቤቶች በዳኝነት እንዲሁም ባንድ ወቅት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በምክትል ፕሬዝዳንትነት ማገልገላቸው የተገለጠ ሲሆን፣ ዘሃራ ደሞ በሱማሌ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተለያዩ ኃላፊነቶች ማገልገላቸው ተጠቅሷል። ሌሊሴና ዘሃራ የተሾሙት፣ የፍርድ ቤቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ብርሃን መስቀል ዋጋሪና ምክትል ፕሬዝዳንት ተናኘ ጥላሁን በፍቃዳቸው ከሃላፊነት በመልቀቃቸው እንደኾነ ተዘግቧል። 4፤ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት "በሂደትና ደረጃ በደረጃ" ከሰሜኑ ጦርነት በፊት ወደነበረበት እንደሚመልስ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። ቦሬል፣ አውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት ዛሬ መግለጫ የሰጡት፣ ብራስልስ ውስጥ ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው። የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በመንግሥትና ሕወሃት መካከል በተፈረመ ሰላም ስምምነት መቋጨቱ አዎንታዊ ክስተት መኾኑን የጠቀሱት ቦሬል፣ የሰላም ስምምነቱ ዘላቂ እንዲኾን ኅብረቱ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በትብብር መስራት እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ቦሬል፣ አውሮፓ ኅብረት የሰላም ስምምነቱን አፈጻጸም በቅርበት በመከታተል ላይ እንደኾነ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና የትግራይ ክልል አመራሮች እንዲረዱትም አሳስበዋል። 5፤ ኢትዮ ቴሌኮም የኢንተርኔት ግንኙነት ያለ "ቪፒኤን" ለማድረግ እንደተቸገረ ተደርጎ የተሠራጨው መረጃ "የተሳሳተ ነው" ሲል ዛሬ ባስተላለፈው መልዕክት አስታውቋል። ኢትዮ ቴሌኮም ያለ "ቪፒኤን" የኢንተርኔት ግንኙነት ለማድረግ "ተጨማሪ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንዳስፈለገው" ተደርጎ የተሠራጨው መረጃም ሐሰት መኾኑን ጨምሮ ገልጧል። ኢትዮጵያ ውስጥ ምክንያቱ ባልተገለጠ ሁኔታ የፌስቡክ፣ ቴሌግራምና ዩትዩብ ማኅበራዊ መገናኛ አገልግሎቶች ከተገደቡ ሁለት ወር የተቆጠረ ሲሆን፣ ደንበኞች የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹን የሚጠቀሙት "በቪፒኤን" በመግባት ብቻ ነው። የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹ ለምን እንደተገደቡ፣ ኩባንያው ያለው ነገር የለም። 6፤ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ከጅቡቲ የቀይ ባሕር ዳርቻ 142 ፍልሰተኞችን መታደግ እንደተቻለ ዛሬ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ፍልሰተኞችን መታደግ የተቻለው፣ ፍልሰተኞቹ በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት በጀልባዎች ቀይ ባሕርን አቋርጠው ወደ የመን ለመሻገር ሲሞክሩ መኾኑን ኢምባሲው ገልጧል። ኢምባሲው፣ ፍልሰተኞቹን ሊያሻግሩ የነበሩ ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችም በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የገለጠ ሲሆን፣ በቁጥጥር ስር የዋሉትን ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ብዛትና ዜግነታቸውን ግን አልጠቀሰም። 7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ9302 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ0088 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 63 ብር ከ6169 ሳንቲም እና መሸጫው 64 ብር ከ8892 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ5844 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ7561 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል።
Show all...
ጠዋት ሰኞ መጋቢት 25/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ ከአማራና ደቡብ ክልሎች የተወከሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አንዳንድ የሁለቱ ክልሎች መንግሥታዊ ተቋማት ሠራተኞች ደመወዝ መክፈል እንደተሳናቸው መናገራቸውን ሰምተናል። በደቡብ ክልል አንዳንድ መንግሥታዊ ተቋማት ከሦስት እስከ አራት ወራት ድረስ የሠራተኛ ደመወዝ እንዳልከፈሉ በምክር ቤቱ የክልሉ ተወካዮች ገልጠዋል። በአማራ ክልልም፣ በርካታ ወረዳዎች በበጀት እጥረት በወረዳ መዋቅርነት መቀጠል በማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ከክልሉ የተወከሉ የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል ተብሏል። የምክር ቤቱ አባላት ይህን የተናገሩት፣ ከፌደራል ሥራ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ጠቅሷል። 2፤ ጤና ሚንስቴር በኦሮሚያ እና ሱማሌ ክልሎች በ18 ወረዳዎች የኮሌራ ወረርሽኝን እስካሁን ማጥፋት እንዳልተቻለ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በሁለቱ ክልሎች በአምስት ወረዳዎች የተከሰተው ወረርሽኝ ግን፣ በቁጥጥር ስር መዋሉን ሚንስቴሩ ገልጧል። ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የኮሌራ ክትባት መሰጠቱን የገለጠው ሚንስቴሩ፣ ወረርሽኙን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠርና ወደ አጎራባች አካባቢዎች እንዳይሰራጭ ለመከላከል ከዓለም ጤና ድርጅት 1.2 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት ጠይቄያለሁ ብሏል። ከድርቅ ጋር በተያያዘ፣ በአንዳንድ ክልሎች የኩፍኝ ወረርሽኝ እና የወባ በሽታዎች መከሰታቸውን ሚንስቴሩ ገልጧል። 3፤ አንጋፋው የኬንያ ተቃዋሚ መሪ ራይላ ኦዱንጋ በዚህ ሳምንት የጠሯቸውን ሁለት አገር ዓቀፍ ጸረ-መንግሥት የተቃውሞ ሰልፎች መሰረዛቸውን አስታውቀዋል። ኦዲንጋ የተቃውሞ ሰልፎቹን የሰረዙት፣ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸው፣ የተቃውሞ ሰልፎቹ እንዲቆሙ ትናንት ምሽት ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው። ፕሬዝዳንቱ ጥሪውን ያቀረቡት፣ በፓርላማው ውስጥ የመንግሥትና ተቃዋሚው ፓርቲ በልዩነቶቻቸው ዙሪያ ንግግር እንዲጀምሩ ነው። ኾኖም ኦዲንጋ በጥያቄዎቻቸው ዙሪያ አዎንታዊ ውጤት ካላዩ፣ በቀጣዩ ሳምንት የተቃውሞ ሰልፎችን እንቀጥላለን በማለት አስጠንቅቀዋል። 4፤ ደቡብ ሱዳን በምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ቀጠና ጥላ ስር ወታደሮቿን ወደ ምሥራቃዊ ኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ልካለች። በቀጠናዊው ድርጅት ውሳኔ መሠረት፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ቡሩንዲ ቀደም ሲል ወታደሮቻቸውን የጦርነት ቀጠና በኾነው ምሥራቃዊ ኮንጎ አሠማርተዋል። የቀጠናው ወታደሮች በአገሪቱ ምሥራቃዊ አውራጃዎች የተሠማሩት፣ የኮንጎ መንግሥትን በመውጋት ላይ ያለውን የኤም-23 አማጺ ቡድን ግስጋሴ ለመግታት፣ ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ለማድረግና በርካታ አማጺዎችን ትጥቅ ለማስፈታት ነው። 5፤ የሱማሌላንድ መንግሥት አሜሪካና አፍሪካ ኅብረት የግጭት ቀጠና በኾነችው ላስ አኖድ ሰላም እንዲሰፍን ብርቱ ጥረት እንዲያደርጉና የሱማሌላንድን ሉዓላዊነት ለሚያከብር ዘላቂ መፍትሄ ድጋፍ እንዲሰጡ ትናንት ባወጣው መግለጫ ተማጽኗል። ሱማሌላንድ በዚሁ መግለጫዋ፣ ጎረቤት አገራት ያደረጓቸውን ጨምሮ ሁሉም የሰላም ጥረቶች በተዋጊ ሚሊሻዎች እምቢተኝነት ሳቢያ ከሽፈዋል ብላለች። የአልሸባብ ታጣቂዎች፣ የሱማሊያ ጦር ሠራዊትና የፑንትላንድ ራስ ገዝ ታጣቂዎች እየወጓት መኾኑን የጠቀሰችው ሱማሌላንድ፣ ፑንትላንድ ታጣቂዎችን ማስገባቷን እንድታቆም አሜሪካ ግፊት እንድታደርግ መጠየቋን ገልጣለች።
Show all...
ምሽት ቅዳሜ መጋቢት 23/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የገንዘብ ሚንስትር ደዔታ እዮብ ተካልኝ ፌደራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የመደበውን የበጀት ድጎማ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ በየወሩ መልቀቅ እንደሚጀምር ትናንት ከፋና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። እዮብ፣ የዘንድሮው በጀት ዓመት ከተጀመረ ጀምሮ ባለፉት በርካታ ወራት ስላልተከፈለው እንዲሁም ፌደራል መንግሥት ላለፉት ሁለት ዓመታት አግዶ በያዘው የትግራይ ክልል የፌደራል ድጎማ በጀት ዙሪያ ግን ውይይት እንዳልተደረገ ገልጸዋል። ፌደራል መንግሥቱ የክልሉን የበጀት ድጎማ ከቀጣዩ ስምንት ጀምሮ የሚለቀው፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ የሚገባ በመኾኑ እንደኾነ በቃለ ምልልሳቸው ላይ ገልጸዋል። 2፤ አዲስ አበባ ውስጥ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ቢሮ ከፍቶ ጥናት ሲያደርግ የቆየው የኬንያው ኬሲቢ ባንክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የባለቤትነት ድርሻ ለመግዛት ውሳኔ ላይ መድረሱን ገልጧል። ባንኩ የባለቤትነት ድርሻ ሊገዛባቸው የሚችላቸውን የተወሰኑ ባንኮች መርጦ እያወዳደረ መኾኑን እና በተለይ ሁለት ንግድ ባንኮች ትኩረቱን እንደሳቡት ቀደም ሲል ለቢዝነስ ደይሊ ጋዜጣ ተናግሮ ነበር። ባንኩ የባለቤትነት ድርሻ የሚገዛበትን ንግድ ባንክ የሚመርጥበት ዋነኛ መስፈርት፣ ባንኩ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ በመመዘን እንደኾነም ገልጧል።ብሄራዊ ባንክ በቅርቡ ባወጣው ፖሊሲ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች እስከ 30 በመቶ የሚደርስ የባለቤትነት ድርሻ ለውጭ ባንኮች መሸጥ እንደሚችሉ ፈቅዷል። ኬሲቢ ባንክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የባለቤትነት ድርሻ መግዛትን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የራሱን ቅርንጫፍ መክፈትን ወይም ከኢትዮጵያ ባንኮች ጋር በትብብር መስራትን በአማራጭነት ይዞ እያጠና መቆየቱ ይታወሳል። 3፤ የኦሮሚያ ኮምንኬሽን ቢሮ ሃላፊ ኃይሉ አዱኛ ነገ በኦሮሚያ ክልል በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አመራር በተመራው ለውጥ በኦሮሚያ ክልል የተገኙ ድሎችንና ስኬቶችን ለማስቀጠል ያለመ ሰላማዊ ሰልፎች እንደሚካሄዱ መናገራቸውን ገልጧል። ሰላማዊ ሰልፎቹ ባለፉት አምስት ዓመታት በክልሉ በተገኙ ድሎችና ስኬቶች ዙሪያ ሰሞኑን ከተደረጉ ክልል-ዓቀፍ ሕዝባዊ ውይይቶች ቀጥሎ የሚካሄዱ መኾኑን የቢሮው ኃላፊ መናገራቸውን ሰምተናል። የክልሉ ሕዝብ ጽንፈኝነትንና አክራሪነትን መታገልና በልማትና ሰላም ላይ በርትቶ መስራት እንዳለበት ያሳሰቡት የቢሮው ኃላፊ፣ የክልሉ ሕዝብ በነገው ክልል-ዓቀፍ ሰልፍ እንዲሳተፍ ጥሪ አድርገዋል። 4፤ የሱዳን ወታደራዊ አመራሮች እና ሲቪል የፖለቲካ ኃይሎች ዛሬ የሲቪል ሽግግር መንግሥት መመስረቻውን የስምምነት ሰነድ ለመፈረም የያዙትን ቀጠሮ ለሌላ ጊዜ ማራዘማቸውን የሱዳን ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የሰነዱ ፊርማ ለሌላ ጊዜ የተላለፈው፣ በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት መካከል ያለው ልዩነት ሊታረቅ ባለመቻሉ እንደኾነ ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ከስምምነት ሰነዱ እስካሁን መግባባት ላይ መድረስ ያልተቻለበት ዋናው የልዩነት ነጥብ፣ የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ምክትል ሊቀመንበር ጀኔራል ሐምዳን ደጋሎ የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ከብሄራዊው ጦር ሠራዊት ጋር ለመዋሃድ በሚያስፈልገው የጊዜ ብዛት ላይ እንደኾነ ተገልጧል። የፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት አዛዦች፣ ከሲቪል መንግሥት ምስረታው በኋላ ከብሄራዊው ጦር ሠራዊት ጋር ለመዋሃድ ረዘም ያለ ጊዜ ይፈልጋሉ ተብሏል። የወታደራዊና ሲቪል የፖለቲካ ኃይሎች ስምምነቱ የሚፈረምበትን አዲስ ቀን ለመቁረጥ ዛሬ እንደገና ይሰበሰባሉ ተብሏል። 5፤ የቱርክ መንግሥታዊ ቴሌቪዥን ቲአርቲ በአፍሪካ አሕጉር ላይ ያተኮረ "ቲአርቲ አፍሪካ" የተሰኘ በዲጂታል የሚሠራጭ የቴሌቪዥን ሥርጭት ከትናንት ጀምሮ በይፋ መጀመሩን ዘግቧል። አዲሱ የጣቢያው ሥርጭት ዝግጅቶቹን የሚያስተላልፈው፣ በስዋሂሊ፣ ሃውሳ፣ እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች እንደኾነ ዘገባው ጠቅሷል። "ቲአርቲ አፍሪካ" በአፍሪካ ዙሪያ አማራጭ ትርክቶችን የሚያንጸባርቁ አፍሪካ-ተኮር ዜናዎችን፣ ዘገባዎችን፣ የምርመራ ዘገባዎችንና ዘጋቢ ፊልሞችን በመላው ዓለም ለሚገኙ አድማጮቹ እንደሚያሠራጭና ለአፍሪካዊያን አድማጮች የሚስማሙ ዓለማቀፍ ዘገባዎችን እንደሚያስተላልፍ ዘገባው አመልክቷል። ጣቢያው ከ15 አገራት በተውጣጡ ሠራተኞች ሥርጭቱን መጀመሩን የጠቀሰው ዘገባው፣ ናይጀሪያ፣ ካሚሩን፣ ጋምቢያ እና ሞሮኮን ጨምሮ በበርካታ አገራት ቢሮዎች ይኖሩታል ብሏል። የቱርኩ ቲአርቲ በአሁኑ ወቅት፣ የዓለማቀፍ፣ የዓረብኛ፣ የሩሲያኛ፣ የጀርመንኛ፣ የፈረንሳይኛ እና የባልካን ጣቢያዎች ያሉት ግዙፍ መንግሥታዊ ጣቢያ ነው።
Show all...
ቅዳሜ መጋቢት 22/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር ከሚካሄደው መኖሪያ ቤቶችን የማፍረስና በግዳጅ የማስነሳት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ጸጥታ ኃይሎች ባንዳንድ አካባቢዎች ቤታቸው ሲፈርስባቸው የተቃወሙ ሰዎችን መደብደባቸውን፣ ማሠራቸውንና ፊሊ ዶሮ በተባለ አካባቢ የሰው ሕይወት ስለማለፉ መረጃ እንዳገኘ ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ባንዳንድ ቦታዎች የቤት ማፍረሱና በግዳጅ ከይዞታ የማስለቀቁ ድርጊት የብሄር አድልዖ እንዳለበት ሰለባዎች ቅሬታ ማቅረባቸውንና አጠቃላይ ርምጃው በርካታ ዜጎች ላይ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማድረሱን ኢሰመኮ ጠቅሷል። ኢሰመኮ የድርጊቱ ሰለባዎች በሕጋዊ መንገድ መኖሪያ ቤት የሚያገኙበትና ለደረሰባቸው የንብረት ጉዳት ካሳ የሚያገኙበት መንገድ እንዲፈለግ ጠይቋል። የክትትል ሪፖርቱን ያወጣው በቡራዩ፣ ሰበታ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ እና መነ አብቹ አካባቢ በሚካሄደው የቤት ፈረሳ እንቅስቃሴ ላይ ክትትል በማድረግ መኾኑን የገለጠው ኢሰመኮ፣ የከተማው አስተዳደር ግን "ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ" የሌላቸውን ግንባታዎች ብቻ ለይቼ እያፈረስኩ ነው ማለቱን አውስቷል። 2፤ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ አንድ የከረዩ ኦሮሞ አባ ገዳን በድብደባ መግደላቸውን ከሟች ቤተሰቦች ሰምተናል። አባ ገዳ ጎቡ ሐዌሌ በድብደባ ሕይወታቸው ያለፈው ባለፈው ቅዳሜ መኾኑን የገለጡት፣ ጸጥታ ኃይሎቹ በሌሎች 18 ያህል አዛውንቶች ላይ ጭምር ድብደባ መፈጸማቸውን የዓይን ምስክሮች ገልፀዋል። የድብደባውና ግድያው ምክንያት ግልጽ አለመኾኑን የገለጡት ነዋሪዎች፣ ድርጊቱ ከተፈጸመበት ቦታ ራቅ ካለ አካባቢ ግን ከሁለት ቀን ቀደም ብሎ በመንግሥትና በኤነግ ሸኔ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እንደነበር መግለጣቸው ተመልክቷል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በድርጊቱ ዙሪያ መረጃ እንደደረሰውና ኾኖም ግን ማስረጃ አጠናቅሮ አለመጨረሱን መግለጡን ተናግሯል ተብሏል። 3፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ትናንት የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ከኾኑት የኮሞሮስ ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ ጋር መወያየታቸውን አስታውቀዋል። ዐቢይ ከፕሬዝዳንት ኡስማኒ ጋር በሁለትዮሽ፣ ክልላዊና በባለ ብዙ ወገን ጉዳዮች ዙሪያ እንደኾነ ገልጸዋል። ከአንድ ወር በፊት የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ኾነው የተመረጡት ፕሬዝዳንት ኡስማኒ አዲስ አበባ የገቡት፣ አፍሪካ ኅብረትንና የኅብረቱ ጽሕፈት ቤት አስተናጋጅ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት እንደኾነ ተገልጧል። 4፤ ዓለማቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) በሱማሉያዋ ፑንትላንድ ራስ ገዝ ቦሳሶ ወደብ አቅራቢያ 11 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች በመኪና አደጋ መሞታቸውንና ሌሎች 20 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ፍልሰተኞቹ አደጋው የደረሰባቸው፣ በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ወደ ቦሳሶ በጨለማ በተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ ሳሉ መኾኑን ድርጅቱ ገልጧል። ፍልሰተኞቹ ከቦሳሶ በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት በኤደን ባሕረ ሰላጤ በኩል ወደ የመን ሊሻገሩ አቅደው የነበሩ ናቸው ተብሏል። ቦሳሶ ለበርካታ ዓመታት በተለይ ኢትዮጵያዊያንና ሱማሊያዊያን ሕገወጥ ፍልሰተኞች ወደ የመን እና ሳዑዲ ዓረቢያ በጀልባዎች የሚሻገሩበት ወደብ ናት። 5፤ የዱባዩ ዓለማቀፍ የወደቦች ኩባንያ በሚያስተዳድረው የሱማሌላንዱ በርበራ ወደብ አዲስ የምግብ ዘይት ማጠራቀሚያ ተርሚናል ማቋቋሙን የሱማሌላንድ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የተርሚናሉ መገንባት የአፍሪካ ቀንድ አገራትን የምግብ ዘይት አቅርቦት ሰንሰለት ወጪ እንደሚቀንሰላቸው ዜና ምንጮቹ አመልክተዋል። ተርሚናሉ ለጊዜው 18 ሺህ ቶን የምግብ ዘይት የማጠራቀም አቅም እንዳለው የጠቀሱት ዘገባዎቹ፣ የምግብ ዘይት ከውጭ በጅምላ በማስመጣት የማሸግ ሥራ እንደሚከናወንና ወደፊትም ወደቡ ላይ የዘይት ማሸጊያ ፋብሪካ ይቋቋማል መባሉን ጠቅሰዋል።
Show all...
ዓርብ መጋቢት 22/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ውስጥ ከፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እየተወያየ እንደኾነ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕስ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ መናገራቸውን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው የመሩት የክልሉ ልዑካን ቡድንና የፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት እየተወያዩባቸው ከሚገኙባቸው አጀንዳዎች መካከል ዋነኛው፣ በትግራይ ክልል የመልሶ ማቋቋም እንቅስቃሴ ዙሪያ እንደኾነ ጣቢያው ገልጧል። 2፤ የብሄራዊ መልሶ ማቋቋሚያና ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በትግራይ ክልል የነፍስ ወከፍና የቡድን ጦር መሳሪያዎችን የማስፈታቱ ሂደት መዘግየቱን መናገራቸውን ሰምተናል። ኮሚሽነር ተሾመ ዛሬ ባሕርዳር ላይ በጉዳዩ ዙሪያ በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ፣ ለሂደቱ መዘግየት ምክንያቶቹ፣ አዲሱ ኮሚሽን በቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠመዱና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምስረታ መዘግየቱ መማኾናቸውን መጥቀሳቸውን አመልክቷል። ኾኖም ኮሚሽነር ተሾመ፣ ከአሁን ጀምሮ የነፍስ ወከፍና ቀላል የጦር መሳሪያዎችን ትጥቅ የማስፈታቱ ሥራ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት ተግባራዊ መኾን ይጀምራል ብለዋል። በምክክር መድረኩ ላይ የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ተገኝተዋል ተብሏል። 3፤ የመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎትን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ለስድስት ዓመታት የመሩት ሮባ መገርሳ ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን ሰምተናል። በሮባ ምትክ፣ በሪሶ አመሎ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኾነው እንደተሾሙ አመልክቷል። ተሰናባቹ ሮባ የኩባንያውን ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሃላፊነት ከመረከባቸው በፊት፣ በኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን በምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ለዓመታት ያገለገሉና በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸው ነበሩ። በተመሳሳይ፣ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የኋላሸት ጀመረ ከሃላፊነት ተነስተው፣ በምትካቸው አብዱልበር ሸምሱ እንደተሾሙ ተገልጧል። 4፤ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የኛንጋቶም ወረዳ አስተዳደር የአንድ እምነት ተከታይ ኡጋንዳዊያን ወደ ወረዳው የገቡት "የምጽዓት ቀንን በመሸሽ ነው" መባሉን እንዳስተባበለ ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል። የወረዳው አስተዳደር፣ 277 ኡጋንዳዊያን ወደ ወረዳው ባለፈው ታኅሳስ መግባታቸውን አረጋግጦ፣ ኾኖም ግን ኡጋንዳዊያኑ "በኡጋንዳ ይጀምራል ብለው ያመኑትን የምጽዓት ቀን ሽሽተው የተሰደዱ ናቸው" ተብሎ የተነገረው "የተሳሳተ መረጃ ነው" ማለቱን ዘገባው ጠቅሷል። ኡጋንዳዊኑ ለኛንጋቶም ብሄረሰብ "የቤተክርስቲያን መልዕክት ለማድረስና አካባቢውን ለመጎብኘት" የገቡ የሐይማኖት ተጓዦች እንደኾኑ የጠቀሱት የወረዳው ባለሥልጣናት፣ ኛንጋቶም ብሄረሰብ ከኡጋንዳ የፈለሰ ነው የሚል አፈ ታሪክ መኖሩንም ተናግረዋል ተብሏል። ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ኡጋንዳዊያኑ "የምጽዓት ቀንን የሸሹ" መኾናቸውን ማረጋገጡን ትናንት ተናግሮ ነበር። 5፤ አሜሪካ የሱማሌላንድ ራስ ገዝ መንግሥት ወታደሮቹን የግጭት ቀጠና ከሆነችው ላስ አኖድ ከተማ እንዲያስወጣ ጠይቃለች። መንግሥትን የሚፋለሙ የላስ አኖድ የጎሳ ሚሊሻዎችም፣ በመንግሥት ኃይሎች ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ አሜሪካ አሳስባለች። ሁለቱ ወገኖች ግጭቱን አብርደው ቀደም ሲል የተደረሰውን ተኩስ አቁም እንዲያከብሩ የጠየቀችው አሜሪካ፣ ሰብዓዊ ቀውሱ እንዳይባባስ ተፋላሚ ወገኖች በንግግር ግጭቱን መፍታት አለባቸው ብላለች። ባለፈው ኅዳር መካሄድ የነበረበት የሱማሌላንድ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መዘግየቱ እንዳሳሰባትም አሜሪካ የገለጠች ሲሆን፣ የፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ መንግሥት ምርጫው የሚካሄድበትን የጊዜ መርሃ ግብር እንዲያሳውቅ ጥሪ አድርጋለች። 6፤ የዓለማቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት መመስረቻ ስምምነት ፈራሚዋ ደቡብ አፍሪካ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቱን ለ"ብሪክስ" አገራት የመሪዎች ጉባኤ ሲሄዱ እንደምታስተናግዳቸው ዛሬ በውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ናለዲ ፓንዶር በኩል አስታውቃለች። የዓለማቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬን "የጦር ወንጀል ፈጽመዋል" በማለት የእስር ማዘዣ ማውጣቱን ተከትሎ፣ በቀጣዩ ነሐሴ የ"ብሪክስ" አገራት የመሪዎች ጉባኤ አዘጋጇ ደቡብ አፍሪካ አቋሟ ምን እንደሚኾን በጉጉት ሲጠበቅ ነበር። ደቡብ አፍሪካና ሩሲያ በሌሎች አገራት ግፊት በድንገት ጠላት ሊኾኑ አይችሉም ያሉት ፓንዶር፣ ፑቲንን በጉባኤው እንዲገኙ እንደተጋበዙ ተናግረዋል። በዓለማቀፉ ፍርድ ቤት ስምምነት መሠረት፣ ደቡብ አፍሪካ ፑቲን ግዛቷን ከተረገጡ አስራ ለፍርድ ቤቱ የማስረከብ ግዴታ አለባት። "ብሪክስ" በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉት ኃያላኑ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ሕንድና ብራዚል የመሠረቱተ ቡድን ነው። 7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ9017 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9808 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 63 ብር ከ5330 ሳንቲም እና መሸጫው 64 ብር ከ8037 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ5545 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ7256 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። አንድ የቻይና ዩዋን ደሞ በ7 ብር ከ0868 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ7 ብር ከ2285 ሳንቲም ተሽጧል ተብሏል።
Show all...
ምሽት ሐሙስ መጋቢት 21/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ ፍትህ ሚንስቴር በሕወሃት ከፍተኛ የሲቪልና የወታደራዊ መኮንኖች ላይ የመሠረተውን የወንጀል ክስ ማቋረጡን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ሚንስቴሩ፣ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ዙሪያ ያለው ተጠያቂነት "ዓለማቀፍ ተሞክሮን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ ሊታይ እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል" ብሏል። ሚንስቴሩ፣ በሕወሃት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የሕወሃት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካዔልንና የአሁኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በሲቪል የፖለቲካ አመራሮች ላይ የመሠረታቸውን ክሶች ያቋረጠው፣ ፌደራል መንግሥቱና ሕወሃት ፕሪቶሪያ ላይ በደረሱበት ሰላም ስምምነት መሠረት እንደኾነ ጠቅሷል። ሚንስቴሩ ክሶቹን ያቋረጠው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕወሃትን ከአሸባሪነት መዝገብ በሰረዘ ማግስት ነው። 2፤ የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን 250 ሺህ የሚደርሱ ተዋጊዎችን ትጥቅ አስፈትቶ መልሶ ለማቋቋም 29 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወይም 555 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የውጭ ዲፕሎማቶች ባቀረበው የገንዘብ ልገሳ ጥያቄ መግለጡን ሰምተናል። ኮሚሽኑ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ተዋጊዎችንና ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት፣ ለመበተንና ወደ ኅብረተሰቡ ለመቀላቀል ባዘጋጀው ዝርዝር ሰነድ ዙሪያ፣ ከዲፕሎማቶች ጋር ሰሞኑን መወያየቱን ሰምተናል። መንግሥት ከ20 እስከ 25 በመቶ የሚሆነውን ወጪ እንደሚሸፍንና፣ ላንድ የቀድሞ ተዋጊ መቋቋሚያ ከ36 ሺህ እስከ 60 ሺህ ብር እንደሚሰጥ በሰነዱ ተገልጧል። በመልሶ ማቋቋሙ፣ የትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላና ደቡብ ክልሎች ታጣቂዎችን ለማካተት የታቀደ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዙር ግን የትግራይ፣ አማራና አፋር ተዋጊዎች ብቻ ይካተታሉ ተብሏል። 3፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ የብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅን ባንድ ድምጸ ተዓቅቦ አጽድቋል። አዋጁን ለምክር ቤቱ ያቀረበው የሕግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ፣ ዲጂታል መታወቂያ ሁሉን ዓቀፍ፣ ወጥ እና አስተማማኝ በሆነ ሥርዓት የዜጎችን መረጃ ለመያዝ የሚረዳና በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ግልጽነትንና ተጠያቂነት ያለበትን አሠራር ለመዘርጋት የሚያስችል መኾኑን ገልጧል። መንግሥት በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ስር የተቋቋመው የዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለወራት የሙከራ ሥራዎችን ሲተገብር መቆየቱ ይታወቃል። 4፤ ኢዜማ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ባለፈው ዓመት መጋቢት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ያስሾሟቸው የመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ቦርድ አባላት ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። ኢዜማ፣ የገዥው ፓርቲ አባላት የሆኑ የቦርድ አመራሮች የተሾሙት ከመገናኛ ብዙኀን አዋጅ በተቃራኒ ነው በማለት ተችቷል። ዐቢይ፣ መንግሥታቸው ነጻ መገናኛ ብዙኀንና ነጻ ሃሳብ እንዲኖር ጥረት እያደረገ መኾኑን ሰሞኑን ለምክር ቤቱ መናገራቸውን የጠቀሰው ኢዜማ፣ የሃሳብ የበላይነት ሊሰፍን የሚችለው ግን መንግሥት መገናኛ ብዙኀንን ነጻና ገለልተኛ ማድረግ ሲችል ብቻ ነው ብሏል። ኢዜማ፣ ገዥው ፓርቲ መገናኛ ብዙኀንን በተጽዕኖው ስር በማስገባቱ፣ ሃሳቦቼ የመደመጥ ዕድል ተነፍጓዋል በማለትም አማሯል። 5፤ ኢሰመኮ በፖለቲካ ፓርቲዎች "የመሰብሰብ መብት ላይ የሚጥሏቸው ገደቦች" እና በአባሎቻቸው ላይ የሚደርሱ እንግልቶች" ለዘለቄታው መቆም አለባቸው ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል። ኢሰመኮ፣ በእናት ፓርቲ እና በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የመሰብሰብ መብታቸው እንደተገደበ አረጋግጫለሁ ብሏል። የጎጎት የጉራጌ አንድነትና ፍትህ ፓርቲ ምስረታ አስተባባሪዎችም "እንግልትና እስራት" እንደደረሰባቸው ኢሰመኮ ገልጧል። በፓርቲዎች ላይ የሚፈጸሙባቸው ክልከላዎችና እገዳዎች፣ "የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና የመሳተፍ መብቶች ጥሰቶች" እንደኾኑ ኢሰመኮ ጠቅሷል። መንግሥት በፓርቲዎች ላይ "ድንገተኛና ከታሰበላቸው ዓላማ በላይ የኾኑ ርምጃዎችን ከመውሰድ እንዲቆጠብ" እና ይልቁንም ለስብሰባ ተሳታፊዎች ጥበቃና ከለላ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት ኢሰመኮ ገልጧል። 6፤ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ደሳለኝ ቦኮንጆ ማንነታቸው ባያልታወቁ ታጣቂዎች ዛሬ መገደላቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል። የከተማ አስተዳደሩ፣ የፓርቲው ሃላፊ ለሥራ ከቤታቸው ሲወጡ በተተኮሰባቸው ጥይት እንደተገደሉ ገልጧል። የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤትም፣ ግድያውን የፈጸመው "የታጠቀ ኃይል" ነው በማለት አስታውቋል። በነቀምቴ ከተማ በመንግሥትና የፓርቲ ሃላፊዎች ላይ ግድያ ሲፈጸም የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። 7፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ከኡጋንዳ የተነሱ ኡጋንዳዊያን የአንድ እምነት ተከታዮች የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው ደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ንያንጋቶም ወረዳ ውስጥ መስፈራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ማረጋገጣቸውን መግለጫውን የተከታተሉ የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ የአንድ እምነት ተከታዮች "የመጨረሻው ምጽዓት" ኡጋንዳ ውስጥ ሊጀምር ተቃርቧል በሚል እምነት ወደ ኢትዮጵያ እንደተሰደዱ ከሳምንታት በፊት የኡጋንዳ ዜና ምንጮች ዘግበው ነበር። መለስ፣ ኡጋንዳዊያኑ ስደተኞች የገቡበትን መንገድ ወይም ብዛታቸውን ይግለጡ አይግለጡ ግን ዜና ምንጮቹ አልጠቀሱም። 8፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8978 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9758 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 63 ብር ከ5273 ሳንቲም እና መሸጫው 64 ብር ከ7978 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ5007 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ6707 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል።
Show all...
ሀሙስ መጋቢት 20/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበልኝ የሰላም ንግግር ጥሪ የለም በማለት አስተባብሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ጥረት አደረኩ የሚለው፣ የቡድኑን አመራሮችና አባላት የትጥቅ ትግላቸውን ትተው ለመንግሥት እጃቸውን እንዲሰጡ በአካባቢ ሽማግሌዎች አማካኝነት ያደረገውን ያልተሳካ ሙከራ ነው በማለት ቡድኑ ገልጧል። ቡድኑ፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ትናንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ላይ፣ ግጭቱን ለመፍታት 10 ያህል ሙከራዎች ተደርገዋል በማለት የተናገሩት ንግግር ተጨባጭ ሁኔታውን በትክክል አይገልጽም ብሏል። ሆኖም ቡድኑ አሁንም በገለልተኛ ሦስተኛ አካል ለሚደረግ ድርድር ዝግጁ መሆኗን በድጋሚ ገልጧል። 2፤ የኦነግ ሠራዊት ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ 100 ያህል ሰዎችን አግተው እንደሚገኙ ተገለፀ። በአካባቢው የፌደራል ፖሊስ አባላት ሠፍረው እንደሚገኙ ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን ሆኖም ፖሊሶች ታጋቾቹን ለማስለቀቅ የወሰዱት ርምጃ የለም ብለዋል። የወረዳው አስተዳዳሪ ሺበሺ አያሌው በበኩላቸው፣ ታጣቂዎቹ በተደጋጋሚ እገታ እንደሚፈጽሙ አምነው፣ ሆኖም የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች በቡድኑ ታጣቂዎች ላይ ርምጃ እየወሰዱ መሆኑን አመልክቷል። አጋቾቹ ላንድ ታጋች እስከ 200 ሺህ ብር ድረስ ይጠይቃሉ ተብሏል። 3. የዋጋ ንረት የኢትዮጵያን የውጭ ንግድ እየተፈታተነው መሆኑን ካገኘናቸው መረጃዎች መረዳት ችለናል። በተለይ የስጋ የወጪ ንግድ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ በተያዘው ዓመት በከፍተኛ ደረጃ ያሽቆለቆለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ወደ ዱባይ የምትልከው የስጋ ምርት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኬንያዊያን ስጋ ላኪዎች እንደተበለጠ ምንጮች ተናግረዋል። ስጋ ላኪዎች በተለይ የፍየል ስጋ ከአገር ውስጥ ገበያ የሚገዙበት ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መወደዱ፣ ኪሳራ ላይ እንደጣላቸው ጨምረው ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት በሰባት ወራት ውስጥ ለውጭ ገበያ የቀረበው 13 ሺህ 800 ቶን ስጋ ሲሆን፣ ዘንድሮ በተመሳሳይ ወራት የቀረበው ግን 9 ሺህ 600 ቶን ስጋ ብቻ እንደሆነ ተገልጧል። 4፤ የኡጋንዳው ፋይንቴክ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ከኢትዮጵያው አዋሽ ባንክ ጋር የሥራ ትብብር መፍጠሩን የኡጋንዳው ዘ ሞኒተር ጋዜጣ ዘግቧል። ኩባንያው ከባንኩ ጋር የፈጠረው የሥራ ትብብር ስምምነት፣ ባንኩ በንግድ፣ በዕርዳታ ሥርጭት እና በኢንሹራንስ ዘርፎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲተገበ እንደሚያስችለው የኩባንያው ሃላፊዎች መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ፋይንቴክ ኩባንያ በኡጋንዳ በሞባይል የገንዘብ ብድር መስጠት አገልግሎት፣ በባንክ እና ኢንሹራንስ ዘርፎች ሰፊ ልምድ ያለው ነው። 5፤ በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፍሎሪዳ ግዛት ተወካይ ማት ገዓዝ አሜሪካ ወታደሮቿን ከሱማሊያ እንድታስወጣ የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል። የገዓዝ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ፣ የአሜሪካ ወታደራዊ አመራሮች አሜሪካ ከምታሰለጥናቸው የሱማሊያ ወታደሮች መካከል ነገ የትኞቹ በመፈንቅለ መንግሥት እንደሚሳተፍ በማይገምቱበት ሁኔታ፣ የአሜሪካ ወታደሮች በሱማሊያ መገኘታቸው አሳማኝ አይደለም ይላል። ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡ፣ የፔንታጎን ባለሥልጣናት የአሜሪካ ወታደሮች ሱማሊያ ውስጥ መስፈራቸው የአሜሪካን ሕዝብ ምን ያህል እንደሚጠቅም ማብራራት አልቻሉም የሚል መከራከሪያም አቅርቧል። በምክር ቤቱ ሕግ መሠረት፣ በረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡ ላይ በ18 ቀናት ውስጥ ውይይት ይደረግበታል። "ዳናብ" የተሰኘውን የሱማሊያ ልዩ ኮማንዶ ብርጌድ የሚያሰለጥኑት የአሜሪካ ወታደሮች ናቸው። 6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8887 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9695 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 63 ብር ከ3673 ሳንቲም እና መሸጫው 64 ብር ከ6346 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ3453 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ5122 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል።
Show all...
ረቡዕ መጋቢት 20/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው የአውሮፓዊያን ዓመት በዓለም ላይ ከተከሰቱት ግጭቶች ሁሉ እጅግ አውዳሚው የትግራዩ ጦርነት እንደነበር ትናንት ባወጣው ሪፖርቱ ገልጧል። ድርጅቱ፣ በኢትዮጵያው ጦርነት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተፈጸሙት ከዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ትኩረት ውጭ በኾነ ሁኔታ እንደኾነ በሪፖርቱ ጠቅሷል። ዓለማቀፍ ድርጅቶች፣ በኢትዮጵያ፣ የመን፣ በርማ እና አፍጋኒስታን ለነበሩ ግጭቶችና ሰብዓዊ ቀውሶች በቂ ምላሽ አልሰጡም በማለትም አምነስቲ ወቅሷል። 2፤ የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ፣ የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ በትግራይ ወቅታዊ ፖለቲካዊ እና የጸጥታ ሁኔታዎች ዙሪያ ከኅብረቱ የዓለማቀፍ አጋሮች ቡድን ጋር መወያየታቸውን ትናንት ምሽት ላይ አስታውቀዋል። አምባሳደር ባንኮሌ፣ የኅብረቱ አጋሮች ቡድን ኅብረቱ-መር ለኾነው የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሃት ለደረሱበት የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት ድጋፍ ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ መጠየቃቸውን ጨምረው ገልጸዋል። 3፤ ከትናንት ወዲያ በ99 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የፒያኖና ቫዮሊን ሙዚቃ አቀናባሪ የእማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ ሥርዓተ ቀብር በመጭው ዕሁድ እየሩሳሌም ውስጥ እንደሚፈጸም ተገለፀ። እማሆይ ጽጌማርያም ለረጅም ዓመታት የተጫወቱበት የግል ፒያኗቸው፣ ለቅዱስ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት እንዲሰጥላቸው እንደተናዘዙ ተገልጿል። እማሆይ ጽጌማርያም በሕይወት ዘመናቸው ከ300 በላይ ረቂቅ ሙዚቃዎችን ማቀናበራቸው የሚነገርላቸው ሲሆን፣ ከወጣትነት ዘመናቸው ጀምሮ እስከ ሕልፈታቸው ድረስ የኖሩት በምንኩስና ሕይወት ነው። 4፤ ኢጋድ በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ድርቅ አሰቃቂ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳያስከትል ለመከላከል ዓለማቀፍ ለጋሾች እጃቸውን እንዲዘረጉ የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ ጥሪ ማድረጋቸውን ዘ ኢስት አፍሪካን አስነብቧል። በቀጠናው 47 ሚሊዮን ሕዝብ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መጋለጡን የጠቀሱት ወርቅነህ፣ 70 በመቶዎቹ ተጋላጮች በኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሱማሊያ እንደሚገኙ መናገራቸው ተገልጧል። ወርቅነህ፣ በቅርቡ ቀናት በቀጠናው አንዳንድ አካባቢዎች የዘነበው ከፍተኛ ዝናብ፣ የዝናብ ወቅቱን ትክክለኛ ገጽታ ላያሳይ እንደሚችል መናገራቸውንም ዘገባው ጠቅሷል። በኢትዮጵያ ድርቁ መጠነ ሰፊ ጉዳት እንዳያደርስ በቀጣዮቹ አራት ወራት 710 ሚሊዮን ዶላር፣ በሱማሊያ 1.6 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በኬንያ 378 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ወርቅነህ አውስተዋል ተብሏል። 5፤ በአፍሪካ ቀንድ የአውሮፓ ኅብረት ልዩ ልዑክ አኒታ ዌበር በተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ዝግ ስብሰባ ላይ ስለ ሱማሊያ ገለጻ ማድረጋቸውን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ዌበር በገለጻቸው፣ ጸጥታው ምክር ቤት በሱማሌላንድ ራስ ገዝ ላስ አኖድ ከተማ ለቀጠለው ደም አፋሳሽ ግጭት መፍትሄ እንዲፈልግ መጠየቃቸውን ዘገባዎቹ አመልክተዋል። የግጭቱ ተሳታፊ አካላት፣ ቀደም ሲል ታውጆ ለነበረው ተኩስ አቁም ተገዥ እንዲኾኑ፣ ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሄ ለማስገኘት እንዲደራደሩና ለግጭቱ ተጎጂዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲቀርብ እንዲፈቅዱ ዌበር ጠይቀዋል ተብሏል።
Show all...
ማክሰኞ መጋቢት 19/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል ወሊሶ ከተማ አካባቢ በተካሄደው "በሕገወጥ የቀኖና ቤተክርስቲያን ጥሰት" ተግባር ውስጥ የተሳተፉና "በሕገወጥ ሲመት ኤጲስ ጳጳስነት" የተፈጸመላቸው 17 ግለሰቦች ለቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ የይቅርታ ደብዳቤ ማስገባታቸውን የቤተክርስቲያኗ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። 17ቱ ግለሰቦች የይቅርታ ደብዳቤያቸውን ያቀረቡት፣ ዛሬ በጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ከሲኖዶሱ ከፍተኛ ኃላፊዎች ከአቡነ አብርሃም እና ከአቡነ ጴጥሮስ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ መኾኑን ዜና ምንጮቹ ጠቅሰዋል። አቡነ አብርሃም እና አቡነ ጴጥሮስም፣ የይቅርታ ደብዳቤውን ለቅዱስ ሲኖዶሱ ለማቅረብ ቃል መግባታቸው ተገልጧል። ቀሪዎቹ ግለሰቦች በቅርብ ቀናት ተመሳሳይ የይቅርታ ደብዳቤ ያስገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዜና ምንጮቹ ጨምረው ጠቅሰዋል። 2፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ስለ ሰላም፣ ስለ ክልልነት ጥያቄ፣ ስለ ምጣኔ ሃብት፣ ስለ መፈናቀል እና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ዐቢይ፣ ከሥልጣን የመልቀቅ ዕቅድ ይኖራቸው እንደኾነ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ሥልጣን መልቀቅ አለመልቀቅ በምርጫ ብቻ የሚወሰን እንደኾነ ምላሽ ሰጥተዋል። ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ መንገደኞች እንዳይገቡ ኦሮሚያ ክልል ላይ ስለሚገጥማቸው ክልከላ ደሞ፣ በከተማዋ ሁከት የመቀስቀስና መንግሥትን በኃይል የመገልበጥ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው የሚገቡ አካላት እንዳሉ ዐቢይ ተናግረዋል። ከክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ፍልሰት፣ በተያዘው ዓመት ከፍተኛ መሆኑንም ዐቢይ ጠቁመዋል። መንግሥታቸው አገር ለማፍረስ እየሠራ ነው ተብሎ ለበቀረበላቸው ጥያቄም፣ ጉዳዩን እንደ ቀልድ እንደሚወስዱትና የአገር መፍረስና መገነጣጠል አደጋ መቆሙን ገልጸዋል። 3፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥታቸው ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሰላም ለማውረድ እንቅስቃሴ መጀመሩን ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ላይ ተናግረዋል። መንግሥት ለበርካታ ዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆነው በክልሉ የሚካሄደው ግጭት እንዲቆም ፍላጎት ያለው መኾኑን ዐቢይ ገልጸዋል። መንግሥት ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ ለማፈላለግ ሲል የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር የሚመሩት ኮሚቴ ማቋቋሙን የጠቀሱት ዐቢይ፣ እስካሁን 10 ያህል የሰላም ጥረቶችን እንደተሞከሩ ጠቁመዋል። ኾኖም ቡድኑ ማዕከላዊ አመራር ስለሌለው የሰላም ፍለጋ ሂደቱ መጓተቱን ጠቅላይ ሚንስትሩ ጨምረው ገልጸዋል። 4፤ የቤንሻንጉል ጉሙዝ መንግሥት ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጉ አንዳንድ ጥቅማጥቅሞችን ለመስጠት መወሰኑን የክልሉ ብዙኀን መገናኛ ዘግቧል። የክልሉ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ፣ ትጥቃቸውን የፈቱ የቀድሞ አማጺያን በማዕድን፣ ግብርና እና ንግድ እንዲሠማሩ የሚያስችሉ እንደኾኑ ዜና ምንጩ ጠቅሷል። ይህንኑ ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግም፣ የክልሉ መንግሥት የእርሻ ትራክተሮችን፣ የማዕድን ማውጫ መሳሪያዎችን እና የልማት ሥራ ማስጀመሪያ መነሻ ካፒታል እሰጣለሁ ማለቱን ዘገባው ጨምሮ ገልጧል። ክልሉ ለዚሁ ሥራ ምን ያህል በጀት እንደመደበ ግን ዘገባው አልገለጠም። 5፤ የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) አንድ የባለሥልጣናት ቡድን ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ ለሚችለው የገንዘብ ድጋፍ የቴክኒክ ዝግጅቶችን ለማድረግ አገሪቱ ውስጥ እንደሚገኝ ሮይተርስ ዘግቧል። መንግሥት ለአገር በቀል የኢኮኖሚ መርሃ ግብሩ ማስፈጸሚያ ድርጅቱ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግለት በይፋ ጥያቄ ማቅረቡን የድርጅቱ ቃል አቀባይ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ድርጅቱ የድጋፍ ጥያቄውን ካጸደቀ፣ ድጋፉ የመንግሥትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ ለመተግበርና የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማረጋጋት ሥራ ለመፍጠር፣ ለሰብዓዊ ዕርዳታና ድህነትን ለመቀነስ ይውላል ሲሉ ቃል አቀባዩ መግለጻቸውን ዜና ምንጩ አመልክቷል። መንግሥት በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍሎች ሰላም ለማስፈን እያደረገ ያለውን ጥረትና ከትግራይ ኃይሎች ጋር የደረሰበት የሰላም ስምምነት አተገባበርን አይ ኤም ኤፍ በአዎንታ ይመለከተዋል መባሉን በዘገባው ላይ ተመልክቷል። 6፤ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ሰሞኑን በኬንያ የተቀሰቀሰእ ጸረ-መንግሥት ሁከት እንዳሳሰባቸው ዛሬ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ፋኪ፣ ሁሉም ወገኖች ሁከትን አስወግደው የአገር አንድነትን መሠረት ባደረገ መልኩ ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ አድርገዋል። ፋኪ በዚሁ መግለጫቸው፣ ባለፈው ነሐሴ በአገሪቱ በተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዊሊያም ሩቶ ማሸነፋቸውን የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያረጋገጠው ሃቅ መሆኑን ጠቅሰዋል። ታዋቂው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ትናንት በጠሩት የተቃውሞ ሰልፍ፣ በተቃዋሚዎች እና ፖሊስ መካከል ግጭትና ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ከተቃውሞ ሰልፉ ዓላማዎች መካከል፣ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን እንዲፈታና ተቃዋሚዎች "ተጭበርብሯል" ለሚሉት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፍትህ መጠየቅ ይገኙበታል። 7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8833 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9610 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 63 ብር ከ0933 ሳንቲም እና መሸጫው 64 ብር ከ3552 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ0269 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ1874 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል።
Show all...
ሰኞ መጋቢት 18/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ አገረ ስብከት የካቲት 23 ቀን በፒያሳው ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ላይ አስለቃሽ ጭስ የተኮሱ አካላት አጣርቶ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ማቋቋሙን አስታውቋል። አገረ ስብከቱ፣ በአዲሱ ሸገር ከተማ ስር ከተካለሉ ቤተክርስቲያናት መካከል መንግሥት በግብረ ኃይሉ ያስፈረሰውን አንድ የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በራሱ ወጭ መልሶ እንዲያስገነባም አሳስቧል። አገረ ስብከቱ ጨምሮም፣ በቤተክርስቲያናት ላይ የሚፈጸመው "አድሏዊ" እና "ኢ-ሕገመንግሥታዊ" ድርጊት እንዲቆም ጠይቋል። 2፤ ብሄራዊ ባንክ ሦስት አዳዲስ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን መንደፉን ገለፀ። ማሻሻያዎቹ የባንኩን ተቋማዊ ነጻነትና የቁጥጥር ሥልጣን በማጠናከር፣ የሰው ኃይልና ዲጂታል አቅሙን በማሳደግና የገንዘብ ፖሊሲውን በማሻሻል ላይ ያተኮሩ እንደሆኑ ገልጿል። የባንኩ ገዥ ማሞ ምኅረቱ፣ በሦስት ዓመታት ውስጥ 70 በመቶ ኢትዮጵያዊያን ለባንኩ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ እንዲኾኑ ግብ እንደተያዘ መጋቢት 14 ቀን በተካሄደ አንድ መድረክ ላይ መናገራቸውን ሰምተናል። ብሄራዊ ባንክ ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኩባንያ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር ፍቃድ በቅርቡ እንደሚሰጥም ማሞ ተናግረዋል ተብሏል። 3፤ በሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው የተመራ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የከፍተኛ መኮንኖች ልዑክ ቅዳሜ'ለት በማዕከላዊ ሱማሊያ የሒራን ግዛት ከተማ በለደወይን መግባቱን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ልዑክ ወደ ሱማሊያ ያቀናው፣ የሱማሊያ መንግሥት በአልሸባብ ላይ ሁለተኛውን ዙር የማጥቃት ዘመቻ በሚያውጅበት ዋዜማ ላይ ነው። ልዑኩ ከሱማሊያ ጦር ሠራዊት አቻዎቹ ጋር እንደሚወያይና፣ ኢትዮጵያ በቅርቡ ወደ ሱማሊያ ያዘመተቻቸው ቁጥራቸው ያልተገለጹ ወታደሮች ከአልሸባብ ጋር ለመዋጋት ያላቸውን ዝግጁነት እንደሚገመግም ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ከልዑካን ቡድኑ ጋር የተወሰኑ የሱማሌ ክልል ባለሥልጣናት አብረው ተጉዘዋል ተብሏል። 4፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ነገ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት እንደሚያቀርቡና ሪፖርቱን ተከትሎ የምክር ቤቱ አባላት ለሚያቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እንደሚሰጡ ምክር ቤቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። ለጠቅላይ ሚንስትሩ ጥያቄና ማብራሪያ የሚቀርብላቸው፣ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሆነ ምክር ቤቱ ገልጧል። ዐቢይ፣ በተያዘው ዓመት ባለፈው ኅዳር ወር በምክር ቤቱ ተገኝተው ለጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል። ዐቢይ፣ ነገ ለምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡት፣ ምክር ቤት በ61 ተቃውሞ ሕወሃትን ከአሸባሪነት ፍረጃ በሰረዘ ማግስት ነው። 5፤ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በብሄራዊ ምክክሩ ለመሳተፍ ፍቃደኛ ያልሆኑ 13 የፖለቲካ ኃይሎችን ለማግባባት ላለፉት 6 ወራት ያደረጋቸው ሙከራዎች እንዳልተሳኩ ሰምተናል። "ቡድን 13" ተብለው የሚጠሩት እነዚሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በአገራዊ ምክክሩ አንሳተፍም ያሉት፣ በምክክር ኮሚሽኑ የፖለቲካ ገለልተኛነት እና በኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች አሿሿም ሂደት ላይ ጥያቄ በማንሳት ነው። ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር ለመስራት ፍቃደኛ ካልሆኑ ፓርቲዎች መካከል፣ ኦፌኮ፣ ኦነግ፣ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ፣ የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ እና ኦብነግ ይገኙበታል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም፣ ፓርቲዎቹ ወደ አገራዊው የምክክሩ ማዕቀፍ እንዲገቡ ጥረት እያደረገ መኾኑን የምክር ቤቱ ሊቀመንበር መብራቱ ዓለሙ ተናግረዋል። 6፤ የከፍተኛ ትምህርት ምዘናና የፈተናዎች አገልግሎት የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል አገር ዓቀፍ መልቀቂያ ፈተና ልክ እንደ ባለፈው ዓመት ሁሉ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቅጥር ግቢ ውስጥ እንደሚሰጥ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ማስታወቁን የአገር ውስጥ ዜና አውታሮች ዘግበዋል። ተቋሙ ለዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ምዝገባ ከቀጣዩ ረቡዕ ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 15 ድረስ እንደሚካሄድና፣ በጠቅላላው 1 ሚሊዮን ተፈታኞች ይመዘገባሉ የሚል ቅድመ ግምት እንደተያዘ መግለጡን ዘገባዎቹ አመልክተዋል። የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል አገር ዓቀፍ ፈተና የሚሰጥበት ጊዜ ግን፣ የተፈታኞች ትክክለኛ ብዛት ከታወቀ በኋላ እንደሚወሰን ተቋሙ ገልጧል ተብሏል።
Show all...
ረፋድ ቅዳሜ መጋቢት 16/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ አብን የአሜሪካ መንግሥት በሰሜኑ ጦርነት ተሳታፊዎች ላይ ያሳለፈው የወንጀል ፍረጃ ሕወሃት "ወልቃይትን መልሶ በኃይል እንዲቆጣጠር ዓላማ ያለው ነው" ሲል ትናንት ባወጣው መግለጫ ተቃውሟል። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ያወጣው ፍረጃ፣ "መሠረተ ቢስ፣ ሃላፊነት የጎደለው እና አድሏዊ" መሆኑን የጠቀሰው አብን፣ የአማራ ክልል ኃይሎች "በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን" አልፈጸሙም በማለት አስተባብሏል። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በአማራ ክልል ኃይሎች ላይ ያሳለፈውን ፍረጃ እንደገና እንድትፈትሽና እንዲያስተካክልም አብን ጠይቋል። የአሜሪካ መንግሥት የወልቃይት አማራዎች በሕወሃት አስተዳደር ስር ለዓመታት ለደረሰባቸው በደልና ለማንነት ጥያቄያቸው እውቅና እንዲሰጥም አብን ጨምሮ ጠይቋል። 2፤ የጉሙዝ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ 300 ያህል አባላቱ ከእስር ተፈቱለት። ሆኖም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ክሳቸውን ካቋረጠላቸው 463 የድርጅቱ አባላት መካከል፣ 214ቱ አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ ሲሉ የድርጅቱ ሊቀመንበር ግራኝ ጉታ ተናገረዋል። የቡድኑ አባላት ከእስር እየተለቀቁ ያሉት፣ ቡድኑ የትጥቅ ትግሉን አቁሞ በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ከክልሉ መንግሥት ጋር በደረሰበት የሰላም ስምምነት መሠረት ነው። 3፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቀሲስ ዐባይ መለስ የተባሉ ካህን የተገደሉት ሸገር ከተማ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አካባቢ መጋቢት 13 በተፈጠረ ጠብ በደረሰባቸው ጉዳት እንደኾነ ትናንት ባሰራጨው መረጃ ገልጧል። ፖሊስ፣ በአንዳንድ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች ዘንድ ክስተቱ ፖለቲካዊ ትርጉም እንዳለው ለማስመሰል የተደረገው ሙከራ ትክክል አይደለም ብሏል። የግለሰቡ አስከሬን ለምርመራ ሆስፒታል ውስጥ እንደሚገኝ የገለጠው የከተማዋ ፖሊስ፣ ክስተቱ አዲስ አበባ ውስጥ እንደተፈጸመ ተደርጎ የተሠራጨው መረጃ ስህተት መኾኑን ጨምሮ ጠቅሷል። ኾኖም ካህኑ ተገደሉ የተባሉበት ጠብ ምክንያቱ ምን እንደኾነ ፖሊስ አላብራራም። 4፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ የኤርትራ ወታደሮች አሁንም ትግራይ ውስጥ አሉ በማለት ትናንት ለትግራይ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ መናገራቸውን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። ጌታቸው የኤርትራና የአማራ ክልል ታጣቂዎች ባሉባቸው አካባቢዎች "የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን" ፌደራል መንግሥቱ ማስቆም አለበት ብለዋል። ከአማራ ክልል ጋር ያለው ችግር በሕገ-መንግስታዊ መንገድ እንዲፈታ የጠየቁት ጌታቸው፣ በኃይል በታያዙ አካባቢዎች ያለው ጉዳይ ካልተፈታ የሰላም ስምምነቱን በማደብዘዝ ወደለየለት ቁርቁስ ለመግባት የሚያስችል ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችልም ገልጸዋል።
Show all...
ዓርብ መጋቢት 15/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ በትግራይ የሚገኙ ጳጳሳት መጋቢት 13 ቀን "መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተክህነት" የተባለ "ሕገወጥ ክልላዊ መዋቅር" መፍጠራቸው፣ የቤተክርስቲያኗን "ተቋማዊ አንድነትና ነባር መዋቅራዊ አደረጃጀት" የሚንድ መሆኑን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ለአሕጉረ ስብከቶች ሊቀ ጳጳስ መሾም የሚችለው የሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፣ አዲስ የትግራይ ሊቃነ ጳጳሳት በውጭ አገራት የቤተክርስቲያኗ አሕጉረ ስብከቶች ራሳቸውን በራሳቸው መመደባቸው የቤተክርስቲያኗን "ቀኖናዊና አስተዳደራዊ አሠራር" ይጥሳል ብሏል። ቤተክርስቲያኗ የጦርነቱ ደጋፊ እንደነበረች የሚያስመስሉ መግለጫዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው የገለጸው ሲኖዶሱ፣ በትግራይ የሚገኙ የአሕጉረ ስብከቶችን በጀት ከቆመበት ጀምሮ እንደሚልክ ገልጧል። ሲኖዶሱ፣ ሁሉንም ችግሮች ለመፍታት ለመጋቢት 21 ለጠራሁት ምልዓተ ጉባኤ በክልሉ ያሉ አባቶች ይገኙ ሲል ጥሪ አድርጓል። 2፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ የክልሉን "ሕገመንታዊ ግዛቶች ማስመለስ" የአስተዳደራቸው ተቀዳሚ ተግባር እንደሚሆን ዛሬ በሰጡት የመጀመሪያ መግለጫቸው ተናግረዋል። ጌታቸው ምዕራብ ትግራይ፣ ደቡባዊ ትግራይ እና ጸለምት አካባቢዎች በኃይል ተይዘው እንደሚገኙና አሁንም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈጸሙባቸው ገልፀዋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ የክልሉን የጦርነት ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ለመመለስ በትኩረት እንደሚሠራም ጌታቸው ተናግረዋል። ጌታቸው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ሕወሃት ባቀረበው ጥቆማ መሠረት የጌታቸውን ሹመት ትናንት ካጸደቁ በኋላ ነበር። 3፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ነገ ከጉራጌ ዞን ተወካዮች ጋር ወልቂጤ ከተማ ውስጥ ሊወያዩ መሆኑን ከምንጮች ሰምተናል። ዐቢይ ከዞንና ከወረዳ ተወካዮች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከሚውጣጠ የጉራጌ ብሄር ተወካዮች ጋር የሚወያዩት፣ በጉራጌ ዞን የክልልነት አደረጃጀት ጥያቄ ዙሪያ ሳይሆን እንደማይቀር ምንጮቻችን ገልፀዋል። ዐቢይ ትናንት በአዲስ አበባ ከጉራጌ ባለሃብቶች ጋር በዞኑ የክልልነት አደረጃጀት ጥያቄ ላይ የተወያዩ ሲሆን ዐቢይ በዚሁ ስብሰባ ላይ የጉራጌ ሕዝብ ከሌሎች አጎራባች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር ባንድ ክልል ቢዋቀር እንደሚሻል መናገራቸውን አመልክቷል። ጉራጌ ዞን የራሱን ክልል ለማቋቋም ቢወስንም፣ ፌደሬሽን ምክር ቤት ግን ከደቡብ ክልል ቀሪ ዞኖች ጋር ወደፊት በሚዋቀረው "ማዕከላዊ ኢትዮጵያ" ክልል ስር እንዲዋቀር ወስኖበታል። 4፤ ኦሮሚያ እና ሱማሌ ክልሎች በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በርካታ ሰዎች በኮሌራ በሽታ መምታቸውን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለፀ። ኮሌራ ወረርሽኙ ባለፈው ነሐሴ ከተከሰተ ወዲህ 48 ሰዎች እንደሞቱና፣ ድርቁ ወረርሽኙን እንዳባባሰው ተቋሙ ገልጿል። ወረርሽኙ በኦሮሚያ ክልል በ15 ወረዳዎች እንዲሁም በሱማሌ ክልል በሦስት ወረዳዎች መከሰቱን ተቋሙ ጠቅሷል ፣ በኦሮሚያ ክልል ከ1 ሺህ 800 በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል ። በበሽታው ሕይወታቸው ካለፉት መካከል፣ 31 ያህሉ ከኦሮሚያ ክልል ናቸው ተብሏል። 6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8704 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9478 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 63 ብር ከ2737 ሳንቲም እና መሸጫው 64 ብር ከ5392 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ5841 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ7558 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። አንድ የቻይና ዩዋን ደሞ በ7 ብር ከ1385 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ7 ብር ከ2813 ሳንቲም እንደተሸጠ ባንኩ ገልጧል።
Show all...
ጠዋት ዓርብ መጋቢት 15/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ ብሄራዊ ባንክ ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኩባንያ የሞባይል ገንዘብ ማስተላለፊያ አገልግሎት ፍቃድ በቅርቡ ሊሰጥ መሆኑን ሰምተናል። ይህን ትናንት ማምሻውን ያስታወቁት የባንኩ ገዥ ማሞ ምኅረቱ እንደሆኑ ተገለፀ። ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚጀምረው የሞባይል ገንዘብ ዝውውርና ግብይት አገልግሎት፣ የኬንያው ሳፋሪኮም ኩባንያ በኬንያና ሌሎች የቀጠናው አገራት የሚጠቀምበትን "ኤምፔሳ" የተባለውን የገንዘብ መላላኪያና መገበያያ ዘዴ ነው። 2፤ ኢትዮ ቴሌኮም የ"ቴሌ ብር" የሞባይል ገንዘብ መላላኪያና መገበያያ አገልግሎት መስጫ መተግበሪያው በርካታ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ አድርጎ በአዲስ መልክ ማበልጸጉን አስታውቋል። የተሻሻለው የ"ቴሌ ብር" መተግበሪያ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የ23 ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማትን መተግበሪያዎች አቅፎ የያዘ እንደሆነ የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የተሻሻለው መተግበሪያ፣ የታቀደ ክፍያ መክፈልን፣ የዕድል ጨዋታን እና ለቡድን ገንዘብ መላክን ያካትታል ተብሏል። "ቴሌ ብር" ባሁኑ ወቅት 30 ሚሊዮን ደንበኞች እንዳሉት ኩባንያው ትናንት የተሻሻለውን መተግበሪያ ይፋ ባደረገበት ስነ ሥርዓት ላይ ተናግሯል። 3፤ አብን ከኢዜማ ጋር በወቅታዊ አገራዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ የመጀመሪያ ዙር ውይይት ማድረጉን ትናንት ማምሻውን ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ሁለቱ ፓርቲዎች ወደፊትም በሚግባቡባቸው አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመወያየትና የጋራ አቋሞችን ለመያዝ መስማማታቸውን አብን ጨምሮ ገልጧል። ሁለቱ ፓርቲዎች እዚህ ስምምነት ላይ መድረሳቸው የተገለጠው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕወሃትን ከአሸባሪነት መዝገብ መሰረዙ ትልቅ ስህተት መሆኑን ጠቅሰው ተቃውሟቸውን ባሰሙ ማግስት ነው። 4፤ የኤርትራው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኦስማን ሳለህ እና የፕሬዝዳንት ኢሳያስ የፖለቲካ አማካሪ የማነ ገ/አብ ወደ ሩሲያ አቅንተው ከአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር መወያየታቸውን የኤርትራ ቃል አቀባይ የማነ ገ/መስቀል በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል። ኦስማን እና ላቭሮቭ ሶቺ ከተማ ውስጥ፣ በሁለትዮሽና የዩክሬኑን ጦርነት ጨምሮ በዓለማቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደተወያዩ ከውይይታቸው በኋላ በሰጡት መግለጫ መግለጣቸውን የማነ ገልጸዋል። ላቭሮቭ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኤርትራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
Show all...
ምሽት ሐሙስ መጋቢት 14/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ ኢትዮጵያ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ያቋቋመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መርማሪ ኮሚሽን እንዲበተን የጀመረችውን ጥረት ማቋረጧን ሮይተርስ ዲፕሎማቶችንና የሰብዓዊ መብት ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንኑ ጥረቱን ያቋረጠው፣ የመርማሪ ኮሚሽኑ የጊዜ ቆይታ ከመስከረም በኋላ እንደማይራዘም ከምዕራባዊያን አገራት ጋር መግባባት ላይ በመድረሱ እንደሆነ ዘገባው ጠቅሷል። ምዕራባዊያን መንግሥታት ኢትዮጵያ የኮሚሽኑ ተልዕኮ እንዲያበቃ አሁን ጉባኤ ለተቀመጠው የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ብታቀርብ "ድጋፍ ልታገኝ ትችላለች" በሚል ስጋት፣ ከመስከረም በኋላ የኮሚሽኑ ቆይታ እንደማይራዘም መግባባት ላይ መድረስን መርጠዋል ተብሏል። አገራት ለጉባዔው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ የሚያቀርቡበት ቀነ ገደብ ዛሬ ያበቃ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ እንደሌለ ታውቋል። 2፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከትግራይ በቀረበላቸው ጥቆማ መሠረት ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አንዲሆኑ ማጽደቃቸውን ጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ጌታቸው የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሩ ሕወሃት ለጊዜያዊ አስተዳደሩ መስራች ኮሚቴ መርጦ ማቅረቡ ይታወሳል። ዐቢይ ጥቆማውን ተቀብለው ያጸደቁት፣ የሚንስትሮች ምክር ቤት ቀደም ሲል ባጸደቀው የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር መሠረት ነው። የክልሉ ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው፣ የክልሉን የፖለቲካ ኃይሎች ውክልና በሚያረጋግጥ ሁኔታ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ዩማዋቀር ሃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ገልጧል። 2፤ አብን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕወሃትን ከአሸባሪነት ፍረጃ መሰረዙ "ተገማች በሆነ ጊዜ ውስጥ ለሌላ ዙር ግጭትና ጦርነት" አገሪቱን ያጋልጣታል ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ውሳኔውን ተቃውሟል። አብን፣ በዚህ ውሳኔ ሳቢያ ለሚመጣው ጥፋት መንግሥት ተጠያቂ ይሆናል በማለት አስጠንቅቋል። ሕወሃት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ አላደረገም ያለው አብን፣ የጦርነት ቀጠና ሆነው የቆዩትን አካባቢዎች፡ለአራተኛ ዙር "የጦርነት አደጋ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች" እየተፈጠሩ መሆኑን ገልጧል። አብን፣ ውሳኔው በጸደቀበት ስብሰባ በርካታ የምክር ቤት አባላት አለመገኘታቸውና 60 አባላት ውሳኔውን መቃወማቸው፣ ውሳኔውን ቅቡልነት ያሳጣዋል ብሏል። ሕወሃት "የአዲስ ታጣቂ ምልመላ፣ ሥልጠና እና የጦርነት ዝግጅት" እያደረገ ይገኛል በማለትም አብን ከሷል። 3፤ አፍሪካ ኅብረት በሱማሊያ ላሠማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል 90 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ጠይቋል። ኅብረቱ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮው የጠየቀው የገንዘብ ድጋፍ ካልተገኘ፣ ተልዕኮው ለሱማሊያ መንግሥት እና ጦር ሠራዊት ወታደራዊ ድጋፍ እየሰጠ ለመቀጠል እብደሚቸገር ኅብረቱ ተናግሯል። ይህንኑ የኅብረቱን የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄ የተናገሩት፣ የኅብረቱ የፖለቲካ፣ ሰላምና ጸጥታ ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንኮሌ ናቸው። ዛሬ ኒውዮርክ ላይ ተልዕኮው በሚያስፈልገው የገንዘብ ድጋፍ ዙሪያ አፍሪካ ኅብረት እና ተመድ የጋራ ውይይት አድርገዋል። አፍሪካ ኅብረት ባሁኑ ወቅት በሱማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ጨምሮ ከ19 ሺህ 600 በላይ ሰላም አስከባሪዎች አሉት። 4፤ የኬንያው አንጋፋው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ለቀጣዩ ሰኞ "የተቃውሞ ሰልፎች ሁሉ ቁንጮ" ያሉትን የተቃውሞ ሰልፍ ጠርተዋል። ኦዲንጋ፣ የተቃውሞ ሰልፉ ሰላማዊ እንዲሆን ጥሪ አድርገዋል። ኦዲንጋ ባለፈው ሰኞ የጠሩት አገር ዓቀፍ ሰልፍ የተካሄደ ሲሆን፣ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት አንድ ሰልፈኛ ተገድሏል። የሰኞውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ፣ ኦዲንጋ በሳምንት ሁለት ጊዜ ማለትም ሰኞ እና ሐሙስ የተቃውሞ ሰልፎች እንዲደረጉ ጥሪ አድርገዋል። ኦዲንጋ አገር ዓቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ የጠሩት፣ የፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ መንግሥት የአገሪቱን የኑሮ ውድነት አልቀረፈም በማለት እንዲሁም እሳቸው የተሸነፉበት ያለፈው የነሐሴው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተጭበርብራል በሚል ምክንያት ነው። 5፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8607 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9379 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 63 ብር ከ1749 ሳንቲም እና መሸጫው 64 ብር ከ4384 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ1049 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ2670 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል።
Show all...
ሐሙስ መጋቢት 14/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የሕወሃት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካዔል የፌደራሉ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕወሃትን ከአሸባሪነት ፍረጃ ማንሳቱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን ለማዋቀር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል አሉ። ደብረጺዮን፣ በትግራይ ክልል በጀት ዝግጅት እና በእስረኞች ዙሪያ ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ግንኙነት እንደተጀመረ እና አዲስ የሚዋቀረው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እደረጃጀት ለፌደራሉ መንግሥቱ እንደተላከ ጠቅሰዋል። ደብረጺዮን ይህን የተናገሩት፣ ትናንት በመቀሌ ለክልሉ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ነው። 2፤ የሕወሃት ከፍተኛ አመራር ጌታቸው ረዳ የትግራይ የጦር ጉዳተኞች ሰሞኑን ያነሷቸው ቅሬታዎች በከፍተኛ ትኩረት እንደሚታዩ እና ማጣራት እንደሚደረግባቸው መናገራቸውን ሰምተናል። የጦር ጉዳተኞቹ ለእነሱ ተብሎ የተገዛ የሕክምና አቅርቦት እየተሸጠ ስለመሆኑ ነግረውናል፣፣ የጦር ጉዳተኞቹ የጉዳት ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል። የጦር ጉዳተኞቹ ከፍተኛ የሆነ የምግብ፣ የሕክምናና የንጽሕና መጠበቂያ አቅርቦት እጥረት እንዳለባቸው በሰላማዊ ሰልፍና ከጌታቸው ጋር ባደረጉት ውይይት መናገራቸው ተዘግቦ ነበር። የጦር ጉዳተኞቹ፣ በመቀሌ አካባቢ ኩዊሃ እና ደጀን ሆስፒታል በተባሉ ሁለት ማገገሚያ ማዕከሎች የሚገኙ ናቸው። 3፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ ጃኮብሰን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተፈጽመዋል በማለት መፈረጁ በአሜሪካና ኢትዮጵያ ግንኙነት ላይ "አንዳችም ሕጋዊ አንድምታ የለውም" በማለት ማረጋገጫ መስጠታቸውን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። አምባሳደር ጃኮብሰን ይህን ማረጋገጫ የሰጡት፣ ትናንት ከውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሚንስትር ደዔታ ምስጋኑ አረጋ ጋር በተወያዩበት ወቅት እንደሆነ ሚንስቴሩ ገልጧል። ምስጋኑ የአሜሪካ ፍረጃ ተገቢ እንዳልሆነ ለጃኮብሰን ገልጸውላቸዋል ተብሏል። 4፤ የተመድ ስደተኞች ኮሚሽን እና ሌሎች ዓለማቀፍ የረድዔት ድርጅቶች ከሱማሊያ ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ ለገቡ ስደተኞች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ 116 ሚሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል። ድርጅቶቹ የሰብዓዊ ዕርዳታ ልገሳ ጥሪውን ያቀረቡት፣ በሱማሌላንድ መንግሥት ወታደሮች እና በጎሳ ታጣቂዎች መካከል ከሚካሄደው ግጭት ሸሽየው ወደ ኢትዮጵያው ሱማሌ ክልል ለገቡ ሕጻናትና ሴቶች ለበዙባቸው ስደተኞች ነው። ከግጭቱ የሸሹ ከ100 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ ሱማሌ ክልል ዶሎ ዞን መግባታቸውን የተመድ መረጃዎች ያመለክታሉ።
Show all...
ረቡዕ መጋቢት 13/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ሕወሃትን ከአሸባሪነት ፍረጃ አንስቷል። ምክር ቤቱ መንግሥት ያቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ የጸደቀው፣ በ61 ተቃውሞና በ5 ድምጸ ተዓቅቦ መሆኑን የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል።መንግሥት የውሳኔ ሃሳቡን ለምክር ቤቱ ከማቅረቡ በፊት፣ የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ተመራጮች የሆኑ የምክር ቤቱ አባላት ትናንት በጉዳዩ ላይ ጠንከር ያለ ውይይት አድርገው እንደነበር ሰምተናል። በትናንቱ ውይይት ላይ፣ ፍትህ ሚንስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እና የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን ማብራሪያ እንደሰጡ ዘገባው ጠቅሷል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕወሃትን በአሸባሪነት የፈረጀው ሚያዝያ 2013 ዓ፣ም ነበር። 2፤ ኢዜማ መንግሥት ሕወሃትን በአሸባሪነት መዝገብ መሰረዙ "ሊቀለበስ የማይችል ጥፋት ነው" ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ኮንኗል። ውሳኔው ጊዜውን ያልጠበቀ፣ ትክክል ያልሆነ እና "ዘላቂ ሰላምንና ቅቡልነትን" የማያመጣ መሆኑን ፓርቲው ገልጧል። ኢዜማ ውሳኔውን የተቃወመው፣ ሕወሃት "ሙሉ በሙሉ ትጥቅ አለመፍታቱን፣ ከፕሪቶሪያው ስምምነት ውጪ ሕወሃት "በብቸኝነት የትግራይ ሽግግር መንግሥት አውራ" መሆኑን፣ መከላከያ ሠራዊት ትግራይን ሙሉ በሙሉ አለመቆጣጠሩ፣ በወንጀል መጠየቅ ያለባቸው የሕወሃት አመራሮች አለመጠየቃቸውን በመጥቀስ ነው። ውሳኔው፣ ሕወሃት ዳግም "የአገር ስጋት የሚሆንበትን ዕድል እንደመስጠት" ይቆጠራል ያለው ኢዜማ፣ ከዚህ በኋላ ሕወሃት በአገር ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ገዥው ፓርቲና መንግሥት ተጠያቂ ናቸው በማለት አስጠንቅቋል። 3፤ ሂውማን ራይትስ ዎች አሜሪካ እና አውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ እያካሄደ ያለውን የተመድ መርማሪ ኮሚሽን የጊዜ ቆይታ እንዳያቋርጡ አዲስ ባወጣው መግለጫጠይቋል። ድርጅቱ፣ አሜሪካ እና አውሮፓ ኅብረት ሰሞኑን እየተካሄደ ባለው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ የመርማሪ ኮሚሽኑን የጊዜ ቆይታ "ከመስከረም በኋላ ላለማራዘም ፍንጭ ሰጥተዋል" ብሏል። ሂውማን ራይትስ ዎች ጨምሮም፣ የአሜሪካ መንግሥት የኮሚሽኑ ቆይታ እንዲራዘም ማድረግ አለበት ብሏል። መርማሪ ኮሚሽኑ ቀጣዩን ሪፖርቱን ለሰብዓዊ መብት ምክር ቤቱ የሚያቀርበው በመጭው ዓመት መስከረም ወር ላይ ነው። 4፤ መንግሥት ዘንድሮ ግማሽ ዓመት ብቻ 100 ቢሊዮን ብር ከብሄራዊ ባንክ በቀጥታ መበደሩን ባንኩ ያወጣውን ሪፖርት ተመልክተናል። መንግሥት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 60 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በሁለተኛው ሩብ ዓመት 40 ቢሊዮን ብር መበደሩን ዘገባው ጠቅሷል። ባንኩ፣ ዘንድሮ የመንግሥት ቀጥተኛ ብድር በከፍተኛ መጠን የጨመረው የመንግሥት ወጪዎች በመጨመራቸው ነው በማለት አመልክቷል። ባንኩ የመንግሥት ቀጥተኛ ብድር ወደ ረጅም ጊዜ ቦንድ ተቀይሯል ማለቱን የጠቀሰው ዘገባው፣ የመንግሥት አጠቃላይ የቦንድ ዕዳ ወደ 433 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ማሻቀቡ በባንኩ ሪፖርት ላይ እንደተመለከተ አውስቷል። ባለፈው ዓመት መንግሥት ከባንኩ የተበደረው ጠቅላላ ብድር 76 ቢሊዮን ብር ነበር። 5፤ የሱሟሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐመድ የሱማሊያ ቀጣዩ አገር ዓቀፍ ምርጫ "የአንድ ሰው አንድ ድምጽ" የምርጫ ሥርዓትን ተግባራዊ እንደምታደርግ መናገራቸውን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ሱማሊያ ባለፉት በርካታ ዓመታት ባካሄደቻቸው ምርጫዎች የሕግ አውጭ ምክር ቤት አባላትን ሲመርጡ የቆዩት የጎሳ ተወካዮች ሲሆኑ፣ ሕግ አውጭ ምክር ቤቱ ደሞ የአገሪቱን ፕሬዝዳንቶች ሲመርጡ ቆይተዋል። ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ ቀጥተኛ ምርጫ ለማድረግ አቅዳ ሳይሳካላት መቅረቱ ይታወሳል። 6፤ የኡጋንዳ ፓርላማ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ለማገድ ያወጣውን አዲስ ጥብቅ ሕግ ከዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ምዕራባዊያን መንግሥታት እያወገዙት ይገኛሉ። አምነስቲ ኡጋንዳ "መድልዖንና ጥላቻን የሚያበረታታውን ይህንኑ አስደንጋጭ ሕግ እንደገና ምፕፈተሽ አለባት" ብሏል። የአገሪቱ ፓርላማ ትናንት ያጸደቀው ሕግ፣ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች የሞት ቅጣትን ጨምሮ የተለያዩ ከባድ እስር ቅጣቶችን ይጥላል። ሕጉ መገናኛ ብዙኀን የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ስላላቸው ሰዎች መብቶች እንዳይዘግቡ ጭምር ይከለክላል። ሕጉ ሥራ ላይ የሚውለው ግን፣ ፕሬዝዳንቱ ከፈረሙበት ብቻ ነው። 7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8553 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9324 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 62 ብር ከ9998 ሳንቲም እና መሸጫው 64 ብር ከ2598 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ57 ብር ከ9214 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ0798 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። @Ethiopianewsagency (ኢዜአ)
Show all...
በአዲስ አበባ የጤፍ ገበያው አሁንም እያወዛገበ ነው ተባለ ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት በሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ለከተማዋ ነዋሪ ጤፍ በመደበኛ ዋጋ እያቀረበ መሆኑን አሳውቆ ነበር። የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ከአራት ቀናት በፊት ነጭ ጤፍ በኩንታል በ5,600 ብር፣ ሠርገኛ ጤፍ 5,400፣ ስንዴ 5,400 እና በቆሎ ደግሞ 3,300 ብር እየተከፋፈለ መሆኑን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስፍሯል፡፡ ይሁን እንጂ ሸማቾች ዋጋው መንግሥት እንደተናገረው እንዳልሆነ ይልቁኑም አንድ ኪሎ ጤፍ እስከ 80 ብር ሲሸጥ መመልከታቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል። አክለውም ባንዳንድ ቦታዎች ቅናሹ እስከተወሰነ ጊዜ ብቻ እንደሚቆይ ተነግሯል ይህ ደግሞ መንግሥት ሰሞነኛ የዋጋ ማረጋጋት እንጂ ዘለቄታዊ የዋጋ ማስተካከያ አልተደረገም ማለት ያሉ ሲሆን በቀጣይ የጤፍ ዋጋ ከዚህም በላይ ጭማሪ ሊኖረው እንደሚችል ነዋሪዎች ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
Show all...
ረፋድ ረቡዕ መጋቢት 13/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ "ልዩ ስብሰባ" ሊያደርግ መሆኑን ሰምተናል። የስብሰባው ዓላማ፣ ሕወሃትን ከአሸባሪነት መዝገብ ለመሰረዝ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የምክር ቤቱ አባል የሆኑ ምንጮች ጠቅሰዋል። በፌደራል መንግሥቱና በሕወሃት መካከል ፕሪቶሪያ ላይ የተደረሰው የሰላም ስምምነት፣ መንግሥት ምክር ቤቱ በሕወሃት ላይ የጣለውን የአሸባሪነት ፍረጃ እንዲያነሳ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ይጠይቃል። 2፤ የኤርትራ መንግሥት አሜሪካ የኤርትራ ጦር ትግራይ ውስጥ የጦር ወንጀሎችና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ፈጽሟል በማለት መፈረጁን አጣጥሎታል። የአሜሪካ ውንጀላ፣ "በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ ያልተመሠረተ" እና "የአሜሪካ የቆየ ኤርትራን የማጥላላት ፖሊሲ" አካል መሆኑን የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ ገልጧል። መግለጫው፣ የፍረጃው ዓላማ፣ ኤርትራንና የኢትዮጵያ መንግሥትን በማስፈራራት ሕወሃት ሌላ ዙር ችግር እንዲፈጥር ከተጠያቂነት ለማትረፍና ለአሜሪካ ቀጣይ ጣልቃ ገብነት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነው ብሏል። ሕወሃት በመጀመሪያው ጥቃቱ በኢትዮጵያ ጦር ሰሜን ዕዝ ላይ ከ3 ሺህ በላይ ወታደሮችን ገድሏል ያለችው ኤርትራ፣ ሕወሃት ሕጻናትን በግዳጅ ለተዋጊነት መመልመሉን ግን አሜሪካ ሆነ ብላ ችላ ብለዋለች በማለት ወቅሷል። 3፤ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ያቋቋመው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽን ትናንት በምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ሪፖርት አቅርቧል። የምክር ቤቱ አባል አገራት፣ በሪፖርቱ ላይ ተንተርሰው አስተያየቶችን ሰጥተዋል። የምክር ቤቱ አባላት በተለይ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰሜኑ ጦርነት ተጎጅዎች የነደፈውን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ እንደሚደግፉ፣ መንግሥት ለወንጀሎች ተጠያቂነትን ለማስፈን ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ ሁሉም ወገኖች ከተመድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽን ጋር እንዲተባበሩና የሰብዓዊ ዕርዳታና የመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት እንዲሻሻል ጠይቀዋል። መርማሪ ኮሚሽኑ ቀጣዩን ሪፖርቱን የሚያቀርበው በቀጣዩ ዓመት መስከረም እንደሆነ ተገልጧል። 4፤ ኢትዮጵያ ለሱማሌላንድ ራስ ገዝ የሾመቻቸው አዲሱ አምባሳደር የሹመት ደብዳቤያቸውን ሰኞ'ለት ለሱማሌላንዱ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ማቅረባቸውን የሱማሌላንድ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ኢትዮጵያ ለሱማሌላንድ የሾመቻቸው አዲሱ አምባሳደር፣ ደሊል ከድር ቡሽራ ናቸው። አምባሳደር ደሊል፣ ከፕሬዝዳንት ቢሂ ጋር በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። 5፤ የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ራይላ ኦዲንጋ ሰኞ'ለት ደጋፊዎቻቸውን ለተቃውሞ ሰልፍ በመጥራት በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠውን መንግሥት ለመገልበጥ ሞክረዋል በማለት ከሷል። ሚንስቴሩ ለተመድ፣ ለአፍሪካ ኅብረትና ለውጭ ዲፕሎማቶች ባሰራጨው መግለጫ፣ ኦዲንጋ በኃይል ሥልጣን ነጥቀው ራሳቸውን በፕሬዝዳንትነት ለመሾም አቅደው ነበር በማለት ወንጅሏል። መግለጫው፣ ኦዲንጋ ቤተ መንግሥቱን በኃይል ለመውረር ደጋፊዎቻቸውን መጥራታቸው "የአገር ክህደት" ነው ብሏል። ኦዲንጋ ከሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱ ውጭ ሥልጣን ለመያዝ ሙከራ ማድረግን፣ "ለበርካታ ዓመታት የተጠቀሙበት የፖለቲካ ስልት" መሆኑን መግለጫው አውስቷል። ባለፈው ነሐሴ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዊሊያም ሩቶ ኦዲንጋን ማሸነፋቸው ይታወሳል።
Show all...
#ሰበር አሳዛኝ ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ ዐረፉ ሐምሌ 9 ቀን 2009 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ ዕድ የሾሙት ጳጳሳት 14 ኤጲስ ቆጶሳት መካከል አንዱ የሆኑት በቀድሞ ስማቸው አባ ኃይለማርያም መለሰ ዶ/ር በጵጵስና ስማቸው ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ዶ/ር የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት እና የውጪ ግንኙነት መምሪያ የበላይ ኃላፊ የድሬዳዋና የጅቡቲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል። ብፁዕነታቸው ለረጅም ጊዜ ከሀገር ውጪና በሀገር ውስጥ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሊሻላቸው ሳይችል ቀርቶ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
Show all...
ማክሰኞ መጋቢት 12/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የኢትዮጵያ መንግሥት አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት "በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች" እና "የጦር ወንጀሎች" ተፈጽመዋል በማለት መፈረጇን በውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ በኩል ባወጣው መግለጫ ውድቅ አድርጎታል። ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ፍረጃው "አንድን ወገን ብቻ በመወንጀል ላይ ያነጣጠረ" መሆኑን እና "አንዱ ወገን በሌላኛው ላይ ለማነሳሳት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል አቀጣጣይ" መግለጫ ነው በማለት ተችቷል። የአሜሪካ ፍረጃ ኢትዮጵያ በጦርነቱ ለደረሰው ጉዳት የሽግግር ፍትህ ለመተግበር እየተሰናዳች ባለችበት ወቅት መውጣቱ "ወቅቱን ያልጠበቀ" ፍረጃ እንደሚያደርገው ሚንስቴሩ ጨምሮ ገልጧል። 2፤ አውሮፓ ኅብረት አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ተፋላሚ ኃይሎች "የጦር ወንጀሎችን" እና "በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን" ፈጽመዋል በማለት ማውገዟን እንደሚደግፍ አስታውቋል። ይህንኑ የኅብረቱን አቋም ዛሬ በትዊተር ገጻቸው ባሠፈሩት መልዕክት ያስታወቁት፣ የኅብረቱ የኅብረቱ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ናቸው። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ትናንት ይፋ ባደረጉት ኦፊሴላዊ የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦር ሠራዊት እንዲሁም የአማራ ክልል ታጣቂዎች በትግራይ ክልል "በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችንና "የጦር ወንጀሎችን" ፈጽመዋል ያሉ ሲሆን፣ የትግራይ ኃይሎች ደሞ "የጦር ወንጀሎችን" ብቻ ፈጵመዋል በማለት ፈርጀዋል። 3፤ የትግራይ ክልል ፖሊስ የጦር ጉዳተኛ የቀድሞ የትግራይ ተዋጊዎች ደረሱብን ያሏቸውን "የአስተዳደር በደሎች" ለማሰማት ዛሬ በመቀሌ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ባካሄዱበት ወቅት የክልሉ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ መተኮሱን ሰምተናል። ሰልፈኞቹ በጦር ጉዳተኞች ማገገሚያ ማዕከል በቂ ምግብና ውሃ አይቀርብልንም በማለት መፈክሮችን ማሰማታቸውን ሲጠቅሱ ፣ ከክልሉ አስተዳደር ቢሮ እንደደረሱ ከሕወሃት ከፍተኛ አመራር ጌታቸው ረዳና ከወታደራዊ ኃላፊዎች ጋር በቅሬታዎቻቸው ዙሪያ ተወያይተዋል ብሏል። ፖሊስ ሰልፈኞቹ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ አሪድ ካምፓስ አካባቢ ሲደርሱ አስለቃሽ ጭስ የተኮሰው፣ ሰልፈኞቹ ከመቀሌ ወጣ ብሎ ከሚገኝ የጦር ጉዳተኞች ማዕከል ወደ ክልሉ አስተዳደር ቢሮ ሲጓዙ እንደሆነ ሰምተናል። 4፤ ታዋቂው የአካባቢ ጥበቃና የብዝኀ ሕይወት ሳይንቲስት ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገ/እግዚአብሔር ትናንት ሌሊት በ83 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ዶ/ር ተወልደ፣ ልውጥ ዘረ መል የእህል ዘሮች ወደ ኢትዮጵያ መግባት የለባቸውም የሚል ጠንካራ አቋም የነበራቸውና፣ በሰብል ዘሮች የባለቤትነት መብትና በዓለማቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሮች ጉልህ አስተዋጽዖ ያደረጉ ናቸው። ዶ/ር ተወልደ ባንድ ወቅት የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብዝኀ ሕይወት ኢንስቲትዩትን በማቋቋምም ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል። ዶ/ር ተወልደ በሙያቸው ላበረከቱት አስተዋጽዖ፣ ከስዊድን "አማራጭ የኖቤል ሽልማት" እና ከተመድ "ሻምፒዮን ኦፍ ዘ ኧርዝ" ሽልማቶች ተሸልመዋል። የዶ/ር ተወልደ የቀብር ስነ ሥርዓት ነገ በቅድስት ሣላሴ ቤተክርስቲያን ይፈጸማል። 5፤ ሩሲያ ቅድመ ሁኔታዎቿ ካልተሟሉ የዩክሬን የእህል ምርት ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ሰሞኑን እንደገና ከታደሰው ስምምነት ልትወጣ እንደምትችል ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ማስጠንቀቃቸውን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ሩሲያ ያቀረበችው ቅድመ ሁኔታ፣ የግብርና ምርቶቼ ለዓለም ገበያ እንዲቀርቡ ዓለማቀፍ ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው የሚል ነው። የሩሲያ ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ ግን፣ ለተቸገሩ የአፍሪካ አገራት የምግብ እህል በነጻ እንደምትልክ ፑቲን ተናግረዋል ተብሏል። ተመድ፣ ቱርክና ዩክሬን ስምምነቱ የታደሰው ለ120 ቀናት መሆኑን ቢገልጡም፣ ሩሲያ ግን ለ60 ቀናት ብቻ መታደሱን በመግለጽ ላይ ትገኛለች። 6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8456 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9225 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 62 ብር ከ7254 ሳንቲም እና መሸጫው 63 ብር ከ9798 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ57 ብር ከ5340 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ58 ብር ከ6847 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል።
Show all...
ረፋድ ማክሰኞ መጋቢት 12/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ታጣቂዎች እና የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ ክልል ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ጾታዊ ጥቃትን ጨምሮ "በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን" ፈጽመዋል በማለት ፈርጀዋል። በተለይ የአማራ ክልል ኃይሎች፣ በምዕራብ ትግራይ "ሰዎችን በግዳጅ የማፈናቀል" እና "የብሄር ማጽዳት ወንጀሎችን" መፈጸማቸውን ብሊንከን ጨምረው ገልጸዋል። ብሊንከን፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ታጣቂዎች፣ የትግራይ ኃይሎችና የኤርትራ ሠራዊት ደሞ፣ "የጦር ወንጀሎችን" ፈጽመዋል ብለዋል። ፍረጃው፣ በአሜሪካ ፖሊሲ ላይ ወዲያውኑ የሚያስከትለው ለውጥ አይኖርም ተብሏል። ብሊንከን፣ ወንጀሎቹን የፈጸሙ አካላት በሕግ መጠየቅ አለባቸው ብለዋል። ብሊንከን ይህን የተናገሩት፣ ዓመታዊውን የዓለም ሰብዓዊ መብቶች ሪፖርት ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነው። 2፤ የኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን አካባቢ አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች መዳ ወላቡ ወረዳ አዲስ በተዋቀረው ምሥራቅ ቦረና ዞን ሥር መካለሉን ተቃውሞው ቅሬታ አሰሙ። አባ ገዳዎቹና የአገር ሽማግሌዎቹ ቅሬታቸውን ለፌደራሉና ለክልሉ መንግሥት ማቅረባቸውን ሰምተናል። የጉጂ ዞን አባ ገዳዎችም፣ የዞኑ ዋና ከተማ ነገሌ ቦረና ለአዲሱ ምሥራቅ ቦረና ዞን መካለሏን በመቃወም ተመሳሳይ ቅሬታ አቅርበው፣ የክልሉ መንግሥት አደረጃጀቱን እንደማይቀይር መግለጡ ይታወሳል። አዲሱ ምሥራቅ ቦረና ዞን፣ ከቦረና፣ ጉጂ እና ባሌ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎችን በማካተት በቅርቡ የተዋቀረ ዞን ነው። 3፤ በኬንያ 43 የፌስቡክ የመልዕክት ይዘት ተቆጣጣሪዎች ያላግባብ ከሥራ ተሰናብተናል በማለት ክስ መመስረታቸውን የኬንያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ግለሰቦቹ ክሱን የመሠርቱት፣ በፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ እና ሜታ ለይዘት ተቆጣጣሪነት ኮንትራት በስጣቸው "ሳማ" እና "ማጆሬል" በተባሉ ሁለት ኩባንያዎች ላይ እንደሆነ ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። የከሳሾቹ አንደኛው ክስ፣ "ሳማ" ኩባንያ ሠራተኛ ማኅበር በማቋቋማችን ከሥራ አባሮናል የሚል ነው ተብሏል። ሌላኛው ክስ ደሞ፣ ከ"ሳማ" በኋላ ኮንትራት የወሰደው "ማጆሬል" ኩባንያ ለተመሳሳይ የሥራ ቦታ እንዳንወዳደር በሜታ ኩባንያ ትዕዛዝ ስማችን በጥቁር መዝገብ አስፍሮ ከውድድር ከልክሎናል የሚል መሆኑን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። 4፤ በሱማሊያ በተከሰተው ድርቅ እስካለፈው ጥር ወር ድረስ በነበረው አንድ ዓመት 43 ሺህ ያህል ሰዎች ሞተዋል ተብሎ በጥናት እንደተገመተ ዓለማቀፍ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። በጥናቱ ግምት መሠረት፣ ከሟቾቹ መካከል ግማሾቹ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጳናት እንደሆኑ ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። የሟቾችን አሃዝ ሪፖርት ያወጡት፣ የዓለም ምግብ ድርጅት እና የዓለም ሕጻናት ድርጅት ናቸው። ባሁኑ ወቅት በአገሪቱ የቀጠለው ድርቅ ምን ያህል ሰው እንደገደለ ኦፊሴላዊ አሃዝ ሲወጣ የአሀኑ የመጀመሪያው ነው። የተመድ የአየር ትንበያ ተቋም፣ ድርቁ ለስድስተኛ የዝናብ ወቅት ይቀጥላል የሚል ስጋቱን በቅርቡ መግለጡ ይታወሳል።
Show all...
ለቸኮለ! ሰኞ መጋቢት 11/2015 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ፌደራል መንግሥቱ የአማራ ክልል ታጣቂዎችን ከክልሉ ግዛቶች ያስወጣ ሲል ዛሬ በኮምንኬሽን ቢሮው በኩል ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። የክልሉ መንግሥት በዚሁ መግለጫው፣ ፌደራል መንግሥቱ በምዕራብ፣ ደቡባዊና ሰሜን ምዕራብ የትግራይ ግዛቶች የአማራ ክልል ታጣቂዎች ይፈጽሙታል ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የማስቆም ኃላፊነት እንዳለበት አውስቷል። መግለጫው፣ በአማራ ክልል ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ባለችው አላማጣ ከተማ የአማራ ክልልን በመደገፍ የተካሄደው ሰልፍ፣ ከአማራ ክልል ሌሎች አካባቢዎች በርካታ ሰዎችን ወደ ከተማዋ በማጓጓዝ የተደረገ "ተቀባይነት የሌለው" ሰልፍ ነው ብሏል። 2፤ ከኦሮሚያ ክልል የተወከሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አፍሪካ ኅብረት ፌደራል መንግሥቱንና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን እንዲያደራድር በደብዳቤ መጠየቃቸውን ሰምተናል። ተወካዮቹ፣ አፍሪካ ኅብረት በኦሮሚያ ክልል በመንግሥትና በታጣቂው ቡድን መካከል ላለው ግጭት ትኩረት አልሰጠም በማለት መውቀሳቸውን ሰምተናል። የምክር ቤቱ አባላት ይህንኑ ደብዳቤያቸውን ለአፍሪካ ኅብረት ጽሕፈት ቤት ማስገባታቸውን ሰምተናል። የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ ባለፈው ወር ለኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሰላም ጥሪ ማቅረባቸውና ቡድኑም ጥሪውን በጥንቃቄ እንደሚቀበለው መግለጡ ይታወሳል። 3፤ የሱዳን ሲቪል የፖለቲካ ኃይሎች፣ የጦር ሠራዊቱና የፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት መሪዎች በመጭው ሚያዝያ ወር አዲስ ሲቪል የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም መስማማታቸውን የሱዳን ዜና ምንጮች ዘግበዋል።ሦስቱ ወገኖች እዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት፣ ትናንት ውይይቶችን ካደረጉ በኋላ እንደሆነ ዘገባዎቹ ገልጸዋል። ሦስቱ ወገኖች፣ መጨረሻውን የሲቪል ሽግግር መንግሥት ምስረታ የስምምነት ሰነድ የሚያዘጋጅ 11 አባላት ያሉት ኮሚቴ አቋቁመዋል ተብሏል። የስምምነት ሰነዱ ከተፈረመ በኋላ፣ ሲቪል የሽግግር መንግሥቱን ሚያዚያ 3 ላይ ለማቋቋም እንደተወሰነ ተገልጧል። 4፤ ዛሬ በኬንያ በኑሮ ውድነት የተማረሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች አደባባይ ወጥተው ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል። የኬንያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ለአገሪቱ የኑሮ ውድነት መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግና ባለፈው ነሐሴ የተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተጭበርብሯል በማለት በጠሩት ሰልፍ፣ አንድ ተቃዋሚ ሰልፈኜ በፖሊስ ጥይት እንደተገደለ የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የተቃውሞ ሰልፉን ተከትሎ፣ ኦዲንጋ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን እስኪያሻሽል ድረስ ዕለተ ሰኞ የተቃውሞ ሰልፍ ቀን ሆኖ ይቀጥላል ብማለት ተናግረዋል። 5፤ የሱማሊያ መንግሥት የግጭት ስትናጥ ወደከረመችው የሱማሌላንዷ ላስ አኖድ ከተማ ልዑካን ቡድኑን መላኩን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ከአገሪቱ ፓርላማ የተውጣጣው ልዑካን ቡድኑ ከአካባቢው የጎሳ ተወካዮች ጋር ተነጋግሯል ተብሏል። በሱማሌላንድ ራስ ገዝ መንግሥት እና በላስ አኖድ አካባቢ የጎሳ ታጣቂዎች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ፣ የሱማሊያ ፌደራል መንግሥት ልዑካን ቡድኑን ሲልክ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ ለማፈላለግ አንድ ልዑካን ቡድን ወደ ሱማሌላንድ ስለመላኩ ከሳምንት በፊት ተዘግቦ እንደነበር ይታወሳል። 6፤ ትናንት የብሪታንያ መንግሥትን የስደተኞች ፖሊሲ የሚያወግዝ ሰልፍ በለንደን መካሄዱን የአገሪቱ ጋዜጦች ዘግበዋል። የተቃውሞ ሰልፈኞች "ዘረኛ" በማለት ያወገዙት የመንግሥት የስደተኞች ፖሊሲ፣ መንግሥት ከፈረንሳይ ወደ ብሪታንያ በጀልባ አቋርጠው የሚገቡ "ሕኀወጥ" የሚላቸውን ጥገኝነት ጠያቂዎች ስደተኞች ወዲያውኑ ወደመጡበት አገር ወይም ወደሌላ ደኅንነታቸው ሊጠበው ወደሚችልበት ሦስተኛ አገር ለማባረር ያወጣውን አዲስ ሕግ ነው። 7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8407 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9175 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 62 ብር ከ3801 ሳንቲም እና መሸጫው 63 ብር ከ6277 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ57 ብር ከ2488 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ58 ብር ከ3938 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል።
Show all...
ቅዳሜ መጋቢት 9/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ የፓርቲውን ቃል አቀባይና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ጌታቸው ረዳ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ትናንት በአብላጫ ድምጽ መምረጡን የትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ዛሬ ዘግቧል። የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር የሚያዋቅረው፣ ለዚሁ ዓላማ የተቋቋመውና ጀኔራል ታደሠ ወረደ የሚመሩት ክልል ዓቀፍ ኮሚቴ ነው። ኮሚቴው፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሁሉን አካታች እንደሚሆን ሲገልጽ የቆየ ሲሆን፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት የሚያቀርበው ግን ሕወሃት እንዲሆን እንደተወሰነ ቀደም ሲል ተገልጧል። 2፤ አዲሱ ጎጎት የጉራጌ አንድነትና ፍትህ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዛሬ በአዲስ አበባ ባደረገው ስብሰባ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱን፣ ሊቀመንበሩንና ምክትል ሊቀመንበሩን መምረጡን ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ 11 የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን የመረጠ ሲሆን፣ መሐመድ አብራርን የፓርቲው ሊቀመንበር እንዲሁም እስር ላይ የሚገኙትን እንዳለ ንዳን ደሞ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡን ገልጧል። ፓርቲው ከሳምንት በፊት ባካሄደው መስራች ጉባኤ፣ 29 ቋሚ አባላት ያሉት ማዕከላዊ ኮሚቴ አቋቁሟል። ፓርቲው፣ ጉራጌ ዞን ራሱን የቻለ ክልል እንዲሆን እንደሚታገል ቀደም ሲል መግለጡ ይታወሳል። 3፤ በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ከሁለት ዓመት በላይ የተዘጉ የትግራይ ክልል ትምህርት ቤቶችን እንደገና ለማስከፈት ዕቅድ መውጣቱን የተመድ ሕጻናት ድርጅት- ዩኒሴፍ ለቢቢሲ ሬዲዮ ተናግሯል። ድርጅቱ፣ ከክልሉ አስተዳደር ጋር የተያዘው ዕቅድ ትምህርት ቤቶችን በመጭው ሚያዝያ ወር ለመክፈት መሆኑን ገልጧል። በክልሉ በጦርነቱ ሳቢያ 2.3 ሚሊዮን ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው እንደሚገኙ ድርጅቱ ጨምሮ ጠቅሷል። 4፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ "የመደመር ትውልድ" የተሰኘውን አዲሱን መጽሃፋቸውን ዛሬ በታላቁ ቤተ መንግሥት በተካሄደ ስነ ሥርዓት ማስመረቃቸውን የመንግሥት ዜና አውታሮች ዘግበዋል። መጽሃፉ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች እንደተዘጋጀና፣ ክልሎች ከመጽሃፉ ሽያጭ የሚያገኙትን ገቢ ለትውልድ ግንባታና ታሪካዊ ቦታዎችን ለማደስ ያውሉታል መባሉን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። በመጽሃፉ ምረቃ ስነ ሥርዓት ላይ፣ ዐቢይ፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የገዥው ብልጽግና ፓርቲ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል ተብሏል። 5፤ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የአገሪቱን ጦር ሠራዊት ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን እንዲጠብቅ በዋና ዋና ከተሞች ሊያሠማራ መሆኑን የአገሪቱ ዜና አውታሮች ዘግበዋል። መንግሥት ሠራዊቱን በከተሞች የሚያሠማራው፣ ተቃዋሚው "የኢኮኖሚ ነጻነት ተፋላሚዎች" ፓርቲ የመንግሥትና የግል ተቋማትን የሚያዘጋ አገር ዓቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ በቀጣዩ ሳምንት መጥራቱን ተከትሎ ነው። ፓርቲው የተቃውሞ ሰልፉን የጠራው፣ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለውድቀት ዳርገውታል በማለት ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን እንዲለቁ ግፊት ለማድረግ ነው። ወጣቱ ጁሌስ ማሌማ የሚመራው የኢኮኖሚ ነጻነት ተፋላሚዎች ፓርቲ፣ በአገሪቱ ፓርላማ በመቀመጫ ብዛት ሦስተኛው ትልቅ ፓርቲ ነው። 6፤ አወዛጋቢውን በብሪታኒያ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በሩዋንዳ የማስፈር ፖሊሲን የነደፉት የብሪታንያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ስቴላ ብሬቨርማን ዛሬ ኪጋሊ መግባታቸውን የብሪታንያ ጋዜጦች ዘግበዋል። ብሬቨርማን በሩዋንዳ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ፣ ብሪታኒያ "ሕገወጥ" የምትላቸውን ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች በሩዋንዳ ለማስፈር በተደረሰው ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ ተገልጧል። የብሪታንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የአገሪቱ መንግሥት በ"ሕገወጥ" መንገድ የሚገቡ ጥገኝነት ጠያቂዎችንና ስደተኞችን በሩዋንዳ ማስፈር ይችላል ሲል በቅርቡ መወሰኑ ይታወሳል። 7፤ የዩክሬን የምግብ እህል ምርት በጥቁር ባሕር ወደቦች በኩል ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ ከሩሲያ ጋር የተደረሰው ስምምነት ዛሬ በድጋሚ ለአራት ወራት መታደሱን የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ዘግቧል። ሩሲያና ዩክሬን ስምምነቱን ያደሱት፣ በተመድና በቱርክ አደራዳሪነት ለበርካታ ቀናት ድርድር ከተደረገ በኋላ ነው። ሩሲያ ስምምነቱ ለሁለት ወራት ብቻ እንዲታደስ ከቀናት በፊት ሃሳብ አቅርባ ነበር። ባለፈው ኅዳር ለአራት ወራት የታደሰው ይኼው ስምምነት፣ የቆይታ ጊዜው በዛሬው ዕለት ይጠናቀቅ ነበር።
Show all...
ጠዋት ቅዳሜ መጋቢት 9/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ የፓርቲው ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ማጨቱን ሰምተናል። ሕወሃት የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ካዋቀረ በኋላ፣ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በሚያደርጋቸው ድርድር መዋቅሩ መጽደቅ ይጠበቅበታል። የትግራይ ዓለማቀፍ ምሁራን ማኅበር ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ዕጩ እንድጠቁም በቀረበልኝ ጥያቄ መሠረት፣ ጡረተኛውን ጀኔራል ጻድቃን ገ/ተንሳይን እጩ አድርጌ አቅርቤያለሁ ማለቱ ይታወሳል። በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የሚቋቋመው፣ ፕሪቶሪያ ላይ በፌደራል መንግሥቱና ሕወሃት መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሠረት ነው። 2፤ የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ያካሄደውን ስብሰባ አስመልክቶ ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ የፓርቲው ባለሥልጣናት ከጥላቻና ከግጭት ቀስቃሽ ንግግሮችና ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳስቧል። ምሁራን፣ የሐይማኖት አባቶች፣ መገናኛ ብዙኀን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችም፣ ከጥላቻና ግጭት አባባሽ እንዲሁም የአገርን ሰላምና ደኅንነት ለአደጋ ከሚያጋልጡ ንግግሮች እንዲቆጠቡ ያሳሰበው ፓርቲው፣ የፍትህና ጸጥታ አካላትም እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችን በቸልተኝነት እንዳይመለከቱ ጠይቋል። ፓርቲው አገሪቱ የገጠሟትን ችግሮች በዝርዝር መመርመሩን ገልጦ፣ ከዋና ዋና ችግሮች መካከል የታሪክ እዳዎች፣ የነጻነት አያያዝ ችግሮችና የኑሮ ውድነት ተጠቃሽ እንደሆኑ አብራርቷል። 3፤ የጉሙዝ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ የታሠሩ 46 አባላቱ መፈታታቸውን ተናገረ። ሆኖም በመተከልና ካማሺ ዞኖች ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ የታሠሩ አባላቱ በሙሉ አለመፈታታቸውን ፓርቲው መግለጡን አመልክቷል። ንቅናቄው ከስድስት ወር በፊት ትጥቁን ፈትቶ በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ከክልሉ መንግሥት ጋር በፈረመው የሰላም ስምምነት መሠረት፣ ሦስት ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎቹ ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀላቸውን የንቅናቄው ሊቀመንበር ግራኝ ጉታ ተናግረዋል ተብሏል። የክልሉ ፖሊስ በበኩሉ፣ የሰው ሕይወት በማጥፋት ከተጠረጠሩት ውጭ ሌሎቹ በሙሉ ፕፈታሉ ማለታቸውን ጠቅሷል። ምርጫ ቦርድ የሰረዝኩትን የንቅናቄውን የሕጋዊ የፓርቲነት ፍቃድ መልሼ ሰጥቻለሁ ማለቱ ይታወሳል። 4፤ ባይደዋ ከተማ ላይ በብሄራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር ያደረጉት የሱማሊያ ፌደራል መንግሥት እና የፌደራል ግዛቶች መንግሥታት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በጋራ ባወጡት መግለጫ መግለጣቸውን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የበይነ መንግሥታት ምክክሩ ያተኮረው፣ የአገሪቱን ተቋማት በማጠናከር፣ የጸጥታ መዋቅር ማሻሻያ በማድረግ እና የፋይናንስ ሥልጣኖችን ያልተማከሉ በማድረግ አስፈላጊነት ላይ ነው። በብሄራዊ ምክክሩ ላይ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐመድ እና የፌደራል ግዛቶች ፕሬዝዳንቶች የተሳተፉ ሲሆን፣ የፑንትላንድ ራስ ገዝ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ደኒ ግን እንዳልተሳተፉ ተገልጧል። ፑንትላንድ በምክክሩ አለመሳተፏ አሳሳቢ መሆኑን የገለጸው መግለጫው፣ ምክንያቱን ለማወቅ ወደ ፑንትላንድ ኮሚቴ እንዲላክ ተወስኗል ብሏል። 5፤ ዓለማቀፉ የነፍስ አድን ድርጅት አይ አር ሲ የዩክሬን የእህል ምርት በጥቁር ባሕር በኩል ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ባለፈው ሐምሌ የተደረሰው ስምምነት ካልታደሰ በምሥራቅ አፍሪካ የ40 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ይወድቃል በማለት አስጠንቅቋል። ተመድ ስምምነቱ ለአንድ ዓመት እንዲታደስ እንዲያደርግ ድርጅቱ ጠይቋል። ከስምምነቱ ወዲህ በጥቁር ባሕር በኩል ወደ ውጭው ዓለም ከወጣው የዩክሬን የምግብ እህል ውስጥ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ሱማሊያ፣ የመን እና አፍጋኒስታን የደረሰው 10 በመቶው ብቻ እንደሆነ ድርጅቱ ገልጧል። ሩሲያ ስምምነቱ ለሁለት ወራት ብቻ እንዲታደስ ሃሳብ አቅርባለች። በተመድና ቱርክ አደራዳሪነት ሩሲያና ዩክሬን የደረሱበት ስምምነት ባለፈው ኅዳር አንድ ጊዜ የታደሰ ሲሆን፣ ቀነ ገደብም ዛሬ ይጠናቀቃል።
Show all...
ምሽት ዓርብ መጋቢት 8/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ካለፈው ሳምንት ሐሙስ ጀምሮ በከተማዋ የባጃጅ ትራንስፖርት ላይ የጣለውን እገዳ ከነገ ጀምሮ እንደሚያነሳ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ መናገሩን የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የባጃጅ አሽከርካሪዎች መደበኛ ትራንስፖርት በሌለባቸው አካባቢዎች እስከ 2 ነጥብ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡና ባንድ ተሳፋሪ ከ5 ብር በላይ እንዳያስከፍሉ ቢሮው የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎትን ለመምራት ባዘጋጀው አዲስ መመሪያ ላይ ወስኛለሁ ማለቱን ዘገባዎቹ አመልክተዋል። አዲሱ መመሪያ፣ የስምሪት መስመሮችን፣ ታሪፎችንና የአገልግሎት መስጫ ሰዓትን የሚወስን እንደሆነ ተገልጧል። በመመሪያው መሠረት፣ ባጃጆች አገልግሎት የሚሰጡት ከንጋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ ብቻ ይሆናል ተብሏል። 2፤ የሕወሃት ሥራ አስፈጻሚ አባልና የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ገለጻ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። ጌታቸው ለብሊንከን ገለጻ ያደረጉት፣ በትግራዩ ጦርነት ለተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት በማስፈን አስፈላጊነት፣ በፌደራል መንግሥቱና ሕወሃት መካከል የተደረሰውን ሰላም ስምምነት ለመቀልበስ በሚጥሩ ኃይሎችና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን በማቋቋም ሂደት ባጋጠሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ መሆኑን ገልጸዋል። "በጦርነቱ በትግራይ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ከብሄራዊ የሕግ ማዕቀፍ የሚያልፉ ናቸው" ያሉት ጌታቸው፣ መንግሥት ባዘጋጀው የሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ ላይ "ዓለማቀፍ ጥረቶች ያስፈልጋሉ" ብለዋል። 3፤ ስድስት አባላት ያሉት የተመድ እና አውሮፓ ኅብረት ልዑካን ቡድን በአማራ ክልል ተገኝቶ በፌደራል መንግሥቱና በሕወሃት መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ከክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገሩን የአገር ውስጥ ዜና አውታሮች ዘግበዋል። ልዑካን ቡድኑ የሰላም ስምምነቱ አተገባበር በአማራ ክልል በኩል ምን እንደሚመስል የመገምገም፣ ለአተገባበሩ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን የመለየት እና በተግዳሮቶቹ ዙሪያ የክልሉን ባለሥልጣናት ምላሽ እና ፍላጎቶች የመስማት ተልዕኮ እንዳለው ዘገባዎቹ አመልክተዋል። 4፤ ከሱማሊያ ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱ ስደተኞች ቁጥር ማሻቀቡ በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ድርጅቱ፣ ለስደተኞቹ መርጃ ተጨማሪ የመድኃኒት፣ የሕክምና ቁሳቁሶችና የሕክምና ባለሙያዎች ድጋፍ ያስፈልጋል ብሏል። ድርጅቱ፣ ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ ከሱማሊያ ሕጻናትና ሴቶች የሚበዙባቸው ከ100 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያው መግባታቸውን ገልጧል። አብዛኞቹ ስደተኞች ተጠልለው የሚገኙት በክልሉ ዶሎ ዞን እንደሆነ የገለጠው ድርጅቱ፣ ለስደተኞቹና በከባድ ድርቅ ለተመታው የስደተኞቹ ተቀባይ ማኅበረሰብ ለ9 ወራት ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ፣ 101 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብሏል። 5፤ ዓለማቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ዛሬ በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቷል። ፍርድ ቤቱ በፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ያወጣው፣ በዩክሬን ላይ ተፈጽመዋል ላላቸው የጦር ወንጀሎች ተጠያቂ ናቸው በማለት ነው። ፍርድ ቤቱ፣ ፕሬዝዳንት ፑቲን ሕጻናትን ጨምሮ ዩክሬናዊያን ዜጎችን ከሕግ ውጭ ወደ ሩሲያ በመላክ ወንጀል ፈጽመዋል ብሏል። በፍርድ ቤቱ በታሪኩ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል በሆነች አገር መሪ ላይ የእስር ማዘዣ ሲያወጣ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው። ሩሲያ የዓለማቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤቱን መመስረቻ ስምምነት ፈርማ የነበረ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ከ6 ዓመት በፊት ሩሲያ የዩክሬኗን ክራይሚያ ግዛት "በወረራ ይዛለች" የሚል ሪፖርት ማውጣቱን ተከትሎ ግን ፊርማዋን አንሳታለች። 6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8305 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9071 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 61 ብር ከ9108 ሳንቲም እና መሸጫው 63 ብር ከ1490 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ57 ብር ከ0711 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ58 ብር ከ2125 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። አንድ የቻይና ዩዋን ደሞ በ7 ብር ከ0609 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ7 ብር ከ2021 ሳንቲም እንደተሸጠ ባንኩ ገልጧል።
Show all...
ዓርብ መጋቢት 8/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው በማለት መናገሩን""ሃላፊነት የጎደለው" ንግግር በማለት እንዳወገዘው ሰምተናል። ኢትዮጵያ፣ የግብጽ ዛቻ የተመድ እና አፍሪካ ኅብረት ቻርተሮችን እንዲሁም በግድቡ ላይ ከራሷ ከግብጽ እና ሱዳን ጋር የተደረሰውን የሦስትዮሽ ስምምነት የሚጻረር መሆኑን ገልጧል ። ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ግብጽ በግድቡ ዙሪያ "ተገቢ እና ሕጋዊ ካልሆኑ" መግለጫዎችን ከመስጠት እንድትቆጠብ ማሳሰቡንም አመልክቷል። 2፤ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን አሁንም በርካታ ሰዎች ታስረው ይገኛሉ ተባለ። አሁንም እስር ላይ ከሚገኙት መካከል፣ ቁጥራቸው ያልታወቁ የምክር ቤት አባላት ይገኙበታል። የደቡብ ክልል ፖሊስ በበኩሉ፣ ከዞኑ የታሠሩት ሰዎች ከ40 እንደማይበልጡ ገልጦ፣ የመታሠራቸው ምክንያት "ብጥብጥ ከማስነሳት" ጋር የተያያዘ መሆኑን አመልክቷል። ሆኖም እስሩ በአብዛኛው ከጉራጌ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ስለመሆኑ፣ ዘገባዎች ሲወጡ መቆየታቸው ይታወሳል። ከዞኑ ዋና ከተማ ወልቂጤ የተያዙት ሰዎች፣ ወደ ቡታጅራ ከተማ ተወስደው እንደታሠሩ ቤተሰቦቻቸው አመልክተዋል። 3፤ የኢትዮጽያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ፣ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉብኝት ካደረጉት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር አዲስ አበባ ውስጥ መወያየታቸውን ኮሚሽኑ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። የኮሚሽነሩና የብሊንከን ውይይት፣ በሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነት፣ በድርቅና ግጭት ተጎጂዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት እና በወንጀል ተጠያቂነት ዙሪያ ያተኮረ እንደነበር ኮሚሽኑ ጠቅሷል። የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ያልተመጣጠነ ኃይል መጠቀም፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እስሮች ጭምር ውይይት እንደተደረገባቸው ተገልጧል። 4፤ አሜሪካ ለሱማሊያ ጦር ሠራዊት ልዩ ኮማንዶ "ደናብ" የምትሰጠውን ሥልጠናና የወታደራዊ ትጥቅ አቅርቦት እንድትቀጥል ከሱማሊያ ጋር ስምምነት መፈረሟን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። አሜሪካ ለ"ደናብ" ልዩ ብርጌድ አባላት ሥልጠና ከመስጠትና ትጥቅ ከማቅረብ በተጨማሪ፣ ለእያንዳንዱ ሰልጣኝ 300 ዶላር ወርሃዊ አበል ትከፍላለች። "ደናብ" ልዩ ብርጌድ፣ ከአልሸባብ ጋር በሚደረገው ሁለንተናዊ ጦርነት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ይነገርለታል። ከአሜሪካ በከል ስምምነቱን የፈረሙት፣ በሱማሊያ የአሜሪካ አምባሳደር ላሪ አንድሬ ናቸው ተብሏል።
Show all...
ሐሙስ መጋቢት 7/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ ኢሰመኮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በባለ ሦስትና ባለ አራት እግር ባጃጆች ላይ ከየካቲት 30 ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ በመላ ከተማዋ የጣለውን እገዳ እንዲያነሳ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። ኮሚሽነ፣ እገዳው በተለያዩ ሰብዓዊ መብቶች ላይ "ተገቢ ያልሆነ ገደብ የሚጥል" እና በሹፌሮች፣ በቤተሰቦቻቸውና በባጃጅ ተጠቃሚዎች ላይ ችግር የፈጠረ ርምጃ መሆኑን ገልጧል። የከተማዋ አስተዳደር፣ የሥራ ፍቃድ ያልተሰጣቸው10 ሺህ ባጃጆች እንዲሁም ከተፈቀደላቸው መስመር ውጪ በዋና መንገዶች ላይ የሚሠሩ ባጃጆች መኖራቸውን ጠቅሶ፣ "አገልግሎትን የሚያሻሽል አሠራር እስክዘረጋ እገዳውን ጥያለሁ ማለቱን ኢሰመኮ ጠቅሷል። ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ፣ አስተዳደሩ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎች፣ አካል ጉዳተኞችን፣ አረጋዊያንን፣ ሴቶችንና ሕጻናትን ታሳቢ ያደረገ ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈልግ ጠይቀዋል። 2፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ በመንግሥትና በግል አጋርነት 100 ሺህ መኖሪያ ቤቶችን ለማስገንባት ዛሬ ከግል ባለሃብቶች ጋር ስምምነት መፈራረሙን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። መኖሪያ ቤቶቹ በ70/30 የቤት መርሃ ግብር እንደሚገነቡ የገለጠው አስተዳደሩ፣ መኖሪያ ቤቶቹ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብሏል። አስተዳደሩ፣ ለቤቶቹ ግንባታ በቂ መሬት ማቅረቡንና ግንባታውም በሁለት ወራት ውስጥ እንደሚጀመር ገልጧል። 3፤ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ዛሬ ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ኒዠር ተጉዘዋል። ብሊንከን ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከሕወሃት ባለሥልጣናት በተጨማሪ፣ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ከረድኤት ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ተነጋግረዋል። ዛሬ ረፋዱ ላይ ደሞ፣ ብሊንከን በቅርቡ ዋሽንግተን ላይ የተካሄደው የአሜሪካና አፍሪካ መሪዎች ጉባኤ የተስማማባቸውን የአሜሪካና አፍሪካ የትብብር መስኮች ማጎልበት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ጋር እንደተወዩ በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል። 4፤ የሱማሊያ ፌደራል መንግሥት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐመድ እና የፌደራል ግዛቶች መሪዎች ለኢትዮጵያ አጎራባች በሆነችው ባይደዋ ከተማ ዛሬ ብሄራዊ ምክክር ጀምረዋል። የፌደራል መንግሥቱ እና የፌደራል ግዛቶች ምክክር አጀንዳዎች፣ የአገሪቱን የጸጥታ መዋቅር መልሶ በማዋቀር አስፈላጊነት፣ የበጀትና ሌሎች ፋይናንስ ነክ ሥልጣኖችን ያልተማከለ ማድረግ በሚችልበት ሁኔታ እና በፌደራል እና በፌደራል ግዛቶች ደረጃ በሚካሄዱ ምርጫዎች ዙሪያ እንደሆነ የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። በምክክሩ ላይ ከፑንትላንድ ራስ ገዝ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ደኒ በስተቀር የሁሉም ግዛቶች ፕሬዝዳንቶች ተገኝተዋል ተብሏል። ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ፣ ቀደም ሲል በፌደራል መንግሥቱ እና በተወሰኑ የፌደራል ግዛቶች መካከል ሻክሮ የቆየውን የበይነ መንግሥታት ግንኙነት ለመጠገን ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። 5፤ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ያሠማራውን የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ቆይታ ላንድ ዓመት አራዝሟል። 17 ሺህ ያህል ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ያሉት የሰላም ማስከበር ተልዕኮው፣ በዓመት በዓለም ከፍተኛው 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በጀት የሚወጣበት ተልዕኮ ነው። የሰላም ማስከበር ተልዕኮው፣ ሰላማዊ ሰዎችን ከጥቃት የመከላከል፣ ለሰብዓዊ ዕርዳታ ሥርጭት ምቹ ሁኔታ የመፍጠር፣ በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና በተቃዋሚው መሪ በተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሬክ ማቻር መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አተገባበር የመደገፍ እና ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የመከታተል ሃላፊነት አለበት። 6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8251 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9016 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 62 ብር ከ2387 ሳንቲም እና መሸጫው 63 ብር ከ4835 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ57 ብር ከ4421 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ58 ብር ከ5909 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል።
Show all...
ጠዋት ሐሙስ መጋቢት 7/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የከተማዋንና የወረዳ ምክር ቤቶች አባላትን እና የምርጫ ክልሎችን ብዛት የሚወስን አዋጅ ትናንት ማጽደቁን ገልጧል። አዋጁ የምክር ቤቶች አባላቱ ብዛት ከ150 እንዳያንስና ከ250 እንዳይበልጥ የሚደነግግ ነው። ምክር ቤቱ አዋጁን ያጸደቀው፣ ምርጫ ቦርድ በተያዘው ዓመት አካሂደዋለሁ ላለው የከተማና አካባቢ ምርጫ ለማድረስ መሆኑን መግለጡን የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ከተማዋ የከተማ፣ የክፍለ ከተማና የወረዳ ምክር ቤቶችን አባላቱ ብዛት የሚወስን ሕግ እስካሁን እንዳልነበራት በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ተገልጧል ተብሏል። 2፤ በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ከሕወሃት አመራሮች ጋር መነጋገራቸውን አስታውቀዋል። ብሊንከን ይህንኑ ውይይታቸውን አስመልክተው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሰጡት መግለጫ፣ የመንግሥትና ሕወሃት የሰላም ስምምነት ተጠናክሮ ከቀጠለ ኢትዮጵያ ወደታገደችበት የአሜሪካው የነጻ ንግድ ዕድል (አጎዋ) ተጠቃሚነቷ እንድትመለስ ሊደረግ እንደሚችል መናገራቸውን ሪፖርተር ዘግቧል። ብሊንከን፣ ኤርትራ ወታደሮች ከሰሜን ኢትዮጵያ እየወጣ መሆኑንም መግለጣቸውንም ዘገባው ጠቅሷል። 3፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ትናንት ባካሄደው ጉባኤ አንዳንድ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የቤተክርስቲያኗ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ሲኖዶሱ፣ ወደ ቤተክርስቲያኗ የተመለሱ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት ቀደም ሲል የሾሟቸው 25 ግለሰቦች፣ በቅርቡ በተደረሰው ስምምነት መሠረት በአምስት ቀናት ውስጥ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በጽሁፍ ሪፖርት እንዲያደርጉ አሳስቧል። መንግሥት በኦሮሚያ ክልል የቤተክርስቲያኗን አሕጉረ ስብከቶችና መንበረ ጵጵስናዎችን በኃይል የያዙ አካላትን እንዲያስወጣና ቢሮዎቹንና ንብረቶችን ለቤተክርስቲያኗ እንዲያስረክብ እንዲሁም የታሰሩ የቤተክርስቲያኗን ኃላፊዎች ምዕመናን እንዲፈታ ሲኖዶሱ ጠይቋል። 4፤ የተመድ ሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮና የኢትዮጵያ መንግሥት በተያዘው የአውሮፓዊያኑ ዓመት በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ የነፍስ አድን ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲሉ አዲስ ባወጡት የጋራ የሰብዓዊ ዕርዳታ ጥሪ አስታውቀዋል። ለሰብዓዊ ዕርዳታው 3.99 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የጋራ የድጋፍ ጥሪ ሪፖርቱ ጠቅሷል። በአገሪቱ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን የውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የገለጸው ሪፖርቱ፣ የዕርዳታ ፍላጎቱ ከፍተኛ መሆኑንና አዳዲስ ዓለማቀፍ ለጋሾች እንደሚያስፈልጉ ገልጧል። መንግሥት እና ዓለማቀፍ ለጋሾች በተያዘው ዓመት 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአደጋ ተጋላጮችን ከቀውስ እንዲያገግሙ ለማስቻል ማቀዳቸውም በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል።
Show all...
ረቡዕ መጋቢት 6/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዛሬ ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውን አስታውቀዋል። ዐቢይ፣ ከብሊንከን ጋር በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮች እንዲሁም በሁለትዮሽና የጋራ ጥቅሞቻችን በሚያጠነጥኑባቸው ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጠለቅ ያለ ውይይት አድርገናል ብለዋል። ዐቢይ፣ የኢትዮጵያንና አሜሪካን የረጅም ጊዜ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ከብሊንከን ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ገልጸዋል። 2፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር ዛሬ ጧት በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል። ውይይቱ፣ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና ሕወሃት የሰላም ስምምነት አተገባበር እና የዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መርማሪዎች ግጭት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ገብተው ሥራቸውን እንዲሠሩ በመፍቀድ ዙሪያ እንደነበር የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ደመቀና ብሊንከንና አካታችና ሁለገብ በሆነ የሽግግር ፍትህ ሥርዓት አስፈላጊነት እና አሜሪካ ለሽግግር ፍትህ ሥርዓት አተገባበር ልትሰጠው በምትችለው ድጋፍ ላይ ጭምር መወያየታቸውን መግለጫው ጠቅሷል። ብሊንከን፣ የሰላም ስምምነቱን ማስቀጠልና የአሜሪካና ኢትዮጵያን የወደፊት ግንኙነት ማጠናከር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል። ብሊንከን፣ ከሕወሃት ባለሥልጣናት ጋር እንደሚወያዩም ይጠበቃል። 3፤ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን አገራቸው በግጭት፣ ድርቅ እና በምግብ ዋስትና እጦት ለተጎዱ ኢትዮጵያዊያን የሚውል 331 ሚሊዮን ዶላር በተያዘው የአውሮፓዊያን ዓመት እንደምትሰጥ ማምሻውን ይፋ አድርገዋል። ከዚሁ የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ፣ 12 ሚሊዮኑ ዶላሩ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኩል ለኢትዮጵያ የሚሰጥ ሲሆን፣ ቀሪው የገንዘብ ድጋፍ ደሞ በአሜሪካ ዓለማቀፍ ተራድዖ ድርጅት (ዩ ኤስ አይ ዲ) አማካኝነት የሚሰጥ እንደሆነ ብሉሊንከን መግለጣቸውን መስሪያ ቤታቸው ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። 4፤ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዳያካሂዱ የሚፈጸምባቸው የማደናቀፍ ተግባር በፓርቲዎቹ ላይ ብቻ ሳይሆን በራሱ በቦርዱ ላይ ጭምር የተጋረጠ አደጋ መሆኑን ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ሰሞኑን በእናት ፓርቲና በባልደራስ ፓርቲ ላይ የተደረገው የጠቅላላ ጉባኤ ክልከላ፣ ቦርዱ ተልዕኮውን እንዳይወጣ የሚያደርግ መሆኑን ቦርዱ ገልጧል። ክልከላውን የፈጸሙት፣ የመንግሥት ሕግ አስፈጻሚዎች መሆናቸውን ደርሼበታለሁ ያለው ቦርዱ፣ የድርጊቱ ፈጻሚ አካላት ግን ድርጊቱን አስተባብለዋል ብሏል። ቦርዱ፣ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ክስ እንዲመሠረትባቸው እንደማያደርግም ገልጦ፣ ሰሞኑን የታሠሩ የጉራጌ አንድነትና ፍትህ ፓርቲ አመራሮች እንዲፈቱም ጠይቋል። ቦርዱ ለጊዜው ለፓርቲዎቹ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄጃ ቦታ እንደሚያመቻች ተናግሯል። 5፤ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር በአገር ዓቀፍ ደረጃ ልመናንና የጎዳና ላይ የወሲብ ንግድን ለማስቀረት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀቱን ገልጿል። "የማኅበራዊ ጥበቃ ፈንድ" የተሰኘው ረቂቅ አዋጅ፣ መንገድ ላይ የሚለምኑና ለልመና ምጽዕዋት የሚሰጡ ሰዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ ነው። ረቂቅ አዋጁ፣ ችግረኞችን ባንድ ቋት መርዳት የሚያስችል ሥርዓት እንደሚዘረጋ የሚንስቴሩ ሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ተናግሯል። ሚንስቴሩ ረቂቅ አዋጁን አጠናቆ፣ ለፍትህ ሚንስቴር እንደላከ ታውቋል። በአዲስ አበባ ብቻ ባሁኑ ወቅት ከ88 ሺህ በላይ ሰዎች በልመና ላይ ተሠማርተው እንደሚገኙ ይገመታል። 6፤ የፌደራል እንባ ጠባቂ ተቋም የኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ የተባለ ጣቢያ ተቋሙ በኦሮሚያ ክልል የሠራቸው የቁጥጥር ሥራዎች የሉም በማለት ያሠራጨውን ዘገባ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አውግዟል። ተቋሙ በመግለጫው፣ የጣቢያው ዘገባ "ተቋሙን ከአንድ የተከበረ ሕዝብ ለመነጠል" የተደረገው ሙከራ፣ "ሃላፊነት የጎደለው" እና "ሃቅን ያላነገበ" ነው ብሏል። ተቋሙ በአዲስ አበባ ከተማ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች በቋንቋቸው እንዳይማሩ መግለጫ አውጥቷል በማለት ጣቢያው ያቀረበው ውንጀላም፣ ሐሰተኛና አሳሳች መሆኑን ተቋሙ ገልጧል። በወቅቱ ተቋሙ ያወገዘው በትምህርት ቤቶች በግዳጅ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ እንዲሰቀልና ሕዝብ መዝሙሩ እንዲዘመር የተደረገውን እንቅስቃሴ መሆኑን መግለጫው ጠቅሷል። ተቋሙ፣ ጣቢያው የተቋሙን ሠራተኞችና የሃላፊዎች ምደባ በብሄር ማንነት ከፋፍሉ ለማቅረብ መሞከሩን ጠቅሶ፣ ዘገባው ሕገ መንግሥታዊ መሠረትም ሆነ እውነታነት የሌለው መሆኑን ገልጦ አጣጥሎታል። 7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8160 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ8923 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 62 ብር ከ4338 ሳንቲም፣ መሸጫው 63 ብር ከ6825 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ57 ብር ከ6638 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ58 ብር ከ8171 ሳንቲም ሲሸጥ ውሏል። @Ethiopianewsagency (ኢዜአ)
Show all...
ማክሰኞ መጋቢት 5/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ፍልሰት መንግሥትን ገልብጦ ሥልጣን የመቆጣጠር ሴራ ነው በማለት መናገራቸው ብዙዎችን አስቆጣ። አዳነች ይህን የተናገሩት፣ ትላንት በከተማዋ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት ነው። አንዳንድ ኃይሎች ወጣቶችን በመቀስቀስ ከተማዋን የሁከት ማዕከል ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነው በማለት ከሰዋል የተባሉት አዳነች፣ ወደ ከተማዋ የሚደረገው ፍልሰት የጸጥታ ስጋት ፈጥሯል በማለት በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል። ሆኖም አዳነች፣ ፍልሰተኞቹ ይመጡባቸዋል ያሏቸውን ክልሎችና ወጣቶችን ይቀሰቅሳሉ ያሏቸውን አካላት በስም አልጠቀሱም ተብሏል።ነገር ግን ብዙዎች ከ አማራ ክልል እንደሆነ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። 2፤-አብን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ "ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት መንግሥትን ለመገልበጥ ያለመ ነው" በማለት በከተማዋ ምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ መናገራቸውን ጠቅሶ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አውግዟል። አብን የከንቲባዋ ንግግር፣ "አደገኛ"፣ "ከፋፋይ"፣ "የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ" እና "የዓለማቀፍ ወንጀል ጥሪ ነው" በማለት ከሷል። አብን አያይዞም፣ የከንቲባዋ ንግግር ለእስካሁኖቹ በሰብዓዊነት ላይ ለተፈጸሙ ወንጀሎችና አሁን "እየታወጀ" ነው ላለው "የዘር ማጥፋት ወንጀል ከለላ የሚሆን አሳፋሪ የወንጀል ድርጊት ጥሪ ነው" በማለት አውግዟል። ፌደራል መንግሥቱና ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ከንቲባዋን "ከሥልጣን እንዲያነሳ" እና "ለፍርድ እንዲያቀርብ" የጠየቀው አብን፣ "መሰል ድርጊት በድጋሚ እንዳይፈጸም ማረጋገጫ እንዲሰጥም" ጠይቋል። 3፤ የጸጥታና ደኅንነት ግብረ ኃይል በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ የዶላር ዝውውር፣ በሐሰተኛ የውጭ ገንዘቦችና የብር ሕትመት ተሳትፈዋል ያላቸውን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገለፀ። ግብረ ኃይሉ፣ ለዶላር መግዣ ሊያውሉት የነበረ፣ ከ600 ሺህ በላይ ጥሬ ብርና በቼክ የተፈረመ 4 ሚሊዮን 900 ሺህ ብር ከጦር መሳሪያዎች ጋር በቁጥጥር ስር አውያለሁ ብሏል። በአዲስ አበባ በድብቅ ሐሰተኛ ዶላርና ብር አታሚ የውጭ ዜጎችም ተይዘዋል መባሉን ዘገባው አመልክቷል። የተጠርጣሪዎቹን ብዛት እና የውጭ ዜጎችን ዜግነት ግን አልጠቀሰም። ግብረ ኃይሉ ርምጃውን የወሰደው፣ ብሄራዊ ባንክ ግለሰቦች ከ100 ሺህ ብር እንዲሁም ድርጅቶች ከ200 ሺህ ብር በላይ ከባንክ ውጭ እንዳያስቀምጡ ያወጣውን መመሪያ መሠረት በማድረግ እንደሆነ ተገልጧል። 4፤ ዕሁድ'ለት የተመሠረተው አዲሱ ጎጎት የጉራጌ አንድነትና ፍትህ ፓርቲ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ትናንት 12 አመራሮቼን አስረውብኝ ነበር ማለቱን ሰምተናል። ፓርቲው ትናንት ታሠሩ ካላቸው አመራሮቹ መካከል፣ 10ሩ ተለቀው ሁለቱ ግን እስካሁንም እንደታሠሩ መሆኑን መግለጡን አመልክቷል። የፓርቲው አመራሮች ታሠሩ የተባለው፣ በአዲስ አበባው የፓርቲው ምስረታ ጉባኤ ተሳትፈው ወደመጡበት አካባቢ በመመለስ ላይ ሳሉ መሆኑን ፓርቲው ገልጿል። 5፤ የኬንያ ፖሊስ ወደ ኬንያ በሕገወጥ መንገድ ገብተዋል በማለት የጠረጠራቸውን 32 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች ዛሬ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ኢትዮጵያዊያኑ በሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት በታንዛኒያ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊጓዙ ያሰቡ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ፖሊስ መግለጡን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ክ18 እስከ 28 እድሜ የተገመቱት ኢትዮጵያዊያኑ በቁጥጥር ስር የዋሉት፣ የናይሮቢ አጎራባች በሆነችው ኪያጂያዶ አውራጃ ውስጥ ነው። ኢትዮጵያዊያኑን በሕገወጥ መንገድ ሳታስገባ እንዳልቀረች የተጠረጠረች አንዴት ሴት በቁጥጥር ስር መዋሏም ተገልጧል። 6፤ የኬንያው ሳፋሪኮም ኩባንያ የገንዘብ መላላኪያና መገበያያ ዘዴ "ኤምፔሳ" በደንበኞቹ ክስ እንደተመሠረተበት የአገሪቱ ጋዜጦች ዘግበዋል። ክሱ፣ ሳፋሪኮም ባንክ ሆኖ ሳይመዘገብ፣ የደንበኞችን የ"ኤምፔሳ" ተቀማጭ ገንዘብ ያለ ደንበኞች ፍቃድ እያበደረ ትርፍ ያጋብሳል የሚል እንደሆነ ተገልጧል። የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክም ይህንኑ የሳፋሪኮም ድርጊት እያወቀ፣ በኩባንያው ላይ ቁጥጥር እንደማያደርግ በክሱ ላይ ተጠቅሷል ተብሏል። ኩባንያው የሳፋሪኮም ሲም ካርዶችን በማለዋወጥ በሞባይል "ኤምፔሳ" ላይ የሚፈጸመውን ዝርፊያ ለማስቀረት በቂ ርምጃ አልወሰደም የሚል ሌላ ክስም ቀርቦበታል። "ኤምፔሳ" በኬንያ 32 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት ሲሆን፣ በኢትዮጵያም በቅርቡ የአገልግሎት ፍቃድ እንደሚያገኝ ይጠበቃል። 7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8106 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ8868 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 61 ብር ከ9707 ሳንቲም፣ መሸጫው 63 ብር ከ2095 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ57 ብር ከ3836 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ58 ብር ከ5313 ሳንቲም ሲሸጥ ውሏል። @Ethiopianewsagency (ኢዜአ)
Show all...
“ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት መንግስትን በመጣል በኃይል ስልጣን ለመቆጣጠር ያለመ ነው”- ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “መንግስትን ለመጣል ከአንዳንድ ክልሎች ከፍተኛ ፍልሰት” እየተደረገ መሆኑን አስታወቀ። ወጣቶችን በማነሳሳት “ወደ ጥፋት ለመግባት” እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን ያስታወቀው፤ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 5፤ 2015 በተጀመረው የከተማዋ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ በቀረበ ሪፖርት ነው። የከተማ አስተዳደሩን የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በንባብ ያቀረቡት የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ አዲስ አበባን “የሁከት አውድማ” ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ከንቲባዋ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝብ የመረጠውን ህጋዊ መንግስት በመጣል በኃይል ስልጣን ለመቆጣጠር በማለም፤ ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት” የጸጥታ ስጋት መሆኑን ለምክር ቤት አባላቱ አስታውቀዋል። በከተማዋ ውስጥ የሚታየው “ጽንፈኝነት፣ ጥላቻ እና ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት” የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች፤ የከተማ አስተዳደሩን አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽ እንዳይሆን ማድረጋቸውንም አዳነች በሪፖርታቸው ላይ ገልጸዋል። በከተማዋ ውስጥ የሚታዩት እንቅስቃሴዎች “ስርዓት አልበኝነት እና የመሬት ወረራ” እንዲስፋፋ እያደረጉ መሆናቸውንም ከንቲባዋ አክለዋል። “ሰላማችንን ለማደፍረስ እንቅልፍ ያጡ የጥፋት ኃይሎች፤ ህዝብን በማደናገር እና በማወናበድ በተለይም ወጣቱን በውሸት ፕሮፓጋንዳ በማነሳሳት ወደ ጥፋት ለመማገድ የሚደረገው እንቅስቃሴ ማንም የማይጠቅም ተቀባይነት የሌለው [ነው]” ብለዋል ከንቲባዋ። @Ethiopianewsagency (ኢዜአ)
Show all...