cookie

We use cookies to improve your browsing experience. By clicking «Accept all», you agree to the use of cookies.

avatar

ኢ.ዜ.አ

The Ethiopian News Agency dispatches text news, audio and video stories about local and international events to media enterprises and the public. www.ena.et facebook.com/ethiopianewsagency Call +1(202) 205-9932 Ext 13

Show more
Advertising posts
410Subscribers
No data24 hours
No data7 days
No data30 days

Data loading in progress...

Subscriber growth rate

Data loading in progress...

ሐሙስ ሚያዝያ 5/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ ኢሰመኮ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት ርምጃና ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ጥቃት የረድኤት ድርጅት ሠራተኞችን ጨምሮ ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል ሲል ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በክልሉ የተፈጠረው ኹኔታ መፍትሄ ካላገኘ፣ "ለከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስጋት" መኾኑን የጠቀሰው ኢሰመኮ፣ ሁሉም አካላት ችግሩን "በምክክርና መግባባት" እንዲፈቱትና መንግሥትም የፖሊሲ ውሳኔውን ለባለድርሻዎች እንዲያስረዳ ጠይቋል። ኢሰመኮ፣ ጸጥታ ኃይሎች "ያልተመጣጠነና ሕይወት የሚያጠፋ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ" እና መንግሥትም ስለደረሰው ጉዳት ምርመራ አድርጎ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ ጥሪ አድርጓል። 2፤ የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ኡመር የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ከፌደራልና ክልል ጸጥታ ኃይሎች ጋር በሚዋሃዱበት ሁኔታ ዙሪያ ትናንት ከክልሉ ልዩ ኃይል ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ጋር መወያየታቸውን የክልሉ ኮምንኬሽን ቢሮ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ቢሮው፣ ሙስጠፋና የክልሉ ጸጥታ ኃላፊዎች በመንግሥት ውሳኔ ዙሪያ ለልዩ ኃይሉ አመራሮች ማብራሪያ እንደሰጡና በጉዳዩ ላይ መግባባት ላይ እንደተደረሰ ጨምሮ ገልጧል። 3፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምሥራቅ በለሳ ወረዳ የአምቡላንስ ሹፌርና አዋላጅ ነርስ በኾኑ ኹለት ሠራተኞቹ ላይ ማንነታቸው ያልታወቀ ታጣቂዎች ሚያዝያ 1 ቀን ጥቃት እንዳደረሱ አስታውቋል። ኹለቱ ሠራተኞች አይባሽካ ቀበሌ ውስጥ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው በምጥ የተያዘችን አንዲት እናት ጤና ጣቢያ ለማድረስ ሲጓዙ መኾኑና የጠቀሰው ማኅበሩ፣ ሠራተኞቹ ሕክምና ላይ መኾናቸውን ገልጧል። ማኅበሩ ጥቃቱን አውግዞ፣ ታጣቂ ኃይሎች ከመሰል ጥቃት እንዲቆጠቡ ተማጽኗል። 4፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአማራ ክልል ለዕርዳታ ፈላጊዎች የምግብ ዕርዳታ ሥርጭት ማቆሙን መግለጡን ሮይተርስ ዘግቧል። ድርጅቱ በክልሉ የዕርዳታ ምግብ ሥርጭት ለማቆም የተገደድኩት፣ በክልሉ ባለው የጸጥታ ኹኔታ ሳቢያ ነው ማለቱን ዘገባው ጠቅሷል። ድርጅቱ ይህንኑ ውሳኔውን የገለጸው፣ የካቶሊክ ተራድዖ ድርጅት ኹለት ሠራተኞቹ በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ አካባቢ በተከሰተ ግጭት መገደላቸውን መግለጡን ተከትሎ ነው። 5፤ "አራት ኪሎ ሜዲያ" የተሰኘው የዩትዩብ ጣቢያ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው ባሕርዳር ውስጥ ትናንት በቁጥጥር ስር መዋሉን ጣቢያው አስታውቋል። ዳዊትን ይዘው የወሰዱት የመከላከያ ሠራዊት አባላት መኾናቸውን ጣቢያው ገልጧል። ዳዊት ቀደም ሲል "የአል ዓይን ኒውስ" ጣቢያ ጋዜጠኛ የነበረ ሲሆን፣ ባኹኑ ወቅት ደሞ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ማኅበር የሥራ አመራር ቦርድ አባል ጭምር እንደኾነ ተገልጣል። 6፤ በቱኒዝያ ጥቁር አፍሪካዊያን ፍልሰተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች የደኅንነት ስጋት እንደተጋረጠባቸው በመግለጽ በተመድ የስደተኞች ኮሚሽን መስሪያ ቤት ያደረጉትን ሰልፍ ፖሊስ በአስለቃሽ ጭስ በትኖ 80 ሰልፈኞችን ማሰሩን የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ዘግቧል። ሰልፈኞቹና ጥገኝነት ጠያቂዎቹ ኮሚሽኑ ከአገሪቱ ባስቸኳይ እንዲያስወጣቸው መጠየቃቸውን ዘገባው ጠቅሷል። አፍሪካዊያን ፍልሰተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች የደኅንነት ስጋታቸው የተባባሰው፣ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ካይስ ሳዒድ ጥቁር አፍሪካዊያን ፍልሰተኞች በብዛት መግባታቸው የቱኒዚያን ዓረባዊ ማንነት ለማጥፋት ያለመ ሴራ እንደኾነ በመግለጽ ፖሊስ "ሕገወጥ" ፍልሰተኞችን እንዲያባርር ባለፈው የካቲት ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ ነበር።
Show all...
ረቡዕ ሚያዝያ 4/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ ትናንት በአማራ ክልል የኮምቦልቻ ከተማ የጸጥታ ዕዝ ከምሽቱ 3:00 ሰዓት በኋላ ማንኛውም ሰው መንቀሳቀስ እንደማይችል ገደብ መጣሉን አስታውቋል። የጸጥታ ዕዙ፣ በከተማዋ አድማ መጥራት ወይም ማስተባበር፣ ያልተፈቀዱ ስብሰባዎችን ማድረግና ጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የከለከለ ሲሆን፣ ከጸጥታ አካላት ተሽከርካሪዎች ውጭ ባጃጅና ሌሎች ተሽከርካሪዎች ከምሽት 1:00 ሰዓት በኋላ እንዳይንቀሳቀሱ ገደብ ጥሏል። መጠጥና ምግብ ቤቶችም ከምሽቱ 1:00 ሰዓት በኋላ አገልግሎት እንዳይሰጡ ተከልክለዋል። 2፤ በአማራ ክልል የወልድያ ከተማ የጸጥታ ዕዝ ከጸጥታ ሰዎች ውጭ ከምሽቱ 3:00 እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት በከተማዋ የማንኛውንም ሰው እንቅስቃሴ ማገዱን አስታውቋል። በከተማዋ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ፣ ጥይት መተኮስ፣ አድማ መቀስቀስ፣ የጸጥታ አካላትን አልባሳት መልበስ፣ ያልተፈቀዱ ስብሰባዎችን ማድረግ፣ ወታደራዊ ሥልጠና መስጠትን ከልክሏል። ቡና ቤቶች፣ ካፍቴሪያዎችና ምግብ ቤቶች ከምሽቱ 2:00 ሰዓት በኋላ አገልግሎት እንዳይሰጡ፣ ባጃጆችም ከምሽቱ 1:00 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት ድረስ እንዳይንቀሳቀሱ ጭምር ዕዙ አግዷል። 3፤ እናት ፓርቲ፣ መኢአድና ኢሕአፓ መንግሥት የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን ማፍረስ በሚመስል መልኩ በክልሉ ከጀመረው "ግብታዊ እንቅስቃሴ" እንዲቆጠብና የሰሞኑ "የጥፋት ጉዞ እንዲገታ" አዲስ ባወጡት የጋራ መግለጫ ጠይቀዋል። መንግሥት አገራዊ ምክክር ተደርጎ የሕገመንግሥት ማሻሻያ እስኪደረግ ድረስ፣ አገሪቱን "ወደ ሁለንተናዊ ቀውስ እየከተታት ያለውን አካሄድ እንዲያቆም" ፓርቲዎቹ ጥሪ አድርገዋል። የክልሉ ልዩ ኃይል መሳሪያዎቹን ወደ ግምጃ ቤት እንዲያስገባ በጽሁፍ ትዕዛዝ ተላልፎለታል ያሉት ፓርቲዎቹ፣ የመንግሥት ርምጃ "ግልጽነት በጎደለው" ኹኔታ እየተካሄደ መኾኑንና አካሄዱ "አገሪቱን ወደ ሁለንተናዊ ቀውስ የሚያስገባ" መኾኑን ገልጸዋል። 4፤የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮንዶሚኒየዬም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ላይ ተፈጸመ በተባለው የማጭበርበር ወንጀል ከተከሰሱ 11 ግለሰቦች መካከል 5ቱን በነጻ እንዳሰናበተ የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ዛሬ በነጻ ከተሰናበቱት መካከል፣ የከተማዋ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የቀድሞ ሃላፊ ሙሉቀን ሃብቱ እንደሚገኙበት ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ቀሪዎቹ አምስት ተከሳሾች በገንዘብ ዋስትና ከእስር ተለቀው ጉዳያቸውን በውጭ እንዲከታተሉ የተወሰነላቸው ሲሆን፣ በቀጣዩ ግንቦት 2 ቀን የመከላከያ ምስክሮቻቸውን እንዲያሰሙ እንደተቀጠሩ ተገልጧል። አንድ ተከሳሽ ግን በሌለበት የጥፋተኛነት ውሳኔ ተወስኖበታል ተብሏል። 5፤ በደቡብ ክልል ቡታጅራ ከተማ የክልሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከጉራጌ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከታሠሩ ግለሰቦች መካከል ለ17ቱ የዋስትና መብት እንደፈቀደላቸው ተገለፀ ። ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸውን ከጠበቀላቸው ታሳሪዎች መካከል፣ የጉራጌ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አለማየሁ ገብረ መስቀል እና የዞኑ የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ፍስሃ ዳምጠው እንደሚገኙበት ጠቅሷል።
Show all...
#NewsAlert በአማራ ክልል የወልድያ ከተማ የሰላምና ጸጥታ ዕዝ ላልተወሰነ ጊዜ በከተማዋ የሰዓት እላፊ ገደቦችንና ክልከላዎችን ጥሏል። ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ የገቡ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላትና አመራሮች ወደተዘጋጀላቸው ማረፊያ እንዲገቡ ያሳሰበው የጸጥታ ዕዙ፣ በተናጥልና በቡድን ጦር መሳሪያ ይዘው እንዳይንቀሳቀሱና ጥይት እንዳይተኩሱ መከልከሉን ጨምሮ ገልጧል። የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላትን ያስከዳ ወይም ከመንግሥት የጸጥታ ኃይል ጦር መሳሪያ የገዛ ወይም የለወጠ ማንኛውም ሰው በሕግ እንደሚጠየቅም የጸጥታ ዕዙ አስጠንቅቋል። የጸጥታ ዕዙ ለጸጥታ ጥበቃ ከተመደቡ ሰዎች ውጭ፣ ከምሽቱ 12:00 እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት በከተማዋ የማንኛውንም ሰው እንቅስቃሴ ማገዱን፣ በማናቸውም ጊዜና ቦታ ጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ፣ ጥይት መተኮስ፣ አመጽና አድማ መቀስቀስ ወይም ማስተባበር፣ የክልሉን ልዩ ኃይል፣ የክልሉንና ፌደራል ፖሊስ ወይም የመከላከያ ሠራዊት አልባሳትን መልበስ፣ ያልተፈቀዱ ስብሰባዎችን ማድረግ፣ ወታደራዊ ሥልጠና መስጠት፣ በሕግ ተፈላጊ ግለሰቦችን መደበቅ ወይም መረጃ ሰጥቶ ማስመለጥ የመሳሰሉት ድርጊቶች የተከለከሉ መኾኑንም አስታውቋል። ቡና ቤቶች፣ ካፍቴሪያዎችና ምግብ ቤቶች ከምሽቱ 2:00 ሰዓት በኋላ አገልግሎት እንዳይሰጡ፣ ባጃጆችም ከምሽቱ 1:00 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት ድረስ እንዳይንቀሳቀሱ ጭምር ዕዙ ከልክሏል።
Show all...
#NewsAlert በትግራይ ክልል ሽራሮ ከተማ ከሚገኝ የዓለም ምግብ ድርጅት የዕርዳታ መጋዘን ውስጥ ለ100 ሺህ ተረጅዎች የሚበቃ ሰብዓዊ ዕርዳታ መዘረፉን ድርጅቱ በቅርቡ እንደደረሰበት ከሁለት የረድዔት ድርጅት ሠራተኞች ሰምቻለሁ ሲል አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል። ዕርዳታውን የለገሰው የአሜሪካው ዓለማቀፍ የተራድዖ ድርጅት መኾኑንና ዕርዳታውን ማን እንደዘረፈው ግን እስካሁን እንዳልታወቀ ምንጮቹ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል። ድርጅቱ በትክክል ከየትኛው መጋዘኑ ዕርዳታ እንደተዘረፈ ባይጠቅስም፣ በኢትዮጵያ የድርጅቱ ኃላፊ ክላውድ ጂቢዳር ግን ለድርጅቱ አጋሮች በጻፉት ደብዳቤ በአገር ውስጥ ገበያዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ምግብ ለሽያጭ መቅረቡ ድርጅቱን እንዳሳሰበው መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ኹኔታው በድርጅቱ ስምና ወደፊት የምግብ ዕርዳታ ልገሳ ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት ላይ ስጋት እንደሚደቅን ኃላፊው መግለጣቸውንና፣ "ዕርዳታ እንዳይዘረፍና ላልታለመለት ዓላማ እንዳይውል አስቸኳይ ርምጃዎችን መውሰድ መውሰድ እንደሚያስፈልግ" በደብዳቤያቸው መጠቆማቸው በዘገባው ተጠቅሷል።
Show all...
ማክሰኞ ሚያዝያ 3/2015 ዓ.ም ዕለታዊ ዜናዎች 1፤ በአማራ ክልል የደብረብርሃንና ደሴ ከተሞች የጸጥታ ዕዞች የተለያዩ ጸጥታ-ነክ ገደቦችንና ክልከላዎችን ተጥለዋል። በከተሞቹ ከተጣሉት ክልከላዎችና ገደቦች መካከል፣ ከመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ውጪ ጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስለ፣ እውቅና የሌላቸው ስብሰባዎችን ማድረግ፣ አድማዎችን ማድረግ፣ ማስተባበር መቀስቀስ እና መታወቂያ ሳይዙ መንቀሳቀስ ይገኙበታል። በደብረብርሃን ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮችም ላልተወሰነ ጊዜ ከመጠለያ ጣቢያዎች ውጭ እንዳይንቀሳቀሱ ገደብ ተጥሏል። 2፤ ትናንት ምሽት በባሕርዳር ከተማ አባይ ማዶ ቀበሌ ባንድ የሆቴልና መጠጥ መሸጫ በደረሰ የቦምብ አደጋ ሦስት ሰዎች ሞተው 10 ሰዎች መቁሰላቸውን ቪኦኤ ዘግቧል። በአካባቢው የሚገኘው አዲስ ዓለም ሆስፒታል ከ10 በላይ በአደጋው የቆሰሉ ሰዎች ለሕክምና ገብተው እንደነበር መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን መልሶ ከማደራጅት ውሳኔ ጋር በተያያዘ፣ በከተማዋ ከዕሁድ'ለት ጀምሮ አገልግሎት ሰጪና የንግድ ተቋማት ዝግ እንደኾኑ ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል። 3፤ በአማራ ክልል የካቶሊክ ተራድዖ ድርጅት ዕሁድ'ለት በቆቦ ከተማ በነበረ የከባድ መሳሪያ ተኩስ የተገደሉበት ሠራተኞቹ ቾል ቶንጊክ የተባሉ የጸጥታ ሃላፊው እና አማረ ክንደያ የተባሉ ሹፌሩ እንደኾኑ መናገሩን የውጭ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ሁለቱ የድርጅቱ ሠራተኞች የተገደሉት፣ ከአካባቢው ወደ አዲስ አበባ በመንቀሳቀስ ላይ ሳሉ መኾኑን ገልጧል። ኾኖም ሁለቱ ግለሰቦች በምን አኳኋን ሊገደሉ እንደቻሉ ገና እንዳላወቀ ድርጅቱ አስታውቋል። 4፤ የፌደራሉ ጤና ሚንስቴር ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ዛሬ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ጉብኝት እንደሚያደርግ የትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ዘግቧል። የልዑካን ቡድኑን የሚመሩት የጤና ሚንስትር ደኤታው እንደኾኑ ዘገባው ጠቅሷል። ባለፉት ጥቂት ቀናት የትምህርት ሚንስቴር ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በመቀሌ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣናት ጋር መምከሩ ይታወሳል። 5፤ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ዛሬ ሞቃዲሾ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የቻይናው ሲጂቲኤን ዘግቧል። ጉተሬዝ በሱማሊያ ጉብኝት ያደርጋሉ የተባለው፣ በአገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ከ8 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ሱማሊያዊያን የድርቅ ተጎጅዎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊ በኾኑበት ወቅት ላይ ነው። 6፤ የኬንያው ፕሬዝዳንት ሩቶ እና ተቃዋሚያቸው ራይላ ኦዲንጋ ለአገሪቱ መረጋጋት ሲሉ የብሄራዊ አንድነት መንግሥት ለመመስረቱ እንዲደራደሩ ግፊት እየተደረገባቸው መኾኑን ደይሊ ኔሽን አስነብቧል። ከብሄራዊ አንድነት መንግሥት ሌላ፣ ሁለተኛው አማራጭ በመንግሥት ውስጥ ለተቃዋሚ ፓርቲው ሊቀመንበር ራሱን የቻለ ቢሮ ማቋቋም መኾኑን ዘገባው አመልክቷል። ፕሬዝዳንቱ ሁለተኛውን አማራጭ ቢደግፉትም፣ ኦዱንጋ ግን ውድቅ አድርገውታል። ሁለቱ አማራጮቹ የቀረቡት፣ በቅርቡ ወደ ኬንያ አቅንተው የነበሩት የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልዑክ ሴናተር ክሪስ ኩንስ እና የኬንያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪዎች አማካኝነት ነው። ኦዲንጋ፣ አሸናፊው ሁሉንም ጠቅልሎ የሚወስድበትን የምርጫ ሥርዓት የሚቀይር ሕገመንግሥታዊ ማሻሻያ እንዲደረግ ሃሳብም አቅርበዋል።
Show all...
#NewsAlert የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ቢሮ በአማራ ክልል ለሕይወት አስጊ በኾነ ሕመም ላይ የሚገኙ ታማሚዎችን ከቦታ ቦታ በሚያጓጉዙ አምቡላንሶች እና የጤና ባለሙያዎች ላይ በቅርብ ጊዜያት የተፈጸሙ ጥቃቶች አሳስበውኛል ሲል ዛሬ ከቀትር በኋላ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የጤና ሠራተኞች፣ አምቡላንሶችና ሆስፒታሎች ዒላማ መኾን እንደሌለባቸው የገለጠው ማኅበሩ፣ የጤና ሠራተኞች፣ አምቡላንሶችና ሆስፒታሎች በማናቸውም ጊዜ ሊከበሩ እና ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገባቸው ናቸው ብሏል።
Show all...
ሐሙስ መጋቢት 28/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ አብን ገዥው ፓርቲ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን "በግዴታ ትጥቅ ለማስፈታት" እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነው ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከሷል። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው፣ ገዥው ፓርቲ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች "በክልሉ ልዩ ኃይል እና በፌደራል የጸጥታ ተቋማት መካከል ከፍተኛ ውጥረት መፍጠሩን" ተረድቻለሁ ብሏል። መንግሥት የጋራ መግባባትና መተማመን ሳይፈጠር የክልሉን ልዩ ኃይል "በድንገትና ያለበቂ የጸጥታ ዋስትና ለማፍረስ" ያሳለፈው ውሳኔና ውሳኔውን ለመተግበር የሚያደርገው እንቅስቃሴ "ኃላፊነት የጎደለው" እና በክልሉና በአገር ዓቀፍ ደረጃ "ከፍተኛ አለመረጋጋት የሚፈጥር፣ ክልሉንና አገሪቱን ወደሌላ የቀውስ አዙሪት የሚከት አደገኛ አካሄድ" መኾኑን ፓርቲው ገልጧል። ገዥው ፓርቲ ውሳኔውን "በአፋጣኝ እንዲቀለብስና ከክልሉ መንግሥትና ሕዝብ ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት እንዲያደርግ" አብን አሳስቧል። 2፤ በአማራ ክልል ከባሕርዳር ወደ ጎንደር በሚወስደው ዋና መንገድ ተሽከርካሪዎች ለሁለት ሰዓታት ያህል መንገድ ተዘግቶባቸው እንደነበር ዶይቸቨለ አሽከርካሪዎች ገለፁ። ሰሜን ወሎ ዞን ጎብዬ በተባለች ከተማ ዛሬ የጥይት ተኩስ ሲሰማ መዋሉን ተገለፀ። ኾኖም ከሁለት ሰዓታት በኋላ፣ አሽከርካሪዎች መታወቂያ እያሳዩና እየተፈተሹ በሁለቱም አቅጣጫ ማለፍ እንደቻሉ መናገራቸውን ሰመተናል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ የክልሉ መንግሥት መንገዱ ተዘግቶ ነበር ስለተባለው መረጃ ያለው ነገር የለም። 3፤ የትምህርት ሚንስትር ደኤታ ሳሙኤል ክፍሌ የመሩት ልዑካን ቡድን ዛሬ መቀሌ መግባቱን የትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ዘግቧል። ልዑኩ፣ መቀሌ የገባው፣ በክልሉ የሚገኙ ለሁለት ዓመታት ትምህርት መስጠት ያቋረጡ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሌሎች ትምህርት ቤቶች ባሉበት ሁኔታ ዙሪያ፣ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲኹም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት መጀመሩን ዘገባው ጠቅሷል። በልዑካን ቡድኑ ከተካተቱ አባላት መካከል፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጣሰው ወልደሃና እና የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኝ ይገኙበታል ተብሏል። 4፤ የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አደም ፋራህ የመሩት ልዑካን ቡድን በጅቡቲ ይፋዊ ጉብኝት እያደረገ መኾኑን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። አደም ከጅቡቲው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሞሐሙድ ዓሊ የሱፍ እና ከፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ እንደተወያዩና ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የላኩትን ደብዳቤ ለፕሬዝዳንት ጌሌ እንደሰጡ ኢምባሲው ገልጧል። 5፤ የሱዳን ወታደራዊ አመራሮችና የፖለቲካ ኃይሎች ዛሬ የሲቪል ሽግግር መንግሥት ማቋቋሚያውን ረቂቅ ሰነድ ለመፈረም ይዘው የነበረውን ቀጠሮ ለሁለተኛ ጊዜ አራዝመዋል። ከመጋቢት 23 ወደ መጋቢት 28 የተራዘመው የስምምነት ሰነዱን የመፈረሙ ቀጠሮ ዛሬ በድጋሚ የተራዘመው፣ የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ምክትል ሊቀመንበር ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ የሚመሩት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ወደፊት ከአገሪቱ ብሄራዊ ጦር ሠራዊት ጋር በሚዋሃድበት የጊዜ ገደብ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ስላልተቻለ እንደኾነ የሱዳን ዜና ምንጮች ዘግበዋል። 6፤ ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ቡድን (ሲፒጄ) ባለፈው ወር በኬንያ በተካሄዱ ጸረ-መንግሥት የተቃውሞ ሰልፎች ወቅት በጋዜጠኞች ላይ ለደረሱ ጥቃቶች ተጠያቂነት እንዲሰፍን ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። የአገሪቱ ባለሥልጣናት በተቃውሞ ሰልፉ ይዘግቡ በነበሩ ጋዜጠኞች ላይ ፖሊሶች ያደረሷቸውን ወከባዎችና አካላዊ ጥቃቶች በጥልቀትና ተዓማኒ በኾነ መንገድ መርምረው ጥፋተኞቹን ለሕግ እንዲያቀርቡ ጥሪ አድርጓል። የመብት ተሟጋቹ ቡድን፣ የተቃውሞ ሰልፎቹን ለመዘገብ የወጡ ሁለት ጋዜጠኞችም ለአጭር ጊዜ ታስረው እንደነበር መረዳቱን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል። 7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ9566 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ0357 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ2303 ሳንቲም እና መሸጫው 65 ብር ከ5148 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ0393 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ2201 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል።
Show all...
ሐሙስ መጋቢት 28/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የኢትዮጵያ ስጋ ላኪዎች ከዛሬ ጀምሮ ስጋ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚያቆሙ ማስታወቃቸውን ሰመቸናል። የኢትዮጵያ ስጋ አምራችና ላኪዎች ማኅበር መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ስወራ ችግርን ሊፈታ አለመቻሉን ጠቅሶ፣ ላኪዎች ስጋ መላክ እንደሚያቆሙ ለግብርና ሚንስቴር ደብዳቤ መጻፉ ታውቋል። ማኅበሩ በደብዳቤው የዘርፉ ችግር አድርጎ የጠቀሰው፣ የኤክስፖርት ቄራዎችን ተከራይተው ምርት ወደ ውጭ የሚልኩ ኩባንያዎች የውጭ ምንዛሬ በመሰወር ሥራ ላይ በመሠማራት ሕግ አክብረው የሚሠሩ ስጋ ላኪ ኩባንያዎችን ከገበያ እያስወጡ ነው የሚል ነው። ቁጥራቸው ከ30 እስከ 40 የሚገመቱ የኤክስፖርት ቄራዎችን ተከራይተው ስጋ የሚልኩ ኩባንያዎች ዋነኛ ዓላማቸው፣ በላኪነት ሽፋን ከብሄራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደኾነ ይነገራል። 2፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተካሄደባቸው ክልሎች በመንግሥትና ሕወሃት መካከል የሰላም ስምምነት ከተደረሰ ወዱህ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ ማድረግ እንደሚቀጥል ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ኮሚሽነ ይህንኑ ተልዕኮውን ለመቀጠል፣ ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን አሠራር ለመዘርጋት ዕቅድ መያዙን ገልጧል። 3፤ ባይቶና አባይ ትግራይ ፓርቲ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ተወካይ የለኝም ሲል ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ባይቶና ፓርቲ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ እንደተወከለ አድርገው መረጃ ያሰራጩት ሕውሃት በፓርቲው ውስጥ ያደራጃቸው ግለሰቦች ናቸው በማለት ፓርቲው ገልጧል። ባይቶና ትናንት ሥራውን በይፋ በጀመረውና 27 አባላት ባሉት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ውስጥ፣ ሁለት ቢሮዎችን የመምራት ሃላፊነት እንደተሰጠው የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቦ ነበር። 4፤ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ሲያደርግ የሰነበተው የኤርትራ ወታደራዊና የደኅንነት ልዐካን ቡድን ትናንት ጉብኝቱን ማጠናቀቁን በኢትዮጵያ የኤርትራ ኢምባሲ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በጉብኝቱ ማጠናቀቂያ ለልዑኩ በተደረገ ግብዣ ላይ፣ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከጀርባው በተወጋበት ወቅት የኤርትራ ሕዝብና ሠራዊት ያደረገለትን ድጋፍ መቼም አይረሳም ማለታቸውን ኢምባሲው ጠቅሷል። የኤርትራ ደኅንነት ሚንስትር ጀኔራል አብርሃ ካሳ በበኩላቸው፣ ሕወሃት በኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሲሰነዝር፣ ኤርትራ አደጋውን ከመመከትና ያንኑ ተከትሎ የተፈጸሙ ወታደራዊ ጥቃቶችን ከማክሸፍ ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበራትም በማለት መናገራቸውን ኢምባሲው ገልጧል። 5፤ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለደቡብ ሱዳን ያቋቋመውን የሰብዓዊ መብቶች ተቆጣጣሪ ኮሚሽን የጊዜ ቆይታን ላንድ ዓመት አራዝሟል። ምክር ቤት የኮሚሽኑን የጊዜ ቆይታ ያራዘመው፣ ኮሚሽኑ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈጽሙ ሲቪልና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ተጠያቂ መኾን አለባቸው በማለት ሰኞ'ለት ሪፖርት ማውጣቱን ተከትሎ ነው። ምክር ቤቱ ኮሚሽኑን ያቋቋመው ከሰባት ዓመታት በፊት ሲሆን፣ የጊዜ ቆይታውን ያደሰው ደሞ በዓመታዊ ጉባዔ ማጠናቀቂያ ላይ ነው። የደቡብ ሱዳን መንግሥት የኮሚሽኑ ቆይታ እንዳይታደስ ጥረት አድርጎ ነበር።
Show all...
በአዲስ አበባ 200 ሺህ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱት በህገ-ወጥ ቦሎ ነው ተባለ፡፡ የተሽከርካሪ እና አሽከርካሪ ቁጥጥር ባለስልጣን እንዳስታወቀው በህጋዊ መንገድ ከምርመራ ተቋማት ቦሎ የሚወስዱ ተሽከርካሪዎች 48 ከመቶ ብቻ ናቸው ብሏል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራቶች በህጋዊ መንገድ ከምርመራ ተቋማት ፍቃድ አግኝተው ቦሎ የወሰዱ ተሽከርካሪዎች 330ሺህ ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡ የአሽከርካሪ እና ተሸከርካሪ ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ደምሴ እንደተናገሩት፣ አሁን ላይ በአዲስ አበባ ደረጃ 650ሺህ ተሸከርካሪዎች እንደተመዘገቡ ገልጸው በየአመቱ ቦሎ የሚወስዱ ተሽከርካሪዎች ግን 450ሺህ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡ የተቀሩት ተሽከርካሪዎች አመታዊ ተሽከርካሪ ምርመራ የት እየሄዱ እንደሚያደርጉና ቦሎም ከየት እንደሚወስዱ አይታወቅም ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ደረጃ እውቅና ተሰጥቷቸው ተሽከርካሪ ምርመራ የሚያደርጉ ከ50 በላይ የምርመራ ተቋት እንዳሉ የተነገረ ሲሆን፣አብዛኛዎቹ የአቅም ክፍተት እንዳለባቸው ተጠቅሟል፡፡ የአሽከርካሪ እና ተሸከርካሪ ቁጥጥር ባለስልጣን እነዚህ ችግሮም ለመቅረፍ ከምርመራ ተቋማቱ ጋር በመቀናጀት አዲስ አሰራር መዘርጋቱንም ነው የገለጸው፡፡ በዚህም ተሽከርካሪዎች አመታዊ የቴክኒክ ምርመራ በቴክኖሎጂ በታገዘ የምረመራ አገልግሎት የሚሰጣቸው ይሆናልም ተብሏል፡፡
Show all...
ማክሰኞ መጋቢት 26/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የጸጥታና ደኅንነት ግብረ ኃይል " በመንግሥት ባለስልጣናትና በከተሞች ላይ በጦር መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ደርሼባቸዋለሁ" ያላቸውን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አውያለሁ አለ። ምሁራን፣ የመገናኛ ብዙኀን ባለቤቶችና የማኅበረሰብ አንቂዎች የታቀፉባቸው ናቸው የተባሉት ኅቡዕ ቡድኖች፣ ጥቃቱን ሊፈጽሙ ያቀዱት በአዲስ አበባ፣ ባሕርዳር፣ አዳማ እና ድሬዳዋ እንደነበር ግብረ ኃይሉ ገልጧል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል፣ ዶ/ር ወንደወሰን አሠፋ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው፣ ፕሮፌሰር ማዕረጉ ቢያበይን እና ዶ/ር መሠረት ወርቁ የተባሉ ተጠርጣሪዎች እንደሚገኙበትና በአንዳንዶቸ ተጠርጣሪዎች እጅ ጦር መሳሪያዎች እንደተያዙ አመልክቷል። ተጠርጣሪዎቹ " የአማራ ሕዝብ በከፍተኛ ጭቆና ውስጥ ይገኛል" በማለት፣ "ሕዝብን በሐይማኖት፣ በብሄርና በጽንፈኛ የፖለቲካ ዓላማ ዙሪያ ደጋፊ ለማሰባሰብ ሲሞክሩ ነበር" ተብሏል። 2፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ከኦሮሚያ ክልል የተመረጡትን አባሉን ዶ/ር ጫላ ዋታን ያለመከሰስ መብት በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ አንስቷል። ጫላ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው፣ የሁሌ ቦራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት ከመንግሥት የግዥ ሥርዓት ውጭ ፈጽመውታል ተብለው በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል መኾኑን ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳቡን ያቀረበው የሕግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ አስረድቷል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ የወንጀል ተጠርጣሪው ጫላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ስለመዋላቸው አልታወቀም። 3፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሌሊሴ ደሳለኝን የከፍተኛው ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ዘሃራ ኡመርን የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ኾነው እንዲሾሙ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ በሁለት ድምጸ ተዓቅቦ አጽድቋል። ሌሊሴ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉና ፌደራል ፍርድ ቤቶች በዳኝነት እንዲሁም ባንድ ወቅት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በምክትል ፕሬዝዳንትነት ማገልገላቸው የተገለጠ ሲሆን፣ ዘሃራ ደሞ በሱማሌ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተለያዩ ኃላፊነቶች ማገልገላቸው ተጠቅሷል። ሌሊሴና ዘሃራ የተሾሙት፣ የፍርድ ቤቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ብርሃን መስቀል ዋጋሪና ምክትል ፕሬዝዳንት ተናኘ ጥላሁን በፍቃዳቸው ከሃላፊነት በመልቀቃቸው እንደኾነ ተዘግቧል። 4፤ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት "በሂደትና ደረጃ በደረጃ" ከሰሜኑ ጦርነት በፊት ወደነበረበት እንደሚመልስ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። ቦሬል፣ አውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት ዛሬ መግለጫ የሰጡት፣ ብራስልስ ውስጥ ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው። የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በመንግሥትና ሕወሃት መካከል በተፈረመ ሰላም ስምምነት መቋጨቱ አዎንታዊ ክስተት መኾኑን የጠቀሱት ቦሬል፣ የሰላም ስምምነቱ ዘላቂ እንዲኾን ኅብረቱ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በትብብር መስራት እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ቦሬል፣ አውሮፓ ኅብረት የሰላም ስምምነቱን አፈጻጸም በቅርበት በመከታተል ላይ እንደኾነ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና የትግራይ ክልል አመራሮች እንዲረዱትም አሳስበዋል። 5፤ ኢትዮ ቴሌኮም የኢንተርኔት ግንኙነት ያለ "ቪፒኤን" ለማድረግ እንደተቸገረ ተደርጎ የተሠራጨው መረጃ "የተሳሳተ ነው" ሲል ዛሬ ባስተላለፈው መልዕክት አስታውቋል። ኢትዮ ቴሌኮም ያለ "ቪፒኤን" የኢንተርኔት ግንኙነት ለማድረግ "ተጨማሪ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንዳስፈለገው" ተደርጎ የተሠራጨው መረጃም ሐሰት መኾኑን ጨምሮ ገልጧል። ኢትዮጵያ ውስጥ ምክንያቱ ባልተገለጠ ሁኔታ የፌስቡክ፣ ቴሌግራምና ዩትዩብ ማኅበራዊ መገናኛ አገልግሎቶች ከተገደቡ ሁለት ወር የተቆጠረ ሲሆን፣ ደንበኞች የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹን የሚጠቀሙት "በቪፒኤን" በመግባት ብቻ ነው። የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹ ለምን እንደተገደቡ፣ ኩባንያው ያለው ነገር የለም። 6፤ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ከጅቡቲ የቀይ ባሕር ዳርቻ 142 ፍልሰተኞችን መታደግ እንደተቻለ ዛሬ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ፍልሰተኞችን መታደግ የተቻለው፣ ፍልሰተኞቹ በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት በጀልባዎች ቀይ ባሕርን አቋርጠው ወደ የመን ለመሻገር ሲሞክሩ መኾኑን ኢምባሲው ገልጧል። ኢምባሲው፣ ፍልሰተኞቹን ሊያሻግሩ የነበሩ ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችም በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የገለጠ ሲሆን፣ በቁጥጥር ስር የዋሉትን ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ብዛትና ዜግነታቸውን ግን አልጠቀሰም። 7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ9302 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ0088 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 63 ብር ከ6169 ሳንቲም እና መሸጫው 64 ብር ከ8892 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ5844 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ7561 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል።
Show all...