ትክክለኛው መንፈሳዊ ብስለት ያስፈልገናል
በመብሰልና ባለመብሰል መካከል ከፍተኛ የሆነ ልዩነት አለ።
1. ሕፃናት (ያልበሰሉ) የሚኖሩት በሕግ ነው። የበሰለ ሰው የሚኖረው በውስጡ ባለው ክርስቶስ ነው።
2. ሰዎችን መመልከት አለመብሰል ሲሆን ኢየሱስን መመልከት ደግሞ ብስለት ነው።
3. ሙሴን/ሕጉን/ እና ኤልያስን/ነቢያትን/ መመልከት አለመብሰል ነው። ኢየሱስን መመልከት ግን ብስለት ነው።
አጋርና ሣራ እስማኤል አብረው ይኖሩ የነበሩት ይሰሐቅ ጡት ከመጥባት እስኪቋረጥ ድረስ ነው፤ ይህ የሚያሳየው መንፈሳዊ ሁኔታን ነው፡፡
"ሕፃኑ አደገ፤ ጡት መጥባቱንም ተወ። አብርሃምም ይስሐቅ ጡት በጣለባት ዕለት ታላቅ ድግስ ደገሰ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ግብፃዊቷ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል፣ በይስሐቅ ሲያሾፍበት ሣራ አየች፤ አብርሃምንም፣ ይህችን ባሪያ ከነልጇ አባርልኝ፤ ምንም ቢሆን የዚህች ባሪያ ልጅ፣ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር ውርስ አይካፈልም አለች። እስማኤል ልጁ ስለ ሆነ ነገሩ አብርሃምን እጅግ አስጨነቀው። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ ስለ ልጁም ሆነ ስለ አገልጋይህ አሳብ አይግባህ፤ ዘር የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ስለ ሆነ፣ ሣራ የምትልህን ሁሉ ስማ። የአገልጋይህም ልጅ የራስህ ልጅ ስለ ሆነ፣ እርሱንም ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ።" (ዘፍጥረት 21:8 - 13 NASV)
ጳውሎስ በቆሮንቶስ የሚገኙ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ገና ሕፃናት የሆኑበትን ደረጃ ሥጋዊነት በማለት ይገልፀዋል፤ በዚህ የመንፈሳዊ ልጅነት ደረጃ ልክ እስማኤል በቤት ውስጥ ችግር እንደ ፈጠረው ሥጋም ችግር ይፈጥራል፡፡
"ወንድሞች ሆይ፤ በክርስቶስ ገና ሕፃናት እንደመሆናችሁ፣ እንደ ሥጋውያን እንጂ እንደ መንፈሳውያን ልናገራችሁ አልቻልሁም። ገና ስላልጠነከራችሁ ወተት እንጂ ጠንካራ ምግብ አልመገብኋችሁም፤ አሁንም ቢሆን ገና ናችሁ። አሁንም ሥጋውያን ናችሁ፤ በመካከላችሁ ቅናትና ክርክር አለ፤ ታዲያ፣ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን? ተግባራችሁስ እንደ ማንኛውም ሰው ተግባር መሆኑ አይደለምን? ምክንያቱም አንዱ፣ እኔ የጳውሎስ ነኝ፣ ሌላው ደግሞ፣ እኔ የአጵሎስ ነኝ ቢል፣ ሰብአዊ ፍጡር ብቻ መሆናችሁ አይደለምን?" (1 ቆሮንቶስ 3:1 - 4 NASV)
በሕግ ውስጥ ለመኖርና ለመመላለስ መምረጥ ወተትን እንደ መጋት (አለመብሰል) ነው፤ የእግዚአብሔርን ፀጋ ወደ መረዳትና ወደ መብሰል መምጣት (ፃድቅ መሆናችንን መረዳት) መቻል አለብን፡፡
"ስለዚህ ጉዳይ የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፤ ነገር ግን ለመማር ዳተኛ ስለ ሆናችሁ ለማስረዳት አስቸጋሪ ነው። በዚህ ጊዜ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፣ ገና የእግዚአብሔርን ቃል የመጀመሪያ ትምህርት የሚያስተምራችሁ ሰው ያስፈልጋችኋል፤ የሚያስፈልጋችሁም ጠንካራ ምግብ ሳይሆን ወተት ነው። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ፣ ከጽድቅ ትምህርት ጋር ገና አልተዋወቀም። ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙን ከክፉው ለመለየት ራሳቸውን ላስለመዱ፣ ለበሰሉ ሰዎች ነው።" (ዕብራውያን 5:11 - 14 NASV)
"ባሪያይቱን ከልጅዋ ጋር አውጣት" የሚለው ትዕዛዝ ዛሬ ለእኛ ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት፤ ጳውሎስ እያለ ያለው ሾልከው የገቡ የሐሰት ወንድሞች ያመጡትን የወግ አጥባቂነት ተፅዕኖ በሌላ አነጋገር ሕጋዊነትና የራስ ጥረትን ከአዲሱ ኪዳን መውጣት አለባቸው ነው፡፡
እናንት ከኦሪት ሕግ በታች ለመኖር የምትሹ እስቲ ንገሩኝ፤ ሕግ ምን እንደሚል አልሰማችሁምን? አብርሃም፣ አንዱ ከባሪያዪቱ፣ ሌላው ደግሞ ከነጻዪቱ ሴት የሆኑ ሁለት ልጆች እንደ ነበሩት ተጽፎአልና። ....." (ገላትያ 4:21-31 NASV ሙሉውን ተመልከቱ)
አብርሃም በሣራ ንግግር ደስተኛ አልነበረም፤ ይህ ለእርሱ ከባድ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ ወደ እግዚአብሔር ቀርቦ በጠየቀ ጊዜ ሣራን (ፀጋን) ስማት ተባለ፡፡
አብርሃም ያንገራገረው እስማኤልን (የራሱን ጥረት ውጤት) ስለሚወደው ነው፤ ልክ እንደዚሁ ዛሬም ብዙዎች የራሳቸውን ጥረት ይወዱታል፡፡ ምንም ያህል የሚወዱት ይሁን እንጂ የፀጋ ድምፅ ትዕዛዝ አስወጣ ነው።
Show more ...